• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 31 October 2015

    ተሀድሶ ክፍል ፰


               ብሉይ ኪዳን እንደ ዘመን፤                        

    ዘመንን የሚያስነቅፈውም ሆነ የሚያስመሰግነው ሰው ነው። የሰው ልጅ፥በአዳም ኃጢአት ምክንያት፡- መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ ወድቆበት ስለ ነበረ፥ ያን ዘመን የተነቀፈ እንዲሆን አድርጐታል። በሕገ ልቡና ዘመን እነ ኖኅ፥ ንጹሕ መሥዋዕት ቢያቀርቡም፥ በአዳም የውርስ ኃጢአት ምክንያት ዘመኑን ከመነቀፍ አላዳኑትም። የዘመናት ጌታ እግዚአብሔር ግን መሥዋዕቱን ውድዶ፣ ፈቅዶ በመቀበል፥ ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸዋል። ዘፍ፡፰፥፳። እነ ሙሴም፡- በእግዚአብሔር በታዘዙት መሠረት፥ በሕገ ኦሪት እየተመሩ አምስት ዓይነት ንጹሐን መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ ኖረዋል። ዘጸ፡፲፪፥፭፣ ዘሌ፡ ከምዕራፍ ፩ እስከ ፭። ይህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነት፥ ዘመኑን፡- ዘመነ ፍዳ፥ ዘመነ ኵነኔ ተብሎ ከመጠራት አልታደገውም። እነ ኢሳይያስን፡- “ጽድቃችንም እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤” ያሰኛቸው፥ በክርስቶስ ቤዛነት ብቻ በተደመሰሰው የአዳም ኃጢአት ምክንያት እንጂ፥ ጽድቅ በራሱ የመርገም ጨርቅ ሆኖ አይደለም። ኢሳ፡፷፬፥፮። ስለዚህ የተነገረውን ቃል ጥሬውን መመገብ ሳይሆን፥የተተረጐመውን ብስሉን በማስተዋል መመገብ ይገባል። “እንዲህ ይላል፤”ማለት ብቻ ሳይሆን፥“ለምን እንዲህ ተባለ፤” የሚለውንም አብሮ ማየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ፡- ሄሮድስ ሰው ሲሆን “ቀበሮ” ተብሎአል። ሉቃ፡፲፫፥፴፪። ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን ደግሞ፥ “እፉኝት” ተብለዋል። ማቴ፡፫፥፯። 

                                                            

    መሥዋዕት እንዲቀርብለት ያዘዘ እግዚአብሔር፥ ይመለከት የነበረው የቀረበውን መሥዋዕት ብቻ ሳይሆን፥ የአቅራቢውንም ሕይወት ነበር። “እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤” ይላል። ዘፍ፡፬፥፬። እግዚአብሔር የመሥዋዕት አቅራቢዎቹን በኃጢአት የቆሸሸ እና በበደል የረከሰ ሕይወት ሲነቅፍ ደግሞ፥ “በሬን የሚያርድልኝ ሰውን አንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደ ሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤ እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና። ይላል። ኢሳ፡፷፮፥፫። ለሚሰሙትና ለሚታዘዙለት ግን እንዲህ አይደለም። ጻድቁ ካህን ዘካርያስ፡- የዕጣን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ባቀረበ ጊዜ፥ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦለት፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፥ ሚስትህም ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤” ብሎታል። ሉቃ፡፩፥፰።                                                                              

