በኩረ ትንሳኤ ክርስቶስ
“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን“ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሠሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም
የዕለቱ ምስባክ
ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ኃያል ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን ወቀተለ ፀሮ በድኀሬሁ
እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ
የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያል
ሰው ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፡፡
ትርጉም፦
እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ
የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኀያል
ሰውጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፡፡
ትንሳኤ ክርስቶስ
ትንሳኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት አነሣሥ ማለት ነው ።እስራኤል ዘስጋ ያከብሩት የነበረው በዓለ ፋሲካ ከባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር ።
የሐዲስ ኪዳን በዓለ ትንሣኤ ግን እሥራኤል ዘነፍስ ወደ ከኃጢአት ጽድቅ የተመለስንበት ከሐሳር ወደ ክብር ከአሮጌው ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነጻነትበዓል ነው ።ፋሲካ በዐረብኛ ፓስኻ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ማዕዶት መሸጋገሪያ ማለትነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በቀደምት ነቢያት የተነገሩና የተጻፉ አንቀጾች ብዙ ናቸው፡፡ የሞቱና የትንሣኤ ምሥጢር በቅዱሳን መጻሕፍት ሰፊ ቦታ ያለው ነው፡፡ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚነገረው ሞትና ትንሣኤ ከቅርቡ /ከመስቀሉ አካባቢ/ በመነሣት እሱ ራሱ መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ቊርባንን በሠራበት ምሽት የሞቱንና ትንሣኤውን ነገር አንሥቶ ለደቀ መዛሙርቱ በሰፊው ገልጿል፡፡ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛለችሁ መጽሐፍ እረኛው ይመታል የመንጋው በጎች ይበተናሉ ያለው ይፈጸማል” ብሎ ነግሮአቸዋል፡፡ ከዚህም ቀደም ብሎ በጉባኤው ይሰበሰብ ለነበረው ሕዝብ ዮናስ በከርሠ አንበሪ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት እንደኖረ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ያድራል፡፡ ነገር ግን ወደገሊላ እቀድማችኋለሁ እያለ ይነግራቸው፥ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ማቴ ፲፪፥፵፣ ፳፯፥፴፩
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሱ በተጻፈው መሠረት የመስቀልን ፀዋትወ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ሞቶ፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሙታንን በሞቱ ሕያዋን ያደርጋቸው ዘንድ ሞተ፡፡ በዕለተ ዓርብ የፈጠረውን አዳም በፈጸመው በደል ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ነፃ ይሆን ዘንድ፥ በባሕርዩ ሞት የሌለበት አምላክ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ዋለ፡፡ ወዳጆቹ የአርማትያሱ ዮሴፍና፥ አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ የሄደው ኒቆዲሞስ በመስቀል ላይ የዋለውን ሥጋውን አውርደው፥ ለመቅበር፤ ከገዥው ከጲላጦስ ለምነው እንዲቀብሩ ተፈቅደላቸው፡፡ ከምሽትም ከመስቀሉ አወረዱት እንደቤተ አይሁድ የአቀባበር ሥርዓትና ልማድ የደቀቀና መዓዛው የጣፈጠ ሽቱ አዘጋጅተው፥ ከጥሩ ሐር በተሠራ በፍታ ገንዘው ዮሴፍ ለራሱ አስወቅሮ ባሳነፀው አዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ታላቅ ድንጋይም አገላብጠው ገጠሙት ማቴ ፳፯፥፶፯‐፶፰፣ ዮሐ፲፱፥፴፰‐፵፪ ይህ ሁሉ ለአይሁድ ሊቃናትና ሕዝብ ደስ የሚያሰኝ አልበረም፡፡ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደረገው ጥንቃቄና የሚሰጠው ክብር ሁሉ፥ በነሱ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡
“ያ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሏልና ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት ሰርቀው፥ ወስደው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብለው ሕዝቡን እንዳያስቱ መቃብሩ ይጠበቅ” በማለት ወስነው ነበር፡፡ በእያንዳንዱ አራት አባል የሚገኝበት በሦስት ፈረቃ የሚጠብቅ የጭፍራ ቡድን ተመድቦ መቃብሩን በንቃትና በጥንቃቄ እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣኖችም ጭፍራው ባለበት መቃብሩን አስቆልፈው በየቀለበታቸው (ማኅተማቸው) አትመውት ነበር፡፡ ማቴ ፳፯፥፷፪-፷፮
ይህ ሁሉ በሚፈጸምበት ዕለትና ጊዜ እነማርያም መግደላዊት፣ ማርያም ባወፍልያና እና ሰሎሜ ከእግረ መስቀሉ ሳይለዩ ከመቃብሩ ፊት ለፊት ቆመው በኀዘን፣ በተሰበረ መንፈስ የነገሩን ፍጻሜ የሚመለከቱ የዓይን ምስክሮች ነበሩ፡፡ ማቴ ፳፯፥፷፩ ይሁን እንጂ ሰውን ለመዳን በፈቃዱ ባደረገው የቸርነት ሥራ፥ በሥጋ ቢሞትም በባሕርዩ ሞት የሌለበትን ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው ሊያስቀሩት የማይቻላቸው በመሆኑ፤ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን ደምስሶ፥ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሌሊተ እሑድ ከሞት ተነሥቷል፡፡ በመቃብሩ ላይ ተገጥሞ የነበረው ታላቅ ድንጋይ ተገለባብጦ የተጠቀለለበት የከፈን ጨርቅ በአፈ መቃብሩ ተቀምጦ ተገኝቷል፡፡ የአይሁድ ጎመድ ሁሉ አልነበረም፡፡ ለጥበቃ ተመርጠው ልዩ መመሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው የነበሩ ጭፍሮችም ራሳቸውን እንኳ መጠበቅ ተስኗአቸው በያሉበት ወድቀው እንደ በድን ሆነው ነበር፡፡ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ያነጉት ቅዱሳት አንስት ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ለማየት ቀዳሚ ዕድል ነበራቸው፡፡ አስቀድማ ለማየት የበቃችው ማርያም መግደላዊት መሆኗን ቅዱስ ወንጌል አስቀምጦታል፡፡ ከሷ በማስከተል፥ ሁሉም ሴቶች አይተዋል፡፡
ጌታችን በተነሣ ጊዜ፥ መልአኩ እንደ ፀሐይ በሚያበራ ልብስ እንደ በረዶ በነጣ ግርማ ርእየቱ በሚያሰፈራ ሁኔታ ተገልጦ ነበር፡፡ ሴቶቹንም “አይዞአችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ ዐውቃለሁ፤ እሱ ከዚህ የለም እንሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል፡፡ ነገር ግን ኑ የተቀበረበትን ቦታ እዩ ካያችሁም በኋላ ፈጥናችሁ ሄዳችሁ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው በገሊላ ይቀድማች ኋል (መታየትን ይጀምርላችኋል) በገሊላ ታዩታላችሁ”ብሎአቸው፥ ወደ መቃብሩ እየመራ ወሰዳቸው፡፡ ሴቶችም ፍርሃትና ድንጋጤ በተቀላቀለበት የደስታ መንፈስ ተውጠው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ ፍርሃት የእግዚአብሔርን መልአክ ማየታቸው፤ ደስታው ደግሞ፥ ትንሣኤውን መስማታቸው ነው፡፡ በደስታ ተሞልተው ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረው፥ እየተቻኮሉ ሲሄዱ ጌታችንን በመንገድ ተገለጠላቸው፡፡
“እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ ቀርበውም ሰገዱለት፤ እሱም አይዞአችሁ አትፍሩ፤ ሂዱ ለወንድሞቻችሁ ገሊላ ይሂዱ ዘንድ ንገሩአቸው በዚያ ያዩኛል” አላቸው፡፡ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያትም ዜናውን ሰምተው ወደተባሉበት ቦታ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ በዚያም ጌታችንን ከሙታን ተነሥቶ አዩት፤ ሰገዱለትም፡፡ ማቴ ፳፰፣ ማር ፲፮፡፩‐፲፪፣ ሉቃ ፳፥፲፪ ለፍቅሩ ይሳሱ፥ ይናደዱ የነበሩ ጴጥሮስና ዮሐንሰም በጊዜው ወደ መቃብሩ ሄደው መነሣቱን አረጋገጡ፡፡ ዮሐ፳፥፩‐፲፩፣ ፲፰
የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኲር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ፥ መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ፥ ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፥ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኝበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ ፋሲካ ደስታ ነው እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለውታል፡፡ የእርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነው ከሞት ከመነሣት ከመቃብር ጨለማ ከመውጣት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከሲኦል እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምን ደስታ ሊኖር ይችላል?
የክርስቶስ ትንሣኤ እግዚአብሔር እኛን ምን ያህል እንደ ወደደን የምናስተውልበት፣ የፍቅሩን ጥልቀት፤ የቸርነቱን ስፋት የምናደንቅበት፤ የነፍሳችን የዕረፍት ቀን ነው፡፡ በሰው ዘንድ በቃል ሲነገር በተግባር ሲፈጸም የሚታየው ፍቅር ዘመድ ወዳጅ የሚለይበት ሰው ከሰው የሚዳላበት፤ ባለ ካባ ከባለ ካባ፣ ባለዳባ ከበለዳባ የሚበልጥበት፤ የሚወደውን የሚወዱበት፤ የሚጠላውን የሚጠሉበት ነው፡፡ ለሚጠሉት ይቅርና ለሚወዱት ተላልፎ የሚሞቱበት ፍጹም ፍቅር በዓለማችን አይታይም፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን የወደደበት ሕይወቱን እስከመስጠት ደርሶ ቤዛ የሆነበትን ምሥጢር የሰው ሕሊና መርምሮ ሊደርስበት የሚችል አይደለም፡፡ ተነጻጻሪ ተወዳዳሪ አቻ ምስያ የሌለው ልዩ ነው፡፡ ከቀደምት አበው እነ አብርሃም ልጆቻቸውን በቁርጥ ሕሊና ለመሥዋዕት አቅርበዋል፡፡ እነ ሙሴ እነ ዳዊት ይመሩት ይጠብቁት ለነበረው ሕዝብ ተላልፈን እንሙት እንቀጣ የሕዝቡን ቅጣት እንቀበል ብለው እንደነበረ ተጽፎአል፡፡ ግን በቅርብ ለነበረ፣እንዲያስተዳድሩ ለተሾሙለት ለተወሰነ ሕዝብና ለወገናቸው ብቻ ነበር፡፡ ሁሉን የሚያጠቃልል ሁሉን የሚያድን አልነበረም፡፡ መድኃኒታችንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስግን በመስቀል ላይ መከራ ተቀብሎ የሞተው፥ ለመላው የሰው ዘር ለአዳም ልጆች ሁሉ ነው፡፡ ቤተሰብና ዘመድ ወዳጅና ጠላት ወንዝና አካባቢ የሚለው አልነበረም፡፡ ከሰው አስተሳሰብ ሚዛንና ግምት የራቀ የጠለቀ ነው፡፡ የወደደን መከራ የተቀበለው እኛ ስለወደድነው አልነበረም፡፡ እሱ ስለ ወደደን ብቻ ነው፡፡ ስንኳንስ ቀድሞ ዛሬም ያደረገልንንና ያደለንን አስበን፥ ፍቅሩን ተገንዝበን፥ ለሰው በጎ ማድረግ፤ በፍቅሩ መመላለስ እጅግ ያዳግተናል፡፡ ከሁሉም የሚረቀውና የሚደንቀው ያጠፋን የበደልን፣ በጥፋታችን ሞትን በራሳችን ላይ ያመጣን እኛ ስንሆን፥ እሱ ስለኛ በደል ተላልፎ በእኛ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ተቀብሎ መሞቱ ይደነቃል፡፡ ለዚህም አንክሮ ይገባል፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ርእዩ መጠነ ዘአፍቀረነ እግዚአብ ሔር … ወሶበ እንዘ ፀሩ ንሕነ ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ እግዚአ ብሔር ምን ያህል እንደወደደን አስተውሉ ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር አለን” ብሎ እንዳስተማረው ስንኳን ተላልፎ እስከመሞት የሚያደርስ ፍቅርና ከፍርድ የሚያድን ምንም መልካም ሥራ ሳይኖረን፤ በሱ ፍቅር የተደረገልንን ቸርነት የምናስብበት የነፃነት የምስጋና ዕለት ነው፡፡ ሮሜ ፭፥፮‐፲በልጁ ሞት ስለካሰልን ይቅርታን አገኝን፤ በአንድ አዳም በደል ምክንያት ኃጢኣት ወደ ዓለም እንደ መጣች፤ በዚችም ኃጢኣት ምክንያት፥ በሰው ሁሉ ሞት እንደተፈረደበት፤ ሰውን ሁሉ በደለኛ፣ ኃጢአተኛ፣ አሰኝቸው፡፡ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣ ሞት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበሩትን የበደሉትንና ያልበደሉትን ሁሉ ገዛቸው፡፡ ታላቁ ሙሴ እንኳን ሌላውን ሲያድን ራሳቸውንም ከሞት ማዳን ስላልተቻላቸው ለሞት ተገዝተዋል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋው ስጦታ በኃጢአታችን ልክ የተደረገብን አይደለም፡፡ ራሱን ቤዛ አድርጎ ካሰልን፤ ከዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ በጥምቀት፣ በሃብት፣ በልጅነት ለሰው ሁሉ ሕይወት በዛለት፡፡ ሮሜ፭፥፲፮‐፲፰ የተነሣውን ክርስቶስን ሐዋርያት አይተውታል ገጽ በገጽ ዓይን በዓይን ፊት ለፊት ተያይተዋል፡፡ ሰግደውለታል፤ አመስግነውታል፤ ደስታቸው ፍጹም ሆኖላቸዋል፡፡ “… እናንተ አሁን ታዝናላችሁ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” ያለው የተፈጽሞላቸዋል፡፡ ዮሐ ፲፮፥፳፪ ለትምህርታቸው መሠረት ለስብከታቸው መነሻ የሆነው የጌታ ትንሣኤ ነው ምስክርነታቸውም የጸናው በትንሣኤ ነው፡፡ የተልእኳቸው ዋነኛ ዓላማ ሞቱንና ትንሣኤውን በመመስከር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሐዋ ፩፥፳፣ ሐዋ ፪፡፴፪፣ ሐዋ ፬፡፳
ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት እየተገለጠ ታይቶአል፡፡ እስከ ዓረገበት ዓረባኛው ቀን ድረስ ከሐዋርያት ብዙ አልተለየም፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በሐዋርያት ትምህርትና ሥርዓተ ጸሎት አካባቢ የነበሩ ሳይቀሩ ብዙዎች አይተውታል፡፡ ከሁሉም በቀዳሚነት ማርያም መግደላዊት ዮሐ፳፥፲፬‐፲፰ በመቃብሩ አካባቢ ነበሩ እነማርያም ባውፍልያ ማቴ ፳፰፥፱ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ ሁለት ደቀመዛሙርት ሉቃ ፳፬፥፲፫‐፴፩ ስምኦን ጴጥሮስ ሉቃ ፳፬፥፴፬፣፩ቆሮ ፲፭፥፭ አሥሩ ደቀመዛሙርት ዮሐ ፳፥፲፱ አሥራ አንዱ ሐዋርት ዮሐ፳፥፳፮ከዳግም ትንሣኤ/ከሁለተኛው ሰንበት/በኋላሰባቱ ደቀመዛሙርት ዮሐ፳፩፥፩‐፳፪ በገሊላ አሥራ አንዱ ሐዋርት ማቴ ፳፰፥፲፮ ማትያስ ባለበት አሥራ አንዱ ፩ቆሮ ፲፭፥፭ ሐዋ ፩፳፥፮ ከአምስት ጀምሮ (፭፻) የሚበዙ ወንድሞች ፩ቆሮ ፲፭፥፯ሐዋርያው ያዕቆብ ፩ቆሮ ፲፭፥፯-፲፪ ሁሉም ሐዋርያት በየጊዜውና በየቦታው አይተውታል፡፡ማር ፲፮፥፲፱፣ ሉቃ ፳፬፥፶፣ ሐዋ ፩፥፫‐፲፪፣ ቁ ፳፮ በመጨረሻም ለቅዱስ ጳውሎስ ተገልጦለታል፡፡ ፩ ቆሮ ፲፭፥፰
እንግዲህ ክርስቶስን የምናገኝው እሱን በማመን ጸንተን፤ በፍቅሩ መስለነው በፈለገነው መጠን ስለሆነ፤ በፍጹም ፍቅሩ በሰጠን የልጅነት ጸጋ የክብሩ ወራሾች ለመሆን እንድንበቃ የትንሣኤውን ብርሃን በየልባችን ይሳልብን! አሜን፡ ሰሞነ ሕማማትንና ሰሞነ ትንሣኤን እንድናከብር ቀደም ሲል በዲዲስቅልያ ኋላም በፍትሐ ነገሥት ታዝዟል፡፡ “እስመ ሰሙን ዐባይ ስሙነ ሕማማት እንተ ትተልዋሂ ሰሙነ ትንሣኤ ወዘይትፈቀድ ከመ ናእምር እስመ ዘሐመ ናሁ ትንሥአ” ሲል ይገኛል፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፱፤ የሰሙነ ትንሣኤ መጨረሻው ስምንተኛው ቀን ዳግም ትንሣኤ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣው አንድ ጊዜ ነው።
ዳግም ትንሣኤ ለምን ተባለ?
