• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 17 November 2015

    አሥሩ የማሕሌት ደረጃዎች ፪

    ስለቅኔ ማኅሌት ባለፈው ተነጋግረን አሥሩን የማኅሌት ደረጃዎች ለዛሬ ልንነጋገር ቀጠሮ ይዘን ነበር የተለያየነው ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እንዲህ እንቀጥላለን፡፡

    የብሉይ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ ላይ በመዝሙር እንዲያገለግል የተፈቀደለት ንጉሡ ዳዊት ነበር፤ የሚገርመው ነገር ለዚህ አገልግሎት ከተመደቡትና ቅብዓ ክሕነት ተቀብተው ከከበሩት ከሌዋውያን ይልቅ ዘፀ 40÷12 ነገዱና ሕዝቡ ከካሕናት ልዩ የነበረው እርሱ ለዚህ የተመደበ ነበር፡፡ በሃያ አራቱም ሰዓት ተመድበው ያለማቋረጥ ከሚያገለግሉ ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት መዘምራን ጋር እንዳንዱ በመሆን አሥር አውታር ባለው በገና በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ምስጋናን ያቀርብ ነበር፡፡

          ዛሬም በሐዲስ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ ለዚህ አገልግሎት የተመረጠው ያሬድ ምንም እንኳን እንደ ጥንቱ በነገድ የተከፋፈለ አገልግሎት ያላት ቤተ መቅደስ ባትሆንም በትምህርት ተቀባይነት ከሱ የሚሻሉ ሌሎች ብዙ ደቀ መዛሙርት እያሉ ምንም ከማያውቁ እረኞች እንዳንዱ የሆነውን ያሬድን እግዚአብሔር ለማኅሌታዊነት መረጠው፡፡ እንደ ንጉሡ ቅዱስ ዳዊት ሁሉ ከልቡ የሚያፈልቃቸውን የመዝሙር ቃላት አሥር ምልክት አውጥቶላቸው አሥር ደረጃ ባለው ማኅሌት ያቀርባቸዋል፡፡

    እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ለማየት ከቅኝት እንጀምራለን፡-

    1.   ቅኝት

    ቅኝት ማለት በቅኔ ማኅሌት የሚዜመውን የእለቱን ቃለ እግዚአብሔር ሊቃውንቱ ሁሉ በጋራ ከማዜማቸው በፊት ከሊቃውንቱ አንዱ የተፈቀደለት ሊቅ የእለቱን ቀለም እንዲቃኘው ይጋበዛል የሚቃኘው ሊቅ አንድ ጊዜ ብቻውን ከዘለቀው በኋላ ሌሎች መምህራን ተከትለው ይሉታል፡፡በዚህ ሂደት ቤተክርስቲያናችን ሁለት ምሥጢራዊ መልዕክቶችን ታስተላልፍበታለች

    1.1 ኃጢአት ወደ ዓለም የገባበትን መንገድ፡- ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በአንድ አዳም ቅኝት በልጆቹ ተቀባይነት ነው፡፡ በገነት ማኅሌት ውስጥ መምህሩ ሰይጣን እንዳስተማረው የሁላችን አባት አዳም በአብራኩ ውስጥ ያለን ፣ ነገር ግን ገና ያልተወለድን ልጆቹ እስክንሰማው እና መቀበል እንድንችል አድርጎ ቅኝቱን አዜመው፡፡ እኛም ተቀብለነው እሱ በቁም ዜማ ያዜመውን እኛ ልጆቹ ጸናጽልና መቋሚያ ጨምረንበት ማለትም እሱ በስህተት የሠራውን እኛ የድፍረት ኃጢአት ጨምረንበት እየተስማማን ስናዜመው ቆየን፡፡

