ኹለተኛ ክፍል
እግዚአብሔር ለቅዱሳን የሰጣቸው ሥልጣን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በክፍል አንድ ምልክታችን መግቢያውን አይተናል፡፡ በክፍል ሁለት ቅኝታችን ደግሞ ቅዱሳን በግዑዛን ፍጥረታትና በርኩሳን መናፍስት ላይ ያደረጉትን ድንቅ ገቢረ ተዓምራት እንመለከታለን፡፡
በግዑዛን ፍጥረታት ላይ
ግዑዛን ፍጥረታት የሚባሉት ሰማይና ምድር፣ ፀሐይና ጨረቃ ሲሆኑ ሰማይና ምድር የእግዚአብሔር ሥራዎች እንደሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፤ የፈጠራቸውም እርሱ ነው፡፡ /ዘፍ 1፥1/ የፈጠረውን ፍጥረት ማዘዝ የሚችለው ባለቤቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ነገር ግን ለአምላክነቱ ቀናዒ ለሕጉ ተቆርቋሪ ለሆኑ ቅዱሳን በሰማይና በምድር ላይ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ለቅዱሳን በሰማይና በምድር ላይ ሥልጣን እንደሰጣቸው ሲናገር “ኤልያስ እንደኛው የሆነ ሰው ነበረ፣ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ ሰማዩም ዝናብ ሰጠ” /ያዕ 5፥17/፡፡ ሰማይና ምድር ማዘዝ ዝናብንም ማዝነብም መከልከልም የሚችለው እግዚዘብሔር አምላክ ሲሆን ነብየ እግዚአብሔር ኤልያስ ግን በአምላኩ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን ሥራ ሲሠራ እንመለከታለን፡፡
ኤልያስ አስቀመድሞ በብሕትውናና በድንግልና ሕይወት በቀርሜሎስ ተራራ የኖረ፣ ንጉሥ አክአብንና ሚስቱን ንግሥት ኤልዛቤልን የእግዚአብሔርን ሕግ ሲጥሱ አይቶ እናዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ሳይል በድፍረት የገሠጸ፣ ሕዝቡን ለማሳት ይተጉ የነበሩ የሐሰት ነቢያትንና ጣዖት አምላኪ ሰዎችን ከስህተታቸው እንዲመለሱ ያስተማረ እውነተኛ ነቢይ ነው፤ የእግዚአብሔር ነቢይ ኤልያስ ስለፈጣሪው ቀንቶ መከራ በመቀበሉ የፈጠረው አምላክ በሰማይና በምድር ላይ እንዲያዝ ሥልጣን ተሰጠው፡፡
ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ምድር የተዘራባትን ፍሬ እንዳታበቅል አዘዘ፤ ሰማይና ምድርም የእግዚአብሔር ነቢይ ያዘዛቸውን ፈጸሙ በዚህ ምክንያት በረሃብና መጥም ሕዝቡ ሲያልቅ እግዚአብሔር ለቅዱሳን የሠጠውን ተአምር የማድረግ ሥልጣን አልቀየረም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ኤልያስ ጸልዮ ሰማይ ዝናብ እንዲሰጥ ምድርም የዘሩባትን እንድታበቅል እስኪያደርግ ድረስ እግዚአብሔር በሥራው አልተቃወመም፤ ሥራውን እንዲሠራ ሥልጣን የሠጠው እርሱ ነውና፡፡
የሥነ ፍጥረት ትምህርት ላይ ፀሐይና ጨረቃ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩ ፍጥረታት እንደሆኑና አገልግሎታቸውም ለሰው ብርሃን እንዲሰጡ ለጊዜ መለኪያነት እንዲያገለግሉ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ /ዘፍ 1፥17/ ፀሐይና ጨረቃን ከተፈጥሮ ሥርዓት በሆነ መንገድ ቅዱሳን ሲጠቀሙባቸው እናያለን፡፡
ኢያሱ ወልደ ነዌ ፀሐይና ጨረቃ ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ መልኩ እንዲህ በማለት አዘዛቸው “በገባዖም ላይ ፀሐይ ትቁም በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፣ ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይም ቆመ ጨረቃም ዘገየ፤ አንድ ቀን ያህልም ለመግባት አልቸኮለም” /ኢያሱ 10፥12-14/፡፡ ኢያሱ ከሕፃንነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን ያመልከው የነበረ፣ ከሙሴ ጋር ሆኖ ደብረ ሲና የወጣ፣ ከሙሴ በኋላ ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን የመራ፣ በእግዚአብሔር መልአክ ፊት በፍርሃት በግንባሩ ወድቆ የአክብሮት ስግደት የሰገደ በመሆኑና አምላኩን የሚያስደስት ሕይወት ስለነበረው ፀሐይና ጨረቃን እንዲያዛቸው እግዚአብሔር አደረገው፤ እግዚአብሔር ከኢያሱ በኋላ ለተነሡ ቅዱሳን ለአቡነ አሮን፣ ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ፣ ለቅዱስ በርሶማና ለአባ ዜና ማርቆስ ፀሐይና ጨረቃን የማዘዝ ሥልጣን ሰጥቶቸዋል፡፡
በርኩሳን መናፍስት ላይ
ርኩሳን መናፍስት ሰውን በመቆራኘት ድዳ፣ ደንቆሮ፣ ሽባ፣ ዓይነስውር በማድረግና የመሳሰለውን ደዌ በማሳደር የሰውን ልጅ ሲያሰቃዩ የሚኖሩ ናቸው፡፡ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ እነዚህ ርኩሳን መናፍስት በቃለ ኃይሉ እያዘዘ በማባረር ዲዳዎችና ደንቆረዎች እንዲናገሩና እንዲሰሙ፣ ዕውራን እንዲያዩ፣ አንካሶች እንዲሄዱ፣ ጎባጣዎች እንዲቀኑ በማድረግና ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸውን ሰዎች በመፈወስ የቸርነቱን ሥራ ሠርቶአል፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን እንመልከት፡-
• “ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ ገሠጸውና አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ እኔ አዝኃለሁ ከእርሱ ውጣ፤ ከእንግዲህም አትግባበት አለው ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ” /ማር.9፥15-16/፡፡
• “እነሆም ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ጎባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም፡፡ ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና አንቺ ሴት ከድካምሽ ተፈወሺ አላት እጁንም ጫነባት ያን ጊዜም ቀጥ አለች፡፡ እግዚብሔርንም አመሰገነች” /ሉቃ.13፥11-14/፡፡
• “በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኩስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ የእግዚብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ ኢየሱስም ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው ርኩሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ” /ማር.1፥13-16/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱና በፈጣሪነቱ ርኩሳን መናፍስትን እንደሚያዛቸውና እንደሚያወጣቸው ሁሉን ትተው በፍጹም ሰውነታቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ለተከተሉት ቅዱሳን ደግሞ በጸጋ ይህንን ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል፡፡“ዐሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው” እንዲል /ማቴ. 10፥1/፡፡ ይህ ሥልጣን የተሰጠው ዓሣ ያጠምዱበት የነበረውን መረባቸውን ቤታቸውንና ያላቸውን ሁሉ ጥለው ለተከተሉት ለሐዋርያትና ሐዋርያትን አብነት አድርገው ለሚነሡ ሁሉ እንጂ ኀብስት አበርክቶ ሲመግብ ለተገኘው ሁሉ ወይም ሲያስተምር ለተለያየ ዓላማ ይከተለሉት የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ አይደለም፡፡ በዚህም ቅዱሳን በተሰጣቸው ሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ሲያስወጡና ሰውን ከሰይጣን ቁራኝነት ነጻ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ከአምላኩ በተሰጠው ሥልጣን በአንዲት ሴት አድሮ ወጥመድ ሲያዘጋጅ የነበረውን የምዋርተኝነት ርኩስ መንፈስ አስወጥቶአል፡፡ “ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን፡፡ እርስዋም ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑለ አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኸ ነበር፡፡ ይህንንም እጅግ ቀን አደረገች፡፡ ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ” /የሐዋ. 16፥16-18/ እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ነገር ይህ ርኩስ መንፈስ ለሰዎቹ የመዳንን መንገድ ካመለከተና እነ ቅዱስ ጳውሎስን እንዲሰሙ ከተናገረ ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ተቸገረ÷ ለምንስ ይህንን ርኩስ መንፈስ አስወጣው÷ ሰይጣን ሁል ጊዜ ለሰው ልጅ የጥፋትን ወጥመድ የሚያዘጋጅ ስለሆነ እነ ቅዱስ ጳውሎስን የተቀበለ በመምሰል ሕዝቡ በወንጌል አምኖ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ እንኳ ወደ ቤተ ጣዖት መሄዱን እንዳይተውና ድኅነታቸው ፍጹም እንዳይሆን ነው፡፡ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት ለሰይጣን መሠዋትንና ወደ ቤተ ጣዖት መሄድን ሲከለክሉአቸው፤ እኛኮ እናንተንም ያገኘናችሁ በእርሱ መሪነት ነው እንዲሉና እርሱ ከሰዎች ሕሊና እንዳይወገድ ለማድረግ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ያስወጣው ይህንን ተንኮሉን ስላወቀበት ነው፡፡ ከዲያብሎስ መልካም ነገር መጠበቅ ከዝንብ ማር፣ ከእባብ እንቁላል እንደመጠበቅ ያለ ነው፡፡
ቅዱሳን ከአምላካቸው በተቀበሉት ሥልጣን መሠረት ሰይጣንን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያስወጡታል፡፡ ሐዋርያት አጋንንትን አስወጥተው ሲመለሱ ደስ ብሎአቸው“ጌታ ሆይ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል”ሲሉት ይህ ለጊዜው በእነርሱ ብቻ ተወስኖ የማይቀር መሆኑን “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ሲወድቅ አየሁ” እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፡፡ በማለት ሥልጣኑን እንደሰጣቸው ነገራቸው፡፡ ይልቁንም ሰይጣንን ማስወጣት ትልቅ ነገር አለመሆኑና ሊደሰቱ የሚገባቸው በምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ነገራቸው “ነገር ግን መናፍስት ስተለገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ በሰማያት ስለተጸፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ” /ሊቃ. 10፥17-20/፡፡ ምክንያቱም አጋንንትን እስከማውጣት ደርሰው ነገር ግን ለእግዚብሔር መንግሥት ያልበቁ እንደ ይሁዳ ያሉ አሉና፡፡ /ማቴ. 7፥10-13/፡፡
ይቀጥላል
0 comments:
Post a Comment