• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 8 November 2015

    ነቢዩ ዘካርያስ

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

    “ዘካርያስ” ማለት “ዝኩር፣ ዝክረ እግዚአብሔር - እግዚአብሔር ያስታውሳል” ማለት ነው፡፡ ይኸውም በምርኮ የነበሩትን አይሁድ እግዚአብሔር እንዳሰባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በምስጢራዊ መልኩ ግን እግዚአብሔር ኹል ጊዜ በእኛ ውስጥ ያለችውን ቤተ መቅደስ (ነፍሳችንን) እንድናንፃት እንደሚያሳስበን፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎአችን ኹሉ እንደሚረዳን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚህ ስም የተጠሩ ከ፴ በላይ ሰዎች አሉ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ በፄዋዌ አገር በባቢሎን የተወለደ ሲኾን አባቱ በራክዩ በባቢሎን ስለሞተ ከአያቱ ሐዶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶአል፡፡ በመኾኑም እርሱና አያቱ በዘሩባቤል መሪነት ከመዠመሪያዎቹ ተመላሾች ጋር ከምርኮ ተመልሰዋል /ነህ.፲፪፡፩፣፬፣፯/፡፡ ትንቢቱንም የዠመረው በ፭፻፳ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡ ከነቢዩ ሐጌ ጋር ማለት ነው፡፡

    ዘካርያስ የገዥው ዘሩባቤል፣ የነቢዩ ሐጌና የሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ወልደ ዮሴዴቅ የዘመን ጓደኛ ነው /ዘካ.፫፡፩፣ ፬፡፮፣ ፮፡፲፩/፡፡ እንደ አይሁድ ትውፊት ነቢዩ ዘካርያስ የነቢዩ ሐጌ የቅርብ ጓደኛ ሲኾን መቃብራቸውም ጐን ለጐን ነው፡፡

    በነቢዩ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
    በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ አንድ አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ አዋጁም አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የሚፈቅድ ነበር /ዕዝራ ፩፡፩-፲፩/፡፡ ነገር ግን አይሁዳውያኑ፥ በባዕድ አገር ኼደው ለመኖር የተገደዱ ስደተኞች እንደመኾናቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር በጣም ይለፉ ነበር፤ ብዙ ሀብት ንብረትም አፍርተው ነበር፡፡ በመኾኑም ብዙዎቹ በጠላት ተወርራ ባዶ ወደ ኾነችው አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የተመለሱት ወደ ፶ ሺሕ የሚጠጉ ብቻ ናቸው፡፡ እነዚኽ የተመለሱትም በ፭፻፴፮ ቅ.ል.ክ. ላይ የቤተ መቅደሱን ሥራ ዠምረዋል /ዕዝ.፫፡፲፩-፲፫/፡፡ ነገር ግን ወደ አገራቸው ሲገቡ አገራቸው ባድማ ኾና ስለነበር፣ የዘር ፍሬ በአገሩ ስላልነበረ፣ እንዲኹም ሳምራውያን ስለተቃወሟቸው /ዕዝ.፬/ የቤተ መቅደሱን ሥራ ለ፲፭ ዓመት አቆሙት፡፡ በ፭፻፳፩ ቅ.ል.ክ. ላይ ግን እግዚአብሔር ነቢዩ ሐጌንና ነቢዩ ዘካርያስን ልኮ የተዠመረውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠናቅቁት አሳሰባቸው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ይኽ ዓመት ዳርዮስ ወደ ንግሥና የመጣበት የቤተ መቅደሱም ሥራ እንዲጠናቀቅ ያዘዘበት ነው፡፡ በዙርያ የነበሩት የፋርስ ነገሥታት ይኽን ቢቃወሙም ዳርዮስ ይኽን እንዲተዉ አዝዟል /ዕዝ.፮፡፮-፲፪/፡፡
    ከአፍአዊው ተግዳሮት በተጨማሪ ውሳጣዊ የኾነ ፈተናም ነበር፤ ቤተ መቅደሱ እንዳይሠራ፡፡ ይኸውም የቤተ መቅደሱ ሥራ ለ፲፭ ዓመታት ስላቆመ በሕዝቡ ዘንድ “እግዚአብሔር ባይፈቅድ ነው” የሚል ስሜት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ግን ሕዝቡ የራሳቸውን ቤት ለመሸላለም ያመጡት ምክንያት እንጂ ትክክል አለመኾኑ እግዚአብሔር በነቢያቱ አድሮ ነግሯቸዋል /ሐጌ.፩፡፬/፡፡

    ትንቢተ ዘካርያስ

    ትንቢተ ዘካርያስ ከደቂቀ ነቢያት መጻሕፍት ትልቁ ነው፤ ባለ ዐሥራ አራት ምዕራፍ፡፡ በውስጡም በጣም ብዙ ኅብረ አምሳሎችን የያዘ ሲኾን በአጠቃላይ ሊመጣ ካለው የመሲሑ ዘመን ጋር የተሰናሰለ ነው፡፡ አንባብያን ይኽን ማመሳከር እንዲችሉ ለናሙና ያኽል በእያንዳንዱ ምዕራፍ የተጠቀሰውን ኅብረ አምሳል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

    1. ምዕራፍ አንድ ላይ ዲያብሎስ እኛን ለመጣል ተነሣስቶ እንደነበርና ጌታችን ግን እኛን ለመርዳት የጠላትን ቀንድ ለመጣል እንደሚመጣ ይገልጣል፡፡

    2. ምዕራፍ ኹለት ላይ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጽዮን መጥቶ አማኑኤል እንደሚባልና በመሞቱም ለሕዝብና አሕዛብ መጠጊያ እንደሚኾን ተጽፏል፡፡

    3. በምዕራፍ ሦስት ላይ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንዲኹም ወደዚኽ ምድር መጥቶ የሰዎችን ኃጢአት እንዴት እንደሚያስወግድ ተተንብዮአል፡፡

    4. ምዕራፍ አራት ላይ ስለ ሐሳዊ መሲሕና ስለ ጌታችን ተነግሯል፡፡

    5. ምዕራፍ አምስት ላይ በዳግም ምጽአት ላይ ሊኾን ያለው ፍርድ ምን እንደሚመስል በግልጥ ያሳያል፡፡

    6. ምዕራፍ ስድስት ላይ “የእግዚአብሔር ቊጥቋጥ” የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ስላለው አኳኃኑን ያስረዳል፡፡

    7. ምዕራፍ ሰባት ላይ እግዚአብሔር (አይሁዳውያኑን) ሲጠራቸው እንዳልሰሙ ኹሉ እነርሱም ሲጠሩት እንደማይሰማቸውና በሮማውያን እጅ እንደሚበትናቸው አገራቸውም ባድማ ኾና እንደምትቀር ይገልጣል፡፡

    8. ምዕራፍ ስምንት ላይ ስለ መንፈሳዊቷ ኢየሩሳሌም ይናገራል፡፡

    9. ምዕራፍ ዘጠኝ ላይ በግልጥ ስለ ሆሣዕና ይናገራል፡፡

    10. ምዕራፍ አሥር ላይ ምእመናን በክርስቶስ ኢየሱስ ኃይል ኹሉንም ነገር ድል እንደሚያደርጉ ይገልጣል፡፡

    11. ምዕራፍ አሥራ አንድ ላይ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ብር ሚዛን እንደሚሸጥ በግልጥ ይተነብያል፡፡

    12. ምዕራፍ አሥራ ኹለት ላይ ክርስቶስን ከማመን የራቁ አይሁድ እንደምን ያለ መከራ እንደሚደርስባቸው ያስረዳል፡፡

    13. ምዕራፍ አሥራ ሦስት ላይ ግልጽ በኾነ አነጋገር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚደርስበት ጸዋትወ መከራ ይናገራል፡፡

    14. ምዕራፍ አሥራ አራት ላይ ደግሞ በስቅለት ጊዜ ስለሚኾነው ክስተት እንዲኹም በዚያ አንጻር ስለ ዳግም ምጽአት ይናገራል፡፡
    ከዚኽም የተነሣ ትንቢተ ዘካርያስ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በጣም ተደጋግሞ እንዲነሣ (እንዲጠቀስ) ምክንያት ኾኗል፡፡ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
    1. የንስሐ ጥሪ /፩፡፩-፮/፤
    2. ንጉሠ ሰማይ ወምድር የኾነ እግዚአብሔር ጽዮንን ለመሥራትና ለማንጻት ያለው ሐሳብ /፩፡፯-፮፡፲፭/፤
    3. በኢየሩሳሌም መፍረስ ጊዜ የተደነገጉ የፆም ቀናት ተለውጠው የደስታ በዓላት እንዲኾኑ የተሰጠ ትእዛዝ /፯-፰/፤
    4. እግዚአብሔር ለመፍረድም ኾነ ለማዳን ታላቅና ቅን ስለመኾኑ /፱/፤
    5. ስለማይረቡና ስለ መልካሙ እረኛ /፲-፲፫/፤
    6. እግዚአብሔር በምድር ኹሉ ላይ ስለመንገሡ /፲፬/፡፡

    እኛስ ከትንቢተ ዘካርያስ ምን እንማራለን?

