• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday, 29 October 2015

    ‹‹መምህር›› ግርማ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዝርዝር ይፋ ሆነ

    አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18 ፣ 2008 ( ኤፍ .ቢ .ሲ )

    ትናንት በቁጥጥር ስር የዋሉት መምህር ግርማ ወንድሙ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። መምህር ግርማ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ወድቅ ተደርጓል።

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ መርማሪ ቡድን ዛሬ ግለሰቡን በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት አቅርቧቸዋል። ፖሊስ ግለሰቡ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ቀሪ የምርመራ ስራ ስላሉብኝ ተጨማሪ 14 ቀን ይፈቀድልኝ ብሏል።

    ተጠርጣሪው በራሳቸውና በጠበቃቸው በኩል ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ በመቃወም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል። የፖሊስ የምርመራ ቡድን በበኩሉ እሳቸው ቢለቀቁ ሌሎች ተፈላጊዎችን እና የተለያዩ ሰነዶችን ስለሚያሸሹብን ጥያቄያቸው ውድቅ ይሁን ብሏል። ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ክርክር መርምሮ ፖሊስ አብዛኛውን የምርመራ ስራ ያካሄደ በመሆኑ ለቀሪ የምርመራ ስራዎቹ ይረዳል በማለት ከጠየቀው የ 14 ቀን ጊዜ ውስጥ 7 ቀን ብቻ ፈቅዷል። ውጤቱን ለመጠባበቅም ለጥቅምት 25 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

    የወንጀሉ ዝርዝር

    ፖሊስ መምህር ግርማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ወንጀል የተፈፀመው መስከረም 2006 ዓ. ም ነው ብሏል። በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ከበደ በመምህር ግርማ የማታለል ወንጀል የተፈጸመባቸው ግለሰብ ናቸው። እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር 400 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ ነበር።

    እንደ ምርመራ መዝገቡ መምህር ግርማ የግል ተበዳይን እምነት በመጠቀም የምትኖርበትን መኖሪያ ቤት እስከ ጥር 30 2006 ሽጠህ ካልወጣህ አስከሬንህ ይወጣል ይሏቸዋል። የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚለው ልጅ ያልወለዱት ባልና ሚስት ከመሞት መሰንበት በማለት ይህንን ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በ 800 ሺህ ብር ይሸጡታል። ቤቱ በዚህ ዋጋ እንዲሸጥ መምህር ግርማ በራሳቸው ሰዎች አማካኝነት ብዙ ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ነው
    የሚለው የምርመራ መዝገቡ።

    ከዚያም መምህር ግርማ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ የግል ተበዳዩን ቦሌ አካባቢ በራዕይ ያየሁት ቦታ አለ እዚያ ነው ገዝተህ የምትኖረው ይሏቸውና ሌላ የማታለያ ዘዴ ቀየሱ ይላል ምርመራው። ቤቱ የተሸጠበትን 800 ሺህ ብር አምጣና እንዲበረክትልህ ልፀልይበት ብለው በመውሰድ በዚያው ውለው አደሩ፤ የግል ተበዳዩም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለመጥፋቱ በትዕግስት ስልክ ቢደውሉላቸውም ስልካቸው ዝግ ሆነባቸው፤ ይባስ ብሎ ከሀገር ወጡ ተባለ የሚለውም ተጠቅሷል።

    የግል ተበዳይ ሁኔታው ማታለል መሆኑን. ስለተረዱ 2007 መጋቢት ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን፥ እርሳቸው ከሄዱበት እስኪመለሱ ፖሊስ የግል ተበዳዩን እና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ቆይቶ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙን ትናንት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነው ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው። ተጠርጣሪው እኔ የተባለውን ሰው ቀይ ይሁን ጥቁር አይቼው አላውቅም፤ ሆን ተብሎ ከጀርባ የተጠነሰሰብኝ ሴራ አለ በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።

    ጠበቃቸውም የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የሚከለክል አይደለም፤ ፖሊስም የሚጠበቁ ምርመራዎቹን አጠናቋል፤ ደንበኛዬ የዋስትና መብታቸው ይከበርልኝ በማለት ጠይውቋል። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ‹‹መምህር›› ግርማ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዝርዝር ይፋ ሆነ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top