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ የምሕረት ቃል ኪዳን ተሰጥቶአቸው ስለነበሩ ወገኖቹ ሲናገር፥ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ ፥እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።” ብሎአል። ሮሜ፡፱፥፩-፭። እንዲህም ማለቱ፡- ምሳሌውን ይዘው ከአማናዊው፥ ንባቡን ሰምተው ከትርጓሜው መድረስ ስለተሳናቸው ነው። የተነገረውን ትንቢት የተቈጠረውን ሱባዔ እያወቁ፥ በከንቱ በመቅረታቸው ነው ።እስራኤልን ችግር ላይ የጣላቸው፥ የኢየሱስ ክርስቶስ አመጣጥ፥ እነርሱ በጠበቁት መንገድና አኳዃን ባለመሆኑ ነው። በተለይም ፈሪሳውያን፡-“መሲሕ ሲመጣ የጦር ኃይል አቋቁሞ፥ ራሱ የጦር መሪ በመሆን፥ የሮማን የቅኝ ግዛት ቀንበር አውልቆ ጥሎ፥ የዳዊትን መንግሥት ያድሳል።” ብለው ይጠብቁ ነበር። ኤሴይ የሚባሉት ደግሞ፡- “መሲሕ ነጻ የሚያወጣን በተአምራት እንጂ በጦር ኃይ ል አይደለም፤” ይሉ ነበር። ሁለቱም ወገኖች፥ መሲሕ እንደሚመጣ፥ የተወሰኑ ምርጥ ጐሳዎችን ነጻ እንደሚያወጣ፥ ዓለም አቀፋዊ መሲሐዊ መንግሥት እንደሚይቋቁምና እነርሱም የመንግሥቱ ባለ ሟሎች እንደሚሆኑ ያምኑ ነበር። የዮሐንስና የያዕቆብ እናት ማርያም ባውፍልያ፥ ከልጆችዋ ጋር እየሰገደች፥ ሹመት የለመነችው ለዚህ ነው። “እነዚህ ሁለት ልጆቼ አንዱ በቀኝህ፥ አንዱም በግራህ ፥በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ።” ስትል መለመኗ፥ ቀኝ አዝማችነት እና ግራ አዝማችነት ሹምልኝ፥ ማለቷ ነበር።                                                                                 “ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው ለሁለተኛው ስፍራ ባልተገኘ ነበር፤”                                      

    ይህ ኃይለ ቃል የሚያመለክተን፡-ሕገ ኦሪት እና መሥዋዕተ ኦሪት፥በሕገ ወንጌል እና በመሥዋዕተ አዲስ መተካታቸውን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ አያይዞ የተናገረው፥ የነቢዩ የኤርምያስ ትንቢት መፈጸሙን ነው። ምክንያቱም፡- ዕብራውያን የተነገረውን ትንቢት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው። “እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና፡- እነሆ ከእስራኤል ቤት(ከዐሥሩ ነገድ) ከይሁዳ ቤት(ከሁለቱ ነገድ) ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል ይላል ጌታ፤ ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ።” የሚል ትንቢት ነበር። ኤር፡፴፩፥፴፩። እስራኤል፡-“ዘመኑን በዘመን ስለ አደሰው፥ አዲስ ሕግ እሠራላችኋለሁ አለ እንጂ፥ ሕጉስ ያው የጥንቱ ሕግ ነው።” እንዳይሉበት፥ አስረግጦ ነግሮአቸዋል። በዚህም፡- እንደ ኪዳነ ኖኅ፥እንደ ግዝረተ አብርሃም፥ እንደ ክህነተ ኦሪት፥ እንደ መሥዋዕተ ኦሪት ያለ አለመሆኑን አስቀድሞ ተናግሮአል። ምክንያቱም የመጀመሪያዋ  ሕግ ደግ ብትሆን ኖሮ ሌላ ደግ ሕግ ይሠራ ዘንድ ባልወደደም ነበር። የመጀመሪያ ው ለስርየተ ሥጋ ሲሆን፥ የሁለተኛው ለስርየተ ነፍስ ነው።        

    የእስራኤል ልጆች ከግብፅ በወጡ በሦስተኛው ወር፥ ሙሴ፡- ወደ ደብረ ሲና ራስ፥ ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- “በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደ አወጣኋችሁ (ፈጥኜ ወደ እኔ ባለሟልነት እንደ አቀረብኳችሁ) አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ፥ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት (ወገን) ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። (ቅዱሳን ነገሥታት፣ ቅዱሳን ካህናት እና ሃይማኖት የሚይዙ፥ ምግባር የሚሠሩ ምእመናን ከእናንተ ይወለዱልኛል።)” ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገር፥ ብሎት ነበር። ሙሴም የሕዝቡን አለቆች ጠርቶ  በነገራቸው ጊዜ፥ በአንድ ቃል፥ “እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ እናደርጋለን፤” ብለው ነበር። ዳሩ ግን እንደ ቃላቸው ሆነው ስላልተገኙ፥ “እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፤” ሲል ወቅሶአቸዋል፥ ቸልም እያለ በየጊዜው ለአሕዛብ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። በዚህም፡- ከአምልኰተ እግዚአብሔር ወደ አምልኰተ ጣዖት ያፈገፈገ፥ ከገቢረ ጽድቅ ይልቅ ገቢረ ኃጢአትን ያዘወተረ ሰውነታቸው፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የተነቀፈ ሆኖአል።                                                                                                                                           

            “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥በልባቸውም እጽፋለሁ፤”                   

    እግዚአብሔር፡- በነቢዩ በኤርምያስ አንደበት የተናገረውን ቃል በመቀጠል፥ “ከዚያ ወራት በኋላ (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም) ከእስራኤል ጋር የምገባው ቃል ይህ ነውና፤. . .ሕጌን በልቡናቸው እኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፋለሁ፥ እኔም አምላክ(አባት) እሆናቸዋለሁ፥ እነርሱም ሕዝብ (ልጆቼ) ይሆኑልኛል።” ብሎአል። በዚህም ልቡናቸውን ለቃለ እግዚአብሔር እንደሚከፍትላቸው ነግሮአቸዋል። በነቢዩ በኢሳይያስም፡- “ልጆችሽም ከእግዚአብሔር የተማሩ (እግዚአብሔር ልቡናቸውን ለቅዱስ ቃሉ የከፈተላቸው) ይሆናሉ።” ተብሎ ተነግሮአል። ኢሳ፡፶፬፥፲፫። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር የልድያን ልብ እንደ ከፈተላት በግብረ ሐዋርያት ተመዝግቦአል። የሐዋ፡፲፮፥፲፬። በአጠቃላይ አነጋገር፥ በመዓልትም በሌሊትም ሕጉን የሚያሰላስል ልብ እንደሚሰጠን የሚያመለክት ቃለ ትንቢት ነበር። በነቢዩ በሕዝቅኤል አንደበትም፡- “አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ፤” ብሎአል። ሕዝ፡፴፮፥፳፮። ቅዱስ ዳዊት፡- “በዝንጉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፥ የእግዚአብሔር ሕግ ብቻ ፈቃዱ የሆነ፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ ምስጉን ነው።” ያለው ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ልብ የተሰጠውን ሰው ነው። መዝ፡፩፥፩። በመሆኑም በርእሱ የተጻፈው ኃይለ ቃል መልእክት የተጻፈ ወንጌል፥ የተቀረጸ ጽላት አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ ማወቅም ማመንም ያስፈልጋል ። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ከአዳም እሰከ ሙሴ ድረስ ሕዝቡን የመራው በሕገ ልቡና ነበር። መናፍቃኑ እንደሚሉት፥ የጽሑፍ ሕግ የማያስፈልግ ቢሆን ኖሮ፥ አገልጋዩን ሙሴን፡- ሕገ ኦሪትን አያጽፈውም ነበር፥ ጽላትም ቀርጾ አይሰጠውም ነበር። በአዲስ ኪዳንም፡- አርባዕቱ ወንጌላውያን፡- ቆዳ ፍቀው፥ ብራና ዳምጠው፥ ቀለም በጥብጠው፥ ብዕር ቀርጸው ወንጌልን ለመጻፍ አይደክሙም ነበር። ስለዚህ ልባችሁን ብራና (ወረቀት)፣ ጽላት አደርግላችኋለሁ ማለቱ፥ ለምን እንደሆነ በሃይማኖት ማስተዋል ይገባል። ለምሳሌ፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ራሱን፥ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤” በማለቱ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፡- “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤” ስለ አላቸው፡- እርሱ የፈጠረው የፀሐይ ብርሃን፥ ሰው የሠራው የሻማ ብርሃን አያስፈልግም ማለቱ ይሆን? ማቴ፡፭፥፲፬፣ዮሐ፡፰፥፲፪።                                             

        “ወንድም ወንድሙን አያስተምርም፤”                                    

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው፡- “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፥ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤” ብሎ ነው። ማር፡፲፮፥፲፭። ራሱ ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤” ብሎአል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፱፥፲፮። ይህ እንዲህ ከሆነ፥ “ወንድም ወንድሙን አያስተምርም፤” ለምን ተባለ? ማለት ያስፈልጋል እንጂ፥ ጥሬ ንባቡን ብቻ ይዞ መከራከር ሰውን ከችግር ላይ ይጥላል። ስለዚህ፡- እግዚአብሔር ለትምህርተ ወንጌል፥ ልቡን ከፍቶለት ያመነውን ሰው፥ “እምነትህን በሥራ ግለጥ፤” ይባላል እንጂ፥ እንደ አዲስ አማኝ፥ “ጌታን ተቀበል፤” እንደማይባል ማስተዋል ተገቢ ነው። “እያንዳንዱም ጐረቤቱን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን (በሃይማኖት የሚመስለውን ወንድሙን)፡- ጌታን እወቅ (እመን) ብሎ አያስተምርም፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም። ”ያለው ለዚህ ነው። ላልተማሩትን እና ላላመኑት ግን፡- “ጌታን እወቅ(እመን)፤” ብሎ ምሥጢረ ሥጋዌን ማስ ተማር ይገባል። “ጌታን እወቅ፥ብሎ አያስተምርም፤” የሚለውን ከነቢያት የጠቀሰ፥ ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼ አለሁ።”ብሎአል። ሮሜ፡፩፥፲፬።                     

