• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 27 June 2016

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፮ (የመጨረሻው )

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

    ✔ ጉባኤ ኦአክ ✔

    በክፍል አምስት ለመግለጽ እንደተሞከረው ቴዎፍሎስ በቅዱስ ኤጲፋንዮስ አማካኝነት ሊያደርገው ያሰበው ነገር አልሰመረለትም፡፡ ነገር ግን በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ላይ እርሱ ራሱ ከሳሽና ዳኛ ለመኾን እጅግ ሲጨነቅና ሲጠበብ ቆይቷል፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነገሮች እንደ ድሮ እንዳሉ በማሰብ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደ ወጣ ማለትም በዚህ በወርሐ ግንቦት አጋማሽ ላይ ስለ ሴቶች አለባበስ አስደናቂ የኾነ ስብከትን ሰበከ፡፡ አውዶክስያም ይህን ስብከት ሰማች፡፡ አንዳንድ ሰዎችም - በተለይ ሴቪሪያን የተባለ - ስብከቱ እርሷን ያነጣጠረ እንደ ኾነ ነገሯት፡፡ እጅግ ተናደደች፡፡ ይህንንም ይዞ ወደ አርቃድዮስ (ወደ ባለቤቷ) ሔደች፡፡ “እኔን ሰደበ ማለት አንተንም ሰደበ ማለት ነው” አለችው፡፡ ብዙዎቹ የታሪክ ጸሐፊዎች የቅዱስ ዮሐንስና የአውዶክስያ ግንኙነት የሚሻክረው በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡

    ያም ኾነ ይህ ነሐሴ መጨረሻ 403 ዓ.ም. ቴዎፍሎስ መጣ፡፡ እንዲመጣ ከተነገረው ከአንድ ዓመት በኋላ መኾኑ ነው፡፡ ከላይ እንደ ተናገርነው ቴዎፍሎስ ደጋፊ እያሰባሰበ በአዙሪት የመጣ ሲኾን አስቀድሞ ግን ሃያ ዘጠኝ ጳጳሳትን በባሕር ወደ ቁስጥንጥንያ ልኮ ነበር፡፡ በመኾኑም እርሱ በዚህ ጊዜ ሲደርስ ሞቅ አድርገው ተቀበሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ሰማ፡፡ ለጠብ እንደመጣም ተረድቶታል፡፡ ምንም ለጠብ እንደመጣ ቢያውቅም ግን ማረፊያ አዘጋጅቶለት ነበር፤ ቴዎፍሎስ አልመጣ ብሎ ወደ አውዶክስያ ሔደ እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- “እንደ ተለመደውና እንደ ትክክለኛ ሥርዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን አልገባም፤ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሔጄ ሰላም እንድለው እንኳን አልጠራኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከእኔ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር ወይም ጸሎት ወይም ሥርዓተ ቅዳሴ እንዳያደርግ ቆረጠ እንጂ፡፡ ከመርከብ እንደ ወረደ ምንም ሳይሳለም በቤተ ክርስቲያኑ በር አልፎ ሔደ፡፡ ለእርሱና አብረዉት ለመጡት አባቶች ብዬ ማረፊያ እንዳዘጋጀሁ ብነግረውም ተማጽኖዬን ንቆ ሔደ፡፡

    ቴዎፍሎስ እንዲህ ገብቶ ለሦስት ሳምንታት ተቀመጠ፡፡ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን የሚያጠቃበት መንገድ ለመዘየድ እንጂ፡፡ በዚህም ቅዱስ ዮሐንስን የሚጠሉ ሴቶችን አሰባሰበ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ጌጠኛ ልብስ ያስተማረው ትምህርት እናንተን ሰድቦ ያስተማረው ነው በማለት፡፡ ከእነዚህ ሴቶች በተጨማሪ ሴቬሪያን እንዲሁም ፕቶሎሚያስ የሚባሉ ኹለት የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀንደኛ ጠላቶችን አገኘ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ቅዱስ ዮሐንስን ለማጥፋት ኅብረት ፈጠሩ፡፡ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ አሁንም ቀጠለ፤ ወደ አውዶክስያ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ጌጠኛ ልብስን በማስመልከት ባስተማረው ትምህርት አኩርፋ ነበርና ቴዎፍሎስ ደግሞ ሲጨምርባት የልብ ልብ ተሰማት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን ለማጋዝ ከቴዎፍሎስ ጋር ተወዳጀች፡፡

