?
ድንግል ማርያምን ጥንተ አብሶ [የዘር ኃጢአት]ይመለከታታል?
ከእነምክንያቱ ሲብራራ!!!
ድንግል ማርያም የዘር ኃጢያት የለባትም ለዚህም እጅግ በርካታ ማረጋገጫዎችን መዘርዘር ሲቻል በዚህ ጽሁፍ ግን ለጊዜው የሚከተሉትን ሶስት ነጥቦች እንመለከታለን
፩.አስቀድመው ነብያት የዘር ኃጢአት [ጥንተ አብሶ ] እንደሌለባት አስረግጠው ተናግረዋል ከነዚህም ጥቂቶቹ ለመመልከት ያህል
፩.፩ ነብዩ ኢሳይያስ «እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ስዶም በሆንን እንደ ግሞራም በመሰልነ ነበር» ኢሳ፩፤፱ ዘር የተባለች ዓለም የዳነባት አምላክ ሰው የሆነባት ድንግል ማርያም ናት ቅዱስ ጳውሎስ በእብራዊያን ክታቡ «የአብራሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም » እብ፩፤፲፮ በማለት ጌታ ሰው የሆነባትን ዘር የአብርሃም ዘር እያለ ይጠራታል ነቢዩ ኢሳያስም እግዚአብሔር ያስቀራት ዘር ያላት እመቤትችንን ነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው ሲሆን ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን ለይቶ በንጽሐ ስጋ በንጽሐ ነፍስ ጠብቆ ከስጋዋ ስጋ ከነፍስ ነፍስ ነስቶ ዓለምን ለማዳን ምክንያት ያደረጋት ዘር ናት፡፡
፩.፪ ነብዩ ዳዊት « የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግስቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ልጄ ሆይ ስሚ እይ ጆሮሽንም አዘንብይ ወገንሽን የአባትሽን በት እርሺ ንጉስ ውበትሽን ወዶአልና» መዝ፵፬፤፱-፲፩ መቼም ማንም ሊከራክር ቢወድ ከእመቤታችን በላይ ለሌላ ይህ ቃል ገላጭ በምንም መልኩ አያስከድም ይልቁንም በምስተዋል ላነበበው ድንግል ማርያምን የሚገልጽ ጥልቅ ትምህርት ማግኘት ይችላልወርቅ የንጽሕና ምሳሌ ሲሆን ደርባ ደራርባ የተባለው ደግሞ ንጽሓ ስጋ ላይ ንጽሓ ነፍስ ንጽሃ ነፍስ ላይ ንጽሓ ልቦና መደራረቧን የሚያስረዳ ነው ወገንሽን የአባትሽን ቤት እርሺ የተባለው ደግሞ ከሰው ዘር በሙሉ መለየቷን የዘር ኃጢአት እንዳላገኛት የሚያስረዳ ነው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እመቤታችንን ልጄ እያለ መጥራቱ ከሱ ዘር እንደምትወለድ ያስረዳናል ጌታም ከሷ ስለተወለደ የዳዊት ሊጅ ተብሎ ተጠርቷል ማቴ፩፤፩ ንጉስ የተባለ ልጇ እይሱስ ክርስቶስ ሲሆን ውበትትሽን ወዷልና ማለት ውበት ንጽሕናሽን ሊዋሃደው ወዷልና ማለት ነው
፩.፫ ጠቢቡ ሰሎሞን «ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም» መኃ፬፤፯ ጠቢቡ ሰሎሞን በመንፈሰ ትንቢት ተቃኝቶ እመቤታችንን ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን የተለየ ንጹህ ነው ብሎ አመስግⶈታል ::
፪. የቅዱስ ገብርኤል ብስራታዊ ሰላምታ እመቤታችን የጥንተ አብሶ ፍዳ (የዘር ኃጢአት ) እንደሌለባት በሚገባ ያስረዳል ይህንንም እንደሚከተለው በሶስት ክፍለን ማየት እንችላለን
" ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ጌታ ካንቺ ጋር ነው
አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ" ሉቃ ፩፣ ፳፰
ግሩም ከሆነው የመልአኩ የምስጋና ቃል ውላዲተ አምላክ ኃጢአት የሚባል ጨርሶ እንደማያውቃት ሶስት ጥልቅ የሆኑ መልእክቶችን እንመልከት
፪.፩" ጸጋ የሞላብሽ ሆይ"
