የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views:
(ክፍል ሁለት)
1. ተአምራት ማድረግ የምን ውጤት ነው?ተአምራት ማድረግ ከሁለት ነገሮች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከመንፈሳዊ ብቃትና ከሰይጣን አሠራር፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የበረታ ሰው መንፈሳዊ ብቃቱ በሕይወቱ በሚገለጡ ተአምራት ሊታወቅ ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የምናገኛቸው ቅዱሳን በገድል ተቀጥቅጠው፣ ሰማዕትነት ከፍለው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሚገባ ተጉዘው ዲያብሎስን ድል ሲነሡት በሕይወታቸው ውስጥ ተአምራት ይገለጣሉ፡፡ ይህም ማለት ተአምራት የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ ነው ማለት ነው፡፡ የተአምራት ስጦታ እንዲሁ በድንገት አይገለጥም፡፡ በዚያ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እያደገ፣ እየተገለጠና እየተመሰከረለት በሚመጣ መንፈሳዊ ዕድገት ምክንያት እንጂ፡፡ ለዚህ ሁለት ምሳሌዎች እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ አራት ምዕራፍ ያለው መንፈሳዊ ዕድገቱ በየዘመናቱ ተገልጦልናል፡፡ በፍኖተ ደማስቆ መመለሱ(የሐዋ8)፤ በአንጾኪያ በሱባኤ መኖሩ(የሐዋ13)፣ ለአገልግሎት ተጠርቶ ከበርናባስ ጋር መውጣቱ እና ከአረማውያን፣ ከአይሁድና ከመናፍቃን ጋር ባደረገው ተጋድሎ የምናገኘው በትምህርትና በተአምራት የተገለጠ ሕይወቱ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ቀስ በቀስ እያደገ (ወየሐውር እም ኃይል ውስተ ኃይል እንዲል) የመጣ ነው፡፡
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወት በመንፈሳዊ ትምህርት፣ በአካባቢያዊ ተጋድሎ፣ ገዳማትን በመሳለምና በመማር፣ ወንጌልን ለአረማውያን በማስተማር እየተገለጠ የመጣ የማያቋርጥ መንፈሳዊ ዕድገት የነበረው ነው፡፡ ክርስትና ድንገቴ ሊሆን አይችልም፡፡(ለዚህ salvation in a moment የሚለውን የአቡነ ሺኖዳን ትምህርት መስማቱ ወይም ማንበቡ ይጠቅማል) ለዚህ ነው ቅዱሳን የነፍሳቸው ቅድስና በሥጋቸው፣ የሥጋቸው በልብሳቸው፣ የልብሳቸው በጥላቸው፣ በመንበራቸው፣ በነኩት ነገር ሁሉ ተገለጠ የምንለው፡፡
ዛሬ የምናያቸው አጥማቂ ወይም ፈዋሽ የሚባሉ ሰዎች መገለጣቸው ድንገቴ ነው፡፡ የታወቀ፣ እያደገ የመጣና የተመሰከረለት መንፈሳዊ ሕይወት አናገኝባቸውም፡፡ እንዲህ ነበሩ እንዲያ ነበሩ እያሉ ተከታዮቻቸው የሚያወሩላቸም ዛሬ ራሳቸው የነገሯቸውን እንጂ ትናንት በነበረው ሕይወታቸው አያውቋቸው፡፡ እነርሱም ያወቋቸው ማጥመቅ ሲጀምሩ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የታወቀው በማስተማሩና በተጋድሎው ነው፡፡ ለቅዱስ ጳውሎስ ተአምራት ማድረግ የጸጋው መገለጫ እንጂ አዘውትሮ የሚያደርገውና ‹‹ኑ ላድርግላችሁ›› ብሎ ሕዝብ የሚሰበስብበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለማስተማር፣ ለመማርና ለገዳማዊ ተጋድሎ በሚሄዱበት ቦታ ሕይወታቸው በተአምራት ተገለጠ እንጂ ክርስትናን በአጥማቂነት አልጀመሩትም፡፡ እስኪ ከዚህ በፊት በመንፈሳዊ ሕይወቱ ወይም በገዳማዊ ተጋድሎው ወይም ሃይማኖትን ለመጠበቅ በከፈለው ዋጋው ወይም ደግሞ በኖላዊ አገልግሎቱ ያወቅነው፣ እግዚአብሔር