• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday 11 November 2015

    «በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ ፣  በሞት ጥላአገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው» (ኢሳ፱፡፩)

     
    እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ

    «በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ   በሞት ጥላአገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው» (ኢሳ)

    ምንጭ፦ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል

    በሰው ልጅ አዕምሮ ሲመዘኑ ይፈጸማሉ ተብለውየማይገመቱ ነገር ግን የተደረጉ በታሪክ መጻሕፍት ምላይ ሰፍረው የሚገኙ ብዙ ድንቅ ድንቅ ነገሮች አለ<፡፡ በተለይም በዘመናችን በሌላው ዘንድ ለመታወቅ ካላቸው ጥማት የተነሳ አንዳንድ ሰዎች የማይወጡትዳገት ፣  የማይወርዱት ቁልቁለት ፣  የማይፈነቅሉትድንጋይ የለም፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊ ዓለም የተፈጸመውንና በኅሊና ከማመላለስ በልቡናም ከማሰብ በላይ የሆነውን የሥጋዌን (የእግዚአብሔርሰው መሆን) ምስጢር የሚያህል ግን ተከስቶ አያውቅም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡ በዚህም ሰው የመሆን ምስጢር ልቡናቸው የተነካአበው «እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል» ብለዋል፡፡አባ ኤፍሬምም ይህንን ድንቅ እዩ ፣ ስለተገለጠልንም ምስጢር ምሥጋና አቅርቡ፡፡ ሰው የማይሆን ሰው  ሆኗልና ፣  ቃል ተዋሕዷል ፣  ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ ፣  ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) ብሎ ድንቅነቱን ገልጿል፡፡ ይህንን የተዋሕዶ ምስጢር ለማወቅ ልቡናችንን እንክፈት፡፡በመንፈሳዊ ዓይን በንጹሕ ልቡና ነገረ ልደቱን እንመልከት፡፡የቅዱሳት መጻሕፍትንም ምስክርነት በጥሞና እንከታተል፡፡

    ፩. ትንቢትና ምሳሌ

    እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በመልካሙ ሥፍራ በኤደን ገነት አኖረው፡፡ በዚህም ሳያበቃ የበለስን ፍሬ እንዳይበላና እንዳይሞት ትእዛዝ የመጠበቅን ሕግ ሰራለት (ዘፍ፪፡፲፯)፡፡ ነገር ግን የጠላታችን ዲያቢሎስን ምክር ተቀብለው የእግዚአብሔርን ፍቅርና ትዕዛዝ እምቢ ብለወ ፣ አማልክት እንሆናል የማለት ስሜት ስላደረባቸው ዕፀበለስን በልተው ፣  ትእዛዙን አፈረሱ፡፡ መርገምም ወደቀባቸው፡፡ ምድርም የበረከት ቦታ መሆኗ ቀርቶ የመርገም ሥፍራ ሆነ፡፡ እሾህና አሜኬላ በቀለባት (ዘፍ ፫፡፲፯-፲፱)፡፡

     በአዳምና በሔዋን በልጆቻቸው ሁሉ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ፣  ርደተ መቃብር ገሃነም ተፈረደባቸው፡፡ ንስሐ ገብተው ቢለምኑት ኃጢአተኛ መመለሱን እንጅ መጥፋቱን የማይፈልግ እግዚአብሔር አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጻም ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት፡፡ ይህንን የተስፋ ቃል በመጠበቅ አባቶች ሁሉ በጾምና በጸሎት ፣  በእንባና በኃዘን ዕድሜአቸውን አሳለፍ፡፡

    አበ ብዙሃን አብርሃም (በዘርዕከ ይትባረኩ ኰሎሙ አሕዛብ ምድር- በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ›› (ዘፍ፲፪፧፫) የሚል የተስፋ ቃል በመያዝ በዘመኑ ሁሉ አምላካዊቃል እውን መሆን ሲጠባበቅ ፣  እግዚአብሔርን ደጅሲጠና ቆየ፡፡ ዘመነ አበው ተፈጽሞ ዘመነ መሳፍንት ሲጀምር የእግዚአብሔርን ሰው መሆን በመጠባበቃቸው ገፉበት፡፡ ሊቀ ነብያት ሙሴ (ነቢየ ያነሥእ ለክሙ እግዚአብሔር  እም አኃዊክሙ ዘከማየ ወሎቱ ስምዕዎ- እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መሃከል እንደኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፡፡ እርሱን ስሙት›› በማለት አስተምሯል (የሐዋ ፯፡፴፮፤ ዘዳ ፲፰፡፲፭)፡፡

     ምሳሌውን በነበልባልና በሐመልማል አምሳል አይቷልና (ዘጸ፫፡፩)፡፡ በዘመነ ነገሥትም ነቢየ ልዑል ዳዊት እግዚአብሔር በይሁዳ ወዐብየ እግዚአብሔርበእስራኤል- እግዚአብሔር ታወቀ ስሙም በእስራኤልከፍ ከፍ አለ›› (መዝ ፸፭፡፩) ብሎ የዘመናት ግድግዳ ሳይከለክለው የክርስቶስን ምስጢር ተናግሯል፡፡  

         ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቦታ (ቤተልሔም ከተማ)

    ልዑለ ባሕርይ አምላክ በቤተልሔም ከተማ በበረት እንደሚወለድ ፣  በጨርቅም እንደሚጠቀለል ሲያጠይቅ ‹‹ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም- በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም  አገኘነው›› ብሏል (መዝ ፻፴፩፡፯)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዕዝራም ‹‹ወናሁ እሬኢ- ነፋስ ዐቢይ ይወፅእ እምውስተ ባሕር- ታላቅ ነፋስ ከባሕር ሲወጣአየሁ›› ብሎ የሥጋዌን ምስጢር ገልጾ አስረድቷል፡፡

    ባሕር የእመቤታችን ፣  ነፋስ የጌታ ምሳሌዎች ናቸው(ዕዝራ ሱቱኤል ፲፪፡፪)፡፡ እነዚህ ደጋግ አበው በምሳሌ ያዩትን ኢሳይያስ ነቢይ አብርቶ አጉልቶ ‹‹ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ፣ ወትሰይሚዮ ስሞ አማኑኤል- እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ብሎ ገልጦ መሰከረ(ኢሳ፯፡፲፬)፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ሚክያስም መሲሑ የሚወለድበትን ሥፍራ ሲመለከት ‹‹ወአንቲኒ ቤተልሄም ምድረ ኤፍራታ ፣  ኢትሐፅፂ እመሳፍንተ ይሁዳ፤ እስመ እምኔኪ ይወፅዕ ንጉሥ ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል፤ አንቺ ቤተልሄም የኤፍራታ ምድር ፣  ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሺም ፣  ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና››ብሏል (ሚክ፭ ፣ ፩-፫)፡፡ ትንቢቱ ተነገረ ሱባዔውም ተቆጠረ እግዚአብሔርም አንድያ ልጁን የሚልክበትወቅት ደረሰ

    ፪. ብሥራት

    የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስገብርኤል በቤተ መቅደስ ወደምትኖር ወደ ድንግልማርያም ተላከ፡ እመቤታችንንም ‹‹ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ›› ብሎ አበሰራት፡፡ ትህትናዋ የተመሰከረላት እመቤትም ‹‹ይህ እንዴት ያለ ሰላምታነው›› ብላ ራሷን ዝቅ አደረገች፡፡ ‹‹ትጸንሻለሽ›› ሲላትም ‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል;›› ብላ ንጽህናዋን ገለጠች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እንዳያሳዝናት ከፈጣሪው ታዟልና ለማመን በመዘግየቱ ‹‹ድዳ ትሆናለህ›› እንዳለው እንደ ዘካርያስ ሳይሆን የዘመዷን የኤልሳቤጥን ታሪክ በምሳሌነት ጠቅሶ አስረዳት፡፡ ለማረጋገጫም ‹‹እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር›› ባላትጊዜ የእምነት እናት ናትና ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ-እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› ብላ በእምነት ተቀበለች (ሉቃ1 ፣ ፳፮-፴፰)፡፡ ወድያውም ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱሰ አንድነት ሳይለይከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በማኅጸኗ አደረ፡፡እመቤታችን ትሕትና ፣  ንጽሕና እና እምነት ይዛ እንደተገኘች የርሷ ልጆች ምዕመናንንም ይህንኑ ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል፡፡

    ፫. እግዚአብሔር ሰው ሆነ

    ወልደ እግዚአብሔር መድኃኔዓለም የሰውን ሥርዓትይፈጽም ዘንድ በእናቱ ማኅጸን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተቀመጠ፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዘመነ ሄሮድስ በቤተልሔም ከተማ በከብቶች በረት ፣  በእኩለ ሌሊት፣  በአጭር ቁመት ፣  በጠባብ ደረት ተወስኖ ተወለደ (ማቴ፪፡፩፤ ሉቃ ፪፡፩-፯)፡፡ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ በራእዩ እመቤታችን ጌታን ስለመውለዷ ሲያስረዳ ‹‹አሕዛብን ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደ‹›› ብሏል (ራእ፲፪፡፭)፡፡ ነቢየ ልዑልኢሳይያስ አስቀድሞ ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና ፣  ወንድልጅም ተሰጥቶናል“ ፣  አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናልና ፣  ስሙም ድንቅ ፣  መካ`  ፣  ኃያል አምላ¡ ፣ የዘላለም አባት ፣   የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል›› ያለው ቃል ተፈጸመ (ኢሳ ፱፣፮)፡፡ ጌታ የተወለደው እንደ ሰው ልማድ ሳይሆን ቃል ከአብ ያለ ድካም ወጣ፣  ከድንግልም ያለ ሕማም ተወለደ ፣ በመወለዱም ድንግልናዋን አልለወጠውም ፣  ሰው በመሆኑም አምላክነቱ አልተለወጠም ፣  ይህም ድንቅ የተዋሕዶምሥጢር ነው፡፡

