አዕዋዳት የሚለው ዖደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ዞረ ማለት ነው። አዕዋዳት ደግሞ በብዙ እየዞረ የሚመጣ ማለት ነው። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጥንት ከሚለው እንደሚጀምር አይተናል። ጥንትነቱም ከፍጥረተ ዓለም፣ ከፍጥረተ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሳድሲቱ ዐምሲት፣ ዐምሲቱ ራብዒት፣ ራብዒቱ ሳልሲት፣ ሳልሲቲ ካልዒት፣ ካልዒቱ ኬክሮስ፣ ኬክሮሱ ሰዓታት፣ ሰዓታቱ ሳምንታት፣ ሳምንታቱ ወራት፣ ወራቱ ዓመታት፣ ዓመታቱ አዝማናት እየሆኑ ዛሬ ካለንበት ላይ ደርሰል። ሳድሲት፣ ዐምሲት፣ ራብኢት … ወዘተ ተብለው የተገለጹት በዘመናዊው አነጋገር ማይክሮ ሰከንድ፣ ሚኒ ሰከንስ፣ ሰከንድ … ወዘተ እንንደሚባሉት እጅግ በጣም ደቃቅ የሆኑ የጊዜ መለኪያዎች ናቸው። ጊዜያቸው ወይም ቆይታቸው ከዓይን ቅጽበት ያነሰ በመሆኑ አንጠቀምባቸውም፤ በዚህም ምክንያት የተለመዱ አይደሉም። ዓለምከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ በፀሐይ 5005 ዓመተ ዓለም ነው። ይኸውም
ሀ. ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው 5500 ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ ይባላል። “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ - አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅህ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው” /ቀሌምንጦስ/ እንዳለው አምስት ቀን ተኩል የተባለው ይህ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ማለት ነው። ይህ ሲተነተን ፦
ከአዳም እስከ ኖህ ያለው ዘመን 2250
ከኖህ እስከ ሙሴ 1588
ከሙሴ እስከ ሰሎሞን 599
ከሰሎሞን እስከ ልደተ ክርስቶስ 1063 ድምር 5500 ይሆናል።
ለ. ከልደተ ክርስቶስ በኋላ ያለው ዘመን ዓመተ ምህረት ፣ ዓመተ ሥጋዌ ወይም ሐዲስ ኪዳን ይባላል። ለምን ዓመተ ምህረት ተባለ? ቢሉ “በዕለት ኅሪት ሰማዕኩከ ወበዕለተ አድኅኖት ረዳዕኩከ - እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለው፣ በመድሃኒተም ቀን ረድቼሃለው” ትን. ኢሳ፤ 49፣8 እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “ወናሁ ይዕዜ እለተ ኅሪት ወናሁ ዮም እለተ አድኅኖት - በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳን ቀን ረዳሁህ” 2ኛ . ቆሮ 6፣2 በሚለው መጽሐፋዊ ቃል ላይ በመመርኮዝ ነው። ከላይ እንደተመለከትነው አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም አድንሃለው ያለው አምላክ የተናገረውን የማያብል ነውና ቃል ከገባለት ቀን ሳይጨምር ሳይቀንስ መጥቶ አድኖናል። የአዳምን መርገም አስወግዶ በድኅነት፣ ባርነቱን አስወግዶ በነጻነት፣ ቁራኝነቱን አጥፍቶ በልጅነት ተክቶለታል። ለዚህም ይህ ዘመን ዓመተ ምህረት፣ ዓመተ ሥጋዌ ይባላል።
