• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 17 November 2015

    ሴቲቱ ማን ናት?


    ሴቲቱ ማን ናት?

    “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች” (ራእይ 12፡1)

    ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ

    ታላቅ ምልክት የተባለችው ድንግል ማርያም ናት፡፤ በሰማይ መታየቷ ሰማይ፣ ከሁሉም በላይ ሆኖ ከፍ ብሎ እንዲታይ እመቤታችንም ልዕልት መሆኗን ያመለክታል፤ ከሴቶች ሁሉ የተለየች የመሆንዋ ምሥጢርም ይህ ነው (ሉቃ 1፡28)፡፡ ምልክቲቱ የተሰጠችው በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ሲያሳይ ይህም በትንቢት “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትጸንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለለች (ኢሳ 7፡14) የተባለው ለመፈጸሙ ማሳየቱን ነው፡፡

    ፀሐይ የተባለው እግዚአብሔር ነው (መዝ 26፡1፣ ዮሐ 8፡12)፡፡ ፀሐይ የብርሃን ምንጭ እንደሆነ ከእርስዋ የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የፍጥረት ሁሉና የመዳን ምንጭ እርሱ ብቻ ነው፤ እርስዋ ተጎናጽፋው ማለት ጌጧ ሆኖ፣ ልጇ ሆኖ “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፡28) እየተባለች፤ አብርታ ደምቃ ታየች፤ በመወለዱም በጨለማ የምንሄድ ሕዝብ ብርሃናችንን እርሱን አየን (ማቴ 4፡14-16፣ ሉቃ 1፡78፣ ዮሐ 1፡8፣ ዮሐ 9፡5፣ ራእይ 21፡23)፤ እርሱ ብርሃን ተብሎ እናቱን እመ ብርሃን (የብርሃን እናት)፣ አሰኝቷታል፡፡ መጎናጸፍዋ በብርሃን የተሞላች መሆንዋን ያመለክታል፤ ይህም “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል” (ሉቃ 1፡30) “ጸጋን የተሞላሽ” የተባለች ሌላ ከሰው ወገን ስለሌለ ፀሐይን ተጎናጽፋ ተባለች ይህም ክብርዋ ነው፡፡

    ጨረቃን ከእግሮችዋ በታች ያላት

    ፀሐይ የአዳኛችን የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ ጨረቃ በተፈጥሮ የራሱ ብርሃን የለውም፡፡ የዚህ ምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ አስቀድሞ በወንጌሉ የጻፈውን ስንመለከት “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም” (ዮሐ 1፡6-9) በማለት ከብርሃን የሚያንሰው ዮሐንስ መጥምቁ እንደሆነ የተናገረውን በድጋሚ በራእዩ አየው፡፡ ፀሐይ የራሱ ብርሃን እንዳለው፤ ጌታ የባህርይ ብርሃን ነው፡፡ ጨረቃ የራሱ ብርሃን እንደሌለው፣ ብርሃንን ከፀሐይ እንደሚቀበል፤ መጥምቁ ዮሐንስ የጸጋ (የስጦታ) ብርሃንን ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋ ይወስዳል፡፡ ጨረቃ ብርሃኑ እያነሰ እያነሰ እንደሚመጣ፤ የዮሐንስም የስብከት ጊዜ እያበቃ እየተፈጸመ፣ የጌታ ትምህርትና ብርሃን እየታወቀ እየጎላ እንደሄደ ራሱ ዮሐንስ መጥምቁ ተናግሯል፡፡ “ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል” (ዮሐ 1፡15) በሌላም ቦታ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” (ዮሐ 3፡30) በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ሴቲቱ ጨረቃን ከእግርዋ በታች አድርጓ መታየቷ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ከሌሎቹ ነቢያት ምንም ቢበልጥ ከእርስዋ ግን ያነሰ ለመሆኑ፤ በጽንሱ ጊዜ ድምጽዋን ሲሰማ ለምትበልጠው ለጌታ እናት በደስታ መዝለሉን ያሳውቀናል (ሉቃ 1፡44)፡፡

