• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ዘመነ ጽጌ - ክፍል ሁለት


    "ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"   (ት.ሆሴዕ 11፥1 )

    ከመምህር ዮሐንስ  ለማ

    እመቤታችን በስደቷ የተጓዘችባቸው

    ሐዋርያዊት የሆነች ቅድስት  ቤተ ክርስቲያናችንከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ክርስቲያናዊ ትውፊታዋን ጠብቃ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በሚገባ አራቅቃ፣ዘመንን በክፍል በክፍል ቀምራ፤ ከመስከረም ጀምሮ እስከ ጳጉሜን ድረስ ያሉት ሰንበታት የራሳቸው የሆነ ከምሥጢረ ድህነት ጋር የተያያዘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜ ሰጥታ የሰው ልጆችን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ለማዳን የተደረገው (የተፈጸመው) አምላካዊ የድኅነት ጉዞ እያዘከረች፣ እያስተማረች...ለዘመናት ቆይታለች፣ አሁንም በማስተማር ላይ ናት። ለወደፊትም እግዚአብሔር እስከ ፈቀደላት ጊዜድረስ ስትመሰክርና ስታስተምር ትኖራለች፡፡ እመቤታችን በትልቅ የምስጋና አገልግሎት ከሚከበሩላት በዓላት መካከል የወርሐ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ ) አንዱና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ልብውስጥ ጥልቅ የልቡና ፍቅር ያለው  ይሕ የወርሐጽጌ ወቅት  አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በክፍልአንድ ጽሐፍ   የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት በማስመልከት ምክንያተ ስደቷንናተያያዥ ርዕሶችን ማስነበባችን  ይታወሳል፡፡አሁን ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደቷ ወቅት  ያሳለፈቻቸውን  ውጣ ውረድና ተያያዥ ክስተቶችን  እንዲሁም የጉዞዋን ዋና ዋና መዳረሻዎችን ጭምር ለማስነበብ እንሞክራለን፡፡

    ንጉሥ ሄሮድስ እና ሰብአ ሰገል

    ከሩቅ ምሥራቅ የመጡት ነገሥታት ( ሰብአ ሰገል ) ለዓመታት ያህል ተጉዘው ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ፡ "አይቴ ሀሎ ንግሥ እስራኤል ዘተወልደ ከመነሃብ ሎቱ አምሃ ወሰጊድ" ..... ይዘን የመጣነውን መባዕ እና ስግደት እናቀርብለት ዘንድ የተወለደውሕፃን ወዴት ነው ‘’ ? ወርቅ ለመንግስቱ፣ ዕጣን ለክህነቱ፣ ከርቤ ስለሞቱ እና በረክትለት ዘንድ የተወለደው የዓለም ንጉሥ የት አለ ? እያሉ ሲፈልጉና ሲያፈላልጉ በመልእክተኞቹ አማካኝነት የሰማው የኢየሩሳሌም ንጉሥ ሄሮድስ ይህ ምንዓይነት ነገር ነው ? የትስ ያለ የዓለም ንጉሥ ነው ? የሚወለደውስ ከማንና መቼ ነው ? አሁን ገናበተወለደ ጊዜ እንዲህ ነገሥታትን ያሰገደ ሕፃን ሲያደግማ እኔንም ያሰጋኛል፤ አልፎም ያጠፋኛልብሎ እጀግ ከመፍራትና ከመደንገጡ የተነሳነገሥታቱን አስጠርቶ ስለ ነገሩ አስፍቶ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በኮከብ መሪነት ለዓመታት ያህል መጓዛቸውንና አጠቃላይ የአመጣጣቸውን ታሪክተረኩለት፡፡ ታሪኩን  ሰምቶና ተረድቶ ከበቃ በኋላንጉሡ ሄሮድስ ለነገሥታቱ ስለ ሕፃኑ ጠቅላላ ሁኔታ እንዲያጠኑ ሲመለሱም ምስጢሩን  እንዲገልጹለትአደራ ብሎ ካሰናበታቸዉ በኋላ መልዓከ እግዚአብሔር ተገልጾ በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸውእንዲመለሱ ስለነገራቸውና ምስጢሩንምስለገለጸላቸው የሄሮድስ ተንኮላዊ አደራን ወደ ጎንትተው መልአኩ እንደነገራቸው በሌላ መንገድ ወደሃገራቸው ተመለሱ፡፡ከሰብአ ሰገል መረጃን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

     ሰብአ ሰገል ወደ እርሱ ባለመመለሳቸው የተበሳጨው ሄሮድስ የራሱን እርምጃ ለመውሰድወሰነ፡፡ ምንጊዜም ሄሮድስ የሚፈልገው በቤተልሔም የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን ሕፃን ክርስቶስን አግኝቶ መግደልነው፡፡    ስለሆነም ሕፃኑ ክርስቶስ ያለበትን ቦታ የሚጠቁም ሰው አላገኘም፡፡ ትክክለኛውን መረጃ ባያገኝም ከሰብአ ሰገል አንደበት የሰማውን ለእንቅስቃሴው መነሻ አድርጎ ተነሣ፡፡ሄሮድስ እንደመረጃ  የተጠቀመው ፡- ሰብአ ሰገልን የመራቸው ኮከቡ  የተገለጠበትን ዘመን ነው፡፡ ሰብአ ሰገልንጠይቆ የኮከቡን  ዘመን ተረድቶ ነበር፡፡ ኮከቡ ለሰብአሰገል ከተገለጠ ወይም ሰብአ ሰገልን መምራት ከጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነው በጥንቃቄተረድቷል፡፡ ሰብአ ሰገልን የመራቸው ኮከብ ሁለት ዓመት ከሆነው የአይሁድ ንጉሥ የተባለው በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን ክርስቶስም ሁለት ዓመት ሊሆነው ይችላል የሚል ግምት መገመት ጀመረ ፡፡

