• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 16 November 2015

    የተሐድሶን ምንነት ሳታውቁ፣ ስለ ተሐድሶዎች ማንነት አትጠይቁ!!


    ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም
    ክፍል አንድ

    በተሐድሶ ዙሪያ በስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ የተጻፉትን ጽሑፎች ከክፍል አንድ ጀምሮ ተከታትለን እናቀርብላችኋለን፡፡

    ስለ ነገረ ተሐድሶ ለመጻፍ የሚነሣ ሰው ከሚቸገርባቸው ጉዳዮች አንዱ€œከእንቅስቃሴው ውስጥ ምኑ ላይ ባተኩር አንባብያን ላይ የሚፈለገውን ግንዛቤ መፍጠር እችላለሁ€� የሚለው ነው፡፡ ስለ ታሪካዊ ዳራውና አመጣጡ፣ ስለ ምንነቱ፣ ስለእንቅስቃሴው መሪዎች ማንነት፣ ስለ ተሐድሶዎች€œአስተምህሮ€�፣ ከፕሮቴስታንት ጋር ስላለው አንድነትና ተመሳሳይነት (ልዩነት ስለሌለው) ወይስ ስለ ምን መጻፍ ቀላል፣ የሁሉንም ልብ የሚያኳኳ፣ ለመፍትሔው የሚያነሣሣ ይሆናል የሚለው የጸሐፊውን ልብ የሚያስጨንቅ ጥያቄ ነው፡፡ እኛም ከምኑ ጀምረን ወደ የት መሔድ እንዳለብን ብንቸገርም የእንቅስቃሴውን ምንነትና መገለጫ ሳያውቁ ወደ ሌላ ርእሰ ጉዳይ መግባት ግን መልካም መስሎ አይታየንም፡፡

    ከዚህ በፊት በአንድ ጽሑፍ ላይ እንደገለጽነው ተሐድሶ እንቅስቃሴ እንጂ እምነት ስላልሆነ የራሱ ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓት የለውም፡፡ ይህንንም ራሳቸው ባዘጋጁት ጽሑፍ ላይ:- €œወደፊት ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ የሃይማኖት ምዕላድ ማዘጋጀት ነው€�ስላሉ እስካሁን በጋራ የተስማሙበት ቋሚ የእምነት መሠረት እንደሌላቸው ሆነው የቀረቡበት ነው፡፡ ሆኖም ግን እስካአሁን እየገለጡት ካለው መረዳት እንደሚቻለው የተስማሙበት ዶግማና ቀኖናቸው ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስና ፕሮቴስታንታዊ ማድረግ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የተሐድሶን ምንነት በቀላሉ መግለጽ ከባድ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንደ ቡድኑና እንደ ግለሰቦች አቅም የሚወሰን እንጂ ቋሚ የሆነ አስተምህሮ ስለሌለው፡፡ የእንስሳትን ትርጉም ከመናገር ምሳሌ መስጠቱ እንደሚቀለው ሁሉ፣ ለተሐድሶም ትርጉም ከመስጠት ይልቅ ዓላማውንና ተግባሩን ማሳየት የተሻለ ገላጭ ስለሚሆን በእርሱ እንጀምራለን፡፡

    ተሐድሶ በአገራችን ዐውድ ሲታይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት እና ሥርዓት በመቀየጥ፣ በመቀየር ወይም በማጥፋት ፕሮቴስታንት ማድረግ፣ ምእመናንን ደግሞ በእምነት ስም አታሎ አስገብቶ ዓለማዊ (ሴኪዩላር) የማድረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፕሮቴስታንቲዝም በምዕራባውያን ዘንድ እምነትነቱ ቢያልፍበትም በእኛ አገር ግን እስከ አሁን ድረስ €œሃይማኖታዊ መልክ እንደ ተላበሰ ስለሆነ ተሐድሶን ለፕሮቴስታንቲዝም ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ተሐድሶና ፕሮቴስታንቲዝም በአካሔድ፣ በስልትና በግብ አንድ ዐይነት ናቸው፡፡ የሁለቱም ግብ ኦርቶዶክሳውያንን ፕሮቴስታንት ከዚያም ዓለማዊ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ቁርኝታቸውን መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም በወጣው ከሣቴ ብርሃን በሚባል ጋዜጣቸው ሲገልጹት፡-

    ባለፉት አሥርና አሥራ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው መሠረታዊ ልዩነት ለማጥናት ሞክረናል፡፡ ያገኘነው ውጤት እኛ እንድትኖረን የምንፈልጋት የታደሰችና ጥንታዊቷ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ከወንጌላውያኑ ጋር ያላት ልዩነት የአምልኮት ባህልና የቋንቋ ብቻ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበናል ይላሉ፡፡

    ይህንን የተናገረው ገድል ወይስ ገደል€� የሚለውን መጽሐፍ የጻፈው ጌታቸው ምትኩ ነው፡፡ ጌታቸው ምትኩ በሌላ ገጽ ላይ ስለ ከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ማኅበር አመሠራረት፣ ስለ ደረሰባቸውስደት€� እና ስለ ወሰዱት እርምጃ ሲገልጽ ደግሞ እንዲህ ብሏል፡-

    በተሐድሶ ጥያቄ ሰበብ በማኅበር ከተሰበሰቡት የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ብዙዎች ከሥራ የመባረር፣ ከቤተሰቦቻቸው የመለያየትና ማኅበራዊ ተቀባይነትን የማጣት ዕጣ ሲገጥማቸው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ድጋፍ በመሻት፣ በነጻነት ቃለ እግዚአብሔርን ለማወቅና ለመማር እንዲሁም አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም በገፍ ነጉደዋል፡፡ በእርግጥ በመሠረታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ረገድ ከወንጌላውያን ጋር የጎላ ልዩነት ባለመኖሩ ወደዚያ መሔዳቸው ክፋት ባይኖረውም €ተሐድሶውን ጎድቶታል፡፡

    ይህ ገለጻ የተሐድሶ ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ እግዚአብሔርን ስታመልክ፣ ላለፉት ሁለት ሺ ዓመታት ወንጌልን ስትሰብክ እንዳልኖረች ሁሉ ዛሬ ክርስቶስን እንዳልሰበከች በድፍረት የሚናገሩ የውስጥ እሾሆች በቀሉባት፡፡ ባያውቁት ነው እንጂ €œመታደስ አለባት የሚሉት ሰዎች ራሳቸው እግዚአብሔርን ያወቁት በእናት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ወንጌል እንደ አዲስ ሊሰበክላት ይገባል ብለው እየተሳደቡ የማርቲን ሉተርን ዓላማ ለማስፈጸም የተቋቋሙትን ድርጅቶች ደግሞ €œወንጌላውያን€� ብለው ጠሯቸው፡፡ እነቅዱስ አትናቴዎስ ከአርዮስ ጋር፣ እነቅዱስ ቄርሎስ ከንስጥሮስ ጋር፣ እነቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከልዮን ጋር እስከ ነፍስ ሕቅታ የተጋደሉላት ንጽሕት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከሉተር ድርጅቶች ጋር በአስተምህሮ አንድነት ስትፈረጅ ከመስማት በላይ የሚያም ነገር የለም፡፡

    የተሐድሶ እንቅስቃሴው ከተጀመረ በጣም ጥቂት ጊዜ ቢያስቆጥርም የመጀመሪያዎቹ የተሐድሶ መነኮሳት ኅብረት ከተወገዙበት ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ወዲህ ግን መልኩን እየቀየረና እየተስፋፋ እንደመጣ ግልጽ ነው፡፡ በተለይም በቅርብ ጊዜ (፳፻ወ፬ ዓ.ም) በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ሰባት ማኅበራትና ዐሥራ ስድስት ግለሰቦች ከተወገዙ በኋላ ሁላችንም የተሐድሶ ጉዳይ ያበቃ መስሎን እጃችንን አጣጥፈን ተቀምጠን ሳለን እነርሱ መረባቸውን ዓለም አቀፋዊ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ከአሜሪካ እስከ እንግሊዝ፣ ከዱባይ እስከ ኢትዮጵያ የሚደርስ ሰፊ መረብ ዘርግተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተናጠል እንቅስቃሴ በጋራ መሆን ይሻላል በሚል ከዐሥር በላይ የሚሆኑ የተሐድሶ ማኅበራት€œየወንጌል አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት€� የሚባል ማኅበር አቋቁመዋል፡፡ ኅብረቱ በከሣቴ ብርሃን አነሣሽነት የተመሠረተ የተሐድሶ ኅብረት ነው፡፡ ሁለተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ መጋቢት ፳፻ወ፯ ዓ.ም ባወጣው ልዩ ዕትም መጽሔት ላይ ኅብረቱ የካቲት ፴/፳፻ወ፭ ዓ.ም እንደ ተመሠረተ፣ መስከረም ፲፮/፳፻ወ፯ ዓ.ም ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕጋዊ ዕውቅና እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡ በመጽሔቱ የኅብረቱ ሥራዎች ተብለው ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል፡-

