• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 20 October 2015

    ምሥጢረ ሥላሴ ክፍል ሁለት

    የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው "አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላከ አብርሃም፣ አምላከ ይስሐቅ፣ወአምላከ ያዕቆብ" የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ይላል፡፡ "እኔ እግዚአብሔር ነኝ" ብሎ አንድነቱን ሦስት ጊዜ አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ ብሎ ሦስትነቱን ለነቢይ ሙሴ አስረድቶታል፣ ነገር ግን ሦስት ጊዜ አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ ስለ አለ ሦስት አማልክት አይባልም አንድ አምላክ ይባላል እንጂ (ዘፀ. 3:15-16)

    ማስረጃ፡-"ስማዕ እስራኤል አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላክከ"
    ትርጉም፡-እስራኤል ስማ አምላክህ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ ከአንድ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ የለም ዘዳግ. 1ኛ ቆሮ 8:4 ዮሐ፡ 7:3፣ 20:17

    ግዕዝ፡-"አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ወኢይትበሃሉ ሠለስተ አማልክተ አላ አሐዱ አምላክ"
    ትርጉም፡-አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ነገር ግን አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም፣(አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሃይ.አበው ም. 25 ቁ. 4) ስለዚህ ምንም ለአጠይቆተ ሠለስቱ አካላት በአካል፣ በስም፣ በግብር በኩነት ሦስት ብንልም በባሕርይ በመለኮት በህልውና በአምላክነት በእግዚአብሔርነት በመንግሥት በሥልጣን በፈቃድ አንድ አምላክ ብለን በአንድ አምላክ የምናምን ስለሆነ አምላክ የሦስቱም አካላት የአንድነት ስማቸው ነው ብለን አምነን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ እንላለን፡፡(ማቴ፡ 28:19፣ ሃይ.አበው ም. 1 ቁ. 1 ፍት፡መን አንቀጽ 1 ቁ. 1)

    አዶናይ: አዶናይ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው ትርጓሜውም አዶናይ ማለት ጌታ ማለት ነው፡፡ "አዶናይ እግዚአብሔር እንዲህ አለ" ሕዝ 2:4 ወደ ወገኖቼ እስራኤል ማንን እልካለሁ? ሲል የአዶናይ ቃሉን ሰማሁ፣ ኢሳ፡ 6:8 ስለ አዶናይ ትርጓሜ የአለቃ ኪዳነ ወልድ መጽሐፈ ስዋስው ወግሥ ገጽ 205 ይመልከቱ፡፡

    ጸባኦት:  ጸባኦት ማለት "መዋዒ (ጸባኢ)እግዚአ ኃይላት" አሸናፊ የመላእክት ጌታ ማለት ሲሆን ጸባኦት የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው፡፡ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባኦት ኢሳ 6:3

    አልፋ ወዖሜጋ: አልፋ ወዖሜጋ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነትና የሦስትነት ስማቸው ነው፣ አልፋ ወዖሜጋ ማለት፣ ቀዳማዊ ወደኃራዊ፣ ርዕስ ወማኀለቅት ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው ማለት ነው፡፡ አንድም በየአንዳንዱ ፊደል ሲተረጎም፡ አ፡ አብ፡ ል፡ ወልድ፡ ፋ፡ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው (ዖሜጋ)  አንድነታቸውን ያሳያል፡፡

    ግዕዝ፡- አነ ውእቱ አልፋ ወኦ፣ ወአነ ቀዳማዊ ወአነ ደኃራዊ
    ትርጉም፡- አልፋ ኦ እኔ ነኝ ቀዳማዊ ደኃራዊ የምሆን እኔ ነኝ ራዕይ 21፡6

    መለኮት:  መለኮት፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ፣ በአምላክነት፣ በመንግሥት፣ በሥልጣን፣ በጌትነት.... አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ የአንድነት ስማቸው ነው፡፡

    ግዕዝ፡- መለኮትኒ ይትዓወቅ ከመ ውእቱ ያኀብር ቅድስተ ሥላሴ፤
    ትርጉም፡-መለኮት ቅድስት ሥላሴን አንድ እንደሚያደርግ ይታወቃል፤

