በቤተክርስቲያናችን ሁሉም አማኒያን እንዲጾሟቸው ከታዘዙት 7 አጽዋማት አንዱ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ የሐዋርያት ጾም በዓለ ጰራቅሊጦስ ከዋለበት ቀን ቀጥሎ ባለው ዕለት ጾሙ የሚጀመር ሲሆን በቅዱ ጴጥሮስ እና በቅዱስ ጳውሎስ በዓለ ዕረፍት ሐምሌ 5 ቀን ጾሙ ይፈጸማል፡፡ የቀኑ እርዝማኔም የፋሲካን (የትንሣኤን) በዐል ቀን መሰረት አድርጎ ከ45 ቀን እስከ 15 ቀን ሊረዝምና ሊያጥር ይችላል፡፡
የሐዋርያት ጾም መጾም የተጀመረው መቼ ነው?
በቀድሞው ዘመን ጾመ ሐዋርያት በዓለ ጵራቅሊጦስ በዋለ በሳምንቱ የሚጀመር ሲሆን የሚፈፀመውም በእመቤታችን ጾም ፍጻሜ ነሐሴ 16 ቀን እንደ ነበረ አንዳንድ መዛግብት ያሳያሉ። ቤተክርስቲያን ይህ ጾም የተጀመረው በሐዋርያት መሆኑን ስታስተምር ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በክርስቲያኖች ከሚጾሙት አጽዋማት አንዱ ስለመሆኑም የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች ምስክርነት እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህም በቅዱስ አትናቴዎስ እና በቅዱስ አምብሮስ ጽሁፎች ውስጥ የሚገኘውን ማስረጃ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አንደ ዋቢ እንጥቀሰው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ (371 ዓ.ም) በስደቱ ወቅት ለንጉስ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክቱ ውስጥ “ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በኋላ የሚጾሙ ሰዎች በመቃብር ስፍራ ይጸልዩ ነበር” በማለት ሲገልጽ ቅዱስ አምብሮስ (397 ዓ.ም) በ61ኛው ስብከቱ ማቴ 9፡ 15 ላይ “ሚዜዎቸ ከሙሽራው ሳሉ ሊያዝኑ ይችላሉን?” የሚለውን መሰረት በማድረግ “በዐቢይ ጾም ወቅት የጌታን መከራ ስናስብ እና ስንጾም እንደቆየን ሁሉ ከትንሣኤው በኋላ ባሉት ቀናት ደግሞ በትንሣኤው ምክንያት ጌታ በመካከላችን ስለሆነ ይህም ለሰውነት ደስ እንደሚያሰኝ ምግብ ስለሆነ እና በዚህም ጊዜ የፍሰሃ ምግብ የሆነውን ጌታን የምንመገብበት ወቅት በመሆኑ አንጾምም፡፡ ነገር ግን ከዕርገቱ በኋላ ወዲያው መጾም እንጀምራለን፡፡ ” በማለት የሰበከውን ስብከት መሰረት በማድረግ ጾሙ ጥንታዊነት ያለው መሆኑን ማወቅ ይቻላል፡፡
ሐዋርያት ከትንሣኤ በኋላ ወደ ዓለም ተላኩ በተለይም መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ በድፍርት እና በኃይል ሰበኩ ለዚህም ሐዋርያት ልክ እንደ ነቢያትና እንደ ጌታቸን የአገልግሎት ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ጾሙ፣ በአገልግሎታቸውም ልክ እንደ ጌታችን በሥራ የሚረዷቸውን 7 ዲያቆናት እንዲሁም ሌሎች ሽማግሌዎችን ሾሙ፣ ጌታ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል የሚባለወን የሐዲስ ኪዳን ሕግ እንዳወጀ ሁሉ ሐዋርያትም የመጀመሪያ የቤተክርስቲያ ጉባኤ የሚባለውን አረማውያን ክርስቲያን ሆነው ለመኖር የሚያስችላቸውን ሕግ ደነገጉ እና ክርስቶስ መድሐኔዓለም መሆኑን ለዓለም ሁሉ አሳወቁ። ቤተክርስቲያን እንደ አዲስ እንድታንሰራራና ኃያል እንድትሆን በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ብዙ ደከሙ ክርስቲያኖችም ከሌላው ሕዝብ የሚለዩበትን ትምህርትና ስርዓት አዘጋጅተው አስተማሩ ይኸው እስከ አሁንም ድረስ ክርስቲያኖች ይህንን ትምህርት ጠብቀው እና ከትውልድ ትውልድ እነዲተላለፍ እያደረጉት ነው።
ጾመ ድኅነት (የረቡዕና አርብ ጾም)
የሐዋርያት ጾም ሰኞ ገብቶ ረቡዕ ጾመ ድኅነት ይጀምራል። ክርስቲያኖች ይህንን ጾም በሣምንት ሁለት ቀን ረቡዕ እና አርብ የሚጾሙበት ምክንያት አለው። ረቡዕ የሚጾምበት ዋናው ምክንያት የአይሁድ ፓርላማ መድሐኔአለም ክርስቶስ ላይ ሞት የፈረደበት ዕለት በመሆኑ ይህንን የሞት ውሣኔ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ በጾም እንዲያስቡት ስለተወሰነ እንዲሁም አርብ የሚጾምበት ምክንያት ጌታ መድሐኔአለም ዓለምን እንዲያድን ለብዙ ዘመናት በተስፋ ሲጠበቅ የነበረበት ዕለት እና ተስፋውም የተፈጸመበት ቀን ስለሆነ ቤተክርስቲያን ይህ ዕለት በመጾም እንዲታሰብ ወስናለች።
የሐዋርያት በረከታቸው ይደርብን
ስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment