የቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያቀረበላትን ሰላምታ መሠረት በማድረግ እናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ዘወትር ድንግልን ሰላም ትላታለች ። ይህ የመልአኩ ገብርኤል ሰላምታ ሞት ለተፈረደበት ለሰው ልጅ ባሕርይ ግሩም ወንጌል (የምስራች) ነው ። ከዚህ የተነሣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ተዋሕዶን የሚሰብኩ ቅዱሳን “መጋቤ ሐዲስ” የመጀመሪያው ወንጌል ሰባኪ (መምህር) ይሉታል ።
ድንግል ማርያምንም በመልአኩ ሰላምታ ዘወትር ሰላም እንድንላት ሥርዓት ሠርተው አልፈዋል ከዚህ በማስከተል ሰላምታዎቹን በዝርዝር እንጽፋለን ።
ደስ ይበልሽ ሉቃ. 1 ፥ 28 ።
መልአኩ ወደ ድንግል ቀርቦ መጀመሪያ የተናገረው “ደስ ይበልሽ” በማለት ነበር ። ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው ። የምሥራች ማለት የደስ ደስ ማለት ነው ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት ድንግልን ደስ ይበልሽ አላት ። ይህ ለድንግል ማርያም ግሩም ጸጋ ነው ። ምክንያቱም የአዳም ተስፋ በእርሷ በኩል እንዲፈጸም እግዚአብሔር ወስኗልና ። ሞት የተፈረደበት በዘመናት እንዲያለቅስ ፣ እንዲፈርስ ፥ እንዲበሰብስ ፥አእምሮውን ንባቡን አጥቶ በሰው ትከሻ ተጓጉዞ ወደ መቃብር እንዲጣል የተፈረደበት የሰው ልጅ ባሕርይ ፣ በድንግል ማርያም በኩል ደስ ይበልህ ተባለ ። ስለዚህ የሰው ዘር በሙሉ የድንግል ደስታ ደስታው ስለ ሆነ “ምልዕተ ጸጋ ደስ ይበልሽ” እያለ ይዘምርላታል ። ድንግል የደስታ መፍሰሻ እንድትሆን በአልቃሻው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔር ወስኗልና ። በመሆኑም ድንግል ማርያምን ደስ ይበልሽ እያለች ቤተ ክርስቲያን የምታመሰግንባቸውን ቃላት እንመልከት ቅዱስ ኤፍሬም የመልአኩን ሰላምታ መሠረት በማድረግ “ተፈስሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት – የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ደስ ይበልሽ” (የሰኞ ውዳሴ ማርያም) “ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት – የመላእክት ተድላ ደስታቸው ጌታን የወለድሽ ደስ ይበልሽ” ወዘተ እያለ እመቤታችንን ሰላም ብሏታል እኛም በውዳሴው ደስ ይበልሽ በማለት ሰላምታ እናቀርባለን ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለድንግል ያለውን ክብር ሲገልጽ “እግዚአብሔር ቃል ነፍስን ሥጋን ከአንቺ ነሥቶ ሰው የሆነ ሙሽራ ከጫጉላው እንዲወጣ ከአንቺ የተገኘብሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ …የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂ ከአንቺ የተወለደ (የወጣ) ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ። እግዚአብሔር በብሩህ ደመና ሁኖ (ተጭኖ) ወደ አንቺ የመጣ በአንቺም ያደረ ምድር ቅድስት ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ፣ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ እግዚአብሔርን የወለድሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ፣ አማኑኤልን የወለድሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ… ወዘተ” በማለት ያመሰግናት እንደነበር ተጽፏል ። ሃይማኖተ አበው ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 252 ክፍል 26 ቊጥር 35-39
