• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 13 November 2015

    ጉባኤ ኒቅያ

    ከይስሐቅ አበባየሁ

    የዚህ ጽሐፍ መታሰቢያነቱ በሞት ለተለዩን ለአቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀ ጳጳስ ይሁንልኝ፡፡ 

    እንደ ኢ/ኦ/ተ ቤ/ክ ስርዓት መሠረት መስከረም ውስጥ ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ጉባኤ ኒቅያ በሰፊው ይታሰባል፡፡ በረከታቸው ይደርብንና አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የቤ/ክ ታሪክ በዓለም መድረክ በሚለው መጽሐፋቸው የቤ/ክ ታሪክን የማወቅ ጥቅሙን ሲገልጡ ‹‹ የቤተክስቲያን ታሪክ ትምህርት የክርስትና እምነት የአምላክ መገለጥ ነው። ይሁን እንጂ በዘመን በቦታ የተደረገ ስለሆነ መቼ? ወዴትና ለምን? እንደሆነ የምታወቅበት ነው። ከቤተልሄም ዋሻ እስከ ቀራኒዮ ድረስ ያለውን ከካታኮምብ የግበበ ምድር ህይወት ጀምሮ እስከ አለንበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ እያወዳደረ ያጠናል። ›› እንኪያስ አባታችን ከጠቆሙን አጠር አድርገን እንጀምር፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሆኖተገልጦበቤተልሔም ተወልደ፣ ወደ ግብጽተሰዶ፣በናዝሬት አድጎ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠመቆ፣በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ፣ በኪደተ እግሩዓለምንእየቀደሰ ፣ ትምህርቱን በስራው እየገለጠ፣ሁሉን እያሳየ በሚያስተምርበት ወቅት በአይሁድ ክፋት እሱ ባስቀመጠው የመዳን መንገድ በቀራኒዮ አደባባይ እንደ ብራና ተወጠረ፡፡ ክርስቶስን ወደመቃብር ያወረዱት አይሁዶች የክርስትና መቃብር ላይ የቆሙ ቢመስላቸውም፤ ነገር ግን ክርስቶስሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ ክርስትናም አብሮት ተነሳ፡፡ባረገ በ10ኛውቀን ኃይልመንፈስ ቅዱስን ከአርያምበተቀበሉ ጊዜ ሐዋርያቱና ሌሎቹየክርስቶስቤተሰቦች ከእርጅናቸው ታድሰው፣ ከፍርሀታቸውታክመው፣ የክርስቶስን ወንጌል በአይሁድ መካከል ሰበኩ፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ግርፋት፣ መታሰር፣ በዲንጋል መደብደብ፣ በሰይፍ መሰየፍ፣ ቁልቁል መሰቀል፣ ግዞት የዘወትር ሽልማታቸው ሆነ፡፡ፈተናቸውም በበዛ ቁጥርብዛታቸውም እንደዛው መጠን ነበር፡፡ክርስቲያኖች ሥጋቸውእንደሽንኩርትተቀረደደ ፣በፈላ ዘይት ተቀቀሉ፡፡ብዙግፍና መከራደረሰባቸው፡፡ ይህእልቂት ከኔሮን ቄሳር ቀጥሎ በተነሱት በዶሚኒያን፣ ትራጃን፣ ዲዮቅልጥያኖስ በከፍተኛ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ በኔሮንቄሳር የተጀመረው ክርስቲያኖችን የመጨፍጨፍበንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዕረፍት ተገኘ፡፡