ሕይወቱን በተአምራት የገለጠለት አንድ ‹የዘመኑ አጥማቂ ወይም ፈዋሽ› አለ? አንዳንዶቹ ከውትድርና እንደመጡ ማጥመቅ ጀመሩ፣ አንዳንዶቹም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ሞክረው የሚፈልጉትን ዕውቅናና ጥቅም ለማግኘት ሲያቅታቸው ወደ ‹ፈዋሽነት›› መጡ፡፡ አንዳንዶች ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ስለሰጣቸው ነው›› ይላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋኮ እንደ ጾታ ምን ሳናደርግ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሴትነትና ወንድነት ነው ሰው ለሆነ ሁሉ የተሰጠ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ያለው ተአምራት(ምትሐት) ግን የሰይጣን ሥራ መገለጫ ነው፡፡ ሰይጣን ሕዝቡን ከእውነተኛው መንገድ ለማስቀረት ምትሐትን ይጠቀማል፡፡ ይሄ ምትሐት ደግሞ የእግዚአብሔርን ስም እስከ መጥራት ይደርሳል፡፡
2. መንፈሳዊ ሕይወት ስንል በአራት መንገድ የሚገለጥ ተጋድሎ ነው፡፡ (1)በዚህ ዓለም በመኖር በተቀደሰ ጋብቻ ጸንቶ፣ በምክረ ካህን ተግቶ፣ በንስሐና በሥጋወደሙ እየኖሩ መንፈሳዊ ግዴታዎችን በመፈጸም (እንደ ቅዱስ ላሊበላና ቅድስት መስቀል ክብራ) (2) በገዳማዊ ሕይወት በመጋደልና በአጽንዖ በኣት(እንደ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ) (3)በክህነት ሕይወት እያገለገሉ ኖላዊ ኄር የሚያሰኝ አገልግሎት በመፈጸም(እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት ጸጋ ዘአብ፣ እንደ ግብጹ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ))ና (4)እምነትን ለመጠበቅ በሚከፈል ሰማዕትነት(እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ቅድስት አርሴማ)፡፡
አንድ ሰው በእነዚህ የሕይወት መንገዶች መጓዙን የሚያሳይ፣ እያደገና እየተገለጠ የመጣ ሕይወት ሳይኖረው ድንገት አንድ ቀን ተነሥቶ ሰይጣን አስወጣለሁ፣ ተአምር አደርጋለሁ የሚል ከሆነ ያ ከሰይጣን አሠራር ነው፡፡ በገድለ ተክለ ሃይማኖትና በገድለ አቡነ ፊልጶስ ላይ ማርያን የሚባሉ አስማተኞች በእሳት ውስጥ በመመላለስ፣ የሰዎችን የነገ ሕይወት በመተንበይ፣ አጋንንትን አዝዘው ድንቅ ነገር በማሠራት ይታወቁ ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ግን በተጋድሎና በጸሎት የእነዚህን ሰዎች አሠራር ድል ነሥተውታል፡፡ እነዚያ ማርያን ዛሬ ቢኖሩ ኖሮ ብዙ ተከታይ ይኖራቸው ነበር፡፡ ሲሞን መሠርይ ሮም ከተማ ላይ ሕዝቡን ተሰናብቶ ዐርጓል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ደርሶ በጸሎት ድል ባያደርገው ኖሮ ብዙ ተከታይ አፍርቶ ነበር፡፡
አንድ ሰው ስመ እግዚአብሔር ስለ ጠራ ብቻ የእግዚአብሔር ነው ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን ስለመጨረሻው ቀን ሲናገር ‹›በዚያን ቀን ብዙዎች፡- ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ተአምራትን አላደረግንምን ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላውቃችሁም፣ እናንተ ዐመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ››(ማቴ 8፣22) ብሎ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ሰዎች