ይህን መሠረታዊ የነገረ ማርያም (Mariology) ትምህርት በተአምረ ማርያም ላይ ተጽፎ የምናነበው ሲሆን አንዳንድ ሰዎች የተአምረ ማርያም መቅድም ላይ የተገለጹት ነገሮች ግራ የሚያጋባቸው ሌሎቹም ክህደት የያዘ አስምስለው የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በይዘት ደረጃ አዲስ የኑፋቄ ትምህርት ባያመጡም ቀድሞ እነ ንስጥሮስና መቅዶንዮስ የተረቱበትን የጥርጥር ትምህርት በመያዝ
፩) እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር እንዴት ታወቀች?
፪) ተአምሯን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታልን?
፫) ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረን? የሚሉትና ሌሎችን ኃይለ ቃሎች እንደ ማሰናከያ አድርገው ያቀርባሉ፡፡
በመሆኑም ለነዚህም ጽንሰ ሐሳቦች መሠረታዊ የሆነ ማብራሪያ ለመስጠት አበው ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ ይላሉና ለጽሑፋችን ያግዘን ዘንድ ኦርቶዶክሳዊ ታሪኮችንና ትውፊቶችን በመተረክ እንጀምራለን፡፡
በቅድሚያ የአንድን ጽሑፍ ትክክለኛ ጭብጥና የጽሑፉንም ትንታኔ ለማቅረብ ጽሑፉንም ለመገምገምና ለመተቸት በርካታ ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህም መካከል የጸሐፊውን ማንነት (ትምህርት)፣ ሕይወት፣ ልምድ፣ የጸሐፊውን ሌሎች ሥራዎች፣ ጽሑፍ በተጻፈበት ወቅት የነበሩትን ተጨባጭ ታሪካዊ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ክስተቶች የዚያን ዘመን የስነ ጽሑፍ ስልት መመልከት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ተአምረ ማርያምን ገለጥ አድርገን ስንመለከት በኅትመቱ ሁለት መቅድሞችን እናስተውላለን የመጀመሪያው መቅድም "የዘወትር መቅድም" የሚል ርእስ ሲኖረው ስለራሱ የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ሁለተኛው ግን መቅድሙ ራሱ መዓልቃ ከተባለች ቦታ ከግብፅ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ይህም ማለት ትርጉም እንጂ እዚህ እኛ ሀገር እንዳልተጻፈ የሚያስረዳ ነው፡፡
በእርግጥ "መቅድሙ ትርጉም ነው ወይስ የእኛ ሀገር ድርሰት (ጽሑፍ)?" የሚለውን ጥያቄ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም እስካሁንየሀገር ውስጥ መሆኑን የሚያመለክት የጽሑፍ ማስረጃ እንዳልተገኘ የነገረ ማርያም ሊቃውንት (Mariologist) ይናገራሉ፡፡
ከምናነበው ተአምረ ማርያም ካለው መቅድም ግን የምንረዳቸው ቢያንስ ሁለት ዐበይት ጥቆማዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ተአምረ ማርያምንና አጠቃቀሙን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሥርዓት ተተርገሞ የመጣልን መሆኑን ነው፡፡ ይህንንም ራሱ መቅድሙ "ይሁ የሥርዓት መጽሐፍ የምሥር ዕፃ ከሚሆን ከመዓልቃ ቦታ ከሐዋርያው ከማርቆስ መንበር ተገኝቶ የወጣ ነው" ሲል ይገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዚሁ በመቅድሙ ቁጥር ስድስት እስከ ስምንት የተገለጸው ቃል የሚያስተላልፈው መልዕክት ነው፡፡ ቃሉ "አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል በሚባሉ ጳጳሳት ዘመን አባ ዮሐንስም ኤጲስ ቆጶስነት በተሸመበት ወራት ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በሶት ዓመት የሥርዓታቸውም መጽሐፍ ከዐረብ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ሰዎች