    በዚህም ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል  ግርዶሽ የፈጠረው ኃጢአት ሁለት አይነት ስም ወጣለት ጥንተ አብሶና ምልዐተ ኃጢአት ተብሎ ይጠራል፤ ጥንተ አብሶ የሚባለው ዜማውን እንዲቃኝ የተፈቀደለት አዳም የቃኘው የመጀመሪያው ኃጢአት ነው ፡፡ እሱም የኃጢአት ሁሉ መሠረት ነው፤ ምልዐተ ኃጢአት የሚባለው አዳም የቃኘውን የኃጢአት ዜማ ተቀብለው ያቀነቀኑ ልጆቹ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ አንድ ሆነው የሠሩት ኃጢአት ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው እንዲሆን ምክንያት የሆኑት እነዚህ ሁለቱም ኃጢአቶች እንደ መሠረትና ግድግዳ ሆነው ነው፡፡ ኃጢአትን ከሥር መሠረቷ አጠፋልን ስንል እነዚህን ሁለቱንም የውሉድንና የአበውን ኃጢአት አጠፋልን ማለታችን ነው፡፡

    1.2 የክርስቶስን የመያዙን ነገር፡- ክርስቶስ በተያዘባት በዚያች የመከራ ምሽት እንዲያው አይሁድ ተነባብረው የያዙት አይደሉም፤ የሚቃኝላቸው ይሁዳ ያስፈልጋቸው ነበር እንጅ፡፡ በእርግጥ እለት እለት በቤተ መቅደስና በምኩራብም ጭምር እየተገኘ የሚያስተምራቸው ቢሆንም ቅሉ እያወቁት የሚያስይዛቸው ፈለጉ፡፡ ለምንድነው ግን አያውቁትም ነበርን? ያሉ እንደሆነ ነገሩ እንደዚያ አይደለም፤ እንኳን በጥብቅ የሚፈልጉትን ክርስቶስን ይቅርና ከሱጋር አብሮ የነበረ ጴጥሮስን እንኳን አውቀውታል፤ ክርስቶስንማ እንዴታ፡፡ ነገር ግን ያለ መሪ እንዳይዙት ምሥጢረ እግዚአብሔር ከለከለቻቸው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን አባታችን አዳምን ሲያስተው እባብን መሪ አድርጎ መጥቷል እንጅ ብቻውን የመጣ አይደለም እንደዚሁም ሁሉ ክርስቶስ በመሪ ሲያዝ እንመለከተዋለን፡፡

    ስለ አዳም ፋንታ ተላልፎ ሊሰጥ የመጣው ጌታ አዳም የተጎዳበትን መንገድ ሊገልጥ በሚችል ፍኖተ ምሥጢር እንደሄደ ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችንም ክርስቶስ የተያዘበትን መንገድ ሊገልጥ በሚችል መንገድ አገልግሎቷን ታቀርባለች፡፡ ይሄውም ልማድ ነው፡- ክርስቶስ የአዳም ቤዛ በመሆኑ አዳም በወደቀበት መንገድ ተጉዞ ፈለገው፤ ቤተ ክርስቲያንም ራሷ ክርስቶስ ነውና ክርስቶስን ፍለጋ እሱ በተጓዘበት ስትጓዝ ትኖራለች፡፡

     እናም ሊቃውንቱ የሚያውቁትን ቀለም እንደማያውቁት ሆነው ዝም ይሉና ከነርሱ አንዱ እንዲቃኘው ያደርጋሉ፡፡ የሚቃኘው ሰው እባብ በመጀመሪያው አባታችን ላይ፣ ይሁዳ በክርስቶስ ላይ ያደረጉትን የስህተት ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ስዕላዊ በሆነ መንገድ የሚያሳይ ነው፡፡ኃጢአት በአንድ ሰው ተቃኝቶ እንደ ገባ ጽድቅ ክርስቶስም በአንድ በይሁዳ ምክንያት መቃኘቱንና በአይሁድ እጅ መግባቱን ለመግለጥ አስቀድሞ የእለቱ ዜማ በአንድ ሰው እንዲቃኝ ይደረጋል፡፡

