• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    ቅዱስ ጴጥሮስ

    የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተሳይዳ ነው።የቤተሳይዳ ትርጉም የዓሣ አጥማጆች ቤት ማለት ነው። ጌታችን በዚህች መንደር ዓይነ ስውሩን ፈውሶታል። ማር፡፰፥፳፪።ኅብስት አበርክቶ የመገበውም ለቤተሳይዳ ቅርብ በሆነ ምድረ በዳ ነው። ሉቃ፡፱፥፲፪።የቤተሳይዳ ሰዎች፡- ትምህርቱን ሰምተው፥ተአምራቱንም አይተው ንስሐ ባለመግባታቸው ከተወቀሱት መካከል ናቸው። ሉቃ፡፲፥፲፫። የአባቱ ስም ዮና ይባላል።ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ ያደገው በቅፍርናሆም ነው። በገሊላ ባሕር ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር ዓሣ ማጥመድ የጀመረው በጐልማሳነቱ ነው። ለደቀ መዝሙርነት ሲመረጥ ዕድሜው ፶፭ እንደነበረ በዜና ሐዋርያት ተገልጧል። ወደ ጌታችን ያመጣው ወንድሙ እንድርያስ ነው። ጌታችንም፡- "አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤አንተ ኬፋ ትባላለህ፤" ብሎታል። ትርጓሜውም ጴጥሮስ(ዓለት) ማለት ነው። ኬፋ በአራማይክ፥ ጴጥሮስ ደግሞ በግሪክ ቋንቋ ነው። ዮሐ፡፩፥፵፩-፵፫።                                              

     

    ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን የተከተለው ሁሉን ትቶ ነው።" ኢየሱስም፡-በኋላዬ ኑና ሰዎችን የምታጠምዱ (የኃጢአት ባሕር ካጥለቀለቀው ዓለም በወንጌል መረብነት የሰውን ሕይወት እየያዛችሁ፥ በደሜ ወደምመሠርታት መርከብ፥ ወደ ቤተክርስቲያን የምታመጡ) አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።" ይላል። ማር፡፩፥፲፯። የቅዱስ ጴጥሮስ ቍጥሩ አዕማድ ወይም የምሥጢር ሐዋርያት ከሚባሉት ከቅዱስ ዮሐንስና ከቅዱስ ያዕቆብ ጋር ነው። እነዚህ ሦስቱ ፥ጌታችን፡- የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት ሲያስነሣ፥ አምላካዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ሲገልጥ፥ በጌቴሴማኔ ለአብነት ሲጸልይ አብረውት ነበሩ። ማር፡፭፥፴፭፣ ማር፡፱፥፪፣ማር ፲፬፥፴፪።                                      

                                      

                   ቅዱስ ጴጥሮስ ፈጣን ደቀመዝሙር ነበር። ጌታ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ ሲራመድ ባየ ጊዜ፥ ጌታን አስፈቅዶ እርሱም ሞክሮ ነበር። ነገር ግን በእምነቱ ገና ስለነበረ፥የነፋሱ ኃይል  አስፈርቶት ተጠራጠረ፤ መስጠምም በመጀመሩ "ጌታ ሆይ፥አድነኝ፤" ብሎ ጮኸ። ጌታም፡-"አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ ?" ብሎ፥ ቀኝ እጁን ይዞ አዳነው ማቴ፡፲፬፥፳፰-፴፩።በፊልጶስ ቂሣርያም "እኔን ማን እንደሆንኩ ታምናላችሁ?" ብሎ፥ጌታ ለጠየቀው ጥያቄ፥ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ፤" በማለት ፈጥኖ የመለሰ እርሱ ነው። በዚህም ምክንያት፡-"የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አልገለጠልህምና (ሥጋዊ ደማዊ መምህር አላስተማረህምና) ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ(ዓለት) ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ (ምእመናንን እሰበስባለሁ) የገሃነም ደጆችም (የገሃነም ደጅ ጠባቂ አጋንንት) አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።" ተብሎአል። ማቴ፡፲፮፥፲፭-፲፱።                        