    ቅዱስ በዚህ ጊዜ በጣም ግራ ተጋብቷል፡፡ ቴዎፍሎስ ለጠብ እንደ መጣ ቢያውቅም የጠቡ መነሻ ምን እንደ ኾነ ሊገባው አልቻለም፡፡ እስኪ ከቃሉ እንስማው፡- “መልካም መስሎ የታየኝን ኹሉ አደረግሁ፡፡ ከገባባት ቅጽበት አንሥቼ ለከተማችን እጅግ የሚንቦገበግ እሳትን ይዞ ለመጣው (ቴዎፍሎስ) እንድንገናኝ፣ ለምን እንደ መጣ እንዲነግረኝ ደጋግሜ ጠየቅሁት፡፡”
    ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ቴዎፍሎስ ቢያስብ ሊያሸንፈው ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደ ሕጉ ማለትም በጉባኤ ኒቅያ እንደ ተወሰነው አምስተኛው ቀኖና ከሔድን ቴዎፍሎስ ያለ አገረ ስብከቱ መጥቶ ነውና ይህን ኹሉ የሚያደርገው፡፡ “ነገር ግን” ይላል ቅዱስ ዮሐንስ “ይህን ላደርግ አልወደድኩም፡፡ እንደ አባቶቼ ሥርዓት አክብሬ ልቀበለውና ላስተናግደው አሰብኩ እንጂ፡፡”

    በመጨረሻም መስከረም መጨረሻ ላይ ከላይ ስንገልጻቸው የነበሩ አካላት በኬልቄዶን አቅራቢያ ኦአክ በተባለ ሥፍራ አስቀድሞ የታሰበበት ሐሰተኛ “ሲኖዶስ” አዘጋጁ፡፡ ቁጥራቸው ሠላሳ ስድስት ሲኾኑ ሃያ ዘጠኙ ከቴዎፍሎስ ጋር ከግብጽ የመጡት ናቸው፡፡ እናም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲመጣና ፍርዱን እንዲሰማ መልእክት ላኩበት፡፡ ፕትርክናውን ስለማይቀበሉ መልእክት ሲልኩ “ለዮሐንስ” የሚል ነበር እንጂ “ለሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ” አይልም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን አልሔደም፡፡ “የጉባኤው” ሕገ ወጥነትን የሚገልጽ ደብዳቤም መልእክቱን ይዘው በመጡ ሰዎች ላከላቸው እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እስኪመጣ ድረስ ብለው ግን ክሱን ይጽፉ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስቀድሞ በምግባረ ብልሹነታቸው ክህነታቸውን የያዘባቸው ካህናትና እነቴዎፍሎስ ራሳቸው ይህን አረቀቁ፡፡ እነቴዎፍሎስ በ29 ነጥብ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ሲከሱት ይስሐቅ የተባለ መነኮስ ደግሞ በ17 ነጥብ ከሰሰው፡፡ እስኪ ከተከሰሰባቸው ነጥቦች ጥቂቶቹን እንመልከት፡- ንግሥቲቱን አልዛቤል ብሎ ሰድቧል [ኤልዛቤል ብሏታል ያሉት ንግሥቲቱ ካሊትሮጳ የምትባል ብእሲታ ማውታ መሬቷን ቀምታት ስለ ነበረችና እንድትመልስላት ስለ ገሠጻት ነው]፤ ካህናትን በድሏል [ገንዘብን ይሰርቁ የነበሩት ክህነታቸውን ስለያዘባቸው ነው]፤ አላስፈላጊ ናቸው በሚል በቤተ ክህነቱ የነበሩ ውድ ንብረቶችን ሸጧል፤ የሽያጩን ገንዘብ ወዴት እንደ ወሰደውም አናውቅም፤ ድግሶችን በማስቀረቱና ለብቻው ስለሚበላ እንግዳ ተቀባይነትን ንቋል፤ ደጋግመው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ደጋግመው ንስሐ እንዲገቡ ያስተምራል፤ አስቀድመው ቤተ ክርስቲያንን ሲጎዱ የነበሩ አሕዛብ ተቀብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ጨምሯል፤ ወደ ታናሽ እስያ በመሔድ ጳጳሳትን ሾሟል፤ ኦሪገናዊ አስተምህሮ ያላቸውን ሰዎች ተቀብሏል፤ ከአጠገቡ ሌላ ሰው ሳይኖር ሴቶችን ይቀበላል የሚሉ ይገኙበታል፡፡