    ፬. ስለልደተ ክርስቶስ የአበው ምስክርነት

    ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን ፣  ስለ ጌታችንም በመልእክቱ በሰፊው አስተምሯል፡፡ አባቶቻችን ተስፋ ያደረጉት በማን መሆኑን ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስክርስቶስ ነው›› ብሏል (ሮሜ ፩፡፫-፭)፡፡ የገላትያን ምዕመናንንም ሲመክር ‹‹የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜእግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ፣  ከሕግም በታችየተወለደውን ልጁን ላከ›› ብሏል (ገላ ፩፡፬)፡፡ 

    ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ ‹‹ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፣  በዓይኖቻችንም ያየውን ፣  የተመለከትነውንም ፣ እጆቻችን የዳሰሱትን እናወራለን›› በማለት በመካከላቸው ስለተመላለስው አብረውት ስለበሉትስለጌታ በበለጠ ሲያስተምርም ‹‹ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን ፣  ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የገለጠውንም የዘላለም ሕይወት እናወራላችኋለን›› ብሏል (፩ኛዮሐ ፩፣፩-፫)፡፡ 

    የሐዋርያትን መንገድ የተከተሉ አባቶችም በትምህርታቸው ይህንን የተዋሕዶ ትምህርትአስፍተውና አምልተው አስተምረዋል፡፡ ለአብነትም የሐዋርያት ደቀ መዝሙር ፎስጢኖስ ‹‹ክርስቶስ ቅድመ ዓለም የነበረ ሲሆን የሰውን ልደት ተቀበለ›› ሲል የአቴናው ኤጲስ ቆጶስ ዲዮናስዮስም ‹‹በፍጻሜው ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልማርያም ማኅፀን አደረ ድንቅ በሚሆን ምስጢርምተወለደ›› በማለት ነገረ ልደቱን መስክሯል፡፡ ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራትም ‹‹ከአባቱ ሳይለይ ከባሕርዩ ሳይለወጥ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ሥጋችንንነስቶ የለበሰ (ሰው የሆነ) ይህ ነው›› ብሏል፡፡ 

    ፭. ሰው በሆነው አምላክ ያለን እምነት

    ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ መጽሐፍን ቃል እንዳልጠነቀቁ ሰዎች ከብር. ይግባውና አምላክ ቅዱሱን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡርወይም ከአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ዛሬ የሚማልድ አልያምሩቅ ብእሲ ብላ አታምንም አታስተምርምም ነገር ግንአባቶቻችን እንዳስተማሩት ቅዱስ መጽሐፍም እንዳረጋገጠው

    ሀ. ‹‹ከሰማይ ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከእመቤታችን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው መሆኑን›› (ሠለስቱ ምዕት)

    ለ. ‹‹ቅድመ ዓለም ከአብ ፣  ድኅረ ዓለምም ከእመቤታችን የተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን›› (ቅ/ አትናቴዎስ)

    ሐ. ‹‹ለወልደ  እግዚአብሔር ሁለት ልደት እንዳለው ይኽውም ቅድመ ዓለም ከአባት ያለ እናት ድኅረ አለም ከእናት ያለ አባት መወለዱ”›› (ቅዱስ ባስልዮስ )

    መ. ‹‹ቃል ሥጋ መሆኑን ነውር በሌለበት ማኅፀን ሥጋን እንደተዋሐደ ዳግመኛም በጌትነቱ የሚኖር እርሱ በጎል (በበረት ) መጣሉን ፣  ሥጋንም ሳይዋሐድ አይዳሰስ የነበረ ወልድ ዛሬ ሥጋን በመዋሐድ መዳሰሱን ፣  የኃጢአትንም ማሠሪያ የሚቆርጥ እርሱ በጨርቅ መጠቅለሉን›› (ቅ/ ዮሐንስ አፈወርቅ)

    ሠ. ‹‹ንጽሕት ድንግል ማርያምም እግዚአብሔርን በሥጋ እንደወለደች›› (ቅዱስ ቄርሎስ) እናምናለን፡፡


    ፮. ማጠቃለያ 

    በአጠቃላይ የልደትን በዓል በምናከብርበት ወቅት ከላይ የጠቀስናቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ማጤን እንደሚገባን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አይሁድ መሲሑ እንደሚመጣ እያወቁ የሚወለድበትንም ቦታ ለሰበዓሰገልና ለሄሮድስ እያመለከቱ እነርሱ ግን ከመዳን እንደዘገዩ ሁሉ እኛም በዓሉን በበዓልነቱ ብቻ እያከበርን ከንስሐና ከሥጋ ወደሙ በመራቅ ከሕይወትመንገድ እንዳንወጣ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም. ይሀንን የተዋሕዶ ምሥጢር ለመረዳት ዘወትር በቤተክርስቲያን በመገኘት ቃለ እግዚአብሔርን መማር ይገባናል፡፡

    እግዚአብሔር አምላክ በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን ያጽናን፤ አሜን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: «በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ ፣  በሞት ጥላአገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው» (ኢሳ፱፡፩) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top