ክፍል-1
ሀ-አስፈላጊነት
መጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚገኝበት ምሥጢር ነው፡፡
1. ድኀነትበጥምቀትነው፤
ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያልተጠመቀ ሰው አይድንም፡፡ የተጠመቀ ግን እንደሚድን በመዋዕለ ትምህርቱ እዲህ ሲል አስተምራል #ያመነ የተጠመቀም ይድናል$ ማር.16 ቁ 16፡፡ ያመነ ይድናል ብቻ አለማለቱን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ጥምቀት ለድኀነት ባያስፈልግ ኖሮ ጌታ ያመነ የተጠመቀም ይድናል ባላለ ነበር፡፡
2. በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤
ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ በሌሊት ወደ ጌታ ዘንድ ሊማር በሄደ ጊዜ ጌታ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› አለው፡፡ ይህ የጌታ ትምህርት ለኒቆዲሞስ ስለረቀቀበትና ስለተቸገረ ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኀፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡
ዳሩ ግን ዳግም ልደት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መሆኑን ጌታችን እንዲህ ሲል አስተምሮታል ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም (ዮሐ. 3÷3-6)፡፡
ከጌታችን ትምህርት የምንገነዘበው በሚታይ ሥርዓት በውኃ በሚደረገው ጥምቀት አማካኝነት ከሥላሴ ልጅነት ካላገኘን በስተቀር እንኳን መንግሥተ ሰማያት ልንገባ ልናያትም እንደማንችል ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ከውኃና ከመንፈስ መወለድ›› ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡
ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ›› አለ እንጂ ‹‹መቼ ካልተጠመቀ›› አለ ብለው ለመከራከር ይከጅሉ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው #ከውኃና ከመንፈስ መወለድ$ ማለት መጠመቅ ማለት እንደሆነ አይጠፋውም፡፡
ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኀፀነ ዮርዳኖስ ዳግም የምንወለደው በጥምቀት ነው፡፡ መወለድ ከእናት ማኀፀን መውጣት እንደሆነ ሕፃኑም ከውኃው ጠልቆ ይወጣልና፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጥምቀት የሚገኘውን ጸጋና ክብር ለቲቶ ሲገልጽለት ‹‹ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደድ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም›› ብሏል (ቲቶ. 3÷5)፡፡ ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብ›› ማለቱ ጥምቀትን ማለቱ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ በጻፈው ክታቡ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ…›› በማለት በጥምቀት አማካኝነት ምእመናን መንጻታቸውንና መቀደሳቸውን አስተምሯል (ኤፌ 5.26)፡፡
3. በጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታን ከማሳደድ ተመልሶ የእርሱ ምርጥ ዕቃ ሊሆን በተጠራ ጊዜ ሐናንያ እንዲህ ብሎታል፡፡ ‹‹አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፡፡ ከኃጢአትህም ታጠብ›› (የሐዋ.22÷16)፡፡ በዚህ መሠረት መጠመቁም ተገልጾአል (ሐዋ.9÷15-16)፡፡
እንግዲህ ምን እንላለን? ታላቁ ሐዋርያ ከኃጢአቱ የነጻውና የተቀደሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን አምኖ ጥምቀትን በመፈጸሙ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአቱ የተወገደለት ሐዋርያ እንዲሆን በተጠራ ጊዜ ሳይሆን ‹‹የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ በተጠመቀ$ ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ድኀነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከእናንተ አንዳንዶች እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል (1ቆሮ.6÷11)፡፡ በበዓለ ሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ልቡናቸው ከተመሰጠው አንዳንዶቹ ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰላቸው ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› የሚል መልስ ነው (ሐዋ.2÷37-38)፡፡
4. እምነት መሠረት ነው፡፡ ፍጹም የሚሆነው ግን በጥምቀት ነው፡፡
እምነት ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ‹‹እመኑ ብቻ ኃጢአታችሁ ይሠረይላችኋል›› ባላቸው፣ እንዲጠመቁም ባላስገደዳቸው ነበር፡፡ በሃይማኖት ጸሎታችንም ‹‹ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› የምንለው በዚህ መሠረት ነው፡፡
5-በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አብረን እንሞታለን ከእርሱም ጋር እንነሣለን፡፡
ማንኛውም ክርስቲያን በማናቸውም ነገር ክርስቶስን ሊመሰል ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሏልና፡፡ ስለዚህ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ሮሜ.6÷ 8፡፡
በጥምቀት ከጌታ ጋር አብረን ልንሞትና ልንቀበር ያስፈልጋል፡፡ እንዴት? ቅዱስ ጳውሎስ የዚህን መልስ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› (ሮሜ.6÷3-4)፡፡ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱም ላይ ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ›› ብሏል (ቆላ.2÷12)፡፡
ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት አንድንኖር እናምናለን ሮሜ.6÷8፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በጥምቀት ከጌታ ጋር መቀበራችንን ለማረጋገጥ አጥማቂው ካህን ተጠማቂውን በተጠራቀመ (ለመጠመቅ በተሞላ) ውኃ ውስጥ መላ አካሉን በማጥለቅ ነው የሚያጠምቀው፡፡
6-. በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይገኛል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያረጋግጥ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› ብሏል (ሮሜ.6÷4)፡፡ የቀደመው በኃጢአት ምክንያት ያደፈ ሰውነታችን የሚታደሰው፣ የሚቀደሰውና አዲስ ሕይወትን የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡
7-. በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን ሲያስትምር ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና ገላ.3÷27፡፡ በጥምቀት በደሙ ከዋጀን ከፈጣሪያችን ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ በተጠመቅን ጊዜ አዲሱን ሕይወት እንጎናጸፋለን፤ ፈጣሪውን መስሎ በተፈጠረው በቀድሞው ሰው በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን ንጽሕናና ቅድስና እናገኛለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደለውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡
8- በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል እንሆናለን፡፡
በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆን መገረዝ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነበር፡፡ አሕዛብ በቁልፈት፣ እስራኤል በግዝረት ይለዩ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአብርሃም ልጆች ሁሉ በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ ሕግ የወጣው፡፡ ግዝረት ደግሞ ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌ ነው (ቈላ. 2÷11-13)፡፡
ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ጥምቀትም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው ጸጋ ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆናችን ይረጋገጣል፡፡
ለ-የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን እንደነበሩት እንደ አይሁድና እንደ ዮሐንስ ያለ ጥምቀት አይደለም፡፡ አይሁድ ትዕዛዘ ኦሪትን ለጣሰ ሰው ይደረግ የነበረ የውኃ መታጠብ ነው፡፡ ከርኵሰት የሚነጻው በውኃ በመታጠብ ነበር (15÷1-18)፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ደግሞ የንስሐ ነበር (ማቴ.3÷5 እና 6)፡፡
ጌታ በዮሐንስ እጅ በባሕረ ዮርዳኖስ የተጠመቀው እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት እንደ ዮሐንስም ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን ስለሚከተሉት ምክንያቶች ተጠምቋል፡፡
1ኛ. ትሕትናንለማስተማር
በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ እጅ መጠመቁ መምህረ ትሕትና መሆኑን ይገልጣል፡፡
2ኛ. ለእኛ አርአያ ለመሆን
ሁለተኛም በጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር ለምንወለድ ለእኛ አርአያ ለመሆን ሊጠመቅ በቅቷል፡፡
3ኛ. ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ደብቆት የነበረውን የዐዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ፡፡
4ኛ. አንድነቱንና ሦስትነቱን ለማግለጥ
በብሉይ ኪዳን በተለያየ ኀብርና ምሳሌ የነበረውን አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጥ ጌታ ተጠምቋል፡፡ ‹‹ሰማያት ተከፈቱ›› የሚለው አነጋገር ሥውር የነበረው ይህ ምሥጢር መገለጡንና ገሃድ መውጣቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ የተዘጋ ቤት ሲከፈት በውስጥ ያለው የተሠወረው እንደሚታይ ሁሉ ከሰው ከእምሮ ረቅቆ የነበረው የሥላሴ ምሥጢርም በጌታ ጥምቀት መገለጡን ያረጋግጣል፡፡ በዚህም ጊዜ የክርስቶስ እውነተኛ አምላክነት በባሕርይ አባቱና በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ተመስሯል፡፡
ምንጭ: ዲ/ን መልአኩ አዘዘው ገጽ
0 comments:
Post a Comment