    ርዕሳችን ጉባኤ ኒቂያ እንደመሆኑ አስቀድመን ጠንቅቀን ማወቅ የሚገባን ነጥቦች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ በጊዜው ስለነበሩ ትርጓሜ ቤቶች ነው፡፡እነዚህም የእስክንድርያ እና የአንጾኪያ ትርጓሜ ቤቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡ የሁለቱም ት/ቤቶች ዋና ዓላማ ለሰው ድኅነት ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጡትን በቅዱሳን አበው ምክኒያት ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡትን የብሉያትንና የሐዲሳትን ቅዱሳት መጻሕፍት ለምዕመናን እንዲገባ አድርጎ መተርጎምና፣ ወደ ቤ/ክ የሚመጡትን አዲስ አማንያንን ለጥምቀት ማዘጋጀትና በክርስትናቸው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሆኖም የእስክንድርያና የአንጾኪያ ትምህርት ቤቶች በቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጐም በኩል በመካከላቸው ታላቅ ልዩነት ነበረ፡፡ የእስክንድርያና ት/ቤት ቅዱሳት መጽሐፍትን አንድምታ ትርጓሜ(Allegorical) በመተርጐም የመጽሐፍትን ምሥጢራቸውን እንጂ ንባባቸውን ቃል በቃል አይከተሉም ነበር፡፡ የአንጾኪያ ት/ቤት ደግሞ የቃል በቃል ትርጓሜን ወይም ነጠላ ትርጓሜን እንጂ አንድምታን አይከተሉም፡፡ የብዙ ክህደት ምንጭም ይኽው ቃል በቃል ትርጓሜ እንደሆነ ይታመናል፡፡

    በመጀመሪያው አራት መቶ ዓመታት ውስጥ ቤ/ክ በብዙ አቅጣጫ የተለያዩ ችግሮች ደርሰዉባት እጅግ ስትሠቃይ ቆይታለች፡፡ ከነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ አንዱ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የዶግማ ትምህርት ልዩነት መፈጠሩ ነው፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ እንደነ ጳውሎስ ሳምሳጢ፣ ሰባልዮ የመሳሰሉት የተነሱበት ነበር፡፡ በተለይም አርዮስ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› ብሎ በመነሣቱ ቤ/ክ ለብዙ ዓመታት እንድትታወክና እንድትበጠበጥ ሆኗል፡፡

    አርዮስ በ260ዓ.ም አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በሊብያ ነው የተወለደው፡፡ የትውልድ ዘሩ ግሪካዊ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አርዮስ መሠረታዊ ትምህርቱን በሊብያ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ እስክንድርያ በመጓዝ በእስክንድርያ ከፍተኛ ት/ቤት ትምህርት አጠናቆ እንደጨረሰ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄዶ በአንጾኪያ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ገብቶ የትርጓሜ መጻሕፍትና የነገረ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡ በጊዜውም ሉቅያኖስ ከተባለ መናፍቅ ዘንድ ተምሯል፡፡ ሊቃውንት አርዮስ ከእስክንድርያ ት/ቤት ይልቅ የአንጾኪያ ት/ቤት የክህደት ትምህርት ቅርበት እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ አርዮስ አብዛኛውን የኑፋቄ ትምህርት  ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾኪያ ት/ቤት ነው፡፡ በአንጾኪያ ትምህርት ከጨረሰ በኋላ አርዮስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ኑሮውን በዚያው አደረገ፡፡

