በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
መክስተ-አርእስት፤
ሀ)ጌታ የተወለደበት ዘመን የዓለም ገጽታ በታሪክ አምድ፤
1) የአይሁድ አመለካከትና ይጠባበቁት የነበረው ተስፈ (ሚስያኒክ ኤክስፔክቴሽን)
2) ኢየሩሳሌምና አካባቢዋ ከፖለቲካ አንጻር
3) የጌታን ልደት ተከትሎ የተከሰቱ ለውጦች
የፋርስ ነገሥታት ጉብኝት፤ቤተልሔምን የከበባት ብርሃናዊ የኮከብ ምልክት፤የጌታ ስደትና በቤተልሔም ሕጻናት ላይ የደረሰ እልቂት፤
ለ) የስደት ምርጫና የስደት ሕይወት፤
ሐ) የቅዱሳን ቤተሰብ የጉዞ ገጠመኞች-ስደት ርሃብና እንግልት በልጅነት፤
መ) ስደተኞች ከቅዱሳን ስደት የምንማራቸው ቁምነገሮች፤
.......................................................
ሀ)ጌታ የተወለደበት ዘመን የዓለም ገጽታ በታሪክ አምድ፤
1) የአይሁድ አመለካከትና ይጠባበቁት የነበረው ተስፈ (ሚስያኒክ ኤክስፔክቴሽን)
የአብርሃም ልጆች አይሁድ ከሉዓላዊ አምላክ ጋር በቀጥታ የመነጋገር ጸጋ ተሰጥቷቸው፣ የፈጣሪ መለኮታዊ ጥበቃ ሳይለያቸው በዓለም ሕዝብ ዝንድ ተከብረውና ተፈርተው የኖሩ ሕዝቦች ሲሆኑ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ዓለምን በሥጋ በሚጎበኝበት በተስፋው ፍጻሜ ዋዜማ በረዥም ታሪኩ በዓለም ይታወቅ የነበረው የአይሁድ እምነት ተዳክሞና ተከታዮቹም የመንፈስ ዝለት አጋጥሟቸው ተስተውለዋል። በአይሁድ መካከል ሰፊ የእምነትና የአመለካከት ልዩነት መከሰቱ አንዱ የተስፋ መቁረጥ ምልክት ሆኖ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ዘመን የነበሩ አይሁድ በእምነታቸውና በአመለካከታቸው በብዙ ቡድኖች ተከፋፍለው የነበረ ሲሆን። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፤
· ፈሪሳውያን፤ በአይሁድ ሕዝብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው ፖለቲካውንና ሃይማኖቱን ያጣመሩ አክራሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ሲሆኑ፣ የንፍስን ሕያውነት፣ የሙታንን መነሳት፣ የመላእክትን ሕልውና የሚያምኑና የመሲህን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁ ክፍሎች ነብሩ።
· ሰዱቃውያን፤ እነዚህ ጥቂት ባለጸጋዎች በሙሴ ሕግ ከተጻፈው ውጭ ምንም ዓይነት ትውፊት የማይቀበሉ ሲሆኑ፣ በእምነት ረገድ ደግሞ የሙታንን መነሳት፣ የመላእክትን ሕልውናና የንፍስን ሕያውነት የማያምኑ ለዘብተኞች ናቸው።
· ኢሴንስ በመባል የሚታወቁት በተባሕትዎ የሚኖሩ ምኑናን ሲሆኑ የቤተ መቅደስን መታነጽና የክህነትን አገልግሎት የማይቀበሉ ክብሎች ናቸው። እንዲሁም ከእነዚህ ከሦስቱ የእምነት ቡድኖች በተጨማሪ፤
· ዚሎትስ(ቀናተኞች)የተባሉ ሀገራቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ኃይልን በመጠቀም እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ሀገር ወዳድ ክፍሎችና ሌሎች ሄሮድሳዊያን የንጉሳውያን ቤተሰቦች ነበሩ።
በአጠቃላይ በዚህ ዘመን የነበሩ አይሁድ በአብዛኛዎቹ በብሉይ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ ላይ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተገለጸውን ኃይለ ቃለ ይገነዘቡት የነበረው ከራሳቸው አመለካከት አንጻር እንጅ ከእግዚአብሔር በጎ ፈቃድና ከዓለም ድኅነት አኳያ አልነበረም። እናም ይጠባበቁት የነበረው መሲህ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተጥሎና በጨርቅ ተጠቅልሎ የሚያለቅስ ምስኪን ሳይሆን፣ ተዋግቶ በጽኑ ክንዱ ኢየሩሳሌምን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ የሚያወጣና 12ቱን ነገደ እስራኤል አንድ አድርጎ ዳግማዊት የሰሎሞንን መንግሥት የሚመሠርት ነው (ኢሳ 56፡9፤ ኢሳ 66፡1፤ ዳን 7፡14)። ወንጌላውያን ደጋግመው እንደጻፉት ጸጋቸው የተወሰደባቸው ሰማያውያን ፍጥረታት አጋንንት እንኳን የክርስቶስን አምልክነት አውቀው በአንደበታቸው ሲመሰክሩ (ማር 1፡24፤ 1፡34) ከፈጣሪ ጋር ቃል በቃል የመነጋገር ጸጋ የተሰጣቸው የአምላክ ወዳጆች እስራኤላውያን ግን ይህ ታላቅ ምሥጢር ተሰውሮባቸዋል። ምክንያቱም ልክ ዛሬ የክርስትና ሃያማኖት እርጅና ተጫጭኖት መልኩ እንደተቀየረና አካሉ እንደጎበጠ ሁሉ እነርሱም በጊዜው ይጠባበቁት የነበረውን ተስፋ በአስቡት ፍጥነት ማግኘት ባለመቻላቸው ውስጣቸው ባዶ ሆኖ በስም ብቻ ይኖሩ ስለ ነበረ ነው።