ብዙዎቻችን የማናደርጋቸውን ሦስት ድንቅ ነገሮች አድርገዋል፡፡ (1)ትንቢት መናገር፣ (2)አጋንንት ማውጣትና (3)ተአምር ማድረግ፡፡ ደግሞም እነዚህን የሚያደርጉት በክርስቶስ ስም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ‹በስምህ› ያሉት፡፡ ነገር ግን ጌታችን ‹ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን› አላላቸውም፡፡ ሦስት አስደንጋጭ መልሶች ለሦስቱ ክህደቶቻቸው ተሰጥቷቸዋል፡፡ (1)ከቶ አላውቃችሁም፣(2) እናንተ ዐመፀኞች፣ (3)ከእኔ ራቁ፡፡
ልክ ዛሬ ሽንጣችን ገትረን እንደምንከራከርላቸው ‹አጥማቂ ነን ባዮች› ትንቢት እየተናገሩ፣ ተአምራት እያደረጉ፣ አጋንንት እያወጡ? ለምን በጌታ ዘንድ ግን ዐመፀኞች ተባሉ፣ ለምን አላውቃችሁም ተባሉ፣ ለምንስ ከእኔ ራቁ ተባሉ፡፡ መልሱ ግልጥ ነው፡፡ ይኼ በምትሐት የመጣ የማስመሰያ ተአምር እንጂ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ምክንያት የተገለጠ ጸጋ አይደለም፡፡ ስለዚህም ሕዝብ ያውቃቸዋል እንጂ ክርስቶስ አያውቃቸውም፡፡
3. ታድያ እነዚህ ሰዎችኮ ፈወስን ይላሉ፤ አጋንንትም ሲናገሩላቸው እንሰማለን፣ በካሴትም ተሸጦ ገዝተን ሰይጣንን ሰምተናል፤ተፈወስን የሚሉም አሉ፡፡ እንዴት ነው? የእግዚአብሔር ጸጋ በተጋድሎ የምትገኝ ናት፡፡ ‹‹እንበለ መከራ ኢይትረከብ ጸጋ›› እንዲል፡፡ አንድ ሰው የተለየ መንፈሳዊ ሕይወት፣ የተለየም ተጋድሎ ከሌለው በቀር ዝም ብሎ ከሁሉ የተለየ ጸጋ አያገኝም፡፡ ለዚህም ነበር ቅዱስ ጳውሎስ በፍኖተ ደማስቆ ጌታ ከተገለጠለት በኋላ አንዴ ተገልጦልኛልና እፈውሳለሁ ብሎ ያልተነሣው፡፡ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጾም፣ ጸሎትና ቅዳሴ ያለበት ሱባኤ ይዞ ነበር(የሐዋ13)፡፡ ከዚህ በኋላ የምናየው የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት የዚህ ሕይወቱ መገለጫ ነው፡፡ ያም አልበቃው ብሎ ‹‹ራሴን እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ›› በማለት እንደነገረን በገድል ላይ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የታወቀ ነበር፡፡ በኋላም በተጋድሎው ጸና፤ እርሱ በደም ለመሰከረለት ቅዱስ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር በተአምራት ቅድስናውን መሰከረለት፡፡
አሁን የምናያቸው ‹‹እናጠምቃለን› ባዮች ግን ሥራቸው ማጥመቅ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ገዳም በእንዲህ ዓይነት ሕይወት ነበሩ ብሎ የሚመሰክርላቸው ገዳም፣ እዚህ አጥቢያ በክህነት እያገለገሉ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲህ ነበረ፣ ምእመናንን ለንስሐና ለሥጋ ወደሙ ሲያበቁ ነበረ፤ በመንፈሳዊ ሕይወት የበረቱ ብዙ ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው አፍርተው ነበረ ብሎ የሚመሰክርላቸው አጥቢያ፣ ወይም ሰማዕትነታቸው እንዲህ ሆኖ ከከሐድያንና ከመናፍቃን ጋር ተገልጦ ነበር የሚል የለም፡፡ በአንጾኪያ ሱባኤ ላይ አናውቃቸውም፣ ተአምራት ግን ያደርጋሉ፣ በጽላልሽ ሲማሩና ሲጋደሉ አናውቃቸውም፣ ፈውስ ሰጠን ይላሉ፡፡ በደብረ ጎልና በደብረ ሐይቅ አናውቃቸውም ተአምር አደረግን ግን ይላሉ፡፡ ይሄ ከሰይጣን ብቻ የሚመጣ ነው፡፡
