ክፍል አንድ
እግዚአብሔር የሠራቸው ታላላቅ ሥራዎችን ስንመለከት በምልክት የተገለጡ ናቸው፤ የሙሴ መስፍንነት፣ የአሮን ሊቀ ካሕንነት የተረጋገጠው በአሮን በትር ምልክትነት ነው፤ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ሊሰዋ በታዘዘ ጊዜ የሞርያ ተራራን እንዲመርጥ የተደረገው እግዚአብሔር በተራራው ላይ ካሳየው የብርሃን ምልክት የተነሣ ነው በእርግጥ እሱም ራሱ ለሌላ ምሥጢር ምልክት እንደ ነበረ ምንም ጥርጥር የሌለው ጉዳይ ነው፤ እርሱ ይስሐቅ ሊመጣ ላለው ለወልደ እግዚአብሔር አምሳል ምልክት ነበርና፡፡ ድንግል ማርያም እና ቅዱስ መስቀልንም ለመዳናችን ምልክት አድርገን የተቀበልናቸው ሲሆን ከዚህ አስቀድሞ ለእነርሱም የተቀመጠ ምልክት ነበራቸው፤የአሮንን ክብር ያስመለሰች በትረ አሮን፣ ድንቅ አድራጊዋ በትረ ሙሴ፣ የይስሐቅ ቤዛ የሚሆን በጉን ያስገኘች ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን እና የቅዱስ መስቀል ምልክቶች ነበሩ፤ ምልክቶቹ ምልክት እየተሰጣቸው ትውልዱን ከተስፋ መቁረጥ ታድገውታል የመዳን ምልክቶችን በሕዝቡ መካከል እንዲገለጡ ማድረጉም በዋናነት ለሕዝቡ ተስፋ እንዲሆኑ ነው፤ እንዳሁኑ ዘመን መያዣ ያልተሰጠው በሩቅ በሚሰማው ተስፋ ብቻ የሚኖር ባለ ተስፋ ትውልድ ነበርና፤ አሁን ሥጋውና ደሙን መያዣ አድርጎ ሰጥቶናል የተስፋይቱን ምድር ከሰላዮች ድምጽ ሰምተን ሳይሆን በዐይናችን አይተን አረጋግጠናል ነገር ግን እስክንወርሳት ብቻ ‹‹ትምጻዕ መንግሥትከ ›› ስንል እንኖራለን መንግሥተ ሰማያት ይሏችኋል ሌላ እንዳይመስላችሁ ክርስቶስ ራሱ ነው መንግሥተ ሰማያት የተባለው፡፡
መንግሥተ ሰማያት እርሱ ከሆነ ደግሞ ያገኘነው መስቀል ላይ ነው እንጅ ከዳዊት ቤተ መንግሥት በሰሎሞን ዙፋን ላይ ተቀምጦ አይደለም ጠላት ይህን ስለሚያውቅ ነው ቅዱስ መስቀልን አጥብቆ የሚቃወመው፤ ከዚህም የተነሣ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ በመቃብር ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል፤ በመሠረቱ ለሰይጣን ይህ ስለማይገባው ነው እንጅ ትክክለኛው የመስቀሉ የመቃብር ሥፍራ የምዕመናን ልቡና ነው እንጅ መሬት ውስጥ አይደለም፤ ቀራንዮ ለመስቀሉ መትከያነት የተመረጠችበትስ ምክንያት ምን ሆነና! ቀዳሜ ፍጥረታት አዳም የተቀበረው እዚያ ስለሆነ ነው፤ የቦታውም ስም ‹‹የራስ ቅል የሚሉት ስፍራ›› ማቴ27÷32 ተብሎ መጠራቱ ለሌላ አይደለም የሁላችንም ራስ የሆነው አዳም ያለበት ስፍራ በመሆኑ ነው እንጅ፡፡ ከዚያ በኋላ መስቀሉ በአዳማውያን ፍጥረታት አዕምሮ ውስጥ እንጅ ከዚያ ውጭ የሚኖር አይደለም ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን መስቀሉ ተቀብሮ በቆየባቸውም ዓመታት የመስቀሉ ፍቅር ከሰው ልጆች አዕምሮ ያልጠፋ መሆኑ ነው፤ መስቀሉ በመቃብር ውስጥ ሳለ ከዚያም አስቀድሞ ከዚያም በኋላ መስቀሉን የተሸከሙ ምዕመናን ቁጥር አልቀነሰም፡፡