    © መጽሐፉን በጥንቃቄ የሚያነብ ሰው እግዚአብሔር በምርኮ (በዲያብሎስ) ለምትፈተን ነፍስ ረዳቷ እንደኾነ ይገነዘባል፡፡ በየትኛውም ዓይነት ፈተና ውስጥ ብንኾንም እግዚአብሔር አይረሳንም፡፡ እኛ እስካልረሳነው ድረስ እግዚአብሔር ፈጽሞ አይተወንም፡፡ አንድ ቀን እንደምንመለስ በማሰብም ይጠብቀናል፡፡ ከተጠቀምንበትም የመውጫውን ቀዳዳ ያሳየናል፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ … እኔም ወደ እናንተ እመለሳለኹ” ሲልም ይኽን ድንቅ ፍቅሩ የሚያስገነዝብ ነው /፩፡፫/፡፡

    © እግዚአብሔር በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል /፩፡፲፮/፡፡ ከእኛ ጋር ለመታረቅ ባለጠጋ ሲኾን ስለኛ ድኻ ኾኗል፡፡ ንጉሥ ሲኾን ስለ እኛ አርአያ ገብርን ነሥቶ መጥቷል፡፡ በእኛ ዘንድ የነበረው ግማት ተወግዶ መዓዛ መለኮቱን ያድለን ዘንድ በቊጣ ሳይኾን በምሕረት ጐብኝቶናል፡፡ ዛሬ ዕርቅን የማንወድ ከኾነ ግን ዕርቁ ለእኛ አልሠራም፡፡ ድኾች ወገኖቻችንን የማንጠይቅ ከኾነ ግን ባለጠግነቱ ለእኛ አልደረሰም፡፡ ዝቅ ማለትን በእኛ ዘንድ ቦታ ከሌላት ንጉሥ ክርስቶስ ወደ ቤታችን አልገባም፡፡ ከኃጢአት ካልራቅን አኹንም ከነግማታችን ነን፡፡ በምሕረት ወደ እኛ ቢመለስም ለዚኽ ያልተገባን ኾነን ተገኝተናልና ቤታችን ገና አልተሠራም፡፡

    © ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን ገና የክርስቶስ ማደርያ ካልኾነ “አማኑኤል - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” አልኾነም፤ መንፈስ ቅደስ አጥር ቅጥራችን አልኾነም /፪፡፭፣ ፲/፡፡

    © ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው መውደቅ አዳማዊነት ነው፤ መነሣት ግን ክርስቶሳዊነት ነው፡፡ እናም ወድቀን የማንቀር ከኾነ ግን ንጉሥ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ወደ ቤታችን ይገባል /፮፡፲፪/፡፡ ምንም እንደ አህያ (ወራዳ) ብንኾንም በእኛ ላይ ነግሦ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” ተብሎ ለመመስገን አይጠየፈንም /፱፡፱/፡፡
    ዘወትር ለማይጠየፈን፣ ከነ ኃጢአታችን ለሚወደን፣ ዘወትር በፍቅር ለሚጠራን ወዳጃችን፣ እድፋሙን ልብስ (ኃጢአታችንን) ተሸክሞ ወደ መስቀል ለወጣው ለታላቁ ሊቀ ካህናችን /፫/፣ በማይተመን ዋጋ እኛን ለመግዛት በሠላሳ ብር ለተሸጠው ቤዛችን /፲፩፡፪/፣ በቊስላችን ላይ ዘይት ያፈስልን ዘንድ ጐኑን በጦር ለተወጋው አፍቃሪያችን /፲፪፡፲/፣ በፈቃዳችን በጠፋን ጊዜ በምሕረቱ ላሰበን አምላካችን ኃይል፣ ክብርና ምስጋና ለዘለዓለሙ ይኹን አሜን!!!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነቢዩ ዘካርያስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top