    በራስዋም ላይ የ12 ከዋክብት አክሊል የሆነላት

    እነዚህ 12ቱ ሐዋርያት ናቸው፡፤ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን፤ እነርሱ በከዋክብት ይመሰላሉ፤ ብርሃኑን የሰጣቸው ልጇ ነው፡፡ እርስዋ ፀሐይን ስትጎናጸፍ እነርሱ በብርሃን ክርስቶስ አምነው ያጌጡ ምስክሮቹ ናቸው፡፤ እርሱን ተወለደ ቤዛ ሆነ ብለው ሲመሰክሩ የእርስዋን ስም እያነሱ ከድንግል ሴት ተወለደ ብለው የመመስከራቸው ምሳሌ ነው (ገላ 4፡4)፡፡ እርስዋን ይዘው ወደ ጌታ ይጸልያሉ “እነዚህ ሁሉ ከኢየሱስ እናት ከማርያም … ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ 1፡13-14) በዮሐንስ ወንጌላዊ አማካኝነት ከመስቀል ስር ያገኙአት የአደራ እናታቸው ናትና (ዮሐ 19፡26-27)፡፡

    እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች (ራእይ 12፡2)

    የሔዋን ባህርይ ያላት ናት እንጂ፣ ኃይለ አርያማዊ (የሰማይ መላእክት ወገን) አይደለችም፣ ለማለት ሲያስቀምጥ፣ በሌሎች ሴቶች ልማድ ጭንቅ እንደአለባቸው ተናገረ እንጂ በእርስዋስ ጭንቅ የለባትም፤ ጭንቅ የሚሆንባት ቀጥሎ ያለው የበረሃ ስደት በነፍስዋ እንደሚያልፍ ዮሐንስ የተገለጸለትን መናገሩ ነው፡፡

    ያለ ጭንቅ እንደተወለደ የምናምንበት ምክንያት፤ ዋናው እግዚአብሔር የድንግል ማርያምን መብት ለመንካት ከሰማይ አልወረደም፤ ድንግል በድንልና መኖር ስትመኘው የነበረው ነው፡፡ ስለዚህም ነው “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” (ሉቃ 1፡34) እያለች የድንግልና ፍላጎትዋን የምትናገረው፤ እርስዋ በድንግልና ኖሯ በድንግልና ነው የወለደችው፡፡ እዚህ ላይ ከመጽነስዋ በፊት ሁሉም ድንግል መሆንዋን ያምናል፤ ነገር ግን ድንቅ ሠሪውን እግዚአብሔርን በመጠራጠር፣ እንዴት ሥጋ ሆኖ ሲወለድ ድንግልናዋ አልጠፋም? ብለው የሚጠይቁ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ልብ ወለድ ጥያቄአቸውን በጥያቄ እንመልስላቸዋለን፡፡

    ኢየሱስ ክርስቶስ ድንጋይ ሳይፈነቅል ከሙታን ተነሥቶ ወጥቶአል፡፡ መልአኩ ነው መጥቶ “ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ” “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም” ብሎ መነሣቱን ያሳያቸው፡፡ እንዴት ድንጋዩን ሳይገለብጥ ጌታ ወጣ? በተጨማሪም ሐዋርያት በራፋቸውን ዘግተው ሳለ እንዴት ሳይከፍት ገባ? (ማቴ 28፡1-5፤ ዮሐ 20፡19)

    መልሱ “የሚሳነው ነገር የለም” ከሆነ ከድንግል ማርያምም በድንግልና ለመጸነሥና ለመወለድ የሚሳነው ነገር ስለሌለ ተዘግቶ የሚኖር የእግዚአብሔር የ9ወር ከ5 ቀን መቅደስ ማሕጸንዋ ተዘግቶ እንደሚኖር የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም በድንግልና ነው የተወለደው ስለዚህ እርስዋ ያለ ጭንቅ ነው የወለደችው (ሕዝ 44፡1-2)፡፡

    የመጽሐፍት አካሄድ በሌሎች ልማድ ያለውን ለሌላ ሰጥተው ይጻፋል፡፡ የድንግል ማርያምም የብዙ ሴቶችን ልማድ ለእርስዋ ሰጥቶ መናገሩ ሴት መሆንዋን ለመግለጽ እንጂ ጭንቅስ የለባትም፡፡ ለምሳሌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰዎችን አጥምቆ ያውቃል? አያውቅም? “ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት” (ዮሐ 3፡26) ይላል፡፡ ያው ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል መልሶ ያጠምቃል ያሉት የሌሎችን ሥራ ለእርሱ ሰጥቶ መናገር መሆኑን “ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም” (ዮሐ 4፡2-3) ይላል፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ አካሄድ ብዙ ሴቶች በጭንቅ ይወልዳሉና፤ የሴቶችን ለድንግል ማርያም ሰጥቶ የናገር ልምድ ነው፡፡

