ምንጩ?
ምንጩ ከነዚህ አንዱ ሊሆን ይችላል፤ አንደኛ፥ከሰዎቹ ጋር ቀጥታ መመሳጠር ሊኖር ይችላል።ሁለተኛ፥ ሰዎቹ እነርሱ ሳያውቁ በቀጥታ ወይም በሌላ ሰው በኩል ያውቃቸዋል። ሦስተኛ፥ያልተለመደ ርቆ የሄደ ስነ ልቡናዊ የአእምሮ ማንበብ ችሎታ ሊኖረው ይችላል። በስነ ልቡና ትምህርት ቋንቋ telepathy ይባላል። ይህንን ቃል እዚሁ አብራርቼው ልለፍ። ከሁለት የግሪክ ቃላት የተሠራ ነው፤ τῆλε (ቴሌ) ከሩቅ፥ ከርቀት ማለት ሲሆን πάθος (ፓቶስ) ይህኛው አንድ የአማርኛ አቻ ቃል የለውም፤ በጥቅሉ ስሜትን፥ እውቀትን፥ ልምምድን ጨምቆ የያዘ ቃል ነው።
ቴሌፓቲ በተለምዶ የታወቁ መስመሮችን ሳይጠቀም ከአንድ ሰው Psi ወይም parapsychology እና mind reading በሚሉት መንገድ ከርቀት የእውቀትን፥ የስሜትንና የልምምድ መረጃን መውሰድ ማለት ነው። ይህ ዘመናዊነትን ይላበስ እንጂ ከጥንቆላ ጋር የተቆራኘና አጋንንታዊ አሠራር ያለበትም ነው። ምክንያቱም፥ አንድ ማንም ሰው ስለ ሌላ ማንም ሰው የተዘረዘረ መረጃ ከሜዳ እንደሚታፈስ ነገር እንደማያፍስ 1ቆሮ. 2፥11 እንዲህ በማለት ይነግረናል፤ በእርሱ ውስጥ ካለውከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰውማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔርመንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንምአያውቅም። ይላል። እግዚአብሔር ሊያሳውቅስ አይችልም? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፤ ወደዚህኛው እመለሳለሁ። ግን ልንቀበለው የተገቡ ሁለት ትልልቅ እውነቶች አንድ ሰው የሌላውን አዕምሮአዊ ማንነት ሊመዘብር አለመቻሉና እግዚአብሔር የሰውን ገመና በመድረክ ላይ የሚያዝረከርክ አምላክ አለመሆኑ ናቸው።
አራተኛ፥ ከአጋንንት የመነጨ ስለ ሰዎቹ በመጠኑ የማወቅ ችሎታ ሊሆን ይችላል። ይህ ከላይ ከተጠቀሰው ከሦስተኛው ጋር የሚቀራረብ ነው። ሰይጣን እውቀቱ ውሱን ይሁን እንጂ ስለ ሰዎች የሚያውቀው እውቀት አለው። ይህንን እውቀት በአንድ መንገድ ወይም በሌላ፥ በቀጥታ ወይም የመንፈስ ቅዱስ እውቀት አስመስሎ ሊሸጥ ቢችል ማስገረም የለበትም። በተለይ ሰይጣን እያስመሰለ የሚያቀርባቸውን ሸቀጦች በውድ ዋጋ የሚገዙ ክርስቲያኖች የበዙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ይህ ከሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመድረክ ላይ እየሠራ ያለ አጋንንታዊ አሠራር መኖሩ ሊስተዋልም ሊያስደነግጥም ይገባል። ሊኖር እንደማይችል መገመት ወይም አይኖርም ብሎ መደምደም የዋኅነት ነው። ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሮናልና አያስደንቅም። አምስተኛ ብዬ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ነው አላልኩም። ምክንያት አለኝ። ከቤት ቤት እየዞሩ ከጥንቆላ ያልተናነሰ ሥራ የሚሠሩና በዚህ የሚተዳደሩ የበዙበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከነዚህ ዘዋሪ ዘጋቢዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች ለ’ነቢያቱ’ እየቀረቡ ንግርት የተነገረባቸውና ከመድረክ የታወጀባቸው ጊዜያት በአገራችንም በምዕራቡም ዓለም ኖረው ያውቃሉ። አንወናበድ። በዚህ ዘመን የምንሰማቸውንና የምናያቸውን ምልክቶች ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ናቸው ብለን ከደምደምን ሰዎች ክርስትና አስነስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያስገቡት ጥንቆላ ውስጥ እንገባለን።
ይህ ከላይ ያየነው ዓይነት አሠራር ቴሌፓቲያዊና ጥንቆላዊ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የምንሄድበትን፥ የምናገለግልበትን ፈር የተለመልን መጽሐፍ ነው። አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት የምናውቀው ቀድመውን ያገለገሉትን ነቢያትና ሐዋርያት (በቃሉ ውስጥ የተጻፉትን ማለቴ ነው) አገልግሎት መልክ በመመልከት ነው። ዛሬ ሙሴና ሳሙኤል ወይም ጳውሎስና በርናባስ ዛሬ ቢኖሩ የባልሽ ስም ገብረ ጊዮርጊስ፥ የባልሽ ወንድም ገብረ ክርስቶስ እያሉ አያፌዙም። የአገልግሎታቸው ትኩረትና ዒላማ የተገለጠ ነውና እንዲህ አይቀላምዱም።
ወደዚህ ‘ነቢይ’ ስንመጣ ግን፥ እንግዳ ነገሮችን ይነግረናል። እነዚህን የሰዎች ምስጢሮች ስለሚያውቅበት ምንጭ ሲናገር አጠገቡ ያለ ዳመና መረጃ እንደሚሰጠው ይነግረናል። ወደዚህ አሳብ ከታች እመለሳለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን “በጾም ፀሎቱ መካከል የእግዚአብሔር መልአክ የሆኑ ሰዎች ይመግቡታል።” ‘መልአክ የሆኑ ሰዎች’ ማለት ምንድርነው? አልገለጠውም። ሰዎቹ መልአክ ሆነዋል? ወይስ መላእክቱ ሰዎች ሆነዋል? ወይስ ይህ አባባል የሰዎቹን መልካምነት በአጋኖ ለመናገር ነው? አገላለጡ ግን እንደዚያ አይመስልም።
“ለሊት ለሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ አንድ ሰው ቢያነስ ለአንድ ዓመት ያህል ፍትፍት በሰሃን እያመጣ ይመግበኝ ነበር። ያንን ሰው እጁን እንጂ አካሉን አላይም ነበር። በመጀመሪያ ሰሞን ህልም ይመስለኝ ነበር። ኋላ ግን በእርግጥ እውን እንደሆነ ያረጋገጥኩት ጠግቤ ከእጁ ከበላሁ በኋላ ውሃ እጠጣና አገሳ ነበር። ያ እጅ በዛ የርሃብ ዘመኔ ያለማንም እርዳታ ራሱ እያጎረሰኝ የርሃብ ዘመኔን አሻግሮኛል።”
ይላል። እጁ ብቻ የሚታይ ሰው ማለት ምንድር ነው? ይህ ነገር ሰው ባይሆንስ? ሰው መሆኑ በምን ይታወቃል? ይህ ለ5 ዓመታት የሆነ ነው።[1] የማን መሆኑ የማይታወቅ እጅ ስላቀረበ የቀረበው ነገር በሙሉ የጌታ ነው ተብሎ መበላት አለበት?
