• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    ማደሪያውን አይቸዋለሁ


    በብሉይ ኪዳን ከነቢያት አንዱ ለእግዚአብሔር ሲሳል ‹‹ኢይሁቦን ንዋመ ለአእይንትየ ወኢድቃሰ ለቀራንብትየ፤ ለዐይኖቸ እንቅልፍን ለቅንድቦቼም ሽልብታን አልሰጣቸውም›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ እስኪያይ ድረስ ለሰውነቱ እረፍትን እንደማይሰጥ በልቡ ጽኑ መሀላን ምሎ እንደ ነበረ ተመዝግቧል መዝ 131÷2፤ እንደ ተናገረውም ‹‹ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ እነሆ በኤፍራታ በዱር ተጥሎ እንደ ኅጻናት ሲያለቅስ ሰማነው ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ አግኝቶ እስኪመለስ ድረስ ሱባዔውን አላቋረጠም::

     በሐዲስ ኪዳንም እንደዚሁ ‹‹ሊቅ አይቴ ተሐድር›› እያሉ ከሀገር ወደ ሀገር እየተዘዋወረ ያስተምር የነበረውን ጌታ በኋላው እየተከተሉ ማደሪያውን እስኪያሳያቸው ድረስ ይጠይቁት የነበሩ ሁለት ሰዎች እንደነበሩ ተጽፏል፡፡ ዮሐ1÷39 እርሱም ያልፈለጉትን የሰው ልጆች ሊፈልግ ነውና የመጣው የሚፈልጉትን ሰዎች ኑ ማደሪያዬን አሳያችኋለሁ ብሎ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ከእርሱ ጋር ውለው ማደሪያውን አይተው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡

    ለቅዱሳን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ከማየት ሌላ ደስታን የሚፈጥርላቸው ምን ነገር አለ? ማደሪያውን ፍለጋ ባሕር ያቋርጣሉ፣ በዋሻ ውስጥ መንገድ ያበጃሉ፣ ዓለም የማትገባቸው በመሆኗ የፍየል ሌጦ የበግ ለምድ ለብሰው በዋሻ በፍርኩታ ሰዎች ሆነው ሳለ ከሰው ተለይተው ይኖራሉ፣ መንገዳቸውን ከዓለም ለይተው ወደ እግዚአብሔር ይጓዛሉ፡፡

    ዛሬ ለብዙ ዘመናት የተመኘሁት ተሳክቶልኝ እኔም የእግዚአብሔርን ማደሪያ ለማየት በጣና ባሕር ጀርባ ላይ እየተጓዝሁ ነው፤ የተጫንሁበት ጀልባ ወደፊት እየተጓዘ እኔ ግን በፍኖተ አእምሮ ወደ ኋላየ ተመልሼ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 8÷23 አንድም እያልሁ እየተረጎምሁ በገሊላ ባሕር ላይ በመርከብ ብዙ ጊዜ ይመላለሱ የነበሩ ደቀ መዛሙርቱን አስታወስሁ፤ኅሊናዬ በገሊላ ባሕር እንጅ በጣና ላይ የሚጓዝ አልመስለኝ አለ መዳረሻዬም የጥብርያዶስ ማዶ ጌታ ተዓምራት ያደርግበት የነበረው ሥፍራ የገሊላ መንደር ይመስለኝ ነበር፡፡ ከመርከብ ስወርድ የጴጥሮስን አማት በንዳድ ታማ ጌታ ሲፈውሳት እንደማገኛት እያሰብሁ ነው የምጓዘው፡፡ እንዲያውም ባይገርማችሁ በአካል ሳይሆን በኅሊናዬ ተነሣሁና ጌታዬን  እንደ ሐዋርያት ከመርከቡ ጀርባ ፈለግሁት በሥጋ ሕግ ተኝቶ የማገኘውና ዓለም እንዲህ በጭንቀት ማዕበል ስትጠፋ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ መናፍቃን ስትዳፈን አይገድህምን? ልለው ፈለግሁ ውስጤን ፍርሃት ተሰማው፤ ያን ጊዜ በዘለዓለማዊ እንቅልፍ ውስጥ የነበርን እኛን ሊያነቃን ተኝቷል እንጅ ለባሕርዩ እንቅልፍ የሚስማማው ይመስልሃልን? ብሎ የሚገሥጸኝ መላኩን የላከብኝ መስለኝ፡፡

    አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከገሊላ ባሕር ወደ ጣና ባሕር ይመለስና ኅሊናዬ ከጣና ባሕር ጋር ይጨዋወታል፤ ስንት ቅዱሳን በአንተ ላይ ተረማምደዋል? ስንቶችንስ ከዓለም ለይተህ በጉያህ ደብቀህ ለክብር አብቅተሀል? አንተ ያየኸውን ምሥጢር እኔም ላየው ተመኘሁ፤ ያኔ እመ አምላክ ከተወደደው ልጇጋር በእንግድነት ወደ አንተ ስትመጣ እንዴት ነበር የተቀበልሀት? በእርግጥ ከዘመዶቿ ከቤተ ልሔም ሰዎች አንተ ትሻላለህ እነርሱ ለማደሪያ እንኳን ሥፍራ አልሰጧትም አንተ ግን ከሔሮድስ ዐይን ደብቀህ ለሦስት ወር አስተናገድሀት፤ እያልሁ የምጠይቀውን ይመልስልኝ፣ የማወራውን ይሰማኝ ይመስል አጫወትሁት፤ እርሱ ግን እንደ ጥንቱ ዝም ብሎ ይሰማኛል፡፡

    እነ አቡነ ሂሩተ አምላክ በድንጋይ ታንኳ፣ እነ አባ ዘዮሐንስ፣ እነ አባ ዘካርያስ በባዶ እግራቸው ባሕሩን አቋርጠው በመካከሉ ወደ አሉ ደሴቶች ሲገቡ በዓይነ ኅሊናየ እየተመለከትሁ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ከዓሦቹ ጋር ቆማ እጇን ዘርግታ የጸለየችበት መሆኑን እያመላለስሁ ሳላስበው ለ2፡30 ተጉዘን የተሳፈርንበት መርከብ ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወደብ ደረሰ፡፡ በመርከቡ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በላኤ መጻሕፍት ጽጉበ ምሥጢራት ተብለው ከሚታወቁት የዘመናችን ጥቂት መምህራን አንዱ የሆኑት ንግግረ ብርቱ አንደበተ ርቱዕ ክቡር ሊቀ ማዕምራን ደጉ ዓለም ካሳ አብረውን ነበሩ ከመርከቧ ስንወርድ አብረውን የነበሩት የገዳሙ አገልጋይ አባ ሃብቴ መንገድ ለመምራት ቀድመው ሲወርዱ እኛም የኔታ ደጉን አስቀድመን እኛ ከኋላ ተከትለን ከመርከብ ወረድን፡፡ 

    በገዳሙ ሕግ ሴቶች ከወደቡ አጠገብ በተሠራ ማረፊያ ላይ ሆነው ጸሎት አድርሰው ይመለሳሉ እንጅ ወደ ገዳሙ መግባት የማይፈቀድ በመሆኑ ሁላችንንም አነሣስታ ወደ ገዳሙ የወሰደችን እህታችንን ወይዘሮ ታድላ (ወለተ ሥላሴ) ከወደቡ አጠገብ ትተናት ወደ ገዳሙ ፊትና ኋላ ሆነን አቀናን፤ የኔታ ደጉና የዓባይ በረሀው መናኝ አባ ኀ/ ኢየሱስ የሚጫወቱትን በቃለ እግዚአብሔር የታጀበ ጨዋታ እየሰማን አንደበታችንን ገትተን ከኋላቸው እንከተላለን፡፡ የገዳሙ ጫካ በገነት ውስጥ ያለን አስመስሎናል አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ፀሐይን አይቶ የማያውቀውን የዳጋን መሬት እየረገጥን ስንሄድ ምእራፈ ቅዱሳን የሚል ጽሑፍ ካለበት የዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ አፅም ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፈበት ሥፍራ ደረስንና አረፍ ስንል የገዳሙ መሥራች አቡነ ሂሩተ አምላክ ወደ ገዳሙ ሲገቡ የተጫኑባትን የድንጋይ ጀልባ በክብር ተቀምጣ አየኋት እሷን ሁላችንም ተሳለምንና ወደ ላይ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ መቅደስ ወዳለበት ተራራ ወጣን፤ ጫካው ሁሉ የዕጣን መዓዛ አለው፤ በዚያ ያገኘናቸው መነኮሳት ሁሉ በቀስታ እንጅ ጮኸው አይነጋገሩም ቤተ እግዚአብሔሩን ተሯሩጠው ከፈቱልንና ጸሎታችንን አድርሰን አንደጨረስን አባቶቻችን የሠሩትን እናይ ዘንድ ወደቤተ መዘክር ገባን፤ ከበሩ በፊት ለፊት የቀደሙት አጼዎቹ በፍጹም ዝምታ ውስጥ ሆነው ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው በተዘጋጀላቸው የክብር ሥፍራ ላይና ታች ሆነው የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠባበቃሉ፤ ኢትዮጵያን የታሪክ ባለቤት ያደረጉት አጼ ዳዊት፣ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ አጼ ፋሲል፣ አጼ ሱስንዮስ ከሸዋ ከጎንደር ተሰባስበው አንድ ቤት ውስጥ ከትመዋል፡፡ እንኳን አንድ ቤት ውስጥ ሊያድር አንድ ሀገር የጠበበውን የኔን ዘመን ትውልድ አሰብሁና ቀናሁባቸው፡፡