    ድንግልም ያው ሴት ናት ሔዋናዊ ሥጋን የለበሰች፤ የሰው ወገን ነች ለማለት “እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች” አለ፡፡ በድንግል ማርያም የእርግማን ውጤት የለባትም በምድር ላይ እንደ እርስዋ የሆነ ሴት የለም፤ ተወዳዳሪ የሌላት ብርክት እንጂ ርግምት እንዳልሆነች “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃ 1፡28) ተብላለች፤ ይህን ያላት ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ ከእግዚአብሔር የተላከ የእግዚአብሔርን ቃል ነው የሚናገረው፤ ያው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በኤልሳቤጥ አድሮ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃስ 1፡42) የተባለችውን እናት እርግማን አለባት ለማለት ቁጭ ብድር ሲሉ ትንሽ ስቅጥጥ አይላቸውም? በትንቢት “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም” (መኃልይ 4፡7) የተባለችን እናት፤ እርግማን እንደሌለባት ያሳየናል፤ በዚህ “ምጥ” በሚለው የሴቶች ልማድ ሴት ናት ለማለት የተጠቀሰ ነው፡፡

    ዘንዶው በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን ሊበላ በፊትዋ ቆመ (ራእይ 12፡4)

    ዘንዶው እያለ የሚናገረው፣ በቀጥታ ዘንዶ አይደለም፤ ይህ በእግዚአብሔር መጽሐፍ አገላለጽ የተለመደ ነው፡፡ “እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” (ማቴ 23:33) በሚለው ውስጥ እናንተ እባቦች ያላቸው በተንኮል የሚታወቁትን ሰዎችን እንጂ የተፈጥሮ እባቦችን አይደለም፡፡ እንዲሁም በዚህ ቦታ ታላቅ ዘንዶ የተባለው ጌታ ሲወለድ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ነው፡፡ “ጌታ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ . . .ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ … ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው” (ማቴ 2፡1-8) ይህ አነጋገር ሊሰግድለት ሳይሆን በቅኔያዊ አነጋገር በእባባዊ ተንኮሉ ሕፃኑን ለመግደል ስለፈለገ በራእይ “ሕፃንዋን ሊበላ” በሚል ቃል ለቅዱስ ዮሐንስ ተገልጾለታል፡፡

    በፊትዋ መቆሙ የድንግል ማርያምን አንድ ልጅዋን ሊገድለው መወሰኑን ያሳያል፡፡ ይህም የንጉሠ ነገሥቱ የክርስቶስ መወለድ ያስቆጣው እንደሆነና በዚህም ውጤት “ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” ይህ እርምጃ ከሚገደሉት ሕፃናት መካከል አንዱ ጌታ ኢየሱስ ይሆናል የሚል ግምትን ያሳያል (ማቴ 2፡10)

    አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች (ራእይ 12፡5)

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም በተወደደ በጽኑዕ ሥልጣኑ መጠበቁን የሚያመለክት ሲሆን ይህም አስቀድሞ ከጽዮን ድንግል ማርያም ላይ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ላይ ተሹሞ እንደሚገዛ የተተነበየውን ያስታውሰናል፤ “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ…ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ” (መዝ 2፡9) እንዲል፡፡ በተመሳሳይም ለዮሐንስ በራእዩ ሲገልጽለት፤ “ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፡፡ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል፡፡ ….በብረት በትር ይገዛቸዋል፤…በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው” (ራእይ 19፡12-16) የተባለውን መሆኑን ስለሚገልጽ ይህን ባለ ግርማ ንጉሥ የወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሌላ ሴት የለችም፡፡

    ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ (ራእይ 12፡5)