የዘመነ ብሉይ እና የዘመነ ሐዲስ ድምር በጠቅላላው ዓመተ ዓለም ይባላል። ይህም 5500 ዓመተ ፍዳ ሲደመር 2005 ዓመተ ምህረት 7505 ዓመተ ዓለም ይሆንል። እንግዲህ አዕዋዳት የሚባሉት ይህንን ዓመተ ዓለምን የምንሰፍርባቸው ወይም የምንለካባቸው ናቸው። እነዚህም በቁጥር ሰባት ሲሆኑ እነሱም፦
1ኛ. ዓውደ ዕለት፦ ከሰኞ እስከ እሑድ ያሉ ቀናት ሲሆኑ እነዚህ ቀናት በየሳምንቱ ተመላልሰው ወይም እየዞሩ የሚመጡ ናቸው። እነዚህ ሳምንታት እየተመላለሱ ወራትን ይፈጥራሉ።
2ኛ. ዓውደ ወርኅ፦ አንድ ወር የሚባለው በፀሐይ ሙሉ ሰላሳ ቀን ሲሆን በጨረቃ አንድ ጊዜ /አንድ ወር/ ሃያ ዘጠኝ ቀን አንድ ጊዜ /በሌላኛው ወር/ ሰላሳ ቀን ይሆናል። ይህ በሰላሳ ቀን በየወሩ እየተመላለሰ ዓውደ ዓመትን ይሰራል።
3ኛ. ዓውደ ዓመት፦ በፀሐይ 365 ቀን ከአስራ አምስት ኬክሮስ /12 × 30 = 360 እና አምስት ጳጉሜን/ ሲሆን በጨረቃ 354 ቀን ከሃያ ሁለት ኬክሮስ ነው። ከላይ አውደ ወርኅ በጨረቃ አንድ ጊዜ ሃያ ዘጠኝ አንድ ጊዜ ሰላሳ ቀናት ብለናል። ይኽም ማለት ስድስት ወራት ሃያ ዘጠኝ፣ ስድስት ወራት ሰላሳ ቀናት ይሆናል። /6 × 29 = 174 ፤ 6 ×30 = 180 ሁለቱ ሲደመሩ 174 + 180 = 354 ቀናት ይሆናል።
4ኛ. ዓውደ አበቅቴ /ንዑስ ቀመር/፦አስራ ዘጠኝ ሲሆን በየአስራ ዘጠኝ ዓመት ዞሮ የሚመጣ ነው። ምክንያቱም ፀሐይና ጨረቃ ተራክቦ የሚያደርጉበት ጊዜ ነው። ፀሐይና ጨረቃ ሁለቱም በዕለተ ረቡዕ በአንድ ኆኅት /መስኮት/ ውስጥ የተፈጠሩ ሲሆን ከዛን ጊዜ ጀምሮ ዑደት ያደርጋሉ።፡ከላይ እንዳየነው በየዓመቱ ፀሐይ ሙሉ 365 ቀናት ስትዞር ጨረቃ ግን 354 ቀናት ብቻ ትዞራለች በመካከላቸው ያለው ልዩነት 11 ቀን ሲሆን ይህ ጥንተ አበቅቴ ይባላል። ሁለቱ በየዓመቱ ተለያይተው ሲዞሩ ቆይተው በአስራ ዘጠኝ ዓመት አንድ ጊዜ በተፈጠሩበት ኆኅት /መስኮት/ ይገናኛሉ፤ ይኽም ዓውደ አበቅቴ ይባላል።
5ኛ. ዓውደ ፀሐይ፦ 28 ዓመት ሲሆን በየሃያ ስምንት ዓመቱ ተመላልሶ /ዞሮ/ የሚመጣ ነው። ምክንያቱ ፀሐይ የተፈጠረችው በዕለተ ረቡዕ ነው። በየሃያ ስምንት ዓመቱ ዕለቱ እና ወንጌላዊው ይገናኙበታል። ዕለቱ ፀሐይ የተፈጠረችበት ቀን ረቡዕ፤ ወንጌላዊው ደግሞ የወንጌላውያን መጀመሪያ ቅዱስ ማቴዎስ የሚገናኙበት ነው። ሊቃውንቱ ረቡዕ ማቴዎስ ይሉታል።