    የመጀመሪያው ስደት

    እንግዲህ በእነዚህና እነዚህን በመሰሉ ክሶች ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ዳኛ ኾነው በሌለበት “ጉባኤ” እንዲህ ብለው በመወሰን ወደ ንጉሥ አርቃዲዮስ መልእክት ላኩ፡- “ዮሐንስ በጉባኤው እንዲገኝ ጠርተነው ነበር፡፡ ነገር ግን ጥፋቱን ስለሚያውቅ ሊመጣ አልወደደም፡፡ ስለዚህ በቀኖናው መሠረት በሕይወት ዘመኑ ኹሉ በግዞት እንዲኖር ወስነንበታል፡፡” ንጉሡ ወደሚወስንበት የግዞት ሥፍራ እንዲጋዝ የሚጠይቅ ሐተታ (ሪፖርት) ነበር፡፡ ንጉሡም ይህን አጽድቆ የሚያግዙትን ወታደሮች ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ላከ፡፡

    ይህን ዜና የሰማው ሕዝብ ለመግለጽ በሚያስቸግር ኹኔታ ገነፈለ፡፡ ወደ ሃጊያ ሶፍያ ሮጠ፡፡ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት ሙሉ ወታደሮቹ ቅዱስ ዮሐንስን እንዳያግዙ ከለከሏቸው፡፡ በኹለተኛው ቀን ላይ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዓውደ ምሕረቱ ወጣ፡፡ ማስተማር ጀመረ፡፡ ስለ ድጋፋቸው በማመስገን በጸሎታቸው እንዲያስቡት ማለዳቸው፡፡ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ ያለው አምላክ አሁንም ከእኛ ጋር ነው” አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ፊትን አይቶ የማያዳላ መምህር ነውና ወደ ተግሣጽ ተሻገረ፡- የጴጢፋራ ሚስት ከዮሴፍ ጋር ዝሙት ለመሥራት እንዳደረገችው ኹሉ ዛሬም ግብጻውያን በቅዱሱ መንፈሳዊት ሙሽሪት (ምእመናን) ለመዳራት እዚህ ድረስ መምጣታቸውን፣ ዛሬም ሄሮድያዳ የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ሽታ እየዘፈነች እንደ ኾነ፣ ትናንት ከእርሱ እየተማረች 13ኛው ሐዋርያ ያለችው አውዶክስያ ዛሬ ግን ከአሳዳጆቹ ጋር ተስማምታ ይሁዳ እንደኾነችበት፣ ይህ ኹሉ ቢኾንም ግን እንደ ኢዮብ “የእግዚአብሔር ስም ለዘለዓለም የተባረከ ይኹን” ማለት እንደሚገባ አስተማረ፡፡ በቀጣዩ ቀን አመሻሽ ላይም በዘዴ ያለ ምንም ግርግርና ትርምስ ራሱን ለወታደሮቹ እጁን በመስጠት ወደ ስደት (ግዞት) በመርከብ ተሳፍሮ ሔደ፡፡

    በጣም የሚገርመው ነገር ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ እነዚያን መነኮሳት ያባረራቸው በኦሪገናዊነት ነበር፡፡ ታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጠስ እንዳለው ግን አሁን ይህን ኹሉ ረሳው፡፡ በቃ - እንዲሁ ታረቃቸው፡፡ ጥንቱም ቅዱስ ዮሐንስን መበ’ቀል እንጂ ዓላማው እነርሱ አልነበሩምና! ይሔ ብቻ አይደለም፡፡ የኦሪገንን መጻሕፍት ተቀብሎ ማንበብ ጀመረ፡፡ ይልቅ ወደ ተወዳጁ አባታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እንመለስ!
    ሊቁ እንደተሰደደ አሳዳጁ ሴቬሪያን በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አትሮንስ ላይ ቆመ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት የሚገባው መኾኑን “መስበክ” ጀመረ፡፡ ሕዝቡ ግን ተቈጣ፡፡ በእሳቱ ላይ ጋዝ ጨምሮባቸዋልና ገነፈሉ፡፡ አባታችንን መልሱልን አሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ ቁስጥንጥንያ ከተማ በሁከት ተናጠች፡፡ ቤተ መንግሥቱ ተሸበረ፡፡

    የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከመጀመሪያው ስደት መመለስ

    በሚቀጥለው ሌሊት ደግሞ ጭራሽ ሌላ ነገር ተከሰተ፡፡ ከሕዝቡ አይደለም፡፡ ከላይ ከአርያም ቁጣ መጣ፡፡ ከተማዋ በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተናጠች፡፡ መሬት መንቀጥቀጡ ለየት ባለ መልኩ በአውዶክስያ መኝታ ቤት በረታ፡፡ ከዚህ የተነሣም ፍላሲላ የተባለች ልጇ ሞተች፡፡ አውዶክስያ ሥራዋን ታውቃለችና ይህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደ ኾነ በማወቅ አርቃድዮስን ማለደችው፤ ቅዱስ ዮሐንስ ከተሰደደበት በአስቸኳይ እንዲመለስ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን አሳምኖ ለማምጣትም ከሚንስትሮቿ አንዱን ደብዳቤ አስይዛ ላከችው፡፡ በደብዳቤዋ ላይ፡- ከእነዚያ ክፉዎች ጋር በመተባበር ላይ እጇ እንደሌለበት፣ ልጆቼን ያጠመቅህልኝ’ኮ አንተ ነህ በማለት ሊቁን እጅግ እንደምታከብረው ገለጸችለት፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ ተመለሰ፡፡ ነገር ግን አለአግባብ በጉባኤ እንደተሰደደ ኹሉ በአግባብ በጉባኤ ሊመለስ እንደሚገባው በማመን ወደ ከተማዋ አልገባም፡፡ በሚዘገይባት እያንዳንዷ ቅጽበት ግን ሕዝቡ እንደገና በቤተ መንግሥቱ ላይ ዓመጹን እየጨመረ ስለሔደ ንጉሡ ይህን በመግለጽ እንዲገባ ለመነው፡፡ ቅዱሱም የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድ ሲል ለመግባት ተገደደ፡፡

    አሳዳጆቹ አፈሩ፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ መንበር ላይ ለመቀመጥ ቋምጠው የነበሩ ኹሉ ቀልባቸው ተገፈፈ፡፡ ሕዝቡም የቅዱስ ዮሐንስን መመለስ ሰምተው ወደ ሃጊያ ሶፍያ ተመሙ፡፡ እነዚያ ምግባር የለሽ መነኮሳት (እነ ይስሐቅ) ሕዝቡን በማሳሳት ሌላ ሁከት ለመፍጠር አስበው የነበረ ቢኾንም ወታደሮች መጥተው ነገሩን አበረዱት፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ቁስጥንጥንያ ሲመለስ ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ከሠላሳ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተቀበሉት፡፡ ሕዝቡም ጧፍና ችቦ አብርተው በመዝሙርና በዕልልታ ተቀበሉት፡፡ ከደስታቸው ብዛት የተነሣም ተሸክመው ወስደው ከመንበረ ጵጵስናው አስቀመጡት፡፡ ንግግር እንዲያደርግ ግድ አሉት፡፡ ተነሣ፡፡ “የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይኹን” የምትለዋን የኢዮብ ቃል አዘውትሮ ይጠቅምባት እንደ ነበር ነገራቸው /ኢዮ.1፡21/፡፡ አሁንም ይህን ቃል ሊደግምላቸው እንደሚወድና ስለ ስደቱና ስለ መመለሱ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን እንደሚፈልግ፣ ጠላቶቹ ከሚወዳቸው ልጆቹ ሊለያዩት ቢፈልጉም ይበልጥ ሌሎች ወዳጆችን እንዳፈራለት፣ አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ይሞላ እንደ ነበር አሁን ግን የከተማው አደባባዮች በሙሉ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ኾኑ፣ ምንም እንኳን በዚያ ሰዓት ፈረስ እሽቅድምድም የነበረ ቢኾንም ተመልካቹ በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደ መጣ፣ የአብርሃም ሚስት ሣራ የግብጹ ንጉሥ ሊወስዳት እንዳሰበ የእርሱ ሙሽሪት (ምእመናንም) ቴዎፍሎስ ሊወስዳቸው ቢያስብም ሊሳካለት እንዳልቻለ፣ ልጆቹ በሙሉ እንዲህ ሲሰበሰቡ ተኩላዎቹ ግን መበታተናቸውን በመግለጽ፣ አውዶክስያም እንዲመለስ በማድረጓ በማመስገንና በዚህ ኹሉ እጅግ ደስ እንደ ተሰኘ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡ ከመጠን ያለፈ ደስታም ስብከቱን ሳይጨርስ እንዲቀመጥ ኾኗል፡፡ በዚህ ጊዜ እነ ቴዎፍሎስ በጣም በመፍራት ሹልክ ሹልክ ብለው ጠፍተው ወደ አገራቸው ሔደዋል፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን አሁንም እንደ አዲስ ጉባኤ ተደርጎ አለአግባብ መሰደዱን የሚገልጽና እንደገና እነ ቴዎፍሎስና አብረው የመጡት ጳጳሳት ባሉበት በአግባብ በጉባኤ ሊመለስ እንደሚገባ ለአርቃድዮስ ይገልጽለት ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ የሚለው ክብርን ፈልጎ ሳይኾን በኋላ “ሕጋዊ ኾነህ አልተመለስህም” ሊል የሚችል አካል እንዳይኖር ምክንያት ለማሳጣት ነው፡፡ አርቃድዮስ በዚህ በማመን ለቴዎፍሎስ መልእክት ልኮለታል፡፡ ቴዎፍሎስ ግን “በአሌክሳንድርያ ያሉ ልጆቼን ትቼ ብሔድ ዓመጽ ያስነሣሉ” በማለት ሊመጣ እንደማይችል ገለጸ፡፡ በመኾኑም እነ ቴዎፍሎስ ባይኖሩም ሌሎች ስድሳ ሊቃነ ጳጳሳት ተሰብስበው ቅዱስ ዮሐንስ ሕጋዊው የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ መኾኑንና የኦአክ ጉባኤን እንደሚያወግዙ በመግለጽ መለሱት፡፡ አርቃድዮስም በጉባኤው ተገኝቶ ነበር፡፡