4. ቅዱስ ጳውሎስ የሐሳዊ መሲሕን አመጣጥ ባስረዳበት ዐንቀጽ ‹‹የእርሱ መምጣት በተአምራት፣ ሁሉና በምልክቶች፣ በሐሰተኞች ድንቆችም በዐመጽ መታለል እንደ ሰይጣን አሠራር ነው›› ብሎ ነበር(2ኛ ተሰ. 2፣9)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ‹እንደ ሰይጣን አሠራር ነው›› አለ? ሰይጣን ሰውን ለማታለል ከፊል እውነት ስለሚያቀርብ፡፡ እኔ አላውቃችህም የተባሉት ተአምር አድራጊዎችም ትልቁ ችግራቸው ሕይወታቸው የዓለም ንግግራቸው የክርስትና ስለነበር ነው፡፡ ባለፈው የጠቀስናቸው የአስቄዋ ልጆች በንግግራቸው ‹‹ጳውሎስ በሚያስተምረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም›› እያሉ ነበር አጋንንትን ሊያወጡ የሞከሩት(የሐዋ. 19፣14)፡፡ አሠራራቸው ለጥቅም ቢሆንም የተናገሩት ግን ስሕተት አልነበረውም፡፡ ጳውሎስ የሚሰብከው ክርስቶስ ነው፡፡ በክርስቶስም ስም አጋንንት ይወጣሉ፡፡ይህንን ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹የሰይጣን አሠራር› ያለው፡፡ የሰይጣን አሠራር ማለት አንድን ስሕተት ትክክል እንዲመስል አድርጎ መሥራት ማለት ነው፡፡
ይህ እንዲሆን ለምን እግዚአብሔር ፈቀደ? ቅዱስ ጳውሎስ መልሱን ይሰጠናል፡፡ ‹‹ነገር ግን በዐመጽ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል(2ኛተሰ. 2፣12)፡፡ ንስሐ ላለመግባት፣ የዐመጽን ሥራ ላለመተው፣ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ሕይወት ላለመመለስ ባመጽን ቁጥር ሐሳውያን መሲሐውያን መላካቸው የማይቀር ነው፡፡ ‹‹ሐሰትን ያምኑ ዘንድ›› እንዳለውም እኛም ሐሰቱን ማመናችን አይቀሬ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለስሕተት አሠራር የሚጋለጡት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያልኖሩ፣ መንፈሳዊ ዕውቀት የጎደላቸው፣ ነገሮችን ሁሉ ከጥቅም ጋር የሚያገናኙና መንፈሳዊ ሕይወትን ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ደቀ መዝሙርነት እንጂ ተከታይነት አይደለም፡፡
ነቢዩ ሆሴዕ ‹ሕዝቤ ዕውቀት በማጣት ጠፋ››(ሆሴዕ 4፣6) እንዳለው የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ብሎም ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አለማወቃችን ከመንፈሳዊ ዕድገትና ለውጥ ይልቅ ተአምራትና ድንቅ ፈላጊ እንድንሆን እያደረገን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያችን ‹‹ራእይ እናያለን፣ አጋንንት እናስወጣለን፣ ተአምር እናደርጋለን የሚሉ መሰል ባሕታውያን ተነሥተው ነበር፡፡ ብዙ ሺ ሕዝብ ተከተላቸው፡፡ አብሯቸው በየገዳማቱ ዞረ፤ አሜሪካ ድረስ መጥተው ሲያጠምቁና ሰይጣን አወጣን ሲሉ ኖሩ፡፡ መጨረሻቸው ግን ለሁላችንም ግልጥ ነበር፡፡ ለራሳቸውም፣ ለእኛም ለቤተ ክርስቲያንም ሳይሆኑ ቀረ፡፡ የተከተላቸውም ሰው፣ ሰይጣን አስወጡልኝ ሲል የነበረውም ሰው ተመልሶ ወደ ጥንት ሕይወቱ ገባ፡፡ ዛሬም ይሄው ነው የተደገመው፡፡ ሞኝ ማለት በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ነው እንዲሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማስተማር፣ መቀደስ፣ ገዳማዊ ሕይወት፣ እንግዶችን መቀበል፣ ከመናፍቃንና ከሐድያን ጋር መጋደል የዘወትር ሕይወታቸው የነበሩ ቅዱሳን ነበሩ፣ አሉም፡፡ እያጠመቁ ሰይጣን ማስወጣት ብቻ ሥራቸው የነበሩ ቅዱሳን ግን የሉም፡፡ ይኼ የደቂቀ አስቄዋ ጠባይ ነው፡፡ ወይም በማጥመቅና ሰይጣን በማባረር ብቻ የሚታወቁ ቅዱሳን አልነበሩም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ስለሚያስተምሩ ነው የምንከተላቸው›› ብለዋል፡፡ አሁን ከዛሬ ጀምሮ ማጥመቅና ሰይጣን ማስወጣት አቁመናል ብለው ትምህርት ብቻ ቢያስተምሩ እውነት ትሄዳላችሁ? ቅዳሴ አስቀርቶ በየሜዳው ፈውስ ፍለጋ የሚያንጋጋን የትምህርት ፍቅር ነው?
