• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 31 October 2015

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት እንድትጀምር ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡

    ሐራ ዘተዋሕዶ

    የሳተላይት ሥርጭቱ መካከለኛው ምሥራቅን፣ ደቡብ አውሮፓንና ሰሜን አፍሪቃን ያካልላል

    (አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፳፬፤ ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አገልጋዮችዋ እና ምእመናንዋ ድምፅዋን የምታሰማበትና መረጃ የምትሰጥበት የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት እንድትጀምር ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡ ከጥቅምት 12 ጀምሮ የዓመቱን የመጀመሪያ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በማካሔድ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ፣የቴሌቪዥን አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል የብር 12 ሚሊዮን 22 ሺሕ ዓመታዊ በጀት ከትላንት በስቲያ ማጽደቁ ታውቋል፡፡

    በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሚል ተዋቅሮ ሥራ አስኪያጅ በመሠየምና እስከ 22 ሠራተኞችን በመቅጠር የሚጀምረው አገልግሎቱ፤ ዝግጅቱንና ቀረጻውን በሀገር ውስጥ በማከናወንበሳተላይት እንደሚሠራጭ ተገልጧል፡፡

    በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሚመራውና ዘጠኝ አባላት ያሉት የብዙኃን መገናኛ ቦርድ፤ የሳተላይት ሥርጭት አገልግሎት የሚሰጠውን የኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ በመምረጥ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

    ባለፈው ማክሰኞ በሚዲያ ጥቅም፣ አሠራርና የወደፊት አቅጣጫ ዙሪያ ለምልአተ ጉባኤው አባላት ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ አመራሮች፤ የሳተላይት ሥርጭቱ ለጊዜው መካከለኛው ምሥራቅን፣ ደቡብ አውሮፓን፣ ሰሜንና ምሥራቅ አፍሪቃን የሚያካልል እንደኾነና ለተቀረው ዓለም ዝግጅቱን በኢንተርኔት በመጫን እንደሚያስተላልፍ አስረድተዋል፡፡

    መምሪያው፣ የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎችን በማስተባበር ያስጠናውን የአገልግሎቱን መተዳደርያ ደንብ፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲና የቴሌቪዥን ሥርጭት መመሪያ ባለፈው ዓመት ግንቦት በቅዱስ ሲኖዶሱ አጸድቋል፤ በቀጣይም የሬዲዮ ሥርጭት ለመጀመር መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡ ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችል መሠረታዊ የኦዲዮ ስቱዲዮ በመንበረ ፓትርያርኩ የሚገኝ ሲኾን አገልግሎቱ የሚፈጥረው የፋይናንስ አቅም ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

    የቴሌቭዥን አገልግሎቱን የ24 ሰዓት ሥርጭት ለማስጀመር ያኽል የጸደቀው የአንድ ዓመት በጀት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚሸፈን ሲኾን ለዘለቄታው ከማስታወቂያ፣ ከአየር ሰዓት ሽያጭና ከበጎ አድራጊዎች በሚገኘው ድጋፍ አገልግሎቱን ያጠናክራል፤ ተብሏል፡፡ በአሌክሳንደርያ ተዘጋጅቶ ቆጵሮስ እና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ የሳተላይት ኩባንያዎች የሚሠራጨው የግብጹ ኮፕቲክ ቴሌቭዥንወጪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመን በኾኑ ባዕለጸጋ መሸፈኑም አገልግሎቱን በፋይናንስ ከመደገፍ አኳያ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ባለሀብቶች የሚያስገነዝበው ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡

    በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ከ50 ሚሊዮን በላይ አገልጋዮችና ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያን፤ከሬዲዮና ከቴሌቭዥን ነባር ሚዲያዎች በተጨማሪ ዘመኑ የሚጠይቀውን የመገናኛ ቴክኖሎጂ ተጠቅማ ምእመናንዋን መጠበቅና ማስተማር ካልቻለች በተለይም ተተኪውን ወጣት ትውልድ ለመድረስ እንደሚያስቸግራት፣ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ይናገራሉ፡፡

    ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የብዙኃን መገናኛ ሥርጭት ጥናቱ ሲጀመር ከተመደቡት ሦስት ብፁዓን አባቶች ጋርየሚዲያ ጥናት እና የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴውን በማስተባበር፤ በግብጽና በእስራኤል ያሉ ተሞክሮዎችን በመዳሰስ፤ የሚዲያ ባለሞያዎችን በማትጋት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

    ብፁዕነታቸው፣ “ሚዲያ እና ዓለምአቀፋዊ አስተሳሰብ”በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የ24 ሰዓት የሳተላይት ሥርጭት የሚጀምረው የቴሌቪዥን አገልግሎቱ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነቷን፣ ሥርዐተ እምነቷን፣ ክርስቲያናዊ ትውፊቷንና ታሪኳን ለማስተማር፤ ቅዱሳት መካናቷንና ቅርሶቿን ለማስተዋወቅ፤ ተማሪዎችንና ምሁራኑን ለጥናትና ምርምር ለማነሣሣት፤ በየአህጉረ ስብከቱ የተሠሩ መልካም ሥራዎችን በማስፋፋትና ተቀራርቦ በመሥራት የምእመኑን ጠንካራ ድጋፍ ለማግኘት የግድ ያስፈልጋታል፤ ብለዋል፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት እንድትጀምር ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top