መንፈስ ቅዱስ ፈጣሬ ዓለማት ገባሬ ዓለማት ነው።
ይህንን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ወመንፈሰ እግዚአብሔር ይጼልል መልዕልተ ማይ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር›› ይላል ። ዘፍ 1 ፥ 2 ።
(የዓለም ሁኔታ) ሳይጸና ፥ ምድር እንደ ውኃ በምትዋልልበት ጊዜ ፥ መንፈስ ቅዱስ ያዘጋጃት ነበር ። ባልጸናችው ምድር ላይ የመንፈስ ቅዱስ መስፈፍ በአንዲት የበረሃ ወፍ ታቅፎ ያልረጋው እንቁላል ረግቶ ጫጩት እንደሚሆን እንደዚሁ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ በመስፈፍ ያልጸናውን ዓለም እንዲጸና አድርጎታል ። ዘማሪውም ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ›› በማለት የምድርና የሰማይ ሠራዊት በአፉ እስትንፋስ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ጸኑ ይነግረናል ። መዝ 32 ፥ 6 ።
ኢዮብም በበኩሉ ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ›› በማለት ፥ በአካላዊ እስትንፋሰ አብ ወወልድ ፥ በባሕርያዊ ሕይወተ አብ ወወልድ ሰው ሁሉ ሕይወትን እንደ ለበሰ ይነግረናል ። ኢዮ 33 ፥ 4 ።
ይህ የኢዮብ ቃልም ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ›› ተብሎ ከተጻፈው ጋር ይስማማል ። ዘፍ 2 ፥ 7 ።
በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከወልድ ጋር በአንዲት መለኮታዊት ክሂል ዓለምን ያሆነ ፣ ያደረገ ፣ የፈጠረ ፣ ፈጣሪ ፣ ገባሪ ፣ ሕያው ጌታ ነው ። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከወልድ ጋር ዕሩየ መለኮት በመሆኑ እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር ይባላል እግዚአብሔር ስሙ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር በማለት ከአብ ከወልድ ጋር ያለውን ዕሪና ፣ እግዚእና ፣ ዕሩየ መለኮትነት ይጠቁማል። በትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ቁልጭ አድርጎ ተርጉሞታል ። ኢሳ 6 ፥ 1-10 ። የሐዋ 28 ፥ 23-28 ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም እግዚአብሔር ብሎ እንደ ጠራው በሐዋርያት ሥራ ተጽፏል ። የሐዋ 5 ፥ 3-4
ከአብና ከወልድ ጋር ዋሕደ መለኮት ዕሩየ መለኮት ቢሆንም ልዩ አካል ነው (ልዩ አካል አለው) ።
ለአብ የራሱ የሆነ አካል አለው ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል አብ ይባላል ፣ አብ የሚለው ስሙም ስመ አካል ነው ። ስመ ግብር ስመ ከዊን አይደለም ።
ወልድም የራሱ የሆነ አካል አለው ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ይባላል ፣ ወልድ የሚለው ስሙም ስመ አካል ነው ፣ ስመ ግብር ስመ ከዊን አይደለም ።
መንፈስ ቅዱስም የራሱ የሆነ አካል አለው ፣ ከሦቱ አካላት አንዱ አካል መንፈስ ቅዱስ ይባላል ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስምም ስመ አካል ነው ። ስመ ግብር ስመ ከዊን አይደለም ።
ይህንንም ትምህርት መጽሐፈ ሕይወት ባሕረ ጥበብ መጽሐፍ ቅዱስ በአጫፋሪ ወይም በመስተጻምር ይገልጸዋል ። ‹‹አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል›› (ኢሳ 48 ፥16)