እንዲያውም በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ኪዳን የተሰጣቸው የጠበል ቦታዎች ነበሩ እንጂ የታወቁ አጥማቂዎች አልነበሩም፡፡ በአካባቢው ያሉ ካህናት በቃል ኪዳን የጠበል ቦታዎች ተመድበው ያጠምቃሉ ወይም በአጥቢያቸው ለሚገኙ ሕሙማን ጠበል ይረጫሉ፡፡ ጌታችን ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ የላከውን ሰው ወደ መጠመቂያው እንጂ ‹‹እገሌ ወደሚባል አጥማቂ ሂድ›› አላለውም(ዮሐ.9፣6)፡፡ በቤተ ሳይዳም የእግዚአብሔር ምሕረት በመልአኩ በኩል ሲወርድ ሕሙማን ይፈወሱ ነበር እንጂ ‹እገሌ የሚባል ሰው ሲያጠምቅ ተገኘ› አልተባለም(ዮሐ 5)፡፡ ነቢዩ ኤልሳዕም ከሶርያ የመጣውን ንዕማንን ‹ሂድና በዮርዳኖስ ታጠብ(ተጠመቅ)› አለው እንጂ ‹እገሌ ያጥምቅህ›. አላለውም(2ኛ ነገሥት 5፣10)፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአቡነ ሐራ ድንግል፣ በቅዱስ ላሊበላ፣ በዋንዛዬ፣ በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት፣ በሸንኮራ ዮሐንስ፣ በጻድቃኔ ማርያም ታሪክ በጠበሉ እግዚአብሔር የሠራው ሥራ ተገልጧል እንጂ የአንድ የተለየ አጥማቂ ሥራ የለበትም፡፡ ታድያ ዛሬ ከየት አመጣነው? ከጠበሉ ወደ አጥማቂው መዞር፡፡
5. እጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ ‹ሰይጣን በመቁጠሪያ ሲደበደብ ይወጣል› የሚለው አስተምህሮ ነው፡፡ ይኼ አስተምህሮ ሁለት ስሕተት አለበት፡፡ የመጀመሪያው በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ለጸሎት ማስታወሻና ማንቂያነት የምንጠቀምበትን መቁጠሪያ ከሥርዓቱ ውጭ በመውሰድ ነገ የእነዚህ ሰዎች የስሕተት አሠራር እንደ ቀደምቶቻቸው ተጋልጦ ሲወድቁ ሕዝቡን መቁጠሪያ እንዲንቅ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች በጾምና በጸሎት፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና በመንፈሳዊ ሕይወት ሳይሆን ሰይጣን በጉልበት ይወጣል ብለው እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡
መቁጠሪያ አገልግሎቱ ለጸሎት ነው፡፡ በተለይም በየሰዓቱ እንዲያስታኩቱ የሚታዘዙት መነኮሳት ለጸሎት ማስታኮቻ ይጠቀሙበታል፡፡ ምእመናን ባለ መቁጠሪያ የሆኑት አሁን በኛ ዘመን ነው፡፡ አንድ ቅዱስ አባት ሲጸልይበት የኖረው መቁጠሪያ በረከቱ አደረበት ቢባል መልካም፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ በረከት በልብሱ ላይ እንዳደረው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በገፍ መቁጠሪያ ገዝቶ እያከፋፈለ በዚህ መቁጠሪያ ራስን በመግረፍ ሰይጣን ይወጣል ብሎ ያስተማረ፣ ሰይጣንንም በመቁጠሪያ ሲያወጣ የኖረ አንድም ቅዱስ የለም፡፡ እስኪ አምጡ? በየትኛው ገድል አገኛችሁት? ከየትኛው ቅዱስ ተማራችሁት? መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የሚወጣው በጾምና ጸሎት መሆኑን ያስተምረናል(ማቴ17፣21)፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቅዱሳን የባረኩት መቋሚያቸው፣ አጽፋቸው፣ ጸበላቸው ድውይ ሲፈውስ እንደነበር ይተርክልናል፡፡ ለመሆኑ የትኛው የዘመኑ አጥማቂ ነው በገድል ተቀጥቅጦ በረከቱን ለመቁጠሪያ ያተረፈው?፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹ከእኔ የተማራችሁትን፣ የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን፣ ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ››(ፊልጵ. 4፣9)ብሎናል፡፡ እኛ ከማንኛው ሐዋርያ፣ ከየትኛውስ ቅዱስ ነው በመቁጠሪያ መደብደብ የተማርነው፡፡
6. በሰይጣን መፈተንና በሰይጣን መያዝ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ አንድ ሰው በክርስትና ሕይወት ከኖረ፣ የጾምና የጸሎት ሕይወት ካለው፣ በቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት(በተለይ ምሥጢረ ንስሐና ቁርባን) ተሳታፊ ከሆነ ሰይጣን በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሰው አይፈተንም ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በልብሱ እራፊ አጋንንትን እያወጣ እርሱ ግን ከዲያብሎ በሚደርስበት ጉስማት ይሰቃይ ነበር(2ኛ ቆሮ. 12፣8)፡፡ ይህም በዲያብሎስ መፈተን ነው፡፡ ኢዮብ በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ግን አልነበረም፡፡ ‹‹ኢዮብ እንደታገሠ ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል›› በማለት ቅዱስ ያዕቆብ የገለጠውም ይኼንኑ ነው(ያዕ.5፣10)፡፡ አሁን ግን ሁሉም በሰይጣን ተይዟል፣ ተተብትቧል፣ እንዲያውም ገና በማለዳ ነው የተያዘው እየተባለ ነው፡፡ በሰይጣን ይሄ ሁሉ ሰው ከተያዘ ያውም በቁርኝት፣ ክርስትና ወዴት አለ? የተጠመቅነው ጥምቀት፣ የተቀበልነውስ ቁርባን ሥራ መሥራት አቆመን? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ከአጥማቂዎች በፊት ቤተ ክርስቲያን አልነበረቺም? ወይም ስታደርገው የነበረቺው ሁሉ ጥፋት ነበር ማለት ነው? ሰው ሊፈተን ይችላል፡፡ በዲያብሎስ ቁርኝት መልሶ ሊያዝ ግን አይችልም፡፡ ክርስትናውን ፈጽሞ ትቶ ‹እክህደከ ሰይጣን›› ባለበት ልቡ ‹‹እክህደከ ክርስቶስ›› ካላለ በቀር፡፡ ምእመናን የበረከት ጥምቀት የሚያስፈልጋቸው በመንፈሳዊ ተጋድሏቸው ውስጥ የሚደርስባቸውን ፈተና ለመዋጋት አንዱ የመውጊያ መንገድ ስለሆነ እንጂ ያለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ከሰይጣን ነጻ ለመሆን አይደለም፡፡
7.በሰው ላይ በሁለት መልኩ ተአምራት ይታያል፡፡ አንዱ የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጥ፡፡ ይኼ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በእንስሳትም፣ በዕጽዋትም፣ በግኡዛን ነገሮችም ላይ ይገለጣል፡፡ የኤርትራ ባሕር የተከፈለው፣፡ በካይሮ አጠገብ የነበረው ተራራ(አል ሙከተም) በቅዱስ ስምዖን ጸሎት የተነሣው፣ የቢታንያ ድንጋዮች የተናገሩት፣ በእነርሱ ቅድስና አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ በሰዎችም ላይ እንዲሁ ሆኖ ያውቃል፡፡ ቀያፋ ስለ ጌታችን ሞት ትንቢት ተናግሯል(ዮሐ. 12፣49)፡፡ ይህ ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ላይ ተገለጠ እንጂ ከቀያፋ ሕይወት ጋር አይያያዝም፡፡ ቀያፋ እንደካደ ቀርቷል፡፡