    አርዮስ ብልህና ዐዋቂ አንደበተ ርቱዕና እምቅ የሆነ የግጥም ችሎታ እንደነበረው ይነገራል፡፡ በጊዜው የእስክንድርያ ፓትርያክ ከነበሩት ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ተቀብሎ አገልግሎት ጀመረ፡፡ አርዮስም በእስክንድርያ ቤ/ክ ‹‹ወልድ ፍጡር›› እያለ ማስተማር ጀመረ፡፡ የዚህ ጊዜ ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አስጠርተው ትምህርት ሁሉ የተሳሳተ መሆኑንና ከስሕተቱ ተመልሶና ተጸጽቶ ከቅዱሳን አበው ሲተላለፍ በመጣው በኦርቶዶክስ እምነት እንዲጸና መከሩት፡፡ እሱ ግን ምክራቸውን ወደ ጎን ትቶ የክሕደት ትምርቱን በሰፊው ማስተማር ቀጠለ፤ የዚህ ጊዜ አርዮስን አውግዘው ከዲቁና ማዕረጉ ሻሩት፡፡ የግብጽ ቤ/ክ ትውፊት እንደሚለው ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ያወገዙት ጌታችን ኢየሱስ በራዕይ ተገልጦ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሌሊት በራዕይ ጌታ ኢየሱስ በህጻን ልጅ አምሳል እንደ ፀሐፍ የሚያበራ ረጅም ልብስ(ቀሚስ) ለብሶ ነበር፡፡ ልብሱ ግን ለሁለት የተቀደደ ሆኖ ያዩታል ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም ልብስህን ማን ቀደደብህ(መኑ ሰጠጣ ለልብስከ?) ብለው ሲጠይቁ ጌታ ኢየሱስም ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› ይላቸዋል፡፡ በዚያኑ ቀን ሁለቱን ተማሪዎቻቸውን አኪላስንና እለእስክንድሮስን  አስጠርተው  የተገለጠላቸውን ራዕይ በመግለጥ አርዮስን እንዳይቀበሉት ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዳይኖራቸው አዘው፤ በዲዮቅልጥያኖስ ሰማእት ሆነው አረፉ፡፡

    ከተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ሞት በኋላ አኪላስ በ303ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ አርዮስም ወደ አኪላስ ቀርቦ ከውግዘቱ እንዲፈታው በከንቱ ውዳሴ አባበለው፡፡ አኪላስም አደራውን በመዘንጋት ከውግዘቱ ፈታው፤ ይባስ ብሎም የቅስና ማዕረግ ሰጥቶ ሾመው፡፡ ሆኖም አኪላስ በሕይወት ብዙ ጊዜ አልቆየም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ በቀጠል እለእስክንድሮስ ፓትርያክ ሆኖ ተተካ፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮስ ክህደቱን ከማሰራጨት አልታቀበም ነበር፡፡ እንደውም ሕዝቡ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበሉ የክሕደት ትምህርቱን በግጥምና ንባብ እያዘጋጀ ማሰራጨት ቀጠለ፡፡ ያም የግጥም መጣጥፍ ‹‹ታሊያ›› ይባል ነበር፡፡ ትርጉሙም ማዕድ ማለትነው፡፡ ሕዝቡ ግጥም ስለሚወድ ትምህርቱን ወደ መቀበል ደርሶ ነበር፡፡ የዚህ ጊዜ እለእስክንድሮስ እየተዘዋወረ ከአርዮስ ኑፋቄ እንዲጠበቁ በትጋት ያስተምር ነበር፡፡ በ320ዓ.ም አንድ መቶ ሚያህሉ የሊቢያና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳትን እለእስክንድሮስ አሰባስቦ የአርዮስን አስተሳስቦ ገልጾላቸው ጉባኤውም አልመለስ ያለውን አርዮስን በአንድ ልብ አውግዘው ከቤ/ክ አንድነት ለዩት፡፡

    አርዮስ ከጓደኞቹ አንዱ ወደ ነበረው ወደ የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ በመገስገስ አንድ በአንድ ዘርዝሮ ነገረው፡፡ አውሳቢዮስም አይዞህ ብሎ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በአርዮስ ጉዳይ ሲኖዶስ አደረገ፡፡ ሲኖዶሱም በግፍ መባረሩን አምኖ ከውግዘቱ ፈቱት፡፡ አርዮስም በ322 ዓ.ም ወደ እስክንድያ ተመልሶ እለእስክንድሮስ ቢያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ እያለ የበፊት ትምህርቱን በስፋት ማስተማር ቀጠለ፡፡ የዚህ ጊዜ ቤ/ክ ታመሰች፡፡ በዚህ ምክኒያት ጉዳዩ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ደረሰ የዚህ ጊዜ የእስፓኝ ጳጳስ ሆስዮስን ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ሲመለስ ጉዳዩ የሃይማኖት ችግር እንጂ አስተዳደራዊ ስላልሆነ በጉባኤ መታየት አለበት ብሎ ለንጉሡ አማከረው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ325ዓ.ም ጉባኤ እንዲደረግ አዘዘ፡፡ በዚህም በኒቅያ 318 አባቶች ተሰበሰቡ፡፡