ይህ ቃል የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነት ይገልጻል ጌታ እግዚአብሔር የተባለው አብ ሲሆን በመስተጻምር መንፈሱ ተብሎ የተጠቀሰው መንፈስ ቅዱ ነው ። ልከውኛል የሚለው ቃለ ትንቢት ደግሞ በሥጋ ማርያም የተገለጸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይጠቁማል፡፡ ‹‹እስመ በፈቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኃነነ-በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ መጥቶ አዳነን›› እንዳለ ሊቁ (የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም) (ማቴ 28 ፥19)
በስሙ ልዩ ነው፤
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ተለይቶ የሚጠራበት አካላዊ ስሙ መንፈስ ቅዱስ ነው ። በመሆኑም በስሙ ልዩ ነው ፣ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ። መንፈስ ቅዱስ ስመ አካል ነው ፣ ይህ ስም የመንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስም ነው መቸም መች በዚህ ስም አብ ወልድ አልተጠሩበትም ፣ ስመ አካለ ወልድ ወልድ ነውና አብ መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም ፣ አብም የአብ ስም ብቻ ነው የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ስም አይደለም ፣ በዚህም ስም ወልድ መንፈስ ቅዱስ አልተጠሩበትም ፣ አይጠሩበትም ።
ስመ አካለ አብ ነውና ። ሥላሴ (አብ ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) ግን አካላቸው ስማቸው ግብራቸው የተለየ ቢሆንም ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ነው ።
አብ ፥ ወልድ ፥ መንፈስ ቅዱስ ፥ ተብለው የሚጠሩ የእግዚአብሔር ሦስቱ አስማተ አካላት ግን አይፋለሱም ይህን በተመለከተ ሊቁ አግናጥዮስ የተናረገውን ቃል እንመልከት
‹‹አብሂ ውእቱ አብ ኢኮነ ወልደ ወኢመንፈስ ቅዱሰ ፣ ወልድሂ ውእቱ ወልድ ወኢኮነ አበ ወኢመንፈስ ቅዱሰ ፣ ወመንፈስ ቅዱስሂ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ኢኮነ አበ ወኢወልደ ። ኢይፈልስ አብ ለከዊነ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፥ ወኢወልድ ለከዊነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ፥ ወኢመንፈስ ቅዱስ ለከዊነ አብ ወወልድ እሉ ሠለስቱ አካላት ፍጹማን ዲበ መንበረ ስብሐት ወእኁዛን በጽምረተ አሐዱ መለኮት ››
ትርጉም
አብም አብ ነው እንጂ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም ። ወልድም ወልድ ነው እንጂ አብን መንፈስ ቅዱስን አይደለም ። መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ አብን ወልድን አይደለም።
አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን ወደ መሆን አይለወጥም ፣ ወልድም አብን መንፈስ ቅዱስን ወደ መሆን አይለወጥም ፣ መንፈስ ቅዱስም አብን ወልድን ወደ መሆን አይለወጥም እሊህ ሦስቱ አካላት በጌትነት በክብር ፍጹማን ናቸው ፤ በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው›› በማለት ተናግሯል (ሃይማኖተ አበው ዘአግናጥዮስ ዘአንጾያ ገጽ 37 ክፍል 1 ቊ 8-9)
ሦስቱ የእግዚአብሔር አካላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፍጹማንና ምሉዐን አካላት መሆናቸውን በብቃት ያስገነዘበው ገለጻ አብ ልብ ሲሆን በልብነቱ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሕሊናቸው በመሆኑ እንደሆነ ፣ ወልድም ቃል ሲሆን በቃልነቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ንግግራቸው በመሆኑ እንደሆነ ፣ መንፈስ ቅዱስም እስትንፋስ ሲሆን በእስትንፋስነቱ ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው እንደሆነ ፥ ወይም ሕይወታቸው በመሆኑ እንደሆነ ፣ የቤተክርስቲያን መሠረታዊና ኦርቶዶክሳዊ እምነት ነው ።
ሠራፂ ነው ።
መንፈስ ቅዱስ ቅድመ ዓለም ወልድን ከወለደ ከአብ ቅድመ ዓለም ስለ ሠረፀ ሠራፂ ይባላል ። ይህም ሠራፂ የተሰኘው ስሙ ከሦስቱ አስማተ አካላት አንዱ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ከሦስቱ አስማተ ግብር አንዱ ነው ። ሠራፂ የሚለው ስሙም ስመ አካል ስመ ኩነት ያይደለ ስመ ግብር ነው ። የመንፈስ ቅዱስ ስመ ግብር ሠራፂ ነው ። የወልድ ተወላዲ የአብ ወላዲ አሥራፂ ስመ ግብር እንደ ሆነ ሁሉ ።
መንፈስ ቅዱስ የሚሠርፀው ከአብ ብቻ ነው ። ይህንንም እውነት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይገልጸዋል ‹‹ወሶበ መጽአ ጳራቅሰጦስ ዘአነ እፌኑ ለክሙ እም ኀበ አብ መንፈሰ ጽድቅ ዘይወጽእ እም ኀበ አብ ውእቱ ሰማዕትየ››
‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ ከአብ የሠረፀ (የወጣ) የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል›› ብሏል ። ዮሐ 15 ፥ 26 ።
በዚህ መለኮታዊ ቃል መሠረት 150 ሊቃውንትና መሰሎቻቸውም ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረፀ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት››
‹‹ከአብ በሠረፀ ጌታ ማሕየዊ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ፣ ከአብና ከወልድ ጋር እንስገድለት እናመስግነውም ፥ በነቢያት አድሮ የተናገረ እርሱ ነው ›› በማለት አቋማቸውን ግልጸዋል ። (ጸሎተ ሃይማኖት ዘኒቅያ) ።
ኤጲፋንዮስ ኤጲስ ቆጶስ ዘቆጵሮስ ደግሞ ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ነባቢ በውስተ ሕግ ወሰባኪ በነቢያት ዘወረደ በዮርዳኖስ ወተናገረ በሐዋርት ወኃደረ በቅዱሳን ወነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ህላዌ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ጰራቅሊጦስ ዘኢተፈጥረ ዘሠረፀ እም አብ ወነሥአ እም ወልድ›› ፡-
ሕግን በሠራ ፥ በነቢያት አድሮ ባስተማረ ፥ በዮርዳኖስ በወረደ ፥ በሐዋርያት አድሮ ባስተማረ ፥ በሊቃውንትም ባደረ ፥ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ። ባሕርየ መንፈስ ቅዱስ ያልተፈጠረ ፥ ከአብ የተገኘ (የሠርፀ) ፥ ቃልነትን ከወልድ ገንዘብ ያደረገ ፥ ፍጹም አካላዊ እንደሆነ በእርሱ እናምናለን» ብሏል ።
አጽናኝ ነው፤
መንፈስ ቅዱስ እረኛቸውን ላጡት በጎች ሰብሳቢ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተለይቶ መቆየት ለማይቻላት ቤተ ክርስቲያን አበረታች ፣ ሞት ፥ ሕማም ፥ ኃዘን ፥ ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ ላጠቃቸው ደቂቅ አዳም አጽናኝ በመሆኑ ፣ ጰራቅሊጦስ ይባላል ። አማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችንም ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል›› ብሏል ። ዮሐ 14 ፥ 16 ። እንዲሁም ‹‹ ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል ›› ብሏል ። ዮሐ 15 ፥ 26 ።
በተጨማሪ ዮሐ 16 ፥ 5-15 ይመልከቱ ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለምን ወረደ ?