ያለ መንፈሳዊ ሕይወት በሰው ላይ የሚገለጥ ተአምር ሰውዬውን አይጠቅመውም፡፡ የእግዚአብሔርን ክብር ግን ይገልጣል፡፡ ልክ የቢታንያ ድንጋዮች በመዘመራቸው እንዳልተጠቀሙት፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ክብር እንደገለጡት፡፡ ከዚህ ዓይነት ሰው የሚወጣ ሰይጣንም(ያውም ከወጣ) ተመልሶ ይገባል፡፡ ያውም ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንትን ይዞ(ሉቃ. 11፣24-27)፡፡ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ላይ አባታችን በአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እያሉ፣ አንድ በሽተኛ መጣ፡፡ የገዳሙ አባቶችም ሰይጣንን አስወጡት፡፡ ሕመምተኛውም ደኅና ሆኖ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ሰይጣን ግን መንገድ ላይ ጠብቆ ተመለሰበት፡፡ ልጁም ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና መጣ፡፡ አሁንም ሰይጣኑ ወጥቶ መልሶ ገባ፡፡ ይህንን ምሥጢር የተረዱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬም ወጣን የሚሉት አጋንንት ለጊዜው ሰውን አስደስተው ተመልሰው ይገባሉ፡፡ አጥማቂዎቹም አልበቁም፣ ደግሞም ተከታይ እንጂ ክርስቲያን አላፈሩምና፡፡ ለዚህም ነው በአንዱ ‹አጥማቂ› ዘመን ሰይጣን የወጣላቸው ሰዎች እንደገና ሌላ ‹አጥማቂ› ሲመጣ መልሰው የሚለፈልፉት፡፡ ሁሉም በመተታቸው ስለሚያስለፈልፉ፡፡
8. ሌላው አሳዛኝ ነገር ምሥጢረ ቀንዲል የነዚህ ‹አጥማቂ ነን ባዮች› መጨዋቻ መሆኑ ነው፡፡ በመጽሐፈ ምሥጢረ ቀንዲል እንደተገለጠው ምሥጢረ ቀንዲል የራሱ ጸሎት አለው፡፡ በአንድ ካህን ብቻም አይፈጸምም፡፡ ከዘይቱ ጋር የሚበራው መብራትም የሚበራበት የራሱ ሥርዓትና ጊዜ አለው፡ ሰባቱ መብራቶች በሰባቱ ጸሎቶች ጊዜ ይበራሉ፡፡ አሁን የምናየው ግን ሰዎች ይመጣሉ፣ ምሥጢረ ቀንዲል አይደገምም፣ የሚበራ መብራት የለም፣ የሚደርስ ኪዳን የለም፤ እንዲሁ ፣አጥማቂዎቹ› እየተነሡ ዘይት ያፈሳሉ፡፡ ይኼ ከማን ያገኘነው ሥርዓት ነው? ምሥጢረ ቀንዲል ያለ ምሥጢረ ቀንዲል ጸሎትና ሥርዓት ሲፈጸም ያየነውስ የት ነው? ከምሥጢረ ቀንዲል በፊትም የሚቀድም ሥርዓት አለ፡፡ መጽሐፈ ምሥጢረ ቀንዲል በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡ አንብቡት፡፡ ወይም የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን(በረከታቸው ይደርብንና) ‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን›› የተሰኘውን መጽሐፍ አንብቡ፡፡ አለበለዚያም ደግሞ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ያዘጋጁትን ‹ምሥጢራ ቤተ ክርስቲያን› የተሰኘውን ማስተማሪያም ተመልከቱ፡፡ አሁን የሚከናወነውን ‹የአጥማቂዎች› የዘይት ማፍሰስና ማጠጣት ሥርዓት የሚመስል ነገር ፈጽሞ በቤተ ክርስቲያን አልነበረም፡ ይህንን ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩ አጥማቂዎች ናቸው እንግዲህ ‹‹ድሮ እዚህ ተምረናል፣ ሰርተፊኬት ወስደናል›› እያሉ የሚያታልሉት፡፡ ታድያ የታለ ትምህርቱ በተግባር የተገለጠው?