2) ኢየሩሳሌምና አካባቢዋ ከፖለቲካ አንጻር
ክርስቶስ የተወለደበት ዘመን እስራኤላውያን የተጣለባቸውን ከባድ የሮማ የአገዛዝ ቀንበር ከላያቸው ላይ አውልቀው ለመጣል ለዘመናት ያካሂዱ የነበረውን የነጻነት ትግል እርግፍ አድርገው ትተው፣ የራሳቸው ውስጣዊ አስተዳደር እንዲኖራቸውና አምልኮታቸውን እንዲያካሂዱ በተሰጣቸው መጠነኛ ነጻነት ረከተው ተስፋ ቆርጠው የተቀመጡበት ዘመን ነበር። በክፋቱ የሚታወቀውና የኢየሩሳሌምን የመጨረሻ ቤተ መቅደስ የሠራው ታላቁ ሄሮድስ ሲሞት ግዛቱ ለሦስት ልጆቹ ተከፋፍሎ፣ ሄሮድስ አርኬላዎስ ሰማርያንና ኤዶምያን፣ ሄሮድስ ፊልጶስ ኢቱሪያን፣ እንዲሁም ሄሮድስ አንቲጳስ ይሁዳንና ፐራኤን ወይም ገሊላን ያስተዳድሩ ነበር። የታላቁ ሄሮድስ የመጨረሻ ልጅ ሄሮድስ አንቲጳስ ምግባሩ ያልተስተካከለ፣ የወንድሙን ሚስት ሄሮድያዳን ያገባና በዚህም ምክንያት መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን የገደለ፣ በተለይም ደግሞ የሮማውን ቄሳር ለማስደሰት ብሎ በአይሁድ መካነ መቃብር ላይ ጢባርያስ የተባለ ዝነኛ ከተማ በመገምባቱ በአይሁድ ዘንድ ጥላቻን ያተረፈና አስተዳደሩ ያልተወደደለት መሪ ነበር። በዚህም ያልተወደደ ምግባሩ ክርስቶስ “ያ ቀበሮ” ብሎ ጠርቶታል።
በዚህ ዘመን የሮማውያን አምልኮ ጣኦት ተከታዮች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱና በተልይም በዓረቢያ ፔንዙላ የነጻ አውጭ ታጋዮች ቁጥር እየተበራከተ በመምጣቱ ስለ ግል ክብሩና ስለ ሀገሩ ሉዓላዊነት ስጋት የገባው የሮማው መሪ አውግስጦስ ቄሳር የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ለሶርያው ገዥ ለቄሬኔዎስና ለገሊላው ንጉሥ ለሄሮድስ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላፏል (ሉቃ 2፡2)። ይሁን እንጅ ሄሮድስ አንቲጳስ ለሕዝብ ቆጠራው የሰጠው ግምት ዝቅተኛ በመሆኑና ትዕዛዙን በወቅቱ ባለማስፈጸሙ እንዲሁም የደቡብ ዓረቢያን ሽምቆች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባለመቻሉ “የቄሳር ወዳጅ” ተብሎ የተሰጠው ክብር ተቀንሶበታል። በዚህም ከፍተኛ ስጋት አድሮበታል።
3) የጌታን ልደት ተከትሎ የተከሰቱ ለውጦች
· የፋርስ ነገሥታት ጉብኝት፤
እንግዲህ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ ለወዳጆቹ የገባውን ቃል ኪዳን ጠብቆ በሥጋ የተገለጠው ኢየሩሳሌም እንዲህ ባለ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረችበት አስቸጋሪ ጊዜ ነው። ከአውግስጦስ ቄሳር ጋር በተፈጠረው አለመግባባ የተደናገጠው ንጉሥ ሄሮድስ የክርስቶስን ልደት ተከትሎ በዘመኑ በሥልጣን፣ በሐብትም ሆነ በጥበብ ከሮማውያን ጋር ይተካከሉ የነበሩ የፋርስ ነገሥታት ሳይታሰብ ለጉብኝት ግዛቱ ውስጥ በመግባታቸውና የአመጣጣቸውን ምክንያት በውል መረዳት ባለመቻሉ ለሮማውያን ሉዓላዊነትና ለሥልጣኑ የነበረው ሥጋት ክፍተኛ ደረጃ ደርሷል፤ መንፈሱ ክፉኛ መታወክ ጀምሯል። ታዋቂው አይሁዳዊ የታሪክ ጸሐፊ ጆሲፈስ እንደሚለው እነዚህ ከሩቅ ምሥራቅ የመጡ ፋርሶች እጅግ በጣም የሰለጠኑ፣ በኮከብ ቆጠራ (አስትሮኖሚ)፣ በሃይማኖትና በፍልስፍና ትምህርት የተራቀቁ፣ እንዲሁም የሮማውያንና የግሪካውያንን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ነበሩ። እነዚህ ነገሥታት“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና”(ማቴ 2፡2) በማለት ስለ ሕጻኑ ክብርና ሉዓላዊነት ከሰጡት ምስክርነት አንጻር ሄሮድስ የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሮበታል። ፋርሶች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ለአይሁድ ሕዝቦች የነበራቸው አመለካከት ክፍ ያለ እንደነበር ይነገራል። ምክንያቱም ፋርሶች ታላቁ ፈላስፋቸው ዞሮአስትሬን ከእስራኤላዊው ነቢይ ከዳንኤል ጋር የጠበቅ ግንኙነት ስለ ነበረውና የአንድ አምላክን ሕልውና (ሞኖዚዝም) ከዳንኤል ዘንድ ስለ ተማረ በርካታ የፋርስ ምሁራን እስራኤልን እንደ ሁለተኛ አገራቸው ይመለከቷት ነበር። ነቢዩ ዳንኤል በስደት በነበረበት ጊዜ በእምነቱና በጥበቡ በፋርስና በባቢሎናውያን ሕዝቦች ዘንድ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ለባቢሎን ንጉሥ ሕልሙን በተረጎመለት ጊዜ በንጉሡ ፊት ቀርቦ“ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፣ ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ” (ዳን 2፡27) በማለት የእስራኤልን አምላክ ታላቅነት በሰፊው መስክሯል። የፋርሶች በአንድ አምላክ ማመን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ እንደሆነ የሚገምቱ ታሪክ ጸሐፊዎች ጥቂቶች አይደሉም።
