• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    መንፈሳዊነት፦ ክፍል ፩

    የሰው መንፈሳዊነት ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን፦ "እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ (በነቢዩ በኢዩኤል የተነገረው ትንቢት ይፈጸምላችኋል) እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ።" ያላቸው ለዚህ ነው። ኢዩ. ፪፥፳፰-፴፪ ሉቃ ፳፬፥፵፱። እነርሱም ተስፋውን አምነው ለአሥር ቀናት ጸንተው በመቆየታቸው ለአሥሩ መንፈሳውያት ማዕረጋት የሚበቁበትንና በአሥሩ የመላእክት ከተሞች እንዳሉ ቅዱሳን መላእክት የሚተጉበትን ጸጋ በእሳትና በነፋስ አምሳል አግኝተዋል። የሐ ፪፥፩-፬። እሳት ብረትን እንደሚያጸናው በመዶሻም በተቀጠቀጠ ጊዜ እንደማይሰበር እነርሱንም በመንፈሰዊ ሕይወት የሚያኖራቸው በገድልም የሚያጸናቸው መንፈስ ቅዱስ ነውና። ነፋስም መልካም መዓዛን ከሩቅ አምጥቶ እንደሚያውድ ለእነርሱ መዓዛ ገነትን አምጥቶ የሚያውዳቸው መንፈስ ቅዱስ ነውና። ከዚህም አስቀድሞ፦ "ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ እኔም አብን እለምናለሁ፣ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይልክላችኋል እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፣ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፥ በእናንተ ዘንድ ይኖራልና፥ ያድርባችሁማልና። ከእናንተ ጋር ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፥ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።" ዮሐ ፲፬፥፲፭-፲፯፣ ፳፭-፳፮። "እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ትመሰክራላችሁ ከጥንት ጀምሮ ከእኔ ጋር ኑራችኋልና።" ዮሐ ፲፭፥፳፮። "እኔ በእውነት የሚሆነውን እነግራችኋለሁ፥ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፥ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።" ብሏቸዋል። ዮሐ ፲፮፥፯። ከዚህም ለግል መንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ ሌላውን ለማዳን ለሚፈጸም መንፈሳዊ አገልግሎት ጸጋው ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም መንፈሳዊነት፦

    ፩ኛ፦ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፤

             ቅዱስ ዳዊት፦ "ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፥ እማንቱ ይምርሐኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ ብርሃንህንና ጽድቅህን (ወልድን በተዋሕዶ፣መንፈስ ቅዱስን ደግሞ በእሳት አምሳል) ላክ፥ እነርሱም ይምሩኝ፥ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራ እና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።" ብሏል። መዝ ፵፪፥፫። "ወመንፈሰከ ቅዱሰ ኢታውጽእ እምላዕሌየ፥ ዕሥየኒ ፍሥሐ ወአድኅኖተከ፥ ወበመንፈስ አዚዝ አጽንዐኒ። ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ፥ ደስታንና ማዳንህን ስጠኝ፥ በጽኑ መንፈስም አጽናኝ።" እያለም ተማጽኗል። መዝ ፶፥፲፩-፲፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የቅዱሳን መሪያቸው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ሲመሰክር፦ "ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም። ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው (ተመርተው) ተናገሩ።" ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ "በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ (የሚሠሩ) ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።" ብሏል። ሮሜ ፲፥፲፬። ይህንንም ይበልጥ ሲያብራራው፦ "እኛ የዚህን ዓለም መንፈስ የተቀበልን አይደለም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ ተቀበልን። ይህም ትምህርታችን ከሰው የተገኘ ትምህርት አይደለም፥ የአነጋገር ጥበብም አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስ የገለጸው ትምህርት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ጥበብም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሆነውን መርምረው ለሚያውቁ ለመንፈሳውያን ነው።" ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፪፥፲፪-፲፫።

     

    ፪ኛ፦ ሁል ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ መሣሪያ መሆን ነው፤

             በሰው ሕይወት አድሮ መንፈሳዊ አሳብ የሚያሳስብ፥ መንፈሳዊ ነገር የሚያናግር፥ መንፈሳዊ ሥራም የሚያሠራ መንፈስ ቅዱስ ነው። የሰው ልጅ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ በሚወለድበት ቅጽበት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የጸጋው ባለቤት ይሆናል። ዮሐ ፫፥፭። በልዩ ጸጋ በእናት ማኅፀን እያለም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሚሆንበት ጊዜም አለ። እግዚአብሔር ብላቴናውን  ኤርምያስን፦ "በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።" ብሎታል። ኤር ፩፥፭። በእግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚገለጥ ቅዱስ ገብርኤልም ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፦"ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል።" ብሏል። ሉቃ ፩፥፲፭። ይልቁንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ የተወለዱ ጃንደረቦች አሉና" ብሏል። ማቴ ፲፱፥፲፪። የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆን ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠ ጸጋ ነው። ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ "እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ እንዲኖር አታውቁምን?... ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?" ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፭፥፲፮ ፮፥፲፱።

           የሰው ልጅ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ እየተመራ የመንፈስ ቅዱስ መሣሪያ መሆኑን ትቶ በፈቃደ ሥጋው መመራት ሲጀምር መንፈስ ቅዱስ ያዝንበታል። "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበት የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።" ይላል። ኤፌ ፬፥፳፱-፴። መንፈስ ቅዱስ ስለ ኃጢአትም ይወቅሳል። ዮሐ ፲፮፥፲-፲፩። መንፈስ ቅዱስ እያዘነበት እየወቀሰውም የማይመለስ ሰው መጨረሻው "ለሰው ኃጢአት እና ስድብ ሁሉ ይሰረያል፥ መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ ግን አይሰረይለትም።" የሚለው የጌታ ቃል ነው። ማቴ ፲፪፥፴፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ "ነገር ግን አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል የሚመጣውንም የዓለምን ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ አይቻልም።" ብሏል። ዕብ ፮፥፬-፮። ይህንን የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት የሚያረጋግጥልን የዴማስ ከኮበለለበት ዓለም አለመመለስ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፲። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላው በመመለሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ተለይቶታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬።

     

                                                                                             ይቀጥላል . . . .

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መንፈሳዊነት፦ ክፍል ፩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top