    ቦታው ቤተልሔም መሆኑ እና የአይሁድ ንጉሥየተባለው ሕፃን የሁለት ዓመት ሕፃን መሆኑ በመረጃ ተደግፏል፡፡ ነገር ግን በቤተልሔም ብዙ የሁለትዓመት ሕፃናት ይኖራሉ፡፡ የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን ሕፃን እንዴት ለይቶ ማወቅ ይቻላል?የሄሮድስ ልቡ የሚረጋጋበት መፍትሔ   አላገኘም፡፡ ሌላ አማራጭ መፈለግ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የሚኖሩትንሁለት ዓመት የሆናቸውን እና ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን ሕፃናት መግደል አማራጭ የሌለውየጭንቀቱ መፍትሔ አድርጎ  ወሰደው፡፡ መፍትሄውም  በቤተልሔም  ሕፃናት ላይ ይህን የእልቂት ትእዛዝ ማስተላለፍ በማሰብ ነው፡፡ ሄሮድስ ከቤተልሔም ሕፃናት አንዱ ተነስቶ እንዳይቀር እጅግ ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ወታደሮቼ በየሰፈሩ እየዞሩ ሕፃናትንቢገድሉ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ይሰውራሉ ሕፃናቱም ከሞት ያመልጣሉ ከሚያመልጡትምሕፃናት አንዱ ክርስቶስ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላውደግሞ የሚገደሉት ሕፃናት ከሁለት ዓመት በታች መሆናቸው በግምት አይታወቁም በማለት ይጨነቅ ነበር፡፡ ሄሮድስ ብዙ ሐሳቦችን ሲያንሸራሸር ከቆየበኋላ ሁሉም ሕፃናት በቤተመንግሥቱ አንድ ቀን ቢገኙ የተሻለ ነገር እንደሆነ አሰበ፡፡ ነገር ግን ሕፃናቱ እንዴት እንደሚሰበሰቡ ሌላ ፈተና ሆነበት በንጉሣዊትእዛዝ  ወላጆች ልጆቻቸውን እየያዙ እንዲመጡ ቢደረግ በኃይል ወይም በግድ የሆነ ነገር ውጤታማ እንደማይሆን እና ብዙ ሕፃናት እንደሚቀሩ መገመት አላቃተውም፡፡ የቤተልሔም ሕፃናት  አንድ ሳይቀር እንዲሰበሰቡ ለማድረግ  የወላጆች ፈቃደኝነት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡  ንጉሥ ሄሮድስ በቤተልሔምና በአውራጃዋ  የነበሩትን ሁለትዓመትየሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉአስገደለ ( ማቴ. 2፡16-18 ) ።

    ሄሮድስ ሕፃናትን ለመግደል በቤተመንግሥቱ ለመሰብሰብ  የተጠቀመበት ምክንያተ ፈጠራ

    የሄሮድስ ቅንዓት እጨመረ ከመሄዱም በላይ ነገሥታቱን ሲጠብቅ ሁለት ዓመት መሆኑን ተከትሎ በነገሩ ተሳልቀውበት (አታልለውት)  በሌላ መንገድ መሄዳቸዉን  ከተረዳ በኋላ  ሰይጣን የጭካኔ ጦሩን መዞ አንድ ጊዜ  በልቦናው ላይ ስለተከለበት ሁለት ዓመትና  ከዚያ በታች ያሉ ሕፃናት ሁሉ በእርዳታ ስም በየሀገሩ እንዲሰበሰቡ የሚል ሰይጣናዊ የአረመኔነት መግለጫ የሆነ አዋጅ በብሔራዊ ደረጃ አሳወጀ፡፡

    ሄሮድስ ሕፃናትን በቤተመንግሥቱ ለመሰብሰብአንድ  ምክንያት ፈጠረ፡፡ እንዲህም አለ የሮሙንጉሥ ቄሣር የላከው መልእክት ከእኔ ደርሷል፡፡ሁለት ዓመት የሆናቸውን እና ከሁለት ዓመት የሚያንሱትን ሕፃናት እንድቆጥር ቄሣር አዞኛል፡፡ለሕፃናቱ ወላጆች ገንዘብ እና ልብስ ይሰጣቸዋል፡፡ሕፃናቱም በቤተመንግስት በመልካም አስተዳደግ ያድጋሉ፡፡ ማርና ወተት እየተመገቡ  ጥበብ እየተማሩ በቤተመንግስት አድገው  የመንግስት ሠራተኞች ይሆናሉ፡፡ ይህንም  የተንኮል አነጋገር በአዋጅ አስነገረ፡፡  ያን ጊዜ አይሁድ የሮሙ ንጉሥ የቄሣር ቅኝ ተገዦች ነበሩ፡፡ ሄሮድስም የአይሁድ ንጉሥሊሆን የቻለው ከቄሣር ተወክሎ ነው፡፡ ስለሆነም ትእዛዙ ከቄሣር እንደመጣ አድርጎ  በውሸት ማዕበል ቤተልሔምን አጥለቀለቃት፡፡  ትእዛዙ ግን ከሮሙ ንጉሥ ከቄሣር የመጣ  ሳይሆን የሐሰት አባት ከሆነው ከዲያብሎስ  የመጣ ነው፡፡ ዛሬም  ሐሰት ከዲያብሎስ እየተወለደ በቤተ መንግስት ያድጋል፡፡ ሐሰት ለገዢዎች የሥልጣናቸው እድሜ ማራዘሚያ ይመስላቸዋልና ነው ( ዮሐ.8፡44 ) ።

    ንጉሥ ሄሮድስ እና የ144000 ሕፃናት ሞት በቤተ መንግስት

    ከዚህ በኋላ ብዙ ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጋር በሄሮድስ ትዕዛዝ  በቤተመንግሥት ለመታረድ ተሰበሰቡ፡፡ ልጅ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን እየያዙ ሲሄዱ ልጅ የሌላቸወ ድሃዎች ደግሞ ሀብት ንብረት  ልብስቀለብ  ለመቀበል የሀብታሞችን ልጆችን እየተዋሱ ይዘው ሄደው ነበርና  በጠቅላላው  በሄሮድስ ቤተመንግስት 144 000 ሕፃናት ተሰበሰቡ፡፡ ሄሮድስ በተንኮል የሰነቀው የተስፋ ዳቦ ሕፃናቱን ምወላጆችንም የሚያጠግብ መስሎ ስለቀረበበቤተልሔም አንድ ሕፃን አልቀረም፡፡ ሄሮድስ የሚፈልገው የአይሁድ ንጉሥ የተባለው ሕፃን ክርስቶስ ግን ከ 144 000 ሕፃናት መካከል አልነበረም፡፡ ሄሮድስ በግብዝ አእመሮው ከ 144 000 ሕፃናት መካከል አንዱ የአይሁድ ንጉሥ የተባለው ሕፃን ሳይሆን አይቀርም ብሎ ሕፃናቱእስኪገደሉ ይቸኩል ነበር፡፡ ሁሉንም ሕፃናት ግደሉ ብሎ ለወታደሮቹ  ንጉሳዊ ትዕዛዙን  አስተላለፈ፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች በአንድ ቀን 144 000  ሕፃናትን አረዱ፡፡  በየሰፈሩ ለቅሶና ዋይታ ሆነ፡፡

