ቅዱስ ኤፍሬም በጥምቀት ላይ እጅግ ጥልቅ የሆነ አስተምህሮ ያለው
አባት ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል ይለናል፡፡ “የሰውነት ትኩሳት ከሰውነታችን
በሚመነጨው ላቦት እንዲቀዘቅዝ እንዲሁ በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል፡፡”
ከዚህ ተነሥተን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ምልከታ የገሃነም ቦታዋ
ከሰውነታችን ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡ እሳቱ የማይጠፋ መባሉም ከእኛ ዘለዓለማዊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን መረዳት
እንችላልን ፡፡ እኛ ዘለዓለማውያን ሆነን ስለተፈጠርን እሳቱም በሰውነታችን ውስጥ ዳግም አይቀጣጠልም፡፡ ይህ
የሚያስረዳን ከጥምቀት በኋላ በራሳችን ፈቃድና ምርጫ በድርጊትም ይሁን በቃል ጌታችንን እስካልካድነው ድረስ የገሃነም
እሳት በሰውነታችን ውስጥ እንደማይኖር ነው፡፡
ስለዚህ መዳን አለመዳን በእጃችን እንደተያዘች መረዳት
እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህን መብታችንን የማንጠቀምበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እርሱም በምጽአትና በሞት ወደ እግዚአብሔር
ለፍርድ የተወሰድንበት ወቅት ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን የገሃነምን እሳት በሰውነታችን ላይ ማቀጣጠልም ይሁን
ማጥፋት ወይም ሰውነታችንን የጌታ ቤተመቅደስ ማድረግ ወይም አለማድረግ የእኛ ፈንታ ይሆናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም
ጥምቀትን ወደሰማያት የምንወጣጣበት መሰላል ብሎም ይጠራዋል፡፡
“እርሱ ወደ ጥምቀት በመውረድ ጥምቀትን መሠረተልን እርሱም በሠራልን ጥምቀት ወደ ሰማየ ሰማያት ተነጠቅን ፡፡”
¨ ቅዱስ ኤፍሬም መጠመቂያ ገንዳውን በክርስቶስ መስቀል ይመስለዋል፡፡ በውስጡም ክርስቶስን
ለብሰን እንወለዳለን ሲለን እንዲህ ይላል፡፡
“የክርስቶስ መንጎች እጅግ ደስ ተሰኝተው የእርሱን አርዓያ
የነሡበትን ሕያውና ቅዱስ የሆነውን መስቀል ከበው ቆመዋል፡፡ በዚያ ውስጥ ፍጥረታት እንደገና ተፈጥረው ይታያሉ፡፡
ሁሉም ሕያውና ቅዱስ በሆነው መስቀሉ ታትመዋል፡፡”
¨ ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታ ትእዛዝ በቀኝ በኩል የጣለው መረብ ፻፶፫ ዓሣት ይዞለት ነበር፡፡ ይህ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡
“ከባህር ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ መረብ ፻፶፫ ዓሣት ተሠግረው
ነበር፡፡ እንዲሁ በእርሱ ስብከት በጥምቀት እቅፍ ዐሥር ሺሕና ከዚያም በላይ የሆኑትን በማጥመድ የእግዚአብሔር ልጆች
እንዲሆኑ ማረካቸው” ይለናል፡፡
¨ “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ አሁን የእነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ” (ሉቃ.፲፪፥፵፰) የሚለውን የጌታ ቃል ለመንፈስ ቅዱስ በመስጠት እንዲህ ብሎ ያስተምራል፡፡
“ጌታችን “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ” ሲል እኔ የማጠምቀው ጥምቀት በዚህ ነው ሲለን ነው፡፡ እሳት ያለውም መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡”
“በጥምቀት እሳት በክፉው ሰይጣን የተቀጣጠለውን እሳት
አጠፋለሁ፡፡ ንጹሕ የሆነው በተጠማቂያን ነፍስ ውስጥ የተቀጣጠለው መለኮታዊው እሳት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በእርሱ
እሳትነት በኀጢአታችንና በመተላለፋችን ምክንያት የተቀጣጠለውን የገሃነም እሳትን ይጠፋልናል፡፡
“ይህ እሳት በምሳሌ በሲና ምድረ በዳ በእሾኽ ቁጥቋጦ ውስጥ