ይህ ከማይታይ እጅ መብላት የዘመናችንም ትክክለኛ ምልክታዊ ምሳሌ ነው። ከመድረክ ላይ ምንም ነገር ይቅረብ፥ ይህ የማን ትምህርት ነው? ከየት የመነጨ ነው? ያቀበለው እጅ የማን ነው? ሳይባል እጅ ብቻ ታይቶ ትምህርቱ ሁሉ፥ ልምምዱ ሁሉ አፈፍ የሚደርግበት ዘመን ላይ ደርሰናል።ሰዎች ከመድረክ ላይ የሚነገረውን ትንቢት ሁሉ እየበሉ ማግሳትን ተያይዘውታል። ማግሳታቸውንም የምግቡ እውነትነት ማረጋገጫ እያደረጉ ናቸው። መታየት ያለበት ነገር፥ የሚያቀብለው እጅ እጅ መሆኑ ሳይሆን የማን እጅ መሆኑ ነው። ትምህርት ብቻ ሳይሆን የማን ትምህርት ነው? ከሰውና ከቴሌቪዥን የተኮረጀ ነው? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ ነው? ምንጩ የት ነው? የሚለው ነው። መድረኩ ላይ ሳይሆን ከመጋረጃው በኋላ ያለው ማን ነው? ብሎ መጠየቅ አጉል ደፋርነት አይደለም። ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መኖር አለበት። በዚህ ዘመን የሞተ ሰውን የሚያናግርን ወይም የሞተ ሰው መልስ የሚሰጠውን አገልጋይ ብንሰማ ምን እንል ይሆን? እርግጠኛ ነኝ በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ባይኖረንም እንኳ ብዙዎቻችን፥ ‘ይህማ ሙታን ሳቢነት ነው እንጂ ሌላ ምን ይሆናል?’ እንላለን። ዘዳ. 18 ውስጥ ያለው አስማተኛም፥ መተተኛም፥በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንምየሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድአይገኝ። የሚለው ቃል ሳይታሰበን አይቀርም። ይህ ‘ነቢይ’ የሞተ ሰውንም ካናገረና የሞተው ሰውም ከተናገረውና መልስ ከሰጠውስ? ሌላ ሴትን ወደ መድረክ አውጥቶ ከተናገረው ደግሞ ይህ ይቀነጨባል፤
ነቢይ በላይ፡- ሌላም ዘመድሽን አየሁ። ዳንኤል ይባላል። እርሱም ተመሳሳይ ህመም አለበት። ሴቲቱ፡-አዎን የእግዚአብሔር ሰው
ነቢይ በላይ፡- በመንፈስ ሳሎኑን ዘልቄ ወደ መኝታ ክፍልሽ ገባሁ። የባለቤትሽን ፎቶ አየሁ። የባለቤትሽ ፎቶ የሚገኘው በመኝታ አልጋሽ አጠገብ ነው።
ሴቲቱ፡-አዎን የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም ትክክል ነው።
ነቢይ በላይ፡- ያንን የባለቤትሽን ፎቶግራፍ አነጋገርኩት። ‹‹አንተ የት ነው ያለኸው?›› አልኩት። እርሱምእንዲህ ሲል መለሰልኝ ‹‹እኔ እኮ ሞቻለሁ›› አለኝ።
ሙታንን ማነጋገር የሚችል ማን ነው? በመንፈሱ ዘልቆ ነው ወደ መኝታ ክፍል የገባውና ፎቶውን ወይም ሙቱን የሚያናግረው በመንፈስ ይመስላል፤ በሥጋ ሳይሆን። መቼም የሞተ ስለማይናገር በወረቀትና መስታወት የተሠራ ፍሬም፥ ‘እኔ እኮ ሞቻለሁ’ አይልም። ሕይወት የሌለው ግዑዝ መጀመሪያውኑ አይሞትምና ሙት ተብሎም ሊጠራ አይችልም። ይህ ስዕል ተናገረ ማለት ተአምረ ማርያም ውስጥ እንዳለው፥ የማርያም ስዕል ድምጽ አውጥታ ተናገረች፥ አለቀሰች፥ ደማች እንደሚባለው ከተረትም የወረደ ነገር ውስጥ መዝቀጥ ነው። ወረቀቱ ካልተናገረ ደግሞ የሞተው ሰው ተናግሮታል ማለት ነው። ይህ ሙታንን ማነጋገር ከአጋንንት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ የሚያስተምረውና ከቶም እንዳይደረግ የተከለከለው ሙታን ሳቢነት ነው። እንደዚህ ያሉ ነገሮችን በግልጽ የሚናገር ሰውን ‘የእግዚአብሔር ሰው’ እያሉ ማሞካሸትን ምን ይሉታል? ይህ እኮ ሊያስደነግጥና ሊያስጠረጥር የተገባው ጉዳይ ነው። ይህ የሰዎችን ስምና ምስጢር የሚያውቅ ሙታንንም የሚያናግር ‘ነቢይ’ ምንጩ ምንድር ነው?
