• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ፤ ወለካልዑ ልደት አመንከሮ፤


       እንኳን ለብርሃነ ልደቱ ወጥምቀቱ አደረሳችሁ፤

                   ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ፤ ወለካልዑ ልደት አመንከሮ፤

                      ቀዳማዊ ልደቱን ረቂቅ፣ ደኃራዊ ልደቱን ድንቅ አደረገው፡፡

    እግዚአብሔር በሰው መካከል ያደረገውንና ለሰው የገለጠውን ነገር ስናስበው አስደናቂና የማይደረስበት ሆኖ እናገኘዋለን፤ ጥንት ሲፈጥረው ጀምሮ ክብርት ዓርአያውን፣ ቅድስት ምሳሌውን ሰጥቶ ሲፈጥረው ከሁሉም የተለየ አድርጎት ነበር፤ የማይሞተው አምላክ ምሳሌውን ሰጥቶ ሕያውና የማይሞት አድርጎ በክብር ቢሠራውም እርሱ ግን ለዚህ የተገባ ሳይሆን ቀረ፤ በክብር ተፈጥሮ በክብር ያልኖረ መሆኑን ስትገልጥ ቅድስት ኦሪት ያለችውን ስሙ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ‹‹በእግዚአብሔር መልክ ፈጠራቸው››በማለት ገናና ክብሩን አንፀባርቃ በቀጣዩ ምዕራፍ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው›› በማለት መሬት ነውና ወደ መሬት የሚመለስ መሆኑን ትናገራለች ዘፍ 1÷27፣ 2÷7፤ ይህ ልማድ ሆኖለት ዛሬም ሰው በእናቱ ማኅፀን ሲፈጠር ‹‹ንግበር ሰብዓ በዓርአያነ ወበአምሳሊነ›› ዘፍ1÷26፤ ኃጢአት ሲሠራ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈርነት ትመለሳለህ›› ዘፍ3÷19፤ እንደገና በንስሐ ቢመለስ ደግሞ ‹‹አዳም ከእኛ እንዳንዱ ሆነ››ዘፍ 3÷22 የሚለው መጽሐፋዊ ቃል ኪዳን ሲፈፀምለት ይኖራል፡፡

    በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ሲያልፍ እግዚአብሔርን መምሰሉ በኃጢአት ምክንያት ጠፍቶበት ነበርና እግዚአብሔር እርሱን መስሎ ወደ ዓለም መጣ፤ ለሰው ሁለተኛ መወለድን ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ሁለተኛ በሥጋ ተወለደ፤ የመጀመሪያው ልደቱ ከላይ እንደተናገርነው ረቂቅ ሲሆን ሁለተኛ ልደቱ ደግሞ ድንቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ እናት ከአባት ብቻ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ መገኘት እንደምን ያለ ረቂቅ ነገር ነው! በዚያውም ላይ አባቱ ሳይቅድመው አባቱ ሳይበልጠው የሚገኝ ልጅ እንደምን ያለነው! ከአባቱ ወደ ኋላ ቀርቶ የታጣበት ጊዜ የሌለ፣ አባቱም ያለ ልጁ የነበረበት ጊዜ ተፈልጎ የማይገኝ ከእውነተኛ ብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን ነው፡፡

    ነገር ግን ይህ ልደት ረቂቅ ከመሆኑ የተነሣ ከፍጡራን አዕምሮ በላይ ነውና ለዚህ ልደት መገለጫ የሚሆነውን ሁለተኛውን ልደት በሰው መካከል አደረገው፡፡ ቀዳማዊው ልደት ከፍጥረት አስቀድሞ የተደረገ ሲሆን ደኃራዊው ልደት ግን ፍጥረት የቀደመው ኋለኛ ልደት ነው፡፡ እንዲህ ግን ስላልን በኋለኛው ልደቱ ምክንያት ቀዳማዊው ደኃራዊ፣ ደኃራዊው ደግሞ ፊተኛ መሆኑ የታመነ ነው፡፡ የመጀመሪያውና የማናውቀው የነበረው መለኮታዊው ልደት ከአብ ተገኝቶ በሥላሴ ዘንድ ብቻ ታውቆ ሲኖር ለፍጥረት የተገለጠው በዚህኛው ልደት በመሆኑ አፈ ወርቅ ዮሐንስ እንዳስተማረን ‹‹ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ ልደት፤ የመጀመሪያው ልደት በኋለኛው ልደት ታወቀ›› ብለን እናስተምራለን፡፡