ጠላት ይህን ሳያውቅ በሠራው ተንኮል መስቀሉ ተቀብሮ እንዳይቀር መንፈስ ቅዱስ በልበ ምድር ያለውን ምሥጢር እንድታወጣ ከሩቅ ምድር እሌኒን ሰው አድርጎ አስነሣ፤ ጊዜው ሲደርስ ከምትኖርበት ምድር አውጥቶ ባላሰበችው መንገድ መራት ለጊዜው መከራ በሚመስል ፍጻሜው ግን ለእግዚአብሔር ሥራ ምቹ ወደ ሆነ የሕይወት መንገድ መራት እሷም ሆነች ሌሎች ወገኖቿ የመንገዷን ምሥጢር ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር የሚያውቅ አልነበረም፤ አብርሃምን በዚያ ዘመን ለለዩ አገልግሎት ከካራን ወደ ከነዓን ሲጠራው የመንገዱን ምሥጢር ማን ያውቅ ነበር፤ ጠርቶ ካመጣውስ በኋላ በሚኖርበት ምድር ማርና ወተትን እንደምታፈስለት የነገረው እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ለምን በረሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ እንዲሰደድ አደረገው፤ ላዩ መከራን የለበሰ ምሥጢራዊ ስደት ስለሆነ ጊዜው ሳይደርስ የተረዳው ማንም አልነበረም፤ ይህችም ሴት እንደዚያው ያለች ሴት ናት፤ ከቤቷ ወጥታ እንድትጣል ያደረገበት የራሱ የሆነ ምሥጢር አለው፤ መቼም እግዚአብሔር ሰውና ጊዜ በጣላቸው ሰዎች የሠራውን ሥራ ሰውና ጊዜ ባነሣቸው ሰዎች አልሠራውም፤ ዳዊት ከሰው ሁሉ ታናሽ ሳለ ጎልያድን አሸነፈ ከሰው ሁሉ ታላቅ በሆነ ጊዜ ግን የቤቱ ልጆች አሳደዱት፣ እረኛ ሳለ አንበሳ በእርግጫ፣ነምር በጡጫ ገደለ ንጉሥ ሲሆን ግን ከምናምንቴዎች አንዱ ሳሚ ወልደ ጌራ ሲሰድበው ዝም አለ፤
ይህችም ሴት በገረድ በደንገጠር የምትንቀሳቀስ ሁሉ የሞላላት ሴት በነበረች ጊዜ ምንም እንደሠራች አልተመዘገበላትም፤ ከክብሯ ወርዳ የተጣለች ስትሆን ግን እግዚአብሔር ለሚፈልገው ሥራ ምቹ የሆነ ሕይወት ተገኘባት፤ በተጣለችበት የባዕድ ምድር ውስጥ ሆና የመስቀሉን ነገር ታስባለች፣ ስለመስቀሉ ሱባኤ ትገባለች፤ በአይሑድ ቅንዓት መሬት ውስጥ ሆኖ ተራራ በሚያክል ቆሻሻ ተከድኖ የሚኖረው መስቀል የብርሀነ መለኮቱ ነጸብራቅ አልተለየውም ነበርና መሬት ሳይጋርደው፣ እንደ ፀሐይ ብርሃን ተራራ ሳይከለክለው ዘወትር በልቧ ብርሃኑ ያንፀባርቃል፤ ግብር ገብታ በብርቱ ፍለጋ እንድተፈልገው ያነሣሳትም ይሄው ነው፤ እግዚአብሔር ለሚሠራቸው ሥራዎች ከሰው የልብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፤
