• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 10 November 2015

    ዘመነ ጽጌ - ክፍል አንድ


    [ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6]

    "ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"   (ት.ሆሴዕ 11፥1 )

    ከመምህር ዮሐንስ  ለማ

    እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ሕግና ስርአትመሰረት ከመስከረም 26 ቀን  እስከ ሕዳር 6 ቀን   ያለው 40 ቀን   የእመቤታችንን እና የልጇን ስደት በማሰብ ወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ ይህ 40ው ቀን የእመቤታችንና የጌታችን ስደት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ  እመቤታችን  በአበባ ጌታችን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን  በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋናይመሰገናሉ ፡፡

     በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው  ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምሥቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስበ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን  ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር  የነበረው አባ ጽጌ ድንግል  ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡  ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሄድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ሲሆን  ይህድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ወቅት ተለይቶለት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን   በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በልጇ የስደት ዘመን ማለትም  ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው  ዘመን ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊቱን በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋርወደ  ምድረ ግብፅመሰደድና መንከራተት እየታሰበ በሊቃውንቱ  የሚደርስ የምሥጋና ጸሎትም  ነው ፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ  ሲሆንበአብዛኛው አምስት ስንኞች ሲኖሩት ብዛቱም 158 ያክል ነው፡፡ እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው  ሁሉ ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረውለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት  እንዲደርስ ምስጢርን ገልጻለታልች ።

     በቅድስት ሐገር ሐገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት ወርኅ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ) ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮችበአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘’ ስለ ልብስ ስለምንትጨነቃላችሁ ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳበክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡እግዚአብሔር፣ ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማይልቁን እንዴት፡፡ እንግዲህ ምን እንበላለን፣ ምንስእንጠጣለን፣ ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ‘’ (ማቴ 5÷28-33) በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገርእንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮየሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡

    የሊቁ  ድርሰትም ፍሬ ከአበባ÷ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘ ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬእየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባሲ መስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል  ልጇን ደግሞ በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እምጕንዱ - ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩምቁጥቋጦ ያፈራል “(ኢሳ . 11÷1) ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ፣ ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬበመመሰል፣ ከዚያው በማያያዝ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር፣ በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታአዋሕዶ ደርሶታል፡፡

    ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እመቤታችንን በአበባ እየመሰለ ከተናገረው   ድርሰቱ መሐከል አንዱ 
    “ ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘዘመነ ጽጌ እንግዳ 
    ወዘመነ ፍሬ  ጽጋብ  ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ 
    ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ
    ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁ ለይሁዳ 
    ፀቃውዐ   መዓር  ቅድው ( ጥዑም ) ወሀሊብ ፀዓዳ” 

     በመከር ጊዜ አበባ፣ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡ የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ፣የኤልዳ ነቢይ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭማርና ፀዐዳ ወተት ይፈሳል ብሎ የተናገረው ትንቢትበአንቺ ታወቀ፣ ተፈጸመ ፡፡ እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትምነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉትሐዋርያት መሆናቸውን ‘’አንዱ ይዘራል አንዱምያጭዳል ‘’ የሚለው ቃል እውነት ሆኗል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ በማለት ተናግሮአል (ዮሐ.4÷37-38)፡፡ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ ለፍሬ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነም ‘’ማዕረረ ትንቢት ‘’ የትንቢት መካተቻ ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ  ድንግል ማርያም በአበባ ትመሰላለች፡፡

    ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ  ‘’ወዘመነጽጌ እንግዳ ‘’  እንግዳ የሆነ አበባአላት፡፡ ከዚህ በኋላ ‘’ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውጋሪሁ ለይሁዳ፣ ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊበ ፀዓዳ ‘’ በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውንትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኅብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጐበኛቸውና ረሃቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ ‘’ብዙ መብል ትበላላችሁ ትጠግቡማላችሁ፣ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፣ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ÷ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ÷ በይሁዳም ያሉት ፏፏቴዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ ‘’ (ኢዩ 3÷18፣ 2÷26) ።

