• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    መስቀልና ደመራ ክፍል ፪


      1ኛ ነቢያትና ሐዋርያትን

    ነቢያትና ሐዋርያት በዘመን፣ በግብር፣ በክብር የማይገናኙ አባቶቻችን ናቸው፤ ነቢያት የምንላቸው ከአዳም እስከ ዮሐንስ መጥምቅ ያሉትን ሲሆን ሐዋርያት የምንላቸው ደግሞ ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያን የምሥራቹን እንዲነግሩ የተላኩ አባቶቻችንን ነው፡፡ በእርግጥ ሐዋርያ የሆነ ነቢይ አናገኝም እንጅ ነቢይ የሆነ ሐዋርያ ማግኘት ይቻላል፤ ለነቢያት የተሰጠው መንፈሰ ረድኤት ሲሆን ለሐዋርያት የተሰጠውን መንፈሰ ልደት ማግኘት ለነቢያት አልተቻላቸውም ሐዋርያት ግን በመንፈሰ ረድኤት ላይ መንፈሰ ልደትን ጨምረው መያዝ ሰለተሰጣቸው ሁሉንም አንድ አድርገው ይዘዋል፤ የመጠን ልዩነት ይኖረው ይሆናል እንጅ ሐብተ ትንቢት ያልተሰጠው ሐዋርያ የለም፤ ለዚህም ነው ሐዋርያው ስለዚህ ዘመን ሲናገር‹‹በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጠን›› ዮሐ1÷18 ሲል አጉልቶ የተናገረው፡፡

    በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት በመፈለግ እንደ ነቢያት ብዙ ድካም የደከመ ሊኖር አይችልም፤ ለዚህ ነው ሊቃውንቱ ነቢያትን በክረምት ገበሬ ሐዋርያትን በበጋ ገበሬ የሚመስሏቸው፤ የክረምት ገበሬ ላዩ ውሃ ታቹ ውሃ ሆኖበት በጭቃ ወጥቶ በጭቃ ይመለሳል ሲገባም ሚስቱ ጎመን ጠምቃ ታቆየዋለች ያን በልቶ ደስ ሳይለው ይተኛል፤ ነቢያትም ዓለምን በጣዖት አምላኪ ነገሥታት በነቢያተ ሐሰት ስብከት ሲንገላቱ ይኖራሉ ሲሞቱም ሲኦል እንጅ ገነት መግባት አይችሉም፤ የበጋ ገበሬ ግን በደረቅ ወጥቶ፣ እሸት በልቶ፣ ተደስቶ ይመለሳል እቤቱ ሲገባም እንጀራው በሌማት፣ጠላው በማቶት ሲቀርብለት ደስ ብሎት ይመገባል ሐዋርያትም ልጅነት አግኝተው ለማስተማር ተልከዋል፣ በሄዱበት ተዓምራት እንዲያደርጉ፣ልጅነትን እንዲሰጡ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል ሌሊት ሞታቸው ሲደርስም መንግሥተ ሰማያት ተከፍቶ ይቆያቸዋል፤

    ቅዱስ ያሬድም 
    ስለነቢያትና ሐዋርያት ሲናገር ‹‹ኖትያት ነቢያት ራግናት ሐዋርያት›› በማለት ነቢያትን በዋናተኛ ሐዋርያትን በጀልባ ቀዛፊዎች መስሎ ይናገራል፤ ከዋናተኞች ይልቅ ቀዛፊዎች ድካም የለባቸውም፤ ዋናተኞች ውሃው አጥልቋቸው፣ መተንፈስ ተስኗቸው አንዳንዶቹ ዳር ይደርሳሉ አንዳንዶቹም በድካም በውሃው ውስጥ ጠልቀው ይቀራሉ፤ ቀዛፊዎች ይሄ ሁሉ የለባቸውም ምናልባት ስጋታቸው ማዕበል ሞገድ ነው እንጅ ሌላ ስጋት አይኖርባቸውም፤ ጀልባዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ለነቢያት በተስፋ እንጅ በአካል ያልተጨበጠች ጀልባ ናት፤ ሐዋርያት ተሳፈሩባት ባሕር የሚመስለውን ዓለም ተሻገሩባት፤ የነቢያት ድካም ጀልባዋ ካለችበት ለመድረስ ነበር ሳይደርሱ ሞት ቀደማቸው፤