     የንጉሡ ወታደሮችምበእርዳታ ስምየሰበሰብዋቸውን ሕፃናት እጅግ በሚዘገንን መልኩ የእናቶቻችውን  ጡት እንኳ በአግባቡ ጠጥተው ሳይጨርሱ አንገት አንገታቸውን በሰይፍ ቆራርጠው ጨረስዋቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሕፃናት እልቂት በንጉሱ ትእዛዝ ምክንያት ከመፈጸሙ አስቀድሞ ንጉሡ ይህንን እኩይ ሐሳብ ሲያስብ  በዮሴፍጠባቂነት፣ በእመቤታችን እናትነትና በቅድስት ሶሎሜ ረዳትነት ያድግ የነበረው  ጌታችን ይህ አዋጅ ከመታወጁና እልቂቱም  ከመፈጸሙ አስቀድሞ መልዓከ እግዚአብሔር  በሌሊት ለቅዱስ ዮሴፍተገልጾ "ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ"  ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው፣ አለ ጊዜውም ደሙን ሊያፈሰው አጥብቆ ይፈልገዋልና እናቱንና ልጁን ይዘህ ወደግብፅ ሽሽ (ማቴ 2፡1-23) ። በማለት ተናግረውና በዚያች ሌሊት ወደ ምድረ ግብፅ ጉዞ ጀመሩ፡፡ታሪኩ በማቴዎስ ወንጌል እና ጥር ሦስት ቀን በሚነበበው በመጽሐፍ ስንክሳር ተመዝግቧል፡፡ነቢዩ ኤርምያስ ስለዚህ ጽኑዕ ኀዘን ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ "ድምፅ በራማ ተሰማ ለቅሶና ብዙ ዋይታ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች መጽናናትንም አልወደደችም የሉምና" የተባለው ተፈጸመ  (ማቴ. 2፡18፣ ኤር. 31፡15 ) ።  ራሔል የያዕቆብ ሚስት የዮሴፍና የብንያም እናት መሆንዋ ( በዘፍጥረት . 30፡22 እና 35፡16 )  ተጽፏል፡፡  የቤተልሔም ሕፃናት በሄሮድስ ሰይፍ በታረዱ  ጊዜ ራሔል አልነበረችም፡፡ ሆኖም ልጆቻቸው የታረዱባቸው እናቶችና የታረዱ ሕፃናት የራሔል የልጅ ልጆች ስለሆኑ  በልጆቻቸውሞት መጽናናት ያቃታቸውን እናቶች በራሔል ወክሎ ይናገራል፡፡ ኤርምያስ  በልጆቻቸው ሞት የሚያነቡትን የእስራኤልን ሴቶች ራሔል ብሏቸዋል፡፡

    ከእመቤታችን ስደት ጋር  ታሪክ ያስተናገደው የዮሴፍ ልጅ ዮሳ

    የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ከእነ ዮሴፍ ጋር አልተሰደደምከአባቱ ቤት ቀርቶ ነበር፡፡ ሄሮድስ እነ ዮሴፍን ለመያዝ ብዙ ጭፍራ ላከ፡፡ የሄሮድስን የተንኮልምሥጢር የሚያውቁ ሰዎች ሄሮድስ ዘመዶችህን ሊያስገድል ብዙ ጭፍራ /ወታደር/ ላከ ብለው ለዮሳ ነገሩት፡፡ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እየሮጠ ወደ ዘመዶቹሲሄድ ሰይጣን ሰው መስሎ መንገድ ዳር ተቀምጦ የት ትሄዳለህ አለው፡፡  ወደ ዘመዶቼ አለ ዮሳ፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች  ለጥቂት ቀደሙህ እሰከአሁን ዘመዶችህን ገለዋቸው ይሆናል፡፡ ምን ያደክምሃል ተመለስ አለ ሰይጣን፡፡ ዮሳም ዘመዶቼ  ሞተውከሆነ  እቀብራቸዋለሁ አልሞቱም  ከሆነሄሮድስ እያስፈለጋቸው መሆኑን አነግራቸዋለሁ ብሎ የሰይጣንን ምክር ሳይቀበል መንገዱን ቀጠለ፡፡እግዚአብሔር ለዮሳ የአንበሳን ኃይል ሰጠው፡፡ እነዮሴፍ ሦስት ቀን የተጓዙትን መንገድ በአንድ ቀን ተጓዘና እነዮሴፍ ከደረሱበት ቦታ ደረሰ፡፡  እነዮሴፍ ሦሰት ቀን በተከታታይ ስለተጓዙ  ደክሞቸአው አርፈው ነበር፡፡ ሰሎሜ  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስታጥበው አገኛቸው፡፡ ዮሳ ሰላምዋላችሁ ሰላም አደራችሁ ሳይል እንደደረሰ በጣም የሚያስደነግጥ ቃል ተናገረ፡፡ እንዲህም አላቸው በቤተልሔም እና በይሁዳ ሕፃን ያዘለች ሴት አትገኝም፡፡ ሁሉንም ሕፃናት ሄሮድስ በሰይፍ አሳርዷቸዋል፡፡ ይህን ሕፃን ኢየሱስ ክርስቶስን ልታስገድሉት ከዚህ ተቀምጣችኋል፡፡ እመቤታችን የዮሳን ቃል በሰማች ጊዜ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰሎሜ እጅ ተቀበለችና አቅፋ ይዛ በሌሊት ብርድ እና በፀሐይ ቃጠሎ መከራ የምቀበለው ከሞትላላድንህ ነው ብላ ጽኑዕ ልቅሶን አለቀሰች፡፡

    ሕፃኑ ኢየሱስ ክርሰቶስ ዮሳን እንዲህ አለው ድካምህ ዋጋ የሚያሰጥ ነው ነገር  ግን እናቴንስለአስደነገጥካት ይችን ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ አለው ፡፡ ወዲያውም  ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ አባቱ ዮሴፍ ቀበረው፡፡ እንደእኛ እንደሰዎች አመለካከት ዮሳ የሚሸለም ሰው ነበር እንጂ የሚቀጣ  ሰውአልነበረም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዮሳ ባጠፋው ትንሽ ጥፋት በሥጋው ተቀጥቶ በነፍሱ ሕያው እንዲሆን አደረገው ፡፡ የአግዚአብሔር ወዳጆችትንሽ ጥፋት ሲአጠፉ በሥጋቸው ይቀጣሉ፡፡ ለምሳሌ አሮን እና ሙሴ የእግዚአብሔር ወዳጆች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ባጠፉት ጥፋት ተቀጡ፡፡ ወደተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ በመንገድ ሞቱ "እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋችሁ ምድር ይህን  ጉባዔ ይዛችሁ አትገቡም" አላቸው ( ዘኁ. 20፡1-13 ) ። ጥበበኛው ሰሎምንም እንዲህ ይላል "ልጄ ሆይ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ  በገሠጸህም ጊዜ አትመረር እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልናአባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ" (  ምሳ. 3፡11 )   ዛሬስ በጌታ ላይ፣ በእመቤታችን ላይ፣ በቅዱሳን ላይ ያልተገባ የሰነፍ ንግግርንስ የሚናገሩ ምንኛ በነፍስ በሥጋ ይቀጡ ይሆን ?