    ያኛው ልደት ረቆብን እንኖር ነበር ይሄኛው ልደት ደግሞ አስደነቀን፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የልደትን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ ‹‹ለዝንቱ ሶበ እዜከሮ ብዙኃ ጊዜያተ አነክር እምኔሁ ወእዴመም፤ ይህን ነገር መላልሼ ባሰብኩት ጊዜ እጅግ አደነቃለሁ›› ሃይ አበ 63÷7 በማለት መንፈስ ቅዱስን ምስክር አድርጎ መገረሙን ይገልጥልናል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ የሁላችን አባት አዳም ከመሬት ባልተለመደ የፍጥረት ሕግ በመገኘቱ፣ አዳምም ሔዋንን ከጎኑ ብቻውን ያለሴት በማስገኘቱ አስደናቂ ልደት ብለን መዝግበነው እንኖር ነበር፤ ይህ ግን ከዚያ በላይ ነው፤ ሰማይና ምድር የማይወስኑት አማላክ እንደምን ሦስት ክንድ ከስንዝር በሆነች ታናሽ ብላቴና ማኅፀን ተወሰነ፤ ከሁሉ በፊት የተገኘ የእርሱን ነገር ስንናገር ዘመናት ቀደሙት ማለታችን ከዘመናት በኋላ የተገኘ ደኃራዊ ሥጋንስ ቅድመ ዓለም ከነበ ረ መለኮት ጋር በመዋሐዱ ቅ.ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው እንደተናገረው ‹‹እምቀድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ሀሎ ….››ብለን ማመስገናችን እንደምን አያስደንቅ፤

    ለሰው ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ የእኛ የሆነውን ሁሉ ለእርሱ አድርጎ የእርሱ የሆነውን ሁሉ ለእኛ ሰጥቶናል በዚህም ቀድሞ ሲፈጥረን ከሰጠን ስጦታ ይልቅ ዛሬ በሐዲስ ኪዳን የሰጠን ስጦታ እጅግ ይበልጣል ነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ ስለዚህ በተናገረበት ድርሳኑ ‹‹ቀዳሚሰ ወሀበነ አርዓያሁ ክብርተ ወደኃሪሰ ነሥአ ሥጋነ ኅስርተ፤ በመጀመሪያው ተፈጥሯችን ክብርት አርያውን ሰጥቶ ፈጠረን በኋላ ግን በኃጢአት የተበላሸ ባሕርያችንን ገንዘብ አደረገ›› በማለት ከቀደመው ይልቅ ያሁኑ ፍቅር እንደ ሚበልጥ ይናገረናል፡፡ ታላቁን ለመምሰል ሁሉም ይፈልጋል ታናሹን ለመምሰል ማን ያስባል፤ ጌትነትን የሚሻ ሰው አይታጣም ባርነትን ግን ማን ይወዳል?እግዚአብሔርነትን ማን ይጠላል ሰው መሆንን ግን የሚወድ የለም፤ ለመታመም፣ ለመሞት፣ ለመራብ፣ ለመለመን፣ በመቃብር ለማደር ወስኖኮ ነው ሥጋን መልበስ የሚቻለው፤ እግዚአብሔር ያደረገው ደግሞ ይህንኑ ነው፤ ታላቅነቱን በታናሽነት፣ ጌትነቱን በባርነት፣ ኃያልነቱን በደካማነት ሰውሮ የጠፋውን በግ ፍለጋ በትህትና ወደ እኛ መጣ ፡፡