ከዚህ ዝግጅት በኋላ ነው ንግሥት እሌኒ ከተጣለችበት አንሥቶ ሰው ያደረጋት እግዚአብሔርን ለማገልገል የተቆረጠ ሀሳቧን ይዛ መስቀሉን ፍለጋ የጀመረችው፤ ሀሳቧን እንዲያሳካ የነገረችው አምላክ ኪራኮስ የተባለውን አይሑዳዊ ሽማግሌ እና መላኩን ላከላት ኪራኮስ የጀመረላትን ምሥጢር መላኩ ተረጎመላት፤ ደመራ ደምረሽ ሰንድሮስ የሚባል ነጭ ዕጣን ጨምረሽ አቃጥይው አላት መላኩ እንደነገራት አድርጋ ብታቃጥለው ጢሱ የሰማዩን ጥግ ደርሶ፣ ወደምድር ተመልሶ መስቀሉ ያለበትን ተራራ በሚያመላክት ሁኔታ ወደ መስቀሉ ሰገደ፤ በዚህ ምልክትነት መስከረም አሥራ ሰባት ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት አሥር ቀን አልቆ መስቀሉን ከልበ ምድር ማውጣት ችላለች፤
መስቀልና ደመራ እንዲህ ነበር የተገናኙት፤ ደመራው መስቀሉን ያስገኘ ሲሆን መስቀሉም ደመራው እንዲሠራ ምክንያት ሆኗል፤ ከላይ እንዳነሳነው መለኮትና ትስብዕት አንድ ደመራ ሆነው መደመራቸው መስቀሉ እንዲሠራ ያስገድዳል፤ ሥጋ ለብሶ ያለ መከራ መኖር የሚቻለው ማነው? ለሥጋውያን ተብሎ የተሠራው ዓለም በራሱ ያለ መከራ እንድንኖር አያሰናብተንም፤ የሁላችን አባት አዳም ሲያርፍ ልጁ ሴትን አሰጠርቶ ‹‹ዛቲ ዓለም ምልዕተ ጻማ ወድካም፤ ይህች ዓለም ጭንቅን የተሞላች ዓለም ናት›› ብሎ መክሮታል፤ ከዚያ እስከ ዛሬ በጽድቅም ይሁን በሐጢአት በማንኛውም መንገድ ቢጓዙ ያለ መከራ መኖር አይቻልም፤ አምላካችንም ሥጋን ለብሶ ክርስቶስ በሚለው የተዋሕዶ ስም ሲጠራ ለሥጋ መከራ መዘጋጀቱን እንረዳለን፤
መስቀሉ የሥጋ ብቻ ነበረ አሁን ግን መለኮትም በሥጋ ባሕርይ የመስቀሉ ተካፋይ ሆነ ይህ የደመራው ውጤት ነው እንጅ ሌላ ምንድ ነው! መለኮት አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን መስቀል የተሸከመ ሥጋን ሲዋሐድ መስቀሉን ሊሸከምለት እንጅ መስቀሉን አስወግዶ ሥጋን ብቻውን የተዋሐደው አይደለም፤ ሥጋ ዐቅም አጥቶ መስቀሉን ከትከሻው ላይ ሳያስወግድ ለዘመናት የተጓዘውን ጉዞ መለኮት ኃይል ሆኖት ያስወግደው ዘንድ ድካሙን ሳይለቅ ኃያል፣ ኃይሉን ሳይለቅ ደካማ ሆነ በምድር ላይ የቆየባቸው ዘመናት በሙሉ የሥጋን መስቀል የተሸከመባቸው ዓመታት በመሆናቸው ራሱን የሚያስጠጋበት ጎጆ እንኳን አልነበረውም፤ እስካሁን በምድር ላይ ከነበሩ ድሆች ውስጥ እንደ እሱና እንደ እናቱ ድሃ መኖሩን በታሪክ አልሰማንም፤ ከሰማይ ወፎችና ከምድር ቀበሮዎች በታች የሆነ ኑሮ ይኖር የነበር እርሱ ብቻ ነውና፡፡ ይሄም እኮ በእፀ በለስ ምክንያት የተሸከምነው መስቀል ነው፤ ባይሆን ልዩነቱ ያኛው ሞትን ያመጣብን መስቀል ሲሆን ይሄኛው ደግሞ ሞትን ያራቀልን መስቀል ነው፤ መስቀልትርጉሙ ምን ጊዜም ትርጉሙ መከራ ቢሆንም እግዚአብሔር ሲያመጣውና ሰው ሲያመጣው የመስቀል ትርጉሙ የተለያየ ነው፤
