እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ
“ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃን ዓቢየ ወለአለሂ ይነብሩ ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ብርሃን ሠረቀ ሎሙ”
በድንቁርናና በቀቢጸ ተስፋ ለነበሩ ሰዎች ፍጹም እውቀት ተሰጣቸው፤ ሞት ባመጣው ምስል ሞትን በመምሰል ለነበሩ ሰዎች ክርስቶስ ተወለደላቸው በሞተ ሥጋ በሞተ ነፍስ ለነበሩ ልጅነት ተሰጣቸው፤ በኃጢአት ለነበሩ ስርየት፤ በክህደት ለነበሩ ሃይማኖት ተሰጣቸው ኢሳ.ም 9፣2 እግዚአብሔር የሁላችን አባት አዳምን በአርአያውና በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ባረከው ሁሉንም እንዲገዛ እንዲነዳ ሥልጣን ሰጠው፤ በረከቱን፣ ሥልጣኑንና ሲሳዩን ከሰጠው በኋላ ፈጣሪውን የሚያስታውስበት ትዕዛዝ አዘዘው፡፡ ትዕዛዙም የፈጣሪና የፍጡር መለያ፣ የአዛዥና የታዛዥ ገደብ፣ ሰው ለሕግ መገዛት እንደሚገባው ለማስረዳት የተደረገ እንጂ የስስት ወይም የንፍገት አልነበረም፡፡
ይህንን ደግሞ አዳምም ሆነ ሔዋን ያውቁታል፤ በምግብ እጦት እንዳይቸገሩ ግን በገነት ያሉትን አትክልት እንዲበሉ ከውኃውም እንዲጠጡ ፈቅዶላቸዋል፡፡ሰው ግን ከፍጥረት አክብሮ አልቆ ያነገሠውን እግዚአብሔርን አስቀይሞ በተሳሳተ ምክር ተመርቶ አትብላ የተባለውን ዕፀበለስን ስለበላ ከፈጣሪውም ትዕዛዝ ስለወጣ በዚህ ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡
ከኤዶም ገነት ተባረረ፣ ከአምላኩ ጋር ተጣላ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው አንድነት ግንኙነት ተቋረጠ “ወደ ወጣህበት ምድር እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ” ዘፍ 3፣19አለው ጥሮ ግሮ እንዲበላ የፈቀደለት የገነት ፍሬ ሳይሆን የተፈጠረባት ምድር ላይ እኛ የምንመገበውን ዕፅዋቱን፣ አዝዕርቱን፣ አትክልቱን፣ እንሰሳቱን ምግበ ሥጋ የሆነውን ሁሉ ነው፡፡እንደ መላእክት ማመስገን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገርን፣ ልጄ ወዳጄ መባልን፣ በቅድስና እያለ አዕምሮ ጠባይ ሳያድፍበት ሀብተ ጸጋ ተሰጥቶት እግዚአብሔርን በሌሊትም በቀንም እያመሰገነ በዚህም ምክንያት ፈጣሪ ጸጋውንና በረከቱን እያበዛለት እጅግ በጣም በደስታ በሐሴት ያለምንም ችግር ለመኖር የበቃው ክርስቶስ በልደቱ ሰው ሆኖ ከጎበኘው በኃላ ነው፡፡
ቀድሞ ግን ሕጉንና ትዕዛዙን በመተላለፍ መጨነቅ መውጣት መውረድ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ደርሶበት በመከራ ጨለማ ውስጥ ሲሰቃይ ይኖር ነበር፡፡ ፭ሺ፭ መቶ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ሰው ቢሯሯጥም ቢደክም እንኳ እግዚአብሔርና ሰው ስላልታረቁ ድካሙ በከንቱ ይመለስ ነበር፤ ምንም ትርፍ ጥቅም ሳያገኝ ባዶ እጁን በከንቱ ይመለስ ነበር፤ ሕያዊት ነፍስ ያለችው የሰው ልጅ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት አጋንንት ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል የሚያሰቃዩት አሳዛኝ ፍጡር ሆነ ፤ ይህም የሞት ቅጣት በእርሱ አቅም ቀላል አልነበረም በእርሱ ብቻም አልቀረም የልጅ ልጆቹም ይህን እዳ በውርስ ተካፈሉት፡፡ “አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ ልብ እንደሌላቸው እንሰሳት ሥጋዊ ባሕሪው አሸነፈው” መዝ 48፣20
