• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    …….እንደ ሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ


    ጸናጽል ድምጹ መልካም የሆነ የምስጋና  ዕቃ በመሆኑ ከቀደሙት ሌዋውያን አሁን እስካሉት የሐዲስ ኪዳኑቤተ መቅደስ መዘምራን ፣ከቀደመው የሙሴ ድንኳ ዛሬ እስከደረስንበት ቅድስተ ቅዱሳን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነው የምንቆም የምስጋና ዕቃ ነው፡፡ ምስጋናችንም ሆነ ዘፈናችን ያለከበሮና ጸናጽል ምን ውበት ሊኖረው ብለን እንጀምራለን? አንጀምረውም፤ የሊቃውንቱ መዳፍ ያለ ጸናጽል አይንቀሳቀስም፣ቅኔ ማኅሌቱም ያለ ከበሮ አይደምቅም ፤ እንደ ጾመ ኢየሱስ ያለ ጨካኝ ቀን ካልወረደበት በስተቀር ቅኔ ማኅሌት ከነዚህ ነገሮች አይለይም፤ ይገርማል! ዳሩ ግን አንድም ቀን ቢሆን በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ለስጋውና ለደሙ ክብር በሚደረገው አገልግሎት ተሳትፈው አይተናቸው አናውቅም ጥንትም ሆነ ዛሬ ከውጭ ብቻ ነው -አገልግሎታቸው፤

            ቅዱስ ጳውሎስ የባዶኅይወት ተምሳሌት አድርጎ  ተጠቅሞበታል ‹‹የሰውን ሁሉ ልሳን ባውቅ ፣በመላዕክትም ቋንቋ ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ነሐስ እንደሚንሿሿም ጻናጽል ነኝ››1ቆሮ 13÷1ይላል

            ይህን ስመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ መቅደሱ ያደገች ነፍሴን አሰብኩና እስራኤል ሲማረኩ ‹‹ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን››ብለው እንደተናገሩ እኔም ለተማረከችውና ባዶዋን ለቀረችው ጽዮን ሰውነቴ አለቀስኩላት ከኔ በቀር ጽዮን ሰውነቴ ባለተስፋ ምድር መሆኗን ማን ያውቅላታል? የተገባላትንስ ቃል ኪዳን ከኔበቀር ማን ያውቅላታል? 
    ስለዚህ ደጋግሜ በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሆኘ ምርር ብየ አለቀስኩላት ደግሜ ደግሜም እንዲህ አልኳት እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደ ሚንሿሿም ጸናጽል ነሽ አልኳት

            እስኪ አስቡት !ያለኔ ማኅሌቱ አይጀመር፣ዝማሬው አያምር ፣የሊቃውንቱ ጉሮሮ አይከፈት፣ ሽብሻቧቸው አያምርበት ፣እጃቸው ያለኔ አይንቀሳቀስ፣ቅኔው መወድሱ ያለኔ አይፈስ፣ ስብሐተ ነግሑ አይደረስ፣አርያሙ አይዜም፣ ዋዜማው አይቆም እስኪ ንገሩኝ ምኑ ነው ያለኔ እሚያምረው፤ በየትኛው አገልግሎት ነው እኔ እማልገባው፤ የትኛውስ ሊቅ ነው ያለኔ በእግዚአብሔር ምስጋና ላይ የተገኘው ፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ እኔ ለዚች ቤተ መቅደስ አገልግሎት አስፈልጋለሁ ፡፡

            ያለዚያማ ማኅሌቱ ምን ውበት ሊኖረው፤ ማንስ ነው እኔ በሌለሁበት ያለ እንቅልፍ እሚያገለግለው፤ ከከበሮው ተስማምቶ በሚወጣው መልካሙ ድምጼ ብዙዎቹ ይመሰጣሉ፣ የድምጼን ውበት በውስጠኛው ጆሯቸው እየሰሙ እንዲህ አሳምሮ የፈጠረኝን ‹‹ድምጹ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑ ››እያሉ ያመሰግናሉ የድምጼን መልካምነት ብቻ እየተመለከቱ ወይ መታደል ብለው ያደንቃሉ፤እኔ እስከማዜም ድረስ በጉጉት ይጠባባቃሉ ፤ሰው ሲዳርም ሆነ ሲሞት ፣ሲሾምም ሆነ ወግ መዐርግ ሲደርስለት ያለኔ ምኑ ያምራል፤አምጡት፣ አምጡት ይባላል

