• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    እንደ ሙሴ ያለ መሪ ክፍል አንድ


    ወደ ሃሳቤ ከመግባቴ በፊት ጥቂት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ህይዎት ላነሳ እዎዳለሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላቅ ስምና ዝና ካላቸው ሰዎች ከፊት ልናስቀምጠው እንችላለን። ሊቀነቢያት ሙሴ ከመወለዱ አንስቶ እስከ ህልፈተ ህይዎቱ ድረስ እግዚአብሔር ታላላቅ ስራዎችን ከእርሱ ጋር ሆኖ ይሰራ ነበር።

    እስራኤል ዘስጋ  በግብጽ ባርነት ሳሉ ይደርስባቸው ከነበረው ሰቆቃ አንዱ ወንድ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የተከለከለ ነበር። ማንኛውም ልጅ ወንድ ሆኖ ከተወለደ ይገደል ነበር። ታዲያ በዚህ ዘመን ነበር ሊቀነቢያት ሙሴ የተወለደው። አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነ ስለነበር በባህር ቢጣልም እንኳን አንዳች ሳይነካው በህይዎት ከባህር ሊወጣ ችሏል። ከዚህም በላይ በእግዚአብሔር ጥበብ በቤተ መንግስት በእንክብካቤ  የንጉሱ ልጅ እየተባለ ነው ያደገው። ነገር ግን እሱ በቤተመንግስት ተደስቶ ቢኖርም በወገኖቹ ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ እለት እለት ያንገበግበው ስለነበር። የንጉስ ልጅ መባልን አይፈልግም ነበር። በኋላም  ወገኖቹ በስቃይ ላይ እያሉ እኔ በቤተመንግስት የላመ የጣፈጠ አልበላም አልጠጣም ብሎ ወሰነ።  የህዝቡን ግፍና መከራ ለማየት በሄደ ጊዜ አንድ ግብጻዊ እስራኤላዊውን ሲደበድበው አገኘው ። በልቡ ውስጥ ቁጭት  ስለነበረው ግብጻዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ታድጎታል። ነገር  ግን ይህን በማድረጉ  ከጠላት ያዳነው ሰው መልሶ አሳልፎ ሊሰጠው እንደሚችል በመረዳቱ ከቤተመንግስት ኮብልሎ  ወደ ምድያም ምድር ተሰደደ ።


    ወደ ምድያም  ምድር በሄደ ጊዜ የምድያሙ ካህን የዮቶር በጎች ጠባቂ ሆኖ ይኖር ነበር ለጌታው ታማኝ ስለነበር ዮቶር ልጁን ድሮለት ሃብት ንብረት አፍርቶ ይኖር ነበር። ይሁን እንጅ እለት እለት የወገኖቹን መከራ እያሰበ ይጨነቅ ነበር። ከሱ በላይ የህዝቡን መከራ ያየ እግዚአብሔር በምድረ በዳ በቁጥቋጦ መካከል በእሳት አምሳል ተገለጾ የህዝቤ መከራ እጅግ በዝቷልና መሪ ሆነህ ነጻ ታወጣቸው ዘንድ እልክሃለሁ ብሎ አናገረው ከዚያም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሎ ከወንድሙ ከአሮን ጋር በመሆን በፈርኦን ፊት ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ህዝበ እግዚአብሔር እስራኤልን  በእምነት የኤርትራ ባህርን ከፍሎ አሻግሮ ከፈርኦን ባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል። ከዚያም በኋላ በምድረ በዳ ህዝቡን ሲመራ ይደርስበት የነበረውን መከራ በትእግስት እያለፈ የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ህዝቡን ወደምድረ ከነዓን ለማግባት እለት እለት ይተጋ ነበር። ህዝበ እስራኤል በተለያየ ጊዜ እግዚአብሔርን ትተው ወደ ጣኦት አምልኮ ይመለሱ ስለነበር  በበደላቸው ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ እንዳያጠፋቸው ስለህዝቡ በጸሎት የሚተጋ መሪ ነበር። መቸም ማንኛውም  ክርስቲያን ስለሊቀነቢያት ሙሴ የህይዎት ታሪክ የማያውቅ ይኖራል ብየ ሳይሆን ጠቁሜ ማለፍ ስለፈለኩ ነው።    

