የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች፦
ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት
ክፍል 5 : የክርስቲያን ኑሮ (የክርስትና ሕይወት ኑሮ)
v ከምዕራፍ 12 - ምዕራፍ 14
Ø ምዕራፍ 12 የክርስቲያን ኑሮ ክፍል መጀመሪያ ምዕራፍ ነው::
Ø የክርስትና ሃይማኖት የእምነት ነገር ብቻ ሳይሆን በኑሮአችንም ውስጥ እንዴት እንደምንመላለስ የሚያስተምረን የኑሮ መመሪያችንም ነው (1ተሰ 4፥1፤ 1ዮሐ 2፥6)
Ø ስለዚህ በሚከተሉት በእነዚህ ሦስት ምዕራፎች ጽድቅን በእምነት የተቀበለ ሰው በኑሮው እንዴት መመላለስ እንደሚገባው እንማራለን:: በዚህም መሠረት:-
· የክርስቲያን ኑሮ በእግዚአብሔር ዘንድ በምዕራፍ 12፤
· የክርስቲያን ኑሮ በምድራዊ መንግሥት ዘንድ በምዕራፍ 13፤
· የክርስቲያን ኑሮ በወንድሞች ዘንድ በምዕራፍ 14 ተመልክቶልናልና በትኩረት እንማረው ዘንድ ይገባናል:: በመሆኑም:-
§ በምዕራፍ 12 ሊኖረን ስለሚገባ መልካም ኅሊና (በጎ ልብ)፣
§ በምዕራፍ 13 በኑሯችን ውስጥ ማድረግ ስለሚገባን ነገር፣
§ በምዕራፍ 14 ደግሞ ማድረግ ስለማይገባን ነገር እንመለከታለን::
Ø እስከ አሁን በተመለከትናቸው 11 ምዕራፎች የእምነት ነገር ምን እንደሆነ እየተረዳን መጥተናል:: አሁን ደግሞ በዚህ በምዕራፍ 12 እና በቀጣዮቹ ምዕራፎች የእምነት ተከታይ የሆነው የመልካም ሥራ ነገር እናያለን::
Ø ይህም የክርስትናው ሕይወትና የመንፈሳዊውን ኑሮ ቅደም ተከተል በሚገባ የሚያስረዳን ነው:: ይኸውም ሰው አስቀድሞ በእምነቱ ይጸድቃል፣ ቀጥሎም በእምነት የተቀበለውን የጽድቅ ሕይወት መልካም ሥራን በመሥራት ይገልጣል::
Ø ይህም በአፅንኦት የሚያስገነዝበን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በእምነት የተቀበለና በክርስቶስ የዳነ ክርስቲያን የመዳን ሕይወቱን የሚገልጥ መልካም አኗኗር ሊኖረው እንደሚገባ ነው::
v ቁጥር 1- 2:-
Ø “እንግዲህ” የተባለው ቃል ከምዕራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ይመለከታል::
Ø በመሆኑም ሐዋርያው እስከዚህ ድረስ ባለው ትምህርት“የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ከተረዳንና ከተቀበልን እንግዲህስ ራሳችንን ደስ የሚያሰኝና ሕያው መስዋዕት አድርገን ርኅራሄ ላደረገልን ለእግዚአብሔር እናቅርብ” በማለት ልመና አዘል ምክር ያቀርባል::
Ø ይህም አቅርቦት መልካም ሥራችንን የተመረኮዘ ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ርኅራሄ ወረታ ወይም ምላሽ እንጂ ምህረቱን ለማግኘት የሚደረግ ሥራ አይደለም::
Ø እናስተውል! ከምእራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነትና ርኅራሄ ከማዳን ሥራው ጋር ተመልክተናል::
Ø አሁን ደግሞ ለዚህ ቸርነቱ የምናቀርብለትን ወረታ ወይም የምላሽ ስጦታ እየተጠየቅን ነው::ለመሆኑ ምን ልንሰጠው ተዘጋጅተን ይሆን?