    ኹለተኛው ስደት

    ምንም እንኳን ቴዎፍሎስ ወደ አገሩ ቢመለስም ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ገዝቷቸው የነበሩና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀንደኛ ጠላቶች የነበሩ እነ ሴቬሪያን፣ አካክዮስና አንቲዮኮስ ግን በቁስጥንጥንያ ነበሩ፡፡ ለጊዜው ተደብቀው የነበረ ቢኾንም ወደ ከተማው ተመለሱ፡፡ መመለሳቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ሊቁ በመመለሱ በማፈራቸው ሊቁ ላይ ስሕተት በመፈለግ አሁንም እንዲሰደድ በመሻት እንጂ፡፡ ጊዜውም እነርሱ ከጠበቁት በላይ ፈጥኖ እንደመጣላቸው ዐዩ፡፡ ሕዳር አጋማሽ ላይ በሃጊያ ሶፍያ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት አውዶክስያ የራሷን ሐወልት አሠራች፡፡ ተመልከቱ! ሊቁ ወደ መንበሩ የተመለሰው ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ኹለት ወር እንኳን አልሞላውም፡፡ እናም አንድ እሑድ ላይ ዝግጅት አዘጋጀች፤ የዘፈን ነው፡፡ ሙዚቃው፣ ዘፈኑ፣ ጫጫታው፣ ጭብጨባው የቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ረበሸ፡፡ በዚያ ሰዓት ቅዱስ ዮሐንስ እየቀደሰ ነበርና፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ ዕለት የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሰማዕትነት በማስታወስ፡- አሁንም ሄሮድያዳ እየተቈጣች፣ እየዘፈነች፣ የዮሐንስን ራስ በውጭት እየፈለገች መኾኗን አስተማረ፡፡ ምንም እንኳን ስሟን ጠቅሶ ባይናገርም ዕለቱ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር ስለ ገጠመ ስብከቱን እንደ ኹልጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ ያስተምር ነበር፡፡ ንግሥቲቱ ግን ንግግሩ ኹሉ እርሷን የተመለከተ ኾነ በማሰብ ተበሳጨች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን የሚያሳድድ ሌላ ጉባኤ እንዲዘጋጅም ዐቀደች፡፡ ወደ ቴዎፍሎስና እርሱን ወደ መሰሉ ሌሎች ጳጳሳት ደብዳቤ በመላክም እንዲሰበሰቡ ጠራቻቸው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥጋ እንዳየ ንሥር ከየአቅጣጫው ተሰባሰቡ፡፡ ቴዎፍሎስ ግን አስቀድሞ ያገኘው ሐፍረት ያውቃልና ነገሮችን በግብጽ ኾኖ ማሤሩን መረጠ፡፡