በዘመነ ኦሪት እነ ኖኀ ፣ እነ አብርሃም፣ እነ ይስሐቅና ፣ እነ ያዕቆብ በዘመነ መሳፍንት እነ ሙሴ እነ አሮንና እነ ኢሳይያስ በዘመነ ነገሥት እነ ዳዊት እነ ሰሎሞንና ሳሙኤል በዘመነ ነቢያት እነ ኢሳይያስ ኤርምያስ የመሳሰሉት ብዙ ታላላቅ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ ተወልደው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አበውም ሆኑ ነገሥታቱም መሳፍንቱም ሆኑ ነቢያት እንኳን ሌላውን ሊያተር ራሳቸውንም ሊያድኑ እንዳልቻሉ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ጥበብ 3፣1 “የደጋግ ሰዎች ነፍስ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት የኃጢያተኞችም መከራ አላገኛቸውም” በማለት በሥልጣነ እግዚአብሔር እየተጠበቀ በሲኦል መቆየታቸውን ይገልጣል፡፡
“ሁላችንም እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል፡፡” ኢሳ 64፣6
እግዚአብሔር አምላካችንንን ያስደሰቱ አባቶቻችን የእውነተኛውን ብርሃን /ክርስቶስ/ ወደዚህ ዓለም መምጣት ይጠባበቁ ነበር፡፡ ያአስጨናቂው ከይሲ የዲያቢሎስ ራስ ተቀጥቅጦ ማየት ይፈልጉ ስለነበር ”አቤቱ እጅህን ላክና አድነን” መዝ 143፣7 “አቤቱ ሰማያትን ቀድደህ ብትወርድ ምነው በለው ጮሁ” ይህን ዓለም ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ማላቀቅ አልተቻላቸውም ነበር ከዚህም የተነሣ መላው የዓለም ሕዝብ ከዲያቢሎስ ቀንበር በታች ወድቆ ለ፭ሺ፭ ዘመናት በእግረ አጋንንት ሲረገጥ በበትረ ኃጢአት ሲቀጠቀጥ የግፍ አገዛዝ ሲገዛ ኖሯል፡፡ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር በመልክ የሚመስለውን በባሕርይ የሚተካከለውን ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፤ ብርሃን ወልድ በሚወለድበት ጊዜ በጨለማ፣ በክህደት፣ በጥርጥር፣ በአምልኮት፣ ጣኦት፣ በገቢረ ኃጢአት፣ በቀቢጸ ተስፋ/ተስፋ በመቁረጥ/ ለነበሩ ሰዎች ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣላቸው፡፡ አምልኮተ ጣኦትን የሚያጠፋ ክህደትን ጥርጥርን የሚያስወግድ ዲያቢሎስን የሚሽር ሞትን መቃብርን የሚደመስስ የሕዝብና የአሕዛብ ተስፋ መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጣ ያቺ ጨለማ ሆና የነበረች እስር ቤት አበራች፡፡
ይህ ታላቅ የምስራች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ለዓለም የተሰበከ ሰላም ደስታና ደኀነት ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ አጻጻፍ ሥዕላዊ ዓይነት ነበር ምክንያቱም ቀድሞ ሥራው ሠዓሊ ነበርና ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሲጽፍ “እነሆ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ መልአኩም እንዲህ አላቸው እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኃለሁ አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኃል ይህም ምልክት ይሆንላችኃልና ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ታገኛላችሁ፡፡”ሉቃ 2፣9-12 በማለት ስለልደተ ክርስቶስ ገልጿል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባውና ዓለምን እንደልብስ በመጠቅለያ እንዲጠቀለል ሁሉን የሚያሳልፍ የሚሳነው የሌለ ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ ኃያል አምላክ ሲሆን እናቱ ድንግል ማርያም እርሱን በምትወልድበት ወቅት በመጠቅለያ ጠቀለለችው፡፡
መድኀን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ እርቃናችንን ሆነን የጸጋ /የልጅነት/ ልብሳችን ተገፎ ነበርና እርሱ ጸጋውን ያለብሰን ዘንድ እርቃኑን ተወለደ ደግሞም በእናቱ አማካኝነት ጸጋውን መጎናጸፍ እንደምንችል አሳወቀን እርሱ ምስጋና ጌትነትን የተጎናጸፈ ባለጸጋ አምላክ ሲሆን እንደ ደኃ እርቃኑን ተወለደ 2ኛ ቆሮ 8፣9 “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ድኃ ሆነ” እኛን ባለጠጋ ያደርገን ዘንድ እመቤታችንንም ማረፊያ ስፍራ ብታጣ በከብቶች ግርግም አስተኛችው፡፡ ዛሬም ድንግል ማርያም ልጇንም ታቅፋ በቤተልሔም ትገኛለች ያቺ ግርግም የቤተክርስቲያን ምሶሌ ናት ፤ቤተክርስቲያንን ሰዎች ባለማወቅ ምንም የሌላት ባዶ ቤት መስላ ትታየቸዋለች ከዚህም የተነሳ ይንቋተል ይሁን እንጂ የተናቀች ስትመስል በውስጧ ግን እናትና ልጁ አብረው ይገኛሉ፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇንም በግርግም እንዳስተኛችው ዛሬም ቢሆን በችግር በእርዛት በረሀብ መጠለያ በማጣት የሚንከራተቱ እናትና ልጁን አምነው ያሉ ወገኖቻችን አሉ ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ወቅቱ የብርድ ወራት ሌሊት ነበር በዚያን ሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ ኖሎት/ጠበቆች/ እረኞች ነበሩ፡፡ እነዚህ እረኞች በፍፁም ትጋት ከብቶቻቸውን ከአውሬ ይጠብቁ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ በሃይማኖት በትጋት ላሉ ይቀርባቸዋል ሲቀርባቸውም የእግዚአብሔር ክብር ጌትነቱ በዙሪያቸው አበራ፡፡ ጊዜው ጨለማ ነበር ወዲያውኑ ብርሃን በራላቸውና ማየት ቻሉ በጎቻቸውንም የበለጠ አወቁ የበራላቸው ብርሃን ምድራዊናሰው ሰራሽ ስላልሆነ መለኮታዊ ብርሃን በመሆኑ ታላቅ ፍርሀት ፈሩ ክብር በማየታቸው ተደናገጡ በቤተልሔም የተወለደው መለኮታዊ ብርሃን የተጎናጸፈ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ቅዱሳን መላእክት የሚያመሰግኑት የሚገዙለትና የሚሰግዱለት እኛን ለማዳን ሲል ራሱን ቢያዋርድ አይተው ሩቅ ብእሲ/ፍጡር/ አድርገው እንዳይቆጥሩት ብርሃኑን ለጠበቆች ገለጸላቸው፡፡