በግዕዝ ቋንቋ ተተረጎመች ቆስጠንጢኖስ የተባለ ንጉሳችን በዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በነገሠም በሰባት ዓመት የሥርዓታቸውም መጽሐፍ እንዲህ ይላል" የሚለው ነው፡፡ ይህ ቃል ከዐረብኛ የተተረጎመ ሳይሆን ከዚሁ ከእኛ ያሉ ሊቃውንት ከግብፅ የመጣውን ሥርዓት በተረጎሙበት ወቅት ስለትርጓሜው የጨመሩት ታሪክ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ዐቢይ ጭብጥ ከግብፅ የመጣው የዐረብኛ የሥርዓት መጽሐፍ ሲተረጎም ለኢትዮጵያውያን በሚያመችና ለአጠቃቀም በሚቀል /በሥርዓተ ጸሎቱ/ የሚገባውን ቦታ ሲያገኝ ለዚህ መግቢያም መርገፍም የሆኑ በዜማ የሚባሉ ነገሮች ስላለው እነዚህን በማደራጀት እንደተዘጋጀ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ የዘወትር መቅድም የሚለው በዚህ አደረጃጀት ወቅት ተለይቶ እንደተቀመጠ እናምናለን፡፡
መቅድሙን የዘወትርና ዋና ወይም የክብረ በዓል ያሰኘውም በንባቡ ጊዜ የሚፈጽመው ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የጊዜ አጠቃቀም ባህልምግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ ከራሱ ከመቅድሙ ንባብ ልንገነዘበው የሚገባንን ከተመለከትን መቅድሙ መጣበት ስለሚባለው ቦታም በጥቂቱ እንመልከት ቀደም ብለንእንደጠቆምነው ከራሱ ከመቅድሙ በተጨማሪ የግብጽ ቤተክርስቲያን ኢንሳይክሎፒዲያ (The Coptic encyclopedia) በዘርዐ ያዕቆብ ዘመን" ለእመቤታችን፣ በስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በጣልያን፣ በሶርያናበግብፅ ያደረገቻቸው ብዙ ተአምራት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቋንቋ በሆነው በግዕዝ ቋንቋ ተተርጉመዋል በዚህ ጊዜ የእመቤታችን 33 በዓላት (፴፫) በዓመት ውስጥ እንዲከበሩ የሚያዝዘው መጽሐፈ ሥርዓት ከመዓልቃ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣተደርጓል ይላል፡፡ (The Coptic encyclopedia page.984)
መቅድሙ የመጣው ከመዓልቃ ከሆነ መዓልቃ ማናት? የሚል ጥያቄ ከተነሣ፣ መዓልቃ በአሁኑ ጊዜ በጥንቱ ካይሮ (Old Cairo) የምትገኝ ጥንታዊትና ታሪካዊት ከመሆኗም ባሻገር ሊቃውንትና መጻሕፍት በብዛት የነበሩባት ቦታ ናት፡፡ በጥንቱ ካይሮ ወይም ምስር ከከሚገኙት ብዙ የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል መዓልቃ ጥንታዊት የእመቤታችን ቤተክርስቲያንናት ከዚህም በላይ ይህች ቤተክርስቲያን በዓለም ላይ ከተሰሩት የመጀመሪያዎቹ ቤተክርስቲያናት ውስጥ የምትቆጠርና በመጀመሪያው መቶ ዓመት ውስጥ የተሠራች እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ግብፅ ውስጥ የነበሩ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አምልኮታቸውን የፈጸሙባት ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ (The flight of the holy family to Egypt page 9) ይህ ደግሞ በራሱ "ከመንበረ ማርቆስ" የተገኘች ለሚለው የመቅድሙ አገላለጽ እውነተኛነት ማረጋገጫ ይሆንልናል፡፡ መዓልቃ በግብፅ ቤተክርስቲያን ታሪክ ለረጅም ጊዜያት መንበረ ፓትርያርክ ከሆኑት ቦታዎች አንዷ ናት፡፡ ለአብነትም ከ፳ሺህ ፺፩ እስከ ፩ሺህ ፩፻፵፭ እና ከ፩ሺህ ፩፻፺፯ እስከ ካልዓይ ቴዎድሮስ ድረስ መደበኛ መቀመጫ ነበረች (፩ሺህ ፪፻፺፬ - ፩ሺህ ፴፻)፡፡ ይህ ካልን ዘንዳ ወደ ተነሳንበት ኃይለ ቃል እንመለስና ለጥያቄዎቹ መሠረታዊ መልስ እንጻፍ
፩) እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር፡፡
እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ስለሚፈጥረው ዓለም አያውቅም ነበርን? የዓለምንስ ፍጻሜ አያውቅምን? የእግዚአብሔርን ፍጹም አዋቂነት የሚያምን ሁሉ አያውቅም ሊል አይችልም ራሱ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው "አሜሃ ይብሎሙ ንጉሥ ለእለ በየማኑ ንዑ ቡሩካኑ ለአቡየ ትረሱ መንግስተ ዘእስተዳለወለክሙ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም፡- ያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል አባቴ የባረካችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀላችሁን መንግስት ትወርሱ ዘንድ ኑ"ሲል አስተምሮናል፡፡ (ማቴ ፳፭÷፴፭) በዚህ ትምህርቱ ዓለም ሳይፈጠር እመቤታችን መታሰቧ ብቻ ሳይሆን ከእርሷሰው ሆኖ ዓለምን ማዳኑ በዕለተ ምጽዓትም በቀኙ የሚቆሙትና በግራ የሚቆሙት ሁሉ መታወቃቸው ተጽፏል፡፡
ዓለም ሳይፈጠር ሥሉስ ቅዱስ በፈቃድ አንድ መሆናቸውንና የአካላዊ ቃል ከእመቤታችን ሰው መሆኑ መታወቁን ብቻ ሳይሆን በሰው ድኅነትም ሥላሴ መደሰታቸውን ለማስረዳት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን እነርሱደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ" ሲል ገልጾለታል፡፡ (ዮሐ ፲፯÷፳፬) ይህ ንግግር አካላዊ ቃል በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ሰውን መውደዱን፣ አብ ቅድመ ሥጋዌ በሥጋዌ መደሰቱን ለመግለጽ የተነገረ ነው፡፡
እመቤታችን በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር የሚለውም ሥጋዊው ዓለም ሳይፈጠር ይታወቃል፤ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑ በመታወቁም እርሷ ዓለም ሳይፈጠር ተመርጣለች ታውቃለች ስለዚህም ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይህን በዚህ መልክ የአምላክ ሰው መሆን መታወቁ ትክክል ነው ነገር ግን እመቤታችን ገና ሳትወለድ እንዴት ልትታወቅ ትችላለች? የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ "ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ ዓዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይቀር በመጽሐፍ ተጻፉ" በማለት ገና ሳንወለድ እግዚአብሔር እንደሚያውቀን ይነግረናል (መዝ ፻፴፲÷፲፭) ነቢዩ ወደፊት የሚመጣው ነገር ከመኖሩ በፊትም አንድስ ስንኳ ሳይቀር በመጽሐፉ ቀድሞ መጻፉን ከነገረን ስለ እመቤታችን እንዲህ መባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን እንረዳለን፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የእግዚአብሔርን ዐዋቂነት ቢያምኑም "እመቤታችን ብቻዋን አትታወቅም" የሚል መከራከሪያን ያመጣሉ፡፡ ይህ ንግግራቸውም ራሳቸው ለእመቤታችን ያላቸውን አመለካከት ወይም ዓይናቸውን ጨፍነው መካድ የሚፈልጉ መሆናቸውን ያሳየናል እንጂ የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀታቸውን ሊያሳይ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል ስለ ሁሉም ግን አልተናገረም አልተጻፈምም፡፡ ትንቢት የተነገረላቸው ወይም በሥራቸው እግዚአብሔርን ምን ያህል ደስ እንደሚያሰኙት እርሱ ያወቃቸው ብቻ ናቸው፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስን "በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ በማኅፀንም ቀድሼሃለሁ"ብሎታል፡፡ (ኤር ፩÷፭) ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ሌሎቹን በእናታቸው ማኅፀን አያውቃቸውም ሳይወለዱና አድገው የሚሆኑትን ሳይሆኑ አስቀድሞ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ ዳዊት "ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ" እንዳለ ሁላችንንምአስቀድሞ ያውቀናል፡፡ (መዝ ፳፩÷፲)
