• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    እግዚአብሔር ለምን ይናገራል?

    በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ቃል በእኛ ዘንድ ካለው ቃል የተለየ ቃል ነው፡፡ ከእኛ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው ካላችሁኝ በእርሱ ዘንድ ያለው ቃል ዓለም የተፈጠረበት ቃል እንጅ እንደ እኛ የተፈጠረ አይደለም፤ ዮሐ 1÷3 የእኛ ቃል አካል የሌለው ዝርው ሲሆን የእርሱ ቃል ግን ከልብ ከእስትንፋስ የተለየ ሦስተኛ የሥላሴ አካል ነው፤ በእኛ ዘንድ ያለው ቃል ስም የሌለው ሲሆን በእርሱ ዘንድ ያለው ቃል ግን በተለየ ስሙ ወልድ ተብሎ የሚጠራ አካላዊ ስም አለው፤ የእኛ ቃል ያልነበረበት ጊዜ ያለውና ኋላም በሞት የሚወሰን ሆኖ ሳለ የእርሱ ቃል ግን አርምሞና ጽርዓት የሌለበት ነው፡፡ እኛ ምናውቀው ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዘመን ነውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ሰሚ ከተገኘ ሳያቋርጥ ይናገራል፡፡ 

    ግን እግዚአብሔር ለምን ይናገራል?

    1. ሌሊቱ እንዲነጋ፡-

     ይህች ዓለም በጨለማ ተጀምራ በጨለማ የምታበቃ ክፉ ዓለም እንደሆነች የታመነ ነው፡፡ በተፈጠረችበት በዚያ በመጀመሪያው ቀን የነበራት ሌሊት አብረዋት በእለቱ የተገኙትንና ከባዶነት የገላገሏትን ብርሃናውያን ፍጥረታትን መላእክትን ጭንቀት ውስጥ ያስገባ አስጨናቂ ለሊት ነበር፤ መላእክት ከብርሃን መፈጠራቸው የከበባቸውን ጨለማ ሊያርቅላቸው አልችል ብሎ በከበባቸው ጨለማ ከተማቸው ተሸበረ፤ ጨለማው ሌላ ጨለማ ፈጠረባቸውና ዲያብሎስ ልንገሥባችሁ አለ፤ ብቻ ያ ጨለማ መዘዙ ብዙ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ጭንቀት ውስጥ ለነበሩ መላእክት ሰምተውት የማያውቁት የእግዚአብሔር ድምጽ ካልሆነ ሌላ ከዚህ ሁሉ ሊገላግላቸው የሚችል ምን ሊኖር ይችላል፡፡ በእርግጥም ይህ ሁሉ ችግርና ጭንቅ ነገር እግዚአብሔር እስኪናገር ድረስ ነበርና እግዚአብሔር ሲናገር ሁሉም ተስተካከለ፡፡

    ዓለም እንድትስተካከል አሁንም የእግዚአብሔር ድምጽ አስፈላጊ ነው፡፡ ያስጨነቀን ሌሊት እንዲነጋ ሽብር የፈጠረብን ነገር እንዲረጋጋ በዙሪያችን ካሉት ጋር አንድ ልሳን እንድንነጋገር እግዚአብሔር ሊናገር ግድ ነው፡፡ እግዚአብሔር እስኪናገር እኮ ነው መላእክት ከአራት ተከፍለው አንዱ ክፍል እንጦርጦስ ሁለተኛው ክፍል በዐየር ሦስተኛው በዚህ ምድር ዐራተኛውም በሰማይ ተነጣጥለው የቀሩት እግዚአብሔር ካልተናገረ በባልና በሚስት በወንድምና በእህት በአባትና በልጅ በአማትና በምራት በጎረቤትና በጎረቤት መካከል አንድነት እንዴት ሊኖር ይችላል፤ መተማመን ይጠፋል አንድነት ፀሐይ እንደነካው ጉም ይሆናል ፍቅር እንደ ጤዛ ፈጥኖ ይረግፋል ውበት እንደ ቅጠል ይጠወልጋል እግዚአብሔር ካልተናገረ ሁሉም ከንቱ ይሆናል፡፡