በዚህም ምክንያት ሄሮድስ በአንድ በኩል ምናልባት የሮም መንግሥት እየተዳከመ በመምጣቱ እነዚህ ነገሥታት ሮማውያንን አስወጥተው እኔን ሉዓላዊት የእስራኤል መንግሥት እንድመሠረት ሊረዱኝ የሆናል ብሎ አስቧል። በሌላ በኩል ግን ለሕጻኑ ብቻ የሚገባውን እጅ መንሻ አቅርበው በሌላ መንገድ ተመልሰው በመሔዳቸው ምን አልባት እሱ ኤዶማዊ እንጅ አይሁዳዊ አለመሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በቤተልሔም የተወለደው ሕጻን በትትክል ለመንግሥትነት የታጨ መስሎ ስለታየው ስጋቱ ጨምሯል።
· ቤተልሔምን የከበባት ብርሃናዊ የኮከብ ምልክት፤
እነዚህ የፍልስፍና ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ በቤተልሔም ስለ ተወለደው ሕጻን በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌላ መንገድ ከሰው ያገኙት ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረም። ከላይ እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር የልባቸውን መሻት አይቶ የተወለደው ሕጻን የሰማይና የምድር ጌታ መሆኑን ገልጾላቸዋል፤ ክብሩን አይተው በረከቱን እንዲቀበሉና ምስክርነታቸውን እንዲያስተላልፉ በብርሃናዊ ኮከብ መርቶ ቅዱሳን መላእክት በከተሙበት ቦታ በፊቱ አቁሟቸዋል። በተወርዋሪ ኮከብ የተመሰለ ራሱ ጌታ ነው። ኮከብ ምሕዋሩን ጠብቆ እንደሚወጣና እንደሚገባ ሁሉ ጌታ በቀጠረው ሰዓት በሥጋ መገለጡን ያመለክታል። “አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል” (ዘኁ 24፡17)” ተብሏልና። እርሱ ራሱ ጌታ በዮሐንስ አድሮ ሲመሰክር “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ” (ራዕ 22፡ 16) ብሏል። ይህ ሁሉ ያልተለመደ ምልክት ልደቱን በተስፋ ለሚጠብቁ ደጋግ ሰዎች ልብን የሚያረጋጋና እፎይታን የሚፈጥር ታላቅ ብሥራት ሲሆን፣ ለሥጋዊ ሥልጣናቸው ለሚጨነቁ ንጉሣዊያን እና ትንቢቱ ላልገባቸው ፈሪሳዊያን ግን አሜን ብለው ሊቀበሉት የማይችሉት የራስ ምታት ነበር።
· የጌታ ስደትና በቤተልሔም ሕጻናት ላይ የደረሰ እልቂት፤
ከላይ እንደተገለጸው ፈላስፎች በሌላ መንገድ ተምልሰው መሔዳቸው ያበሳጨውና ለሥልጣኑ ካለው መጓጓት አንጻር በተከሰተው ሁኔታ የተስፋ መቁረጥና የአእምሮ መታወክ የገጠምው የገሊላ ንጉሥ ሄዶሮድስ በቤተልሔም የተወለደውን፣ ነገሥታት ወድቀው የሰገዱለትንና፣ እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ የገበሩለትን (ማቴ 2፡11)የዓለም መድኃኒት ለመግድል ውስኗል። ይህን ካላደረገ የመንፈስ እረፍት አያገኝምና። እነሆ ከጌታ የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” (ማቴ 2፡11)ይሚለውን ትዕዛዝ ያስተላለፈው በዚህ ሰዓት ነበር። የሕጻኑን ንጉሥ ስደት ተከትሎ ሄሮድስ በቁጣ በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ በግፍ እንዲታረዱ አደረገ። በዚህም መላዋ የአይሁድ ምደር በሐዘን በትር ተመታች፤ የብዙ እናቶች ጡታቸው ፈሰሰ፣ እንባቸው ምድሪቱን አራሰ። በዚህ ግፍ የተሞላበት ጭፍጨፋ ያለቁት ሕጻናት ቁጥር በሶሪያውያን ትውፊታዊ 64 እልፍ በኢትዮጵያውን ደግሞ 14 እልፍ እንደነበር ይተረካል። በዚያ የመከራ ዘመን ከሞት ከተረፉት ጥቂት ሕጻናት መካከል በብሥራተ መልአክ የተወለደው መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንዱ ነው። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የቅድስት ድንግል ማርያም አክስት ስትሆን፣ አባቱ ዘካርያስ ደግሞ በቤተ መቅደስ እግዚአብሔር እንዲያገለግል የተቀባ ደግ ካህን ነበር።
