• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 21 November 2015

    ኅዳር 12 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታላቅ በዓል


    ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ
    ሚ-መኑ
    'ካ-ከመ
    'ኤል- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው) ማለት ነው፡፡

    ይህ ታላቅ መልአክ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል፡፡
    ይህ ታላቅ መልአክ ያደረጋቸው የሠራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ተአምራት አሉት፡፡ ስለዚህ ስለ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፤ ጠባቂነትና አማላጅነት ከአባቶቻቸው የተማሩትን በኑሮአቸው ያዩትን አባቶቻችን ጽፈዋል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከጻፉት አባቶች መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፡-
    + ዮሐንስ አፈወርቅ
    + ኤዎስጣቴዎስ ዘአንፆኪያ
    + ቅዱስ መቃርዮስ+ ቅዱስ ያሬድ
    + አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
    + የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባዲማቴዎስ ናቸው፡፡

    እኛም የአባቶቻችንን አንደበት አንደበታችን አድርገን በኅዳር 12 ክቡር ገናና የሆነ ቅዱስ ሚካኤል ካደረጋቸውና ከሠራቸው ብዙ ተአምራት ውስጥ የተወሰኑትን በመልአኩ ተረዳኢነት እንዲህ ብለን እንናገራለን አንጽፋለን፡፡ ንግስት ክሌዎፓትራ ‹‹ሳተርን›› ለሚባለው ጣዖት የሠራችው ቤተ ጣዖት በእስክንድርያ ነበር፡፡ ይህ ቤተ ጣዖት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ /312 - 326/ ዘመን ድረስ ነበር፡፡ እለ እስክንድሮስ ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝቡ ከልቡ ገና የአምልኮ ጣዖት ስላልጣፋ 18 ፓትርያርኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ ብለው ተቃወሙት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ ቤተ ጣዖቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ቤተክርስቲያን አደረገው፡፡ ከዚህ በኋላ በቅዱስ ሚካኤልም ስም አብያተ ክርስቲያናት መታነጽ ጀመሩ በዓሉ በዚህ ቀን እንዲከበር ተወስኗል፡፡

    እንዲህም ሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዋብለት ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያረጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን አጡ፡፡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት፤ ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስን ወደ በጎች እንዲሔድና በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ አዘዘው፤ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሔዶ አንድ ዓሣእንዲወስድ አዘዘው፡፡ መልአኩም ወደ ቤት ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አስጠነቀቀው፡፡ ወደ ባለ ስንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በእርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ፡፡ ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው፤ እጅግም አደነቀ፤ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደው አደረገ፡፡ የተራቡ ድሆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው፡፡

    ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠላቸው ዱራታዎስንም የዓሳውን ሆድ እንዲሰነጥቅ አዘዘው፤ በሰነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሳው ሆድ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዋብስታን እንዲህአላቸው፡፡ ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሳውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ፤ እግዚአብሔር አስባችኋልና በጎ ሥራችሁን መስዋዕታችሁን ምጽዋዕታችሁን በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፡፡ በኋላኛውም መንግስት ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል፡፡››

    በአንድ ዘመን ብዙ ሰዎች ከግብፅ አውራጃ መጥተው ወደ ባሕር ማዶ ሄዱ፡፡ ከባሕሩም በደረሱ ጊዜ በመርከብ ላይ ተሳፍረው ከየብሱ ጥቂት በራቁና ወደ ባሕሩ መካከል በደረሱ ጊዜ ጽኑ ነፋስ ተነሳባቸው ለመስጠም እስኪ ደርሱድረስ፡፡ የማዕበሉ ሞገድ እየጨመረ እየጸና ከፍ አለ፡፡ ታላቅም ማዕበል መጥቶ ሊገለብጣቸው ደረሰ፡፡ ፍጹምጥፋትና ክፉ ሞት እንደ መጣባቸው ባዩ ጊዜ ጽኑ ሐዘን ያዛቸው፡፡ የሚያድናቸው የሚያጽናናቸው አጥተው ተስፋ ቆረጡ፡፡ ያን ጊዜ እንዲህ ብለው ጮኹ፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃቸው ግሩም ገናና የምትሆን ሚካኤል ሆይ የተአምራትና የይቅርታ መልአክ ነህና፡፡ ልዑል ቸርነቱን የሚገልጥብህ መልአክ ሆይ! እግዚአብሔር ፍቅሩን የሚያስታውቅብህ መልአክ ሆይ ወደኛ ተመልከት እርዳን፡፡ የተጨነቅን እኛን አድነን፡፡ ከመጣብን ሞትና ጥፋት እንድን ዘንድ ስለኛ ወደ ፈጣሪህ ወደ ፈጣሪያችን ወደ እግዚአብሔር ለምንልን፡፡ አሁን የሞት መጋረጃ ዓይናችንን ሸፍኖታልና፡፡ ፍጹም የጥፋት ጥላንም አይተናታልና›› ብለው በፍጹም ልቦናቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ በመርከብ ውስጥ ያሉት ሁሉ ጽኑ ለቅሶ እያለቀሱ መራራ እንባ እያፈሰሱ ጮኹ፡፡ከባሕር ጽኑ ማዕበል ከሞት ያድናቸው ዘንድ ያን ጊዜ በዚያች ሰዓት እግዚአብሔር የልቦናቸውን ሐዘንና ልመናቸውን ሰማቸው፡፡ ያን ጊዜም ይገዳቸው ዘንድ ቸር መልአኩን ሚካኤልን ላከላቸው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወረደ መርከቡን በእጁ ይዞ ሳበው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉትንም ወደ የብስ አወጣቸው፡፡ በደኅናቸው ተሻገሩ፤ ክፉ ነገር ጥቂትስ ስንኳ ፈጽሞ አላገኛቸውም፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ገናና የሆነ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ልመናውና አማላጅነቱ ፈጽሞ ይጠብቀን፡፡ ከጽኑ ጠላት እጅ በክንፎቹ ጋርዶ ይሰውረን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
    ድርሳነ ሚካኤል ዘኅዳር

    ምንጮች
    መጽሐፈ ስንክሳር ዘኅዳር
    የሐመር መጽሔት 1993 ዓም መጋቢትና ሚያዚያ ተያያዥ ገጾች

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ኅዳር 12 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታላቅ በዓል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top