• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 17 November 2015

    Cana The Gelila /ቃና ዘገሊላ

    የቃና ዘገሊላ አጭር ታሪክ፦

    ቃና ዘገሊላ ከጥምቀት በኋላ በማግሥቱ ማለትም ጥር 12 ቀን የሚውለውን በአል የምንጠራበት ስም ነው። ትርጉሙን በተመለከተ ግን ቃና ዘገሊላ ማለት ሁለቱም ቃላት (ቃና እና ገሊላ) የቦታ ስሞች ሲሆኑ  ቃና ዘገሊላ ማለት ወይም ስንል በገሊላ ውስጥ የምትገኝ ቃና የተባለች ቦታ ወይም ከተማ ማለት ሲሆን በዚች ቦታ የተፈጸመውን ታሪክ የምናስብበት ዕለት ነው።

    ይህ ቦታና ይህ ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለዓለም ያሳየበትና አምላክነቱንም የገለጸበት ዕለት ነው። ታሪኩንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደሚከተለው ጽፎታል።

    “ በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤  ኢየሱስም ደግሞደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።  የወይንጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅእኮ የላቸውም አለችው። 

    ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።  እናቱምለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉአለቻቸው።  አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻትልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠውነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራይይዙ ነበር።  ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸውአላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። 

    አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ሰጡትም። 

    አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤  ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤  አሳዳሪውሙሽራውን ጠርቶ።  ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥  ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን  የወይን ጠጅ እስከአሁን አቆይተሃል አለው።

    ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃናአደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱምበእርሱ አመኑ ”። ዮሐንስ 2፡ 1-11

    ቃሉ እንደሚለን ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም፤ ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ዚህ ሰርግ ቤት ታድመው ወይም ተጋብዘው ስለነበረ በዚያ ተገኝተዋል።  ሆኖም ግን ባለሠርጎቹ እንደ ሰውነታቸው  ጥሪ ቢያስተላልፉም  ሁኔታው ግን አምላካዊ እቅድ ነው።

    በዚህ ላይ ግን ማተኮር የምንፈልገው

    በእመቤታችን፤ በጌታ እና ሠርጉን በደገሱት ሰዎች መካከል በተካሄዱት ውይይቶች እና በውጤታቸው ላይ ይሆናል።

    1.      ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ወደ አምላኳና ወደ ልጃ በመሄድ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለቺው

    2.     ጌታም አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገናአልደረሰም አላት።  

    3.     እመቤታችንም ተመልሳ  የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው
    4.     ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው።

    5.     ሰርገኞቹ እመቤታችን በነገረቻቸው መሠረት ጌታ ያላቸውን አደረጉ

    6.     ውሃውም የወይን ጠጅ ሆነ

    አሁን በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚታየው በማላጅና በተማላጅ መካከል የተካሄደ የምልጃ ክንውን ነው

    ማላጅ ማለት ሁለት ክፍሎችን የሚያስታርቅ፤ ወይም ከተማላጁ አንድ ነገርን ጠይቆ ለሚማልድለት ክፍል መስጠት፤ ወይም የምልጃውን ውጤት ለሚማልድለት ክፍል ማድረስ ነው።

    ተማላጁ እሽ ካለ እሽታውን እንቢ ካለም እንቢታውን ለሚማልድለት ክፍል ያደርሳል። በመሆኑም እመቤታችን ልጇና አምላኳ ልመናዋን ተቀብሎ እንደሚፈጽምላት በአምላካዊ ትበቡ አስታውቋታል፤ ማለትም ልመናዋን ተቀብሏል፤ በመሆኑም ያቀረበችለትን የምልጃ ልመና ለመፈጸም ለሠርገኞቹ የሚያዛቸውንም ጭምር ታውቅ ስለነበረ  ወደ ሠርገኞቹ ተመልሳ “የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው። እርሱም (ጌታም) እመቤታችን  እንዳለቺው አንድ ነገርን አላቸው ይኸውም  “ ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸውየሚል ነው ”

     እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ልጇና አምላኳ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልመናዋን እንዳልተቀበላት ብታውቅ ኖሮ የሚላችሁን አድርጉ ሳይሆን ልትል የምትችለው እንዳልተቀበላት መናገር ወይም ዝም ማለት ነበር ። በመሆኑም በእመቤታችን ምልጃ መፈጸሙን የምናውቀው

    ለጌታ ምልጃዋን ወይም የሚፈለገውን ነገር ጠቅሳ በመናገሯ፤

    ተመልሳም ለሰርገኞቹ የሚላችሁን አድርጉ በማለቷ፤

    ጌታም ልክ እሷ እንደተናገረች “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” በማለቱ እና

     ከሁሉም በላይ ያቀረበቺው የምልጃ ጥያቄ ሳይለወጥ በሥራ ላይ መዋሉ ወይም መፈጸሙ ነው። ባይቀበላት ኖሮ ግን ያቀረበቺው ጥያቄ የለመነቺው ልመና ሳይቀየር እርሱው ራሱ አይፈጸምም ነበር። ማለትም የለመነቺው ሰርገኞቹ ወይን እንዲያገኙ ነበር ያንኑ አደረገላቸው።

    አምላካችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ስለናቱ ስለቅድስተ ቅዱሳን ስለወዳጆቹ ቅዱሳን ሁሉ ብሎ በደላችን ይቅር ይበለን፤ የንስሐ ዘመን ይጨምርልን፤

    ከአባታችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሳንወጣ በፈቃዱ እና በትእዛዙ መመራት እንድንችል፤

    በስማችን ብቻ ሳይሆን በሥራችን፤ በጠባያችን፤ በአጠቃላይ በሕይወታችን ሁሉ የአባታችንን ፈለግ ለመከተል እንበቃ ዘንድ አባታችንና አምላካችን ጽናቱን ይስጠን።

    እኛም እንደ ሰውነታችን ድካም ቢበዛብንም ወድቀን የምንቀር ሳንሆን ፈጥነን የምንነሣ፤ በንስሐ የምንመለስ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምናደርግ መሆን ይጠበቅብናል። በዚህ ጊዜ ተስፋችን ይበዛል፤ ከሁሉም በላይ በዘላለም መንግሥት ድሆች ሳንሆን ሐብታሞች እንሆናለን፡

    በፈቃዱ  ከተጓዝን የአባታችን የሆነው ሁሉ የእኛ ስለሆነ የማያልፈውን የአባታችንን መንግሥት፤ የማያልቀውን የአባታችንን ሐብት የመውረስ መብት ይኖረናል።

    ለአባታችን የማንታዘዝ፤ በባሕርያችን፤ በሥራችን በሕይወታችን ሁሉ አባታንን የማንመስል ከሆን ግን አባታችን ያለውን ሁሉ  የመውረስ መብታችንን ሊነፍግገን ይችላል። መልካም ልጅና ለአባቱ የሚታዘዝ ልጅ እንጅ የተወለደ ሁሉ የወላጁን ሐብት የመውረስ መብት አይኖረውም። ማለትም በ40 ወይም በ80 ቀናት ወይም ከዚያም በላይ ባለው ዕድሜ የተጠመቀ ሁሉ ሳይሆን ጥምቀቱን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያስመሰከረ ብቻ የጸጋው ተካፋይ የምንግሥቱም ወራሽ ይሆናል።

    በመሆኑም በክርስቲያናዊ ሥነምግባር ጸንተን በአምላካችንና በአባታችን በመድኃኔ ዓለም ፈቃድ ኖረን የአባታችንን መንግሥት ለመውረስ እንበቃ ዘንድ የአምላካችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፤ የንስሐ ጊዜንም ጨምሮልን ለሚቀጥለው ዓመትም ይህንን በአል ለማክበር ያብቃን ።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    አሜን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: Cana The Gelila /ቃና ዘገሊላ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top