• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 20 October 2015

    ልጄን ከግብፅ ጠራሁትት.ሆሴዕ 11፡1

    የብኤሪ ልጅ ነቢዩ ሆሴዕ ይህንን የትንቢት ቃል የተናገረው ከክርሰቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምእተ ዓመት አጋማሽ ገደማ ሲሆን ሆሴዕ የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ያድናል ማለት ነው፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪኳ ከተዘረዘሩላት ሀገሮች መካከል ግብጽ አንዷ ስትሆን ግብጽ የብዙኀን አባት አብርሃም በረሃብ ምክንያት የተሰደደባት፣ ዮሴፍ በባርነት የተሸጠባት፣ ወገኖቹ እስራኤላውያን ለሁለት መቶ አስራ አምስት ዓመታት ያህል በባርነት የተገዙባት በኋላም የአለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ድንግል ማርያም ጋር የተሰደደባት ሀገር ስትሆን መሪዎቿም አህዛብ አማልዕክቷም ጣኦታት ነበሩ፡፡

    ነቢዩ ሆሴዕ የጌታችንን ሥደት ቀድሞ በትንቢት ከተናገሩት ውስጥ ሲሆን ልጄን ከግብፅ ጠራሁት በማለት የስደቱን ማብቃት ተናግሯል፡፡ በዚህ ትንቢት መሰረት መሰደዱን አልተነበየም፡፡ ነገር ግን ከስደት መመለሱን መናገሩ ካልተሰደደ መመለስ የለም በመመለሱ መሰደዱን ተናገረ፡፡

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የእመቤታችንን እና የልጇን ስደት በማሰብ ከመስከረም 26 እስከ ሕዳር 6 ያለውን ግዜ ወርኃ ጽጌ በማለት ታከብረዋለች፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ምድሪቱ በአበባ የምትሞላበት ጊዜ ከመሆኑም በላይ አበው ሊቃውንት እመቤታችንን በብዙ ኅብር መስለዋታል፡፡ በአበባ /ጽጌ/፣ በወይን ሐረግ፣መልካሙን የወይን ፍሬ አስገኝታለችና አበባ ፍሬን እንዲያስገኝ ድንግል ማርያምም ለሰው ያልተቻለውንና የማይቻለውን አንዴ ብቻ የሆነውን መለኮትን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በማህፀንዋ ተወሰነ፡፡

    አዳምና ልጆቹ እንዳይበላ በተከለከለችዋ ፍሬ ምክንያት ገነትን ከሚመስል ቦታ እግዚአብሔርን ከሚያክል ጌታ ተለዩ የሰዎች ድቀት ተጀመረ ሁሉን አጣ የመጀመሪያ በደል /ጥንተ አብሶ/ ማለት ይህ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የመለየትን ረጅም ግዜ ገፋ ገዥ የነበረው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሰለጠነበት፣ ጠላት በዛበት፣ ምድሪቱን ከፋችበት አዳምም ባለቀሰው መሪር እንባ ተስፋ ተሰጠው የህይወት ፍሬንም ዳግም እንዳይበላ በሱራፊ ታጠረችበት፡፡ ይህም የሚያመላክተው ሞትን የምታመጣ ዕፀ በለስን የበላ አዳም ደግሞ ዕፀ ህይወት ቢበላ ኖሮ ካሳ የማያስፈልገው ኢመዋቲ (immortal sinner) እንዳይሆን የእግዚአብሔር ቸርነት ከለከለችው፡፡

    ያንን የጨለማ ዘመን ፍጹም ተስፋ ያልጠፋበት ፍጹምም ተስፋ ያልተፈጸመበት ዘመን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ጀምሮ ለአርእስተ አበው ቃል ኪዳን ይገባ ነበር፡፡  በዚህም ቃል ኪዳን ውስጥ እመቤታችን በተስፋ አበው ውስጥ ታልፍ ነበረ "ማርያምሰ ተሐቱ ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባህርይ ጸአዳ" " ማርያምም በአዳም አብራክ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራ ነበር" በማለት ቅዱስ ያሬድ ገልጦታል፡፡ ነገር ግን የአበው ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት ሲፈፀም የድንግል ማርያም የህይወት ፍሬ /በገነት ተከልክላ የነበረችው የገነት ፍሬ/ አማናዊው ጌታ የሚበላ የሕይወት ፍሬ ሆኖ ከእመቤታችን ተወለደ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ገለጸው፡፡