ነቢየ እግዚአብሔር ኤርሚያስ የተናገረው ግን በተለየ ሁኔታ ትንቢት የተነገረላቸው ሰዎች አስቀድሞ የሚሆኑትና ቅድስናቸው የታወቀላቸው መሆኑን መናገር ነው፡፡ "ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ" ያለው ገና ሳይወለድ ነው፡፡ ነቢይነትን ተሹሞ ወይም ተቀብቶ በምድር ላይ ከመጣ በኋላ አይደለም ነገር ግን ከተወለደና ካደገ በኋላ የሚደርስበት በዓርግና ቅድስና ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን መናገሩ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎም ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት "ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደተነገረው ትንቢት በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ" ያለው "ጢሞቴዎስ" በስም ተጠቅሶ ትንቢት ተነግሮለት አይደለም፡፡ ፩ኛ ጢሞ ፩÷፲፰ ነገር ግን ስለ ሐዲስ ኪዳን ካህናትና ሐዋርያት የተነገረው ለእርሱ የተነገረ መሆኑ የታወቀ በመሆኑ ነው፡፡
እንደዚሁ ሁሉ ስለ አምላክ ሰው መሆን አስቀድሞ የታወቀነው ሲባል እመቤታችን ትታወቃለች ማለት ነው፡፡ ሥጋዌውን ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር ያውቀዋል ያስበዋል ማለትም እመቤታችን ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡
፪. ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ
አንዳንድ ሰዎች በአጉል ዐወቅን ፈሊጥ እንዲህ ዐይነት አገላለጽ የአለማወቅ ይመስላቸዋል፡፡ አሁን አሁንማ አንዳንዶቹ "ይህን የጻፉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ቢያውቁ እንዲህ አይም ነበር" እስከ ማለትም ደርሰዋል፡፡ ለመሆኑ የትኛው ነው መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቀው?ቀደም ብለን በመግቢያው ላይ የእመቤታችን ተአምር ከየት ከየት እንደተተረጎመና ምን ዐይነት ሊቃውንት እንዳስተረጉሙት በመዓልቃ ከነበሩት ሊቃውንት ጥቂቶቹን አስቀድመን ያየነው የማናውቃቸውን ቅዱሳን አበው መዳፈር አይገባም ለማለት ነው፡፡ መጽሐፍ "ለቅኖች ምስጋና ይገባል" ይላል፡፡ ቅኖችን የማያመሰግኑ ሰዎች ግን ይኖራሉ ይህም በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ለቅኖች የሚገባውን ምስጋና ካለማወቅ ሲሆን ሁለተኛው ግን ቅኖችንም ካለማወቅ ነው፡፡ አሁን የምናየው ግን "ቅኑን" አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ቅንነትን ወይም ቅን የሚያሰኘውንም አለማወቅን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን በአለማወቅ ፍጹምነት ደረጃ ላይ መድረስም ነው፡፡