    በዚህ በወርኃ ጽጌ ( በዘመነ ጽጌ )   የሚጾሙክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾመ ጽጌ መንፈሳውያን ሰዎች ሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ወይም የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖና ከታዘዙትከ7ቱ አጽዋማት ውጪ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰው የመጾሙን ዋጋያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ ‘’እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል’’ (ሉቃ. 7፡47) የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋር ይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾም የለባቸውም፡፡ የማይጾሙሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ተደርጎ ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡ "ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ"  (ማቴ. 6፥16 ) ። የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ጾም ነው፡፡

    ጽጌ ማለት አበባ ማለት  ሲሆን  ምድሪቱ  በአበባ የምትሞላበት ጊዜ በመሆኑ አበው ሊቃውንትእመቤታችንን በብዙ ኅብር መስለዋታል፡፡ በአበባ /ጽጌ/፣ በወይን ሐረግ፣ መልካሙን የወይን ፍሬ አስገኝታለችና አበባ ፍሬን እንዲያስገኝ ድንግልማርያምም ለሰው ያልተቻለውንና የማይቻለውንአንዴ ብቻ የሆነውን መለኮትን በአጭር ቁመትበጠባብ ደረት በማህፀንዋ ወሰነችው ፡፡   አዳምና ልጆቹ እንዳይበላ በተከለከለችዋ ፍሬ ምክንያት ገነትን ከሚመስል ቦታ እግዚአብሔርን ከሚያክልጌታ ተለዩ የሰው ልጅ ድቀት ተጀመረ ሁሉን አጣ የመጀመሪያ በደል /ጥንተ አብሶ/ ማለት ይህ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የመለየትን ረጅም ግዜንገፋ ገዥ የነበረው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሰለጠነበት፣ጠላት በዛበት፣ ምድሪቱ ከፋችበት አዳምምባለቀሰው መሪር እንባ 5500 ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሐልሁ የሚል ተስፋ ተሰጠው የህይወት ፍሬንም ዳግም እንዳይበላ በሱራፊታጠረችበት፡፡ ይህም የሚያመላክተው ሞትን የምታመጣ ዕፀ በለስን የበላ አዳም ደግሞ ዕፀ ህይወት ቢበላ ኖሮ ካሳ የማያስፈልገው ኢመዋቲ (immortal sinner) እንዳይሆን የእግዚአብሔር ቸርነት ከለከለችው፡፡

    ያ የጨለማ ዘመን ፍጹም ተስፋ ያልጠፋበት ፍጹምም ተስፋ ያልተፈጸመበት ዘመን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ጀምሮ ለአርእስተ አበው ቃልኪዳን ይገባ ነበር፡፡ በዚህም ቃል ኪዳን ውስጥ እመቤታችን በተስፋ አበው ውስጥ ታልፍ ነበረ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓ "ማርያምሰ ተሐቱ ውስተከርሱ ለአዳም ከመ ባህርይ ጸአዳ ፤ ማርያምም በአዳም አብራክ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራ ነበር" በማለት ገልጦአታል፡፡ ነገር ግን የአበው ተስፋ፣የነቢያት ትንቢት ሲፈፀም የድንግል ማርያም የህይወት ፍሬ /በገነት ተከልክላ የነበረችው የገነት ፍሬ/ አማናዊው ጌታ የሚበላ የሕይወት ፍሬ ሆኖ ከእመቤታችን ተወለደ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስውዳሴ ማርያም ሲናገር ‘’ ከፈለነ ንብላዕ እምዕጸሕይወት ዘውዕቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ መጸአ ወአድኅነነ ፤  ዳግመኛከዕፀኅይወት  እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም እኛን ስለመውደድ ሰው ሆኖ ያዳነን የክርስቶስ ክቡርሥጋው  ክቡር ደሙነው ‘’ በማለት እንደገለጸው፡፡ በወርኃ ጽጌ እመቤታችን ጌታን በጀርባዋ አዝላ በረኀ ለበረሃ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የተሰደደችበትን ሙሉ  ታሪክ  በጥልቀት ስንመለከት፡፡