እናስተውል የሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ ጎሎአቸዋል በተባለበት ዘመን ጸጋ የሞላብሽ የሚል ልዩ ምስጋና የቀረበላት እመቤታችን ብቻ ናት በጥንተ አብሶ ፍዳ ምክንያት ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲህ ነበር የተባለው
"ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር (ጸጋ )ጎሎአቸዋል" ሮሜ፫፤፳፬
እንግዲህ ሁሉ ጸጋ ጎሎአቸዋል የተባለው ሁሉ ኃጢአት ስለሰሩ አይደለም ነገርግን አዳማዊ መርገም በሁሉ ስለደረሰ ነው ለዚህም ነው
"ኃጢአት ባልሰሩት ላይ እንኳን ሞት ነገሰ " ሮሜ፭፤፲፬ ተብሎ የተጻፈው ታድያ ሰው ሁሉ መረገመ አዳም ስለደረሰበት ከጸጋ በታች ከተባለ ድንግል ማርያም እንዴት ጸጋ የሞላብሽ ተባለች ? ይህ በርግጥም እመቤታችን የዘር ኃጢአት ፍዳ እንደማይመለከታት ያስረዳናል ድንግል ማርያም ይህ የምስጋና ቃል የቀረበላት ጌታን ገና ከመጽነሷ በፊት ነው ይህ ማለት ደግሞ ጌታችን ሰው ሆኖ ጸጋ ለጎደለው አለም ካሳ ቤዛ ሳይሆንለት ድንግል ማርያም ጸጋ የሞላብሽ ተባለች ማለት ከእናቷ ማህጸን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን ጠብቋታል ማለት ነው
፪.፪ ከሴቶች መካከል
ሁለተኛው ነጥብ ድንግል ማርያም ከሴቶች ተለይታ የተባረከች እንድትባል ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ በዘር ኃጢአት ምክንያት በሌሎች የደረሰ መረገም በእርሷ ስላልደረሰ ነው እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይህ ምስጋና ባልተገባትም ነበር ስለ ሌሎች የሰው ልጆች መጽሓፍ ቅዱስ ሲገልጽ
" ልዩነት የለም ሁሉ ከበደል በታች ናቸው" ሮሜ፫፤፳፪ ይላል
ስለእመቤታችን ሲናገር ግን ከሴቶች መካከል ብሎ መለየቷን በግልጽ ያስቀምጣል እንግዲህ ሰው ሁሉ ያለ ልዩነት ከበደል በታች በተባለበት ዘመን እርሷ የተለየች ከተባለች በእርግጥም ወላዲተ አምላክን የውርስ ኃጢአት ፍዳ አይመለከታትም ማለት ነው ። እመቤታችን ከብር ምስጋና ይግባትና የጥንተ አብሶ ፍዳ ይመለከታታል ከተባለ የእርሷ መለየት የቱ ጋ ሊሆን ነው? ስለዚህም የመልአኩ የሰላምታ ቃል ስህተት ነው እንላለን? አንልም እውነታውን ይዘን ድንግል ማርያም በእውነት ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን የተለየች ንጽህይት ቅድስት መሆኗን እንመሰክራለን እንጂ
፪.፫ የተባረክሽ ነሽ
በሶስተኛ ደረጃ ከመልአኩ የምስጋና ቃል ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት እንደሌለባት የሚያስገነዝበን የተባረክሽ ነሽ የሚለው ኃይለ ቃል ነው በጣም የሚገርመው በዚሁ ተመሳሳይ ቃል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስም በተመሳሳይ ስፍራ ምስጋና ቀርቦለታል
"አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው"ሉቃ፩፤፵፪
እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለንና እመቤታችንም ይተባረክሽ ነሽ ጌታም የተባረከ ነው የሚል ተምሳሳይ ምስጋና ቀርቦላቸውል ይህ ማለት ሁለቱንም የጥንቱ መርገም እንደማይመለከታቸው ያመልክታል የበረከት ተቃራኒ መርገም ነው ስለዚህም የተባረክሽ ነሽ ማለት መርገም የሌለብሽ ነሽ ማለት ሲሆን ጌታ ደግሞ የተባረከ ነው ሲባል መርገምን የሚያርቅ ማለት ነው። ልዩነቱን ልብ እንበል እምቤታችን የተባረክሽ ስትባል ከእናቷ ማህፀን ጀምሮ ልጇ ከምርገም ጠበቃት ማለት ሲሆን እርሱ ጊን የተባረከ ነው ሲባል ለባህሪው መርገም የማይስማማው ከሌሎች መርገምን የሚያርቅ ማለት ነው።