    ምሥጢር የነበረው የመለኮት ልደት በሥጋ ልደት ሲገለጥ የሚደነቅ እንጅ የማይመረመር ነገርን ይዞ ብቅ አለ፤ በቀዳማዊ ልደቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ሆኖ ያለና የነበረ ቀዳማዊ ቃል አሁን በሥጋ በተወለደው ሁለተኛ ልደቱ ከእኛ ጋር ተካከለ፤ በሰማዩ አምላክ ዘንድ ‹‹አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ፤ አዳም ከእኛ እንዳንዱ ሆነ›› ተብሎ ሲነገር በእኛ በመሬታውያኑ ዘንድ ደግሞ ‹‹ወኮነ ሰብዐ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት፤ ከኃጢአት በቀር እንደኛ ፍጹም ሰው ሆነ›› ተብሎ ተዘመረ፡፡ ቅ.ቄርሎስ ስለዚህ ነገር ‹‹ውዕቱ ዕሩይ ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ በመለኮቱ ወዕሩይ ምስሌነ ውዕቱ ዝንቱ አሐዱ ምስሌነ በትስብዕት፤ እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮቱ ትክክል ነው ይህ አንዱ ሰው በመሆን ከእኛ ጋር ትክክል ነው›› በማለት አድንቆ ይናገራል፡፡ ከመላእክት አንዱን አንኳን ሊልክለት የማይገባው ሆኖ ሳለ ሰውን እንዲህ አድርጎ ረዳው፡፡ ሲረዳውም ርቆ መከራውን በረድኤት ያስወገደለት አይደለም፤ ለመከራው መነሻ የሆነውን ሥጋ ለብሶ ለባሕርዩ ቅርብ ሆኖ ነው እንጅ፤ አፈወርቅ የሐንስ የቅዱስ ጳውሎስን መልዕክት በተረጎመበት ድርሳኑ ‹‹ውዕቱ ይረድኦሙ በጻሕቅ ዐቢይ በመከራሆሙ እስመ በሕማሙ አእመረ ምንዳቤሁ ለሕማም፤ መከራን በመቀበሉ የመከራን መጥፊያ መጥፊያውን አውቋልና በመከራቸው ሁሉ ይረዳቸዋል›› ዕብ 1÷18 ይላል፡፡ መከራውን ሊያስወግድ ያሰበበት መንገድ መከራን የሚቀበል ሥጋን በመልበስ መሆኑ አስገርሞት ነው እንዲህ የሚለው፤ እኛ የምናስበው ኃይለኛውን አስሮ ቤቱን ለመበርበር ኃይለኛ ሆኖ የሰማይ ሰራዊትን አስከትቶ ይመጣል ብለን ነበር እርሱ ግን ደክሞ አበረታን፡፡ ማቴ 12÷29፣ ማር 3÷27

    በእርግጥ ኃይለኛው ደካማውንማ ቢያሸንፈው ምን ይገርማል1 ደካማው ኃይለኛውን ቢያሸንፈው ነው እንጅ ዘመን የማይሽረው መደነቅን የሚፈጥረው፤ እስካሁን እየተደንቅን ያለነው እኮ ዳዊት ጎልያድን ስላሸነፈው፣ 1ሳሙ 17÷50፣በሴቶቹ በዲቦራና በዮዲት ሲሣራና ሆለሆርኒስ መሳ 4÷4፣ ዮዲ 13÷9 ስለተሸነፉ እንጅ ነገሩ ቢገለበጥ ኖሮ ባልደነቀንም ነበር፤ ጌታችንም በመለኮታዊ ክብሩ ሳይሆን በሥጋ ተገልጦ ባደረገው ሰውን የማዳን ሥራ ስንደነቅ የምንኖረው ከዚህ መገለጥ የተነሣ ነው፡፡

