መግቢያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም ወደዚህ ምድር ከመምጣቱ በፊት እኛ የሰው ልጆች የምናውቀው ሞትን ብቻ ነበረ። ሞት ለእኛ እጅግ የቀረበና ከእያንዳንዳችንም ሆነ ከመላው የሰው ዘር በላይ እጅግኃይለኛ ነበረ። ምድር የሞት እስር ቤት እኛ የሰው ልጆችደግሞ ረዳት የሌለን የሞት ባሪያዎች ነበርን። ነገር ግን ሰውበሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ "ሕይወት ተገለጠ"፣ ተስፋ የሌለን መዋቲያን፣ የሞት ባሮች ለነበርን "የዘላለም ሕይወት ተገለጠልን" (፩ ዮሐ. ፩*፪)። ይህንንም የዘላለም ሕይወት በዓይናችን አየነው፤ ተመለከትነው፤ በእጃችንም ዳሰስነው (፩ዮሐ. ፩*፩)። እኛ ክርስቲያኖችም ይህንን የዘላለም ሕይወት ለሁሉም ገለጥነው (መሰከርነው) (፩ ዮሐ. ፩*፩)። ከክርስቶስ ጋር በኅብረት ስለመኖርም በዚህ ምድር እያለን እንኳን ዘላለማዊ ሕይወትን መኖር ጀመርን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት እንደሆነ አወቅን፤ እርሱም የመጣው ለዚህ ነበርና። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነና እውነተኛ ፍቅር ማለት ይህ ነው፡፡ "በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና" እንዲል (፩ዮሐ. ፬*፱)። ስለዚህ "ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም"(፩ዮሐ. ፭*፲፪)።
ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ወሰን የሌለው ነው። ምክንያቱም የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሁሉም ሰው "በቀላሉ" ሊኖረው ከሚችለው በእርሱ ከማመንና ከመታመን በቀር ሌላ መስፈርት አይፈለግብንምና። "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና" (ዮሐ. ፫*፲፮)፤ "እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔየሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው" እንዲል (ዮሐ. ፮*፵፯)። የእኛ እውነተኛ ሕይወት የሚጀምረው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት ነው። እምነት፣ ቀስ በቀስ ሊያነጻን፣ ሊያድሰንና አማልክት ዘበጸጋ ሊያደርገን ለሚችል ለኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ልባችንና በፍጹም ኃይላችን በቁርጥ ሐሳብ ራሳችንን ለእርሱ እንድንሰጥ ያደርገናል።ሕይወታችን ሕይወት የሚሆነው በክርስቶስ ስንኖር ብቻነው። ከዚህ በተቃራኒው የሆነ ነገር በሙሉ ሞት ይባላል።ሞት ኃጢአት፣ ኃጢአት ደግሞ ሕይወት ከሆነውና የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር መለየት ነው።
ለመሆኑ ክርስቲያኖች ምንድን ናቸው? ክርስቲያኖች ለባሴ ክርስቶስ (ክርስቶስን የለበሱ)፣ ዘላለማዊ ሕይወትን የያዙማለት ናቸው። ቅዱሳን ደግሞ ዘላለማዊ በሆነ በክርስቶስ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ሞት የማይሠለጥንባቸው ፍጹማን ክርስቲያኖች ናቸው። ሁለንተናዊ ሕይወታቸው በክርስቶስ የሆነ ነው። ቅዱሳን በክርስቶስ በመኖር እርሱ የሠራቸውን ሥራዎች መሥራት ይችላሉ - "ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ" (ፊልጵ. ፬*፲፫)፤ "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል" እንዲል (ዮሐ. ፲፬*፲፪)።
ለምሳሌ "የሐዋርያት ሥራ" ማለት ሐዋርያት በክርስቶስ ኃይል የሠሯቸው የክርስቶስ ሥራዎች ማለት ነው። የቅዱሳን ሕይወት ማለት ደግሞ የሐዋርያት ሥራ ቀጣይ ክፍል ማለትነው። ልክ እንደ ሐዋርያት ሁሉ በቅዱሳን ሕይወት ውስጥምአንድ ዓይነት ወንጌል፣ አንድ ዓይነት ሕይወት፣ አንድእውነት፣ አንድ ዓይነት ጽድቅ፣ አንድ ዓይነት ፍቅር፣ አንድዓይነት እምነት፣ አንድ ዓይነት ዘላለማዊነት፣ አንድ ዓይነት ሰማያዊ ኃይል፣ አንድ አምላክ፣ አንድ ጌታ እናገኛለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ስለሆነ (ዕብ. ፲፫*፰) በየዘመናቱ እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሱ ቅዱሳንአንድ ዓይነት ኃይል ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን በሐዋርያት ሥራ አብነት የቅዱሳንን የሕይወት ተጋድሎ መጻፍ፣ ማንበብና መከተል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። በዚህ መሠረት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ቀጥሎ ከተነሡት ቅዱሳን ጀምሮ ያሉትን አበውና እማት ሕይወት በመጻፍና በማስተማር የቅዱስ ሉቃስን ሥራ እየፈጸመች ትገኛለች።
በቤተ ክርስቲያናችን የቅዱሳንን የሕይወት ተጋድሎ በስፋት ከትቦ የሚገኘው መጽሐፍ ስንክሳር ይባላል። ይህ መጽሐፍ በዓመት ውስጥ ባሉት ቀናት ታስበው የሚውሉትን ቅዱሳን ዜና ገድል በቅደም ተከተል የያዘና በሚገባ የተዋቀረ ስለሆነ ለማንበብ እጅግ የተመቸ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህንን መጽሐፍ እንድታነቡት ተጋብዛችኋል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ይቀጥላል!
0 comments:
Post a Comment