6ኛ. ዓውደ ማኅተም /ማዕከላዊ ቀመር/ 76 ዓመት ነው። ሰባ ስድስት ዓመት የሆነው በ76 ዓመት አንድ ጊዜ አበቅቴው እና ወንጌላዊው ይገናኙበታል። ማኅተም ማለት መፈጸሚያ፣ መደምደሚያ ወይም መጨረሻ ማለት ነው። ለምን መጨረሻ /ማኅተም/ ተባለ ? ቢሉ የአበቅቴ እና የወንጌላውያን መጨረሻ የሚገናኙበት ስለሆነ ነው። በሰባ ስድስት ዓመት አንዴ የአበቅቴ ፍጻሜ 18 እና የወንጌላውያን ፍጻሜ ዮሐንስ ይገናኛሉ። “ጥንቱሰ ለቀመር ዕለተ ሰሉስ ወወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰሉስ ወወንጌላዊሁ ዮሐንስ - የቀመር /የቁጥር/ መጀመሪያ ማክሰኞ፣ የወንጌላውያን መጀመሪያ ማቴዎስ ሲሆን የቀመር መጨረሻ ሰኞ የወንጌላውያን ፍጻሜ ዮሐንስ ነው” እንዲል። አበቅቴ አስራ ስምንት የሚሆነው በየአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ሲሆን 18 በሆነ በዓመቱ አበቅቴው ዜሮ ነው የሚሆነው። /ወደፊት ስለ አበቅቴ በዝርዝር እንመለስበታለን/ በየአስራ ዘጠኝ ዓመቱ 18 ቢሆንም ግን ከወንጌላዊው ጋር ማለትም ወንጌላዊው ዮሐንስ ከሚሆንበት ዓመት ጋር የሚገናኙት ግን በሰባ ስድስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ዓውደ ማኅተም ሰባ ስድስት የሆነው።
7ኛ. ዓውደ ዐቢይ ቀመር /ዐቢይ ቀመር/፦ 532 ዓመት ነው። በዚህን ጊዜ ሶስት ነገሮች በጋራ ይገናኛሉ። እነዚህም ዕለት፣ አበቅቴ እና ወንጌላዊ ናቸው። እለቱ ሰኑይ /ሰኞ/ አበቅቴውና ወንጌላዊው ከላይ እንዳየው 18 አበቅቴ እና ወንጌላዊው ዮሐንስ ይሆናሉ። 18 አበቅቴ ለአበቅቴ ፍጻሜ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ለወንጌላውያን ፍጻሜ ነው ብለናል። በተጨማሪ እዚህ ጋር ሶስተኛ ሆኖ ለዐቢይ ቀመር መገኛ የሆነው ዕለት ነው። ዕለቱም ሰኞ ነው። የቀመር መጀመሪያ ሰሉስ /ማክሰኞ/ መሆኑን ደጋግመን በተለያየ ቦታ ተመልክተናል። የቀመር መጃመሪያው ማክሰኞ ከሆነ ደግሞ ፍጻሜው ሰኞ ይሆናል ማለት ነው።
እነዚህ ሰባቱ አዕዋዳት ሲሆኑ አዕዋድም የተባሉት አንድ ጊዜ ተፈጽመው ወይም ታይተው የሚቀሩ ሳይሆን በሌላ ጊዜ ተመላልሰው የሚመጡ በመሆናቸው ነው። ከእነዚህ አዕዋዳት ውስጥ ለበዓላትን አጽዋማት በምናወጣበት ጊዜ በዋናነት የሚያስፈልጉን ሶስቱ ሲሆኑ እነዚህን በደንብ ልናውቃቸውና በቃላችን ልንይዛቸው ይገባል። በተቻለ አቅምም ከነምክንያታቸው እንድናውቃቸው ይመከራል። እነዚህም፦
· ዐቢይ ቀመር 532 ዓመት፤ ትልቁ መስፈሪያ ሲሆን ከዚህ በላይ ስለሌለ ዐቢይ ወይም ትልቁ ተብሏል።
· ማዕከላዊ ቀመር 76 ዓመት፤ መካከለኛ መስፈሪያ ሲሆን በትልቁ መስፈሪያና በትንሹ መስፈሪያ መካካል ስለሆነ ማዕከላዊ ቀመር ተብሏል።
· ንዑስ ቀመር 19 ዓመት ናቸው። ንዑስ ማለት ትንሽ ማለት ሲሆን ከሌሎቹ ትንሹ በመሆኑ ንዑስ ቀመር ተብሏል።
0 comments:
Post a Comment