የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜሰዎች ትርጓሜ፦
ምዕራፍ 10
Ø ይህ ምዕራፍ የእስራኤል የእምቢተኝነት ምዕራፍ ተብሎ የሚጠራ ነዉ። ሐዋርያው እስራኤል የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል ያልወረሱበትን ምክንያት ሲመረምር የእግዚአብሔር እዉነት የተነካ መስሎ ስለታየ እስራኤል ያልዳኑበት ምክንያት አለማመናቸው እንደ ሆነ በአጽንኦት ያስረዳል።
Ø በምዕ 10 የእግዚአብሔር ድህነት ለሁሉ እንደሆነ ተረጋግጧል። እግዚአብሔር ደህንነትን ለሁሉ ሲያዘጋጅ ሁሉንም ደግሞ ሲጠራ ለሰው ፊት አድልቶ አህዛብን እንደመረጠ እና እስራኤልን እንደጣለ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ ተወዳጅ የነበሩት ወገኖች እስራኤል እንዲሰሙ አደረገ (ማቴ 10 ፥ 5 – 6 ፣ የሐዋ. 11 ፥ 19 ፣ 13 ፥ 42 – 46)
Ø በደህንነት ጉዳይ ላይ ከእግዚአብሔር ምርጫ ውጪ ከሰው የሚጠበቅ ምንም ነገር የሌለ ቢሆን እስራኤል ያለጥርጥር በዳኑ ነበር ምክንያቱም ተመርጠው ነበርና። ነገር ግን እግዜአብሔር መርጦ ያንን የሰው ልጅ በእምነት ካልተቀበለ የመዳን እድሉ ያልፈዋል ማለት እንደሆነ ያሳያል። (ማቴ. 23 ፥ 37)
Ø እስራኤልን አልመረጣቸውም ሊባል ይችላልን? ከቶ አይቻልም። ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ እጆቹን ዘርግቶላቸው ነበር ተብሎአልና። (10፥21)
ቁ. 1 – 4፦
Ø ሐዋርያው ወደ አህዛብ ዘወር ብሎ ነበርና ወገኖቹን እስራኤል ፈፅሞ እንደዘነጋቸው ብዙዎች ገምተው ነበር። (ሐዋ. 18 ፥6 ፣ 21 ፥ 21 ፣)
Ø ይህ ሀሳብ እውነት አለመሆኑን ሐዋርያው በዚህ አንቀጽ አጽንኦት ሰጥቶ ያስረዳል። መርሳትና መጥላት የማይታሰብ እንደሆነ ከመግለጥም አልፎ የዘወትር ጭንቀቱና ሃሳቡ ስለወገኖቹ መዳን እንደሆነ ይገልጣል።
Ø ምክንያቱ ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ ፅድቅን ለማግኘት የሚመኙ ቢሆኑም በተሳሳተ መንገድ ስለሆነ የሚሄዱት የመዳንን መንገድ ሊያገኙ አለመቻላቸው ነው።“በእውነት አይቅኑ እንጂ እንደሚቀኑ እመሰክንላቸዋለሁ ” ይላልና።
Ø እዚህ ላይ የሚያስተምር ስለጽድቅ የሚሆነው ቅንዓታቸን ምንም ያህል ኒያይልም በእውነትና በማስተዋል ላይ ካልተመሰረተ ምንም ሊያተርፍልን አለመቻሉን ልብ እንድንል ነው።
Ø እስራኤል የእግዚአብሔርን ጎዳና ትተው የራሳቸውን መከተላቸው ያስከተለባቸው ሁለት ትልልቅ ችግሮችን ነው። እነሱም፦
1) ጽድቅ የሚገኝበትን እውነተኛ መንገድ ተሳሳቱ።
2) ለእግዚአብሔር ጽድቅ መገዛት አቃታቸው። ይህም የእግዚአብሔርን ጽድቅ ትተው የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም በመጣራቸው ነው።
ማስገንዘቢያ ፦
Ø ልናስተውል የሚገባን ነገር እነዚያን እስራኤልን የሚመስሉአቸው ብዙዎች ዛሬም ያሉ መሆኑን ነው።
Ø ዛሬ ብዙዎች የልብ ቅናት አላቸው ጽድቅን መፈለግም የሕይወታቸው አይነተኛ ጉዳይ ነው። ነገር ግን የሚፈልጉትን ጽድቅ በተገቢው መንገድ የማይሹት ከሆነ ከቶ ሊያገኙት አይችሉም።
Ø ለእግዚአብሔር መቅናት፣ ሃይማኖትንም ማክበር ምንም ያህል የተመሰገነ ቢሆን በተሳሳተ መንገድ የሚከናወን ከሆነ ወደ መዳን ከቶም ሊያደርስ አይችልም።
ቁ. 5 – 13 ፦
Ø ” የሚያምኑ ሁሉ ይፀድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍፃሜ ነው” ለዚህ ቃል ሐዋርያው የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ለማቅረብ ይፈልጋል።
Ø ይህም በእምነት የሆነው ፅ በሙሴ አፍ የተመሰከረለት እንደነበረ ነው። (ዘዳ. 30 ፥ 11 - 14)።
Ø ” ይህ ደግሞ በወንጌል የምንሰብከው የእውነት ቃል ነው።” በማለት ሐዋርያው በእምነት ስለሚሆነው ጽድቅ አስቀድሞ በሙሴ የተነገረዉን ቃል ይተረጉማል። (ምዕ. 10 ፥ 8)።
Ø ”የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉይድናል”የሚለውም ቃል አስቀድሞ የተነገር እንደሆነ በነብዩ በኢዩኤል ትንቢት ታይቷል። (ኢዩ. 2 ፥ 32)።
Ø ደህንነት ለተወሰነ ወገን ሳይሆን ለሚያምን ሁሉ የተሰጠ እንደሆነ ካስረዳ በኋላ ሁሉም ሊያገኘዉ የሚችልበትን መንገድ ለማብራራት በ 3 መንገድ ብቻ ያስረዳል።
እነሱም ፦ 1) በልብ ማመን (10፥ 9 ፣ ያዕ. 2 ፥ 19)።
2) በእምነት መጥራት (10 ፥ 12 - 13)
3) በአፍ መመስከር (10 ፥ 10 - 11)።
Ø እነዚህ ሦስት ነገሮች ደህንነት ለመቀበል መሠረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።
ቁ. 14 – 21 ፦
Ø ሐዋርያው እዚህ ጋር ሊያስረዳ የሚፈልገው በልብ ሊተመን፣ በእምነትም ሊጠራ ደግሞም በአፍ ሊመሰከርለት የሚያስፈልግው ”አዳኝ ” ማንነት ይድን ዘንድ ለሚያስፈልገው ሁሉ ይሰበክ ዘንድ መልዕክተኞች እንደሚያስፈልጉ፣ ምስክርነታቸውም ወሳኝ እንደሆነ ነው።
Ø ምክንያቱም ምንም ”አመነ ወይም አላመነም” ለመባል አስቀድሞ ሲነገረዉ ይገባል። (ኢሳ 52፥7)
Ø እስራኤል ግን ስላልሰሙ ሳይሆን በሰሙት ቃል ስላላመኑ ከመዳን ውጭ መሆናቸው ተናግሯል (ኢሳ 53፥1)
Ø ይህ የመዳን ጥሪ በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በእኛም ዘንድ ቢሆን እንዲሁ ስለሆነ በማስተዋል እንድንታዘዝ ቃሉ ይመክራል (ኤፌ 2፥4 ፣ 2ጴጥ 3፥9)
0 comments:
Post a Comment