የመጨረሻ ክፍል
( ከባለፈው የቀጠለ……)
6. ቁም
በቤተ ክርስቲያናችን ቁም ንባብ፣ ቁም ዜማ ፣ ቁም ጸናጽል ያለ ሲሆን ሁሉም ትርጉማቸው ተመሳሳይ ነው፤አሁን ግን የምናየው ቁም ጸናጽልን ነው፡፡ በንዋያተ ቅድሳት ክፍል የምናየው ስሆነ ነው እንጅ ጸናጽ በራሱ የክርስቶስን መከራ የአበውን ተስፋ ፍጻሜ የሚያሳይ ነው- አሠራሩ፡፡ በጸናጽል ከምናቀርባቸው አንልግሎቶች አንዱ ይህ የቁም ጸናጽል ሁለት ነገሮችን የሚያሳይ ነው
1. የመጨረሻዋን ቀን ለማስታወስ
በእግዚአብሔር ፊት የምንቆምባት የመጨረሻቱ የፍርድ ቀን በሁችንም ሕይወት የምትታወስ ቀን ናት ኃጥአንም ሆነ ጻድቃን የማትቀር በመሆኗ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ሀለወነ ኩነ ንቁም ቅድመ ምኩናኑ ለክርስቶስ ሁላችንም በክርስቶስ ፊት እንቆም ዘንድ አለንና›› እያለ ያችን ቀን ያስታውሳታል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ስዚች ቀን ሲናገር ከምፈራቸው ሦስት ቀኖች አንዷ ናት ብሏታል፤እንኳን በፈጣሪ ፊት መቆም በንጉሥ ፊት መቆም እንኳን ምንኛ ያስፈራል፡፡ ይህች ቀን ግን የመጨረሻውን ፍርድ መስማት በቅድመ እግዚአብሔር የምንቆምባት ሰዓት ስለሆነች የምታስፈራ እንላታለን፡፡
ታዲያ ሊቃውንቱ ያንጊዜ ማረን ራራልን ለማለት ዛሬ እንደነቢዩ ዳዊት ‹‹በጽባሕ እቀውም ቅድሜከ ወአስተርኢ ለከ፤ በማለዳ በፊትህ ቆሜ እታይልሀለሁ›› መዝ 63 እያሉ በቁም ጸናጽል ፈጣሪያቸው ፊት ቆመው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ ምንጊዜም ቢሆን ማኅታውያኑ በእጃቸው በጨበጡት ጸናጽል ቁም ዜማውን እየጸነጸሉ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ሀወነ ኩልነ ንቁም ቅድመ ምኩናኑ ለክርስቶስ›› እያሉ ማሰብ ይገባቸዋል
2. ክርስቶስ በዐውደ ፍትሕ መቆሙን ለማስታዎስ፡-
ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነት የተሸሙ ሹማምንት ሁሉ ፍርድ እንዲሰጡ ተጠይቀው በአንድ ወንጀለኛ ላይ ተስማምተው የፈረዱበት ጊዜ በታሪክ ከዚህ ቀን በስተቀር ይገኛል ብየ አላስብም፤ ከሆነም እንኳን በቅዱስ ጳውሎስ ላይ እንደተደረገው በወንጀለኛው ላይ ይግባኝ ተጠይቆበት የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ የዛሬው ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው፤ የሹመት ዘመኑን የጨረሰው ሀና በዚያው ዘመን ባለሥልጣን የነበረው ቀያፋ ሌሊቱን ሙሉ ሲያዩት ካደሩ በኋላ ሲነጋ ደግሞ ወደ ቤተ መንግሥት ሹማምት ነገሩ ተመልሶ ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ እየተመላለሰ የክስ ሂደቱ ሲታይ አረፈደ፤ በእርግጥ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰበው ክርስቶስ የሚሞትባት ቀትረ ዐርብ እስክትደርስ እንጅ ፍርዱ እንደማይቀየር በእርሱ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ዝም ብሎ ፍርዱን ተቀበለ፡፡