    ጥጦስና ዳክርስ ( ሁለቱ  ወንበዴዎች )

    ጥጦስ እና ዳክርስ ሁለት ወንበዴዎችመተዳደሪያቸው ቅሚያ ነበር፡፡ እነዮሴፍ ከገሊላበወጡ ጊዜ ወንበዴዎቹ ተከተልዋቸው፡፡ በበረሃ ቢፈልጓቸውም እስከ ስድስት ቀን አላገኝዋቸውም፡፡ በሰባተኛው ቀን አገኝዋቸውና ዛሬስ እግዚአብሔር ከእጃችን ጣላችሁ ብለው እየሮጠ  ሄዱባቸው፡፡ሰሎሜ አስቀድማ ልብሷን ጥላላቸው ሸሸች፡፡ወንበዴዎቹ ከእነዮሴፍ እጅ የተገኘውን ቀምተው ከሄዱ በኋላ ጥጦስ ዳክርስን  እንዲህ አለው፡፡ ይቺ ሴት የነገሥታት ወገን ትመስለኛለች፡፡ ሕፃኑምከነቢያት አንዱ ይመስለኛል፡፡ የቀማናቸውን እንመልስላቸው? ዳክርስም ጥጦስን እንዲህ ያለውን ርኅራኄ ከየት አገኘኸው? ይህን ውንብድና ያስተማርከኝ አንተ ነህ፡፡ ሌላው ደግሞ ዛሬ የቀማነው የእኔ ድርሻ ነው የራስህን ድርሻ ወስደህ የእኔን ድረሻ እንመልስላቸው ትላለህ ?  አለው፡፡ እነዚህ ሁለት  ቀማኞች አንድ ቀን የቀሙትን አንደኛው ሲወስድ በሌላ ቀን የቀሙትን ደግሞሁለተኛው ይወስድ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የቀሙትየዳክርስ ድርሻ ነበር፡፡ ጥጦስም ከገሊላ እስከዚህ የቀማነውን አንተ ውሰድ ይህን  ለእኔ ስጠኝና ልመልስላቸው አለው፡፡ ዳክርስም  በዚህ ሐሳብ ተስማማ፡፡ ዳክርስ ያልታደለ ሰው ነው፡፡  ጥሩ እድል ገጥሞት ነበር አልተጠቀመበትም፡፡  በትንሽ ርኅራኄ ብዙ በረከት አመለጠው፡፡  ወደ አርሱ ያንዣበበውን ፀጋ ለጓደኛው ሰጠው፡፡

    እመቤታችን ሁለቱ ወንበዴዎች ቁመው በዚህሐሳብ ሲወያዩ አይታ ፈራች፡፡ ወንበዴ የቀማውን ይዞ ይሄዳል እንጂ ለምን ቁሞ ይማከራል?  ምን አልባትልጆቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሕፃን ምክንያት ልጆቻችን ሞቱብን ብለው ልጄንሊገሉብኝ ይሆናል ብላ ጽኑዕ ለቅሶን አለቀሰች፡፡ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስም እናቱም ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት፡፡ አይዞሽ እናቴ አታልቅሺ አይገሉኝም እንመልስላቸው እያሉ ነው፡፡ እኔ በቀራንዮ ስሰቀል እነሱም በቀኜ እና በግራዬ ይሰቀላሉ አንዱ አምላክነቴን አምኖ ይድናል ሁለተኛው ግን አይድንም፡፡ ከዚህ በኋላ ጥጦስየተባለው ወንበዴ ገንዘባቸውን መለሰላቸውና ጌታን አቅፎ ይዞ ሲሄድ ሰይፉ ወድቆ ተሰበረበት፡፡  በጣም አዘነ፡፡ ጌታ የሰይፍህን ስብርባሪ ሰብስብ አለው፡፡ ጥጦስ የሰይፉን ስብርባሪ ሰበሰበ፡፡  ጌታም እንደቀድሞው ይሁንልህ አለው፡፡ ሰይፉም እንዳልተሰበረ ሆነ፡፡ ጥጦስ ሕፃኑ ከነቢያት ወገን ይመስለኛል ብሎ የገመተው ግምት  እውን ሆነለት፡፡ ተአምራቱን አየና አደነቀ፡፡  ጌታ ጥጦስን እንዲህ አለው፡፡ አዳምን ቀድመኸው ገነት ትገባለህ፡፡ ጥጦስም ሄዶ ጌታ የነገረውን ሁሉ እና ያደረገለትንተአምራት ለጓደኛው ነገረው፡፡ ጓደኛው ግን አላመነም፡፡ ጥጦስ የተባለው ወንበዴም ጌታ በተሰቀለ ጊዜ በጌታ ቀኝ ተሰቅሎ ፀሐይ ስትጨልም አይቶ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት አምኖ  "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው፡፡ ኢየሱስም እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከኔ ጋር በገነትትሆናለህ" ( ሉቃ. 23፡42 ) ። ጌታ አዳምን ቀድመኸው ገነት ትገባለህ ብሎ በጫካ የሰጠውን ተስፋ በመስቀል ላይ ፈጸመለት፡፡