በዕውቀትና በቅድስና ወደ ፍጹምነት የሚሄዱ መኖራቸውን ያህል በርኩሰትና በአለማወቅ በድፍረትና በትንዕቢትም ወደ ፍጹምነት የሚሔዱ አሉ ማለት ነው፡፡ ቅንነትን አለማወቅን ያነሳነው በድንገት አይደለም፡፡ በቅንነት የሚያስብ ሰው ቢያንስ ይህን መጽሐፍ /ተአምረ ማርያምን/ ለአገልግት የሚጠቀሙበት ኦርቶዶክሳውያን ወይም ቤተ ክርስቲያኗ ራሷ ስለ ሥነ ፍጥረት የምታስተምረው ትምህርት ምንድነው? ለመሆኑ ፍጥረታት ለምን ዓላማ ተፈጠሩ ትላለች? እያለ ይጠይቃል፡፡ ለጥያቄው የሚያገኘው መልስ "እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ" የሚል ከሆነ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ መሆኑን ተረድቶ ያንን ሊተች ይችላል፡፡
ሥነ ፍጥረት ላይ ያለው ለየት ያለ ከሆነ ግን የየዚህ የተአምረ ማርያም አገላለጽ ምን ማለት ነው? በሥነ ፍጥረት ላይ ካለው /ፍጥረታት ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ለመኖር ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ፣ ለአንክሮ ለተዘክሮ/ ለእነዚህ ለሶስቱ ዓላማዎች ተፈጠሩ ከሚለው ትምህርት አንጻር ምን ማለት ነው? ሥነ ጽሑፋዊ አገላለጹስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሥነ ጽሑፍ ትውፊት አንጻር ምን መልእክት አለው? የሚለውን ይጠይቃል፡፡
እነዚህን ነገሮች ለማየት ደግሞ እንኳን ሃይማኖት ያለው ሆኖ ቀርቶ በሥነ ጽሑፍ ግምገማም ዕውቀትና ግንዛቤ መያዝ ብቻ ሊበቃ ይችላል፡፡ እኛም የዚህን ጥያቄ መልስ የምንመልስላችሁ ከዚሁ ነጥብ በመነሣት ይሆናል፡፡ ፍጥረታት የተፈጠሩበት አላማ ከላይ የተገለጹት ሦስቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የእግዚአብሔርን ስሙን ቀድሶ ክብሩን ወርሶ ለመኖሩ የተፈጠሩ አሉ የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ሰውና መላእክት ናቸው፡፡ ሰውና መላእክት እግዚአብሔርን በማመስገናቸው ለእግዚአብሔር የሚጨምሩለት ክብር የለም፡፡ ነገር ግን የተፈጠሩለትን ዓለማ ውጤታማ በማድረግ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ክብር ይወርሳሉ፡፡
ከቅዱሳት መጻሕፍት መሰጠት በኋላ የሰው ልጅ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል አምኖ መጠቀም በቃለ መጻሕፍትም መኖር ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህም ስለ እመቤታችን የተጻፈውን መፈጸም ይገባል፡፡ ራሷ እመቤታችን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ኤልሳቤጥ እንዳመሰገኑኝሁሉ "ከአሁን በኋላ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል" በማለት ገልጻዋለች፡፡ ሉቃ ፩÷፵፰፡፡ ይህን ቃል ስትናገር ቅዱስ ሉቃስ እመቤታችን ጋር አልነበረም ነገር ግን ትመሰገን ዘንድ ጸጋውን የሰጣት እግዚአብሔር በጸጋ ገልጾለት በኋላ ዘመን በመጽሐፉ ገለጸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎ እንደተናገረው "እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጠራቱ አይጸጸትምና፡፡ "ሮሜ፲፩÷፳፱
ስለዚህ በክርስቶስ አምናለሁ ለሚል የወንጌል ቃል መቃወም አይችልም፡፡ "ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል" በሚለው ቃል እንስማማለን ነገር ግን የመቅድሙ ቃል የሚለው "ፍጥረት ሁሉ እመቤታችን ለማመስገን ተፈጠረ" ነው ስለዚህ ይህ እንዴት ሊስማማ ይችላል እንል ይሆናል፡፡ ለዚህም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉ አንዳንድ አገላለጾችን ካስተዋልናቸው ልንቸገር አንችልም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ "በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣች" ሲል ገልቷል፡፡ ሉቃ ፪÷፩ ታዲያ ቄሳር አውግስጦስ ያወጣው ትእዛዝ በውኑ ለዓለም ሁሉ ነውን? አይደለም፡፡