    ሰውን እንዲህ አድርጎ ልክና መጠን በሌለው ፍቅር ይወደው ዘንድ እግዚአብሔርን ምን አተጋው፤ መንፀፈ ደይን ለወደቀው ሰው ቤዛ ይሆን ዘንድ የብርሃን ማደሪያ ያለው እርሱ በከብቶች በረት ተጣለ እርሱ በክብር በተገለጠ ጊዜ የሲና ተራራ ክብሩን መሸከም አልችል ብላ ተጨነቀች ስለእርሷ የተባለው እንዲህ ነው‹‹እግዚአብሔርም በእሳት ስለወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር›› ዘጸ 19÷18ተብሎ ነው የተጻፈው፡፡

    ቢሆንም ግን በደብረ ሲና ጢሱን አየን እንጅ መልኩን አላየንም፤ ደነገጥን እንጅ ቀርበን አላመሰገንንም፤ እንዲያውም ‹‹ውረድና ለሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከነርሱ ብዙዎችም እንዳይጠፉ ንገራቸው›› ዘጸ19÷21፣24 ተብለን በፊቱ መቆምን ተከልክለን ነበር አሁን ግን እንዲህ አይደለም፤ በመላዕክቱ ስብከት ተጠርተን እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሂደን በፊቱ ‹‹ ስብሐት ለእግዚአብሔር…………›› ሉቃ 2÷10 ልንል ተገብቶናል፡፡ እውነት ነው! ይህ ነገር እኛ በፊቱ እንድንቆም ድፍረትን የሰጠን ቢሆንም ለአጋንንትና ለአይሁድ፣ ለመናፍቃን ግን አስደንጋጭ ዜና ነበር፤ ቅዱስ ኤፍሬም በሃይማኖተ አበው ‹‹ እምደብረ ሲና ወጽአ ድንጋጼ ወሀውክ ላዕለ አይሁድ ወእምኔኪሰ ኮነ ድንጋጼ ላዕለ ሔሮድስ ወዲያብሎስ ወአጋንንቲሁ፤ ከደብረ ሲና በአይሁድ ላይ ድንጋጼ ሀውክ ተደረገ በአንችም በአይሁድ፣ በሔሮድስ፣ በዲያብሎስና በሰራዊቱ ላይ ድንጋጼ ተደረገ›› ብሎ ያደንቃል፡፡

    መሰወሪያውን ጨለማ አድርጎ የሚኖረው ጌታ እንደ ቀድሞው በድንግዝግዝ ያይደለ በግልጥ በመካከላችን ሆኖ፣ በጨርቅ ተጠቅሎ፣ በኤፍራታ ተጥሎ ብናየው መዝ 131÷6 ገረመንና እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‹‹ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ ወለካልዑ ልደት አመንከሮ፤ ቀዳማዊ ልደቱን ረቂቅ፣ ደኃራዊ ልደቱን ድንቅ አደረገው›› እንላለን፡፡ ደብረ ሲናን ያንቀጠቀጠ ግርማው፣ ሕዝቡን በነጋሪት ድምፅ የገሠፀ ቁጣው ዛሬ እንዴት በሥጋ ተሸፈነ፤(ተገለጠ) ቤተ ልሔም እንደምን አልተንቀጠቀጠች፤ ቀርበው ያሟሟቁት አድግና ላህም ፣የሰገዱለት ሰብዓ ሰገል እንደምን አልተገሠፁ፤ መንክር ልደት፡፡

    እግዚአብሔርን ለሰው ፣ሰውን ለእግዚአብሔር የገለጠ ልደት በመሆኑ ወቅቱንም ዘመነ አስተርዕዮ(ኢጲፋንያ) እንለዋለን የመታየት የመገለጥ ዘመን ማለታችን ነው፡፡ የእኛን ብናይ በኃጢአት ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት የሚታይ መልክና ዉበት አልነበረንም፤ ኃጢአት ዕርቃኑን ላቆመው ሰው መሸሸግ እንጅ መታየት እንዴት ያምረዋል፤ በእግዚአብሔርም በኩል ብናይ ለመላእክት እንኳን ታይቶ የማያውቅ ጌታ ነው በእኛ ዘንድ የታየው፤ የሰው ዐይኖች ፀሐይን እንኳን ማየት እንደምን ይቻላቸዋል፤ ከፀሐይ ይልቅ እግዚአብሔር የሚያበራ እሳት ነው ዐይኖቻችን ሊያርፉበት የማይቻላቸው የሚንቦገቦግ ፀዳል ከፊቱ ይወጣል፤ ቅ.ኤፍሬም በውዳሴው ‹‹ንዑ ርዕዩ ዘንተ መንክረ…….ወዘ ኢይትረአይ ተርእየ፤ይህን ድንቅ ምሥጢር ኑ እዩ………የማይታየው ታይቷልና›› እያለ ይጣራል፡፡