       ከላይ በርእሱ የተጠቀሰውን  ቃል  ( ልጄን ከግብፅ ጠራሁት  ።  ት.ሆሴዕ  . 11፥1  ) የሚለውን  የትንቢት ቃል የተናገረው ከክርሰቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምእተ ዓመት አጋማሽገደማ የነበረው  የብኤሪ ልጅ ነቢዩ ሆሴዕ   ነው ። ሆሴዕ  ማለት   እግዚአብሔር ያድናልማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪኳ ከተዘረዘሩላት ሀገሮች መካከል ግብጽ አንዷ ስትሆን ግብጽ የብዙኀን አባት አብርሃም በረሃብ ምክንያት የተሰደደባት፣ ዮሴፍ በባርነት የተሸጠባት፣ ወገኖቹ እስራኤላውያን ለሁለት መቶ አስራ አምስት ዓመታት ያህል በባርነት የተገዙባት በኋላም የአለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር የተሰደደባት ሀገር ስትሆን መሪዎቿም አህዛብ አማልዕክቷም ጣኦታት ነበሩ፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ የጌታችንን ሥደት ቀድሞ በትንቢት ከተናገሩትውስጥ  አንዱ ሲሆን ልጄን ከግብፅ ጠራሁት በማለት የስደቱን ማብቃት ተናግሯል፡፡ በዚህ ትንቢት መሰረት መሰደዱን አልተነበየም፡፡ ነገር ግንከስደት መመለሱን መናገሩ ካልተሰደደ መመለስየለም በመመለሱ መሰደዱን ተናገረ፡፡

    የጌታን ሕይወት ከእመቤታችን የእመቤታችንንከጌታ ለያይቶ ማየት አይቻልም መለኮታዊ ተግባራትን እና የማዳን ስራዎችን  ካልሆነ በቀር ምክንያቱም ለእርሱ ብቻ የተወሰነና ሊያደርገው የተገባ የአባቱ ተልዕኮ ስለነበረ "ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም አንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁ" (ዮሐ.6፥38 ፣ ዮሐ.5፥30) ። ነቢያት የተነበዩት ጊዜ ደርሶ በነቢዩ በሆሴዕ እንዳለውናመልአኩ ገብርኤል ለዮሴፍ ተገልጦ እንደነገረው አንድ ልጇን ይዛ ወደ ግብጹ ተሰደደች ( ማቴ.2፥13 ) ።