ቤተ ክርስቲያንም “ሙሐዘ ፍስሐ-የደስበታ መፍሰሻ” በማለት ታመሰግናታለች ። ቅድስት ድንግል ማርያም በመልአኩ ብሥራት በግብረ መንፈስ ቅዱስ ቃለ እግዚአብሔር ወልድን ከፀነሰች በኋላ “ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ – ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሤት ታደርጋለች” በማለት ደስታዋን በመዝሙር ገልጻለች ። ለድንግል ማርያም የሆነው ደስታ ሁሉ የሰው ልጆች ደስታ ነው ። በድንግል ማርያም በኩል ደስታ ለሰው ሁሉ ስለ ደረሰ ድንግል ማርያም የደስታ መፍሰሻ ናት ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የድንግል ማርያም ደስታ እንዴት ወደ ፍጥረት ሁሉ እንደ ደረሰ ሲገልጽ ጌታ ሲወለድ በጨለማ ለነበሩ እረኞች “እነሆ ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ” አላቸው ይለናል ወንጌላዊው ። ቅዱስ ጳውሎስም የድንግልን ልብ በደስታ በሐሤት የሞላው ክርስቶስ የእኛም ተድላ ደስታ መሆኑን ሲጠቁም “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ” በማለት ጽፎልናል ። ፊልጵ.4 ፥ 4 ።
ተፈሥሒ ተፈሥሒ እያለ ያመሰገናት ቅ/ኤፍሬም የድንግል ማርያም ደስታ የሰው ሁሉ መሆኑን ሲጽፍ “ተፈሣሕ ወተሐሠይ ኦ ዘመደ እጓለ እመሕያው እስመ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም ወመጠወ ወልዶ ዋሕደ ከመ ይኅየው ኩሉ ዘየአምን ቦቱ እስከ ለዓለም – በእርሱ የሚያምን ሁሉ እስከ ዘለዓለም ይድን ዘንድ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለሙን እግዚአብሔር ወዶታልና የሰው ልጅ ሁሉ ደስ ይበልህ” አለ ። እንዲሁም “ትትፌሣህ ወትትሐሠይ ኩሉ ነፍስተ ሰብእ – የሰው ልጅ ሰውነት ሁሉ ፈጽሞ ደስ ይላታል” አለ ። እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ድንግልን ደስ ይበልሽ የማይል በአዳም የተነጠቀው ተድላ ነፍስ በክርስቶስ ያልተመለሰለት ብቻ መሆን አለበት ። ድንግልን ደስ ይበልሽ ባልን ቊጥር እኛም የተድላ ደስታዋ ተካፋይ መሆናችንን ተገንዝበን በገብርኤል ሰላምታ ደስ ይበልሽ እንላለን ።
ሰላምታ “ጸጋን የተሞላሽ ሆይ!”፡-
መልአኩ ጸጋ እግዚአብሔር ላንቺ ምሉዕ ሁኗልና ደስ ይበልሽ በማለት አከበራት ። ፍጥረት ሁሉ እንደሚያውቀው የሰው ልጅ ከጸጋ እግዚአብሔር ተለይቶ ኀፍረቱን የሚሸፍንበት አጥቶ ይንገላታ እንደ ነበር ግልጽ ነው ። የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል ። እግዚአብሔርን አጥቷል ። ዔድን ገነትን አጥቷል ። ፍጹም ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቷል ። አሁን ግን በቅዱስ ገብርኤል በኩል የምንሰማው ከሰው ልጆች መካከል አንዷ ለሆነች ለሰው ልጆች የባሕርይ መመኪያ ለድንግል ማርያም “ጸጋን የተመላሽ” በማለት ሲያበሥራት ስንሰማ ያስደስታል ። ይህ ጸጋ በድንግል ማርያም ሳይወሰን ለፍጥረት ሁሉ ይደርሳልና ።
ድንግል ማርያም ምልዕተ ጸጋ ናት ። ጸጋውም ለፍጥረት ሁሉ ከተሰጠው ጸጋ ይበልጣል ። ከነቢያት ጸጋ የድንግል ጸጋ ይበልጣል። እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን ተናገሩ ። እርሷ ግን በጥበበ እግዚአብሔር እርሱን ወለደችው ። ከሐዋርያትም የድንግል ጸጋ ይበልጣል እነርሱ ከእርሷ የተወለደውን ኢየሱስን ለፍጥረት ሰበኩ እርሷ ግን ወልዳ አሳደገችው ። ከቤተክርስቲያን ጸጋ የድንግል ጸጋ ይበልጣል ለቤተ ክርስቲያን ልሳን ፥ ትንቢት ፥ ስብከት ፥… ተሰጥቷል ። ድንግል ባለቤቱን ፀንሳ ወለደችው ። በእርሷ በኩል የመጣው የእግዚአብሔር ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሁሉ ተሰጠ ። ኢስይያስ «ሕፃን ተወልደ ለነ ወልደ ተውህበ ለነ = ሕፃን ተወለደልን ወንድ ልጅ ተሰጠን» ። ኢሳ. 9 ፥ 6 ።
ኢየሱስ ክርስቶስን የሰው ዘር የተቀበለበት እጁ ድንግል ናት ። የሰው ልጅ ባሕርይም በድንግል ተጀምሮ በእርሷ ጸጋ የተሰጠው በመሆኑም የፍጥረት ሁሉ የባሕርይ መመኪያ እመ አምላክ ሆነች ።
ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ። ሉቃ 1 ፥ 28 ።