    መሠረታዊ የአርዮስ ክህደቶች

    1.ኛ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር አልነበረም (ሎቱ ስብሐት)

    2.ኛ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ ነው (ሎቱ ስብሐት)

    3.ኛ የተፈጠረ እንጂ ከአብ የተወለደ አይደለም (ሎቱ ስብሐት)

    4.ኛ በመጀመሪያ ዓለሙን ይፈጥርበት ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን ፈጠረው፤ እርሱም ዓለምን ፈጠረ፡፡ ባጠቃላይ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ የሚል ነበር (ሎቱ ስብሐት)

    ባጠቃላይ አርዮስ ያቀረባቸው ጥቅሶች ተመረመሩ፣ ወልድ በባሕርይ ፍጡር ከተባለ በመዳን ላይ ስለሚደርሰው አደጋ ወዘተ በስፋት ተነጋገሩበት፡፡ በተለይም ወጣቱ አትናቴዎስ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፣ አዳኝ ነው፣ ማዳኑን ካመንክ የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብህ፤ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በ(ማቴ 1፡21፣ ኢሳ 45፡21፣ ሆሴ 13፡4፣ ሉቃ 1፡47፣ 1ኛ ጢሞ 1፡1፣ ቲቶ 1፡3፣ ቲቶ 2፡10-13፣ ቲቶ 4፡7፣ የሐዋ 4፡12፣ 1ኛ ጢሞ 4፡10፣ ይሁ 1፡25፣ ሉቃ 2፡11፣ ዮሐ 4፡42፣ ሉቃ 11፡20፣ ማቴ12፡28 ማር 1፡19 ሉቃ 8፡39 ሉቃ 11፡20፣27) እንደተቀመጠና በተለይም ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል የጠፋው በግ ምሳሌ የተቀመጠውን ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከመዳናችን በማያያዝ እሱ አምላክ ካልሆነ እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ ያዳነን እሱ አምላክ መኾኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ፍጡር ፍጡርን ማዳን አይችልም በማለት አርዮስን በጉባኤው ረቶታል፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና በባሕርይም ከአብ ጋር አንድ ስለመሆኑ የቀረበውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ከመረመሩ በኋላ በፍልስፍና ገመድ ተጠላልፎ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ ያለውን አርዮስን አውግዘው ከቤ/ክ አንድነት ለዩት፡፡      

    ጉባኤ ኒቅያ ቤ/ክ አንድነቷን የጠበቀችበት፣ አርዮስና አርዮሳውያን የተወገዙበት፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ አዳኝነት፣ ጌትነት፣ መድኃኒትነት የተመሠከረበት፣ ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ትምክህት የሆነበት… ወዘተ፡፡ ቤ/ክ ይህን ጉባኤ ትቀበላለች ትልቅም ስፍራ አላት፡፡

    ዋቢ መጽሐፍት

    1.ኛ የቤ/ክ ታሪክ በዓለም መድረክ፡- (አቡነ ጎርጎርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)) 2.ኛ የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ፡-(ምክረ ሥላሌ(ቀ/ዶ/ር)) 3.ኛ የቤ/ክ ታሪክ (ከሉሌ መልአኩ) 4.ኛ ኦርቶዶክስ ምን ማለት ነው፡- አጭር ጽሑፍ (አቤል ሃይሉ(ዲ/ን ዶ/ር))

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር   

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ጉባኤ ኒቅያ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top