    ጌታ የተወለደባት ቤተ ልሔም ያደገባትም ናዝሬት በሕዝቡ ዘንድ ምንኛ የተናቁ እንደነበሩ አታስታውሷቸውም፤ ቤተ ልሔምን የእግዚአብሔር መጽሐፍ ‹‹አንቺ ቤተ ልሔም በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ›› ሚክ 5÷2 ይላታል፤ ናዝሬትም እንኳን ክርስቶስ ደግ ሰው ይወጣባታል ተብላ እማትጠረጠር መንደር ናት ዮሐ 1÷47በነዚህ መንደሮች ተወልዶ ማደጉኮ ያለ ምክንያት አይደለም፤ ሕዝብ በረሳቸው በነዚህ አንጻር በኃጢአት የተረሳ ሰው በጽድቅ የሚታሰብበት ዘመን እንደደረሰ ለማስረዳት ነው እንጅ፡፡ እነዚያ ባለ ብዙ ሰራዊት ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርቡባታል፣ መላእክት ደጅ ይጠኑባታል፣ እረኖች ይዘምሩባታል ብሎ ቤተ ልሔምን ማን አሰባት፤ ናዝሬትንስ ‹‹በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይችላልን?›› ብለው ይሳለቁባታል እንጅ ‹‹ናዝሬት እምገሊላ ትንዕስ አፀደ ወበጸጋ ትትሌዓል ፈድፋደ፤ ናዝሬት በቦታነቷ ከሁሉም ታንሳለች በጸጋ ግን ከሁሉም ትበልጣለች›› ብሎ የሚዘምርላት የለም፤ በልደቱ ዳግም ወለደን፣ በመገለጡ ክብራችንን ገለጠው፤ ስለክብራችን የሚሰብኩ የኮከብና የመላክ ሐዋርያን አስነሣልን ማቴ 2÷2፣ ሉቃ 2÷9

    የተወደዳችሁ የልዑሉ አምላክ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ሆይ! ሁለተኛውን ልደቱን ለሁለተኛው ልደታችን ምልክት እንዳደረግነው ሁሉ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ትንሣኤም ሙታን ከመቃብር ለሚያደርጉት ለኋለኛው ልደት ምልክት ነውና ትንሣኤያችን እንደ ትንሣኤው በብርሃን የተከበበ የክብር ትንሣኤ እንዲሆን ልንተጋ ይገባናል፤ ቤተ ክርስቲያንን ተስፋ የምታደርገው ያልተፈጸመላት ተስፋዋ ይህ ነውና ለዚህ ተስፋ የተጋን ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ምድር መኖራችን ለሚመጣው ሕይወት ለመዘጋጀት ነውና ከዚህ ዓላማችን ፈቀቅ የሚያደርጉንን ጠብና ክርክርን፣ ራስ ወዳድነትን ቁጣንና እንደዚህ ያሉ እግዚአብሔር የሚጠላብን ክፉ ነገሮችን ሁሉ አስወግደን ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር መኖርን የዘወትር ተግባር ልናደርግ ይገባናል፡፡

    ‹‹ጸግዋ ሰላመ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ፤ አቤቱ ለሀገራችን ሰላምን ስጣት››

    በድጋሜ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ፣ ጥምቀቱ አደረሳችሁ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ፤ ወለካልዑ ልደት አመንከሮ፤ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top