መላእክት ደግሞ እኛን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ሥልጣን ስላላቸው ግርማቸውም አሰፈሪ ስለሆነ ኖሎት /እረኞች/ አይተው ፈሩ መልአኩም አይዟችሁ አትፍሩ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል የዓለም መድኃኒት የሚሆን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ከዳዊት ባሕርይ ተወልዷልና እናንተንም ሰውንም ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ነገር እነግራቸኃለሁና ብሎ አረጋግቶ ታላቅ የምሥራች ነገራቸው፡፡ ማንም ሊንቀው የማይችል በእግዚአብሔር የጌትነቱ ብርሃን ፊት መቆም የሚችለው መልአክም መልሶ እንዲህ አላቸው እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምሥራችን እነግራችኃለሁና አትፍሩ አላቸው ፍርሃትን ማራቅ ለመላእክት ልማዳቸው ነውና ለምሳሌ በትንቢተ ዳንኤል ም 10፡12 ቅዱስ ገብርኤል “ዳንኤል ሆይ አትፍራ” ብሎታል ስለዚህ መልአኩ ጠበቆችን /እረኞችን/ አትፍሩ አላቸው ቀድሞ በሥጋት በግብርናተ ዲያቢሎስ ሥር የሚገኙ የአዳም ልጆች ጨለማ የተባለ ቀቢጸ ተስፋ በላያቸው ነግሶ ዲያቢሎስም የሰው ልጆችን በማስፈራራት ይገዛ ነበርና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነፃ በመውጣታቸውን ይህንን ታላቅ ደስታ ሊያበስራቸው የተላከው መልአክ ታላቅ የምሥራችን ነገራቸው ይህም ደስታ ምድራዊ ደስታ ብቻ አይደለም ሰማያዊ ደስታም ጭምር ነው የሰው ልጆች ከተጫነባቸው የሞት ቀንበር ነጻ የሚሆኑበት ከደረሰባቸው መራራ ኀዘን የሚጽናኑበት ነውና የማያልፍ ደስታ ራሱ እግዚአብሔር ነው በዳዊት ከተማ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኃልና ብሎ መልአኩ አበሰራቸው መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ የሆነ እርሱ ነው ትንቢተ ሆሴዕ 13፣4 “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔ በቀር ሌላ መድኃኒት የለም” ብሎ በነቢያት የተናገረ አምላክ በከብቶች በረት ተወለደ፡፡
“ከሕሊናት ሁሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል ምድራዊት ሴት ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች እርሱም እናቱን ፈጠረ ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያስረዳ ዘንድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ አምላክ ሲሆን በሥጋ ተገለጠ ከፍጹም አምላክ የተገኘ ፍጹም አምላክ ሰው ሆኖ ከሰው ተወለደ ይህውም ከፍጹም አምላክ የተገኘ ፍጹም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ ነው እርሱም በሥጋ ያደረ ሥጋ አይደለም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ነው እንጂ” ሃይማኖተ አበው ኤፍሬም ሶሪያዊ ም 47፣ ክፍል 1 ይህንን ዜና ለመመልከት ስብአሰገል በኮከብ ተመርተው እጅ መንሻ ገጸበረከት ይዘው ድንግል ማርያምንና ልጇንም በበረት በከብቶች ግርግም አዩ፡፡
ይቺ የታደለች የቤተልሔም በረት የጽድቅ ፀሐይ ወጣባት የሰውና የመላእክት መዘመሪያ መቅደስ የምስራች መስሚያ ዓውደምህረት ሆነች፡፡ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም የዘለዓለም ብርሃኗ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጧ ተወልዷልና በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ በጨለማ ተውጦ ለነበረው ለሰው ልጅ የብርሃን ጮራዋን ፈነጠቀች መላእክትን ከሰማያት ሳበቻቸው ነገሥታትን ከሩቅ ምሥራቅ ጠራቻቸው እረኞችንም ወደ ብርሃኗ ጋበዘቻቸው፡፡