ቅዱስ ሉቃስ "ዓለም" ያለው በአውግስጦስ ቄሳር ግዛት ሥር ያሉትን አገሮች እና በዚያም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ በማጠቃለል እንጂ ዓለም የሚለውን ቃል ባለማወቅ ወይንም የዓለሙን ገዥ የእግዚአብሔርን ሥልጣን ለአውግስጦስ ቄሳር በመስጠት አይደለም፡፡ የመቅድመ ተአምረ ማርያም ጸሐፊዎችም መቅድሙን የጻፉት በሐዲስ ኪዳን ዘመን ነው፡፡ ስለዚህ "ፍጥረት ሁሉ" ሲሉ አማኞችን ብቻ እንደሚመለከት ግልጽ ነው፡፡ በዚያውም ላይ እመቤታችን "ትውልድ ሁሉ" ካለችው ጋር ልዩነት የለውም፡፡ "ለማመስገን ተፈጠረ" ማለትም ከዚህ በኋላ /እመቤታችን ከተናገረች በኋላ/ ያለው ትውልድ በወንጌል የማያምንና በቃለ መጻሕፍትም የማያምን ካልሆነ በቀር እመቤታችን ማመስገን ግዴታው ነው፡፡ ኤልሳቤጥን በወንጌል ሊቃውንትንም በኤፌሶን ጉባኤ ተመልክቶ "የጌታዬ እናት""ወላዲተ አምላክ /Theotokos/ እያለ ያመሰግናል፡፡
ስለዚህ እንዲህ እያለ ለማመስገን ተፈጠረ ቢባል ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? ዓረፍተ ነገሩ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ብቻ አይገልጽም ከዚህ ያለፈና ሆን ተብሎ የእግዚአብሔርን ክብር ለእርሷ ለመስጠት የተጻፈ ነው የሚል ካለ ማስረጃውን አቅርቦ ለዚያውም በቅንነት ቋንቋው እንዲታረም ቢጠይቅ ያስመሰግነው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም ጌታን ሳያውቁ እመቤታችን ሊያውቁ እርሱን ጌታዬ ሳይሉ እርሷን የጌታዬ እናት እርሱን አምላክ ሳይሉ እርሷን ወላዲተ አምላክ ብለው ሊያመሰግኑ የሚችሉ ሰዎች የሉም፡፡ አማኙ /ምእመኑ/ ጌታችንን ሳያመሰግን የጌቶች ጌታ ሳይል በእርሱ ማመኑን ትቶ ለእመቤታችን የአምምልኮት ምስጋና ቢያቀርብ የፈጣሪን ምስጋና ለእርሷ ለምን እንሰጣለን የሚል ጥያቄን ማንሣት ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ግን አልተደረገም ሊደረግም አይችልም፡፡
፫. ተአምሯን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል፡፡
ይህን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት በመጀመሪያ በመቅድሙ የተጻፈውን ቃል እንዳለ መመልከት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ "አስቀድመን እንደተናገርን የታወቀ ምክንያት ኃጢአት ደዌ ካልከለከለው በዚች ቀን ተአምሯን ሰምሮ ሥጋውን ደሙን ይቀበል፡፡ ሥጋውን ደሙን መቀበል ካልተቻለው ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሂድ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል ይደረግልኛል በማለት ቢሰማ፡፡" ይላል የዚህን አንቀጽ መልእክት አንድ በአንድ በመተንተን ስንመለከት የሚከተሉትን ሦስት ዐበይት መልእክቶች እናገኛለን፡፡
ሀ.ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ፡- ይህ አንቀጽ በመጀመሪያ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዋናነት የሚያስተላልፈው መልእክት ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በፍትሐ ነገሥት "ከቀዳም ሥዑር በቀር ቅዳሜ ቅዳሜ እና እሑድ እሑድ በቤተ ክርስቲያን ተሰብስባችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀብላችሁ ደስ ይበላችሁ"ተብሎ ታዝዟል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በበረሐ ያሉ ባሕታውያን ሳይቀሩ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋው ደሙን የሚቀበላቸው ሰንበት ነው፡፡ /በዓላት- ምን? ለምን? እንዴት? ገጽ ፵፮ እና ፷፮/