            ይህን ሁሉ ክብሬን አየሁና በሰዎች መካከል በኩራት ተቀምጨ ሳለሁ ከእለታት ባንድ ቀን የሥጋየን መጋረጃ ግልጥ አደረግሁና ነፍሴን ተመለከትኋት ፤ ትጮኻለች ፣አዳመጥኳት፤ላደርገው የሚገባኝን እንኳን ያለደረግሁ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ ፤አንደሚጮኽ ነሐስ፣እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ እያለች ታንጎራጉራለች

            የሚጎሰመው ነጋሪት ፣የሚመታው ከበሮ፣ የሚንሿሿው ጸናጽል ለራሳቸው ምን ተጠቅመዋል? ከነሱ በኋላ እየተነሣ ስንት ትውልድ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሰ፣ከተስፋው የደረሰ፤ ሌላው በነሱ ተጠቅሞ አድማሳትን በቅድስናው ሲያካልል፣ መላዕክትን ሲያክል እነሱ ግን አሁንም ምድራውያን ናቸው፡፡ በዚህኛው ትውልድም አልተለወጡም ጌታ እስኪመጣ ከዚህ ዓይነት ኅይወት የሚወጡም አይመስሉም፤

            እኔም እንደነሱ ነኝ! ቃሉን እሰብካለሁ፣ ዝማሬውን እዘምራለሁ፣መወድሱን እቀኛለሁ፣ሰዓታቱን አደርሳለሁ መጽሐፍ ቅደዱስን ከዳር እስከዳር አውቀዋለሁ ዳሩግን መች እኖርበታለሁ ፤ ሰዎቹ ከአፌ የሚወጣውን ቃሉን እየሰሙ የኅይወቴ ነጸብራቅ እየመሰላቸው ይገረማሉ ፣እንደኔ ለመሆን ይቀናሉ እኔ ግን ሳላስበው እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ምክንያቱም እጮኻለሁ እንጅ ለምን እንደምጮኽ እንኳን አላውቅም፤ በምጮኸው ጩኸት ከቶ አልለወጥም፤ ከኔ በኋላ እየተነሱ ብዙዎቹ ከምሥራቅና ከምዕራብ እየመጡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብተዋል ፤ ከኔ በኋላ ቃሉን የሰሙት በቃሉ ተለውጠው ንስሐ ገብተዋል እኔ ግን ዛሬም ሳያውቅ እንደ ሚጮሕ ነሐስ፣ ሳይወድ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡

            የምጮኸው ገብቶኝ ቢሆንኮ ከኔ እሚቀድም ማንም አልነበረም ከባለድጓው በፊት ከባለቅኔውም አስቀድሞ መንግሥቱን የምወርስ እኔ ነበርሁ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ኅይወት የሌለኝ ቆርቆሮ ነኝ፤ ድምጼ መልካም ነው፣ ትጋቴ ግሩም ነው፣ከምስጋናው ጋር መስማማቴ፣በሁሉም እጅ መግባቴ መልካም ነበር ሆኖም ፍቅር የለኝምና ምን ይሆናል፡፡  ሥጋየን ለሰማይ አዕዋፍ ብሰጥ ፣ያለኝንም ለድሆች ባካፍል ፣ የድሆች አባት ብባል ፣አጥንቴም እስኪታይ ብጾም ብጸልይ ፍቅር ግን ከሌለኝ ያው እንደሚጮኸው ነሐስ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል መሆኔ አይደለ! ሥጋውን ደሙን ካልተቀበልኩ የኔ መጮኽ ምን ሊጠቅም !

            ለካ ለሥጋውና ለደሙ እሚያስፈልገው በበጎ ዝምታ ዝም ያለው እንደኔ የሚንሿሿው ጸናጽል አይደለም ብላ ነፍሴ ስታለቅስ እኔንም አስለቀሰችኝ ፡፡

                  ኦ!አምላኬ ጸናጽልነቴን ለውጥልኝ፣ ነሐስነቴን አርቅልኝ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: …….እንደ ሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top