ፍርዱን ከሰውልጆች ያስወግድ ዘንድ በፍርድ ዐደባባይ ቆሞ ፍርድ ተቀበለ፤ ‹‹አዳም ሆይ ቀድሞ መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ትመለሳለህ……..›› በፈራጁ ላይ ካልፈረዱበት ፍርዱ ከሰው ልጆች እንዴት ሊወገድ ይችላል፡፡ ኢሳ 53÷6 በነገር ሁሉ የተፈረረደበትንአዳምን መስሎ በመምጣቱ ሰራዊተ መላእክት በፊቱ ቆመው ማገልገል የማይቻላችው የሰራዊት ጌታ በዳኞች ፊት ቆሞ የሞት ፍርዱን ሰማ፡፡
ምሥጢሩ ግን አባቱ አዳም በአጋንንት አለቃ ፊት ቆሞ ከነልጅ ልጆቹ ለክፉ ግብሩ የሚገባውን ቅጣት እየተቀበለ የነበረበት ወቅት ነበርና የማይፈረድበት ሆኖ ሳለ በፍርዱ የአባቱ የአዳም የእናቱ የሔዋን ፍርድ እንዲወገድ ፍርድን ከሊቃነ ካህናትም ከመሳፍንተ አሕዛብም ተቀበለ፡፡ በእርግጥ እነርሱ በእርሱ ላይ ሲፈርዱበት እርሱ ደግሞ ክህነትን ከካህናቱ መንግሥትን ከነገሥታቱ ነጥቆ በነገሥታቱ ሹመት ተሸሞ የዚህን ዓለም ገዥ ሞትን የዘለዓለም ሞትን ፈረደበት፡፡ ለዚህም ነው ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ መንግሥት ባሉ ባለሥልጣናት ፊት ቆሞ ፍርድን የተቀበለው፡፡
አባቶቻችንም ጸናጽሉን ቁም ብለው የሰየሙት በእግዚአብሔርፊት ለፍርድ የቆመውን ጌታ በኅሊናቸው እያስታዎሱ ለሰው ብለህ ይህን ሁሉ መከራ ተቀበልህ እያሉ የሚያዜሙበት ጊዜ ስለሆነ ነው
1. መረግድ፡-
ጸናጽሉ በቁም ከተዘለቀ በኋላ ቃለ እግዚአብሔሩን መልሰው በመረግድ ይደግሙታል፤ መረግድ ሊቃውንቱ በሰቂለ ኅሊና ሆነው አካላቸውን ከማንቀሳቀስ ጋር የሚጸነጽሉት የጸናጽል ዓይነት ነው፤ ከበሮውም በሰፊው በኩል ተደጋግሞ ስለሚመታ በጣም ይደምቃል፡፡
ምሥጢሩም፡- መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው የእለተ ዐርብ መከራው እጥፍ ድርብ ቢሆንም በዘንግ ራስ ራሱን እየደበበደቡ ‹‹መኑ ኮርዓከ፣ መኑ ጸፍዓከ›› ሲሉት ነበርና በዘንግ መመታቱን ለማስረዳት ነው፡፡ ከቁም ቀጥሎ መሆኑም የጌታ መደብደቡ መገረፉ ከፍርዱ በኋላ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ በዚያውም ላይ መረግድ ደረባ አለው ‹‹መጠውኩ ዘባንየ ለቅስፈት ወመልታህቴየ ለጽፍዓት፤ ጀርባየን ለግርፋት ጉንጨን ለጽፋት ሰጠሁ›› ኢሳ 53 ያለው የነቢይ ቃል መድረሱን ለማስረዳት ፍርዱ እጥፍ ድርብ ነበርና መላልሰው ደራርበው ይጸነጽሉታል፡፡
2. ጽፋት፡-
ጽፋት ንዑስና ዐቢይ ተብሎ በሁለት ይከፈላል ንዑስ ጽፋት በጣም ፈጣን ጽፋት ሲሆን በመካከሉ በዐቢይ ጽፋት ያሳርፉታል፡፡ ብዙ ጊዜ ከቁም ከመረግድ በኋላ ማኅሌቱ የሚጠናቀቀው በጽፋት ነው በተለይማ ማኅሌቱ በሰላም የሚጠናቀቅ ከሆነ ያለ ጽፋት አይጠናቀቅም፡፡ በእርግጥ ሰላም የሌለው ማኅሌት የለም ዓመት እስከ ዓመት የሚቆመው ማኅሌት ከብርሃን፣ ስብከት፣ ኖላዊ፣ ዘመነ ጽጌ በስተቀር የሚጠናቀቀው በሰላም ነው በዘመነ ጽጌም ቢሆን በታች ቤት ባህል ነው እንጅ በላይ ቤት ከማኅተ ጽጌ ቀጥለው ከመዝሙር በፊት ምልጣን ስለሚመሩ ሰላም ይኖራቸዋል ሰላም የማያቀርቡበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲገልጡት በብሉይ ኪዳን የነበረውን አገልግሎት ለማስታዎስ ነው ይላሉ በዚያ ክፉ ዘመን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ ሳይፈጸም ሰላማችን ክርስቶስ ሳይወለድ ምን ሰላም አለና ሰላም ይጸፋሉ፡፡ ጽፋት ማለት ጸናጽሉም ከበሮውም ፈጠን ፈጠን ብሎ የሚቀርብ ነው፡፡