ሕጻናትን ከእናታቸው ጉያ እየነጠቀ ይቀስፍ የነበረው ሄሮድስ ዮሐንስ ከልደቱ ጀምሮ የእግዚአብሔር በረከት ያልተልየው መሆኑን ስለሚያውቅ አድነው በአለበት አንገቱን በሰይፍ እንዲቀሉት መልእክተኞችን ላከ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ መኖሪያ ቤታቸው በመካከለኛ የኢየሩሳሌም ክፍል በመሆኑ ከዚህ ቅጣት ሊያመልጡ እንደማይችሉ የተገነዘቡት ወላጆቹ አስቀድመው መክረው ቅድስት ኤልሳቤጥ በሙት ባሕር አጋባቢ በሚገኘው የናዝሬት ደቡባዊ ተራራማ ክፍል ይዛው እንድትሰደድ አደረጉ። የሄሮድስ መልእክተኞች እያሰሱ መጥተው ዘካርያስን ልጁን እንዲያቀርብ አስጨነቁት፤ እርሱ ግን ልጁ ያለበትን ቦታ ጠቁሞ ከሚያሳይ በዚህ ምክንያት የሚመጣውን መከራ በጸጋ መቀበልን መረጠ። ከሚያገለግልበት ቤተ መቅድስ አጠገብ በሰይፍ ተከልሎ በሰማዕትነት አለፈ። የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥም ብዙ ሳትቆይ ልጇን በበረሃ ትታ ዘካርያስ በተከለለ በ40ኛው ቀን ከዚህ ዓለም ተሰናበትች። በሄሮድስ ምክንያት ወላጆቹን ያጣው ቅዱስ ዮሐንስ በ30 ዓመቱ ለአገልግሎት እስከ ተጠራበት ቀን ድረስ ኖሮውን በምድረ በዳ አድርጎ አንበጣና የጋጃ ማር እየተመገበ በብቸኝነት አደገ።
ለ) የስደት ምርጫና የስደት ሕይወት፤
አንድ ሕዝብ ወይም ግለሰብ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ወይም በችግር ምክንያት ከሀገሩ ወጥቶ የተወለደበትን አካባቢና ቀየውን ትቶ ይሰደዳል። በተለይ በፖለቲካ ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎች ሕይወታቸው ሁልጊዜ ስጋትና ሰቀቀን የተሞላበት ነው። የጌታ ስደት ፖለቲካዊና ሃማኖታዊ ይዘት ያለው በመሆኑ፣ ከሞት የመትረፉ ጉዳይ ለእናቱና ለወዳጆቹ ለጊዜው እፎይታን ቢፈጥርም ነገር ግን“በአንችም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፍል” (ሉቃ 2፡ 34)ተብሎ ትንቢት የተነገረባት ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ምክንያት ያሳላፈቸው የመከራ ጊዜ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም። አንድ ሕዝብ ወይም ግለሰብ አስገዳጅ በሆነ ክፉ አጋጣሚ ስደትን እንደ አማራጭ ሲቀበል የሚሰደድበትን ሀገርና ሕዝብ አስቀድሞ ማጤን የግድ ይሆናል። ምክንያቱም ስደተኛው የሚሰደድበት አካባቢ ሰላም የሰፈነበት መሆኑን፣ ወይም ለስደተኛው ከለላ ሊሆኑ የሚችሉ የሚያውቃቸውና የሚዘመዳቸው ግለሰቦች መኖራቸውን ማረጋገጥ ይገባልና። እነዚህ ቅዱሳን ቤተሰቦች ቅድስት ድንግል ማርያምና አረጋዊ ዮሴፍ ከመጀምሪያው ስደትን እንደ አማራጭ ሲቀበሉ የሚሰደዱበት ሀገር ምርጫ እነርሱ መክረው የተስማሙበት ሳይሆን አስቀድሞ በተቀመጠው ትንቢታዊ ቃል መሠረት በመንፈስ ቅዱስ ውሳኔ የተፈጸመ ነው። የተጻፉትም የትንቢት ቃላት እንዲህ የሚሉ ናቸው፣ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” (ኢሳ 19:1)። “እም ግብፅ ጸዋዕክዎ ለወልድዬ” “እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” (ሆሴ 11፡1)።
እዚህ ላይ ይህ ትንቢታዊ ቃል መጠነኛ ማብራሪያን ይጠይቃል። ምክንያቱም ኢየሱስ ወደ ግብፅ የወረደው ጥንቁልናን ሊማር ነው ብለው የሚያምታቱ አሉና። ጌታ ወደ ግብፅ የወረደው በደመና ተጭኖ ሳይሆን በእግር ተጉዞ ነው። አባቶቹ ጥንታዊያን የእስራኤል ልጆች በርሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ ተሰደው ሲመለሱ በደመና ከፀሐይ ግለት እየጠበቀ ይመራቸው ነበር። አሳዳጃቸው ፈርኦን ሊደርስባቸው በተቃረበም ጊዜ በደመና ከልሎ ከሞት ስውሯቸዋል። ስለዚህ ይህ ቃል ጌታ በመለኮታዊ ጥበቡ ራሱንና ድንግል ማርያምን ጨምሮ ተከታዮቹን በስደት ከሚገጥማቸው ከብዙ ሥጋዊ መከራ የታደገ መሆኑን ያመለክታል። በይበልጥም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ እንደሚለው “በደመና ተጭኖ ይመጣል” የሚለው ቃል መለኮት የሰውን ሥጋ መዋሐዱንና ስደቱም በተአምር ሳይሆን በለበሰው ሥጋ መከናወኑን የሚያመለክት ነው። ጌታ ወደ ግብፅ የተሰደደበት ሁለተኛው ምክንያት የአባቶቹን የእነ አብፍሃምን፣ የእነ ያዕቆብን፣ የእነ ሙሴንና የሌሎችንም አበው ስደት ለማዘከር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስማቸው የሰፈረ ብዙ ቅዱሳን በእርሱ ፈቃድ ወደ ገብጽ ተሰደው ብዙ መከራ ተቀብለዋልና። ከእነዚህ አበው የስደት ተመክሮ ምን ልንማር እንደሚገባን በመጭረሻ እናያለን። በሦስተኛ ደረጃ ጌታ ወደ ግብፅ የተሰደደበት ዋናው ምክንያት የበርካታ ቅዱሳን እግር የረገጣት ይህች ባለታሪክ ሀገር ጥንቁልና የበዛባት የጣኦት ምድር ስለ ሆነች ጣኦታትን ከግብፅ ምድር ለማጥፋትና ዲያብሎስንም ለማባረር ነው። “ጉየተ ሕጻን አጉየዮ ለዲያብሎስ”እንዲሉ ሊቃውንት። ወደ ግብፅ ተሰዶ መመለስ ማለት ከሲኦል ወጥቶ ገነት መግባት ማለት ነው። በዚህም ነፍሳት ከሲኦል ወጥተው ወደ ገነት የሚሸጋገሩበት ጊዜ መቃረቡን ያመለክታል።