    መጽሐፍ ቅዱስ የድንግል ማርያም ልጅ በሰማይ እንደሚኖር በግልጽ ከተናገረ፤ ይህ “ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ” የሚለውን ለሌላ ሴት ልጅ፣ ልንሰጠው በፍጹም አይገባም፤ ምክንያቱም “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው (ዮሐ 3:13) ብሏልና፡፡ የሰው ልጅ የሚለው ደግሞ ከሰው ወገን እርሱን የወለደች ሌላ ከሌለች መጽሐፍ “ከኢየሱስ እናት ከማርያም” (ሐዋ 1፡14) ካለን፤ እናት የሆነችው ሌላ ባለመኖርዋ ሴቲቱ ድንግል ማርያም መሆንዋ ግልጽ ነው፡፡

    ወደ ዙፋኑ፣ በሚለው አገላለጽ ውስጥ ባለ ዙፉን፣ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን ያሳውቀናል፡፡ ስለዚህ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ግርማው ነው ሄዶ የተቀመጠው፡ “ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይላልና (ዕብራ 1፡3)፡፡ “ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ” (ሐዋ 1:11) አስቀድሞ በትንቢት፣ ራሱ እግዚአብሔር ሊያድነን ተወልዶ፣ ያንኑ የተዋሐደውን ሥጋ ይዞ ወደ ሰማይ እንደሚያርግ በልበ አምላክ በዳዊት አንደበት “በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (መዝ 67:33)፣ “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ 46:5) በመባል ተተንብዮአል፡፡ ይህን ትንቢት ሊፈጽም ጌታ “ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃስ 24:51) “በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” (ማር 16:19)፡፡ ልብ እናድርግ ልጅዋ እንዲህ ወደ ሰማይ ከወጣ፡፡ የዚህ ባለ ሥልጣን እናት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡

    ሴቲቱም ወደ በረሀ ሸሸች (ራእይ 12፡6)

    “ሴቲቱም ወደ በረሀ ሸሸች” ሲል ከእርስዋ ጋር ልጅዋ ዮሴፍና ቅዱሳን መላእክት መኖራቸው አይካድም፡፡ ምክንያቱም ሊናገሩለት በፈለጉት አስጠጋግቶ መናገር የመጽሐፍ ልማድ ነው፡፡ ለምሳሌ “ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም” (ኢሳ 51:2) በሚለው ውስጥ ብቻውን የሚለው ቃል ብቻ አንድን አያመለክትም፤ ሚስቱን ይዞ ነው የተጠራውና፤ ከእርሱም ጋር የወንድሙ ልጅ ሎጥ ነበረ፡፡ በዋናው መናገር ልማድ ነው፡፡

    ሌላም ምሳሌ ብናይ “አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ” (ሕዝ 33:24) ከእርሱ ጋር ሚስቱ አሸከሮች ከእርሱ ጋር የተሰደዱ ዘመዶቹ አሉ፡፡ በአዲስ ኪዳንም “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።” (Ebera 11:8) የሚለው በአንድ ሰው አንቀጽ ነው በዋናው ሌሎችን አጠቃልሎ መናገር የመጽሐፍ ልማድ መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡

    የስደተኞች እናት ስደትን ልትባርክ፣ ከልጅዋ ጋር በረሀ ለበረሃ ተንከራታለች፡፡ ለዚህ ነው “ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ” በሚለው ውስጥ ዝግጅቱ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረ ስለመሆኑ፡- “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” (ሆሴዕ 11፡1) ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ስለመሰደዱ ወንጌላዊው ማቴዎስ ሲጽፍ፣ “የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” (ማቴ 2፡13-15)፡፡ ልጇን ከእባቡ ሄሮድስ ለማዳን የግብፁን አሸዋ ግለት፣ የውኃውን ጥም፣ ርሃቡን ሁሉ ታገሰች፡፡ በራእይ ላይ እንዲህ የተባለች ሴት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሌላ ሴት የለችም፡፡ “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ 5፡10) ይህን “ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን…ወደ በረሀ ሸሸች” የሚለውን የሚፈታልን ራሱ እዚያው ዮሐንስ ነው፡፡ ይህ “አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ” መሄድዋን ያመለክታል፡፡ ይህም ድንግል ማርያም ይህን ያህል ዘመን በበረሃ ቆይተው እንደመጡ የሚናገረው የታሪክ መጽሐፍዋ ጋር አንድ ነው፡፡

