ጥቅሙስ?
ካለፈው የቀጠለ፤
ይህን ያህል በምንጩ ላይ ካልኩ ወደ ሁለተኛው ነጥብ ልምጣ። የዚህ ነገር ጥቅሙስ ምንድርነው? የጸጋ ስጦታዎች የተሰጡት ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ነው። ይህ ‘ነቢይ’ አንዲትን ሴት ወደ መድረክ ጠርቶ ዘመዶቿንና ምስጢሯን መናገሩ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጸው ከቶ እንዴት ነው? ቲ. ቢ፣ ጆሹዋ አንድ የእግር ኳስ ቡድን እንደሚያሸንፍ ወይም አንድ ታዋቂ [ዘፋኝ] እንደሚሞት የተነበየውን ከዚህ ቀደም እንደጠቀስኩት ማለት ነው። ማይክል ጃክሰን መሞቱ ወይም የማንችስተር ቡድን ማሸነፉ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጽበት ምንም ነገር የለም። የሰውየው ትከሻ ላይ ኮከብ ከመጨመሩ ሌላ ማለት ነው።
የአንዲት ሴት ወደ መድረክ ተጠርታ ወጥታ የዘመዶቿ ስምና ገመና መነገሩ በዚያ ለታደመው ጉባኤ የሚፈይደው ከሌለ፥ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጸውና የሚገነባበት መንገድም ከሌለ፥ ጥቅም ቢኖረውና ጥቅሙም ለሴቲቱ ከሆነ የጉባኤው ስሜትና ጊዜ መወሰዱ ለምን አስፈለገ? እንደ አንድ ታዛቢ ብናስተውል ጥቂት ነገሮችን እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን። እነዚያም፥አንደኛ፥ በዚያ ድራማ ውስጥ የታየው ነገር ሁሉ ‘ነቢዩን’ የሚያጎላ፥ ደማቂና ተደናቂ የሚያደርግ ነገር መሆኑ፤ ሁለተኛ፥ ማኅበረ ምእመናኑን ወይም ቤተ ክርስቲያንን ከቶም የሚያንጽ ነገር አለመኖሩ፤ሦስተኛ፥ ክርስቶስ አለመታየቱ ናቸው። እነዚህ ቪድዮዎች ተመልካች ቀድቶ ስሕተትን ሊገልጥ የለጠፋቸው ሳይሆኑ በአዘጋጁ ክፍል በጥንቃቄ ተሠርተው ሌሎችን ለማስተማር ወይም ለማስተዋወቅ ሲባል ወደ አየር የተላኩ ናቸው።
ለክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ የዚህ ፋይዳው ምንድር ነው? ጸጋ የተሰጠው ለማኅበር እነጻ እንጂ ለእዩኝ እወቁኝ አለመሆኑ ለምን አይገባንም? ከላይ በጠቀስኩት ቃለ መጠይቅ ይህ ሰው ለምን ይህን እንደሚያደርግና ጥቅሙስ ምን ስለመሆኑ ተጠይቆ ሲመልስ፥ ስም የመጥራቱ ጥቅም አንድ ሰው በጉባኤ ውስጥ ቢኖር ያንን ሰው ብቻ ሳይሆን የዘመዶቹንም ማንነት ነግሮ ‘ኬዛቸውን’ መንገሩ እነሱንም ማገልገል ነው ብሎ፥ “እኔ ስጸልይለት የሱን ፋሚሊ ስም ከነገርኩት፥ የሱን ስም ከነገርኩት፥ ቤተ ሰቡን ከነገርኩት፥ ጓደኞቹን ከነገርኩት፥ እግዚአብሔርን ከማመን በላይ፥በወቅቱ የሚገለጠውን የጸጋ ስጦታ ከማመን በላይእንዲያምንና ተጠቃሚ እንዲሆን ነው።” ብሎአል።[1] የጉባኤው ድራማ ምክንያቱ እንግዲህ ይህ ነው። እግዚአብሔርን ከማመን በላይ እና የሚገለጠውን የጸጋ ስጦታ ከማመን በላይ ማመን ሲባል እምነትን በነቢዩ ቃል ላይ ማድረግ ይመስላል። ይህ የቃል-እምነት ትምህርት ነው። እምነት በጌታ ላይ ነው ወይስ በቃሉና በስጦታው ላይ ነው መሆን ያለበት?