ሐ) የቅዱሳን ቤተሰብ የጉዞ ገጠመኞች-ስደት፣ ርሃብና እንግልት በልጅነት፤
የእግዚአብሔር መልእክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ“ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ” የሚለውን መልእክት እንዳስተላለፈ ድንግል ማርያምና ጻድቁ ዮሴፍ ዕቃ እንከውናለን፣ ንብረት እንሰበስባለን አላሉም። ወዲያውኑ በፍጥነትና በድንጋጤ ተነስተው ከቤተልሔም ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፉባትና ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ጡት ያጠባችባት ቦታ ከቤተልሔም በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ የምትገኝ ዋሻ ነች። ይህች ዋሻ የድንግል ማርያም ዋሻ በመባል ትታወቃለች። ክርስቲያኖችም እስላሞችም በእኩልነት ያከብሯታል። ከጊዜ በኋላ በተጠረበ ነጭ ድንጋይ የተገነባ በየጊዜው ብዙ ተሳላሚዎች የሚመላለሱበት ቤተ ክርስቲያን ታንጾባታል። ነጭ ድንጋይ የድንግል ማርያም የጡት ወተቷን ጠብታ ይወክላል። በዚህ አስቸጋሪ የስደት ጉዞ ዮሴፍና መላው ቤተሰብ አያህን ለመጓጓዣነት እንደተጠቀሙ በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች መዝግበውታል። አህያ በዚያ ዘመንና ከዚያም በፊት በነበሩ ዘመናት ቀላልና የተለመደ የመጓጓዣ እንስሳ እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ ተመሳሳይ ታሪክ ያስነበበናል። “ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ”(ዘፀ 4፡20፣ ዘካ 9፡9)። እንደ አርሜንያውያን ትውፊት እነዚህ ቅዱሳን ስደተኞች ቀጥሎ ያረፉባት ከተማ ሳምሶን ፍልስጥኤማውያንን የገደለባት አስቃሎን ትባላላች (መሳ 14፡19)። አስቃሎን ታላቁ ሄሮድስ ለመዝናኛ እንድትሆን የመረጣትና በብዙ ኅብረ-መልክ አስውቦ የሠራት ከተማ ነበረች። ቀጥሎም በዓለም እጅግ በጣም ጥንታዊ በምትባለው በሄብሮን ከተማ(ዘኁ 13፡22) አልፈው ጋዛ ደረሱ። በጋዛ ከተማ የተቀመጡት ለሁለት ቀናት ያህል ብቻ ነበር። በዚያ ሳሉ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለጉዞ እንዲሆናቸው የላከችላቸውን በርከት ያለ ልብስ ክፍለው ለነዳያን መጽተው ቀሪውን ለሕጻኑ ድልዳል እንዲሆን ካዘጋጁ በኋላ በአህያ ላይ ሆነው ጉዟቸውን ወደ ግብፅ ቀጥለዋል። ኢትጵያውያን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደቷ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዳለፈችና በጣና ሐይቅ ውስጥ እንዳረፈች ይተርካሉ።
የቅዱሳን ቤተሰብ የስደት ጉዞ ሲነሳ ሁልጊዜ በሰው አእምሮ ውስጥ የሚመላለሰው ባልሰለጠነ ዘመን፣ ከእግር ጋራ የሚስማማ ጫማና ጥማትን የሚቆርጥ ቀዝቃዛ ውሃ በማይገኝበት በምድረ በዳ 485 ኪሎ ሜትር አቋርጦ መጓዝ አካሉ ላልጸና ለጋ ሕጻንና ከሚተናኮላቸው የበረሃ አውሬ ወይም ቀማኛ ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሣሪያ ለሌላቸው ምስኪኖች ምን ያህል አስፈሪና ከባድ እንደሆነ ነው። ዘመኑ ክረምት ነው፤ ከላይ ዶፍ ይወርዳል፤ በቀን የበረሃው ዋዕየ ፀሐይ እንደ ሰም ያቀልጣል፤ መጠለያ ድንኳናቸው ቀና ብለው የሚያዩት ሰማይ ብቻ ነው። ይሁን እንጅ በዚህ ሁሉ አስፈሪ የመከራ ጉዞ ውስጥ አልፎ አልፎ በድንገት እየተከሰተ መግቦቱንና ታዳጊነቱን የሚያሳያቸው የልዑል እግዚአብሔር መለኮታዊ ጥባቆት ለልቦናቸው ማረፊያ ወደብ ለሐዘናቸውም መጽናኛ ይሆናቸው ነበር። ለቅዱስ ዮሴፍና ለቅድስት ድንግል ማርያም ይህ አጋጣሚ የተሰደዱለት ሕጻን የሰምይና የምድር ፈጣሪ መሆኑን ከመቸውም በበለጠ የተረዱበት ጊዜ ነበር። ሲጓዙ ውለው ጭልምልም ሲል በሚያሳዝን