ምሥጢሩም፡- በምሴተ ሐሙስ በጠባብ በር በሰፊ በር እያወጡ እያስገቡ ለመታረድ እንደ ሚያቻኩሉት በግ ያቻኩሉት ነበርና አባቱ አዳምን ለሞተ ሥጋ ለሞተ ነፍስ የሚነዱት አጋንንት እያጣደፉት ነበርና ወደ ሞት የወሰዱት ለካሳ ነው፡፡
3. አመላለስ
በአቡንና እስመ ለዓለም ጊዜ በወረብ ፋንታ የሚባል ነው፡፡ ዜማው ቀለል ያለና ብዙ ጊዜ ደግሞ ተመሳሳይ ነው፤ እንደ ወረብ ከበሮ ያሳዝላል፤ በአብዛኛው እንደ ወረብ አስረጋጭ አይኖረውም
ምሥጢሩም፡-
1. የሰው ልጅ አንድ ጊዜ ወደ ኃጢአት ሌላ ጊዜ ወደ ጽድቅ ሲመላለስ ጨለማና ብርሃን በሚመላለሱባት ዓለም የሚኖር ደካማ ፍጥረት ነውና አንተ ግን የሰውን ድካሙን የምታውቅ አምላክ ከመዓት ወደ ምህረት ከቁጣ ወደ ትዕግሥት ተመለስ ማለት ነው፡፡
2. ክረምትና በጋውን የሚያፈራርቀውን ብርሃናትን የሚያመላልሰውን ነፋሳትን የሚያነፍሰውን ማያትን የሚያፈሰውን ጌታ በመለኮታዊ ባሕርዩ እዚያ የሌለ ሆኖ ከዚህ ወደዚያ የማይወስዱት ሆኖ ሳለ በለበሰው ሥጋ ግን አንዱ ላይ የሚገኝ ሌላው ላይ የሚታጣ በመሆኑ ከሀና ወደ ቀያፋ ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ ያመላለሱትን ለመግለጥ ነው፡፡
4.ወረብ:-
ወረብ ምን አልባት በፆም አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ማኅሌታዊ አገልግሎት ጊዜ ወረብ ሊኖር ይችላል፡፡ ከበሮ የሚያሳዝል በአስረጋጭ የሚታጀብ በጸናጽል ተጀምሮ በጭብጫቦ የሚጠናቀቅ በመሆኑ የተማረውንም ያልተማረውንም ትኩረት ስለሚስብ ድምቀት ከሚታይባቸው አገልግሎቶች አንዱ ነው፤ ሊቃውንቱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የክርስቶስን ነገረ መስቀሉን በግልጥ የሚሰብክ አገልግሎት ነው፡፡
ሊቃውንቱ መቋሚያቸውን አንስተው በትክሻቸው ተሸክመው ወደ ቀኝ ቀደ ግራ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልብን ይማርካሉ አስረጋጮቹ በመካከል ከወዲያ ወዲህ እየተመላለሱ በተለይማ እንደ ላሊበላ ባሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት ከልብ ለሚመለከት ሰው በሰማይ እንጅ በምድር ያለ አይመስልም፡፡
ምሥጢሩ ግን የእለተ ዐርብ የክርስቶስ መከራውን ለመግለጥ ነው፡፡ በእለተ ዐርብ ከፊት ያለው ሲለቀው ከኋላ ያለው ይስበዋል በጀርባው ይወድቃል ከኋላ ያለው ሲለቀው ከፊት ያለው ይስበዋል በግንባሩ ይወድቃል መስቀሉን በትክሻው አሸክመው እንዲህ ከቀራንዮ እስከ ሊቶስጥሮስ ባለው ፍኖተ መስቀል ሲያነሡት ሲጥሉት አድረው ነበርና ሊቃውንቱም ወደ ፊት ወደ ኋላ እየተመላለሱ በትክሻቸው እንደ መስቀል መቋሚያቸውን ተሸክመው ወደ ቀኝ ወደ ግራ ወደ ፊት ወደ ኋላ እየተመላለሱ ከፍ ዝቅ ብድግ ቁጭ እያሉ ነገረ መስቀሉን በፍኖተ መስቀል እንደ ሚጓዙ አድርገው ያሳያሉ፡፡
0 comments:
Post a Comment