    የጋራ የሆነ የእምነት መግለጫ ማዘጋጀት፣

    የጋራ የሆነ በየደረጃው ላሉ የሚያ ለግል የማስተማሪያና የማሠልጠኛ ማቴሪያል ማዘጋጀት፣

    የቤተ ክርስቲያኒቷ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚጠቀሙበት የጋራ የሆነ ሥርዐተ ትምህርት መቅረጽ፣

    የቤተ ክርስቲያኗን ብርቱ ጎንና ደካማ ጎን ለይቶ በማውጣትና በመጽሐፍ ቅዱስ በመመዘን ሊጸና የሚገባው እንዲጸና፣ ሊወገድ የሚገባው እንዲወገድ፣ ሊሻሻል የሚገባው እንዲሻሻል፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትይዘው ሲገባ ያልያዘችውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ደግሞ እንድትይዝ ለማድረግ ብርቱ የሆነ የጋራ ተሐድሶአዊ ምእላድ ማዘጋጀት የሚሉት ይገኙበታል በማለት የወደፊት ዕቅዳቸውን ገልጸዋል፡፡

    ተሐድሶ እስከ አሁን እንቅስቃሴ ብቻ እንደ ነበረ አሁን ግን እየሰፋና ወደ ተቋምነት እያደገ እንደሆነ ይህ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ እነርሱ በየጽሑፎቻቸው ኦርቶዶክሳዊ አይደለንም፣ የፕሮቴስታንት ቅጥያዎች ነን እያሉ እየገለጹ ዛሬም ስለ ተሐድሶ መኖር አለመኖር የሚከራከሩ የዋሀን አሉ፡፡ እንቅስቃሴው ገባን የሚሉት እንኳን ማወቅ የሚፈልጉት ተሐድሶዎች እነማን እንደሆኑ እንጂ ስለ እንቅስቃሴው ምንነት፣ ስፋት፣ አደጋና ከእነሱ ስለሚጠበቀው ድርሻ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የተሐድሶዎችን ማንነት ማወቅ ብቻውን ዕውቀት አይደለም፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ጥቅምም የለም፡፡ ስለ ተሐድሶ ሲታሰብ የሰዎችን ማንነት ከማወቅ ያለፈ ሥራ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ሁሉ ነገር እንዲነገረን መፈለግ ሳይሆን መገለጫ ቸውን ዐውቀን በዚህ መሠረት ማንነታቸውን መለየት እና መመዘን የእኛ ሥራ መሆን አለበት፡፡

    ብዙ ሰዎች የሚጠይቋቸው የተለመዱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ €œእገሌ ተሐድሶ ነው? ከሆነ ለምን ከቤተ ክርስቲያን አልታገደም? ለምን አልተወገዘም? ስለ እመቤታችን እያስተማረ ለምን ተሐድሶ ይባላል? ግእዝ እየጠቀሰ ለምን ኦርቶዶክስ አይደለም ትላላችሁ?የሚሉ ጥያቄዎች ይሰማሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ €œእገሌ በጣም የምንወደው ሰባኪ ስለሆነ ተሐድሶ እንዳትሉት፣ እገሊት ስትዘምር ድምጿ ስለሚያምር እንዳትነኩብን€� ብለው ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን በላይ ያስቀመጡም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የተሐድሶን ምንነት ካለ መረዳት የሚመጡ ችግሮች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያ ይህንን እንወቅ፡፡ ግእዝ የሚጠቅስ፣ ስለ እመቤታችን የሚያስተምር (ስልት ስለሆነ)፣ ወይም ድምጹ የሚያስገመግም ሰባኪ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ ራሳቸው አንድ ሥልጠና ላይ የተናገሩትን ከዚህ መጥቀስ ይበጃል፡፡