ሁኔታ እዛፍ ስር እጥፍጥፍ ብለው ይተኛሉ። ሕጻኑ ኢየሱስ ብርዱን መቋቋም ተስኖት ሲንቀጠቀጥ ወይም ከፀሐይ ግለት የተነሳ ሰውነቱ እንደ ሰም ሲቀልጥ ይደነግጣሉ። ነገር ግን ለእነርሱ ፍርሃትና ባዶነት የሚሰማቸውን ያህል በተቃራኒው በአረፉበት ቦታ ዙሪያ የብርሃን ድንኳን ተተክሎ፣ ቅዱሳን መላእክት ዙሪያውን ከበውት፣ ሰማያዊ መዓዛ ዕጣን ሲያሸቱ ሰማያዊ የምስጋና ቃል ሲያዳምጡ ያድራሉ። ውሃ ከአለት ላይ እየፈለቀላቸው ይጠጣሉ። መና ከሰማይ እየውረደላቸው ይመገባሉ። እነዚህ ቅዱሳን ቤተሰቦች ነቢዩ ኤልያስ የንግሥት ኤልዛቤልን ዛቻ ፈርቶ በተሰደደበት በቤርሳቤህ በረሃ (1 ነገ 19፡3) በበለጠ የተረዱትና ያስተዋሉት ይህን ድንቅ የእግዚአብሔር ምሥጢር ነበር።
በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጉዞ አልፈው ምድረ ግብፅ ደረሱ። እዚያ እንደ ደረሱ መላዋ ሀገሪቱን ብሩህ ደመና ከበባት፤ ሕጻኑ ኢየሱስ ዓይኖቹን ቀና አድርጎ በአንክሮ ተመለከተ። ባልተለመደ ሁኔታ እጆቹን አንስቶ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ባረከ። ከደመናውም የሚያስፈራ መብረቅና ነጎድጓድ ምድሪቱን አናወጣት፤ የግብፅ ጣኦታት በያሉበት ፈረሱ፣ አጋንንት ወጥተው ተሰደዱ። ከዚህ በኋላ ሕጻኑ ኢየሱስ ወደ ትውልድ ሃገሩ ወደ ናዝሬት ከመመለሱ በፊት ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሆኖ እርሱ ባረፈባቸው የግብፅ ከተሞች ሁሉ ልዩ ልዩ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል። በእነዚህ የተባረኩ ቦታዎች በአብዛኛዎቹ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውባቸው በአሁኑ ጊዜ የእግዚአብሔር በረከት ያልተለያቸው በክርስቲያኖች የሚጎበኙ የአምልኮት ማዕከላት ሆነው ይገኛሉ።
መ) ስደተኞች ከቅዱሳን ስደት የምንማራቸው ቁምነገሮች፤
የስደት ምንጩ የሀገር ፍቅር፣ የሃይማኖት ክብርና የዓላማ ጽናት ሊሆን ይችላል። በፖለቲካም ይሁን በሃይማኖት ለተሰለፉበት ዓላማ እስከ መጨረሻው መስዋዕትነትን ለመክፍል የሚዘጋጁ ሁሉ ባለክብር ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለ እውነት ብለው የሃይማኖታችን መሪ ክርስቶስ በተሰደደበት መንገድ የተሰደዱ ቅደምት የሃይማኖት ሰዎች ብዙዎች ሲሆኑ፣ ከእነርሱ አንዱ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። ሙሴ ከስደተኛ ቤተሰብ የተወልደ ከመሆኑም በላይ ግብጻዊው ወጣት በዕብራዊ ወንድሙ ላይ ግፍ ሲሠራበት በተመለከተ ጊዜ ስለ እውነት ሲል ግብፃዊውን ተበቅሎ (ገሎ)ወደ ምድያም ተሰዷል (ዘፀ 2፡15)። ምድያም ኢትጵያዊ እንደሆነ የሚነገርለት ለሙሴ አስተዳደራዊ ጥበብን ያስተማረው አስተዋይ ካህን የዮቶር መቀመጫ ሀገር ናት። ሙሴ ያሳደደው የግብፅ ንጉሥ ሲሞት በጽኑ አገዛዝ የሚሰቃዩትን ወገኖቹን ከባርነት ነጻ እንዲያወጣ ወደ ግብፅ መልሶ ተጠራ። ጥሪውን ተቀብሎ ተመለሰ። የፈርኦን የልጅ ልጅ እየተባለ በቤተ መንግሥት በድሎት ከመኖር ይልቅ ከስደተኛው ወገኑ ጋር ስደተኛ መሆንን፣ አብሮት ለተሰደደው ሕዝብ ሲል መከራ መቀበልን መረጠ። በእግዚአብሔርም ፊት ለመንጋው ያለውን ታማኝነት በጽናት አረጋገጠ (ዕብ 3፡2)። ይሁን እንጅ ሙሴ ጥፋት ሲፈጸም አይቶ መታገስ የሚችልበት ኅሊና የለውም። በሌላ በኩል ግን ርኅሩኅ በመሆኑ እግዚአብሔር እስራኤላውያን በፈጸሙት በደል አዝኖ “ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው”(ዘፀ 32፤10) ባለው ጊዜ ከራሱ ክብር ይልቅ የሕዝቡን ደኅንነት በማስቀደም ወገኖቸን ከምታጠፋ የእኔን ስሜን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስስ ብሎ የተማጸነ፣ ሕዝቦቹን ከጥፋት ያዳነ ደግ የሃይማኖት መሪ ነው። ሌሎችም ከሙሴ በኋላ የተነሱ የእስራኤል ነቢያት ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ሙሴን አብነት አድርገው በመከራ ጊዜ አጋርነታቸውን ለማሳየት ከሕዝባቸው ጋር አብረው ተሰደዋል፤ ለመንጋው ያላቸውንም ታማኝነትም በጽናት አረጋግጠዋል።
ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ለሕዝባቸው ደኅንነት ሲሉ የተሰደዱ የሃይማኖት መሪዎች ብዙዎች ናቸው። ይሁንና በሃይማኖት መሪዎችና መሪዎችን በሚከተሉ መንጋዎች መካከል ሊኖር የሚገባው መከባበር፣ መደማመጥና መተሳሰብ ከሌለ አንዱ ለሌላው ብሎ መሰደዱ ወይም እረኛና መንጋ (ጠባቂና ተጠባቂ) ተብሎ መሰሙ ትርጉም አይኖረውም። ለሕዝቡ ቆመናል ብለው የተሰለፉ ገልጋይ ካህናትም ሕዝቦች ከቀጥተኛው የእምነት መንገድ ሲወጡ ሊገስጿቸውና ሊያስተካክሏቸው ካልቻሉ፣ ወይም ሕዝቦች እርስ በራሳቸው በዘር በጎሳ እየተናከሱ ሲፋጁ በመካከል ሆነው (ወገንተኝነት ሳያሸንፋቸው) እውነቱን እየመሰከሩ የተለያዩትን አንድ ካላደረጉ፣ የክርስቶስ እንደራሴዎች ሳይሆኑ ጥቅማቸውን ብቻ እያስከበሩ መንጋውን ወደ ጥፋት ጎዳና የሚመሩ ምንደኞች ያስብላቸዋል። በእንደራሴነት መቆማቸውም ሆነ ለሕዝባቸው ሲሉ መሰደዳቸው ጥቅም ፈላጊ እንጅ እውነተኝ አገልጋይ ሊያድርጋቸው አይችልም። በተሰለፉበት ዓላማ አልጸኑምና ከእግዚአብሔርም ከሀገርም የራቁ የሁለት ዓለም ስደተኞች ሆነው ይቀራሉ። ታሪክም ለዘለዓለም ሲያጋልጣቸው ይኖራል። የሁለቱን ስደተኛ የሃይማኖት መሪዎች የሙሴንና የአሮንን ታሪክ እንደገና ብንመለከት ለዚህ አባባል ትክክለኛ ማረጋገጫ ነው። እስራኤላውያን ከእውነተኛው መንገድ ወጥተው መሪዎቻቸውን መጋፋትና በራሳቸው ፈቃድ መራመድ በጀመሩበት ጊዜ ሁለቱ ካህናት አሮንና ሙሴ የወሰዱት እርምጃ የተለያየ ነበር። ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተጠርቶ በደብረ ሲና ተራራ ላይ ሁለቱን ጽላቶች ከፊጣሪው ዘንድ ለመቀበል በጾምና ጸሎት ላይ እያለ እስራኤላውያን ተሰብስበው አሮንን አማልክት ሥራልን ብለው በአስቸገሩት ጊዜ አሮን ራስ ወዳድነት አሸንፎት ምን አገባኝ ብሎ የፈለጉትን ጣኦት አቁሞላቸዋል፤ በጣኦቱ ፊት ሲጨፍሩም ከዳር ቆሞ በዝምታ ተመለከቷቸዋል። ሙሴ ግን ከደብረ ሲና እንደ ተመለሰ ይልቁንም ልቡናቸው በመብልና በመጠጥ ደንዝዞ ይጨፍሩ በነበረበት ሰዓት በመካከላቸው ተገኝቶ ጣኦታቸውን በያዘው ጽላት ቅጥቅጦ ሰባብሮባቸዋል፣ ስለ በደላቸውም የንስሐ ቅጣት ሰጥቶ አስተካከሏቸዋል (ዘፀ 32፡20)።
በዛሬዋም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት የተለያየ ዓላማ ይዘው የተሰለፉ አገልጋዮች ብዙዎች ናቸው። በምዕመናንና በካህናት መካከል እየተከሰተ ያለው ያልተለመደ መዘናጠል አስደንጋጭ ቢመስልም አባቶቻችን ሐዋርያትም ሆኑ ቀደምት ነቢያት ያገልግሉት በነበረው ሕዝብ እጅ መከራን የተቀበሉ በመሆኑ ይህ ለካህናት አዲስ ነገር ሊሆንብን አይገባም። ካህናቱ በመንፈሳዊ ዓላማቸው እስከ ጸኑ ድረስ ምዕመናኑ የጎሰኝነትና የፖለቲካ ትኩሳታቸው ሲበርድላቸው እውነትን ፍለጋ መመለሳቸው አይቀርም። ይልቁንስ የሚያሳዝነው የአገልጋዮች ሆድ አደር መሆንና በተለይም እርስ በራሳቸው የሚያሳዩት መካካድ ነው። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተሰለፉበት መንፈሳዊ ተግባር ስኬታማ እንዲሆኑና በምእመናን መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ማየት ከፈለጉ ከሁሉ አስቀድሞ በመካከላቸው መነቃቀፍን አርቀው (አንዱ የሌላውን ሥራ ማፍረሱን ትተው) ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መከበር በአንድነት መቆምና በሚሰጡት አመራር ዙሪያ መመካከር ይጠበቅባቸዋል። በዓለንበት ዘመን በተልይ በስደት የምትኖረው ቤተ ክርስቲያን የምትመራው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በሌላቸው ሰዎች በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ “ምን ዓለበት” በሚል ቋንቋ ያልተለመዱ ሰርጎ-ገብ ልማዶችን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋር አዳብሎና አቻችሎ ለማራመድ እየተደረገ ያለው ሙከራ አደገኛ አዝማሚያ ነው። የመንጋው እረኛ እንደ አሮን አድርግ የተባለውን ብቻ የሚያደርግ በራሱ የማይተማመን ሆድ-አደር ከሆነ ነገ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን የገጠማቸው ከባድ ፈተና ቢያጋጥመው በጽንስ፣ በጋብቻ፣ እና በሥርዓተ ቀብር ዙሪያ ሊከሰቱ በሚችሉት አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ መፍተሔ ለመስጠት መቸገሩ የማይቀር ነው።