እውነት ነው! ሰው ያመጣው መስቀል ሁላችንን ለመከራ ፣ ለሞት አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ትርጉሙ እንደ ግብሩ መከራ ሊሆን ይገባዋል፤ እግዚአብሔር ያመጣው መስቀል ግን መከራነቱ ለሰይጣን እንጅ ለእኛ ባለ መሆኑ ሕይወት እንጅ መከራ ሊባል አይገባውም፤ የተሸከምነውን የመስቀላችንን ትርጉም የሚለውጠውን የክርስቶስን መስቀል እንዴት መከራ ብለን ልንተረጉመው እንችላለን፤ ቅዱስ ያሬድ መስቀልን ሲተረጉመው ‹‹መስቀል ብሂል እፀ ሕይወት ብሂል፤ መስቀል ማለት የሕይወት ዛፍ ማለት ነው›› ብሎ ይተረጉምልናል፤ አዳም ከገነት ሲወጣ በመላዕክት እንዲጠበቅ የተደረገው የሕይወት ዛፍ ቅዱስ መስቀል ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡
እንደዚያ ከሆነ ደግሞ በእጸ በለስ ሁላችን እንደ ተጎዳን በእጸ ሕይወትም ተጠቃሚዎች ሁላችንም ስለምንሆን አሁንም አስቀድመን በመከራው እንደተባበርን በደስታውም እንተባበራለን ፤ሞትም ሕይወትም አንድ አድርጎናል፤ በእርግጥ ሞት እኛን የሰው ልጆችን ማስተባበር ቢችልም እንኳን ሰውና እግዚአብሔርን ሰውና መላእክትን መለያየቱ አልቀረም፤ እነርሱ ሕያዋን ሲሆኑ ሰው በሞት ጥላ ውስጥ የሚኖር አሳዛኝ ፍጥረት ሆኗል ባሕርዩ ያልሆነ መንገድን መርጧልና በባሕርይ የሚመሳሰሉት ፍጥረታት ሳይቀሩ ተለይተውታል፤ የክርስቶስ ሕይወት(መስቀል) ግን ሁሉንም አስተባብሯል፤ በአንጻሩ ሰውና ዲያብሎስን ለያይቷል፣ ቁራኝነትን አጥፍቷል ከማኅፀን ጀምሮ ቁራኝነት እማይቀር ዕዳ በመሆኑ ምንም ሳያውቁ ሕጻናት የአባት ዕዳ ለልጅ እንዲሉ የዕዳው ተካፋይ ሆነው ይወለዳሉ፤ ጌታችን በማኅፀነ ማርያም ሲፀነስ ጀምሮ የእኛን መስቀል መሸከም ሲጀምር የእርሱ የሆነውንም ለእኛ ስለሰጠን እኛና ጠላታችን ሰይጣን መለያየታችን በመስቀሉ ተረጋግጧል፤ እኛና ሰይጣን ለተለያየንበት የአምላካችን መስቀል ምልክቱ ደመራ መሆኑ የእኛን ወደ እርሱ መሰብሰብ የጠላታችንን መበተን የሚያስረግጥልን ነው፡፡ እስከ መስቀል ድረስ ባሉት ቀናት ሲናገር የነበረውን ትዝ ይበላችሁ! ‹‹ወብየ ካልዐትኒ አባግዕ እለ ኢኮና እምዝንቱ አጸድ ወኪያሆንኒ ሀለወኒ አምጽኦን ዝየ፤ ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱንም ላመጣቸው ይገባኛል›› ዮሐ10÷16 በማለት ሊሰበስበን እንደመጣ ይናገራል፡፡ መስቀሉ ፍጥረት አንድ ደመራ ሆኖ የተሠራበት ስለሆነ በደመራ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፤ መስቀሉ አንድ ደመራ ያደረጋቸውን በድምሩ ከማየት ይልቅ በዝርዝር ለማየት ያክል በቀጣይ የጡመራ መድረክ ይጠብቁን!
ይቀጥላል
0 comments:
Post a Comment