    1.የእመቤታችንና የልጅዋ  ምክንያተ ስደት ወደምድረ ግብጽ

    የእመቤታችን ስደት ብለን ስንናገር ከልጅዋ ጋርመሆኑን አንባቢ ሁሉ ልብ ሊለው የተገባ ሲሆን ስለ የእመቤታችን ስደት ምክንያት አበው ያስተማሩንን፣መጽሐፍት የመዘገቡልንን በጥቂት እንዘረዝራለን፤ትንቢተ ነቢያት እግዚአብሔር ሊያደርግ ያሰበውን ፈቃዱን ሁሉ ለሰው ልጅ እየገለጠ ነቢያትን ትንቢትእያናገረ መምህራንን እየላከ መጽሐፍትን እያጻፈ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ "እግዚአብሔርይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ" እግዚአብሔር ለህዝቡ በመጽሐፍ ይናገራቸዋል መባሉ "በቀንናበሌሊት ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባቸው ነበር፣አዎ ልኬባቸዋለሁ"  ( ኤር.7፥25 ) በማለትገልጧል፡፡ ከነዚህም ትንቢታት መካከል ስለእመቤታችንና ጌታ ስደት ሲሆን፡-  ( ነቢዩ ኢሳይያስ. 19፥1) "ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል ፤ እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረወደ ግብጽ ይመጣል ‘’፡፡  ትንቢተ ስምዖን፡- "ባንቺ ደግሞ ሰይፍ ያልፋል አላት" ( ሉቃ. 2፥34 ) ።ስምዖን በንጉሡ በጥሊሞስ ጊዜ መጻህፍተ /ብሉያትን/ ከጥንቱ ዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ለማስተርጎም ሰባ ሊቃናትን ባዘዘበት ወቅት ስምዖን የኢሳያስ መጽሐፍ ይደርሰዋል፡፡ "እነሆ ድንግልትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንምአማኑኤል ትለዋለች"፡፡ የሚለው ቃል ሲተረጎምቢከብደው እንዴት ድንግል ትጸንሳለች ብዬ ልተርጉም ብሎ ሴት ትወልዳለች በማለት ቢጽፍተኝቶ ሲነሣ የጻፈው ጠፍቶ ድንግል ትጸንሳለችየሚል ተጽፎ ያገኛል፡፡ ይህ መሆኑ ቢገርመውመልአኩ መጥቶ ይህንን ሳታይ አትሞትም ብሎትተሰወረ፡፡ በዚህም የትንቢቱን ፍጻሜ በቤተመቅደስ እጅግ አርጅቶ ሳለ ጠበቀ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችንእንደ አይሁድ የመንጻት ሕግ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተመቅደስ ሲወስዳት ትንቢቱን ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን የጌታን ማዳን አየ "እነሆ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት"  (ሉቃ. 2፥34 ) በማለት ትንቢቱ መፈጸሙን ሲያይ ይህንን ካየሁ ባሪያህን በሰላም አሰናብተው ብሎ ሲለምን ገና ወደፊት የሚሆነውን የእመቤታችንን ስደት በልጇ አማካኝነት ወደፊት የሚደርስባትን መከራ ተነበየ፡፡ "ወለኪሰ ይበውእ ውስተ ነፍስኪ ኩናተ ኑፋቄ" ሰይፍ ያረፈበትን ለሁለት እንደሚከፈልሁሉ የእመቤታችን ልብ ከሐዘን ምሬት የተነሣ እንደምትጎዳ የተነበየው ትንቢት ይፈጸም ዘንድከልጅዋ ጋር ተሰደደች ልብዋን  እንደ ሰይፍየከፈሉትየእመቤታችን አምስቱ ሐዘናት የሚባሉት፤

    አይሁድ እንዲገድሉት በቤተመቅደስ ስምዖንትንቢት በተናገረ ጊዜ  ( ሉቃ.2፥34 ) ።

    እጅና እግሩን አስረው በጲላጦስ አደባባይ በገረፉትጊዜ  ( ዮሐ. 19፥1 ) ።

    ጌታን ከኢየሩሳሌም ለበዓል ሔደው ሲመለሱበመንገድ ባጣችው  ጊዜ  (ሉቃ. 2፥41 ) ።

    በዕለተ ዓርብ ዕራቆቱን ተቸንክሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል በሰቀሉት ጊዜ ( ማቴ.27፥38 ) ።

    ወደ አዲስ መቃብር ውስጥ ባወረዱት ጊዜያዘነችው ሐዘን ( ማቴ.27፥59 ) ።

    አረጋዊው ስምዖን የተናገረው ትንቢት በእመቤታችን የሕይወት ዘመን ሁሉ በልጅዋ ምክንያት ሰይፍየተባለ መከራ አልፎባታል በዚህም ሊቁ አባ ሕርያቆስ የእመቤታችነን ምልጃ ሲጠይቅ "አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኀዘ እም አዕይንትከወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ" ድንግል ሆይበልጅሽ ፊት የወረደውን ከአይንሽ የፈሰሰውን ዕንባ አሳስቢ በማለት ለኛ ለኃጢአተኛ ልጆችዋ የምታማልደን ስለእንባዋ ይቅር እንደሚለን የተናገረው፡፡