    እመቤታችን መከራንና ስደትን የጀመረችው እርሷ ተፀንሳ ከተወለደችለት ጊዜ አንስቶ ነው በወርኃ ጽጌ እመቤታችን ጌታን በጀርባዋ አዝላ በበረሃ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የተሰደደችበትን ሙሉ ሕይወት በጥልቀት እናስነብባለን፡፡

    የጌታን ሕይወትከእመቤታችን የእመቤታችንን ከጌታ ለያይቶ ማየት አይቻልም መለኮታዊ ተግባራትን እና የማዳን ስራዎችን በቀር ምክንያቱም ለእርሱ ብቻ የተወሰነና ሊያደርገው የተገባ የአባቱ ተልዕኮ ስለነበረ "ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም አንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁ"፡፡ ዮሐ.6፡38 ፣ ዮሐ.5፡30 ነቢያት የተነበዩት ጊዜ ደርሶ በነቢዩ በሆሴዕ እንዳለውና መልአኩ ገብርኤል ለዮሴፍ ተገልጦ እንደነገረው አንድ ልጇን ይዛ ወደ ግብጹ ተሰደደች፡፡ ማቴ.2፡13

    የእመቤታችን ምክንያተ ስደትየእመቤታችን ስደት ብለን ስንናገር ከልጅዋ ጋር መሆኑን አንባቢ ሁሉ ልብ ሊለው የተገባ ሲሆን ስለ እመቤታችን ስደት ምክንያት አበው ያስተማሩንን፣ መጽሐፍት የመዘገቡልንን በጥቂት እንዘረዝራለን፤

    1. ትንቢተ ነቢያት
    እግዚአብሔር ሊያደርግ ያሰበውን ፈቃዱን ሁሉ ለሰው ልጅ እየገለጠ ነቢያትን ትንቢት እያናገረ መምህራንን እየላከ መጽሐፍትን እያጻፈ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ "እግዚአብሔር ይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ" እግዚአብሔር ለህዝቡ በመጽሐፍ ይናገራቸዋል መባሉ "በቀንና በሌሊት ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባቸው ነበር፣ አዎ ልኬባቸዋለሁ" ኤር.7፡25 በማለትገልጧል፡፡ ከነዚህም ትንቢታት መካከል ስለ እመቤታችንና ጌታ ስደት ሲሆን፡- ነቢዩ ኢሳይያስ 19፡1 "ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል" እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፡፡ በማለት ሲናገር ከሙሴና ከአሮን ጸሎት የተነሳ የግብጻውያን የእጃቸው ሥራ መጥፋቱን፣ እግዚአብሔር በናቡከደነጾር አድሮ ወደ ግብጽ መምጣቱን፣ጣዖታትን ማጥፋቱን የተነበየበት ከመሆኑ በላይ በዘባነ ማርያም ኅዙል /በማርያም ጀርባ ታዝሎ/ በፈጣን ደመና በተመሰለች ከእመቤታችን ጋር ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡

    ሊቃውንት እመቤታችንን ሲመስሏት ደመና ኢሳይያስ የሚሏትም ስለዚህ ነው፡፡ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ግብጽ በጣዖታት የተሞላች በመሆኗ የጌታችን ስደት በግብጽ ያሉ ጣዖታትን ለማጥፋት እንዲሆን ተጠቅሷል፡፡ ግብጻውያን ከጥንት ጀምሮ የላም፣ የፍየል፣ የአንበሳ ምስልን በመቅረጽ ያመልኩ ነበር፡፡ እነዚህን ለማጥፋት የጌታ ስደት ወደ ግብጽ ይሆን ዘንድ ትንቢት አናገረ፡፡ ከዚህም ባሻገር በኛ ሕይወትም ውስጥ ጌታን ለመቀበል ጌታ ስራ እንዲሰራብን በቅድስና ለመኖር የልብን ጣዖታት ማጥፋት ማጽዳት ይገባል፡፡ አልያ ጌታንና ጣዖትን በልባችን ማኖር አንችልም ቅዱስ ጳውሎስ "መኑ ደመሮ ለብርሃን ምስለ ጽልመት" ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር መስማማት አለው ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና፡፡ ያለው ለዚሁ ነው፡፡

    *.ቅዱስ ዳዊት፡-  መዝ. 83፡3 "ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች"፡፡ በማለት ሲተነብይ ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ሲል ነቢያት የተነበዩት ፍጻሜውን በእመቤታችን ማግኘቱን አንድም እመቤታችንበስደት ግብጽ መኖርያዋ ማድረጓን ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ሲል ዮሴፍና ሰሎሜም የሚኖሩበት ቤት ማግኘታቸውን ተናገረ፡፡ ለእመቤታችን ማደሪያ ጠፍቶ ማደሪያዋን ግብጽ ማድረጓን ተንብየዋል፡፡

    *.ነቢዩ ሆሴዕ፡- "እስራኤልን ሕጻን በነበረ ጊዜ ወደድኩት ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት" ምዕ. 11፡1 እስራኤል በግብጽ ሳሉ እንደተመረጡ ከዚያም አገር አውጥቶ መንግስት ይሆኑ ዘንድ እንዳበቃቸው የተናገረበት ትንቢት ከመሆን ጋር የጌታችን ወደ ግብጽ መሰደድ ሔሮድስ እስኪሞት በዚያ መቀመጡን ከዚያም መመለሱን የሚያመለክት መሆኑን ቅዱስ ማቴዎስ የነቢዩን ቃል ፍጻሜ አድርጎ ተናግሯል፡፡ ማቴ. 2፡15

    *.ትንቢተ ስምዖን፡- "ባንቺ ደግሞ ሰይፍ ያልፋል አላት" ሉቃ. 2፡34 ስምዖን በንጉሡ በጥሊሞስ ጊዜ መጽሐፍትን /ብሉያትን/ ከጥንቱ ዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ለማስተርጎም ሰባ ሊቃናትን ባዘዘበት ወቅት ስምዖን የኢሳያስ መጽሐፍ ይደርሰዋል፡፡ "እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች"፡፡ የሚለው ቃል ሲተረጎም ቢከብደው እንዴት ድንግል ትጸንሳለች ብዬ ልተርጉም ብሎ ሴት ትወልዳለች በማለት ቢጽፍ ተኝቶ ሲነሣ የጻፈው ጠፍቶ ድንግል ትጸንሳለች የሚል ተጽፎ ያገኛል፡፡ ይህ መሆኑ ቢገርመው መልአኩ መጥቶ ይህንን ሳታይ አትሞትም ብሎት ተሰወረ፡፡ በዚህም የትንቢቱን ፍጻሜ በቤተ መቅደስ እጅግ አርጅቶ ሳለ ጠበቀ፡፡

    ዮሴፍና እመቤታችን እንደ አይሁድ የመንጻት ሕግ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተመቅደስ ሲወስዳት ትንቢቱን ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን የጌታን ማዳን አየ "እነሆ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት" ሉቃ. 2፡34 በማለት ትንቢቱ መፈጸሙን ሲያይ ይህንን ካየሁ ባሪያህን በሰላም አሰናብተው ብሎ ሲለምን ገና ወደፊት የሚሆነውን የእመቤታችንን ስደት በልጇ አማካኝነት ወደፊት የሚደርስባትን መከራ ተነበየ፡፡ "ወለኪሰ ይበውእ ውስተ ነፍስኪ ኩናተ ኑፋቄ" ሰይፍ ያረፈበትን ለሁለት እንደሚከፈል ሁሉ የእመቤታችንን ልብ ከሐዘን ምሬት የተነሣ እንደምትጎዳ የተነበየው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከልጅዋ ጋር ተሰደደች ልብዋእንደ ሰይፍ የከፈሉት የእመቤታችን አምስቱ ሐዘናት የሚባሉት፤
    *.አይሁድ እንዲገድሉት በቤተመቅደስ ስምዖን ትንቢት በተናገረ ጊዜ፣  ሉቃ.2፡34
    *. እጅና እግሩን አስረው በጲላጦስ አደባባይ በገረፉት ጊዜ፣ዮሐ. 19፡1
    *.ጌታን ከኢየሩሳሌም ለበዓል ሔደው ሲመለሱ በመንገድ ባጣችው ጊዜ፣ ሉቃ. 2፡41
    *.በዕለተ ዓርብ ዕራቆቱን ተቸንክሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል በሰቀሉት ጊዜ፣ ማቴ.27፡38
    *.ወደ አዲስ መቃብር ውስጥ ባወረዱት ጊዜ ያዘነችው ሐዘን፣ ማቴ.27፡59
    አረጋዊው ስምዖን የተናገረው ትንቢት በእመቤታችን የሕይወት ዘመን ሁሉ በልጅዋ ምክንያት ሰይፍ የተባለ መከራ አልፎባታል በዚህም ሊቁ አባ ሕርያቆስ የእመቤታችነን ምልጃ ሲጠይቅ "አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኀዘ እም አዕይንትከ ወወረደ ዲበገጸ ፍቁር ወልድኪ" ድንግል ሆይ በልጅሽ ፊት የወረደውን ከአይንሽ የፈሰሰውን ዕንባ አሳስቢ በማለት ለኛ ለኃጢአተኛ ልጆችዋየምታማልደን ስለእንባዋ ይቅር እንደሚለን የተናገረው፡፡

    2. ስደተ ቅዱሳንን ለመባረክ ተሰደደ፡-የክርስትና ህይወት የመስቀል ላይ ጉዞ በመሆኑ ክርስቶስን አምነው ለተከተሉት ሁሉ በመከራና በስደት እንደሚያልፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከአለም ተመርጠው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር"እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ"በማለት ተናገረ፡፡ ማቴ. 16፡24 በዚህም ቃል መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ክርስቲያኖች በብዙ መከራ ውስጥ አለፉ በበረሃ ተሰደዱ፣ በዱር በገደሉ ተቅበዘበዙ በሰይፉ ተተረተሩ፣ በድንጋይ ተወገሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን በእምነት የተሰደድን የተጨነቅን የምንጸልየው ስደትን ከኛ በፊት በሕጻንነቱ በቀመሰ ስደትን በሚያውቅአምላክ ፊት ነው፡፡

    3. ጣኦታተ ግብጽን ለማጥፋት ተሰደደ፡-
    ግብጽ ከነገሥታቶቿ ጀምሮ ጣኦትን የሚያመልኩ አህዛብ የነበሩ ህዝቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጣኦታት ደግሞ የእንስሳትን ምስል በማስመሰል ደንጊያ ጠርበው እንጨት አለዝበው ማዕድን አቅልጠው የበሬ፣ የላም፣ የአንበሳ፣ የወፍ ምስል አስቀርጸው ያመልኩ ስለነበር ከተማዋ በጣኦታት የተሞላች ነበር፡፡ ለዚህም ጌታችን ጣኦታትን ሊያፈርስ ወደ ግብጽ ተሰደደ ገና ከተማዋ ሲገባ በጣኦታቱ ላይ ያደሩ አጋንንት ይጮሁ ጣኦታቱም ይሰባበሩ ጀመር፤