    ግዕዝ፡- እስመ አሐዱ ውእቱ መለኮት ተዋሕዶቶሙ ውእቱ መለኮት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወበዝንቱ አእመርነ ከመ አሐዱ ውእቱ መለኮት ዘቦቱ ሠለስቱ አካላት፣ወኢንክሐድ አሐደ መለኮተ ዘቅድስት ሥላሴ፡፡
    ትርጉም፡- መለኮት አንድ ነውና የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አንድነታቸው ነው፣ የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ እንደሆነ በዚህ አወቅን፣ የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ መሆኑን ፈጽመን አንካድ ሃይ. አበው ዘአትናቴዎስ ም. 25 ቁ 5-14
    ንህነሰ ከመዝ ንሰግድ ለአሐዱ አምላክ ባሕቲቱ ወንትአመን በአሐዱ መለኮት ዘሠለስቱ አካላት ወኢንበውእ ኀበ ከፊለ መለኮት ወመንግሥት አላ ንሰብክ ገሐደ ወንብል አሐዱ መለኮት ወአሐዱ ህላዌ ወአሐዱ ፈቃድ ወአሐቲ ሥምረት ሠለስቱ አካላት ወሠለስቱ ገጻት ወቦሙ ይደሉ ተጠምቆ ወአሚን፡፡ ወሶበሂ ንሬሲ ቅድስተ ሥላሴ ፍሉጣነ መለኮት ዘከመ አካላቲሆሙ ንትአመን እምነተ ሠይጣናዌ፡፡
    ትርጉም፡-እኛ ግን ለአንድ አምላክ ብቻ እንሰግዳለን፣ ሦስቱ አካላት አንድ በሚሆኑበት በአንድ መለኮት እናምናለን፣ መለኮትንና መንግሥትን ወደመክፈል አንገባም፣ አንድ መለኮት፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ፈቃድ፣ አንዲት ሥምረት (ውድ) ሦስት አካላት፣ሦስት ገጻት፣ ብለን በጎላ በተረዳ ነገር እናስተምራለን እንጂ፤ በእነሱም አምኖ መጠመቅ ይገባል፣ ቅድስት ሥላሴን በአካል ልዩ እንደሆኑ በመለኮት ልዩ ናቸው ብንል ግን ከሰይጣን የተገኘ እምነትን እናምናለን ማለት ነው፣ ሲል ዲዮናስዮስ ዘአንጾኪያ በመለኮት አንድ መሆናቸውን አስረድታል፡፡(ሃይ. አበው ም. 111 ቁ. 3-4)

    ቦሙ አአምን ወእትአመን ከመ እሙንቱ መለኮት ወህላዌ ወእሙነ እብል ከመ እሙንቱ መለኮት ወለለአሐዱ አሐዱ እም አካላተ ቅድስት ሥላሴ ያበጽህ ፍጹመ መለኮተ ምስለ ዘዚአሁ አካል ወስም ወዝኒ ዘመለኮተ ዚአሁ፣
    ትርጉም፡-እነሱ መለኮት ባሕርይ እንደሆኑ በነሱ አምናለሁ፣ እታመናለሁ፣ እነሱ መለኮት እንደሆኑ በእውነት እናገራለሁ፣ ከቅድስት ሥላሴ አካላት አንዱም አንዱ ከገንዘቡ አካል ከገንዘቡ ስም ጋር ፍጹም መለኮትን ገንዘብ ያደርጋል ይህም አካል ስምየመለኮት ገንዘብ ነው(ባስልዮስ ዘአንጾኪያ ሃይ. አበ. ም. 96 ቁ. 5-7 )