    እግዚአብሔር ካልተናገረ ማን ራሱን ያውቃል፤ እውቀት የሚጀምረው ራስን ከማወቅ ሲሆን የመጀመሪያው ጥያቄም እኔ ማነኝ የሚለው ነው፤ መላእክት የጀመሩበት የመጀመሪያው ጥያቄም ይህ ነበር ‹‹መኑ ፈጠረነ ወእምአይቴ መጻዕነ፤ ማን ፈጠረን ከወዴትስ መጣን›› በሚል እርስ በእርሳቸው መነጋገር ጀመሩ አዋቂ ነኝ የሚል ማንኛውም ሰው ሊጠይቀው የሚገባ ሰውም ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄም ይህ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ራስን ከማወቅ የሚቀድም እውቀት ስለሌለ ነው፡፡ ታዲያ መልሱ ከእግዚአብሔር ቃል እንጅ ከሌላ አይደለምና እርሱ እስኪናገር ዝም ብሎ መጠየቅ መልካም ነው፤ ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን መናገር የማይጠብቅ ሰው እንዴት ራሱን ማወቅ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር የሚናገረውን ማዳመጥ በእርግጥም ራስን ወደ ማወቅ ያደርሳል፡፡

    እውቀት ለተከፈለባቸው መላእክት የእውቀት አድማሳቸውን ያሰፋ ዘንድ እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረበት ቃሉ ተናገረ፤ ‹‹ለይኩን ብርሃን›› አለ ያን ጊዜ ነው ኅሊና መላእክት በእውቀት የተሞላችው፤ እግዚአብሔር እስኪናገር ዝም ብለው በተስፋ ይጠብቁት የነበሩ መላእክት ሁሉ አንድ ላይ ቃላቸውን ከፍ አድርገው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› ሲሉ ይኖራሉ፡፡ ሃይማኖታቸውን የገለጠላቸው የእግዚአብሔር መናገር ነበር የሃይማኖት ምሥጢር እንዲገባን እግዚአብሔር ቢናገር መልካም ነው፤ ቃላችን አንድ እንዲሆን እርግማናችን በምስጋና እንዲለወጥ ሕይወታችን እንዲጣፍጥ እግዚአብሔር እንዲናገር ጸልዩ፡፡ እርሱ ዝም ካለ ሌሊታችን እንዴት ይነጋል እርሱ ባይናገር በመካከላችን ገብቶ የሚከፋፍለው ሰይጣን እንዴት ከእኛ ይርቃል እርሱ ባይናገር ከተማችን እንዴት ይረጋጋል፡፡ እግዚአብሔር ይናገረን፡፡

    2. ሰውን ሰው ለማድረግ ይናገራል፡- እንደምታውቁት ሰውን ሰው ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል እንጅ ሌላ እንዳልሆነ የተገለጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ እስኪናገር ድረስ ሰው ምን ነበረ? ካላችሁኝ ሕልውናው ያልታወቀ ሳይፈጥረው ከሚያውቀው ከእግዚአብሔር በስተቀር በማንም ዘንድ ያልታወቀ ነበር የእግዚአብሔር ቃል ግን የሌለውን ሰው ፈልጎ አመጣው ለመኖርም አበቃው፤ ሳይፈጠር እኮ አመድና ትቢያ ነበር የእግዚአብሔር ንግግር ግን ከአመድና ትቢያ ለየችው እንደ እግዚአብሔር መልክ እና አርዓያ የሆነ ሰው እንዲሆን አደረገችው፡፡ ተፈጥሮው ምድራዊ ሆኖ ሳለ ‹‹ሀገራችን በሰማይ ነው›› ብሎ እንዲናፍቅ ያደረገው የማያውቀውን የሰማይ ከተማ እንዲጠይቅ ያደረገው ሌላ ምንድነው የእግዚአብሐየር ቃል ነው እንጅ፡፡

    ሰው ሆይ! ሰው የሆንከው በእግዚአብሔር ቃል ነውና ቃሉን ከመስማት እትቦዝን ቃሉን በሚሰሙ ሰዎች ዘንድ ከንቱነት የለም፤ አለማመንም የራቀ ነው፤ ጭንቀትና ችግርም የተወገደ ነው፤ ቃሉን ስማ ብትታመም ትፈወስበታለህ ዮሐ 4÷50 ብትፈርስ ትሠራበታለህ ዮሐ 11÷39 ብታጣ ታገኝበታለህ ማቴ 17÷27 ብትሰበር ትጠገንበታለህ ማቴ 12÷13 ብታዝን ትጽናናበታለህ ሉቃ 7÷11 ዘመድ ብታጣ ዘመድ የሆንሃል ባጠቃላይ ሰው እንድትሆን ቃሉን ስማ ፡፡

    ገንዘብ ሰው አያደርግም ሹመት ሽልማትም ጠባይን አይለውጥም የስኬት ማማ ላይ መቀመጥ የሙላት ከፍታ ላይ መፈናጠጥ የልብ በደስታ መናጥ ሰው አያደርግም እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ የነበረው ናቡከደነፆር ከሰውነት ወደ አውሬነት ባልተለወጠም ነበር ዳን 4 አምላክህ እግዚአብሔር የሚናገርህን ባትሰማ እንዴት ሰው ልትሆን ትችላለህ አስተውል! ሰው የመሆንህ ምሥጢር የእግዚአብሔርን ቃል መስማትህ ነውና ሁልጊዜ ቃሉን የምትሰማ ሁን፡፡

    3. ያልጸናው እንዲጸና ነው፡- እግዚአብሔር የሚናገረው ቃል ውኃ ያጸናል ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ላይ በደረቅ እንደሚሄድ ሰው የሄደው የቆመበትን ባሕር ቃሉ አጽንቶለት ነው፤ ውሃውን ከመርከብ ይልቅ የጠነከረ ከጠጠር ይልቅ የጠጠረ አድርጎለት ያለ ምርከብ ተጓዘበት ሳያጠልቀው በላዩ ተመላለሰበት ማቴ 14፡፡ ለዚህ ዓለምም ቢሆን መሠረት ሳይኖረው የመጽናቱ ምሥጢር ቃለ እግዚአብሔር ነው ወደታች ወርዶ እንዳይወድቅ ወደላይ ወጥቶ ሰማይ እንዳይሆን ባለበት እንዲጸና ሌላ ምን ምክንያት ይኖረዋል ብላችሁ ነው፡፡

    ቃሉን የሚሰማ ጸንቶ ይኖራል፤ ባለ ትዳር በትዳሩ ፍቅረኛ በፍቅሩ ቃል የተጋባ ሰው በቃል ኪዳኑ ምዕመን በሃይማኖቱ ካህኑ በክህነቱ መነኩሴ በገዳሙ ተማሪ በትምህርቱ ድንግል በድንግልና መጽናት ለምን የሚያቅተው ይመስላችኋል፡፡ ቃሉን መስማት ያቆመ እንደሆነ ሁሉም ባለበት መጽናት ይሳነዋል ጓደኝነት በመለያየት ፍቅር በመጠላላት መተሳሰብ በመረሳሳት ዝምድና በባዳነት ማግኘት በማጣት ጤነኝነት በበሽተኛነት አዋቂነት በድንቁርና እመቤትነት በግርድና ይለወጣል፡፡ እግዚአብሔርን በመስማት ለሚጸኑ ብቻ ሁሉ ይቻላቸዋል ከሰባት ሺህ ዓመት በላይ እርጅና ሳይኖርበት ምድርን ከድኖ ስለቆመው ሰማይ ሲናገር ነቢዩ የተናገረው ቃል ምንኛ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹ወበቃለ እግዚአብሔር ጸንዓ ሰማያት፤ ሰማያት በእግዚአብሔር ቃል ጸኑ›› መዝ 32 በማለት ለዚህን ያክል ዘመን መጽናታቸውን በማድነቅ ይናገራል፡፡ የእኛ ቤት ጠባብ ስትሆን ስንት ድጋፍ ያስፈልጋት ይሆን በእኛ እድሜ የተሠራች ሲሆን ስንት ጊዜ ታድሳ ይሆን ያለ እርጅና ሁል ጊዜ አዲስ ሆኖ የሚኖር ምንም አይነት ቤት ሊኖረን አይችልም የእግዚአብሔር ቃል ያጸናው ይህ ሰማይ ግን ሁል ጊዜ አዲስ ነው፡፡