    2.   መቀበል፡-

    ዜማው ከተቃኘ በኋላ ሊቃውንቱ አንድ ሆነው በአንድ ድምጽ ይቀበሉታል፤

    ይህም የሆነው፡-

    ጌታችን በይሁዳ እጅ ተላልፎ ስለመሰጠቱ፡- ይሁዳ አይሁድን አስከትሎ ሲሄድ ‹‹ዘእስእሞ ውዕቱ ኪያሁ አሀዙ፤ የምስመው እርሱ ነው ያዙት›› ማቴ 26÷48 ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ነበርና ሂዶ ከሳመው በኋላ ነበር አይሁድ ተነባብረው የያዙት፤ ይህን ድርጊታቸውን ሊገልጥ በሚችል ሁኔታ ሊቃውንቱም አንዱ የቃኘውን ቃለ እግዚአብሔር መልሰው ይቀበሉታል፤ ይሁዳ አስያዘህ አይሁድም እንዲህ ተነባብረው ያዙህ ስትል ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስን መከራውን እያሰበች ትኖራለች

    በዚያውም ላይ አይሁድ ከይሁዳ እጅ ሲቀበሉት፤ ይሁዳም ሲያስይዛቸው ሞቶ የሚቀር መስሏቸው ነው እኛ ግን ዛሬ ይህን ስናደርግ በሕይወታችን ለዘለዓለማዊ ተዋሕዶ የተቀበልነው ነው ስንል ቃለ እግዚአብሔሩ በሊቃውንቱ ልብ ሳይጠፋ ተዋሕዷቸው ይኖራል፡፡

    3.   መምራት፡

     መምራት የሚባለው በቅኔ ማኅሌት ሕግ ከማኅሌቱ መጀመር ጀምሮ የሚባለውን የእለቱን ቃለ እግዚአብሔር ሃሌታ ያለውን በሃሌታ፤ ሃሌታ የሌለውን ደግሞ ከመጀመሪያው እየጀመረ አንዳንዱን እስከመጨረሻው እየዘለቀ፤ አንዳንዱን ደግሞ እንደ ሕጉና እንደ ሥርዓቱ ጀምሮ በዙሪያው ያሉት ሊቃውንት እንዲቀበሉት ያደርጋል፡፡ የቅኔ ማኅሌት መሪነት በሁለት መንገድ ይፈፀማል

    ሀ/ ከሊቃውንቱ ተረኛው ወይም በሊቃውንቱ የተፈቀደለት

    ለ/ ከሊቃውንቱ ትልቅ የሆነው ተመርጦ እንዲመራው ይደረጋል፤ ብዙ ጊዜ እንደ አንገርጋሪ ያሉ ምራቶች ለታላላቅ ሰዎች የሚሰጡ ናቸው፡፡

    ያሬዳውያኑ በዚህ ሥርዓተ ማኅሌት ውስጥ ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልዕክት

    3.1 ክርስቶስን እንዲገሉት መሪ የሆናቸውን ቀያፋን ለማመልከት ነው፡፡

    ክርስቶስ የተሰቀለበት ዓመት ተረኛው ሊቀ ካሕናት ቀያፋ ነበር ክርስቶስ እንዲገደል ለሕዝቡ ምክር ከመስጠት ጀምሮ የመሪነቱንም ሥራ የሠራው እርሱ ነው ‹‹ቀያፋም አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ሊሞት ይሻላል›› ዮሐ 1814፡፡

     ሕዝቡን ብዙ ጊዜ እያባበሉ እሽ በጀ ያሰኟቸው የነበሩ ካሕናቱና የሕዝቡ አለቆች ናቸው ማቴ 27÷20

     ለዚህም ይመስላል አባቶቻችን ለመሪነት ከአበው መካከል ታላቁን መርጠው እንዲመራ የሚያደርጉት፡፡ የደብሩ ወይም የገዳሙ አስተዳዳሪ ካለ ምራቱ ለሌላ ሰው አይሰጥም፡፡