    የመለኮት ትርጓሜው፣ ባሕርይ፣ ሕይወት፣ ብርሃን፣ ጌትነት፣ አምላክነት፣ አገዛዝ (ግዛት) እና ክብር ስለሆነ ሥሉስ ቅዱስ በዚህ ሁሉ አንድ ናቸውና በአንድነት ይጠሩበታል፡፡ (ሃይ. አበ. ም. 11 8፡፡11፡13፡፡ 7፡30፡፡ መዝ 102፡22፡፡ ሮሜ፡፡ 1፡20 2ኛ ጴጥ 1፡3፡፡ 2ኛ ቆሮ 13፡4)፡፡ ሦስቱ አካላት አምላክ አምላክ አምላክ ስለተባሉ አንድ አምላክ እንጅ ሦስት አማልክት እንደማይባሉ ሁሉ፣ ሦስቱ አካላት መለኮት መለኮት መለኮት ስለተባሉ አንድ መለኮት ይባላሉ እንጂ ሦስት መለኮት አይባሉም፡፡ "ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት" በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ይሆናሉ፤ አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ነገር ግን አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም፡፡(ሃይ. አበ. ም. 24 ቁ. 3)

    እኁዛን እሙንቱ በጽምረተ አሐዱ መለኮት፣ ወበዝንቱ አሐዱ መለኮት ይሰመዩ እግዚአብሔር፤
    ትርጉም፡-በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት የተገናዘቡ ናቸው በዚህ በአንድ መለኮት እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ (ሃይ. አበ. ም. 91 ቁ. 10 - 11) መለኮትን እንደ ጊዜ ግብሩ ለሥላሴ በተለየ አካላቸው፡ አብ መለኮት፣ ወልድ መለኮት፣ መንፈስ ቅዱስ መለኮት ብሎ በቅጽልነት ወይም በቂ አድርጎ፣ መለኮት ብሎ አብ፣ መለኮት ብሎ ወልድ፣ መለኮት ብሎ መንፈስ ቅዱስ የሚል መጽሐፍ ቢገኝ፣ አንድ መለኮትይባላል እንጂ ሦስት መለኮት አይባልም፣ለምሳሌ፣ መለኮት ብሎ በተለየ አካሉ ለእግዚአብሔር ወልድ ሲሠጥ፣
    ንባብ፡-ወተወለደ መለኮት በሥጋ፣
    ትርጉም፡-መለኮት በሥጋ ተወለደ (ቅዱስ ያሬድ ድጓ) ክቡር አንተ ዕፀ መስቀል ወክቡር ዘቀደሰከ ደመ መለኮት ቃል፡፡ ትርጉም፡-የከበርህ አንተ ዕፀ መስቀል የአካላዊ ቃል መለኮት ደም የቀደሰህ ክቡር ነህ፡፡ በመልዕልተ ዝንቱ መስቀል አመ ሞተ መለኮት በትስብዕቱ፣በዚህ መስቀል ላይ መለኮት በሰውነቱ በሞተ ጊዜ፡፡ (መስተብቁዕ ዘመስቀል) ይገብር መንክራተ በመለኮቱ ወይትዌከፍ ሕማማተ በትስብዕቱ፣
    ትርጉም፡-እንደ አምላክነቱ ተአምራትን ያደርጋል፣ እንደሰውነቱ መከራን ይቀበላል፡፡(ዮሐንስ ዘአንጾኪያ በሃይ. አበው) "ወኢሞተ መለኮትየ አላ ጼወውኩ ሲኦለ"መለኮቴ (አምላክነቴ) አልሞተም ሲኦልን ማረኩ እንጂ ይላል፡፡(ሃይ. አበው ዘኤጲፋንዮስ)