     አይ የኔ ነገር! አሁን በሞተ ሰው ይቀናል! ለነገሩ አለሁ መስሎት የሞተው የኔ ዘመን ትውልድ ነው እንጅ እነሱስ ቤተ መንግሥታቸውን ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ሲያንፁ ከውጭ ዶላር ሳይሆን ሀገሪቱን የሚባርክ ግማደ መስቀልና መጽሐፍ ሲሰበስቡ የኖሩ ሕያው ሥራ ያላቸው ናቸው፡፡

         ሌሎችም ስማቸው የማይታወቅ ነገሥታትና ግብጻውያንም ኢትዮጵያውያንም ሊቃነ ጳጳሳት አጽማቸው በሙዚየሙ ውስጥ ተቀምጧል አጽማቸውን እጅ ነስተን በጠንካራ መንፈስ የተሠሩ የአባቶቻችንን ዘመን የማይሽራቸው ሥራዎች ተዟዙረን አየን፤ የሰው ቁመት ልክ የሆኑ የብራና መጻሕፍትን እርጅና የማይበግራቸው የነገሥታት አልባሳትና ነጋሪቶችን ሌሎችንም አይተን ከዚያ ስንወጣ ከተራራው ግርጌ ወደ ተሠራው የአቡነ ሒሩተ አምላክ መታሰቢያ ቤተ መቅደስ ነው ያመራነው፡፡

     

               ሁላችንንም ያስደሰተን ጫካ ውለው ጫካ የሚያድሩት አባ ይትባረክን ማግኘታችን ነው፡፡ አባ ይትባረክ ለሥጋቸው መሸፈኛ ያገለደሟትን እርጅና የተጠናወታት አቡጀዴ እንዳገለደሙ ከወደ ምሥራቅ በኩል ከተሠማሩበት ሥራ ተፈልገው መጡልን፤ እንደ ሙሴ ፀሊም ሲናገሩ ክብራቸውን ለመሰወር የነገሩን ድርድር ያበላሻሉ የቅዱሳንን ልማድ ለማያውቅ ሰው የዘነጉ ይመስላሉ፤ ወዲያው ነበር ጸጋ እግዚአብሔር የጎበኘቻቸው ሰው መሆናቸውን ያወቅሁት፡፡ እንዲህ አይነት ብዙ ሰዎችን በመጽሐፈ መነኮሳት አውቅ ስለነበር ነው እንጅ በጸጋ ተገልፆልኝ አይደለም፡፡ 