ዳግም ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት፡- በኣከባበር፥ በሥርዓት የመጀመሪውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡ የትንሣኤ ዕለት የሚባለው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤ በሙሉ በዚህ ቀን ይደገማል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁለት መጠሪያ ስሞች አሉት፡፡ እነዚህም “ፈጸምነ አግብኣተ ግብር” ይባላሉ፡፡ “ፈጸምነ” የተባለበትም፤ የሰሙነ ትንሣኤን በዓል አክብረን ፈጸምን ማለት ነው፡፡ “አግብዖተ ግብር” የተባለበትም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባ ወአቡየ ግብርዘወሀብከኒ ፈጸምኩ...እኔ ልሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ” ያለውን ከቅዳሴ በኋላ ሊቃውንት በዚህ ቀን ስለሚዘምሩት ነው፡፡ ዮሐንስ ፲፯፥፬
በተጨማሪም የሐዋርያው ቶማስ ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡ ዳግመኛ ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ሳሉ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ሳለ ደጁም ተዘግቶ ሳለ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በመካከላቸው ቁሞ እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ ሁለት ሰዓት አሳልፎ ስለመጣ “እምድኅረ ሰሙን” አለ እንጅ፥ በስምንተኛ ቀን ሲል ነው፡፡ በመጀመሪያው መገለጡ ያልተገኘው ሐዋርያው ቶማስ ትንሣኤውን አላመነም ነበርና፤ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ እጆቼንም እይ፤ እመን እንጅ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው፡፡ ቶማስም መለሰ “ጌታዬ አምላኬ ሆይ” አለ፡፡ መዳሰሱን ሲያይ “ጌታዬ”፤ ማቃጠሉን ሲያይ“አምላኬ” አለ፡፡ ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ ሕያዊት ሁና፤ (በሕይወት ትኖራለች) በሕንድ አገር ከታቦት ጋር በመንበሩ ላይ ያስቀምጧታል፡፡ በዓመት በዓመት በእመቤታችን በዓል በአሰተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ፥ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያረፋል፤ እንዲሁ በዓመቱ የሚሾመውን ተራምዳ ትይዘዋለች፤ እንዲህ እያለች ትኖራለች፡፡ ይህም የሚያስተምረን የጌታን ተአምራት፤ የሐዋርያውን ሥልጣንና ብቃት ነው፡፡ጌታም ቶማስ ሆይ! ብታየኝ አመንክን? ሳያዩኝ የሚያምኑብኝ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡ ዮሐ ፳፩፥፳፬-፳፱ ለብርሃነ ትንሣኤው ያደረሰን አምላካችን፥ እስከ ፍጻሜ ሕይወታችን በሃይማኖት የቀናን፤ በምግባር የጸናን ያድርገን! አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ
መልካም የትንሣኤ በዓል ለመላው ኦርቶዶስ ተዋህዶ
ReplyDelete