    ለካ ቃሉን የሚሰሙ እንዲጸኑ በማድረጉ ነው ሙሴ በሲና ተራራ አርባ ቀንና ሌሊት ያለ መብልና መጠጥ የቆየው፣ ኤልያስ እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ የተጓዘው፣ አባ ተክለ ሃይማኖት ለሰባት ዓመት በአንድ እግር የቆመው፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሰባት ዓመት በእያንዳንዱ እለት ነፍስ ከሥጋ የሚለይ ብርቱ ብርቱ መከራን የተቀበለው የሰማዕታት ልብ ወደ እሳትና ስለት ያለመፍራት የገሠገሰው፣ የጻድቃንም ልብ ዓለምን ንቆ ወደ ገዳም የኮበለለው ቃሉን የሚሰሙትን የሚያጸናቸው እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ አንተኮ በገባኸው ቃል ላለመጽናትህ ለክርስትና ሕግ ታማኝ ላለመሆንህ፣ በቅዱስ ቁርባን ላለመወሰንህ፣ አንድ ጊዜ ወደ መዝሙር ሌላ ጊዜ ወደ ዘፈን ለመመላለስህ፣ በእግዚአብሔር ፊት የማትወደውን ኃጢአት ለመፈጸምህ ምክንያቱ ቃሉን አለመስማትህ ነው፡፡ ግድ የለህም ቃሉን የምትሰማ ሁን ያን ጊዜ ባለህበት ትጸናለህ፡፡ ዛሬ የምትጾም ነገ የምትበላ፣ ዛሬ የምታምን ነገ የምትጠራጠር፣ ዛሬ ቄስ ነገ የምታጨስ አትሆንም በመንፈስ ጀምረህ በሥጋ እንዳትጨርስ ከጎኑ በፈሰሰ ማየ ገቦ የተቀደሰች በደሙ ፈሳሽነት የተፈወሰች ነፍስህ እንዳትረክስ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ እንዲፈስ፣ የወጣው ልብህ እንዲመለስ፣ በኃጢአት የወየበው ማንነትህ እንዲታደስ ቃሉን የምትሰማ ሁን፡፡

    አንተ ካልተጠቀምክበት እግዚአብሔር ሌላ ለምን ለምን ይናገራል፤ ያንተ ደዌ ካልተፈወሰ፣ ሰላምህ ካልተመለሰ፣ እርጅናህ ካልታደሰ፣ ጉስቁልናህ ካልተቀደሰ፣ እውቀትህ ካልጎለመሰ፣ ለምን ይናገራል፤ ግድ የለህም እመንና እንደ አባትህ ዳዊት ‹‹አጸምዕ ዘይነብበኒ እግዚአብሔር አምላኪዬ፤ ፈጣሪየ እግዚአብሔር የሚናገረኝን አዳምጣለሁ›› መዝ 84 በል፤ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሰላምን ይናገራልና ሰላም በሌለው ዓለም ውስጥ ስትኖር በሰላም እንድትኖር ያደርግሃል በጨለማ ውስጥ ብትሄድ እንኳን ለመንገድህ ብርሃን ይሆንልሀል፡፡

    4.ወገኖቹን ሁሉ ከሞት ሊያድናቸው፡-

    ምን አልባት የሞት መንገድ ምንድነው ብሎ የሚያስበ ሰው ካለ መልሱ አንድ ነው ቃሉን አለመስማት ነው፤ የሞት መጀመሪያው ቃሉን አለመስማት ነውና፡፡ ሰው ሞትን ሳያውቅ የቆየባቸው ጥቂት ዓመታት ምን ዓይነት እንደሆኑ ማወቅ ትፈልጋላችሁ ቃሉን በመጠበቅ የተመላለሰባቸው ዓመታት ናቸው፤ ቃለ እግዚአብሔር የሰው ሕይወት መጠበቂያ ነው ማለት ነው፡፡ ቃሉን የማንጠብቅ ሆነን የመጣብን ሞት እንደ ገና ቃሉን በመጠበቅ እንደሚወገድልን የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ዘአቀበ ቃልየ ኢይጥዕሞ ለሞት፤ ቃሌን የሚጠብቅ ሞትን አይቀምስም›› ዮሐ 8÷51 በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ ለዚህ ነው የሕይወት እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም በቅዱስ ሜጽሐፍ ውስጥ ቃሉን ትጠብቅ እንደነበረ ተደጋግሞ የተመዘገበላት ሉቃ 2÷51 ቃሉን በመጠበቅ የሚቀድማት እንደሌለ የታመነ ነው ምክንያቱም ከዚያ በፊት የቃል አፍራሹ የአዳም ልጆች በመሆናችን ሁላችንም ቃሉን መጠበቅ ተስኖን ነበርና፡፡ እሷ ግን የአካላዊ ቃል እናቱ ናትና ቃሉን ጠብቃ የሞት   መድኃኒት ክርስቶስን አስገኘችልን፡፡

    እንግዲያውስ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ለምን ይናገራል ካላችሁኝስ ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጅ ማን እንዳይጠፋ ወዶ ይናገራል፤ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው በሕይወትም ይኖራሉ ቃሉን የሚጠብቁ ወደ ገነት ይገባሉ ቃሉን የማይጠብቁ ግን ከገነት ይሰደዳሉ፡፡

                                 

                                             እግዚአብሔር ከስደት ይጠብቀን !!!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: እግዚአብሔር ለምን ይናገራል? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top