እግዚአብሔርን ከማመን በላይ እና የሚገለጠውን የጸጋ ስጦታ ከማመን በላይ ማመን ሲባል እምነትን በነቢዩ ቃል ላይ ማድረግ ይመስላል። ይህ የቃል-እምነት ትምህርት ነው። እምነት በጌታ ላይ ነው ወይስ በቃሉና በስጦታው ላይ ነው መሆን ያለበት?
አንዳንዶች ይህንን ምስጢር የማወቅ ነገር ‘የመገለጥ ስጦታ’ ብለውታል። እንደዚህ የተባለ ስጦታ ያለ ይመስል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጸጋ ስጦታዎች በተዘረዘሩባቸው ምዕራፎች (ሮሜ. 12፤ ኤፌ. 4፤ 1ቆሮ. 12፤ 1ጴጥ. 4) መገለጥ የተሰኘ ስጦታ የለም። ከቃሉ ጋር የሚቀራረበው ይህ መገለጥ የተጠቀሰው በ1ቆሮ. 14፥29-30 ነው። ይህም ስለማን እንደሚናገር በቦታው ስናይ ከአንድ በላይ ሆነው በልሳን ስለሚናገሩ ሰዎች ከተናገረ በኋላ ከአንድ በላይ ሆነው ትንቢትን ስለሚናገሩ ነቢያት በተናገረበት ቦታ ነው። ነቢያትም ሁለትወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለትፊተኛው ዝም ይበል ይላል። እነዚህ ሰዎች በጉባኤው ያሉ ሰዎች ሲሆኑ የሚናገሩትን ነገር የሚለዩትም (ይለዩአቸው የሚላቸው) እዚያው ያሉቱ ናቸው። እንጂ መገለጥ የሚባል ስጦታ የለም። ሲሉ ሰምተን ወይም ተነግሮን፥ ‘እገሌ በመገለጥ የሚያገለግል አገልጋይ’ የምንለውም እኛ ነን እንጂ ቃሉ አይደለም። እንደዚህ የሚያስቡ ክርስቲያኖች፥ ማለት፥ የመገለጥ ስጦታ የሚሉት ነገር ያለ የሚመስላቸው ሰዎች፥ እነዚያ ይህ ስጦታ ያላቸው ሰዎች የሰዎችን ምስጢርና ገመና ገላልጦ የሚያዩበት መነጽረ-መለኮት የተገጠመላቸው ሰዎች እንደሆኑም ይገምታሉ። አንዳንዶቹ፥ ‘ከመቼው አጋለጠኝ’ ብለውም ይፈራሉ። ከፈሩ ቀድሞውኑ አውቀውታል፤ ካወቁ፥ ላሳወቃቸው መንፈስ ቅዱስ አክብሮትን አቅርበው በጸጸት መመለስ ነበረባቸው እንጂ ያን ሰውረው ልባቸው እየመታ ለፍተሻ መቅረብ አልነበረባቸውም። መገለጥ የሚለውን ቃል ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለት አቅጣጫ ተጠቅሞበታል። አንዱ የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ ሲሆን ሁለተኛውን ጳውሎስ የተረዳውን ሰማያዊ ምስጢር ለመግለጥ ነው። ይህኛው ጳውሎስ የሚናገረው መገለጥ ምስጢር ሆነው ኖረው ኋላ የታወቁትን የክርስቶስን ማንነት፥ እግዚአብሔርንና የማዳኑን እውነትና መንገድ ጠንቅቆ መረዳትን ነው። ይህንን መረዳት ቅዱሳኑ ሁሉ እንዲካፈሉትም ጸልዮአል፤ ኤፌ. 1፥17-19። በ2ቆሮ. 12፥1-7 ስለ ግል ልምምዱም ተናግሮአል። ታዲያ ይህ ሰማያዊ ምስጢር እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን የማዳኑን እውነትና መንገድ መረዳትን እንጂ የሰውን ገመና ማወቅ አይደለም። አሃ!? በአዲስ ኪዳን ጴጥሮስ የሐናንያንና የሰጲራን ምስጢር ማወቁስ? ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ከብሉይ ኪዳን ኤልሳዕም ሰዎች በስሜት ሕዋሳት ብቻ ሊያውቋቸው የማይችሉ ነገሮችን ሲያውቅ እናስተውላለን። ኤልሳዕን ብናጤን፥ ለምሳሌ፥ ሎሌው ግያዝ በምስጢር ከሶርያዊው ንዕማን ገንዘብና ልብስ ሲወስድ በዓይኖቹ ሳያይ አይቶአል፤ 2ነገ. 5፥2027፤ ሶርያውያን የተደበቁበትን ቦታ ለእስራኤል ንጉሥ ይጠቁም ነበር፤ 6፥8-12፤ የከበበውን የማይታይ ሠራዊት አይቶ ነበር፤ ቁ. 16-17። እነዚህ በእግዚአብሔር ላይ ወይም በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥፋቶች ናቸው። በምንም መንገድ ለራሱ ስም መደነቂያ ያደረጋቸው አይደሉም። ከላይ እንዳየነው፥ አንቺ እናት በእርግጥም የእግዚአብሔርነቢይ እንደሆንኩኝ እንድታውቂ የባለቤትሽን እህትስም ልንገርሽ? ብሎ የመታወቂያ ወረቀት እንዳደረገው አላደረጉም። ወደ ጴጥሮስ ስንመጣ፥ ይህ የጴጥሮስ እውቀት እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለሕዝቡ መታነጽ ካደረጋቸው ያልተደገሙ ነገሮች አንዱ ነው። ይህ የጴጥሮስ ድርጊት ከዘመናችን ‘መገለጦች’ በብዙ የተለየ ስለመሆኑ ከአራት አቅጣጫዎች እንይ።
አንደኛው ድርጊቱ ራሱ ነው። ጴጥሮስ ይህንን ነገር ቀጥሎ ቀጥሎ፥ ደግሞ ደጋግሞ ሲያደርግ አይታይም። ከዚህ አንድ ቦታ በቀር ሌላ ቦታና ሌላ ጊዜ ይህን አላደረገም። ስለዚህ ይህ የጸጋ ስጦታ ሳይሆን እግዚአብሔር በጊዜው ለአንድ ግብና ዓላማ የከሰተው ነገር ነው። ዛሬ ይህን መሳዩ ምስጢር የመግለጥ ጉዳይ የጸጋ ስጦታ እስኪመስል ድረስ በአንድ ጉባኤ ውስጥም እንኳ በየሳምንቱ፥ ምናልባት ከዚያም በላይ ይደርጋል። የሚገለጡት ጉዳዮች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የስም፥ የስልክ ቁጥር፥ ወዘተ፥ ነገሮች መሆናቸውም ሳይዘነጋ ነው። የነሐናንያ ድርጊት ተራ ቅጥፈት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ላይ፥ በእግዚአብሔር ላይ የተቃጣ ሴራና ደባ ነው። ይህ የክብደቱን ያህል፥ በስውርነቱ ልክ ወደ ሜዳ መውጣት ነበረበት።