በአጠቃላይ ድንግል ማርያም ከላይ በመልአኩ የሰላምታ ንግግር ከብዙ በጥቂቱ እንደተመለከትነው የዘር ኃጢአት በፍጹም እንደማይመለከታት ነው ይህም አምላክ አለምን ለማዳን ከእርሷ ከስጋዋ ስጋ ክነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ለምሆን ያዘጋጃት በመሆኗ የእርሷ ንጽህና በሰው ልጆች መዳን ውስጥ በምክንያትነት ወደፊት በቀጣዩ ክፍላችን የምንመለከተው ይሆናል
3.እመቤታችን ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት አለባት ማለት የጌታችንን ንጹሐ ባህሪውን መዳፈር ነው
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሰው ሲሆን ስጋና ነፍስን ከሰማይይዞ አልወረደም ሰው የሆነው የእኛን ባህሪይ ተዋሕዶ ነው።ይህን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል"እንግዲህ ልጆቹ በስጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይስለጣንያለውንእንዲሽር-እንዲሁ ተካፈለ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም''ዕብ2፤14-15
እንግዲህ ጌታ ሰው ሲሆን ስጋንም ነፍስንም ከድንግል ማርያም ከነሳእርሷ ደግሞ መርገም ነክቶአታል ከተባለ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታ ኃጢአትያለበትን ስጋ ተዋሐደ ልንል ነውን?እንዲህማ ካልን ተረፈ አይሁድ ሆነናል ማለትነው ምክንያቱም ደፍረው ጌታን ኃጢአት አለበት ያሉት አይሁድ ናቸውና
" ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን" ዮሐ 9፤24
እኛስ ከእመቤታችን ምንም ምን ኃጢአት ያላወቀውን ስጋ እንደነሳ እንመሰክራለን እንደ እውነተኞቹ አባቶቻችን ጌታችን ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መወለዱን እናምናለን እንመሰክራለን
" ኦ ድንግል አኮ ዘተአምሪ ርስሐተ ከመ አንስት እለ እምቅድሜኪ ወእምድሬኪ አላ በቅድስና በንጽሕና ስርጉት አንቲ " ትርጉም"ድንግል ሆይ ካንቺ አስቀድመው ካንችም በኋላ እንደ ነበሩ ሴቶች አደፍ ጉድፍን የምታውቂ አይደለሽም በቅድስና በንጽሕና ጸንተሽ ኖርሽ እንጂ"ቅዳሴ ማር5፤42
መቼም አባቶቻችን እነ ቅዱስ ኤፍሬም እነ አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የደረሱአቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት የማይቀበል ኦርቶዶክሳዊ አለ ማለት እጅግ ይከብዳል ፡፡ እንግዲህ ቅድስት ቤተክርስትያን ስለነገረ ማርያም በጥንቃቄ የምታስተምረው ስለድንግል ማርያም የምናምነው ነገር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከጌታችን ማንነት ጋር ተያያዥነት ስላለው ነው እግዚአብሔር ይግለጥልንና ጌታ ከእመቤታችን መርገም ያለበትን ስጋ ተዋሐደ ማለት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መሰረታዊ ተቃርኖዎችን ያስነሳል።
ማሳሰቢያ
ታድያ አንዳንዶች በቤተክርስትያኒቱ የሌለ አስተምህሮ በብሎጎቻቸው እና በመጻሕፍቶቻቸው የኦርቶዶክስ እያስመሰሉ አንዳንድ ጥልቅ ግንዛቤ የሌላቸውን የዋሃን ክርስትያኖችን ለማሳሳት የሚያደርጉትን የስህተት ተልዕኮ አውቀን ልንጠነቀቅ እንደሚገባ ብሎጋችንን ለምትከታተሉ ምዕመናን ሁሉ አበክረን እናሳስባለን
ከላይ በተነሳው ጥያቄ ላይ እስከ ክፍልሶስት ድረስ በተከታታይ ምላሽ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል በዚህ ጽሑፋችንም ቀጣዩን ክፍልይዘንላችