• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ


    አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

    እንኳን ለታለቁ ጻድቅ ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ እያልን የገድል መጽሐፋቻን ዋቢ በማድረግ ታሪካቸውን እነሆ ብለናል፡፡ “መልካም በዓል” ይሁንላችሁ

    እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡ /እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል/መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

    አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ ግብጽ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ፡ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ በዚሁ መሰረት አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው ታህሳስ 29 ተወለዱ፡፡ ዓይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ አፈፍ ተነስተው “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘአውጻእከኒ እምጽ ልመት ውስተ ብረሃን” ብለው በማመስገናቸው ኋላም ምድራዊ መብል መጠጥ ሳይመገቡ ሳይጠጡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መላዕክትን ይመስላሉ።

    ሦስት ዓመት ሲሆናቸው ቅዱስ ገብርኤል ከእመቤታችንና በገነት ካሉ ቅዱሳን ዘንድ አስባርኮ ገዳማውያን ካሉበት አበ ምኔት ወስዶ ከበሩ አኖራቸው፡፡ አባ ዘመደ ብርሃን አሳድጎ አስተምሮ ከመዓርገ ምንኩስና አድርሷቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ “ሀብተ ፈውስ” ተሰቷቸዋል፡፡ በአንድ ቀን እልፍ እውራንንና አንካሳን ፈውሷል፡፡ ኋላ ግን ኤጲስ ቆጶሳቱ ካህናቱ ዝናቸውን ሰምተው እየመጡ የጸሎት ግብር የሚያስፈቷቸው ቢሆን ቅዱስ ገብርኤል በክንፉ ነጥቆ ከጌታ ፊት አቀረባቸው፡፡ በገድልህ በትሩፋትህ ከሞተ ነፍስ ከርደተ ገሃነም የሚድኑ ብዙ ነፍሳት አሉና ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ግባ፡፡ ኑሮህም ከ60 አናብስተና ከ60 አናምርት ጋር ይሁን አላቸው፡፡ ጌታዬ ምን ተመግበው ይኖራሉ? ብለው ጌታን ጠየቁት፡፡“ዘኬድከ ጸበለ-እገሪከ ይልህሱ ወበውእቱ ይጸግቡ…” የረገጥከውን ትቢያ ልሰው ያው ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ፡፡ ብሏቸው ውሳጤ ገዳም ገብተው ከአናብስትና አናምርት ጋር ይኖሩ ጀመር።

    ከዐራቱ አበይት ነቢያት እንዱ ዳንኤል በአናብስት ጉድጓድ በጣለ ጊዜ አናብርቱ እንደ ድመት ከእግሩ በታች ሆነው እንደተገኙ የረገጡትን ትቢያ ይልሱ ይታዘዟቸውም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ መልአኩ 30 ዓመት ከቆዩ በኋላ ጌታ ባንድነት በሦስትነት ተገልጾ “ምን ላድርግልህ ትሻለህ?” አላቸው፡፡ መጀመሪያ ላሉበት መጸለይ ይገባልና የምድረ ጋቦታን ሰዎች ማርልኝ አሉት፡፡ 3000 ኃጥአንን ከሲኦል አውጥቶ ገነት አግብቶላቸዋል።

    “ሑር ምድረ ኢትዮጵያ ወበህየኒ ሀላዉከ ነፍሳት ዘታወጽኦሙ – ወደ ኢትዮጵያ ሂድ” አላቸው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ ነፋስ ጭኖ ምድረ ከብድ አድርሷቸዋል፡፡ ዳግመኛም ወደ ዝቋላ ደብር ቅዱስ ወስዷቸው ከዚያ ሆነው በንጽሐ ልቦና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃጢአት አይተው ከባሕሩ በራሳቸው ቆመው ይጸልዩ ጀመር፡፡ አርባ ቀን ሲሆናቸው መልአኩ መጥቶ “ዘገብረ ተዝካረከ ወዘጸውዐ ስመከ እምሕር ለከ ብሎሀል” አላቸው፡፡ መላ ኢትዮጵያን ካልማረልኝ አልወጣም ብለው መቶ አመት ሲጸልዩ ኑረዋል፡፡ ከመቶ አመት በዃላ ጌታ “ተንስእ ወጻእ መሐርኩ ለከ ኩሎ ኢትዮጵያ ምሬለሃለሁ ውጣ”ብሏቸው ወጥተዋል።

    ከዚህ በኋላ ምድረ ከብድ ወርደው ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ሆነው ሰባት ዓመት እንደ ትኩል ዓምድ ሆነው ዓይናቸውን ሳይከድኑ ሰባት ዓመት ቆመው ጸልየዋል፡፡ ሰይጣንም በምቀኝነት ተነሳስቶ ቁራን መስሎ መጥቶ አይናቸውን አንቁሮ አሳወራቸው፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጽሙ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው እፍ ብሏቸው አድነዋቸዋል፡፡ ከዚያ ተነስተው ወደ ዝቋላ ሲሄዱ ሥላሴን በአምሳለ አረጋውያን ከጥላ ሥር አርፈው አገኟቸው፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን አሏቸው፡፡ አዝለው ከሸኙአቸው በኋላ በአንድነት በሦስትነት ሆኖ ታያቸው ደንግጠው ወደቁ፡፡ አንስተው ዝቋላ ወርደህ ጠላቶችህን ተበቀላቸው አሏቸው፡፡ በዘባነ መብረቅ ደርሰው ሰባቱን ሊቃነ መላእክት አጋዥ አርድገው እልፍ አዕላፍ አጋንንትን በማጭድ አጭደዋል፡፡ እንዲህ ለሰሚዕ እፁብ በሆነ ግብር ዓመት በኢትዮጵያ 262 ኖረው በ562 ዓመታቸው በተስፋቸው ያመነውን በኪዳናቸው የተማጸነ ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው በዕለተ እሑድ እንዳረፉ የገድላቸው መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top