    ነቢያት የደከሙትን ድካም ባይጠቀሙበትም ለልጆቻቸው ጥቅምን አስገኝቶላቸዋል፤ ሐዋርያት የገቡት በነቢያት ድካም ነውና፤ አንዳንድ ጊዜ አንዱ የዘራውን ሌላው ያጭደዋል ነቢያትም የዘሩትን የትንቢት ዘር ሐዋርያት አጭደውታል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ወንጌል የነቢያት ዘር ናት ዳሩ ግን ዘሩት እንጅ አፍርቶ ፍሬ እስኪያፈራ መቆየት ባለመቻላቸው ፍሬውን የበሉት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው፡፡ ከወንጌል ውስጥ ስትመለከቱ ሐዋርያት እሸት ይበሉ እንደ ነበረ ተጽፏል ነገር ግን የእርሻው ባለቤት ማን እንደሆነ አልተጻፈም ማቴ12÷1 የእርሻው ባለቤት ነቢያት ናቸው እንጅ ሌላ ማን ይሆናል፡፡ ዘሩ ሲዘራ ያልደረሱ ሐዋርያት እሸቱ ሲደርስ ጌታ በእርሻ መካከል ይዟቸው ገባ የገበሬዎቹ የነቢያት ጌታ ክርስቶስ የተዘራውን ዘር እንዲሰበስቡና በጎተራው ውስጥ እንዲያከማቹለት ይህን አድርጎታል እንጅ ያለ ምክንያት እንዲህ የሚያደርግ ይመስላችኋል፡፡ በወቅቱ የነበሩትም ሰዎች ስለሰንበት ይከራከሩ ነበር እንጅ ስለ እሸቱ አልነበረም፤ ይህም ማለት ነቢያትን በሐዋርያት የሚተካ የነቢያትና የሐዋርያት ጌታ እንደሚመጣ ቢያውቁም ጊዜው አሁን አይደለም ብለው የአይሑድ ምሁራን በክርስቶስ አለማመናቸውን መናገር ነው፡፡

    ተቃዋሚው መንፈስ ብዙ ቢናገርም መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአበው ፋንታ ውሉድን ለመተካት ከተቃዋሚው መንፈስ ጋር ብርቱ ፉክክርን ሲያደርግ ታዩታላችሁ፤ ነቢያትን ያስገደለ ጠላት በነቢያት እግር የሚተኩትን ለማጥፋት ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ የክርስቶስ አመጣጥ ግን በአባቶቻቸው ፋንታ የሚወለዱ ልጆችን አለቆች አድርጋ ቤተ ክርስቲያን እንድትሾም ለማድረግ ነውና ነቢያትንና ሐዋርያትን አንድ ማኅበር አደረጋቸው፤ አንድ ማኅበር በነቢያትና በሐዋርያት መካከል እንዲመሠረት ምክንያት የሆነው የመስቀሉ ነገር ነው፡፡ ሐዋርያ ስለመስቀሉ ሲናገር ገባሬ ሰላም ብሎ ይጠራዋል ኤፌ2÷13 ሁለቱን ያዋሐደ ገባሬ ሰላም መስቀሉ ነው እንጅ ሌላ ምንድ ነው፤ ሁለቱን አንድ አድርጎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ያወረሰ፣ አንድ ጊዜ የሁለቱንም ሐጢአት የደመሰሰ እንደ ክርስቶስ መስቀል ምንም የለም፡፡ ከመስቀል በኋላ አንድ አድርጎ መንግሥቱንና ጽድቁን አወረሳቸው፤ ደመራው እስከዚህ ድረስ ነበርና ፡፡ አሁን እረኛው አንድ፣ መንጋውም አንድ ስለሆነ ከፊት ከፊታችን የሚሄደውን አንዱን እረኛ ተከትለን ወደ ዕረፍት እንገባለን፡፡

    2ኛ ሙታንና ሕያዋን

    አዳም በእጸ በለስ ምክንያት የተሸከመው መስቀል ሞትን አመጣብን ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ብሎ የተሸከመው መስቀል ግን ሞትን ገደለልን፤ በዚህ ምክንያት የሞት መውጊያው ሲሰበር፣ የመቃብርም ይዞ ማስቀረት ሲቋረጥ፣ የጨለማውም ኀይል ሲሻር ከመስቀሉ ሥር ብዙ ሙታን እንደ አሸን ብቅ ብቅ አሉ፤ ምድር እሰከዚያች ቀን ድረስ ሙታንን ትቀበል ነበር እንጅ ሕያዋንን ማስገኘት አልቻለችም ነበር፡፡ የዛሬውን ምን ልዩ ያደረገው ይመስላችኋል፤ ቀኑ የፍቅር ቀን እኮ ነው! ሙታንና ሕያዋን ለምድራችን አዲስ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲፈላለጉ የመጀመሪያው ቀን ነው! ነገሩ ስለ ጻድቅ ስንኳን የሚሞት በጭንቅ በማይገኝባት ዓለም ስለሐጢአተኞች የሚሞት ሰው በተገኘባት በዚች ቀን ሙታንና ሕያዋን እንደምን አይዋደዱም! ይገርማል! ሙታን ሕያዋንን ፍለጋ ከመቃብር ወጥተው ወደ ከተማ ገቡ፤ ማንም በዐይኖቹ ማየት ያልቻለውን እውነት ሊመሰክሩ አንደበታቸውን በእውነት ከፈቱ፤