    እመቤታችን ከልጇ ጋር በስደት ከተጓዘችባቸውሀገራት መካከል ፦

    የድንግል ማርያም የስደትዋ ምስጢር ጸጋው የበዛላቸው ሊቁ  ቅዱስ አባት አባ ጽጌ ድንግል  "በሰቆቃወ ድንግል" በስፋት እንደገለጹት በዚህዓለም ላይ የኖረና ለወደፊትም የሚኖር ፍጡር እንደ ድንግል ማርያም አለመኖሩ አበክረው ያሰምሩበታል፡፡ ሊቁ ይህንን ድርሰታቸው ሲጀምሩም፡-
    ማኅሌተ ጽጌ፡-
    በስመ እግዚአብሔር ሥሉስ ሕጸተ ግጻዌ ዘአልቦ 
    ሰቆቃወ ድንግል እጽሕፍ በቀለመ አንብዕ ወአንጠብጥቦ 
    ወይሌ ወላህ ለይበል ለዘአንበቦ 
    ከማሃ ሀዘን ወተሰዶ ሶበ በኩለሄ ረከቦ
     ርእዮ ለይብኪ ዓይነ ልብ ዘቦ.... 
    ብለው ነው፡፡
    ይኸውም እንኳንስ በዓይነ ሕሊና ወደ ምድረ ግብፅወርዶ ያየውና የሰማው አይደለም እንዲሁ ለይኩን ብሎ ያዳመጠው እንኳ ሳይቀር ከብዝሐ መከራዋተነስቶ እንደሚያለቅስ ይገልጽልናል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት መንፈሳዊ ዓላማና በምሥጢረ ድኅነት ዉስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ያለውእንጂ በአጋጣሚ የተገኘ እንዳልሆነ እንዲሁም የተነገረው ቃለ ትንቢት ለመፈጸም እንደሆነ ከላይተመልክተናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሲያትቱ ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል፡-"ወፍኖቶሂ ዘእም ዓለም ርኢኩ አዕፃዳተ ኢትዮጵያ ይደነግፃ" ከጥንት የታሰበ መንገዱን አየሁ የኢትዮጵያ አውራጃዎችም ይደነግጣሉ (እንባቆም3፡6-7) የሚለው ትንቢት በማራቀቅ እመቤታችን በመዋዕለ ስደቷ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመምጣት ሃገራችንን ጎብኝታ ሕዝባችንን በአሥራት ተሰጥታ (ከልጇ ተቀብላ) እንደሄደችበመተረክ ሊቃውንት መምህራኑ ያራቅቃሉ፡፡ እመቤታችን ስትሰደድ ያልደረሰበት መከራ፣ያልተፈራረቀባት ችግር ... አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖግን ስለሚደርስባት ነገር ፈጽሞ አታስብም ነበር፡፡ የምታስበው ልጇ እንዳይሞትባት ብቻ ነው፡፡ "ይእቲትበኪ ወትቤ ቀቲሎትየ ይቅድሙ፣ እም ይርአይ ለወልድየ ዘይትከአው ደሙ " ትርጉም እርሷምይህንን ሰምታ አለቀሰች የልጄ ደሙ ሲፈስከምመለከትስ እኔን ያስቀደሙ፣(ሰቆቃወ ድንግል)እንደለ ደራሲ፡፡

    ሀ . ገዳመ ጌራራል /ጌራራል ከተባለ ጫካ /፡ -መልአክ ለዮሴፍ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደግብፅ ሽሽ ካለው በኋላ እመቤታችን ቅድስትድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአመቤታችን ጠባቂ ዮሴፍ የእመቤታችን አክስት ወይም የሐና እህት ሰሎሜ አራቱ ጉዞአቸውን ጀምረዋል፡፡ ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ የተነገራቸው ቢሆንም ወደ ግብፅ ከመሄዳቸውበፊት ብዙ አገሮችን ዙረዋል፡፡ ከቤታቸው እንደወጡጌራራል ወደተባለ ጫካ ነበር የሄዱት  (ማቴ. 2፡13 ) ።  እነዮሴፍን በገዳመ ጌራራል መላዕክት እየመጡ  እያጽናኑዋቸው አርባ ቀን ተቀምጠዋል፡፡ ከአርባ ቀን በኋላ አንድ አውሬ አዳኝ አያቸው፡፡ እርሱም በፍጥነት ሄዶ ማርያምንና ዮሴፍን ሰሎሜንም በጌራራል ጫካ ትላንትና አየኋቸው ብሎ ለሄሮድስ ነገረው፡፡ ሄሮድስም በጌራራ ጫካ መኖራቸውን በሰማ ጊዜ ደስ ተሰኘ፡፡ ይህንን ወሬ ላመጣለት አውሬ አዳኝ እነዮሴፍን ካሳየህኝ የመንግስቴን እኩሌታ እሰጥሃለው ብሎ በጣኦቱ ማለለት፡፡ ሄሮድስ በሀገሩ ሁሉ አዋጅ ነጋሪ /መልእክተኛ/ ላከ፡፡  አዋጅ ነጋሪው በሀገሩ እየዞረ ሁላችሁም የሄሮድስ ወታደሮች ነገ በሄሮድስ ቤተመንግስት እንድትገኙ በማለት አስጠነቀቀ፡፡ወታደሮቹም የሄሮድስን ቤተመንግስት አጥለቀለቁት፡፡ ሄሮድስም ወደ ጌራራል ጫካ ላካቸው፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች የጌራራልን ጫካከበቧት፡፡ ነገር ግን እነዮሴፍን አላገኙዋቸውም፡፡ ወታደሮቹ እርስ በራሳቸው እንዲህ ተባባሉ፡፡ እነዮሴፍ የትሄዱ ምድር ዋጠቻቸውን ?  ይሉ ነበር። እነዮሴፍን ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ የሄሮድስ ሰራዊት በማያውቁት መንገድ ወሰዳቸው፡፡

    ለ . ጥብርያዶስ ፦ ከዚህ በኋላ የእመቤታችን ዘመድየኬፋዝ ንጉሥ ወደ አለበት ወደ ጥብርያዶስ ሄዱ፡፡ እመቤታችንም ሄሮድስ እንደሚያሳድዳት ዘመዷ ለሆነው ንጉሥ ነገረችው፡፡ ንጉሡም  ሄሮድስ የሚያሳድድሽ በምን ምክንያት ነው ብሎ ጠየቃት፡፡ ይህን ሕፃን ለመግደል ስለሚፈልግ ነው አለችው፡፡ ንጉሡም እመቤታችነን ከዚህ ከእኔ ቤት ተቀመጪ አላት፡፡ ቤተሰቦቼንም ማርያም ከእርሱ ቤትመኖርዋን ለማንም እንዳይነግሩ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሄሮድስ ግን በብዙ ሀገሮች እየዞረ ቢፈልጋት ሊአገኛት አልቻለም፡፡ ሄሮድስ እንዲህ ይል ነበር፡፡ ማርያምን ምድር ዋጠቻትን? ሄሮድስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያደረገው ጥረት የደከመው ድካም እጅግ ብዙ ነው ያለውን ኃይል አሟጦ ተጠቅሞአል የሚፈልገውን አለማግኘቱ ደግሞድካሙን ውጤት አልባ አድርጎታል፡፡ ከብዙ ቀናትበኋላ ሄሮድስ ጥብርያዶስ በሚባል ሀገር እመቤታችን መኖርዋን ሰማ፡፡ እመቤታችን ወደአለችበት ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ መልእክተኛ ላከ፡፡ሄሮድስ የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡ ንጉሥ ሆይ ሰላምታ ይገባሃል፡፡ ማርያምን ከነልጅዋ ያዝልኝ ብዙ ወርቅ እና ብር እሰጥሃለሁ በእኔ እና በአንተ መካከል ጽኑዕ ፍቅር ይሆናል፡፡  ንጉሡምየሄሮድስን ደብዳቤ አንብቦ በጣም ተገረመ፡፡ እንዲህም አለ፡፡ ማርያም በእኔ ቤት መኖርዋን ለሄሮድስ ማን ነገረው? መቼም ሰው አልነገረውም ሰይጣን ነግሮታል እንጂ፡፡ የእመቤታችን ዘመድየሆነው ንጉሡም ሄሮድስ የላከውን መልዕክትለእመቤታችን ነገራት፡፡ እመቤታችንም በጣም ደነገጠች፡፡ ንጉሡም እኔ ከሞትኩ ትሞቻለሽ እኔ ከዳንኩ ትድኛለሽ አትፍሪ፣ ለሄሮድስ አሳልፌ አልሰጥሽም አላት፡፡ ‘’ ወትቤ ማርያም ዘፈቀደአምላከ እስራኤል ለይኩን /ማርያምም የእስራኤል አምላክ የፈቀደው ይሁን ‘’ አለች/፡፡ በዚያች ሌሊትየእግዚአብሔር መልአክ  መጥቶ ሲነጋይህን ሀገር ለቀሽ ወደ አድባረ ሊባኖስ ሂጂ አላት፡፡ በዚያም እኔ መጥቼ ተነሺ እስክልሽ ድረስ ተቀመጪ አላት፡፡ በነጋ ጊዜ መልአኩ የነገራትን ለንጉሡ ነገረችው፡፡ ንጉሡም ደስ ብሎት የሦስት ቀን መንገድ እሰከዛብሎን እና እስከንፍታሌም ድረስ ሸኛቷት  ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡

    ሐ . አድባረ ሊባኖስ ፦  እመቤታችን ከዮሴፍ እና ከሰሎሜ ጋር በደብረ ታቦር ጥግ አልፋ ወደተወለደችበት ወደ ደብረ ሊባኖስ ወጣች፡፡ ኰኵህከ ሚባለ ዛፍ ስር ተቀምጣ አለቀሰች፡፡ እንዲህምአለች፡፡ አቤቱ እሰከመቼ ድረስ ካንዱ ሀገረ ወደሌላው ሀገር ስዞር እኖራለሁ ነፍሴስ ምን ያህልጸናች፡፡ ከዚህ በኋላ ያለችበትን ቦታ ሰው እንዳያውቅ ወደ ጫካው ገባች ለአሥር ቀናት ያህል ሰው ሳያያት ተቀመጠች፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ አውሬ አዳኝ ከሩቅሆኖ አያት፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾች ነበሩት፡፡ ውሾቹ ጌታቸውን ትተው እየሮጡ ሄዱና ከእመቤታችንእግር በታች ሰገዱ፡፡ እመቤታችንም በእግርዋ የረገጠችውን መሬትም ይልሱ ነበር፡፡ አውሬ አዳኙ ከሩቅ ሆኖ ውሾቹን ጠራቸው፡፡  ውሾቹ ግን ወደ አንተ አንመጣም አንተ ምን ትሰጠናለህ ከአንድ ጉራሽ በቀር የዕለት ምግባችን ዕንኳ አትሰጠንም አሁንስ ፈጣሪያችንን አግኝተናል ይሉት ነበር፡፡ ድንግልማርያም ውሾቹ የተናገሩትን ሰምታ አደነቀች፡፡ ፍጥረት ሁሉ ለሚፈሩህ ፈጣሪ ምስጋና ይገባሃልብላ አመሰገነች፡፡ ውሾቹም ከእመቤታችን እግር ስርተኙ የሰው ልቡና በተንኮል ሲሞላ እና ከሰው ቅንነት ሲጠፋ ለሰዎች መገለጥ የሚገባው ምሥጢርለእንስሳት ይገለጣል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክለበለአም ሳይገለጥ ለተቀመጠባት አህያ እንደተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ( ዘኁ. 22፡23-30  ) ።  የበለአም ታሪክ በዚህ አውሬ አዳኝላይ ተደግሞአል፡፡  ሄሮድስ ፈጣሪውን ወደ በረሃ አሳደደው፡፡ ውሾቹ ግን ወደ በረሃ ለተሰደደው ፈጣሪያቸው እና ለእናቱ ሰገዱ፡፡ ይህ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ ሰዎች በገንዘብ ፍቅር እና በሥልጣን ጥማት ሲቃጠሉ ከውሾቹ ያንሳሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አውሬ አዳኙ ውሾቹን እየፈለገ መጣ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከልጅዋ ጋር ጫካውን ስታበራ አያትና እጅግ አደነቀ፡፡ መንፈስ /ምትሐት/ እየታየው መሰለው፡፡  እመቤታችን ምን ትፈልጋለህ አለችው፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾቼን እፈልጋለሁ አላት፡፡ እመቤታችንም ውሾች ምንያደርጉልሃል አለችው፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾች አውሬዎችን ይገሉልኛል፡፡ የአውሬዎችን ሥጋ እበላለሁ ቆዳቸውንም እሸጣለሁ አላት፡፡ እመቤታችንም ዛሬ ከምታድናቸው አውሬዎች የበለጠ ነገር አግኝተዋል የእግዚአብሔርን መሲሕ አይተሃልና ወደ ሀገርህ ግባ እኔ በዚህ ጫካ መኖሬን ለማንም አትንገር አለችው፡፡ ውሾቹንም ወደ ጌታችሁ ሂዱ አለቻቸው፡፡ ውሾቹም ለፈጣሪያቸው እና ለእመቤታችን ከሰገዱ በኋላ ወደ ጌታቸው ሄዱ፡፡ አውሬ አዳኙም እያደነቀ ሄደ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በጫካው ውስጥ ነበረች፡፡ በኤልያስ ዘመን ጣዖት አምላኪዋ ኤልዛቤል ነቢያትን ካህናትን ባስገደለቻቸው ጊዜ እግዚአብሔርን ከኤልዛቤል ዓይን የሠወራቸውበጫካ የሚኖሩ ጻድቃን እየመጡ ከእመቤታችን ይባረኩ ነበር፡፡