ለሙሴ የታየው እሳት ነው ፡፡ ሙሴ ያየው እሳት እሾኹንና ቁጥቋጦውን አላቃጠለውም ነበር፡፡ ነገር ግን በጥምቀት
በእናንተ ውስጥ የተቀጣጠለው መለኮታዊ እሳት የኀጢአት ቁጥቋጦውን አቃጥሎ ያጠፋዋል ፡፡ ስለዚህም እርሻው እስከሰማይ
የሚደርስ ፍሬን ያፈራል፡፡
¨ ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ነቢዩ ኤርምያስን በፀነሰችው ማኅፀን መስሎ ያስተምራል፡፡
“ነቢዩ ኤርምያስ ገና ከእናቱ ማኅፀን ሳለ ተቀደሰ ተማረ፡፡
ደካማ የሆነችው ማኅፀን የፀነሰችውን ቀድሳ የወለደች ከሆነ እንዴት ጥምቀት ከእርሷ ማኅፀን የተፀነሱትን ይበልጥ
ቀድሳ አትወልዳቸው ይሆን? ጥምቀት ተጠማቅያንን ንጹሐንና መንፈሳውያን አድርጋ ትወልዳቸዋለች፡፡”
የውኃንም ተፈጥሮ በማንሣት ጥምቀትን በውሃ ተፈጥሮአዊ ጠባይ
መስሎ ያስረዳል፡፡ “ውኃ በተፈጥሮው እንደመስታወት ነው ፡፡ አንድ ሰው በውኃው መስታወትነት እርሱ ምን እንደሚመስል
ተረድቶ እራሱን ያስተካክላል ፡፡ ወደ ጥምቀት ተመልከት በእርሱ ውስጥ ያለውን ውበትን ልበሰው፡፡”
በሥነ ፍጥረት የመንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ መስፈፍን ለጥምቀት
ሰጥቶ ይተረጉመዋል “በሥነ ፍጥረት መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ በመስፈፉ ምክንያት ውኃ ፀንሳ ዓሣትንና አእዋፋትን
እባብንም አስገኝታ ነበር፡፡ እንዲሁ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስ ውኃ ላይ በመስፈፉ ምክንያት በንስር የሚመሰሉትን
ደናግላንንና ጳጳሳትን ወለደች፡፡ በዓሣት የተመሰሉትን ራሳቸውን ለመንግሥተ ሰማያት ጃንደረቦች ያደረጉትንና ቅዱሳንን
ወለደች፡፡ አስቀድሞ ተንኮለኞች የነበሩትን በእባብ የሚመሰሉትን ወገኖች ደግሞ የዋሃን ርግቦች እንዲሆኑ አድርጋ
ወለደቻቸው፡፡”
ቅዱስ ኤፍሬም አዳም በክርስቶስ አካል ተጠምቆአል ብሎ ያስተምራል፡፡
“በጌታ ጥምቀት አዳም በገነት ዛፎች መካከል ያጣውን የጸጋውን
ልብስ አገኘው፡፡ እርሱ ወደ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ በውኃ ውስጥ ያንን የጸጋ ልብስ ለብሰው በእርሱም አጌጦና ተውቦ
ወጣ፡፡ ምኅረቱን ሙሉ ለሙሉ የሰጠን አምላካችን እርሱ የተመሰገነ ይሁን፡፡”
በጥምቀት የምንለብሰው መንፈስ ቅዱስን ቅዱስ ኤፍሬም ያዕቆብ በፎኖተ ሎዛ በሕልም ባየው መሰላል መስሎ ይገልጸዋል፡፡
“ወንድሞች ሆይ ዐይኖቻችሁን ክፈቱና ተመልከቱ ልክ ያዕቆብ
እንደተመለከተው መሰላል ዓይነት በአየሩ ላይ በዐይን የማይታይ አምድ ተተክሎ ይታያችኋል፡፡ የዚህ አምድ መሠረቱ
በመጠመቂያው ውኃው መካከል ሲሆን ጫፉም የሰማይን ደጆች ይነካል፡፡ በእርሱም ወደ መጠመቂያው ገንዳ ብርሃን ይወርዳል
፡፡ በእዚህም አምደ ብርሃን በኩል ተጠማቂያን ወደ ሰማያት ይነጠቃሉ ፡፡ በዚያም በአንድ ፍቅር ይገለጣሉ፡፡”
ስለጌታ ጥምቀት አስፈላጊነት ሲያስተምር እንዲህ ይላል ፡-
“ ውኆች በእኔ ጥምቀት ይቀደሳሉ፡፡ ከዚህ ውኃ የሚጠመቁ በእኔም
ምክንያት እሳታውያንና መንፈሳውያን ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ካልተጠመቁ በቀር ፍጹማን አይሆኑም፤ እኔም ከመሠረትኩት
ጥምቀት የሚጠመቅ ሰውም የሲኦል ሞት አይኖርበትም”
“እኔ በመሠረትኩት ጥምቀት እስረኞች ነጻ ይወጣሉ፡፡ የተጻፈውም
የእዳ ደብዳቤ ይሰረዛል፡፡ በጥምቀት ውኃ ውስጥም ተጠማቅያን እኔን ለማገልገል ሥልጣንን ይረከባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ
ሁሉ የሚሆነው እኔ ተጠምቄ ጥምቀትን ከባረኩዋት በኋላ ነው፡፡”
ጥምቀትን ሲያመሰግናትም እንዲህ ይላል፡፡
“ በልቡናችን ዐይኖች ጥምቀት እንዴት ውብ ናት ፡፡ ሁላችን ወደ
እርሱዋ እናስተውል፡፡ ማኅተም እንዲቀረጽ እንዲሁ እኛም በጥምቀት አርዓያውን እንመስል ዘንድ ተቀርጸናል፡፡ የበጎቹ
ልብ እንደ ወተት ነጭ ነው፡፡”
Source: http://eotcmk.org/site/component/contentbloglist/?task=editcontent&catid=22&id=1192
0 comments:
Post a Comment