              ጌታችን መከራ መስቀሉንና ትንሣኤውን በተናገረ ጊዜ፥ ፈጥኖ "አይደረግብህ፤" ያለ ቅዱስ ጴጥሮስ ነው። ጌታም፡-"አንተ ሰይጣን ወደ ኋላዬ ሂድ፤" በማለት ገሥጾታል። በዚህም በጴጥሮስ አንጻር የሰውን ድኅነት የማይሻ ሰይጣንን እንደገሠ ፀው እናስተውላለን። ማቴ፡፲፮፥፳፩-፳፫። ምክንያቱም፡- ቅዱስ ጴጥሮስ  "አይደረግብህ፤" ማለቱ ለጌታ አዝኖለት ነውና። ግብር የሚቀበሉ ሰዎች፥ "መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር አይገብርምን?" ባሉትም ጊዜ፥ ፈጥኖ "አዎን ይገብራል፤" ብሏል። ጌታ ግን፥ ማስገበር እንጂ መገበር እንደማይገባው በምሳሌ ከነገረው በኋላ፥"ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር ታገኛለህ፤ ያንን ወስደህ ስለ እኔና አንተ ስጣቸው።" ብሎታል። ማቴ፡፲፯፥፳፬-፳፯። ጌታችን፥የጸሎተ ሐሙስ ምሽት፥ "በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤" ባላቸውም ጊዜ፥"ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከ ልም፤" በማለት ፈጥኖ መልሶአል። ጌታም፡-"ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤" ብሎታል። አሁንም ፈጥኖ፥ "ሞትም ቢመጣብኝ አልክድህም፤" ብሎአል። ማቴ፡፳፮፥፴-፴፭። ጌታ የተናገረው ቃል በተፈጸመበት ጊዜም በመራራ ልቅሶ ንስሐ ገብቶአል። ማቴ፡፳፮፥፷፱-፸፭። ጌታችን በአይሁድ እጅ በተያዘ ጊዜም ፈጥኖ ሰይፉን በመምዘዝ፥ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ የማልኰስን ጆሮ ቆርጦ ጥሎታል።ጌታ ግን "ሰይፍ የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና፥ ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤" ብሎታል። ማቴ፡፳፮፥፶፩-፶፪።  

                            

             ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ከበረከት ጋር ለደቀመዛሙርቱ በመገለጥ አብሮአቸው ተመግቦአል።በመጨረሻም፡- ቅዱስ ጴጥሮስን "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?" በማለት ሦስት ጊዜ ጠይቆታል።እርሱም፡-"ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ፤" ሲል ሦስቴም መልሶለታል። ከጥያቄዎቹም ጋር፡-ግልገሎቼን (ሕጻናትን፣ወጣንያንን) አሰማራ፥ ጠቦቶቼን(ወጣቶችን፣ማዕከላውያንን) ጠብቅ፥በጎቼን (አረጋውያንን ፣ፍጹማንን) አሰማራ፥ ተብሎአል። ዮሐ፡፳፩፥፩-፲፯።      

     

    ቅዱስ ጴጥሮስ በአራቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሚገኘው የሐዋርያት ዝርዝር ላይ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ ይገኛል። ይህም የሆነው፡- በሽምግልናው፥ በቂሳርያ በተሰጠው ቃል ኪዳን፥ የሐዋርያት አፈ ጉባኤ ሆኖ ይናገር ስለነበር እና በጥብርያዶስ በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ነው። በይሁዳ ምትክ ሌላ ሐዋርያ እንዲመረጥ አሳብ ያቀረበ እርሱ ነው። የሐዋ፡ ፩፥፲፮ -፳፫። የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በተሰጣቸውም ዕለት የሐዋርያት አፈ ጉባኤ ሆኖ ወንጌልን የሰበከ ሦስት ሺህ ሰዎችንም ያሳመነ እርሱ ነው። የሐዋ፡፪፥፲፬-፲፯።ከዚህ በኋላ ፍርሃት ርቆለት፥ በጌታ ስም ሕሙማንን የሚፈውስ፥ ስለ ስሙም በድፍረት የሚመሰክር ሆኖአል። የሐዋ፡፫፥፮፣፬፥፩-፳፪።ቆርኖሌዎስን በማጥመቅ፥ ወንጌልን ቀድሞ ለአሕዛብ የሰበከ እርሱ ነው። የሐዋ፡ ፲፥፩-፲፩። ከተሰጠው ጸጋ የተነሣ የአካሉ ጥላ ያረፈበትን ሁሉ ከማናቸውም ደዌ ይፈውስ ነበር። የሐዋ፡፭፥፲፭። በሰንሰለት ታስሮ ወደ ወኅኒ በተወረወረ ጊዜ፥የጌታ መልአክ የወኅኒውን ቁልፍ ከፍቶ፥ ሰንሰለቱን ፈትቶ አድኖታል። የሐዋ፡፲፪፥፩-፲፩። በ፶ .. ገደማ በኢየሩሳሌም በተካሄደው የሐዋርያት ሲኖዶስ፥ ከአንጾኪያ ክርስቲያኖች ለቀረበው ጥያቄ የመጀመሪያውን መልስ የሰጠ እርሱ ነው።የሐዋ፡፲፭፥፩-፵፩።                   