    4. ሰው መሆኑን ለመግለጽ ተሰደደ፡-
    ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ሳይለቅ ከሄድሮስ ዓይን መሠወር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በአምላካዊ ጥበቡ ከሄሮድስ ዓይን ተሰውሮ ቢሆን ሥጋ መልበሱ ሰው መሆኑን አይገለጽም ነበር፡፡ በሄሮድስ ዓይን የማይታይ ከሆነ ሥጋ ሳይለብስ የለበሰ መስሎ የተገለጸ ሥጋና አጥንት የሌለው /ምትሐት/ ነው በተባለም ነበር፡፡ ከአዳም አካል አንድም ያልጎደለው ሙሉ ዳግማዊ አዳም መሆኑን እና የለበሰው ሥጋ የሚደማ የሚቆስል በሰይፍም ሆነ በጦር ቢወጋ ጉዳት የሚደርስበት ሰብአዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ስደተኛ ሆነ፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከጠላቱ ማምለጥ የሚችለው ከጠላቱ ፊት ዞር በማለቱ እና በመሸሹ ስለሆነ ጌታም ከጠላቱ ከሄሮድስ ለማምለጥ ሰው እንደመሆኑ ወደ ግብጽ ሸሸ፡፡

    5. ዲያብሎስን ለማሳደድ ተሰደደ፡-
    አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት እየራቀ ሄደ፡፡ ይህን የፈጣሪና የፍጡር መራራቅ ያመጣው ዲያብሎስ ሲሆን በፈጣሪ መራቅ ፈንታ እርሱ መቅረብ ይፈልግ ነበር፡፡ ስለሆነም ፈጣሪው ከሰው ጓሮ ወደ ወጣበት የሰው ልጅ ሳይጠራ መምጣት ወይም መቅረብ ጀመረ፡፡ ዲያብሎስ የአዳምን ልጆች ተቆጣጠራቸው፡፡ ልባቸውን በፍቅረ ጣኦት ሸፍኖ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዳያዩ አደረጋቸው ብዙ የአዳም ልጆችም የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይሆንየሰይጣንን ፈቃድ ሲፈጽሙ ኖሩ፡፡ ጌታም "አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጪ ይጣላል"፡፡ ዮሐ. 12፡31 በማለት ሰይጣን ዓለሙን ተቆጣጥሮት እንደነበረ ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ በለበሰ ጊዜ የፈጣሪና የፍጡር ግንኙነት እንደገና ተመሠረተ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ለቆ በመውጣቱ ዲያብሎስን ከተቆጣጠረው ከሰው ልቡና አስወጣው ጌታ ከሄሮድስ ፊት እየራቀ ሲሄድ ዲያብሎስም ከሰው ፊት እየራቀ ሄደ፡፡ የጌታ ስደት በተዘዋዋሪ የዲያብሎስ ስደት ሆነ ጌታ የሚቀበለው መከራ ሁሉ ዲያብሎስን በርቀት የሚመታ መሣርያ ነበር፡፡

    በመጨረሻም በመስቀል ላይ የሆነው የጌታ ሞት የዲያብሎስ ሞት ሆነ፡፡ጾመ ጽጌከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ቀን ያለው 40 ቀን ዘመነ ጽጌ ይባላል፡፡ ይህ 40ው ቀን የእመቤታችንና የጌታችን ስደት የሚታሰብበት ወይም የሚከበርበት ዘመን ነው፡፡ በተለይም በ40ው ቀናት ውስጥ በሚገኝ አሑደች ካህናትና ምዕመናን ቤተክርስቲያን ያድራሉ፡፡ ካህናቱ ይዘምራሉ /ማህሌተ ጽጌን/ ይቆማሉ ምዕመናን ያጨበጭባሉ እልል አሜን ይላሉ፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችን በአበባ ጌታችን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ፡፡የጽጌ ጾም ከወቅቱ ጋር ተያይዞ የሚጾሙ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾመ ጽጌ መንፈሳውያን ሰዎች ሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ወይም የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖና ከታዘዙት አጽዋማት ውጪ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰው የመጾሙን ዋጋ ያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ "እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል፡" ሉቃ. 7፡47

    የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋር ይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾምየለባቸውም፡፡ የማይጾሙ ሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡ "ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ" ማቴ. 6፡16 የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ጾም ነው፡፡

    ይቀጥላል

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ልጄን ከግብፅ ጠራሁትት.ሆሴዕ 11፡1 Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top