ሦስተኛው የሰላምታ ቃል እግዚአብሐር ከአንቺ ጋር ነው የሚል ነው በአዳምና በሔዋን በደል ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በረድኤት እንጂ በኩነት ከሰው ጋር ያልነበረ አምላክ በአዳምና በሔዋን በደል ከሰው የተለየ አምላክ አሁን ግን ከአንቺ ጋር ነው የሚለው ሰላምታ መንፈስን የሚፈውስ ነው ። አካል ዘእም አካል ፥ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ፥ ከአብ የተወለደ ወልድ ፥ ከድንግል ነፍስን ሥጋን መንፈስን ነሥቶ ስለ ተወለደ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ ከድንግል ጋር ነበር ። ከድንግል ጋር እንደ ሆነ የተነገረው የሰላምታ ቃል ለእኛም ጭምር ስለ ሆነ የመልአኩን ሰላምታ “እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ” እያልን ለድንግል ስናሰማ እኛም ደስ ይለናል ። ኢሳ. 7 ፥ 14 ።
ከድንግሊቱ የሚወለደው አማኑኤል ይባላል በተባለው መሠረት ሲወለድ አማኑኤል ተባለ ። አማኑኤል ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው ። ከድንግል ጋር የሆነ ጌታ ከእኛም ጋር ነውና ደስ ሊለን አግባብ ነው ። በስሙ ስንሰበሰብ ። ማቴ. 18 ፥ 2ዐ ። እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእኛ ጋር ነውና ። ማቴ.28 ፥ 28-29 ።
ይህም ብሥራት ለድንግል መነገሩ የድንግል ባሕርይ ባሕርያችን ነውና የእኛም ብሥራታችን ነው ። ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም “ዓቢይ ውእቱ ክብር ዘተውህበ ለከ ኦ ገብርኤል መልአክ ዜናዊ ፍሡሐ ገጽ ሰበከ ለነ ልደተ እግዚአ ዘመጽአ ኀቤነ” ማለትም “ወደ እኛ የመጣ የጌታን ልደት የሰበክልን ፍሡሐ ገጽ መልአክ ገብርኤል ሆይ ላንተ የተሰጠህ ክብር ታላቅ ነው” ማለት ነው ። ኤፍሬም “ሰበከ ለነ” ማለቱ ልደቱ ፣ ብሥራቱ የሰው ልጅን ሁሉ እንደሚመለከት ለመግለጽ ነው ። ከድንግል የተወለደው ልዑል አምላክ ከእኛ ጋር ነውና ደስ ይበለን እኛም ድንግልን “እግዚአብሔር ምስሌኪ” እያልን ሰላም እንበላት ። በሌላም ገጽ ቅ.ኤፍሬም የመልአኩ ቃል (ብሥራት) ለሕዝብ ሁሉ መሆኑን ሲገልጥ “ተፈስሒ እስመ ተወከፍኪ ቃሎ ለመልአክ ፍሥሐ ኲሉ ዓለም = የዓለሙን ሁሉ ተድላ ደስታ የመልአኩን ቃል ስለአመንሽ ደስ ይበልሽ” አለ ። ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ያድኅነነ እመዓተ ወልዳ ። አሜን ።
ተከታዩን ትምህርት በተከታዩ ሰንበት ከደብረ ታቦር በኋላ በሚውለው ሰንበት ይመልከቱ ።
«አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ» ሉቃስ 1 ፥ 28 ።
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ደስ ይበልሽ ካለ በኋላ የተናገረው ሰላምታ “የተባረክሽ ነሽ” የሚል ነበር ። የሰው ዘር በመጀመሪያዎቹ ሰዎች በደል ምክንያት “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ በጭንቅ ትወልጃለሽ … ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን በሕይወት ዘመንህ በድካም ከእርሷ ትበላለህ እሾህና አሜክላን ታበቅልብሃለች የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ ወደወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ተብሎ ተረግሞ ነበር ዘፍ. 3 ፥ 16-21 ።
ይህ ከባድ መርገም በሰው ሕይወት እንዲበዛና እንዲከሠት ምክንያት የሆነውን የአውሬውን ራስ የሚቀጠቅጥ ልጅ እንደሚወለድ ለአዳም እግዚአብሔር ቃል ገባለት ። ዘፍ. 3 ፥ 15-16 ።
ለአብርሃም ደግሞ በዘሩ የምድር አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ተስፋ ሰጠው ።ዘፍ. 12 ፥ 4 ።