ነገር ግን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አንድ ሰው ሥጋውን ደሙን እንዳይቀበል ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም በዚህ አንቀጽ የተገለጹት አንደኛ የታወቀ ምክንያት /እንደ ወሊድ፣ ሐዘን፣ ለቅሶ፣../ የመሳሰሉት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ ይከለክሉታል ተብለው ከተጠቀሱት በመጨረሻ የተገለጸው ደግሞ ደዌ ነው፡፡ አንድ ሰው በደዌ ምክንያት ፈሳሽ ነገር ከሰውነቱ እየወጣ፣ ደም እየፈሰሰው ይህን የመሰሉ ነገሮች እያሉበት ሥጋውን ደሙን ላይቀበል ይችላል፡፡
እነዚህ ሁሉ ግን ሰውየውን በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ተገኝቶ ከመጸለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን ምንባባት ከመስማት ግን ላይከለክሉት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እነዚህ ምክንያቶች ካልከለከሉት በቀር ሥጋውን ደሙን ይቀበል በማለት ወንጌልን ይሰብካል እንጂ ከወንጌል የወጣ ቃል የለውም፡፡
ለ.ቤተ ክርስቲያን አትቅር፡- ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሥጋውን ደሙን መቀበል ባይቻልህ ግን ሥጋውን ደሙን መቀበል አይቻለኝም ብለህ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሔድ አትከልከል ነው የሚለው፡፡ ተአምረ ማርያም ከቅዳሴ በፊት ያለው የቤተ ክርስቲያን የጸሎት ክፍል አንድ አካል ነው፡፡ መቅድሙም የሚለው "ሥጋውን ደሙን መቀበል ካልተቻለው ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሒድ" ነው፡፡ ይህም ማለት ባትቆርብም ቤተ ክርስቲያን አትቅር ማለት ነው፡፡ በጸሎቱ ትምህርቱና በመሳሰለው መርሐ ግብር ሁሉ ተሳተፍ፡፡ ዕለቱ ሰንበትና በዓላት ከሆነ አንድ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ካልሔደ በዚያም ተገኝቶ ካልተማረ ካላመሰገነ ክርስትናውን በምን ይገልጸዋል?
በዚህ አገላለጽ"ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሒድ"የሚለውን በአስተውሎትና በቅንነት ከተመለከትነው የሚናገረው ስለተአምሯ ብቻ አይደለም፡፡ "ተአምሯን አታስታጉሉ" ሲል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂዳችሁ በዚያ ባለው አገልግሎት ተሳተፉ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ተአምረ ማርያም እንዴትና መቼ እንደሚነበብ እናውቃለን፡፡ ከተአምሩም በፊት ከተአምሩም በኋላ ሌሎች ጸሎቶችና ምንባባት አሉ፡፡ ይህን አጠቃላይ አገልግሎት ለምእመኑ በታወቀ በተረዳ ነገር በዚህ ስያሜ ማስታወቅ ክፋትም ኃጢአትም አይደለም፡፡ ሌላው አገልግሎት በዚህ አገላለጽ ለምን ጠሩት ቢባል በትርጓሜ ውዳሴ ማርያም ላይ እንደተጻፈው ሌላውን አገልግሎት በመናቅ በማቅለል ሳይሆን ለእመቤታችን ባላቸው ፍቅር ነው፡፡