    የገና በዓል ደረሰ፡፡ ከዚህ በፊት ንጉሡና ንግሥቲቱ በጌታችን ልደት በዓል ዕለት በሃጊያ ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ ያስቀድሱ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በኦአክ ጉባኤ ጥፋተኛ የተባለ ጳጳስ በሚቀድስበት ቤተ ክርስቲያን መገኘት እንደማይችሉ አርቃድዮስ ለቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ላከበት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስና ቤተ መንግሥቱ እንዲህ ሳይግባቡ እስከ ፋሲካ 404 ዓ.ም. ድረስ ቆዩ፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን አሁንም ትምህርቱን እያስተማረ ነው፡፡ እነዚያ እርሱን ለማሳደድ ድጋሜ በአውዶክስያ የተጠሩት ጳጳሳት ግን በምን ምክንያት ሊያሳድዱት እንደሚገባ በየጊዜው ይሰበሰባሉ፤ ምንም ምክንያት አጡበት እንጂ፡፡ ይጠብቁ የነበረው የተንኮል ዘዴ የማያጣውን የቴዎፍሎስን ሤረኛ ዘዴ ብቻ ነበር፡፡ ቴዎፍሎስ አሁን አንድ ዘዴ አገኘ፡፡ በወርሐ ግንቦት 341 ዓ.ም. ላይ በአንጾኪያ የወጣ ቀኖና ነበር፡፡ ቀኖናዉን ያወጡት ግን አርዮሳውያን ጳጳሳት ናቸው፡፡ ጊዜ ከተወሰኑት ቀኖናዎች መሠረት አራተኛው ቀኖና፡- “በትክክለኛ ምክንያት ይኹን በግፍ ከመንበሩ እንዲወርድ ከተወሰነበት በኋላ ያው ሲኖዶስ ሳይመልሰው ወደ መንበሩ ቢመለስ መጀመሪያ በተወሰነበት መሠረት ስደቱ የጸና ነው” ይላል፡፡ እነዚህ አርዮሳውያን ይህን ቀኖና ያወጡት ቅዱስ አትናቴዎስን ከመንበሩ ለማሳደድ ብለው የወሰኑት ነው፡፡ ቴዎፍሎስ ግን በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ላይ ምክንያት ቢያጣ ለማጥቃት ሲል ብቻ የአርዮሳውያን ቀኖና ጠቀሰ፡፡ ተመልከቱ! በመጀመሪያው ስደት ላይም ልክ እንደዚሁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ለማሳደድ ሲል ብቻ የኦሪገን ትምህርትን ጠቀሰ፡፡ አሁንም እንደዚሁ የአርዮሳውያንን ቀኖና በኦርቶዳክሳዊው አባት ላይ ጠቀሰ፡፡

    በዚህ ጊዜ ግን አሳዳጆቹ ተጨነቁ፡፡ ምክንያቱም በአንድ መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሰደድ ይፈልጋሉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስን የሚያሳድዱት ቴዎፍሎስ በጠቀሰው ቀኖና መሠረት ከኾነ አርዮሳውያን እንደሚያስብላቸው አሰቡ፡፡ በዚህ መኻል የቴዎፍሎስን ምክር ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ ይህም ቢኾን ግን ንጉሡ ሊቁን እንዲያሳድደው መወትወታቸውን አላቆሙም፡፡

    በዓለ ትንሣኤ ሲቃረብ ንጉሥ አርቃድዮስ ወደ አፈወርቅ መልእክት ላከ፡፡ ትእዛዝ ነበር፡፡ “ከእንግዲህ ወዲህ በሃጊያ ሶፍያ አገልግሎትህን መስጠት አትችልምና አቁም” የሚል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን፡- “ቤተ ክርስቲያን በአደራ የተሰጠችኝ ከእግዚአብሔር እንጂ ከአንተ አይደለችም” በማለት ማስተማሩን ቀጠለ፡፡ በሕዝቡና በወታደሮች መካከል ደም ማፋሰስ ሊያመጣ ሲል ግን በመንበረ ጵጵስናው ተወስኖ ተቀመጠ፡፡