በቤተልሔም በረት ተጋብዘው የመጡ የሩቅ ምሥራቅ ነገሥታት ለሕፃኑ የባሕርይ /የአምልኮት/ ለእናቱ የፀጋ ስግደት ሰገዱና ሳጥናቸውን ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና፣ ከርቤ ገበሩለት /አቀረቡለት/ ወርቁን ማቅረባቸው የቀድሞ ወርቅ እናቀርብላቸው እንገብርላቸው የነበሩ ነገሥታት ኃላፊያን ናቸው አንተ ግን ለዘለዓለም የማታልፍ ንጉሥ ነህ ሲሉ ወርቅ ባሕርይ ነህ ሃማይማኖታትን ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዕጣን ማቅረባቸው ቀድሞ ዕጣንን የምናጥንላቸው ጣኦታት ኃላፊያን ናቸው፡፡ አንተ ግን ለዘለዓለም ካህን ነህ አምላክ ነህ፣ እንዲሁም ዕጣን መልካም መዓዛ አለው አንተም ምዑዝ ባሕርይ ሲሉ ገበሩለት፡፡
በመጨረሻም ከርቤ ገበሩለት ይህን ማቅረባቸው ከርቤ የተሰበረውን እንደሚጠግን የተለያየውን አንድ እንደሚያደርግ አንተም ከመላእክት ማኀበር ተለይቶ የነበረውን አዳምን ከመላእክት ጋር አስታርቀህ አንድ ታደርገዋለህ ዳግመኛም ተለያይተው የነበሩትን ሕዝብና አሕዛብ አንድ ታደርጋቸዋለህ ሲሉ አቅርበዋል፡፡ ሌላው ግን ከርቤ መራራ ነው አንተ ምንም አምላክ ብትሆን ስለሰው ልጆች ብለህ መራራ ሞትን ለማጥፋት ስለ ሰው ሞትን በስጋህ ትቀምሳለህ ሲሉ አቅርበዋል፡፡ በክርስቶስ ልደት ወቅት የተደሰቱና እጅ መንሻ የገበሩ ስብአሰገል ብቻ አልነበሩም በዚያች ግርግም /በረት/ የነበሩ ላሞ፣ በሬና አህያ ሲሆኑ እነርሱም ያላቸውን ሀብት ትንፋሻቸውን ገበሩ፡፡
ወልደ እግዚአብሔርም የእነርሱን ትንፋሽ አልናቀም ተቀበላቸው እንጂ ሰው የሚንቃት ጠረኗ ትንፋሿ የሚከረፋ የምታስጠይፍ አህያ እንኳ ጌታዋ በበረት ራሱን አዋርዶ ስለተወለደ ደስ ብሏት ጌታዋ እንዳይበርደው ያላትን ትንፋሽ ገበረች ፈጣሪዋም “የአንቺስ ትንፋሽ አያስፈልገኝም” ሳይላት ተቀበላት ይህ ምሳሌ ነው በረቱ የቤተክርስቲያን ከብቶቹ የምዕመናን የክርስቲያኖች ምሳሌ ሲሆኑ እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ እግዚአብሔር የሁሉንም ትንፋሽ ሳይንቅ እንደተቀበለ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች በትንፋሽ የተመሰለውን ጸሎታችንን ምስጋናችንን ያለንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ብናቀርብ እግዚአብሔር ሳይጸየፈን ሳይንቀን እንደሚቀበለን ሲያስረዳን ነው፡፡ በመሆኑም እነዚያ እንሰሳት ያላቸውን ለእግዚአብሔር ስጦታ አምኃ አድርገው እንዳቀረቡ እኛም ያለንን ማቅረብ አለበን ከእንሰሳት ማነስ የለብንም፡፡
በእግዚአብሔር ስም ተቸግረው ላሉ ምስኪናን ወገኖቻችን አምላካችን የሰጠንን የአቅማችንን ያህል ልንመጸውት ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሁሉንም ምጽዋት የሚቀበል ነውና፡፡
እንግዲህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከኀዘን ነጻ ሆነን ሰላምን አግኝተናል ስለዚህ ይህንን ታላቅ የምሥራች ተብሎ የተገለጸልንን በዓል ስናከብር ያገኘነውን እንደ ድመት ለብቻ ይዞ ማኩረፍ ሳይሆን ምንም የሌላቸው ከችግረኞች ነዳያን ጋር አብረን መመገብ ገንዘብ ማድረግ አለብን፡፡
ምንጭ ከምክሖን ለደናግል የፌስ ቡክ ገጽ የተወስደ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
0 comments:
Post a Comment