              

    ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፋ ያለ ሆኖ ሪዛምና ራሰ በራ ነበር።በፍልስጥኤም፣ በሶርያ፣ በጳንጦን፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በቢታንያና በሮሜ ሰብኳል። በሮሜ ለ፳፭ ዓመታት እንዳስተማረ የሮማ ሰዎች ይናገራሉ።በቅድሚያ ሮሜ ገብቶ ያስተማረ ግን ቅዱስ ጳውሎስ ነው።ለዚህች ከተማ መልእክት እንዲጽፍ ያደረጉት በኔሮን የጥፋት አዋጅ ምክንያት ተሰደው ቆሮንቶስ የገቡት አቂላስና ሚስቱ ጵርስቅላ ናቸው። እርሱ በአንድ ቦታ ብቻ ስለማያስተምር፥ ለዚያች ሀገር ጳጳሳትን ከሾመላት በኋላ ወደ ስብከቱ ሲሄድ ነበር ቅዱስ ጴጥሮስ ሮም የደረሰው። ከላይ እንደተገለጠው የተጠራው በ፶፭ ዓመቱ ነው፥ከጌታ ጋር ያሳለፈው ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው፥ ዙሮ ያስተማረው ለ፳፯ ዓመታት ነው፥ በሮሜ በማስተማርና በእስር የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው።ከቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ አንፃር ትክክለኛው ይህ ነው።                                                        

              ቅዱስ ጴጥሮስ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር አንድ ዓመት ካስተማሩ በኋላ ክርስትና ወደ ቤተ መንግሥት ገባ። የቅርብ ባለሥልጣናት የሆኑ የአልቢኖስና የአግሪጳ ሚስቶች ክርስቲያኖች ሆኑ። በዚህን ጊዜ የክርስትና ጠላት ኔሮን በቅንዓት ተነሣባ ቸው።ኔሮን በሮም የነገሠው በ፶፬ .. ነው፥ በነገሠ በዓመቱ የአባቱን ልጅ አስገደለ፥ በ፶፱ .. እናቱን በመርዝ ገደለ፥ በ፷፪ .. የልጅነት ሚስቱን አግታሺያን አስገደለ፥ ከእርሷ በኋላ ያገባትን ፓፕያንም በርግጫ ብሎ ገደላት፥በ፷፬ .. በጥጋብ የሮማን ከተማ እሳት ለቀቀባት። የሮማ ሕዝብ እጅግ በመቆጣቱ፥ አንደኛ፡-የሮማ ጣዖታት በክርስቲያኖች ላይ ተቆጥተው እሳት አዘነሙ። ሁለተኛ፡- ክርስቲያኖች ከተማዋን አቃጠሉ፥ የሚል ሁለት ዓይነት ወሬ አስወራ። የተቆጣውም ሕዝብ ክርስቲያኖችን እያሳደደ ይገድል ጀመር። ቅዱስ ጳውሎስ በእስር ቤት ስለነበር በዚያው ተሰይፎ ዐረፈ። ይህን የሰሙት የአግቢኖስና የአግሪጳ ሚስቶች፥ ቅዱስ ጴጥሮስን፡- "ባይሆን አንተ እንኳ ትረፍልን፤"ብለው፥ በቅርጫት አድርገው፥ በገመድም አስረው ከከተማዋ ግንብ ላይ አውርደው አስመለጡት።                   

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ ጴጥሮስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top