    እኛ ኢትዮጵያውያን ከዓለም ልዩ የሚያደርገን ብዙ ነገር አለ። በተለይ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ዓለምን የሚያስደንቅ ነው። በሃገራችን ያለው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርስ ከዓለም ቀዳሚት ሃገር ኢትዮጵያ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው። ህዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን እንኳን ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ከኢትዮጵያ ቀጥሎ የሚታወቁ ህዝቦች መሆናቸውን ያረጋግጥልናል << የእስራኤልልጆችሆይ፥እናንተ ለእኔእንደ ኢትዮጵያልጆችአይደላችሁምንይላል እግዚአብሔር  ት አሞ 9፥7 >> ሃገራችን ኢትዮጵያ በህገልቦናም ሆነ በህገ ኦሪት እግዚአብሔርን የምታመልክ እንዲሁም በዘመነ ሃዲስ ጌታ ባረገ ባመቱ ክርስትናን በእግዚአብሔር ፈቃድ አምና የተቀበለች ሃገር ነች። በዚህም የተነሳ በተለያየ ዓለም የነበሩ ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደዚች ቅድስት ምድር መጥተው ብዙ ፍሬ አፍርተውባታል። እስካሁንም እነሱ የዘሩት መልካም ፍሬ ለህዝቧ በረከት እያሰጠ ይገኛል።

    ዛሬ ላይ ከአንዳንድ ሰዎች የስንፍና ንግግር እምንሰማበት ጊዜ አለ። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እየመነመነች ነው፣ ህዝቧም ወደሌላ እምነት እየሄደ ነው፣ አገልጋዮቿም እየተለያዩ ነው የሚሉ፣ ኢትዮጵያውያን ሆነው የኢትዮጵያን ማንነት ማወቅ የሚችሉበት መንፈሳዊ እውቀት የተነሳቸው ሰዎችን እነሆ እናያቸዋለን፣ እንሰማቸዋለን። ነገር ግን ለትንሳኤ ስቅለት ዋዜማው እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እየሰፋች እንጅ እየመነመነች አይደለም። ሌሎች የእምነት ተቋማት ቤተ እምነታቸውን ሲዘጉና ሲሸጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ግን በአረብ ሃገራት ሳይቀር ያማሩ ህንጻ አብያተክርስቲያናትን እየገዙ እየገነቡ ይገኛሉ። ከምንም በላይ ይህች ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሚመራት መሆኑ የሚታወቀው አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩ አገልጋዮች በስጋዊ ጥቅም ተታለው ከአላማቸው ፈቀቅ ቢሉም እንኳን ህዝቡ በዚህ ሳይናወጽ ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት ሳያቋርጥ በምህላና በጸሎት ቤተክርስቲያኑን በዝማሬና በጸሎት የሚጠብቅ ነው።

    ዛሬ ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የፈተና ወቅት ልንለው እንችላለን። ነገር ግን በዚህ ፈተና ግን ትወድቃለች ማለት የቤተክርስቲያኒቱን ማንነት መዘንጋት ነው። ቤተክርስቲያን ድሮም ቢሆን ማእበል በበዛበት ውቅያኖስ መካከል የምትጓዝ የእግዚአብሔር መርከብ ተብላ ነው የተሰየመችው። አንዳንዶች ወቅታዊውን ችግር ብቻ በመመልከት የማያንጽ ንግግር በአንደበታቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ።ይህ ግን ትክክል አይደለም። ምክንያቱም የነዮዲት ጉዲትንና የነግራኝ መሐመድን ዘመን ስናስበው  ከዛሬው ጋር የሚነጻጸር አይደለም። እርግጥ ነው ፈተናዎች ተጋርጠዋል። ከባድ መስሎ የታየውም የውጭውን ፈተና ለመቋቋም ደፋ ቀና ስትል የውስጡ ፈተና ጉልበት አግኝቶ ሊያናውጻት በመሞከሩ ነው። ነገር ግን ልጆቿ ተስማምተው ወደአንድነት ቢመጡ የሚቀረፍ ፈተና ነው። <<የገሃነምደጆችም አይችሉአትም ማቴ 16፥18 >> 

           የችግሩ መንስኤ አካላት የምንላቸው

    1 ምድራዊውን እንጅ ሰማያዊውን ክብር የዘነጉ አንዳንድ የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች

    2, የበግ ለምድ ለብሰው በመካከላችን የገቡት ተኩላዎች

    3, ለሆዳቸው ያደሩ አላማቸውን በጥቅም የለወጡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች

    4, ከላይ የተገለጹት አካላት አላማና አካሄድ ያልገባቸው እንዲሁም ስለሃይማኖታቸው እውቀት ሳይኖራቸው በምናለበት የሚጓዙ የዋሃን ምዕመናን ናቸው

     ለዚህ መፍትሄው ደግሞ ለቤተክርስቲያን ቅን መሪ አስተማሪ የሚሰጥ እግዚአብሔር ስለሆነ ስለህዝቡ እራሱን ለሞት እንኳን ቢሆን አሳልፎ የሚሰጥ እንደ ሙሴ ያለ መሪ እንዲሰጠን መጸለይ።

    ለአባቶቻችንም በጎ ህሊና ሰጥቶ ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን ክብር ተመልክተው ለመንጋው አርአያና ምሳሌ ሆነው ቤተክርስቲያንን እንዲመሩ በጸሎት ማሰብ፣።

    አንድ ሃሳብና አንድ መንፈስ ሆኖ ተኩላዎቹን ከመካከላችን ነቅሎ ማስወጣት።

    አላማቸውን የዘነጉትን በአንድነት ሆኖ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ።

     የዋሃኑን በቃለ እግዚአብሔር በማነጽ እውነቱን እንዲረዱ ማድረግ ነው።

    ይህን ለማለት ያስደፈረኝ በእያንዳንዱ ስህተት ጀርባ ንጹሃን ነን ብለን ሌላውን የምንኮንን ሰዎች እጅ እንዳለበት ለማየት በመቻሌ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች የምዕመናን የቤተክርስቲያን ተሳትፎ ከድንበሩ አልፎ ቤተክርስቲያን መስርተው ያለስርዓት ሲጓዙ ይታያሉ ። ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚመሰረት፣ ማን መመስረት እንዳለበት ፣ እንዲሁም ማን መምራት እንዳለበት በስርዓተ ቤተክርስቲያን ተደንግጓል። ከዚህ የወጣ አካሔድ ምናልባት በስጋ ጥቅም ያስገኝ ይሆናል ለነፍስ ግን አይጠቅምም። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው የቤተክርስቲያን ማእከላዊነት ባለመጠበቁ ነው። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ቤተክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ በስጋዊ ሃሳብ ለሚኖሩ የተመቻቸው ይመስላል። ይህ በአስቸኳይ መቆም ያለበት ተግባር ነው ።ብዙ ጊዜ ሰዎች በቀጥታ የሚሰሩት ስህተት እንጅ በተዘዋዋሪ የሚፈጽሙትን ደባ የሚያስኮንን አይመስላቸውም። እንደውም ትልቁ ኃጢአትና በደል ከጀርባ ሆኖ የሚሰራው ክፉ ተንኮል ነው።  በሰው ሃሳብ ተመርቶ ክፉ ስራ የሚሰራ በእባብ ሲመሰል ለሌላው ክፉ ምክርን የሚለግስ ደግሞ በዲያቢሎስ ነው የሚመሰለው። የዲያቢሎስ ክፉ ስራ የተገለጸው በእባብ ተመስሎ የሰራው ተንኮል ነው። ዘፍ 3፥1  እስከዛሬም ድረስ እባብ የስድብ ምሳሌ ሆኖ የቀረው የሰይጣን መልእክተኛ ሆኖ ለሄዋን የማይገባ መልእክት በማስተላለፉ ነው ዘፍ 3፥14 ። ስለዚህ በሃገር መሪዎችም ሆነ በሃይማኖት አባቶች ጀርባ በጎውን ክፉ በማስመሰል ነገር አጣፍጠው በማቅረብ በሰይጣን የተካኑ ብዙ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ አሉ።<< እንዲህ ያሉት ለገዛሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምናበሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮልየሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። ሮሜ 16፥18 >>  የእነዚህን ክፉ ሰዎች አላማ መረዳት ነው መፍትሄው። ይህ ከሆነ ሁሉም በሰላም መኖር ይችላል።

    ይቀጥላል , , , , , , , , , , ,, , , , , , , , , ,

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: እንደ ሙሴ ያለ መሪ ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top