• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው ወይስ እውነት ? ክፍል ሁለት

     

    ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት

     

    ብዙዎቻችን ስለ አለቃ ገብረሐና ከልጅነታችን ጀምሮ ሰምተናል፡፡ አለቃ እንዲህ አሉ፣ይህንን መልስ ሰጡ፣እገሌን እንዲህ ብለው ቀለዱበት ወዘተ እየተባለ ተነግሮናል፡፡ታድያ ዘመኑ እየረዘመ ሲመጣ በብዙዎች ዘንድ አለቃ በተረት እንደነ ስንዝሮ የምናውቃቸው ሰው ናቸው ወይስ በዚህች ምድር አካል ነሥተው፣ነፍስ ዘርተው ተመላልሰዋል? የሚለው ጥያቄ ይነሣል፡፡ የዚህ ጥያቄ መነሻ ምክንያቱ ሁለት ይመስለኛል፡፡ አንዱ የታላላቅ ሰዎችን ሥራ በሚገባ መዝግቦ፣መታሰቢያቸውን አደራጅቶ፣ሥራቸው በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ልማዳችን እጅግም በመሆኑ አለቃ በቃል ብቻ በሚነገረው ሥራቸው እና ታሪካቸው የተነሣ ወደ ተረትነት በመቀየራቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዘመናችን ከኮምፒውተር፣ ከስልክ፣ ከመኪና እና ከአውሮፕላን ጋር የተያያዙ ቀልዶች ሁሉ በስማቸው ሲነገሩ ጊዜ አለቃ ገብረ ሐና እግዚአብሔር የፈጠራቸው ሰው ከመሆን ይልቅ በየዘመኑ የተነሣ ትውልድ ማለት የሚፈልገውን ሁሉ በስማቸው የሚልባቸው የተረት ገጸ ባሕርይ መስለው ታዩ፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና ግን በዚህች ምድር በኢትዮጵያ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ፎገራ ወረዳ ፣ናበጋ ጊዮርጊስ አጥቢያ ተወልደው ያደጉ የተፈጥሮ ሰው ናቸው፡፡ይህንን በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያገኛቸውን ያህል ማስረጃዎች ቀጥሎ ያቀርባል፡፡

     

    1. ትውልዳዊ

     

    ከአለቃ ገብረ ሐና የተወለዱ፣ ዘራቸውንም ከእርሳቸው ጀምረው የሚቆጥሩ ትውልዶች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን ያደረጉት ለተለየ ጥቅም ነው እንዳንል በዚህ ምክንያት ያገኙት ጥቅም የለም፡፡ ይህን የሚሉት የትውልድ እና ቀደምትን አክብሮ የማንሣት ኢትዮጵያዊ ባሕል አስገድዷቸው ብቻ ነው፡፡ ናባጋ ሄደን ብንጠይቅ የአለቃ ገብረ ሐና ዘር በዝቶ ተባዝቶ እናገኘዋለን፡፡ አለቃ ገብረ ሐና አለቃ ሥኑን ወለዱ፣ አለቃ ሥኑ ደግሞ አለቃ ኃይሉን ወለዱ፣ አለቃ ኃይሉም ዛሬ ናባጋ የሚኖሩትን ቄስ አሰጌን ወለዱ፡፡ የልጃቸው የወይዘሮ ጥሩነሽ ትውልድም እዚያው ፎገራ ይገኛል፡፡ እኔ አግኝቼ ለማናገር አልቻልኩም እንጂ፡፡ በእርግጥ የአቋቋሙ ሊቅ ተክሌ ልጅ እንዳልነበራቸው ከደብረ ታቦር ሊቃውንት እና ከተወላጆቻቸው ተነግሮኛል፡፡ ይህንን ትውልድ ስንመለከተው ከሦስቱ ልጆች እና የልጅ ልጆቻቸው መካከል ሁለቱ እንደ ገብረ ሐና «አለቃ» የሚለውን መዓርግ ደርሰውበት ነበር፡፡ቄስ አሰጌም ቢሆኑ የቤተ ክህነቱን ትምህርት ተምረውታል፡፡

     

    ናበጋ ወርጄ የአካባቢውን ሕዝብ ስጠይቅ የአለቃ ገብረ ሐና መንደር መሆኑን፣ ትውልዶቻቸው እነ ማን እንደሆኑ ነግረውኛል፡፡ የቄስ አሰጌ ልጆችም ዘራቸውን ሲቆጥሩት አለቃን ያነሷቸዋል፡፡

     

    2.አካባቢያዊ

     

    ናበጋ ጊዮርጊስ አለቃ ገብረ ሐና ቤት ሠርተውበት የነበረው ቦታ ዛሬ ሸንበቆ እና ቡና በቅሎበት ይታያል፡፡ እኔ እንዲያውም ይህ ውኃ ተከትሎ የሚበቅል ሸምበቆ አለቃን አይለቃቸውም ወይ አሰኝቶኛል፡፡ያኔ ከዐፄ ቴዎድሮስ ሸሽተው ዘጌ ደሴት ሲገቡ ያገኙት እና እንቅስቃሴውን ተመልክተው የአቋቋሙን ሥርዓት የቀመሙበ ሸምበቆው ነበር፡፡ ዛሬም በቤታቸው በቅሎ ይታያል፡፡ በናባጋ ጊዮርጊስ ደብር አለቃ የሕይወታቸውን የመጨረሻ ዘመናት የጸለዩበት ቦታ፣ ያድሩበት የነበረው ጥንታዊው ዕቃ ቤት፣ የተቀበሩበት ቦታ ዛሬም ይታያል፡፡ በመቃብራቸው ላይ የአካባቢው ሰዎች አክብረው ቤተ ልሔም ሠርተውበታል፡፡ ከዚሀም በተጨማሪ በዐፄ ምኒሊክ ተሾመው ያገለገሉበት እንጦጦ ራጉኤል፣ ጎንደር በኣታ ለማርያም ደብር የአለቃ ገብረ ሐናን አገልግሎት እና ማንነት ይመሰክራሉ፡፡

     

    3.ቅርሶች

     

    ከአለቃ ገብረ ሐና ጋር የተያያዙ ቅርሶች ዛሬም ይገኛሉ፡፡ ይለብሱት የነበረው እና የፈትሉ እና የጥልፉ ውበት የዚያን ዘመን ጥበብ የሚያሳየው ቀሚሳቸው ቅዳጅ፣ የመጽሐፋቸው ማኅደር በናበጋ ጊዮርጊስ፤ያሠሩት ከበሮ በጎንደር በኣታ ለማርያም የአቋቋም /ቤት ዛሬም ይገኛል፡፡

     

    4.የዘመነኞች ምስክርነት

     

    አለቃ ገብረ ሐና ጋር በአንድ ዘመን የመኖር እድልን ያገኙ ሰዎች አለቃ ገብረ ሐናን በተመለከተ የገለጿቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከጣልያናዊው አንቶንዮ አባዲ ጋር ደብዳቤ ይለዋወጥ የነበረው የዋድላው አሰጋኸኝ ጥር ስድስት ቀን 1858 . በጻፈው ደብዳቤ «አለቃ ገብረ ሐናን ንጉሥ መቱ ዋቸው በሽመል፡፡ ወደ ትግሬ ወደ ላስታ ተሰደዱ፡፡ እጅግ ተዋረዱ፡፡ እኔም በዋድላ አገኘኋቸው ወደ ቆራጣ ሄዱ፡፡» በማለት መግለጡ በዘመኑ አለቃ ገብረ ሐና እንደነበሩ የሚያመላክት ነው፡፡ በአለቃ ገብረ ሐና ዘመን የነበሩት አለቃ ለማ ኃይሉም ስለ አለቃ ገብረ ሐና ልዩ ልዩ መረጃዎችን ይሰጡናል፡፡

     

    5. የትምህርት ቤት የዘር ሐረግ

     

    በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ትውፊት መሠረት የታላላቅ ትምህርቶች ምስከሮች የዘር ሐረግ አላቸው፡፡ የድጓ፣ የቅኔ፣ የቅዳሴ፣ የአቋቋም፣ የትርጓሜ ወዘተ...፡፡ አለቃ ገብረ ሐና በአቋቋም ትምህርት ቤት በጎንደር በኣታ የመምህራን የዘር ሐረግ ውስጥ ስማቸው ይወሳል፡፡

     

    6. ፎቶ

     

    አለቃ ገብረ ሐና ፎቶአቸው ለትውልድ ከተቀመጠላቸው ጥቂት የጥንት ሊቃውንት አንዱ ናቸው፡፡ 1890 ዓም ሙሴ ሜንሮስ የተባለ ኢጣልያዊ ያነሣቸው ፎቶ ግራፍ እና አንድ እስካሁን ፎቶ አንሺውን ማወቅ ያልቻልኩት በኢንተርኔት የተለቀቀ ፎቶ ግራፍ አግኝቻለሁ፡፡

     

    የአለቃ ቀልደኛነት ከየት መጣ?

    የአለቃ ገብረ ሐና ቀልደኛነት ከየት መጣ? የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የተሟላ መልስ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን የተሻለ ግምት ለማቅረብ ብቻ እንሞክራለን፡፡ በአንድ በኩል የደብተራ ዘነብ፣ የአለቃ ገብረ ሐና፣ የዲማው ካሣ ጉዱ በአንድ ተመሳሳይ ዘመን መገኘት ዘመን ሊቃውንቱ በአዲስ መሥመር /አፈንግጦሽ/ የተጓዙበት ዘመን ይሆን? ያሰኘናል፡፡ ደብተራ ዘነብ ያዘጋጁት መጽሐፈ ጨዋታ ቅኔውን እንዴት አድርገው እያዋዛ ለሚያስረዳ አገላለጥ እንደተጠቀሙበት፣ አለቃ ለማ ኃይሉ ሕልውናውን የመሰከሩለት፣ በኋላም ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፋቸው የኪነ ጥበብን መልክ ቀብተው ያቀረቡት ጉዱ ካሣ ቅኔውን ሥርዓቱን ለመተቸት እንዴት እንዳዋለው ስናጤን እነዚህ ሰዎች የጎጃምን ቅኔ ሲቀምሱ ማን? ምን? አቀመሳቸው እንድንል ያደርገናል፡፡ ምናልባትም አንድ ተመሳሳይ መምህር ገጥሟቸው ይሆን ያሰኘናል፡

     

    በሌላ በኩል ደግሞ ፎገራን የሚጎበኝ ሰው ስለ አለቃ የሰላ ቀልድ አንድ ነገር ይጭርበት ይሆናል፡፡ ፎገራ ከኦሮምያዋ ግንደ በረት ጋር የተያያዘው የባርያ ንግድ አንዷ መተላለፍያ ነበረች፡፡ ወደ ደብረ ታቦር መንገድ ወጣ ብላ የምናገኛት «ኢፋግ» የባርያ ንግድ ማረፊያ ነበረች፡፡ ወረታ ፣በጠቅላላውም ፎገራ በጥንቱ የሲራራ ንግድ ዋነኛ መናኸርያ ነበረች፡፡ ታድያ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል በፎገራ የትግራይ፣የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች ተጽዕኖ ይታይ በታል፡፡ አለባበሱን፣ የፀጉር አቆራረጡን፣ ከወገብ በላይ ራቁት መሆንን ስትመለከቱ የእነዚህን ሕዝቦች አሻራ ታያላችሁ፡፡ በአካባቢውም በልዩ ልዩ ሕዝቦች የሚጠራ መንደርም አለ፡፡ለምሳሌ የትግሬ መንደር፡፡ ይህ ሁኔታ በአለቃ ገብረ ሐና ሕይወት ውስጥ ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? አለቃ አማርኛም ኦሮምኛም ትግርኛም የተቀላቀለበት ቀልድ የሚቀልዱት በዚህ ምክናያት ይሆንን አሰኝቶኛል፡፡

     

    ሌላም ነጥብ እናንሣ፡፡ የፎገራ ገበሬዎች ከዘመን የመፍጠን ጠባይ ይታይ ባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከኮርያ ባለሞያዎች የሩዝን ሁኔታ ተረድተው ለገበሬዎች ያስፋፉት አንድ የፎገራ ገበሬ ናቸው፡፡ ዛሬ የፎገራን መሬት ያለበሰው ሩዝ የኒህ ትጉ ገበሬ የአሠረጫጨት ዘዴ ውጤት ነው፡፡ የግብርና ባለሞያዎች በአዳዲስ ዘር አሠረጫጨት እና ገበሬውን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ጋር በማለማመድ ጉዳይ ከኒህ ገበሬ የሚቀስሙት ይኖር ይሆን? አስቲ እንጨምር፡፡ የፎገራ ገበሬ የሚያመርተው ሩዝ ዘለላው እሾህ ስላልነበረው ወፍ እየጠረጠረ ያስቸግረው ነበር አሉ፡፡ ታድያ ከዘመን የቀደሙ አንድ ገበሬ ዛላው እንደ ገብስ እሾሃማ የሆነ ዘር በምርምራቸው ማግኘታቸውን፣እንዲያውም በስማቸው ይህንን ዘር ለመሰየም እንቅስቃሴ መጀመሩን ከባለሞያዎች ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ከዘመን አፈንግጦ መጓዝ የሀገሩ ልማድ ይሆን? ገና ብዙ የአንትሮፖሎጂ፣የግብርና እና የታሪክ ምርምር የማሻው በመሆኑ ከኔ ይልቅ በዚህ ሞያ ልሒቅ ለሆኑት እንዲቀጥሉበት አደራ እላለሁ፡፡

     

    የአለቃ ገብረ ሐናን ቀልዶች ስንመለከት ቅኔያውያን ናቸው፡፡ በኋላ በዝር ዝር ለማስረዳት አንደምሞክረው የአለቃ ቀልዶች አመራማሪ፣ አስደናቂ፣ እንደ ጥቅስ ሁልጊዜ ሊነገሩ የሚችሉ፣ ፈጣን ናቸው፡፡ ይህ የአለቃ ቀልዶች ጠባይ ከምሁርነታቸው የመነጨ ይመስላል፡፡ አንድን ነገር ገልብጠው ማሰብ ይቸሉ ነበር፡፡ ጣና ሐይቅ ወስጥ የሸንበቆውን ንቅናቄ ተመልክተው ከዝማሜው ጋር ማዋሐዳቸው የአእምሮአቸውን ስለት ያስረዳናል፡፡ ከተሰጥኦዋቸው ጋር ቀልዳቸውን ያስዋበው የመላው ዕውቀታቸወ ነው፡፡

     

    የአለቃ ገብረ ሐና ሰብእና እና አስተዋጽዖ

     

    ሰብእና

     

    ብዙዎቻችን በቀልዳቸው ብቻ የምናውቃቸው አለቃ ገብረ ሐና በብዙ ሞያዎች የተካኑ ነበሩ፡፡ ባለ ቅኔ፣ የአቡሻክር እና የመርሐ ዕውር ሊቅ፣ የድጓ ምሁር፣ የፍትሐ ነገሥት ሊቅ፣ የአቋቋም ዐዋቂ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት መምህር ነበሩ፡፡ታደያ በሥራዎቻቸው እና በቀልዶቻቸው የእነዚህን ነፀብራቅ እናገኛለን፡፡ አለቃ ለማ ኃይሉ ስለ ሊቅነታቸው ሲመሰክሩ «የሞያ መጨረሻ እርሳቸው አይደሉም ወይ? የሐዲስ መምህር ናቸው፣ ፍታነገሥትን በርሳቸው ልክ የሚያውቀው የለም፤ ይኸ የቁጥሩን ÷መርሐ ዕውሩን፣ አቡሻከሩን የሚያውቅ ነው ባለሞያ፡፡ መቼም ለዚህ ለዝማሜ እሚባለው፤ ለመቋሚያ፤ እገሌ ይመስለዋል አይባልም፤ ከገብረ ሐና ፊት የሚዘም የለም» ይላሉ፡፡ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴም «አለቃ ገብረ ሐና እጅግ የተማሩ የጎንደር ሊቅ ነበሩ፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ ኃይለ ቃልና ጨዋታ ያውቁ ነበር» በማለት ይገልጧቸዋል፡፡ በጎንደር አድባራት ሊቀ ካህንነት፣ በአዲስ አበባ እንጦጦ ራጉኤል እና በአቡነ ሐራ ገዳም ተሾመው ማገልገላቸውን ስናይ ይህንን ዕውቀታቸውን ያስረዳልናል፡፡ እንዲያወም በዚያ ዘመን ከከበሩት አድባራት አንዱ አቡነ ሐራ ደንግል ገዳም ስለነበር ለዚያ አለቃ ሆኖ መሾም የታላቅነት ምልክት መሆኑን አለቃ ለማ ገልጠዋል፡፡

     

    .አለቃ ገብረ ሐና የድኾች ጠበቃ

     

