• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 17 November 2015

    ትንሣኤ ዘክርስቶስ


    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀር ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት በተዋሕዶ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው ፡፡ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትምና ፤ » ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡መዝ15÷10፡፡ሐዋርያው ቅዱስጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ( ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመስጠት) ሞቶአልና ፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ) ÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም) ÷ በእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤ » ብሏል፡፡ 1ኛ ጴጥ 3 ÷ 18፡፡

    እንዴት ተነሣ 

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው ፡፡ ይኽንንም ፡- « ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ ( ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና ) ፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ( ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት ÷ ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም ፡፡(ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም )፡፡ ላኖራት ( ነፍሴን በገነት ÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ ፤ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡ » በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል ፡፡ ዮሐ 10 ÷17 – 18 ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ፡- « ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም ፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ » በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢት ነበር ፡፡ ኢሳ 53 ÷ 7 ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህ የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል ፡፡ 1ኛ ጴጥ 2 ÷ 23 ፡፡ በዚህ ዓይነት ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል ፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና ፡፡ ዮሐ 11 ÷ 25፡፡

    ይህ እንዲህ ከሆነ ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ፡- « የሕይወትን ራስ ገደላችሁት ፤» በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ ፡- « እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው ፤» ለምን አለ; የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል ፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም» ፤ የሚሉ አሉና ፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ናቸው፡፡ ሐዋርያው « እግዚአብሔር አስነሣው ፤» ሲል « እግዚአብሔር » የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻ አይደለም፡፡ወልድም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ዮሐ1÷1፡ የሐዋ 20 ÷ 28 ፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ 1 ÷ 2፡፡ ስለዚህ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው « አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ ፤ አንድም ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ ÷ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ ፤» ተብሎ ይተረጐማል፡፡ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው ፡፡ « እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ፤ ጠላቶቹንም በኃላቸው መታ ፤ » እንዲል፡፡መዝ77÷65፡፡

    ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ 

    በእስራኤል ባሕል የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር የመቀበር ልማድ አላቸው ፡፡ ዮሴፍ የእስራኤልን ልጆች ፡- « እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንስታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤ » ብሎ ያማላቸው የአባቶቹ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አፅም ካረፈበት ለመቀበር ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. 50 ÷ 25 ፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢይ ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ ፤ » ብሏል ፡፡ 1ኛ ነገ 13÷31፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት ከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ « ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው ÷ ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው ÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ ፤» እንዲል ማቴ27÷59፡፡ይህምየሆነውእርሱባወቀበርሱጥበብነው፡፡ እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል ፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ የነበረው ሰው የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ በተአምር ተነሥቷል፡ ፡ 2ኛነገ 13 ÷ 20፡፡ እንግዲህ ጌታችንም ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ ሞትን ድል አድር ጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው ፤» ባሉት ነበር ፡፡ ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፡፡ በአዲስ መቃብር የተቀበረው፡፡

    እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ 

    ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኃላ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- «ጌታሆይ÷ያሰው( ክርስቶስ ) ገና በሕይወቱ ሳለ ፡- ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን ፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ፡- ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም ፡- ጠባቆች አሉአችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው ፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠብቁ ፡፡ » ማቴ 27 ፡ 63÷66፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር ድንጋዩ እንደታተመ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም ምንም የማይግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረ ነው ፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው በተዋሕዶ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ እያዩት ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር ፡፡ ዮሐ 8÷59 ፤ 10÷39 ፡፡ ይህም የሆነው እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ 20÷19 ፤ 26፡፡ በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እንደታተመች የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ 7÷14፡፡ ማቴ 1÷20 – 23 ፣ ሉቃ 2÷ 6-7፡፡

    መቃብሩን ማን ከፈተው                                                                                                                                   ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ መቃብሩን ማን ከፈተው; ለምንስ ተከፈተ ; የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል ; በወንጌል እንደተጻፈው የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ እሑድ በማለዳ ፀሐይ ሲወጣ መግደላዊት ማርያም ÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር ፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው « ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል ; » የሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና ፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡ እርሱ ግን ፡- « አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ ፤ ተንሥቷል በዚህ የለም ፡፡» አላቸው፡፡ ማር 16÷1-6፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው ፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ፡- ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው ፡- እናንተስ አትፍሩ ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና ፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም ፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ 28÷1-6፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው ዮሐ. 20÷7 ፡፡

    በኵረ ትንሣኤ                                                                                                                                                      ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የበኵር ልጅ ነው ፡፡ ዕብ 1÷6 ፣ ሉቃ 2÷7 ፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ « አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል ፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል ፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው ፤» እንዳለ ፡፡ 1ኛ ቆሮ 15÷20-23፡፡ በተጨማሪም ፡- « በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው) ፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል ፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው) ፤ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው ፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵርነው፡፡»የሚልአለ፡፡kAላ1÷16-18፡፡ቅዱስዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም ÷ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን ፤» ብሏል፡፡ ራእ 1÷5 ፡፡

    በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ 1ኛ ነገ 17÷ 22 ፣ 2ኛነገ 4÷32 – 38፡፡ በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ ÷ አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል ፡፡ ማቴ 9÷25 ፣ ሉቃ 7÷15 ፣ ዮሐ 11÷44፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል ፡፡ ማቴ 27÷53 ፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ:- ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል ፡፡ ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም ፡- « ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና ፡፡» በማለት ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ 6÷9 ፡፡ ጌታችንም ፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ ፤» ብሏል፡፡ ራእ 1÷18 ፡፡

    ተስፋ ትንሣኤ

    በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር ፡፡ 1ኛ ቆሮ 15÷ 22 ፡፡ « ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ(እስከክርስቶስ)ድረስሞት ነገሠ፤»እንዲል፡፡ሮሜ5÷14፡፡ከዚህየተነሣእነአብርሃምእንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው ፡፡ እነ ኢሳይያስ ፡- «ጽድቃችንም ሁሉእንደመርገምጨርቅነው፤»ያሉትለዚህነው፡፡ኢሳ64÷6፡፡ እነኤርምያስም፡-«ለሥጋለባሽሁሉሰላምየለም፡፡ስንዴንዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል ፡፡ ኤር 12÷ 13 በዚህ ምክንያት የብሉይ ኪዳንዘመንዘመነፍዳ÷ዘመነኵነኔ÷ዘመነጽልመትተብሏል፡፡በዚህ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት ፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ ፤ ኃይልህን አንሣ÷እኛንም ለማዳንና፤ (በሥጋ ተገልጸህ÷ሰው ሁነህ አድነን)፤» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል ፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ « ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን ፤( ብርሃን ወልድን ÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን ፤ እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ ወደ ገነት መንግሥተ ሰማያት ይውሰዱን ) » ፤ እያሉም አብን ተማጽነዋል ፡፡ መዝ.40 ÷3 ፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ስለነበር ነው ፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና ፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል እንደሚወጡ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና ፡፡

    የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርÑEቸዋል ፡፡ ይህም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል ፡፡ ምድራዊውን እንዲንቁ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርÑEቸዋል ፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን ፡፡» እንዲል ፡፡ 2ኛ ጴጥ 3 ÷13 ፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል ፡፡ « አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ ፡፡» እንዲል ፡፡ ራእ 21÷ 1 – 3፡፡ እግዚአብሔርም ፡- « እነሆ ÷ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም ፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ ፤ እነሆ ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት ÷ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁና ፡፡» ብሏል ፡፡ ኢሳ ፡ 65 ÷17 ፡፡

    ሙታን እንዴት ይነሣሉ

    እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል ፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፡ 4÷10 ፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ፡ 5÷24 ፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል ፡፡ በቃል ፡- « በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል ፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ ፡፡ » ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ 5÷29 ፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል ፡፡ ዮሐ 11÷43 ፡፡ ቅዱሳን ነቢያት ፡- እነ ኢሳይያስ « ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡ » ብለዋል ፡፡ ኢሳ 26÷19 ፡፡ እነ ዳንኤልም ፡- « በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ( ሁሉም ) ይነቃሉ፤ እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስkCልና ፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን 12÷2፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል ፡- እግዚአብሔር በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ ፡- « እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስልሃልን ; » ሲል ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ ፤ » የሚል መልስ ሰጥቶቷል ፡፡ በመጨረሻም እነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- « እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ ፡፡» በማለት ገልጦታል፡፡ ሕዝ 37÷ 1 – 10 ፡፡

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር « ነገር ግን ሰው ፡- ሙታን እንዴት ይነሣሉ ; በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ ; የሚል ይኖር ይሆናል ፡፡ » ብሎ ከጠየቀ በኋላ ፡- « አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም ፡፡ » ብሏል ፡፡ ከዚህም አያይዞ « የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው ፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል ፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል ፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ ፡፡ እንዲሁ ደግሞ ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል ፤ ኋለኛው አዳም ( ክርስቶስ ) ሕይወትን የሚሠጥ መንፈስ ሆነ ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም ፡፡ የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው ፡፡ ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል ፡፡ 1ኛቆሮ 15÷ 35-49፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል 3÷ 21 ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ፡- « እርሱን እንድንመስል እናውቃለን ፤ ብሏል፡፡1ኛዮሐ3÷2፡፡

    የትንሣኤ ጸጋ
    በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው ፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል ÷ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ፡፡ ሙታን የነበርን ሕያዋን ÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን ÷ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ « ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ ; ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ ; » የምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ 13÷ 14 1ኛቆሮ 15÷ 55 ፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ « እኛ አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን ፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል ፡፡ » የምንል ሆነናል ፊል 3÷20 – 21 ፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤ ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው ፡፡ « ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ ÷በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና ፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና ÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡ » እንዲል ፡፡ 2ኛቆሮ 5÷1 – 2 ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ ፤ » ብሏል፡፡ 1ኛ ጴጥ 1÷3 ፡፡ ቅዱስ ጳውለሮስም ፡- « በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳየን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሣን ፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን ፡፡ » ብሏል፡፡ ኤፌ 2÷6 – 7፡፡

    የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን ፡፡

     source: በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማ/መ/ማኀበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሥልጠና ክፍል 

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ትንሣኤ ዘክርስቶስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top