ለይስሐቅም ለያዕቆብም ለአበው ሁሉ ይህ ቃል ኪዳን ተሰጣቸው ። በመጨረሻ ላይ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያስወግድ የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጥ ቡሩክ የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወለድባት ቅድስት ማርያም ቡሩክት ነሽ ተባለች ። ቡርክት ማለትም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት የበረከት እናት ማለት ነው ። የማኅፀንዋ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስም ቡሩክ ነው ፥ ቡሩክ ይባላል ። ሉቃስ 1 ፥ 42 ።
እርሱ ቡሩክ ሳለ ማለትም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ሁኖ ሳለ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሁኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ፣ ስለ እኛ በዕንጨት መስቀል ተሰቅሎ ከእርግማን አዳነን ። ገላ. 3 ፥ 13 ።
እግዚአብሔርም በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በምድራውያንና በሰማያውያን በረከት ባረከን ። ኤፌ. 1 ፥ 2-4 ።
ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለኛ ሲመጣ ከተባረከችው ድንግል የተወለደውን ቡሩኩን የማኅፀኗን ፍሬ አምኖ በመስቀሉ እርግማኑ የተወገደለት መሆኑን በእርግጠኛነት የተቀበለ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ” ብሎ ከሚጠራቸው ቡሩካን ጻድቃን ጋር ይቈጠራል ። ማቴ.25 ፥ 34)
ምእመናንና እመቤታችን፡-
ምእመናን እመቤታችንን ይወዷታል ፣ ያከብሯታል “ት“ትምክሕተ ኩልነ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ- አምላክን የወለድሽ እመቤታችን መመኪያችን ነሽ” እያሉ ያወድሷታል ። ምክንያቱም ግልጽ ነው አምላክን ፀንሳ ስለ ወለደች የሰው ልጆች የባሕርይ ትምክሕት የሆነውን ጌታ ስልተሸከመች፣ ኅብስተ ሕይወት የሕይወት እንጀራ ከእርሷ ስለተገኘ ፥ ብርሃነ ሕይወት ክእርሷ ስለወጣ ፥ ሐረገወይን ከእርሷ ስለ በቀለ ፣ ማየ ሕይወት ከእርሷ ስለ መነጨ ፥ እግዚአ አጋእዝት የእርሷ ልጅ ስልሆነ ነው ። በሌላም በኩል ከእግረ መስቀሉ ስለ ተሰጠቻቸው ምእመናን ይወዷታል።
በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን ሁላችን ድንግል እናታችን መሆኗን ልናምን ይገባናል ። እነኋት እናትህ ብሎ ለዮሐንስ ሲሰጥ ዮሐንስን ለመሰልን እናት ሁናናለችና ። እነሆ ልጅሽ ብሎ ዮሐንስን ሲሰጣትም ልጆቿ ሁነናልና ። ዮሐ. 19 ፥ 29 ።
ከዚያም በላይ በጸሎቷ ይማፀናሉ “ሰአሊ ለነ ቅድስት” በማለትም ጸሎቷን ይሻሉ “በእንተ ማርያም ጸዋሪትከ በእንተ ማርያም ሐፃኒትከ፣ በእንተ ማርያም ወላዲትከ” በማለት ይጸልያሉ ፣ ሕዋሳቶቿንም ማላጅ በማድረግ ስለ ተሸከመህ ስለማሕፀኗ ፣ ስለ ጠባሃቸው ስለ ጡቶቿ ፥ ስለ አዩህ ስለ ዐይኖቿ ፥ በፊትህ ስለ ፈሰሰው ስለ እንባዋ ይቅር በለን ይላሉ። አሜን ፥ ስለ እናቱ ይቅር ይበለን፡፡
ዕረፍተ ድንግል፡-
መተርጉማን አበው እንደሚተርኩት እመ እግዚአብሔር ጸባኦት ድንግል ማርያም በተወለደች በስልሳ አራት ዓመቷ በዘመነ ሉቃስ ጥር 2ዐ ቀን ዐርፋለች ። አበው ስለ ዜና ዕረፍቷ የሚተርኩበት ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም እንደ ገለጸው የድንግል ማርያም ዕድሜ 64 ሊሆን የቻለው ከወላጆቿ ጋር 3 ዓመት ፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት ፣ በቤተ ዮሴፍ 9 ወር፣ ከጌታ ኢየሱስ ጋር 33 ዓመት ከሶስት ወር፣ ከጌታ ሞት በኋላ በቤተ ዮሐንስ 15 ዓመት ስለ ተቀመጠች ዕድሜዋ ተገናኝቶ 64 ዓመት ይሆናል ። የእርሷን ስም የሚገልጹ የውዳሴ ድርሰቶችም በዕድሜዋ ልክ ተደርሰዋል ፣ ለምሳሌ የውዳሴ ማርያም ቊጥር 64 ነው ። የመልክአ ማርያም ቊጥርም 64 ነው ።
ጸሎታ ለማርያም ወሥእለታ ያድኅነነ እመዓተ ወልዳ ። አሜን ።
0 comments:
Post a Comment