              ኋላ ጠይቀን እንደ ተረዳነው የቤተ ክርስቲያኑን ቅጥር ብቻቸውን በድንጋይ የቀጠሩት እሳቸው መሆናቸውን ስንሰማ ገረመን፤ ተዟዙረን ስናየው ለአምስት ለስድስት እንኳን የሚያስቸግር ድንጋይ አለው እሳቸው ግን ከብት እንደ ሚነዳ እረኛ ሂድ እያሉ እየገፉ እንደሚያመጡት መነኮሳቱ ነገሩን፤ በጎናቸው ተኝተው አያውቁም ከሰው ጋርም አይገናኙም ከደሴቱ ወደ የትም ወጥተው አያውቁም  እንዲያውም ሲያጫውቱን ምን አሉን መሰላችሁ አንድ ቀን ድንጋይ ከዋሻ ሲፈለፍሉ መሬት ተደረመሰብኝ አሉ ከላይ የነበረው ቋጥኝ ድንጋይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲወድቅ እኔን ሳይጎዳኝ ከሦስት ተፈረካከሰ እኔም ድንጋዩ አንድ መሆኑ የአንድነት ከሦስት መፈረካከሱ የሦስትነት ምሳሌ ነው እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን እያስተማረኝ ነው ብየ ወደ ሥራየ ቀጠልሁ አሉን::

               እንዲህ ያሉ ራሳቸውን ያስገዙ ሰዎች መኖራቸውን ሳይ የእግዚአብሔር ማደሪያዎቹ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ናቸው እንጅ ሌላ ምን ማደሪያ አለው? ብየ በውስጤ አሰብሁ ድንጋይ ወድቆባቸው የማይሰበሩ ይልቁንም ቋጥኝ ድንጋይ የሚፈረካክሱ ጠንካራ የንጉሥ ቤቶች እነዚህ አባቶቻችን ናቸው፡፡  ልቡ የተሰበረ ሰው እንኳን ድንጋይ የሰይጣንን ወጥመድ ይሰብራል፤ ማን የሚጠነክር ይመስላችኋል? የዚህን ዓለም ድንጋይ በሥጋ ኃይል መስበር የሚቻል ሲሆን የሰይጣንን ወጥመድ ግን በመብልና በመጠጥ ሳይሆን በቃለ እግዚአብሔር በሚገኝ መንፈሳዊ ኃይል ብቻ ነው መስበር የሚቻለው፡፡ ሁሉን የሰበረ ሶምሶን የተሸነፈው በሰይጣን ወጥመድ ብቻ ነው፡፡

             ይህን ሁሉ አድርገን ከአቡነ ሂሩተ አምላክ ቤተ ክርስቲያን ልንወጣ ስንል ሁላችንም እንግዶች በመሆናችን ምክንያት አርፋችሁ እግራችሁን ታጥባችሁ ነው የምትሄዱት ተብለን ወደ ማረፊያ ስንሄድ በዚያው እግረ መንገዳችንን ወደ ጸሎተ ማዕድ ይዘውን ገቡ፤ ጸሎተ ማዕድ ማለት ዘወትር ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሙሉ መዝሙረ ዳዊት በቀን እስከ ሰባት ጊዜ ድረስ የሚደረስበት በሁሉም የአንድነት ገዳማት ሥርዓት የማይታጣ ቤተ ጸሎት ሲሆን እዚያ ገብተን አባ ይትባረክና ሌሎችም የገዳሙ አበው መነኮሳት ጸሎተ ማርያም ደገሙልን፡፡ ጸሎቱን ጨርሰው አረፍ በሉ አሉንና የገዳሙን ታሪክ ነገሩን፤ መምህር ደጉ ጠሩኝና አየህ ኢትዮጵያን የሚጠብቃት ከዚህ የሚደርሰው መዝሙረ ዳዊት ነው አሉኝ ዘወር ብየ ግድግዳውን ሳይ ገዳሙን በልዩ ልዩ መንገድ የሚረዱ እና አትርሱን ያሉ ባለ ተስፋዎች ስም ዝርዝር በግድግዳው ተጽፏል፤ አይ! ይህን ጊዜ ስማችሁ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ይሆናል ብየ ቀናሁባቸው፡፡