    ስትሰብኩ ኢየሱስ ብቻ አትበሉ፣ መድኀኔ ዓለም፣ መድኀኒታችን አምላካችን፣ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በሉ፡፡ ከቻላችሁ ግእዝ ጥቀሱ፣ ግእዝ ከተናገራችሁ ትታመናላችሁ፣ ሕዝቡ ይሰማችኋል፡፡ ከአዋልድ መጻሕፍትም ለምሳሌ፡- ከውዳሴ ማርያም፣ ከሰዓታት፣ ከዚቅ፣ ከመልክአ መልኮች ጠቅሳችሁ ማስተማር ትችላላችሁ፡፡ ስለ ማርያምም አስተምሩ፣ ድንግል ስለመሆኗ፣ በከብቶች በረት ኢየሱስን ስለ መውለዷ፣ በስደት ስለ መንገላታቷ አስተምሩ፡፡ ብቻ ዓላማችሁን ሳትስቱ ሰዎች በሚሰሟችሁና በምትታመኑበት መንገድ ካስተማራችሁ ሕዝቡን መያዝ ትችላላችሁ፣ ቆይታችሁ ዋናውን ትምህርት ታስተምራላችሁ ብለዋል፡፡

    ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መናገር የማደናገሪያ ስልት እንጂ የስብከታቸው ዓላማ እንዳልሆነ መረዳት አለብን፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸው የቴሌቪዥን መርሐ ግብራት የእመቤታችንን ሥዕል ከጐናቸው አድርገው ቢያስተምሩ ተአማኒነትን ለማግኘት እንጂ በእመቤታችን አማላጅነት ወይም በሥዕላት ክብር አምነው እንዳልሆነ እነርሱም እኛም እናውቃለን፡፡ ስለ እመቤታችን እናስተምራለን ብለው ጀምረው ስለ እመቤታችን አንድም ነገር ሳይናገሩ €œጸሎተኞች፣ ጸሎታችሁ ያልተሰማው በስሙ ስለማ ትጸልዩ ነውብለው በቅዱሳን ስም መጸለይ እንደማይገባ ሲናገሩ ካልገባን እየበለጡን ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ኦርቶዶክሳዊ በሚመስል ርእስ እኛን በመሸንገል ኑፋቄያቸውን ለማስገባት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ እንጂ ስለ ቅዱሳን ክብር በመቆርቆር እየተናገሩ ነው የሚያስብል ምን ነገር አለው?

    እነሱም ይህ ስልት የበለጠ አዋጭና ለአቅጣጫ ማስቀየሪያ እንደሚበጅ ዐውቀው በደንብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ እነሱ ቅኔ ሲቀኙ፣ የተማሩባቸውን እና ያስተማሩባቸውን ወይም ያገለገሉባቸ ውን አጥቢያዎች ሲናገሩ፣ የእኛ አጀንዳ የተሐድሶ አደገኛነት ሳይሆን የተናገሩት ጉዳይ እውነትነት ላይ ይሆናል፡፡

    ለምሳሌ ብንጠቅስ የሰሜኑን የተሐድሶ እንቅስቃሴ (በተለይ አብነት መምህራን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ) ከጽጌ ሥጦታው ጋር ሆኖ የሚመራው ሙሴ መንበሩ የሚባል ግለሰብ፡- €œቤተ ክርስቲያን እንደምታውቀኝ ለማረጋገጥ እነብሴ ሣር ምድር ሔዳችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ ብሎ ስድስት አድባራትን ይጠራል፡፡ ከዚያም ቅኔ ይቀኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪ ጌታ እንደሆነም ይናገራል፡፡ የሚገርመው ግን ይህንን ሁሉ የሚልበት ቪሲዲ ርእስ ኦርቶዶክስ መልስ ካላት እኛም ጥያቄ አለን የሚል ነው፡፡ የቪሲዲው ርእስ ራሱ አቅራቢዎቹ ኦርቶዶክሳውያን እንዳልሆኑ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ያለነው ብለው ሊያሳምኑን ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንድ የዋሀን ደግሞ ይህንን ተከትለው €œኦርቶዶክሳዊ ናቸው፣ ይሄው ቅኔ እየተቀኙ፣ የቀደሱበትን ቦታ እየተናገሩ€� ብለው ይከተሏቸዋል፡፡