ኃይልን ለመስጠት
ድኩማነ ኃይል ደቂቀ አዳም ይህን ዓለም በወንጌል ለመለወጥ ከአርያም ኃይል ያስፈልጋቸው ስለነበር ኃይልን ሊያለብሣቸው ነው የወረደው ‹‹እነሆም ፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ ፤ እናተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› እንዳለ መድኃኒታችን ። ሉቃ 24 ፥ 49 ። የሐዋ 1 ፥ 8
ሐሰተኛውን ዓለም ለመውቀስ፣
‹‹እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ፥ ስለ ጽድቅም ፥ ስለ ፍርድም ፥ ዓለምን ይወቅሳል ፤ ስለ ኃጢአት ፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው ፤ ስለ ጽድቅም ፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው ፤ ስለ ፍርድም ፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው›› እንዳለ ጌታ በወንጌለ መንግሥቱ ። ዮሐ 16 ፥ 8-12 ።
አዎን በእውነተኛው ጌታ አለማመን ፣ ድል ስለ ተነሣው ጠላት ውድቀት አለማወቅ ፣ በኢየሱስ ክርስቶ ወደ ቀደመ ክብር መመለስን አለማመን በደል ስለ ሆነ ይህንኑ ግልጽ አድርጎ ለመውቀስ ነው የመጣው ።
ወደ እውነት ሰዎችን ለማድረስ (ለመምራት)፤
‹‹ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እጂ ከራሱ አይነግርምና የሚመጣውንም ይነግራችኋል›› ይለናል ጌታ ። ዮሐ 16 ፥ 13 ። ዘማሪው ቅዱስ ዳዊትም «ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ» ይላል ። መዝ 142 ፥ 10 ።
ኃጢአተኞችንም ወደ ንስሐ ይመራል ። መዝ 14 ፥8 ።በክርክር ጊዜም እውነቱን ይገልጻል ። ማቴ 10 ፥ 20-23 ።መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን መርቶ ያደረሰበት እውነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ዮሐ 14 ፥ 6።1ቆሮ12፥3 ።
ለማጽናናት ወረደ፡
ዓለም ኃዘንተኛ ስለ ሆነ ሊያጽናና ሐዋርያትም ከኢየሱስ ተለይተው መኖር ስለማይችሉ ስለ ወንጌል የሚገጥማቸው ፈተናም ብዙ ስለ ሆነ ለማጽናናት መጣ ። ዮሐ 14 ፥ 16 ። ዮሐ 15 ፥ 26 ። ዮሐ 16፥ 5-16 ።
አልቃሻውን ዓለም ሊያጽናና ለመጣው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱ ክብር ፥ ምስጋና ፥ ውዳሴ ፥ ቅዳሴ ፥ አኮቴት ይሁን ።
ስለ ወልድ ለመመስከር
ዓለም ወልድን ስላላወቀው ስለ ወልደ እግዚአብሔር በሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን አድሮ ለመመስከር ተገለጠ ። ዮሐ 15 ፥ 27 ። 1ቆሮ 12 ፥ 3 ።
መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለማችን በምን አምሳል ወረደ
በዓውሎ ነፋስ አምሳል ወረደ
‹‹ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው›› ተብሎ እንደ ተነገረ መንፈስ ቅዱ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የተገለጠው በዓውሎ ነፋስ አምሳል ነበር ። ሐዋ 2 ፥ 2 ።
በብሉይ ኪዳንም እግዚአብሔር በዓውሎ ነፋስና በወጀብ ውስጥ መንገድ እንዳለው ተተንብዮ ነበር ፥ እዲህ ተብሎ ‹‹እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው ፥ በደለኛውንም ፡- ንጹሕ ነህ አይልም ፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው ፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው›› ። ናሆ 1 ፣ 3 ። እግዚአብሔር በነቢዩ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም በዓውሎ ነፋስ አምሳል ተገልጦአል ። ነፋስም የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ እንደ ሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሮአል ። ዮሐ 3 ፥ 8 ።
ከዚህ በተረፈ በነፋስ ለምን እንደ ተመሰለ በሌላ ክፍል እንመለከታለን ።
በአምሳለ እሳት ወረደ፤
መንፈስ ቅዱስ በንጹሐን ሐዋርያት ላይ የወረደው በዓውሎ ነፋስ አምሳል ብቻ አልነበረም ። እንደ ወርቅ ሊያጠራቸው በእሳት አምሳልም ነበር እንጂ ‹‹እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው›› የሚለው ቃል ግልጽ የሚያደርገው ይህንኑ ነው ። ሐዋ 2 ፥ 3 ። የሐዋ 2፥ 3 ።
እሳትም የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል ማቴ 3 ፥ 11 ።
ምንጭ ቃለ ጽድቅ- ያልታተመው መጽሐፍ በመምህር ልዑለቃል አካሉ
0 comments:
Post a Comment