    ሀ.ስደተ ቅዱሳንን ለመባረክ  ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደዱ

    የክርስትና ህይወት የመስቀል ላይ ጉዞ በመሆኑ ክርስቶስን አምነው ለተከተሉት ሁሉ በመከራናበስደት እንደሚያልፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስከአለም ተመርጠው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱሲያስተምር "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" በማለትተናገረ ( ማቴ. 16፥24 ) በዚህም ቃል መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ክርስቲያኖች በብዙ መከራ ውስጥ አለፉ በበረሃ ተሰደዱ፣ በዱር በገደሉ ተቅበዘበዙ በሰይፉ ተተረተሩ፣ በድንጋይ ተወገሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን በእምነት የተሰደድንየተጨነቅን የምንጸልየው ስደትን ከኛ በፊት በሕጻንነቱ በቀመሰ ስደትን በሚያውቅ አምላክ ፊት ነው፡፡

    ለ. ጣኦታተ ግብጽን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ወደምድረ ግብጽ ተሰደዱ

    ግብጽ ከነገሥታቶቿ ጀምሮ ጣኦትን የሚያመልኩ አህዛብ የነበሩ ህዝቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጣኦታትደግሞ የበሬ፣ የላም፣  የአንበሳ፣ የወፍ ምስል አስቀርጸው ያመልኩ ስለነበር ለዚህም ከሙሴና ከአሮን ጸሎት የተነሳ የግብጻውያን የእጃቸው ሥራ መጥፋቱን፣ እግዚአብሔር በናቡከደነጾር አድሮ ወደግብጽ መምጣቱን፣ ጣዖታትን ማጥፋቱን የተነበየበት ከመሆኑ በላይ በዘባነ ማርያም ኅዙል /በማርያምጀርባ ታዝሎ/ በፈጣን ደመና በተመሰለች ከእመቤታችን ጋር ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡ ሊቃውንት እመቤታችንን ሲመስሏት ደመና ኢሳይያስ የሚሏትም ስለዚህ ነው፡፡ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ግብጽ በጣዖታት የተሞላች በመሆኗ የጌታችን ስደት በግብጽ ያሉ ጣዖታትን ለማጥፋት እንዲሆን ተጠቅሷል፡፡ ግብጻውያን ከጥንት ጀምሮ በማስመሰል ደንጊያ ጠርበው እንጨት አለዝበው ማዕድን አቅልጠው  የእንስሳትን ምስል  የላም፣የፍየል፣የአንበሳ የወፍ  ምስልን በመቅረጽ ያመልኩ ስለነበር ከተማዋ በጣኦታት የተሞላች ነበር ፡፡እነዚህን ለማጥፋት የጌታ ስደት ወደ ግብጽ ይሆን ዘንድ ትንቢት አናገረ፡፡ጌታችን ጣኦታትን ሊያፈርስወደ ግብጽ ተሰደደ ገና ከተማዋ ሲገባ በጣኦታቱላይ ያደሩ አጋንንት ይጮሁ ጣኦታቱም ይሰባበሩ ጀመር ። ከዚህም ባሻገር በኛ ሕይወትም ውስጥ ጌታን ለመቀበል ጌታ ስራ እንዲሰራብን በቅድስና ለመኖር የልብን ጣዖታት ማጥፋት ማጽዳትይገባል፡፡ አልያ ጌታንና ጣዖትን በልባችን ማኖርአንችልም ቅዱስ ጳውሎስ "መኑ ደመሮ ለብርሃንምስለ ጽልመት" ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር መስማማት አለው ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔርቤተ መቅደስ ነንና፡፡ ያለው ለዚሁ ነው፡፡ ቅዱስዳዊት፡-  ( መዝ. 83፥3 ) "ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች"፡፡ በማለት ሲተነብይ ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ሲል ነቢያት የተነበዩት ፍጻሜውንበእመቤታችን ማግኘቱን አንድም እመቤታችን በስደት ግብጽ መኖርያዋ ማድረጓን ዋኖስምጫጭቶችዋን የምታኖርበት ሲል ዮሴፍና ሰሎሜም የሚኖሩበት ቤት ማግኘታቸውን ተናገረ፡፡ለእመቤታችን ማደሪያ ጠፍቶ ማደሪያዋን ግብጽ ማድረጓን ተንብየዋል፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ፡- "እስራኤል ሕጻን በነበረ ጊዜ ወደድኩት ልጄንም ከግብጽጠራሁት"  ( ምዕ. 11፥1 )   እስራኤል በግብጽ ሳሉ እንደተመረጡ ከዚያም አገር አውጥቶ መንግስት ይሆኑ ዘንድ እንዳበቃቸው የተናገረበት ትንቢትከመሆን ጋር የጌታችን ወደ ግብጽ መሰደድ ሔሮድስ እስኪሞት በዚያ መቀመጡን ከዚያም መመለሱን የሚያመለክት መሆኑን ቅዱስ ማቴዎስ የነቢዩን ቃል ፍጻሜ አድርጎ ተናግሯል  ( ማቴ. 2፥15 ) ።

