• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ ምዕራፍ ዐሥራ አንድ፡-


    የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎችትርጓሜ፡-

    ምዕራፍ ዐሥራ አንድ፡-

    v  ይህ ምዕራፍ በእግዚአብሔር ማዳን ሥፍራ የአሕዛብን በእምነት መተከል የሚያሳይ ምዕራፍ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የእስራኤልን የወደፊት ሁኔታ የሚገልጥ ስለሆነ ለእስራኤልም የተስፋ ምዕራፍ ተብሎ ይጠራል::

    v  ቁጥር 1-6

    Ø  የዚህ ክፍል ማለት ከቁጥር 1 – 6 ያለው ማለት ነው ዋና ነገር “እንግዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን?” የሚል ጥያቄያዊ ቃል ነው:: ምክንያቱም በዚሁ መልዕክት ምዕራፍ 10፥21 ላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር ቀኑን ሁሉ እጆቹን ወደ እስራኤል ቢዘረጋም እስራኤል እንቢ በማለት ጥሪውን ተቃውመው ነበርና::

    Ø  በዚህ ምክንያት እስራኤል ጠቅላላው ተጥለዋልን? በማለት ሐዋርያው ቀጣዩን ነገር ማስረዳት ይፈልጋል::

    Ø  መልሱም “ኸረ ከቶ አይደለም” የሚል እንደሆነ በመግለጥ እግዚአብሔር የእስራኤልን መዳን ጨርሶ እንዳልዘጋው ለማሳየት ራሱን በምሳሌነት ያቀርባል::

    Ø  ይኸውም የእግዚአብሔር አምላካዊ ምርጫ የሚያምነውን ሁሉ እንደሚያጠቃልል፣ እንዲሁም ለመዳን የሚሆን ማንም የለም ተብሎ ተስፋ በሚቆረጥበት ጊዜም ቢሆን ሰው ባያውቃቸውም እግዚአብሔር የተመለከታቸው ለድኅነት የሚሆኑ እንደሚኖሩም የኤልያስን ዘመን በመጥቀስ ያስተምራል::

    Ø  እንደ ነቢዩ  ኤልያስ እይታ በዚያን ዘመን እግዚአብሔርን የሚያመልክ እና ለእግዚአብሔር የሚቀና ከእርሱ ውጭ ማንም ያለ አልመሰለውም ነበር::

    Ø  “ለበዓል ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቻለሁ” ይህ ለነቢዩ  የተሰጠ አምላካዊ መልስ ነው::

          ዐይንን ከራስ ላይ አንስቶ ወደ እግዚአብሔርና አሠራሩ ማተኮር ምንኛ የተባረከ መንፈሳዊ እረፍት ነው!!

    Ø  እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በፀጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ (11፥5):: ይህም የሚያስረዳን የማንም ሁኔታ ለመዳን አይሆንም በተባለበትና ተስፋ በተቆረጠበት ወቅትም ቢሆን በመለኮታዊ ፈቃዱና በፀጋውም ምርጫ ለድህነት የተጠሩ ደግሞም የተመረጡ የመኖራቸውን እውነት ነው::

    Ø  ይህን ለድኅነታችን የተመረጥንበትን የፀጋ ምርጫ ማጣጣልና የዳንበትን የኪዳን ደም መርገጥ ስርየት የሌለው ኃጢአት እንደሆነ ተፅፎልናልና እናስተውል (ዕብ 10፥29-31)::

    v  ቁጥር 7-10

    Ø  ይህ ክፍል እስራኤል በአብዛኛው የተስፋውን ቃል  እንዳልተቀበሉ የሚያስረዳን ክፍል ነው::

    Ø  ምክንያቱ ደግሞ:

    ·         የልባቸው እልከኝነት፤

    ·         የኅሊናቸው መደንዘዝ /ትኩረት አልባ መሆን/

    ·         ዐመፀኝነትና ተቃውሞአቸው /ማር 3፥22፣ ዮሐ 12፥37፣ ሮሜ 10፥21/

          ዐመፀኝነትና ተቃውሞ ከሚያመጣብን ትልቁ ችግር ዋነኛው የመልካም ነገሮች ግርዶሽ ወይም በጎ  ኅሊናን ማጣት ነው:: ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የመጨረሻው የውድቀት ዳርቻ ነው::