    ሰሞነ ሕማማት እንደ ተጀመረ ሊቀ ጳጳሳቸው ቅዱስ ዮሐንስ በመንበረ ጵጵስናው ውስጥ የቁም እስረኛ መኾኑንና በበዓለ ትንሣኤ በካቴድራላቸው እንደማይገኝ ዐወቁ፡፡ ዓርብ ስቅለት ላይ አርባ የሚኾኑና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን የሚደግፉ ጳጳሳት ንጉሡና ንግሥቲቱ ሊቁን ወደ አገልግሎት እንዲመለስ ለመኗቸው፡፡ አውዶክስያ ግን ሰድባ መለሰቻቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ ከጳጳሳቱ ጳውሎስ የሚባል አንዱ እግዚአብሔርን ልትፈራ እንደሚገባና በልጆቿ ላይ ቁጣን ሊያመጣ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ነገር ከማድረግ እንድትቆጠብ ገሠጻት፡፡

    በዓለ ትንሣኤ ደረሰ፡፡ ዕለቱም እሑድ ሚያዝያ 17 ነበር፡፡ በዋዜማው ማለትም በ16 ንዑሰ ክርስቲያኖች ለመጠመቅ ተዘጋጁ፡፡ አገልግሎቱም በሀጊያ ሶፊያና በሃጊያ ኢሬኔ ይደረግ ጀመር፡፡ ሊቂዮስ በሚባል አሕዛባዊ መሪ የሚመሩና 400 የሚኾኑ የተመለመሉ ወጣቶች ወደ አብያተ ክርስቲያናቱ ገቡ፡፡ ጳጳሳቱና ካህናቱ አገልግሎቱን እንዲያቆሙ ነገሯቸው፡፡ ኃይልን በመጠቀምም ተጠማቂዎቹን ደበደቧቸው፤ ለመጠመቅ ውኃው ውስጥ ዕራቁታቸው የነበሩት ሴት ተጠማቂያን ያለ ልብስ ሸሹ፡፡ የመጠመቂያው ውኃ ወደ ደም ተለወጠ፡፡ የምሥጢረ ቁርባን ንዋያተ ቅዱሳት በአሕዛብ ወታደሮች ረከሱ፡፡ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን እንደ ለበሱ ወደ ከተማው ተሰደዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ራሱ ኹለት ጊዜ ከተቃጣበት ሞት ተረፈ፡፡ ደጋፊዎቹ ናቸው የተባሉ ኹሉ ወደ እስር ቤት ተወሰዱ፡፡ እንኳንስ በአካል ተገኝቶ በዓይነ ሕሊና እንኳን ሲያስቡት የሚያሰቅቅ ግፍ ተፈጸመባቸው፡፡ ይህን በቅርብ ርቀት ኾነው ያስፈጽሙ የነበሩት የቅዱስ ዮሐንስ ቀንደኛ ጠላቶች አንቲዮኮስ፣ አካኪዮስና ሴቬሪያን ናቸው፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለኹለት ወራት ሙሉ እንዲህ የቁም እስረኛ ኾኖ ቆየ፡፡ በዓለ ኃምሳ እንዳለፈ ቀጥላ በነበረችው ሐሙስ ማለትም ሰኔ 9 ላይ ግን አንቲዮኮስ፣ አካኪዮስ፣ ሴቬሪያንና ሲሪኖስ ትዕግሥታቸው ተሟጠጠ፡፡ ንጉሥ አርቃድዮስ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ስደት እንዲያጸድቅ ጫና አሳደሩበት፡፡ ንጉሥ አርቃድዮስ እስከ አሁን ድረስ ስደቱን ያላጸደቀው እንደ መጀመሪያው ስደት ሁከት ይነሣል ብሎ ፈርቶ ነው፡፡ በመጨረሻ ግን ሰኔ 20 ቀን 404 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ከአርቃድዮስ አንድ መልእክተኛ ተላከ፤ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ፡፡ ወዲያውኑ ቤተ ክርቲያኒቱንና ከተማይቱን ለቆ ወደ ስደት ሊወጣ እንደሚገባው ወደ ውሳኔ መድረሱን የሚያሳወቅ ነበር፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳቱን ሰብስቦ የመጨረሻ ንግግርና ጸሎት አደረገላቸው፡፡ ዕረፍት ላደርግ ነውና እዚህ ቆዩኝ ብሎም ኦሎምፒስንና እርሷን የሚመስሉ ታማኝ አገልጋዮችን እንዲህ አላቸው፡- “የእኔ ጉዳይ ወደ ፍጻሜ እንደ ደረሰ ይታየኛል፡፡ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ፊቴን የምታዩ አይመስለኝም፡፡ እናንተን የምጠይቃችሁ አንድ ነገር ብቻ ነው፡- ለቤተ ክርስቲያን የምታደርጉትን አገልግሎት ማንም እንዳያሰናክላችሁ፡፡ አገልግሎታችሁን ቀጥሉ፡፡ በእኔ ቦታ የሚተካው ሰው እርሱ ሹመት የማይፈልግና እርሱ ፈቅዶ ሳይኾን በኹሉም ስምምነት የሚሾም ከኾነ ልክ እንደ ዮሐንስ አድርጋችሁ ተቀበሉት፡፡ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ለእርሱም አድርጉለት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ጳጳስ ልትኾን አይገባምና፡፡ እንዲህ ብታደርጉ ምሕረትን ታገኛላችሁ፡፡ እኔንም በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡

    በዚህ ጊዜ ኹሉም በኀዘን ተዋጠ፡፡ ግማሹ ያለቅሳል፤ ግማሹ በአሳብ ተውጦ ሰማይ ሰማዩን ያያል፡፡ እነ ኦሎምፒያስ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እግር ሥር ወድቀው ያለቅሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከካህናት አንዱን ጠርቶ በዙርያ ያለው ሕዝብ ኹኔታውን ሰምቶ ረብሻ እንዳይፈጥር እንዲወስዳቸው ነገረው፡፡ በምዕራብ በኩል እርሱን ይጠብቁ ወደ ነበሩት ምእመናን ከመውጣት ይልቅም ደም ማፋሰስ እንዳይኾን ከቤተ ክርስቲያኑ ምሥራቅ አቅጣጫ ወጥቶ ለወታደሮቹ እጁን ሰጠ፡፡

    በስደቱ ምን ምን እንደ ገጠመው በቅርቡ በታተመውና “ወደ ኦሎምፒያስ የተላኩ መልእክታት” በሚለው መጽሐፍ እንድትመለከቱ እጋብዛችኋለሁ፡፡

    ዕረፍቱ 

    ሞቱን ለሚናፍቁ አሳዳጆቹ ኹሉ ዕድሜው ረዘመባቸው፡፡ በመንገድ ላይ በሕመም ወይም በአየር ኹኔታው ተለዋዋጭነትና ቅዝቃዜ ከዚህ ከተረፈም አይሲያራውያን በተባሉ ዘላኖች ተገድሎ ይሞታል ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ ይህ ግን አልኾነም፡፡ ይባስ ብሎም በዚያ ኩኩሰስ በተባለና ለስድት በተመረጠለት ቦታ ኾኖ በኦሎምፒያስ አማካኝነት በቁስጥንጥንያና በዙርያዋ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ማስተዳደሩን ቀጥሏል፡፡

    በመኾኑም በዚህ እጅግ በመናደድ ፈጥኖ ይሞት ዘንድ ከቤተ መንግሥቱ ኹለት ወታደሮችን አስላኩ፡፡ ሰኔ አጋማሽ 407 ዓ.ም. ላይ ኩኩሰስ ደረሱ፡፡ ለሦስት ወር ያህልም በእግር እንዲጓዝ አደረጉት፤ በትኅርምት ባለቀ ሰውነቱ እንዲሞት ነበር፡፡ በመጨረሻም መስከረም 14 ቀን 407 ዓ.ም. በአርማንያ ባሲሊቆስ በተባለ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሥጋዉንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ በ60 ዓመቱ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተናገራት ቃልም፡- “ስለ ኹሉም ነገር ክብር ለእግዚአብሔር ይኹን” የሚል ነበር፡፡
    ዕለተ ዕረፍቱን በተመለከተ በየአብያተ ክርስቲያናት ልዩነት አለ፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው ግንቦት 12 ነው፡፡ ስለ ልዩነቶቹ መረዳት የሚፈልግ ካለ የኅዳር 17 ቀን ስንክሳር መመልከት ይችላል፡፡
    የቅዱሱ ሰውነት ወደ ቁስጥንጥንያ የተመለሰው ከሠላሳ ዓመት በኋላ ሲኾን ያረፈውም በሃጊያ ኤሬኔ ነው፡፡

    አነሣስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን እግዚአብሔር ክብር ኃይል ወእዘዝ ለዓለም ወለዓለም አሜን!!!

    ምንጭ:- መቅረዝ ዘተዋሕዶ

    Next
    This is the most recent post.
    Older Post
    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፮ (የመጨረሻው ) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top