    ሌላ አንድ ማሳያ ብናይ አንድ የመጋቤ ሐዲስነት ማዕርግ የተሰጠው ሰው የጻፈው መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል አሳብ አስፍሯል €œይህ ሄኖክ የተናገረውና በሐዋርያው በይሁዳም የተጠቀሰውን ትንቢት ቃል በቃል በዚህ በ፷፮ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በምትጠቀምበት በሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ (መጽሐፈ ሄኖክ) ላይ ተጠቅሶ ይገኛል€� ይላል፡፡ ይህ ንግግር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአፍኣ ያለ ሰው የተናገረው እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቆሞ የሚሰብክ ሰባኬ አይመስልም፡፡ የገጸ ንባቡ አሳብ መጽሐፍ ቅዱስ የሚባለው ስድሳ ስድስቱ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሌላ የተለየ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳላት የሚያደርግ ነው፡፡ ይኸው ሰው በአንድ ወቅት በአንድ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ላይ €œእኔ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ተቋም ተሐድሶ አለ ብየ አላምንም፣ ካለ ቢሮውን ቢያሳዩን€� ብሎ ሲከራከር የነበረ መሆኑን ስናስብ ብዙ ነገር ያስጠረጥራል፡፡ ከዚህ ንግግሩ በኋላ ደግሞ ቦንጋ ሔዶ በዝግ ስብሰባ€œተሐድሶ የሚባሉ የተወሰኑ አካላት አሉ፣ ብዙዎቹ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ያሳደዳቸው ናቸው€� ብሎ ማኅበረ ቅዱሳንን በመክሰስ ራሱን ነጻ ለማድረግ ሲተጋ ነበር፡፡

    እነርሱ ለእኛ ማደናገሪያና መከራከሪያ የሚሆኑ ጉዳዮችን እየጫሩ እኛ በማይጠቅመው ነገር ስንወጠር ሥራቸውን እየሠሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተረፈ አርዮሳዊ የሆኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን በማታውቀው ግን በቤተ ክርስቲያን ስም በሚተላለፍ መርሐ ግብር ላይ €œበምድር ላይ ሞቼ ነበር ብሎ ቆሞ ሲያወራ የሰማነው ወይም ሲናገር ያየነው ፍጡር አልነበረም፣ የለምም፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር፡፡ የሚልስብከት እንዲሰበክ ዕድል ፈጠርንላቸው፡፡ በብዙ ድካምና በብዙ መከራ የሚገባባትን የእግዚአብሔርን መንግሥት መጠጥ ቤት የመግባት ያህል አቃለው ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፣ በአፉ መስክሮ ይድናልና፣ መንገዱ ረጅም አይደለም ወገኖቼ፤ ውጣ ውረድ የለበትም፡፡ የምትከፍለው አይደለም፣ የተከፈለበት ነው፡፡ አንተ የምታደርገው ነገር አይደለም፣ የተደረገልህ ነው፡፡ የምትሆነው አይደለም፣ የሆነልህ ነው፡፡ ይህንን ብታምን በአፍህ ብትመሰክር ትድናለህ፡፡ ከምንድንነው የምትድ ነው? ከኀጢአትና ኀጢአት ከሚያመጣው ሞት€� በማለት በወንጌል ቃል ይሳለቁበት ጀመር፡፡ እንዲያውም ዋናው ዓላማቸው በጸጋው ድናችኋልና አትድከሙ በመሆኑ ዕለት ዕለት የሚሉን €œየእግዚአብሔር ቃል የሚነግረን መዳን ማለት በልብ ማመንና በአፍ መመስከር እንጂ እኛ በድካም የለመድነውን አይደለም፡፡ እየታገልን አንዴ ሲሳካ አንዴ ሳይሳካ እያለቃቀስን የምንኖረውን አይደለም€� የሚል ያለፈበት የፕሮቴስታንት €œስብከት€� ነው፡፡

    ይህ ሁሉ የሆነው በእኛ መተኛት እንጂ በእነርሱ ትጋት እንዳልሆነ ሁላችን ውስጣችንን ስንፈትሽ የምንረዳው እውነት ነው፡፡ ስለ ጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ያልሰማንበት ጊዜ ረጅም ነው፣ እስካሁንም ከዚህ አዚም ያልተላቀቅን እንኖራለን፣ ጉዳዩን የምናውቀውም ትኩረት ሰጥተን የሰማንበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ከማድላት ይልቅ ለሰዎች የወገንንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ዛሬም ዓላማቸውን ራሳቸው ስለገለጹት እንጂ እኛ መርምረን ደርሰንበት አይደለም፡፡ ከእንቅልፋችን እስካልነቃን ድረስ ችግሩ ይቀጥላል፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰው ኦርቶዶክሳዊ ለመባል መስፈርቱ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ማስተማሩ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነኝ ማለቱ አይደለም፡፡