ተናጋሪው በተደረገለት ቃለ መጠይቅ ላይ ይህ የስዎች ምስጢር እንዴት እንደሚታወቀው ሲናገር፥ አንዳንድ ጊዜ ድምጽ እንደሚሰማ፥ አንዳንዱ ድምጽ በጆሮ የሚሰማው፥ ሌላው በልቡ የሚሰማው መሆኑን ከዘረዘረ በኋላ፥
ሌላኛው ግን በጣም በአብዛኛው የሚነግረኝአጠገቤ ዳመና ቆሞ ነው። በቁመቴ ልክ የሚቆምዳመና አለ፤ በጣም፥ መዓዛው በጣም ነው ደስየሚለው፤ እና፥ አንዳንድ ጊዜ እራሱ እንትን አያልኩኝመጨበጥ እፈልጋለሁ እንደዚህ ! ግን አልችልም።እሱ ሲሄድ ነው ምሄደው፤ ከፊቴ ሲሄድ እሄዳለሁእከተለዋለሁ፤ ጎኔ ላይ ይቆማል፤ ሰው አስመጥቼአሁን መልክት ስናገር አሁን አጠገቤ ቆሞ ነውሚነግረኝ፤ ሙሉ መረጃ ያወራልኛል። ብሏል። [2]ይህ ሙሉ መረጃ የሚሰጥ በቁመቱ ልክ የሆነ ዳመና ከዳመናነቱና ሙሉ መረጃ የሚያወራ ከመሆኑ በቀር ማንነቱ ወይም ምንነቱ አልተነገረም። ይህ ዳመና የተባለው ማን ወይም ምን የሚሉት ደመና ነው? ይህ የዚህ ነገር ምንነት መጠየቅና ከቃሉ አንጻር መፈተሽ የለበትም? ወይስ ክርስቲያን ሁሉ የሚሆነውን ምልክትና ምትሃት ሁሉ የእግዚአብሔር አሠራር ነው ብሎ በየዋህነት ብቻ መግጋት አለበት?
ቀደም ብዬ እንዳልኩት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀደሙት ቅዱሳን አገልግለው የሄዱበትን ፈር ተከትለን እንድናገለግል ፈር ቀድደውልናል። እንዲህ ያለ ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ውስጥ ለማን እየታየ የዘመድና የአማቾች ስምና ምስጢር እየተናገረ ነቢይነቱን ማረጋገጫ አደረገ? ብለን ብንጠይቅ አንድም ምሳሌ አናገኝም። የተጻፈው ሁሉ ለከንቱ ሳይሆን ለትምህርታችን ከተጻፈልን ከሕይወታቸውና ከአገልግሎታቸው ልንማርና ልንመስላቸው ይገባናል እንጂ የገዛ ቀዳዳቸውን ቀድደው በቀላሉ የሚወናበዱ ሰዎችን አስከትለው መንጎድ እንደ ዘበት የመሰላቸው ሰዎች በሚሸነቁሩት ሽንቁር ሾልከን መውጣት የተገባ አይደለም።
የዕውር መሪና የጋዜጣ ስነ መለኮት
ዛሬ መሠረታዊ የክርስትና ትምህርትና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሳይማሩ የሚያስተምሩ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውን እንደ ስነ መለኮት ሊቅ የሚቆጥሩ የተደናገሩ ሰዎች እያደናገሩ ይገኛሉ። ከዘመናችን ‘ነቢያት’ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተው የተማሩ እንዳሉ እስታቲስቲክስ የለኝም። የተማሩ አለመሆናቸውን ግን ከሚያስተምሩት ሰምቶ መናገር ይቻላል። ይህኛው ‘ነቢይ’ ታሽቶሎጂ በሚባል ኮርስ ከመንፈስ ቅዱስ ኮሌጅ መመረቁን ተናግሯል፤ የመጽሔቱ ዘጋቢም ጽፎለታል። ዶሮን ሲያታልሏት እንደሚሉት ነው? ወይስ አንባቢዎችን ሲያታልለን መሆኑ ግልጽ አይደለም? በዚህ ዘመን፥ ያውም በዚህ ዘመን ላለመማር አእምሮን ዘግቶ መቆለፍና ሌሎችም ቃሉን እንዳይማሩና እንዳይመረምሩ ማድረግ ከሰነፍም የማይጠበቅ ነው። እነዚህ ያልተማሩ አስተማሪዎች ከእነርሱ የባሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው። በ2008 በአትላንታ ዕውሮችን መረዳት ወይም ስለ ዕውሮች