              ከዚህ ወጥተን በቅርቡ ያረፉት የደብረ ዘይቱ አባ ምን ይችል ወደ አሠሩት ማረፊያ ገባንና እግራችን አባቶቻችን አጠቡን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ያጠበባት ቀን ትዝ አለችኝና በልቤ አብረህ እንዳጠብኸው እንደ ይሁዳ ሳይሆን እንደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትህ እባክህ ጌታየ እግሬን ብቻ ሳይሆን ነፍሴንም ጨምረህ እጠብልኝ ብየ ለመንሁት፡፡ በእርግጥም አጥበውኝ ሲጨርሱ የማላውቀው ደስታ ተሰማኝ ‹‹ሊታጠብ የሚወድ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም ሁለንተናው ንጹሕ ነው›› ዮሐ 13÷10 ብሎ ጌታዬ በጆሮየ የነገረኝ መሰለኝ፡፡

               ይህ ሁሉ ሆኖልን ጥቂት አርፈን ከገዳማውያኑ ዳቤ ተመግበን ወደ ባሕርዳር ልንመለስ ስንል ከወደቡ ላይ ወይዘሮ ታድላን ጨምረን በጋራ የመጨረሻ ጸሎተ ማርያም ሊደግሙልን የገዳሙ አበው ከአበ ምኔቱ ጀምረው ተሰባሰቡና ጸልየውልን ባርከውን መርቀውን በገዳሙ ትልቅ ጀልባ ጉዟችንን ወደ ባሕር ዳር አደረግን መርከቡ መልሕቁን ሲያነሣ የኔም ኅሊና መልሕቁን አነሣና በሀሳብ ባሕር ይንሳፈፍ ጀመር፡፡ እየራቅን ስንሔድ ዳጋ አረንጓዴ መሶበ ወርቅ መስሎ ከባሕሩ መካከል ቆሞ አየሁት ነቢዩ ዳዊት ‹‹....አድባር ውስተ ልበ ባሕር፤....በባሕር ሆድ ውስጥ ያሉ ተራሮች›› መዝ 45÷2 የሚላቸው እነዚህን ነው፤ ብየ ሳስብ ከጎን የመጣ ሌላ ሀሳቤ ደግሞ ‹‹...አድባር ውስተ ልበ ባሕር›› የሚላቸውማ በባህሩ ሆድ ውስጥ ቆመው የጸለዩ እነክርስቶስ ሠምራን ነው አለኝ፤ ነቢዩ ዳዊት የተረጎመልኝ ነው የመሰለኝና እውነት ነው ብየ ‹‹አድባር ውስተ ልበ ባሕር››የሚባሉትማ እንደነ አባ ይትባረክ ያሉት በውኃ ቀለበት ውስጥ የሚኖሩ ቅዱሳን ናቸው አልሁ፡፡ 

              መልሕቁን ያነሣ ልብ ወደ ወደቡ እስኪደርስ ድረስ ብዙ ያስባልና እኔም በዚህ ባሕር ላይ እኮ የአባቶቻችንን ነፍሳት ከገነት ሾልኮ ገብቶ የሰረቀ ዲያብሎስን ለማምለጥ አባቶቻችን እንደ ተጓዙበት ሁሉ ዲያብሎስን አዝለው የአባቶቻችንን ስጦታ ሊሰርቁን የሚገቡ ተጓዦችም አሉ ብየ ብዙ አሰብሁ፡፡ ሁሉ ሲጠፋ አቤሜሌክን በእንቅልፍ መጋረጃ ሰውሮ ከአሕዛብ ዐይን የጠበቀ እግዚአብሔር ይጠብቅልን እንጅ ሌላ ምን እላለሁ፡፡

                 ለዚህ ጽሑፌ ስም ሳወጣለት መጀመሪያ እንደ ሐዋርያቱ ‹‹ሊቅ አይቴ ተሐድር?›› ብየው ነበር፤ ስመለስ ግን ‹‹ማደሪያውን አይቼዋለሁ›› አልሁት እግዚአብሔር ካደረበት ሰው በስተቀር ማንም ሊያደርገው የማይችለው ሥራን የሚሠሩ ሰዎችን በማየቴ ማደሪያውን አይቼዋለሁና፡፡እናንተም ሂዱ ከዚህ የሚበልጥ ታያላችሁ፡፡

    sb9897256@gmail.com 

                                                              የአባቶቻችን ልጆች ያድርገን   !!!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ማደሪያውን አይቸዋለሁ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top