    ዘንዶውም… ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት (ራእይ 12፡13)

    በነቢዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና” (ኢሳ 9፡6) የተባለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ኃያሉን ልጅ በመውለዷ፣ እርሱን መቋቋም ቢያቅተው፤ ከእርስዋ ሥጋ ነሥቶ ነው ድል ያደደረገኝ በማለት ምክንያተ ድኂን፣ መሠረተ ሕይወት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ዘንዶው ማሳደድ ጀመረ፡፡ ለጊዜው በሄሮድስ አድሮ ኃያል ወልድን የወለደች እመቤታችንን ወደ ግብጽ ያሳደዳት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከሰው ልጆች ልቦና ውስጥ የእመቤታችንን ፍቅሯን፣ አማላጅነትዋንና የጸጋ እናትነትዋን ለማስወጣት እያሳደደ ይገኛል፡፡

    በዚህ ዘመን ልብ ይስጣቸውና እንደ ሄሮድስ ሰይጣን ያደረባቸው ሰዎች፤ ልጇን እፈልጋለሁ፣ እርስዋን ግን አንፈልግም የሚሉን ሁሉ እናቱን መቀበል ማለት ልጇን መቀበል መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፤ (በማቴዎስ 10፡40-42) “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል” ያላቸውን ሐዋርያትን እንኳ የተቀበለ፣ ላኪውን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበለ ከሆነ፤ እናቱንማ መቀበል እንዴት ልጅዋን መቀበል አይሆን?

    “ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል” ካለን፣ ድንግል ማርያምም ይህ ማዕረግ አላት፤ እርስዋን መቀበል፣ የእርስዋን የስደትዋን ዋጋ፣ የጸሎትዋን ዋጋ እንቀበላለን ስንላቸው፣ እንዴት አታገኙም ሊሉን ይችላሉ? “ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙሬ ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም” እያለን፣ እርስዋ ከደቀ መዝሙርነትም አልፋ እናቱ ናት፣ በእርስዋ ስም ብናበላ ብናጠጣ ዋጋ አታገኙም ለምን ይሉናል? ይህ ሁሉ ከንቱ ድካም፣ በስጦታ (በጸጋ) እናታችን የሆነችውን የአምላክነን እናት (ዮሐ 19፡26) ከልባችን ሊያሳድዱ መፈለጋቸውን ያሳያል፡፡

    ስለ እርስዋ አማላጅነት ሲነሣ ቁጭ ብድግ እያሉ የሚቃወሙ እኒህ የዲያብሎስ ጀሌዎች፤ ይህን ጠላትነት ከዘንዶው ካልሆነ በቀር ከየት ሊያገኙት ይችላሉ? በቃና ዘገሊላ ማማለዷን ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች፤ አሁን አሁን በሥጋ ሳለች ይሁን እንቀበለው አማልዳለች፤ አሁን ግን የለችም፣ አታማልድም ይሉናል፡፡ ልብ ልንል የሚገባው ሐዋርያትን “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡” (ማቴ 28፡20) ያለው ጌታ አሁን እነርሱ በሥጋ ኖረው አይደለም፤ በነፍስ ስላልሞቱ አሁንም ከእርሱ ጋር ስላለ ነው፡፡ ከእመቤታችንም ጋር አብሮ ለመኖሩ በመልአክ አንደበት “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፡28) ካላት ከእርስዋ ጋር እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለመኖሩ ምን ጥያቄ አለው፡፡ እርስዋ በነቢዩ እንደ ተነገረው “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ተብላለችና (መዝ 44፡9) ማንም ከልባችን ሊያሳድዳት አይችልም::

    እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት (ራእይ 12፡14)

    የታላቁ ንሥር የተባለው አባቷ አብርሃም ነው፡፡ አብርሃም በሁለት ክንፎቹ የተመሰሉት ምግባርና ሃይማኖቱ ናቸው “እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ” (ያዕቆብ 2:21-23)፡፡ ክንፍ በቀጥታ ክንፍ ተብሎ እንደማይተረጎም ለመረዳት፣ ለምሳሌ ”በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል” (ዘጸ 19:4) “በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ” (መዝ 16፡8) “በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ” (መዝ 17፡10) “ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” (ማቴ 23፡37) በሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ውስጥ እግዚአብሔር ክንፍ አለው ብለን እንደማንተረጉም የታወቀ ነው፣ ምሳሌ እንጂ፡፡

    ስለ ሰዎች በተነገረውም “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ” (ኢሳ 40:31) ሲባል ክንፍ አውጥተን እንበራለን ማለት እንዳልሆነ፣ እንዲሁ ድንግል ማርያም የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት ሲባል ክንፍ አላት ማለት አይደለም፣ ምግባርና ሃይማኖትዋን በክንፍ መሰሎት ነው፡፡

    እመቤታችን ድንግል ማርያም ሃይማኖትዋ ጽኑ በመሆኑ፤ ከቤተ መቅደስ ስታድግ ስለ አምላክ መወለድ በእምነት ስትጠባበቅ የኖረች ከመሆንም አልፎ ያቺ ድንግል ሴት ላይ ደርሼ እያገለገልሁ ከእርስዋ ጋር በኖርኩ ማለትዋ የምግባርዋን ትሕትና ያሳያል፡፡ ለዚህም ነው ይህን ትሕትናዋን መጽሐፍ ጽፎ ሲያስቀምጥልን “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአል” በማለት የገለጠችው (ሉቃ 1፡48)፤ ስለ አማኝነትዋ አክስትዋ ኤልሣቤጥ “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት” አለቻት (ሉቃ 1፡45)፡፡

    እኛም ልጆችዋ እኒህን ሁለት አክናፎች ሊኖረን ይገባናል፡፡ ሃይማኖት አለኝ በማለት ብቻ አይዳንምና፡፡ ምግባር የሌለው ሰው እምነቱ ምን ይጠቅመዋል? “አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም:- አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።…ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። (ያዕቆብ 2:21-26)

    ሌላው ሁለቱ ክንፎችዋ ንጽሕናዎችዋ ናቸው፡፡ ዘንዶውን ንጽሕና ስለአላት አልተቋቋማትም፡፡ በዚህ ንጽሕናዋ አመለጠችው እንኳን የአምላክ ማደሪያ ንጽሕት መባል ሊያንሳት ሌሎች አማኞችም ንጹሐን እንደሚባሉ፤ “እንደ ንጽሕት ድንግል” (2ኛ ቆሮ 11:2) ተብሎ ተነግሯል፡፡ እመቤታችን በጸጋ ብቻ ሳይሆን በማኅጸንዋ በመሸከም የንጽሕና ማደሪያ ሆናለችና፣ ንጽሕና ያላት እናት ናት፡፡

    እመቤታችን በውስጥ፣ በውጪም በሁለት ወገን ድንግል በመሆንዋ ሁለት ክንፍ ካለው ንስር ጋር ተነጻጽራ በመቀመጥዋ፤ በአሳብዋ ድንግል ለመሆንዋ “ወንድ አላውቅም” በአሳቤም የለም፣ እንዴት ይሆንልኛል በማለትዋ ታውቋል፤ በሥጋዋም ድንግል ስለሆነች፣ ከመውለድዋ በፊት ድንግል፣ በወለደች ጊዜ ድንግል፣ ከወለደች በኋላ በድንግል የኖረች ማሕፀንዋ “ተዘግቶ ይኖራል” ሰውም አይገባበትም በሚለው ትንቢት ያወቅናት፤ ይህቺ ሴት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡ (ሕዝ 44፡1-2)

    እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ (ራእይ 12፡15)

    እባብ እያለ የሚናገረው፣ በቀጥታ እባብ አይደለም፤ ይህ በእግዚአብሔር መጽሐፍ አገላለጽ የተለመደ ነው፡፡ “እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥” (ማቴ 23:33) በሚለው ውስጥ እናንተ እባቦች ያላቸው በተንኮል የሚታወቁትን ሰዎችን እንጂ የተፈጥሮ እባቦችን አይደለም፡፡ ስለዚህም እባብ ያለው ጌታ ሲወለድ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ነው፡፡ “ጌታ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ . . .ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ” (ማቴ 2፡1-8)