ሐ.አትጠራጠር፡- ሦስተኛውና የመጨረሻው የዚህ አንቀጽ መልእክት በታወቀ ምክንያት "በዚህች ዕለት" ሥጋውን ደሙን መቀበል ባይቻልህ ለሌሎቹ የተደረገው አይደረግልኝም የዕለቱ በረከት አይደርሰኝም ብለህ አትጠራጠር የሚል ነው፡፡ መጽሐፉ የተአምራት መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ተአምራትም የሚደረገውና ተአምራትም የሚያሰኛቸው ከዘወትራዊ የሕይወት ተግባራትና ድርጊቶች የተለየ ለሰው የማይቻል በእግዚአብሔር ብቻ የሚቻል ነገር መደረጉ በመሆኑ አንተም "ይደረግልኛል" በማለት በእምነት ከጸሎቱ ተካፍለህ ከተአምሯ ሰምተህ ብትሔድ በዕለቱ የቆረቡትን ሰዎች በረከት ታገኛለህ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተፃፈ ነው፡፡ ራሱ ጌታችን በወንጌል የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት ቢኖራችሁ ተራራ ማፍለስ ባሕር መክፈል… ትችላላችሁ ሲል አስተምሮአል፡፡ ይህም በእምነት ኃይለ እግዚአብሔርን በረከተ እግዚአብሔርን ታገኛላችሁ ከእግዚአብሔር ትገናኛላችሁ ማለት ነው፡፡
ሥጋ ወደሙ በየሳምንቱ ወይም ከዚህ ባነሰም ይሁን በበዛም የምንቀበለው ለዚሁ ኃይለ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርገን ኃጢአታችን አስተሥርየን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ አግኝተን ለመኖር ነው፡፡ በዚያች ዕለት አልቻልህ ብሎ ባትቀበል በእምነትም ይህን ታገኛለህና አትጠራጠር ይሉናል ሊቃውንቱ፡፡
ይህን የሚመስል ታሪክ በሐዋርያት ሥራ ተጽፎአል፡፡ በዘመነ ሐዋርያት ቅድሚያ የሚሰጠው አገልግሎ የስብከተ ወንጌልና ሰዎችን በክርስቶስ ማሳመኑ ስለነበረ ሐዋርያት ለበሽተኞች ተረጋግቶ ለመጸለይና ለመፈወስ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ ጊዜ አማኞቹ "አድርጉ" ተብለው በሐዋርያት ሳይታዘዙ "በሽተኞቹ የሐዋርያት ጥላቸው ባረፈባቸው ጊዜ ይፈወሳሉ" ብለው አምነው ሐዋርያት በሚያልፉበት መንገድ ዳር የፀሐይን አቅጣጫ አይተው ጥላቸው በሚያርፍበት በኩል በሽተኞችን ደረደሩ፡፡ እግዚአብሔርም እምነታቸውን አይቶ በሐዋርያት ጥላ ብዙ በሽተኞችን ፈወሰ፡፡ ሐዋ ፭÷፲፭
በሽተኞችን ወደ ሐዋርያት ማቅረብ ያልተቻላቸው ደግሞ "በሐዋርያት የልብስ ቁራጭ ከደዌያችሁ ትፈወሳላችሁ" የሚል ትምህርት ሳይሰጣቸው በእምነት ከሐዋርያት የልብስ ቁራጭ በመውሰድና በሽተኞቹ ላይ በማድረግ በሽተኞችን ይፈውሷቸው ነበር፡፡ "እግዚአብሔር በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ ሐዋ ፲፰÷፲፩፡፡
መቅድመ ተአምረ ማርያምም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር ክርስቲያኖቹ እምነት በሽተኞቹ ወደ ሐዋርያት ሳይቀርቡ እንዲህ ያለ ተአምራት እንዳደረገላቸው ፈውስ ሥርየተ ኃጢአት እንደሰጣቸው ሁሉ እናንተም ቤተ ክርስቲያን መጥታችሁ ከጸሎቱ ተሳትፋችሁ ቃለ እግዚአብሔር ተአምረ ማርያም ተአምረ ኢየሱስ ሰምታችሁ በረከቱ ይደረግልናል ጸጋው ይሰጠናል ብላችሁ ብታምኑ ይደረግላችኋልና አትጠራጠሩ፡፡ ብቻ "ይደረግልናል" ብላችሁ በማመን ስሙ ጸልዩ ይላል፡፡ የመቅድሙ መልእክት ይሔ ሆኖ ሳለ "ዐውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም" እንደሚባለው ሰዎችን ሆን ብሎ ለማጠራጠርና ከቅዱሳን በረከት ለመለየት አጋንንት በሰዎች አድረው ሊቃውንቱ ያላሉትንና ሊሉም ያላሰቡትን ያቀርባሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ "ሥጋውን ደሙን አትቀበሉ ሥጋ ወደሙ መቀበል እና ሥጋ ወደሙ ሳይቀበሉ ተአምረ ማርያም መስማት እኩል ናቸው" የሚል ትምህርት አስተምራ አታውቅም እንዲህም አታምንም፡፡ ተአምሯን የሚሰሙትና የሚያሰሙትም ሥጋውን ደሙን የተቀበሉ ወደፊትም የሚቀበሉ ናቸው እንጂ አረማውያን ወይም በሥጋ ወደሙ የሚጠራጠሩ አይደሉም፡፡ "ይደረግልኛል በማለት ቢሰማ" የሚለው ጊዜ የተገደበ ነው፡፡
ታዲያ ይህ በውኑ ለምእመኑ መንፈሳዊ ሕይወት መጨነቅ ወይስ ለኑፋቄ ሽፋን መፈለግ?ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ፪ኛ ቆሮ ፲፪÷፪፡፡ይቆየን፡፡
0 comments:
Post a Comment