    ስለዚህ መለኮት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነታቸውን የሚያስረዳ ረቂቅና ምጡቅ፣ ልዑልና ግሩም፣ ምሉዕና ስፉሕ የሆነው የባሕርያቸው የግብር ስም እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡(ዮሐ/አፈ/ ወር/ ሁለተኛ ድርሳን) መለኮት፣ ንጉሥ፣ ሥሉጥ፣ ኃያል፣ ዐቢይ፣ ክቡር፣ አዚዝ፣ ሕያው፣ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው፤ እንዲህ ግን ስለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮት፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ሥልጣን፣ አንድ ኃይል፣ አንድ ጌትነት(ጌታ)፣ አንድ ክብር፣ አንድ እዘዝ፣ አንድ ሕይወት ይባላሉ እንጂ፣ሦስት መለኮት፣ ሦስት መንግሥት፣ ሦስት ሥልጣን፣ ሦስት ኃይል፣ ሦስት ጌትነት (ጌታ)፣ ሦስት ክብር፣ ሦስት እዘዝ፣ ሦስት ሕይወት አይባሉም፣መሐሪ፣ ከሃሊ፣ ሠራዒ፣ መጋቢ፣ አኃዚ ..... የሚለው ሁሉ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው "ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ባስልዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ፣ፈቃደ አብ፣ ፈቃደ ወልድ፣ ፈቃደ መንፈስ ቅዱስ፣ ሥምረተ አብ፣ ሥምረተ ወልድ፣ ሥምረተ መንፈስ ቅዱስ፣ ባሕርየ አብ፣ ባሕርየ ወልድ፣ ባሕርየ መንፈስ ቅዱስ፣ አብ ብርሃን፣ ወልድ ብርሃን፣ መንፈስ ቅዱስ ብርሃን፣ ቢል አንድ ፈቃድ፣ አንድ ሥምረት፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ብርሃን ..... ይባላል እንጂ፤ ሦስት ፈቃድ ሦስት ሥምረት ሦስት ባሕርይ ሦስት ብርሃን አይባልም፡፡

    ለሥላሴ የምናቀርበው የአምላኮ ምስጋናም አንድ ምስጋና ነው፡፡ ቅዱስ ውዱስ ስቡሕ እኩት... ቢልም የባሕርይ ምስጋና የሚመሰገኑበት የአንድነት ስማቸው ነው፡፡ ምስጋናቸውም ለአጠይቆተ ሠለስቱ አካላት ሦስት ጊዜ እየተደጋገመ ቢነገርም፣ አንድ ስብሐት፣ አንድ ቅዳሴ፣ አንድ ውዳሴ፣ አንድ አኰቴት... ይባላል እንጂ ሦስት ስብሐት፣ ሦስት ቅዳሴ፣ ሦስት ውዳሴ፣ ሦስት አኰቴት አይባልም፡፡

    ለሥላሴ የምንሰግደው የአምልኮ ስግደትም አንድ ስግደት ነው፡፡ በስግደትም ጊዜ ለአጠይቆተ ሠለስቱ አካላት ሦስት ጊዜ ብንሰግድም በአካል፣ በስም በግብር ሦስት የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት አንድ አምላክ መሆኑን ለማስረዳት አንድ ስግደት እንሰግዳለን እንጂ ሦስት ስግደት አንሰግድም፡፡ ይህም ማለት ለሥላሴ የምንሰግደውን ሦስት ስግደት አንድ ስግደት እንላለን ማለት ነው፡፡
    ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሠለስቱ አካላት ወሠለስቱ ገጻት ወአሐዱ መለኮት ቅዱሳን ወዕሩያን በኩሉ ግብር ይሴብሑአሐተ ስብሐተ ወይሰገዱ አሐተ ስግደተ፡፡
    ትርጉም፡-በአካላት በገጻት ሦስት በመለኮት አንድ በሚሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን በአካላት ልዩ ናቸው በሥራ ግን አንድ ናቸው አንዲት ምስጋና ይመሰገናሉ አንዲት ስግደትም ይሰገድላቸዋል፡፡(ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ሃይ. አበው ም. 113 ቁ. 1)ማስረጃዎችን ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን

    አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ሰባተኛ "ሥላሴ ያለመለያየት በመለኮት አንዲት ትክክል ናት፤ ያለመለወጥም በአካል ሦስት ናት፤ በመንግሥት አንዲት፣ በፈቃድም አንዲት፣ በኃይልም አንዲት፣ በጌትነትም አንዲት" ናት በማለት አንድነታቸውንና የአንድነት ስማቸውን አስረድቷል፡፡(ሃይ. አበው ም. 11 ቁ. 5-6)

    ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ (318ቱ) ሊቃውንትም በገጽ በአካል ፍጹማን የሆኑ ሦስቱ አካላትም እስከ ዘለዓለም ድረስ በመለኮት አንድ ናቸው፤ አንድ ጌታ ከሦስት የማትከፈልከአንዱ ወደ አንዱ የማታልፍ አንዲት መንግሥት ናቸው ብለዋል፡፡(ሃይ. አበው ም. 19 ቁ. 4-6)

    አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡- መለኮትስ አንድ አምላክ፣ አንዲት መንግሥት፣ አንዲት ሥልጣን፣ አንዲት አገዛዝ የሚሆን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ብሏል፡፡(ቅዳሴ ሕርያቆስ) ሦስት አካላት በየአካላቸው አሉ ብንልም ፍጹም ባሕርይን አንድ ህልውናንም አንድ ብለን አንድ መንግሥት አንድ እበይ(ጌትነት)አንድ ክብር ነው እንላለን፤ አካላት ሦስት ስለሆኑ በመለኮት ህላዌ (አኗኗር) የማይከፈልና የማይለይ አንድ ብርሃን ሲሆን አብ ብርሃን፣ ወልደ ብርሃን፣ መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ይባላሉ፡፡

    ዳግመኛም በመለኮት አኗኗር አንድ ሕይወት ሲሆኑ፣ አብ ሕይወት፣ ወልድ ሕይወት፣ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ነው እንላለን፡፡ ዳግመኛም አብ አንድ ይባላል፣ ወልድ አንድ ይባላል፣ መንፈስ ቅዱስም አንድ ይባላል፤ ከአካላትም እያንዳንዱ አንድ ህላዌ አንድ አምላክ ናቸው፤ ሦስት አማልክት ግን አይባሉም፤ መገናዘብ እንደሌላቸው ሦስት ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎች፣ በሦስት አማልክት፣ በሦስት መለኮት የምናምን አይደለንም፤ ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያደርጋቸው በሦስት አካላት በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ ብሏል ዮሐንስ ዘአንጾኪያ 47ኛ (ሃይ. አበው ም. 96 . 8. ፣ 114 ቁ. 4-6) ኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ አማኑኤል፣ መድኅን መድኃኔ ዓለምአካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ በዘመነ ሥጋዌ የተጠራባቸው ስሞች ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ አማኑኤል፡ መድኅን መድኃኔ ዓለም ሲሆኑ እኒህም ስሞች ከዘመነ ሥጋዌ አስቀድመው በትንቢተ ነቢያት የተነገሩ ናቸው፡፡
    አማኑኤል: አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነስቶ (ተዋሕዶ) ከእኛ ጋር አንድ ባህርይ ሆኖ አዳነን ማለት ነው፣ ኢሳ 7 :14

    ኢየሱስ:  ኢየሱስ ማለትም ወገኖቹን በኃጢአታቸው ምክንያት ከመጣባቸው ፍዳ የሚያድናቸው መድኃኒት ማለት ነው፡፡ (ማቴ 1:21 ተረፈ ኤርምያስ)መድኅን መድኃኔ ዓለምመድኅን መድኃኔዓለም ማለትም የዓለም መድኃኒት ማለት ነው፡፡እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ (ሉቃ 2:11)እነሆ መድኃኔዓለም ተወለደ (ቅዱስ ያሬድ ድጓ)ክርስቶስክርስቶስ ማለት መሲሕ (ቅቡዕ) ንጉሥ ማለት ነው፡፡ ዳን. 9: 25-26 ማቴ 1:16
    ጰራቅሊጦስጰራ: ቅሊጦስ ማለት መጽንኢ መንጽሒ መስተፍሥሒ መስተሥረዪ ማለት ሲሆን አካላዊ እስትንፋስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በተለየ አካሉ የሚጠራበት ስሙ ነው፡፡እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ ርሱም ከአብ የወጣ (የሠረፀ) የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ርሱ ስለኔ ይመሰከራል፡፡ ዮሐ፡ 14:6 ፣15:16
    ይቀጥላል ..................
    ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሜን !

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ምሥጢረ ሥላሴ ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top