    እመቤታችንና ንጉስ ደማትያኖስ

    አውሬ አዳኙ ከሰባት ቀን በኋላ ደማትያኖ ስለተባለው ንጉሥ ያየውን ሁሉ ነገረው፡፡ ደማትያኖስም አውሬ አዳኙ የነገረው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አሥር የቤተመንግስት ሰዎችን ከአውሬ አዳኙ ጋር ላከ፡፡  የተላኩት ሰዎች በደረሱጊዜ እመቤታችንን ከልጅዋ ጋር አገኝዋት፡፡ እመቤታችን ግን ለማንም አትንገር ያለችውን ስለተናገረ አውሬ አዳኙን በቁጣ ተመለከተችው፡፡ አውሬ አዳኙም የጨው ድንጋይ ሆነ ( ማቴ. 8፡4  )።  የሎጥ ሚስት ታሪክ በአውሬ አዳኙ ተደግሞአል፡፡ እግዚአብሔር ሎጥን በእሳት ከምትጋየው ከሰዶም ባወጣው ጊዜ ወደኋላህ አትመልከት ብሎት ነበር፡፡ የሎጥ ሚስት ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ ወደ ኋላዋ ወደ ሰዶም ተመለከተችና የጨው ሐውልት ሆነች ( ዘፍ. 19፡26 ) ።  ከቤተ መንግስት የተላኩት ሰዎችም እመቤታችን ያደረገችውን ተአምር አይተው በጣም ደነገጡ፡፡እመቤታችን እኔም እንደ እናንተ ሰው ነኝና አትፈሩብላ አረጋጋቻቸው፡፡ መልእክተኞችም ንጉሡ ደማትያኖስ እንደላካቸው ነገርዋት፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው እመቤታችንን ከልጅዋ ጋር እንደአገኝዋት እና አውሬ አዳኙ የጨው ድንጋይእንደሆነ ለደማትያኖስ ነገሩት፡፡ በማግስቱ ደማትያኖስ ብዙ ሠራዊት አስከትሎ ወደእመቤታችን ሄደ፡፡ ብዙ ሠራዊቱን ከተራራው ስር ትቶከሰባቱ ጋር እመቤታችን ወደ አለችበት ጫካ ገባ፡፡ እመቤታችን እንደ አጥቢያ ኮከብ ስታበራ አገኛት፡፡ ንጉሡ ደማትያኖስ ለእመቤታችን ከሰገደ በኋላ አንቺ ከማን ወገን ነሽ ከየት ሀገርስ የመጣሽ ነሽ ብሎ ጠየቃት፡፡ እመቤታችንም እኔ እስራኤላዊት ነኝ፡፡የይሁዳ ክፍል ከምትሆን ከቤተልሔም ነው የመጣሁት አለችው፡፡ እመቤታችንም ሄሮድስን ፈርቼ ነው አለችው፡፡ ንጉሡም ሄሮድስ ለምን ይጠላሻል አላት፡፡ እመቤታችንም እንዲህ አለችው፡፡ ሁለንተናው እሳት የሆነ ግሩም መልአክ ገብርኤል መጥቶ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እነሆወንድ ልጅ ትወልጃለሽና ስሙንም አማኑኤል ትይዋለሽ  አለኝ፡፡ እንደነገረኝ ይህን ሕፃን በድንግልና ጸንሼ በድንግልና ወለድኩት፡፡ ከተወለደ በኋላ ሰብአሰገል የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ የት ነው እያሉ መጡ፡፡ ይህን ነገር ሄሮድስ ሰማ፡፡  ስለዚህእኔን እና ሕፃኑን ሊገድለን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊትበዚህ ቦታ አባቴና እናቴ ነበሩ እኔም የተወለድኩት በዚህ በደብረ ሊባኖስ /በሊባኖስ ተራራ/ ነው አለችው፡፡  ደማትያኖስም የአባትሽ እና የእናትሽ ስምማን ይባላል ? አላት፡፡ እመቤታችንም አባቴ ኢያቄምእናቴ ሐና ይባላሉ አለችው፡፡ ደማትያኖስም እነዚህን ሰዎች አውቃቸዋለሁ አላት፡፡ ደማትያኖስ . ብዙሠራዊት ያለው ኃያል ንጉሥ ስለሆነ ከዚህ በኋላ አሥር ነገሥታት እንኳ ቢገቡ አንቺን ማግኘት አይቻላቸውም አትፍሪ አላት፡፡ ወደ ኃላውም በተመለሰ ጊዜ የጨው ድንጋይ የሆነውን ሰውአየውና ይህ ሰው ለምን የጨው ድንጋይ ሆነ አላት፡፡ እመቤታችንም በኃጢአት ነው አለችው፡፡ ከዚህበኋላ እመቤታችን ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፡፡የጨው ድንጋይ የሆነውን ሰው አስነሳችውና ለማንም አትንገር ብዬህ ነበር ለምን ነገርህ አለችው፡፡ የጨው ድንጋይ የሆነው ሰው ኃጢአቱን አምኖ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ የተነገረንን ምስጢር እንጠብቅ፡፡ ብዙ ጊዜ ኃጢአት የሚፈትነን በንግግራችን ነው፡፡ ንጉሡ ግን ይህን ተአምር ባየጊዜ እጅግ ደነገጠ፡፡ እመቤታችን በቀኝ እጅዋ ይዛ አትፍራ አለችው፡፡ እመቤታችን ስትይዘው ድንጋጤውና ፍርሃቱ ለቀ ቀው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ለእመቤታችን ሰገደላትና አባቴና እናቴ ስማቸውን ሲጠርዋቸው በልጅነቴ የምሰማቸው ሚካኤልናገብርኤል ሩፋኤል ከሚባሉት አንዱ አንቺ ነሽ አላት ከማድነቁ የተነሣ፡፡ እመቤታችንም እኔ የእነሱ የጌታቸው ባሪያ ነኝ አለችው፡፡ ንጉሡም ብዙ ገጸበረከት ገንዘብ ይዞ እመቤታችንን ተቀበይኝ አላት፡፡ እመቤታችን ግን ምንም ስደተኛ ብትሆንም አልተቀበለችውም፡፡ ለድሆች ስጣቸው በሰማይመዝገብ ታገኛለህ አለችው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ እመቤታችንም በደብረ ሊባኖስ ሦስት ወር ያህል ተቀመጠች፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሊባኖስ በተባለው ተራራ እነዮሴፍ መኖራቸውንሰምቶ በሠራዊት አስከብቦ ሊይዛቸው ሞከረ፡፡

    ጊጋር የሶርያ ገዥ /ጊጋር መስፍነ ሶርያ/

     አንድ የሶርያገዥ /መስፍነ ሶርያ/ ጊጋር የተባለ ሰውየሄሮድስን እኩይ ምክር ሰለሰማ ወደ እመቤታችን መልእክተኞችን ላከ፡፡ ጊጋር የላካቸው ሰዎች በፈረስእየጋለቡ በፍጥነት ደርሰው የሊባኖስን ተራራ ሄሮድስ በሠራዊት ሊያስከብበው ነውና ሊባኖስንለቃችሁ ሽሹ አሏቸው፡፡ መልአኩም መጥቶከሊባኖስ ውጡ አላቸው፡፡ እመቤታችን ጌታችንዮሴፍና ሰሎሜ ደብረ ሊባኖስን ለቀው ሄዱ፡፡ ከዚህበኋላ ጊጋር መልእክተኞችን ልኮ እነ ዮሴፍን ከደብረሊባኖስ እንዳስወጣቸው ሄሮድስ ሰማ፡፡የምንፈልጋቸውን ሰዎች ያሸሽህብኝ አንተ ነህበማለት ጊጋርን ተጣላው፡፡ ሄሮድስ ወታደሮቹን ልኮ የሶርያ ገዢ ጊጋርን አስያዘና በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ጊጋርም በሰማዕትነት ሞተ ። ነሐሴ 16 ቀን በሚነበበው ስንክሳር ይህን የጊጋርን ታሪክ እናገኛለን፡፡