    “ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” (ማቴ 2፡16) እባቡ ሄሮድስ ይህን ያደረገው ከሚገደሉት ሕፃናት መካከል አንዱ ይሆናል በማለት በመገመት ለወታደሮቹ ልኮ ሕፃኑን ለመግደል መሞከሩ ነበረ፡፡

    ወንዝ የሚያህል ውኃ የተባለው ለወታደሮቹ የተተላለፈው ትእዛዝና የሠራዊት ብዛት በቤተ ልሔም መሠማራቱ ሕፃኑንና እናቱን ለመግደል የተተላለፈው ትእዛዝ ነው፡፡

    ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው (ራእይ 12፡16)

    ዮሴፍና ድንግል ማርያም ቤተ ልሔም ተቀምጠው ሳሉ ሄሮድስ መጥቶ እንዳያጠፋቸው ከሄሮድስ የተላለፈውን ትእዛዝ እንዳይፈጸም የጌታ መልአክ ተንኮሉን በመንገር እንደረዳቸው ለማመልከት ምድሪቱ ረዳቻት በማለት ተናገረ “የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው” (ማቴ 2፡13)

    ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ (ራእይ 12፡17)

    ዘንዶው በእርስዋ ላይ ለምን ተቆጣ?

    ከግዛቱ ከሲኦል ነፍሳትን የሚነጥቀውን ልጅ ወለደችበት

    ዘንዶው ለ5500 ዘመናት የሰውን ዘር በሲኦል ሲቀጣ ኖሮአል፡፡ ነገር ግን አምላክ አንዲት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያምን አስቀረለን፣ ከእርስዋም ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ለዚህ ነው በትንቢት “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር” (ኢሳ 1፡9) ያለው፡፡

    ከጨለማ የሚያወጣውን ልጅ ስለ ወለደችበት ተቆጣ

    ዘንዶው ለ5500 ዘመናት በጨለማ ሲገዛ ነበረ፡፡ እመ ብርሃን (የብርሃን እናት) ስትመጣ ግን “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” (ኢሳ 9፡2) ይህን “የዓለም ብርሃን” (ዮሐ 8፡12) የሆነ ጌታ መጥቶ የጨለማውን ገዢ አስወገደው፤ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን” (ቆላስይስ 1:13) ስለዚህ ከእርስዋ ባይወለድ ኖሮ አያሸንፈኝም ነበረ ብሎ አስቧልና ተቆጣት፡፡ ስለዚህም እስከ አሁን ድንግል ማርያምን የሚሳደቡ ለምን ከጨለማ በእርስዋ ሥጋ ነሥቶ አወጣን በማለት ሳያውቁም ሆነ አውቀው ክብርዋን የማይናገሩ ስለሆነ ሐዋርያው ይሁዳ ስለ እነርሱ “እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ፡፡ . . .ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት” (ይሁዳ 13) ይላቸዋል፡፡

    የሰው ልጆች ሁሉ ሊያጠፉ ነበረ፣ ነገር ግን መድኃኔ ዓለምን ወለደችበት

    “ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና…ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ” (ሉቃ 2፡11) ሰዎች መድኃኒታቸውን ያገኙት ከእርስዋ ጋር ነው፡፡ ሰይጣን ግን ሰዎች እንዲድኑ እንደማይፈልግ እንዲህ ተጽፎአል “ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል” (ሉቃስ 8፡12) ባጠቃላይ ሰይጣን ዓለምን ከእርስዋ ተወልዶ ስላዳናቸው በእርስዋ ላይ ተቆጥቶአልና ልብ አድርጉ አንድ መናፍቅ መጥቶ ስለ ድንግል ማርያም ስትናገሩ ከተቆጣና ከተቃወመ የተቆጣው የዲያብሎስ ወገን መሆኑን አስተውሉ፡፡

    ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ (ራእይ 12፡17)

    ከዘርዋ የቀሩት ለጊዜው በዘር እስራኤላዊ የሆኑ 144 ሺህ ሕፃናት ናቸው፡፡ “ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ” (ማቴ 2፡16) እነዚህ ሕፃናት ንጽሕና ያልጎደፈባቸው ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ልጅ ለበጉ በኩራት የሆኑና ለእግዚአብሔር መንግሥት ተዋጅተውአሁን በዙፋኑ ፊት ሌትና ቀን ሲያመሰግኑት የሚኖሩ ሆነዋል፡፡ “አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም፣ የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ… .ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም” (ራእይ 14፡1-5)