    አለቃ ገብረ ሐና ምንም ከመኳንንቱ እና ከመሳፍንቱ ጋር ቢውሉ፣ምንም እንኳን የእንጦጦ ራጉኤል ሰዎች እንደሚናገሩላቸው በዐፄ ቴዎድሮሰ ቤተ መንግሥት ከምኒሊክ እና ከእቴጌ ምንትዋብ ቀጥለው ግብር የሚቀመጡት ገብረ ሐና ቢሆኑም ድኾች ሲጨቆኑ እና ሲያዝኑ ግን አይወዱም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የአቡነ ሐራ ገዳም አካባቢ ርሃብ ገብቶ ገበሬው ሲቸገር ቢያዩ «እናንተ ባገኛቸሁ ጊዜ ለአቡነ ሐራ እንደሰጣችሁ ሁሉ እናንተ ሲቸግራችሁ ደግሞ አቡነ ሐራ ይሰጧችኋል» ብለው ከሥዕለት የተሰበሰበውን ገንዘብ አውጥተው ለገበሬዎች አከፋፈሉት፡፡ በዚህ ጉዳይ ተከስሰው ከፍርድ ሚኒስቴሩ ከአፈ ንጉሥ ነሲቡ ዘንድ ቀርበው ሊፈረድባቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሊቀ መኳስ አባተ ያለው ዐፄ ምኒሊክ አለቃ ገብረ ሐናን ሲያደነቁ እንደሚሰሙ እና አፈንጉሥ ለሚሰጡት ፍርድ እንዲጠነቀቁ በማመልከታቸው ጉዳዩ ወደ ዙፋን ችሎት ተመራ፡፡ ዐፄ ምኒሊክም አለቃ ገብረ ሐናን የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ አንተ አይደለህም ወይ? እስቲ ምን ይላል ንገረን? አሏቸው፡፡ አለቃም «ፍትሐ ነገሥቱማ ሲሦውን ለካህናት፣ሲሦውን ለሠራያን ይገባል ይላል፡፡ እኔም ክፉ ቀን ስለሆነ ለሕዝቡ አካፍየዋለሁ፡፡ አቡነ ሐራ አባታቸውን አይጦሩበት፣ልጃቸውን አይድሩበት» ሲሉ መለሱላቸው፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና ከምኒሊክ ባለሟሎች ጋር ተጣልተው ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ አበባን ለመልቀቅ ያበቃቸውም መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ግብዝናውን እየተሾሙ የድኻውን ካህን መሬት እየወሰዱ ካሀኑን በቶፍነት ስም ጭሰኛ ማድረጋቸውን በመቃወማቸው ነበር፡፡ አለቃ ይህንን አሳዛኝ አሠራር ፊት ለፊት ተቃውመውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአዲሰ አበባ ይወጡ ተብለው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በቅተዋል፡፡

     

    . አለቃ ገብረ ሐና ንጉሥ የማይፈሩ

     

    ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ በሚባልበት በዚያ ዘመን ነገሥታቱን እና መኳንንቱን በመገሠጽ አለቃን የሚወዳደር አልነበረም፡፡ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን አምስት ልዑክ ይበቃል ብለው ዐፄ ቴዎድሮስ ያነሡትን ሃሳብ አለቃ ገብረ ሐና አልተቀበሉትም፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን ሲመረቅ አለቃ ተጋብዘው ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም እንዴት ነው ቤተ ክርስቲያኑ ብለው ቢጠይቋቸው ማነሡን ለመግለጥ «ለሁለት ካህን እና ለሦስት ዲያቆን በቂ ነው» አሏቸው፡፡ በዚሀም ከቴዎድሮስ ጋር ተኳረፉ፡፡

     

    አስተዋጽዖ

     

    1.ዝማሜ

     