    ተሐድሶ ማለትም ጫካ ውስጥ የኖረ አውሬ ማለት ሳይሆን ከቤተ ክርስቲያን ጉያ የወጣ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበሩ፣ አሁንም አሉ፣ ነገር ግን በትምህርታቸውም ሆነ በዓላማቸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን አይደሉም ነው የተባለው፡፡ እነ አርዮስም እስከሚወገዙ ድረስ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ከተወገዙም በኋላ ብዙዎችን ከመንገድ ያስወጡት መናፍቃን ነን ብለው ሳይሆን ክርስቲያኖች ነን ብለው ነው፡፡ ዛሬም ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተምረናል፣ ቀድሰናል፣ እናም ኦርቶዶክሳውያን ነን ቢሉም ትመምህርታቸው ግን ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ብላ ዕውቅና የሰጠቻቸው ቅዱሳን አበው ይህንን ዕውቅና ሲሰጡ መስፈርቶቹ የቅድስና ሕይወት፣ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ፣ የቤተ ክርስቲያን ምስክርነትና ጥንታዊነት ናቸው እንጂ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው የአገልግሎት ቦታ አይደለም፡፡

    ስለዚህ ከዚህ በኋላ ተሐድሶዎች እነማን እንደሆኑ ንገሩን ማለት መብቃት አለበት፡፡ ሚዛኑ ካለን በሚዛን መዝነን ማንነታቸውን ማወቅ ከባድ አይሆንም፡፡ ምናልባት ማንነታቸውን የምንጠይቀው የራሳችንን ሥራ ለማቃለልና ሥናወራ እንዲመቸን ለማድረግ ካልሆነ በቀር በሥራቸው ታውቋቸዋላችሁ ስለተባልን በሥራቸው መመዘን ነው፡፡ በድምጽ መጎርነን እና ማማር፣ በመልክ ማማር፣ በታዋቂነት፣ ወዘተ ስም ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን የምናስበልጥ ከሆነ ክርስትና ውስጥ አይደለንም ማለት ነው፡፡ ስለ እንቅስቃሴው ሲነገረን ጆሮ ዳባ ልበስ የምንል ከሆነ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደሆነ ቁረጡ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉዋቸው€� /የሐዋ. ሥራ ፬፥፲፱-፳/ በማለት የተናገሩትን የአባቶቻችንን የሐዋርያትን አሰረ ፍኖት ከመከተል ይልቅ በከንቱ ውዳሴ ተጠልፎ አርዮስን ከውግዘቱ በመፈታቱ እንደተቀሰፈው አኪላስ መሆናችንን መረዳት ይገባናል፡፡ በሃይማኖታችን እያሾፍንበት እንደሆነ ማወቅም ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የገሃነም ደጆች አይችሏትም ስለ ተባለች ሁሉንም ፈተናዎች አሸንፋ እስከ ዓለም ፍጻሜ ትዘልቃለች፡፡ እኛ ግን ነቅተን ቅጽራችንን ካልጠበቅን የተቀደሰውን አሳልፈን እንሰጣለን፣ ከሰማያዊ ርስትም ዕጣ ፈንታ እናጣለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን ጸንተን ብንገኝና በአቅማችን እኔስ ምን ማድረግ እችላለሁ? ብለን ብንነሣ፣ በጠላት የተዘጋጀልን ፈተና የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሆኑን ተረድተን መንፈሳዊ መሣሪያዎቻችንን ሁሉ ታጥቀን መነሣት አለብን፡፡ ፈተና ከሌለ ጽናት፣ ጽናት ከሌለ ድል፣ ድል ከሌለ የድል አክሊል አይገኝምና፡፡

    ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ 23ኛ ዓመት ቁጥር 1/ቅጽ 23፣ቁጥር 329 መስከረም 16-30 ቀን 2008 ዓ.ም

    ይቆየ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የተሐድሶን ምንነት ሳታውቁ፣ ስለ ተሐድሶዎች ማንነት አትጠይቁ!! Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top