    የቤተ ልሔም ሕፃናት መሆናቸው የሚተታወቀው፡- “ከሴቶች ጋር ያልረከሱ”፤ “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት”፤ “በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም” የሚሉት አባባሎች ናቸው፡፡ ሕፃናቱ ከሁለት ዓመት በታች ስለሆኑ ድንግል ናቸው፣ ውሸት አያውቁም፣ ነውር የሆነ ኃጢአት አልሠሩም እኒህን በኩር የተባሉ መጀመሪያ ከበጉ ክርስቶስ በፊት ለሰማዕትነት የተዋጁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ዘንዶው ሄሮድስ ሕፃናቱን የሚገድለው ንጉሥ ክርስቶስ ከእነርሱ መካከል ይሆናል በማለት ስለሆነ ለበጉ ሲሉ የተዋጁትን ሊዋጋቸው መሄዱን በራእይ ተገለጸ፡፡

    ሌላው ከዘርዋ የቀሩት እኛ ምእመናን ነን፡፡ ከመስቀል ስር የተረከብናት እናታችን ናት፡፡ ወንጌል ለሐዋርያት በመሰጠቱ ለእኛ አልተሰጠንም እንደማንል ሁሉ፤ ለቅዱስ ዮሐንስም እናት እንድትሆነው ስትሰጥ ለእኛም እናታችን ሆናለች (ዮሐ 19፡26)፡፡ ፈጣሪ አስቀድሞ ለእናትነት የመረጣትና የመሠረታት፤ መሠረተ ሕይወት ድንግል ማርያም የሰው ልጆች ሁሉ እናት ናት፡፡ በትንቢት “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት” ይላታል (መዝ 86፡5)፡፡ እናት የተባለችው ጽዮን ድንግል ማርያም ለመሆንዋ አስቀድሞ ኢሳይያስ ዘር ባያስቀርንል እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ቃል ጠቅሶ አስተምሮበታል (ሮሜ 9፡29)፡፡ “እነሆ፥ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዓለት አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም”(ሮሜ 9፡32-33) ብሎአል፡፡ ድንጋዩ (ዐለቱ) ክርስቶስ ነው (ኤፌ 2:20) ስለዚህ በድንጋይ የተመሰለው ክርስቶስ በየት ኖረ? ብንል በጽዮን ይለናል፡፡ ባጠቃላይ ጌታ ለእናትነት የመረጣት ጽዮን የሰው ሁሉ የጸጋ እናት ስለ ሆነች ዘሮችዋን እኛን አሁን ዘንዶው እየተዋጋን ነው፡፡ ማርያም ማርያም አትበሉ ይለናል፡፡ ዘንዶው ስሟ ሲጠራ ስለ እርስዋ ድምጽ ሲሰማ ይቆጣል፡፡ እኛ ልጆችዋ ግን ድምጽዋን ስንሰማ በደስታ ዮሐንስ መጥምቁ በማኅፀን ሳለ በደስታ እንደዘለለ እንዘላለን፣ እንደሰታለን (ሉቃ 1፡41)፡፡ ዘንዶው ይሰድባታል፣ ጠላቷ ነውና፤ እኛ ደግሞ ትውልድ በመሆናችን ልጆችዋ ነንና እናመሰግናታለን “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል` ብላናለችና እንታዘዛታለን (ሉቃ 1፡48)፡፡

    አመስግነናት፣ ወድደናት፣ እናቴ ብለናት፤ እናት ለልጆችዋ የምታወርሰውን አዲሲቷን ምድር መንግሥተ ሰማያትን (ራእይ 21፡1-2) በአማላጅነትዋ በአባትዋ በዳዊት ትንቢት መሠረት “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፡፡ ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ” (መዝ 44 (45)፡16-17) እንዳለው ስምዋን አሳስበን አዲሲቷን ምድር እንድታወርሰን የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልን፡፡

    በአማላጅነትዋም ዘወትር አትለየን ምስጋናችንን ውዳሴያችንን ትቀበለን
    “ሰዓሊ ለነ ቅድስት”
    ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሴቲቱ ማን ናት? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top