    አለቃ ገብረ ሐና ለቤተ ክርስቲያን እና ለኢትዮጵያ ካበረከቱት ነገር አንዱ «የተክሌ ዝማሜ» የሚባለው ነው፡፡ አለቃ ገብረ ሐና ይህንን የመቋሚያ ስልት ያዘጋጁት ከዐፄ ቴዎድሮስ ሸሽተው ዘጌ በገቡ ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ የነበረውን የሸንበቆ ውዝዋዜ ተመልክተው ከአቋቋሙ ስልት ጋር አዋሕደው ከባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ ጋር በመሆን ነበር፡፡ ባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ ወደ ዓለም ስላልተመለሱ አለቃ ገብረ ሐና ይህንን አዲስ ዝማሜ ይዘው ጎንደር ገቡ፡፡ ወዲያወም የአቋቋሙ መምህር አለቃ ገብረ ሐና ለተማሪዎቻቸው አዲሱን ዝማሜ ማስተማር ጀመሩ፡፡ጎንደሮች ሲያገለግሉ ሸማቸውን ታጥቀው ስለነበር በሚያዘሙበት ጊዜ በተመስጦ ወዲያ እና ወዲህ ሲሉ ሸማቸውን እያስጣለ ቢያስቸግራቸው ካህናቱ ተመካክረው አለቃ ይህንን ዝማሜ እንዳያስተምሩ ወሰኑባቸው፡፡ በዚሀ ጊዜ አለቃ ለልጃቸው ለተክሌ ደብቀው ማስተማር ጀመሩ፡፡

     

    ተክሌ የደርቡሽን ወረራ ሸሽቶ ወሎ ራስ ሚካኤል ዘንድ በሄደ ጊዜ ተንታ ሚካኤል ሲመረቅ ያንን ተደበቆ የኖረ ዝማሜ አወጣው መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ፣ሕዝቡ እና ካህናቱ ተገርመው ያዳምጡት እና ያዩት ጀመር፡፡ ሲጨርስም ራስ ሚካኤል በተንታ ሚካኤል ይህንን ዝማሜ እንዲያሰተምር አደረጉ፡፡ በኋላም የደብረ ታቦሩ ራስ ጉግሣ ራስ ሚካኤልን ለምነው ለደብረ ታቦር ኢየሱስ አለቃ አድርገው ተክሌን ወሰዱት እርሱም በዚያ ሲያስተምር ቆይቶ እዚያው ዐረፈ፡፡ ዝማሜውም በስሙ «ተክሌ» እየተባለ ተጠራ፡፡

     

    እንዲያውም ተክሌ በሞቱ ጊዜ

     

    ተከሌ ገብረ ሐና ተከተተ ጣቱ

    መንክሩን ክሥተቱን የዘመመበቱ

     

    ብላ አልቃሽ ገጥማ ነበር፡፡ ራስ ጉገሣም «ምን ተክሌ ሞተ ትሉኛላቸሁ ደብረ ታቦር ኢየሱሰ ፈረሰ በሉኝ እንጂ፤ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቢፈርስ ከዚህ አስበልጬ እሠራው ነበር ተክሌን ግን ከየት አገኘዋለሁ» ማለታቸው ይነገራል፡፡

     

    2. ሰም እና ወርቅ ቀልድ

     

    ብዙዎቻችን አለቃን የምናውቃቸው በሰም እና ወርቅ ቀልዳቸው ነው፡፡ ሌቨን ዶናልድ የተባሉ ደራሲ «ሰም እና ወርቅ»» Wax and gold በተሰኘው መጽሐፋቸው አለቃ ገብረ ሐና በሰም እና ወርቅ ቅኔያቸው፣ በቀልዳቸው እና በፈጣን መልሳቸው እንዲሁም በሂሳቸው የታወቁ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ የአለቃ ገብረ ሐና አብዛኞቹ ቀልዶች ሰም እና ወርቅ ቅኔ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን የግእዝ ቅኔ ስልት የተከተለ ነው፡፡

     

    ምንጭ  ዐረፈ ዓይኔ ሐጎስ፣ አለቃ ገብረ ሐናና አስቂኝ ቀልዶቻቸው፣ አዲስ አበባ፣1979 ዓም፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ታኅሣሥ 101978 ዓም(ምን ሠርተው ታወቁ) ዓምድ) መንግሥቱ ለማ፣ መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ፣ አዲስ አበባ 1959 ዓም፣ገጽ 137-138፤ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣የሕይወት ታሪክ፣አዲስ አበባ፣1918 ዓም፣ገጽ 89 ኤልሳቤጥ ገሠሠ፣ በአለቃ ገብረ ሐና የሚነገሩ ቀልዶች፣ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል ለዲግሪ ማሟያ የቀረበ፣ አአዩ፣ 1974 ዓም፤ Sven Rubenson, ed. Acta Ethiopica: Tewodros and His Contemporaries 1855-1868, p259

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው ወይስ እውነት ? ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top