ሁለተኛው ተቀባዩ ነው። ጴጥሮስ ይህንን ነገር በቀጥታ የተናገረው ለማን ነው? በመጀመሪያ ራሱን ሐናንያን ነው የጠየቀው። ኋላም ራሷን ሰጲራን ነው የጠየቃት። የጅምላ ርችት አልተኮሰም። “እዚህ ጉባኤ ውስጥ እርስትህን ሸጠህ ግማሽ ገንዘብ እቤትህ ደብቀህ የመጣህ . . .” አላለም። የኛዎቹ የ’መገለጥ’ አገልጋዮች ርችት አርከፍካፊዎች እየሆኑ አንድ ሰው ለመጠቆም ሲሉ ጉባኤውን የሚያንገላቱ መሆናቸውን መረዳት ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። የአሁኖቹ ስም መጥራት ሲጀምሩም ይህ የጅምላ ተኩስ ‘የመገለጥ አገልጋዮቻችን’ ዋና መታወቂያ ነው።ሦስተኛው ግቡ ነው። በዚህ በነሐናንያ ሥራ ውስጥ የሰይጣን እጅ አለበት፤ መንፈስ ቅዱስን የመዋሸት ነገር አለበት፤ በእግዚአብሔር ላይ የተቃጣና የተሰነዘረ መሳሪያ አለ። ገና የተወለደች ጨቅላ ቤተ ክርስቲያን ከክፉ ንዋያዊ እርሾ መጠበቅ አለባት። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ስር ሳይሰድድ መቀጨት ነበረበት። ይህን መሳይ የወቀሳ፥ የተግሳጽ፥ ኃጢአትን የመንቀስ፥ ትምህርት ከመድረክ አይሰማም። ከላይ እንደተባለው በነቢያቱ ኃይል ኃጢአት ተሸንፎ ወይም ዘማሪው እንዳለው ሰይጣን ከአገር ተባርሮ ስለሆነ ይሆን?አራተኛ፥ ዓላማው ነው። ምን ነበር? ሐዋ. 5፥11 እንደሚለን፥ በቤተ ክርስቲያን ሁሉናይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።በቤተ ክርስቲያንም፥ ከቤተ ክርስቲያን ባሻገርም ፍርሃት። እንዲያው ድንጋጤ አይደለም። አክብሮት ያለበት ፍርሃት ነው። አከታትዬ ካየኋቸው የዚህ ሰውና ሌሎችም በርካታ የዘንድሮ ‘ነቢያት’ ግርግሮች ውስጥ በሰሙት ሁሉ ላይ ፍርሃትን የሚፈጥር ነገር አላየሁም። በሰሙት ሁሉ ላይ የሚለው ቃል ክርስቲያኖችን ብቻ የተመለከተ ሳይሆን ያኔ የማያምኑትን አሕዛብና ሃይማኖተኛ አይሁድንም የጨመረ ቃል ነው። ዛሬስ? ዛሬማ ቤተ ክርስቲያን በዘንድሮ ‘ነቢያት’ ማላገጫ እየሆነች ናት። አክብሮትን የተላበሰ ፍርሃት ቀርቶ በወጉ ደንገጥና ሰግጠጥ ማለት እንኳ ተባርሮ እየጠፋ ነው። ይህን እየጻፍኩ ሳለሁ (በማርች 2015 አጋማሽ) በቤተ ሰብ ጉዳይ ምክንያት ናዝሬት ቆይቶ የተመለሰ ጓደኛዬ፥ ልክ ከሁለት ወር በፊት እዚያ ስለተደረገ የሌላ የአንድ ‘ነቢይ’ ድርጊት አጫወተኝ። ይህኛው ‘ነቢይ’ የሞተና የተቀበረ አንድ ሰውን ጌታችን አልዓዛርን እንዳስነሣው ከሙታን ለማንሣት በመሞከር ከአንድ ጉባኤ ሕዝብ ጋር በተቀበረ በ3ኛው ቀን (3ኛ ቀን! እንደ አልዓዛር 4ኛ ቀን አይደለም) መቃብር አስቆፍሮ፥ ሳጥን አስከፍቶ፥ ሬሳ አስወጥቶ፥ መነሣቱን ለማረጋገጥ ወደ ሆስፒታል አስወሰደ። ‘ከተነሣ ለምን እራሱ ተነሥቶ አልሄደም? ለምን ወደ ሆስፒታል አመጣችሁት?’ ነበር የዶክተሩ ጥያቄ። የፌዝና የምጸት ጥያቄ ነበረ። በመጨረሻ ፖሊስ ተጠርቶና ጣልቃ ገብቶ ኖሮ ሬሳው ከመቃብር ሲወጣና ሳይነሣ ሲቀር አፍረው ተበታትነው ነበርና ያጀቡት ጥቂት አጃቢዎችና ነቢዩ በግዴታ መልሰው እንዲቀብሩት ተደርገዋል። በሌላው አገር ይህ ድርጊት ሬሳ በመረበሽ ወንጀል የሚያስከስስ እና የሚያስቀጣ ነው። ደህና፥ ክሱና ቅጣቱ ቢቀር የክርስትናና የክርስቶስ ስም መጉደፍ እንደምን ዝም ይባላል? አንዴ የሞተ ሰውን ሁለቴ የሚቀብሩ አሳፋሪ ጉዶች! ያሳፍራሉ እንጂ የሚያፍሩ ግን አይመስሉም። ከዚህ በፊትም አንሞትም ይሉ የነበሩ ሰዎች ቤትና አገልግሎት ውስጥ ሞት ገብቶ ሲደነግጡና መሪው ጉዳዩን ሊደብቅ በማለት ሬሳ ሲያሸሽ ስለተያዘበት ጉዳይ ጽፌ ነበር። ምድራዊ ችግርን ብቻ ሳይሆን ሞትንም በጥሎ ማለፍ ተሻግረው፥ ወይም እንደ ኤልያስ ተነጥቀው አክሊል ባቋራጭ ሊቀበሉ የሚቃጣቸውም ከተነሡ ቆይተዋል። የዛሬ 30 ዓመት አዲስ ክርስቲያን ሳለሁ የሥጋ ሞት አንሞትም ከሚሉት መካከል አንዱ ገጥሞኝ ነበር። ይህ ሰው አሁንም አልሞተም፤ ግን በጣሙን እያረጀ ነው። ቶሎ ካልተነጠቀ የባሰ እያረጀ እዚሁ መኖሩን የሚወድደው አይመስለኝም። ዛሬም አንሞትም የሚሉ አዳዲሶች ተነሥተዋል። ከየመድረክ የምንሰማቸው ‘መገለጦች’ በቃሉ ሳይፈተሹም እንኳ ስሜታዊና ግምታዊ መላ ምቶች ካልሆኑ፥ የተሰሉ ልምምዶች መሆናቸው እየተገለጠ የመጣው ቆይቶ ሳይሆን ገና ከጅምሩም ነው። የሚያሳዝነው በስሕተት ነፋስ የሚነዳው አጨብጫቢው መንጋ ነው። አንዳንዱ ውኃ ሲወስድ እንደሚያሳስቀው እየሳቀ ይወሰዳል። በዚህ ዘመን እስከ ሲዖል ደጅም እየሳቁ የሚደርሱ ሰዎች በዝተዋል። አንዳንዱ እያጨበጨበ ወደሚሸለትበት መሸለቻ እየተወሰደ ነው። ቀደም ሲል በጠቀስኩት ‘ነቢይ’ ጉባኤ እየተደመሙ የሚስቁና የሚያጨበጭቡ አጨብጫቢዎች ቤቱን ሞልተው ሲታዩና የተናጋሪው እንቅስቃሴና ሁኔታ የተዋጣለት የመድረክ ተዋናይ ሲያስመስለው ቦታው የሆነ ሰርከስ ወይን ቴያትር ቤት ቦታ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል። ክርስቲያኖች በአጠቃላይ የሚነገረንን፥ የምንሰማውንና፥ የሚሆነውን በቀላሉ የምናምን ሰዎች ነን። መመርመርና መጠየቅ ነውርና እምነት ማጣት ይመስለናል፤ አንዳንዶች መጠየቅና መመርመር እምነት ማጣት ነው ተብሎ ተነግሮአቸው ይህን አምነው ተቀብለዋልና በዘመናቸው ሁሉ ከመድረክ የሚሰጣቸውን ሁሉ እንደ ዶክተር መድኃኒት ምንም ሳይጠይቁ ሲውጡ ይኖራሉ።
[1] ከላይየተጠቀሰው።
የዚህን ጽሁፍ የመጨረሻ ክፍል በመጪው ይዘን እንቀርባለን።
0 comments:
Post a Comment