     የክርስቶስ የመከራውን ነገር የመራው የካሕናቱ አለቃ ቀያፋ ነበርና ያንን ለማስታዎስ ነው፡፡ መሪው በእጁ መስቀል ይዞ ነው የሚመራው፡- በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ክርስቶስ እንዲሞት ቁርጥ ምክርን በመከረው በቀያፋ ምክንያት መስቀል ተሸክሞ መታየቱን የምትገልጥበት መንገድ ከመሆኑም በላይ እንደታዘዘችው ማቴ 16÷24 ለዘለዓለም መስቀሉን ተሸክማ እንደምትኖር ለዓለም የምትመሰክርበት አገልግሎቷም ነው፡፡

     ከቀያፋ ቀጥለው ሕዝቡ ሁሉ ይሰቀል፣ ይሰቀል ማለታቸውን ለመግለጥ ከመሪው ተቀብለው ሁሉም ሊቃውንት ያዜሙታል ይሰቀል ብለው የጮሁትን ጩኸት ወደ ምስጋና ለውጦልን ‹‹በመስቀሉ …አግብኦ ለብዕሲ ዳግመ ውስተ ገነት፤ በመስቀሉ የሰውን ልጅ ዳግመኛ ወደ ገነት አስገባው›› ብለን እነሱ በምሬት የጮሁትን ጩኸት እኛ በምስጋና እንጮኸዋለን፡፡

     ያኔ የነበረው ሕዝብ የባርነት ኑሮ ስለመረረው ይጮሀል እኛ ደግሞ ስለተደረገልን ነገር እናመሰግናለን፡፡

    3.2 መሪው የአዳም ምሳሌ ነው፡-አባታችን አዳም የተገባለት የቃል ኪዳን ሰዓት እንደደረሰ ሲያውቅ በሀፍረት አንገቱን በደፋባት በዚያች እለትና ሰዓት በእለተ ዐርብ በሲኦል ውስጥ በአፀደ ነፍስ በነፍሳት መካከል ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት›› ብሎ ዘመረ፤ እንዳይፈራ በእግዚአብሔር ፊት ፈሪ እንዲሆን ያደረገው ኃጢአቱ ተወግዶለታል፣ እንዳያፍር ኃፍረቱን ሊያስወግድለት ልጁ ክርስቶስ በሱ ፋንታ ራቁቱን ያለ ሀፍረትን በአደባባይ ታይቶለታል፣ እንዳይሸሽ እዳው ተከፍሎለታል ስለዚህ እንዳይዘምር ማን ይከለክለዋል፡፡ ለቅሶ በጀመረባት በዚያች ሰዓት መልሶ እንደገና በእግዚአብሔር ምህረት ለምስጋና ልጆቹን ቀሰቀሰባት፡፡ ተንሥኡ ለጸሎት ብሎ የጀመረውን ዜማ ልጆቹ ሁሉ ተቀብለው ‹‹እግዚኦ ተሣሀለነ›› አሉት

          ይህን ለመግለጥ ቤተ ክርስቲያናችንም መሪው አስቀድሞ ያለውን ቀለም ሊቃውንቱ ይቀበሉታል፡፡ በማኅሌቱ እንዲህ ሲሉ ሊቃውንቱ ያድሩና የቅዳሴው ጊዜ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹ በቅብብሎሽ ያሰሙትን ጩኸት ሰምቶ ፈጥኖ ደርሶ ‹‹ሰላም ለኩልክሙ›› የሚለውን የምሥራች ያሰማበትን ሰዓት ይመስልልናል፡፡ ያ ሰዓት ሕዝቡ ክርስቶስን አይተው የተፅናኑበት ሰዓት ነበር ይህም የቅዳሴው ሰዓት ክርስቶስ በመሰዊያው ላይ ቀርቦ የሚሰጥበት ሰዓት ነው፤ ያ ሰዓት የመጨረሻው የዕርቅ ሰዓት ነበር ይህም የቅዳሴ ሰዓት የመጨረሻው የዕርቅ ሰዓት ነው፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱን ማኅሌታቸውን የሚያደማድሙት ሰላሙን ብለው ነው ሰውና እግዚአብሔርን አስታርቆ ሰላምን የሚፈጥረው የመሥዋዕቱ ጊዜ ደረሰ ማለታቸው ነው፡፡ 

                    ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አሥሩ የማሕሌት ደረጃዎች ፪ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top