9. ክርስትና ስለ ክርስቶስና በክርስቶስም ስለሚገኘው ድኅነት ማመንና መስተማር ነው፡፡ ስለ ቅዱሳንና ስለ ቤተ ክርስቲያን የምንማረውም ቅዱሳን የወይኑ ግንድ ቅርንጫፎች፣ ቤተ ክርስቲያንም የወይኑ እርሻ ስለሆነች ነው፡፡ የዘመኑ አጥማቂ ነን ባዮች ግን ብዙ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ስለ ሰይጣን በማስተማር፣ ሰይጣንን በማስለፍለፍና ሰይጣን ያለውን እየቀዱ በካሴት በመሸጥ ነው፡፡ ምእመናኑም ሰይጣንን ሰምተው ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ይጣላሉ፡፡ መተት፣ ድግምት፣ መድኃኒት ተደርጎብሃል/ሻል እያለ ስለሚነግራቸው፡፡ እስኪ የትኛው ሐዋርያ ወይም ቅዱስ ነው ይህንን ያህል ስለ ሰይጣን የሰበከን? ሰይጣን ገናና ሆኖ፣ ሁሉን የሚቆጣጣር ሆኖ፣ ምእመናንን እንደፈለገ ሃያ ሠላሳ እየሆነ እንደሚሠፍርባቸው ሆኖ እየተሰበከ ነው፡፡ መቼም ሰይጣን በሐዋርያትና በሠለስቱ ምእት፣ በሰማዕታትና በቅዱሳን አበው ያጣውን ቦታ እንደ ዘንድሮ ያገኘበት ዘመን የለም፡፡ ክርስትና ክርስቶስን ወድደን የምንከተለው እንጂ ሰይጣንን ፈርተን የምንከተለው አይደለም፡፡ በአእምሯችን ቦታ ሊኖረው የሚገባውም በመስቀል የተፈጸመልን የማዳን ሥራ እንጂ የሰይጣን ታሪክ፣ አሠራር፣ ትምህርትና ድንቅ ሥራ አይደለም፡፡ አሁን ግን ቦታውን የያዘው ሰይጣን ነው፡፡ ሰው መስማት የሚፈልገው ስለ ሰይጣን ነው፡፡ ስለ ክርስቶስ አይደለም፡፡
ማጠቃለያ
በነሐሴ 2007 ዓም በተደረገ አንድ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 432 የግል አጥማቂዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከአነዚህ መካከል ስማቸው የገነነ አምስት አጥማቂዎች አሉ፡፡ እስካሁን 7 መጻሕፍትንና ወደ 100 የሚጠጉ የሰይጣን ምስክርነቶችን በድምጽና ምስል ለቅቀዋል፡፡ በቅርቡ ዋና ዋና የሥራቸውንና የትምህርታቸውን ሐሳዊ መሲሕነት የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ይኖራል፡፡ ቸር ያሰንብተን፡፡
0 comments:
Post a Comment