     መ . ደብረቶና ፦ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ወደ ደብረ ቶና ሄዱ፡፡ በደብረ ቶና የይሁዳአገሮች ይታያሉ፡፡ እመቤታችን ብዙ መንገድ በመሄድ ደክማ ነበርና አልሲስ ከተባለ ዛፍ ስር ተቀመጠች፡፡በጣም ስለደከማት ከዛፉ ስር ተኛች፡፡ መላእክት ነፍሷን በራዕይ ወደ ጽርሐ አርያም ወሰዷት፡፡ የእሳት መጋረጃዎች በቀኝና በግራ በግራ ተከፈቱ፡፡ ልጅዋ ኢየሱስ ክርሰቶስ የሰው ዓይን ያላየውን የሰው ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና ያልታሰበውን በመንግሥተ ሰማያት የሚገኘውን ብዙ ምሥጢርነገራት፡፡ የሰው ልጆች ለዘለዓለም የሚወርሱትንእጅግ ደስ የሚያሰኘውን ዓለም አየች፡፡ ከዚህ በኋላ ነፍሷ ወደ ሥጋዋ ተመለሰች፡፡ ከእንቅልፏ በነቃች ጊዜ ልጅዋን ለምን ወደዚህ የመከራ ዓለም መለስኸኝ አለችው፡፡ ሕፃን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላት ያለመከራ ፀጋ አይገኝም፡፡ በዚህ ዓለም በእኔ ስም መከራ የተቀበሉ ሁሉ በወዲያኛው ዓለም ደስ ይላቸዋል፡፡ አንቺም በወዲያኛው ዓለም ደስ ይልሽ ዘንድ በዚህ ዓለም በመከራ ውስጥ ማለፍ ይኖርብሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ከደብረ ቶና ወጥተው ወደ ሲዶና ሄዱ፡፡ ከሲዶናምወጥተው ወደ ደብረ ዘይት ሄዱ፡፡

    ሠ .  ቤተልሔም ፦ ከደብረ ዘይትም ወጥተው ወደቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉ ከሄሮድስ ሠራዊት አንዱ አያቸው፡፡ በፈረስ እየጋለበ በፍጥነት ከሄሮድስ ቤተመንግሥት ደርሶ ማርያም እና ዮሴፍ ሰሎሜም በቤተልሔም አሉ ብሎ ለሄሮድስ ነገረው፡፡ ሄሮድስ ይህን ዜና ያመጣለትን ሰው እንዲህ አለው የነገረኸኝ ነገር  እውነት ቢሆን የመንግሥቴን እኩሌታ እስጥሃለሁ እውነት ባይሆን ግን አንተን እገልሃለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ እነ ዮሴፍ በዚህ ቦታ አሉ እየተባለ ተራራውን ሸለቆውን ዋሻውን በሠራዊት እያስከበበ ቢፈልግ ሳያገኛቸው ቀርቷል፡፡ ፈልጎ አለማግኘቱ በብስጭት ላይብስጭት ስለጨመረበት አሁን ግን ፈልጎ ባያገኛቸው የጠቆመውን ሰው ለመግደል ቆርጦ ተነሣ፡፡ በዚያች ሌሊት ገብርኤል ወርዶ ዮሴፍንእንዲህ አለው፡፡ በነቢይ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሽሽ (ት.ሆሴዕ . 11.1 ) ፡፡ እነ ዮሴፍም በዚች ሌሊት ቤተልሔምን ለቀው ወጡ፡፡ በነጋ ጊዜ ሄሮድስ ቤተልሔምን አስከበባት፡፡ እመቤታችንበታየችበት አካባቢ የተገኙትን ሰዎች ወንዶችንምሴቶችንም አስገደለ፡፡ ሰዎችን ጨርሶ ከዶሮ እስከውሻ ያሉ እንስሳትን ሁሉ አስገደለ፡፡ ሰማዩም እንደደም ቀይ ሆነ ደም መሰለ፡፡

    ሄሮድስ ላስገደላቸው ሰዎች ከሰማይ አክሊልወረደላቸው፡፡ የአክሊሉን መውረድ የተመለከቱየሄሮድስ ሠራዊትም በማርያም ልጅ በሕጻኑ በኢየሱስ ክርስቶስ  እናምናለንአሉ፡፡ የሥልጣንፍቅር ውስጡን ያጨለመው ሄሮድስ ግን በድንግል ማርያም ልጅ ያመኑትን ወታደሮች በሰይፍ አስቆራረጣቸው፡፡ ማርያምን በቤተልሔም አየኋት ብሎ የነገረውን ወታደርም በሰይፍ አስቆራረጠው፡፡ የሰዎችን ደም በማፍሰስ የሚረካ እየመሰለውየደም ማፍሰስ ሱስ ያዘው፡፡ ዛሬም ምድራችን የምስኪኖቹን ደም በማፍሠስ ወንበርበሚያደላድሉት የስልጣን ዘመን በሚያራዝሙ ግፈኞች ተሞልታለች፡፡ ይቆይ ይሆናል  እንጂ ሁሉምየዘራውን እንደሚያጭድ ይህ ታሪክ ያስረዳልና፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ በፈረስ ላይ ሆኖሲሄድ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ የፈረሱን አፍንጫ  መታው፡፡ ፈረሱ ወደ ላይ ሲዘል በላይ የነበረ ሄሮድስ በታች ሆነ በታች የነበረ ፈረስምበላይ ሆነ፡፡ ሄሮድስ ተንኮታኮተ፡፡ አጥንቱ ተሰባበረ ሥጋው ተቆራረጠ፡፡ የብዙዎችን ደም ባፈሰሰበት መሬት ላይ የእርሱም ደም ፈሰሰ፡፡ ሠራዊቱ ተሸክመው ከቤቱ አደረሱት፡፡

     ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ
    ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
    አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን  !!!!!!

    ክፍል ሦስት ይቀጥላል … … … … … … ይቆየን::

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ዘመነ ጽጌ - ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top