    Ø  በዚህ ክፍል በቁጥር 9 ላይ የተጠቀሱ:

    ·         ማዕዳቸው ወጥመድና አሸክላ፣ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤

    ·         ዐይኖቻቸው እንዳያዩ  ይጨልሙ፤

    ·         ጀርባቸውንም ዘወትር አጉብጥ የሚሉት የመዝ 68፥22-23 ቃላት ልናስተውላቸውና ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡን አምላካዊ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው:: ምክንያቱም ይህ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን በሚወዱት ላይ የሚሆን የማይለወጥ የእግዚአብሔር ፍርድ ነውና (ዮሐ 3፥17-21፣ ሮሜ 1፥24፣ 26፣ 28)

    ማስገንዘቢያ :-

    Ø  ይህ ከቁጥር 1 እስከ 10 ድረስ የተነገረው ቃል ዛሬ ላለነውም ክርስቲያኖች ከፍ ያለ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው:: ምክንያቱም ሰው ወንጌልን ፈጽሞ ሰምቶ ወዲያው መታዘዝ ወይም ማመን ካልቻለ ሁለተኛ ሰምቶ የመቀበሉ ወይም የመታዘዙ እድል እጅግ የጠበበ ወይም ከቶ የማይቻል ነውና:: ይህም የሚሆነው:-

    ·         ባለመቀበሉና ባለማመኑ ከምርጫ ውጪ የሚያደርገው የእግዚአብሔር ውሳኔ ይመጣበታልና (ዕብ 12፥16-17፣ 2ቆሮ 6፥1-2)

    v  ቁጥር 11-16

    Ø  “እንግዲህ የተሰናከሉት እስኪወድቁ ድረስ ነውን?” ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ተሰናክለው የወደቁት እስራኤል የመነሣት ተስፋ የላቸውም ወይ? የሚል አንድምታ ያለው ነው::

    Ø  መልሱ ደግሞ “የለም ከቶ አይደለም” ነገር ግን የአሕዛብ መዳን አስቀንቶአቸው እንዲመለሱና እንዲያምኑ ነው:: ይህም አስቀድሞ ያለውን አምላካዊ ቃል የሚያስታውስ ነው::

    ·         “እነርሱ አምላክ ባልሆነው አስቀንተውኛልና እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ” ብሎ ነበርና (ዘዳ 32፥21)

    Ø  በእርግጥም እስራኤል ባለመታዘዛቸው የወንጌሉ አገልግሎት ወደ አሕዛብ ዘወር ብሏል (ሐዋ 13፥44፣ 48)

    ማስገንዘቢያ:- ይህ ከቁጥር 11-16 ያለው ክፍል በአፅንዖት የሚያስረዳን:

    Ø  የእስራኤል በኩራት ማለትም የቀደሙት (አብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ) ቅዱሳን ስለሆኑ እስራኤል (ልጆቻቸው) የሚቀደሱበት ዘመን እንደሚመጣ፤

    Ø  ያም ዘመን የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ መድኅናቸው ዘወር የሚሉበት ዘመን እና ክርስትናን የሚቀበሉበት ዘመን እንደሆነ፤

    Ø  ስለዚህም እኛ በእምነት በኩል ሕዝብ የሆንን (1ጴጥ 2፥9) ያን ዘመን በተስፋ እየጠበቅን በፀሎት የእስራኤልን ቅሬታ ልናስብ እንደሚገባን::

    v  ቁጥር 17-24

    Ø  በእነዚህ ቁጥሮች ላይ ታላቅ የወይራ ዛፍና ቅርንጫፎችዋ በምሳሌነት ተመልክተዋል:: ስለሆነም :-

    ·         ዛፊቱ : የተስፋ ቃል ናት::

    ·         ስሮቿ : የተስፋ ቃል የተሰጣቸው አባቶች ናቸው::

    ·         ቅርንጫፎቿ : እስራኤላውያን ነበሩ::

    ·         ዘይቱም : የተስፋው ቃል መፈፀምና የበረከት መገኘት ነው::

    Ø  የተስፋው ቃል የሚፈፀመው በእምነት ነውና እምነት የሌላቸው ቅርንጫፎች (ያላመኑት እስራኤላውያን) ከዛፉ ተቆርጠው ወድቀው የተስፋውን ቃል በእምነት የተቀበሉትና የበረሃ ወይራ ተብለው የተገለጡት አሕዛብ በዛፊቱ ላይ ገብተዋል (ተተክለዋል)