Ø ብዙ ጊዜ ሲሆን የምናየው እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በስጦታነት የምናቀርበው ያለንን ገንዘብ አልያም ከእኛ ውጭ የሆነውን ነገር ነው::
Ø ሐዋርያው የሚነግረን ግን:-
· እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መስዋዕት ወይም ስጦታ ከእኛ ውጭ የሆነ ነገር ሳይሆን የራሳችንን ሰውነት ማለትም ልባችንን እንድንሰጠው ነው:: እርሱም:-
1. ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችን፣
2. በልባችን መታደስ የተለወጠ ማንነት እና
3. ይህንን ዓለም ያልመሰለ አኗኗራችን ነው::
ማስገንዘቢያ :-
Ø ብዙ ጊዜ በክርስትና ኑሯችን ተመላልሰን የቤተክርስቲያንን ቅጥሮች ወይም በሮች ስመን እና ጥቂት ሳንቲም ዘርዝረን ለድሆች ሰጥተን መምጣት አልያም ጥቂት ሰዓት በጸሎትና በጾም ቆይተን መመለሱ ብቻ በቂያችን እንደሆነ ስንገምት እንታያለን:: ይህ ነገር ለክርስቲያን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ነገር ግን አይደለም:: ዋናውና ቀዳሚው ያለንን ሳይሆን ራሳችንን ለቅዱሱ አምላካችን ለእግዚአብሔር በቅድስና መስጠት ነው:: ራስን መቀደስ፣ መለየት!
v ቁጥር 3-8:-
Ø ይህ የአካልና የብልቶች ምሳሌ ዓይነተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ሆኖ በ1ቆሮ 12፥12-27፣ በኤፌ 4፥15-16 እና በቈላ 1፥18 ደግሞ ቀርቧል ወይም ይገኛል::
Ø በዚህ ትምህርት ውስጥ ሐዋርያው በተለይ ስለመንፈሳዊ ስጦታዎችና ስለቤተክርስቲያን ሥራ ይናገራል:: ስለሆነም:-
· ትንቢት :- ተብሎ በቁጥር 6 ላይ የተገለጠው ቃል የወደፊትን ነገር መናገር ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚደረገውን የወንጌል ስብከትም የሚያመለክት ነው:: (1ቆሮ 14፥1-5) ይህም የቀሳውስትን ሥራ የሚያመለክት ነው::
· አገልግሎት :- ተብሎ የተገለጠው የዲያቆናቱን የተልዕኮ ሥራ የሚያሳይ ነው (ሐዋ 6፥1-6)
· መምከር :- ደግሞ የንስሐ አባት ሥራ ነው (ቁጥር 8)
· መማር :- ደግሞ በሽተኞችን የሚጠይቀውና የሚንከባከበው ወገን ሥራ ነው::
· መግዛት ወይምማስተዳደር :-የዓለቃ ሥራ ነው::
Ø እንግዲህ የክርስትና ማኅበር ወይም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እያንዳንዳቸው በተሰጣቸው ሙያ ሊተጉ ይገባል::
Ø እያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ተሰጥቶናልና (ኤፌ 4፥7)፤ ሁላችንም በተሰጠን ሥጦታ ሳንኮራ በመጨረሻው ቀን የጌታችንን ምስጋና እንቀበል ዘንድ በትጋት እናገልግል (ማቴ 25፥21-23)
v ቁጥር 9-13
Ø በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በቀዳሚነት የምንመለከተው ፍቅርን የሚያመለክቱ ሁለት ቃሎችን ነው
· ፍቅር
· መዋደድ የሚሉት ናቸው
Ø ይህም አንደኛው እግዚአብሔር የሚያፈቅርበትን ከፍ ያለውን ነገር የሚገልጥ ሲሆን ሁለተኛው እርስ በእርስ ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚገልጥ ነው:: እነዚህ ቃሎች በ ዮሐ 21፥15-17 እየተፈራረቁ የተነገሩ ናቸው::
Ø ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤
· ይህ ቃል እግዚአብሔርን የምናፈቅርበት ፍቅር ሲሆን ምልክቱም :-
- ክፉ ነገርን መጸየፍ እና ከበጎ ነገር ጋር መተባበር ነው
Ø በወንድማማች መዋደድ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፤
· ይህ ደግሞ የአንድ አባት ልጆች የሆንን (ዕብ 2፥10-11) ክርስቲያኖች ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚያመለክት ነው::: ምልክቱም:-
- በ1ጴጥ 4፥8 ላይ የተገለፀው የሌላውን ኃጢአትና ድካም በመሸፈንና በመቻቻል እንዲሁም በመከባበር የሚገለጥ ፍቅር ነው::
Ø ከ11-13 ባሉት ቁጥሮች የምናስተውላቸው ደግሞ ለመልካሙ የክርስትና ኑሯችን መሠረታዊ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች ነው:: እነርሱም:-
· ለመልካም ሥራ አለመለገም /ዳተኛ አለመሆን/፤
· በመንፈስ መቃጠል /ለመንፈሳዊ ነገር መቅናት/፤
· ለጌታ መገዛት /ክርስቶስን ብቻ ማምለክ/፤
· በተስፋ ደስ መሰኘት /የጌታን መምጣት መናፈቅ/፤
· በመከራ መታገስ /የክርስትናውን ፈተና አለማማረር/፤
· ቅዱሳንን መርዳት /ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ማገዝ/::
Ø እዚህ ጋር ልብ ልንላቸው የሚገቡና በዓለም ሰዎችና በውጭ ባሉ ጠላቶች ዘንድ የምናደርጋቸው ሦስት ወሳኝ ነገሮች ናቸው::
1. በተስፋ ደስ እንዲለን :- ተስፋ ምን እንደሆነ በምዕራፍ 8፥16-25 አይተናልና::
2. በመከራ እንድንታገስ :- የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን በዚህ በሰይጣን ግዛት ውስጥ መከራ እንደሚገጥመን የታወቀ ስለሆነ (1ዮሐ 4፥4-6፣ ገላ 4፥29፣ ዮሐ 15፥18)
3. በጸሎት እንድንጸና :- ጸሎት ተስፋችን ላይ እንድናተኩርና በመከራችን እንድንበራታ ስለሚያደርገን
v ቁጥር 14-21
Ø በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በዋናነት የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንማራለን
1. መከራ ለሚያደርሱብን መጸለይ ከጌታ የተማርነውና የበለጠ ክብር የሚያመጣልን እንደሆነ (ሉቃ 23፥34)
2. ከደስተኞች ጋር ደስታቸውን መካፈል፤ ከመከረኞች ጋር አብሮ መቸገር:: ይህም ሕይወት ከጌታችን የተማርነው ነውና:: ጌታችን እርሱ :-
§ “በመከራቸው ሁሉ ጨነቀው” (ኢሳ 63፥9)
§ በድካማችን ይራራል (ዕብ 4፥15)
§ የኃዘንተኞችን ሐዘን ተካፈለ (ዮሐ 11፥33-35)
§ በሠርግ ቤት ታደመ (ዮሐ 2፥1-2)
3. የትዕቢትን ሐሳብ ትተን የትህትናን ነገር መሥራት:: ይህም ከጌታችን የተማርነው ስለሆነ እናስተውለው:: ጌታችን እርሱ:-
§ ከድሆች ተወለደ፤
§ ከተዋረዱት ጋር ተቀመጠ፤
§ የተማሪዎቹን እግር ሊያጥብ ተንበረከከ (ዮሐ 13፥4-5)
4. ክፋትን በክፋት አለመመለስና በፈንታው መልካም የሆነውን ማሰብ:: ይህም:-
§ በዓለም ካሉትና ካልዳኑት ሰዎች የምንለይበት ብቸኛው የክርስቶስ ሕይወት ነው::
5. በቀልንና ፍርድን ለእግዚአብሔር መስጠትን:: ይህም:-
§ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፍርድ ማመንና መደገፍን የሚያመለክት ነው::
“እግዚአብሔር በእኔና ባንተ መካከል ይፍረድ” 1ሳሙ 24፥12-13
0 comments:
Post a Comment