የካህናት አስተማሪነታቸው በአገልጎሎት ላይ ሊኖራቸው በሚገባው ተመሳሳይነት ያለው አቋም ብቻ ሳይሆን በግል ሕይወታቸውም በሚያሳዩት አርዓያነት ጭምር ነው። ሙሴና አሮን በዓላማ ጽናት ወይም ለእስራኤላውያን በሚያስተላልፉት መንፈሳዊ አመራር ረገድ ልዩነት እንደነበራቸው ሁሉ በሥነ-ምግባርም እንዲሁ የሚያፈርስና የሚገነባ (የተለያየ) አቋምና ይዘት ነበራቸው። ሙሴ ከሚወዳቸው ተከታዮቹ መካከል በትውልድ የማትመሳሰለውን ኢትዮጵያዊት በማግባቱ ሰውን በሰውነቱ የሚያከብር፣ የፈጣሪ በጎ ፈቃድ ምን እንደሆነ የገባው፣ ሚዛናዊ የሃይማኖት መሪ መሆኑን አስመስክሯል። አሮን ግን የሙሴን ከኢትዮጵያዊት ጋራ በጋብቻ አንድ መሆን እንደ ውርደት በመቁጠር ባሰማው ተቃውሞ የሰው ልጆች በእኩልነት የተፈጠሩ መሆኑን የዘነጋና የአምላክን ሚዛናዊነት የሚቃወም ወይም በዘመናችን ቋንቋ የዘረኝነት አስተሳሰብ የሚያጠቃው ጠባብ መሆኑን አሳይቷል። ሁሉንም አማኞች በእኩል ዓይን እንዲመለከት አደራ የተጣለበት የእግዚአብሔር እንደራሴ እርሱ ብቻ ሳይሆን እህቱ ማርያምንም የሐሳቡ ደጋፊ አድርጎ በሙሴና በኢትዮጵዊት ሚስቱ ላይ የነቀፌታ ቃል ሲናገር፣ ጥላቻንና መለያየትን ሲሰብክ በመገኘቱ ሰው ፊቱን ያዞረባቸውን ምስኪኖች የማይረሳ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር “ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በደመና ዓምድ ውርዶ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ለፍርድ ቆመ። ማርያምና አሮንን ጠርቶ ስለ ጥፋታቸው በኃይለ ቃል ገሰጸ፣ በፊታቸው እውነተኛ የቅጣት ፍርዱን አስተላለፈ። አሮንና ማርያም መድኃኒት በሌለው የለምጽ በሽታ ተመቱ። የሙሴን አመራር አልቀበልም ብሎ አምጾ የቆየው አሮን እግዚአብሔር ወርዶ ከፈረደበት በኋላ ወደ ልቡ ተመለሰ። በደለኛ መሆኑንም አምኖ ተቀበለ። ስለ ራሱና ስለ እህቱ ስለ ማርያም እንዲህ ሲል ወንድሙ ሙሴን ለይቅርታ ተማጸነ “ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን። ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን” (ዘኁ 12፡12)። ሙሴ ግን ደግና ርኅሩኅ በመሆኑ የሚጭክን ልብ የለውም። ወደ እግዚአብሔር እጆቹን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ዳሰሳቸው በምሕረት እጁ ፈወሳቸው።
በእኛስ ዘመን ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን መለያዬትን ከማን ነው እየተማሩ ያሉት? ከካህናት አይደለም እንዴ! የምታወራው የፈጠራ ወሬ ነው፤ እኔ እንዲህ ዓይነት ችግር የለብኝም የሚል ወገን ካል ልቡን ለፈጣሪ ያስፈትሽ። እሱ ኩላሊትን ይመረምራል፤ የተደበቀውን ይገልጣል። እናስተውል! አምላካችን ከመለኮታዊ ክብሩ ወርዶ ወደዚህ ክፉ ዓለም ተሰዶ መከራን የተቀበለው ከእራሱ ጋር ሊያስታርቀን፣ በእምነትና በሥጋዊ የዘር ሐረግ ተለያይተን የነበርነውን የሰው ልጆች በመንፈሳዊ ልደት አገናኝቶ በስሙ አንድ ሊያድርገን ነው። እናም መለያየትናን ዘርኝነትን እግዚአብሔር አይወድም። የዳዊት ልጅ ሰሎሞን “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች” ይልና፤ ስድስት ነገሮችን ከዘረዘረ በኋላ ሰባተኛውን ሲገልጽ “በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ”(ምሳሌ 6፡16) ብሏል።
ስለዚህ አንዱ በሌላው ማሳበቡን ትተን እያንዳንዳችን ልንስተካከልና የለውጥ ጀማሪዎች ልንሆን ያስፈልጋል። የመለያየትንና የጎሰኝነትን መንፈስ ያረገዘ፣ በጥላቻ የተመረዘ ልብ ይዞ ሀገር እገነባለሁ፣ ወይም የአድነትን ወንጌል እሰብካለሁ ማለት እያፈረሱ መገንባት እየገነቡ ማፍረስ ነው። በዚህ ዘመን ጎሰኝነትና መለያየት ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖትም ሆነ በሀገር ደረጃ ምን ያህል እንደ ጎዳን አሁን ካልገባን ለለውጥ ራሳችንን ልናዘጋጅ አንችልም። ካልተለወጥን ደግሞ የምንመኘው ሰላምና ብልጽግ ሕልም ብቻ ሆኖ ለመቅረቱ ተጠያቂው እኛው ራሳችን ነን እንጅ እግዚአብሔር አይደለም። እንደ ሙሴና እንደ አሮን ፈጣሪ በአካል ወርዶ በፍርድ ዙፋን ላይ እስከሚቀመጥ መጠበቅ አይገባንም። ለውጥ ከራሳችን መጀመር አለበት። ይህ ካልሆነ ግን አይደፈሬውን የሚደፍር፣ ትዕቢተኛውን የሚያሳፍር እግዚአብሔር ቢዘገይም ቆይቶ ፍርዱን ማስተላለፉ አይቀርም።
ክብር ምስጋና ጌትነት ከምድር እስከ ሰማይ ለእርሱ ይሁን።
የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና በረከት አይለዬን፣ አሜን።
ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ
0 comments:
Post a Comment