    ማስገንዘቢያ :-

    1.      በዘመናችን በእምነት ተመክተው አይሁድን የሚጠሉ ካሉ የሚከተሉትን ቁም ነገሮች ልብ ሊሉ ይገባል:: ይኸውም:

    ·         ይህ ጥላቻ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑንና ያመንነው እኛ ለእነርሱ ባለ እዳ መሆናችንን፤

    ·         መዳናችን የመጣው ከእነርሱ መሆኑን (ዮሐ 4፥22)፤

    ·         የነቢያቱ ምስክርነት የሆነልን ከእነርሱ እንደሆነ፤

    2.     በእስራኤል አሁን ከሆነባቸው ነገር ለራሳችን ማስጠንቀቂያ እንድንወስድ የሚያስፈልግ መሆኑን መገንዘብ (ምዕ 11፥20)

    3.     እግዚአብሔር የእስራኤልን ልብ እልከኛ በማድረግ ፍርዱን እንደገለጠ እኛንም በመምረጡ ቸርነቱን እንዳሳየ ልናስተውል ይገባናል::

          በእግዚአብሔር ዘንድ ቸርነቱ ብቻ ሳይሆን ፍርዱም ስፍራውን ይዞ እንዳለ የምናስብ ምን ያህሎቻችን እንሆን?

    v  ቁጥር 25-32

    Ø  “ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምስጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ” (ቁጥር 25)

    Ø  የቱን ምስጢር እናውቅ ዘንድ?

    ·         ድንዛዜው የሆነው በሁሉ በኩል ሳይሆን በአንዳንድ  በኩል መሆኑን፤

    ·         ይህም ድንዛዜ የሆነባቸው ለጊዜው እንጂ ለዘለዓለም አለመሆኑን፤

    ·         ይህም “እስከ” በሚል ቃል ማለትም የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል::

    Ø  ይህም በኋለኛው ጊዜ እስራኤል ሁሉ እንደሚድኑ የሚያመለክት ነው::

    Ø  ነቢዩ ኢሳይያስ ኪዳኑ ለእስራኤል በሞላ እንደሚፈፀም እና እስራኤልም ተመልሰው ወደ ዛፊቱ (ወደ ተስፋይቱ) እንደሚገቡ አስቀድሞ አመልክቷል:: (ኢሳ 59፥20-21፣ 27፣ 29)

    Ø  በዚሁ በሮሜ መልዕክትም “የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?” ተብሎ ተፅፏልና (ሮሜ 3፥3) እግዚአብሔር የገባውን ቃል ይፈፅም ዘንድ በቃሉ ታማኝ ነው::

    Ø  ታዲያ ይህ የእስራኤል ሙላት (የእስራኤል መላዋ መዳን) የሚሆነው መቼ ነው?

    ·         መድኃኒት ከፅዮን ሲወጣ (ምዕ 11፥26 ፣ ኢሳ 59፥20-21)፤

    ·         ይህም ማለት ጌታችን ተመልሶ ወደ ዓለም ሲመጣ ያን ጊዜ የወጉት ሁሉ ያዩታል ስለእርሱም ያለቅሳሉ (ራዕ 1፥7)፤

    ·         በዚያን ጊዜ መታወራቸው ይወገድና በእርሱ ያምናሉ፤

    ·         ለእርሱ የሚሆነውም ሕዝብ በአንድ ቀን ይወለዳል (ኢሳ 66፥8)፤

    ·         ገና ወደፊት የእስራኤል ሕዝብ በዓለም ነገዶች መካከል ለምስጋናና ለበረከት ይሆናሉ (መዝ 86፣ ኢሳ 19፥24፣ 35፣ 66፥10-22፣ ሆሴ 14፥4-8፣ ሰፎ 3፥14-20)::

    v  ቁጥር 33-36

    Ø  የዚህ ክፍል መሪ ሐሳብ “ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን ባለመታዘዝ ዘግቶታል” የሚለው የቁጥር 32 ቃል ነው::

    Ø  ይህም የሚነግረን ምስጢር የእግዚአብሔር እንኳን በረከቱ ፍርዱም ቢሆን ለመዳን የሚቀሰቅስ አዋጅ መሆኑን ነው::

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ ምዕራፍ ዐሥራ አንድ፡- Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top