    የግብጹ ስደተኛ የያዕቆብ ልጆች ግብጽን ለቀው ሲወጡ በጉዞው ሙታንም የተሳተፉ መሆናቸውን ብናውቅም የሚናገሩ እና በሕይወት የሚንቀሳቀሱ ሙታን ግን አልነበሩም፤ እንዲያው የተስፋይቱን ምድር ተስፋ የሚያደርግ አጥንታቸው ብቻ በልጆቻቸው ትከሻ ላይ ሆኖ ወጥቷል እንጅ፤ የዛሬው ፍልሰት ከዚያኛው በእጅጉ የተለየ እንደሆነ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡ ከታደለው የሕይወት ስጦታ የተነሣ ሞት አካባቢውን ለቆ ስለጠፋ በሩ እንደተለቀቀለት እስረኛ ሙታን ከመቃብር እየወጡ ከተማውን ሞሉት፤ ሙታን ከሕያዋን ጋር አፍ ለአፍ ያነጋገረ ቀን ነው! ደመራው የሞቱትንም የሚለይ አይደለምና ከሞትም መንደር አምጥቶ ደመራውን ታላቅ አደረገው፤ የዚህ ደመራ ታላቅነት እስከ ሲኦል ድረስ መታየት የሚችል ታላቅነት ያለው ነው፡፡

    3ኛ ጻድቃንና ሐጥአንን

    በሕይወት አለን የሚሉትን ወንድማማቾች ሳይቀር የአዳም በደል ነጣጠላቸው፤ አንዱን በደግነት ሌላውን በክፋት ሁለት ሀሳብ እንዲያስቡ አደረጋቸው፡፡ የክርስቶስ ጽድቅ ግን አንድ ሃሳብ ፈጠረላቸው፤ ሐጢአት ወንድምን የማያሳይ ድቅድቅ ጨለማ ሲሆን ጽድቅ ግን ከመቃብር በታች ላለ ሰው እንኳን እንድንራራ ያስገድደናል፤ በዓለም ላይ በእድሜአችን ያየነው ትልቅ ቁም ነገር፡- በምድር ላይ ከሚንቀሳቀስ ውሸት ይልቅ መቃብር የከደነው እውነት የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ ዝም ይላል እንጅ እውነት ሞቶ አያውቅም፤ ውሸት ግን የማይሞተው ለራሱ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም የተወለደውም ከሞት በኋላ ስለሆነ ውሸት ሕይወት ይኖረዋል ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ ለዚህ እኮ ነው ነፍሰ ገዳዩ ቃኤል ድምጹ ጠፍቶ ሳለ የሞተው አቤል ግን እስከ ዛሬ ይናገራል ዕብ11÷6

    ምንም አቤል ሳይገድል በመገደሉ ሳይበድል በመደሉ ክርስቶስን ቢያስመስለውም ሞቱ ለሰው ልጆች የጠቀመው ነገር እንደሌለ እናውቃለን የፍጡር ደም ሊያስታርቀን ባለመቻሉ እኛ ሁላችን በመከራ ውስጥ ልንቆይ ተገደድን፤ ሞቱን ማን አይቶታል በጫካ ውስጥ ማንም ሳያይ የተፈጸመ ሞት እኮ ነው፡፡ የክርስቶስ ሞት ግን እንደዚያ አደይደለም፤ ከፍ ካለው ስፍራ ከረጅሙ ተራራ ላይ የተደረገ ከመሆኑም በላይ የሞቱንም ፍርድ በቤተ ክሕነትና በቤተ መንግሥት ታውቆ ተረድቶ የተደረገ ነው፡፡

    ከተራራ ላይም አውጥተው ሰባት ክንድ ከሆነው መስቀል ላይ ከፍ አድርገው ለሁሉ እንዲታይ አድርገው ነበር የሰቀሉት፤ ከቤት ውስጥ ያለን መብራት በቤት ውስጥ ላለው ሁሉ ያበራ ዘንድ ከፍ አድርገው በመስቀል ላይ ይሰቅሉታል እንጅ ማን እንቅብ ደፍቶ ከታች ያስቀምጠዋል፤ በቤት ውስጥ ያለ መብራት ከፍ ብሎ በተሰቀለ ጊዜ ሁሉን እንዲያስተያይ የክርስቶስ ሞትም ጻድቃነ ብሊትንና ጻድቃነ ሐዲስን እንዲተያዩ አደረጋቸው፤ በመስቀል የተፈጸመው ዕርቅ የሐጥአንን በደላቸውን ደመሰሰላቸው የጻድቃንን ጽድቃቸውን አረጋገጠላቸው፡፡ ጻድቃንም ሆኑ ሐጥአን በጸጋው መንግሥቱን አንድ ሆነው ወረሱ ኢያሱ በኢያሪኮ እንዳደረገው አሞራውያን ወጥተው እስራኤል ምድሪቱን የወረሳት አይደለም እንዲያው የደመራ ጊዜ ስለሆነ ለሁሉም አንድሐገርን አውርሷቸዋል፡፡ ደመራው እንዲህ የተገለጠ ሲሆን እስከ መንግሥተ ሰማያት ድረስ ይቀጥላል።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መስቀልና ደመራ ክፍል ፪ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top