      “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤”                   

         ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- የነቢዩን የኤርምያስን ትንቢት ከጠቀሰ በኋላ፥ ዕብራውያን ምዕራፍ ፰ን የደመደመው፡- “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።” በማለት ነው። አነጋገሩ ምሳሌያዊ ነው፥ “ይህ ቤት ያማረ ያጌጠ ነበረ፥ ሊፈርስ ቀርቦአል፤ ይህ ልብስ የሞቀ የደመቀ ነበረ፥ ሊያልቅ ቀርቦአል፤” እንደ ማለት ነው።                    

    በኦሪቱ፡-ከእንስሳት ወገን ንጹሕ የሆነ እና እንከን የሌለበት መሥዋዕት ተመርጦ ይቀርብ ነበር። ዘጸ፡፲፪፥፭፣ ዘሌ፡፳፪፥፳፬፣ ፩ኛ፡ጴጥ፡፩፥፲፰። አቅራቢው እጁን በእንስሳው ራስ ላይ በመጫን፥ ኃጢአቱን ያሸክመው ነበር። ዘሌ፡፩፥፬፤፲፮፥፳፩፣ ኢሳ፡፶፫፥፮፣ ፩ኛ፡ጴጥ፡፪፥፳፬። የኃጢአት ደመወዝ ሞት በመሆኑ፥ አቅራቢው፡- ኃጢአቱን የተሸከመለትን እንስሳ ያርደዋል። ሮሜ፡፮፥፳፫፣ ዕብ፡፱፥፳፭። ካህኑ ደግሞ፡- የመሥዋዕቱን ደም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል። ዘሌ፡፩፥፭፤፲፯፥፲፩፣ ዕብ፡፱፥፲፪። እንደ መሥዋዕቱም ዓይነት፥ ከታረደው እንስሳ፥ልዩ ልዩ ክፍልና ብልት ያቃጥላል። ዘፍ፡፰፥፳፩፣ ሮሜ፡፲፪፥፩፣ ፪ኛ፡ ቆሮ፡፪፥፲፬፣ ኤፌ፡፭፥፪። “እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፡- አሮንን እና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፡- የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤የሚቃጠለው መሥዋ ዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሙሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ (የመሠዊያው እሳት እስኪነጋ ድረስ በበላዩ እየነደደ በመሠዊያው ላይ ይተዉት፥ ስቡንም በመሠዊያው ላይ ያቅልጡት)፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። (እሳቱ መሠዊያውን እንዳይጐዳው ደግሞ፥ ፈቀቅ አድርገው በጉድጓዱ ውስጥ ሲነድ ይደር)። ካህኑም የበፍታ (የነጭ ሐር) ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። ልብሱንም (ነጩን የሐር ልብስ ያወልቃል፥ ሌላም(ተርታ) ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል። እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ (በመሠዊያው ላይ እንጨት ይጨምር፥ በእንጨቱም ላይ ሊቃጠል የቀረበውን ሥጋ ያኑር)፥ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። (ድኅነት ሊደረግበት የተለየውንም ስብ ጨምሮ ያጢሰው)። ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፥ አይጠፋም።” በማለት ነገረው፥ ይላል። ዘሌ፡፮፥፰-፲፫። ሐዋርያው፡- አሮጌና ውረጅ ያለው ይኸንን ነው።                                                                                             

    በአዲስ ኪዳን ግን፥ ክርስቶስ እንጂ፥እንስሳት የሚሠዉባት ቤተክርስቲያን የለችንም ፥ ነፍስ የተለየው፥ እሳት መለኰት የተዋሀደው፥ የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትባት እንጂ፥ የእንስሳት ሥጋ የሚቃጠልባት፥ ስቡም የሚጤስባት ቤተክርስቲያን የለችንም። መሥዋዕታችን፥ የአዲስ ኪዳን በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤” ይላል። ዮሐ፡ ፩፥፳፱፣፴፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ፋሲካችን(የፋሲካ በግ) ክርስቶስ ታርዶአ ልና፤(እንደ ታረደ በግ፥ በመስቀል ላይ፥ሥጋውን ቆርሶልናልና፥ ደሙንም አፍስሶልናልና) ብሎአል። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።  
      

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሀድሶ ክፍል ፰ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top