ግንዛቤ ማግኘት ይቻል ዘንድ ፈቃደኛ ሰዎች ለአንድ ሰዓት ፈቃደኛ ዕውር ሆነው ዓይናቸው ሙሉ በሙሉ ተሸፍኖ በከተማው የተለያዩ ክፍሎች ይመላለሱ ነበር። መሪዎቻቸውን አንዳንድ ጥያቄ ከመጠየቅ በቀር ጭላንጭል እንኳ እንዲያዩ አይፈቀድም። ጉዞአቸውን ጨርሰው ከተመለሱ በኋላየዓይናቸው ሽፋን ሲነሣ ነው ይመራቸው የነበረው ሰው ራሱ ዓይነ ስውር መሆኑን የሚያውቁት። ይህ ማለት መሪው ሰው ከተመሪው የተሻለ ምንም የማያይ የመሆኑ ገላጭ ነው። ይህን የዕውር ዕውርን መምራት ቃል
መጀመሪያ የተናገረው ጌታ ነው፤ ማቴ. 15፥14። ይህ ዕውርነት የዓይን ዕውርነት የልቡና ስውርነት ነው። ራሳቸውን እንደ አላዋቂ ከቶም ሳያዩ እንደ ሊቅ ሊቆጥሩ መሞከራቸው ሊያስገርም አይገባም። አለመማርን በመማር ሊለውጡና ሊያሸንፉት ይቻላል። የመምሰልን ድፍረት ግን በመማርም መለወጥ አይቻልም። ከዓመታት በፊት በአንዲት በማገለግልባት ቤተ ክርስቲያን የነበረች እኅት እንማርበት በነበረ አንድ ርእስ ላይ ተከራክራ፥ ተከራክራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማሳመኛ ቃልና ለምትለው ነገር ማስረጃ ስታጣ፥ “ይሄ ቲዮሎጂ ነው፤ ማንም እኮ ቲዮሎጂ ሊኖረው ይችላል፤ ማንም ሰው ቲዮሎጂያን ነው።” አለች። እኔም፥ “በመጠኑ ልክ ነሽ፥ ግን ቲዮሎጂው ከየት ነው የሚመጣው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ከጋዜጣ?” አልኳት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ካልወጣ ከጋዜጣ መሆኑ አይቀርም። ዛሬም የጋዜጣ ስነ መለኮታውያን ድምጻቸው አጉል ጎልቶ እየወጣ ይገኛል። አጉሉ ነገር ጉልህ አወጣጡ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱና ድርጊቱ፥ ውጤቱና መዘዙም ጭምር ነው። እንደ አንዳንድ መድኃኒቶች የጎን ጠንቆቹም ብዙ ናቸው። አስተምህሮታዊ፥ ስነ መለኮታዊ ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትምህርት ጤንነት ላይ ትኩረት ማድረግን አጥብቀው የሚሸሹ አከርካሪ የሌላቸው መሪዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው። አንዳንዶቹ ራሳቸውም ያልተማሩና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ጊዜ የሚያሳልፉ ስላልሆኑ ነው። ሌሎቹ ግን ስነ መለኮት አስፈላጊ ሳይሆን አላስፈላጊ፥ ተግባራዊ ሳይሆን ንድፈ አሳባዊ፥ አንድ የሚያደርግ ሳይሆን የሚለያይ፥ የሚታወቅ ሳይሆን እርግጠኛ ሆነው ጠንቅቀው የማያውቁት ረቂቅ፥ መንፈሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊነት የሌለበት አእምሮአዊ ብቻ ስለሚመስላቸው ነው። በእውነት ግን ስነ መለኮት አላስፈላጊ ቢሆን ጳውሎስ እንደ ሮሜ፥ ኤፌሶን፥ ቆላስይስ ያሉትን መልእክቶች ባልጻፈም ነበር። ደግሞም ስነ መለኮት ተነድፎ የተቀመጠ ንድፍ ሳይሆን ተመርምሮ የሚታወቅ ትምህርት ነው። ስነ መለኮት አይለያይም፤ ከለያየ የሚለየው ስነ መለኮትን ፈርተው የሚሸሹ ጥራዝ ነጠቆችን እንጂ መርምረው የሚነጋገሩበትን አይደለም። ይህ ደግሞ መለየት አይባልም፤ ቀድሞውኑ ፈርተው ሸሹ እንጂ ወደ መድረክ አልመጡምና። ስነ መለኮት ተግባራዊ ነው፤ ችግሮቹ ተግባራዊ ከሆኑ መፍትሔዎቹ እንዴት ተግባራዊ አይሆኑም? ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይሁን ማለትና ማድረግ ተግባራዊ ነው። ስሕተትን ማመልከትና እንከንን ማጥራት ተግባር ነው። ስነ መለኮት መንፈሳዊነት እንደሌለበት የሚያስቡ መንፈሳዊነትን አእምሮን ከመጠቀም የገነጠሉ ናቸው። ስነ መለኮት የማይታወቅ፥ ረቂቅ ነው የሚሉ ጊዜ ወስዶ ቀምሞ ከማብሰል እንደ በሶ በጥብጦ መጠጣትና መጋት የሚፈልጉ ናቸው። ስለዚህ ዛሬ የተበላሸ ነገር በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ እየተዝረከረከ ሲታይ ዝምታ ታለፈና ማጨብጨብ እየተለመደ ነው። ብዙ አማኞች የእግዚአብሔርን ቃል ካለማወቃቸው የተነሣ፥ በሥርዓትም ካለመማራቸው የተነሣ እውነትንና ስሕተትን መለየት አይችሉም። ስለዚህ ሁሉ እውነትና የእግዚአብሔር እየመሰላቸው በመደነቅ ያጨበጭባሉ። ምልክትና ተአምራት ሁሉ ከጌታ የተደረገ ይመስላቸዋል። የመጨረሻው ዘመን ምልክት ተብሎ በግልጽ የተነገረን ነገር በክርስቶስ ስምና በአጋንንታዊ ምትሐት የሚደረጉ ድንቅና ተአምራት እንዲሁም የስሕተት ትምህርቶችና አሳች ሰዎች ናቸው። ሰይጣን የሚሠራቸው ምልክቶች እኮ ጌታ ከሚሠራቸው ከውጪ ሲታዩ ልዩነት የላቸውም። ልዩነቱ ምንጩ ነው። በምልክቶች ምልክትነት ብቻ ለሚወናበድ መንጋ ምልክቶች በቀላሉ ተብትበው የሚጎትቱ ገመዶች ናቸው። ሙሴ በትሩን ሲጥል እባብ ሆነች፤ ኢያኔስና ኢያንበሬስም ያንኑ አደረጉ። ተመሳሳይ ነው። ውኃውንም ደም አድርገዋል። ጓጉንቸሮችንም ቅማልንም አውጥተዋል። ያደረጉት ድርጊት ተመሳሳይ ነው። አድራጊዎቹ ግን የተለያዩ ናቸው። ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያትይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳእስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉማቴ. 24፥24። ምልክትና ድንቆች የነቢይነትና የሐዋርያነት ብቸኛ ምልክቶች አይደሉም። ምልክት አይተው ግራ ለሚጋቡ ወይም ለሚከተሉ ሰይጣን ምልክቶችን በገፍ እየፈበረከ ሊያቀርብ ምንም አይሳነውም፤ ችሎታው አለው፤ ፋብሪካውም አለው። ሰይጣን የመንፈስ ፍሬን ነው ማፍራት የማይችለው እንጂ ተአምራትና ድንቆችን መሥራት ይችላል። ሰይጣን የጸጋ ስጦታ የሚመስሉ የተጭበረበሩ ልምምዶችንም በገፍ በማምረትም ብቻውን ያለ ጨረታ ያሸነፈና ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ሰይጣን ራሱን እንደ ብርሃን መልአክ አድርጎ፥ አገልጋዮቹን ደግሞ የጽድቅ አገልጋዮች አስመስሎ ወደ መድረክና ወደ ምስባክ መውጣትና ማውጣት ይችላል። በተለይ በዘመን መጨረሻ ያለን እኛ ይህንን እየሰማንና እያየንም ነን።
ይቀጥላል…
[1] እላይ የተጠቀሰው፤ ገጽ 5። እንዲሁም፥
http://www.prophetbelay.com/index.php/about–us/about–prophet–belay
0 comments:
Post a Comment