    ሐ . ሰው መሆኑን ለመግለጽ  ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደደ

    ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ሳይለቅ ከሄድሮስ ዓይን መሠወር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በአምላካዊ ጥበቡ ከሄሮድስ ዓይን ተሰውሮ ቢሆን ሥጋ መልበሱ ሰው መሆኑን አይገለጽም ነበር፡፡ በሄሮድስ ዓይን የማይታይ ከሆነ ሥጋ ሳይለብስ የለበሰ መስሎየተገለጸ ሥጋና አጥንት የሌለው /ምትሐት/ ነው በተባለም ነበር፡፡ ከአዳም አካል አንድም ያልጎደለው ሙሉ ዳግማዊ አዳም መሆኑን እና የለበሰው ሥጋ የሚደማ የሚቆስል በሰይፍም ሆነ በጦር ቢወጋ ጉዳት የሚደርስበት ሰብአዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ስደተኛ ሆነ፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከጠላቱ ማምለጥ የሚችለው ከጠላቱ ፊት ዞር በማለቱ እና በመሸሹ ስለሆነ ጌታም ከጠላቱ ከሄሮድስ ለማምለጥ ሰው እንደመሆኑ ወደ ግብጽ ሸሸ፡፡

    መ . ዲያብሎስን ለማሳደድ ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደደ

    አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት እየራቀ ሄደ፡፡ ይህን የፈጣሪና የፍጡርመራራቅ ያመጣው ዲያብሎስ ሲሆን በፈጣሪመራቅ ፈንታ እርሱ መቅረብ ይፈልግ ነበር፡፡ስለሆነም ፈጣሪው ከሰው ጓሮ ወደ ወጣበት የሰው ልጅ ሳይጠራ መምጣት ወይም መቅረብ ጀመረ፡፡ዲያብሎስ የአዳምን ልጆች ተቆጣጠራቸው፡፡ልባቸውን በፍቅረ ጣኦት ሸፍኖ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዳያዩ አደረጋቸው ብዙ የአዳምልጆችም የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይሆን የሰይጣንን ፈቃድ ሲፈጽሙ ኖሩ፡፡ ጌታም "አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጪ ይጣላል" (ዮሐ. 12፥31 ) በማለት ሰይጣን ዓለሙን ተቆጣጥሮት እንደነበረ ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ በለበሰ ጊዜ የፈጣሪና የፍጡር ግንኙነት እንደገና ተመሠረተ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ለቆ በመውጣቱ ዲያብሎስን ከተቆጣጠረው ከሰው ልቡና አስወጣው ጌታ ከሄሮድስ ፊት እየራቀ ሲሄድ ዲያብሎስም ከሰው ፊት እየራቀ ሄደ፡፡ የጌታ ስደት በተዘዋዋሪ የዲያብሎስ ስደት ሆነ ጌታ የሚቀበለው መከራ ሁሉ ዲያብሎስን በርቀት የሚመታ መሣርያ ነበር፡፡ በመጨረሻም በመስቀል ላይ የሆነው የጌታ ሞት የዲያብሎስ ሞት ሆነ፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
    አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን  !!!!!!

     ይቀጥላል … … … … … … ይቆየን   ……………

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ዘመነ ጽጌ - ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top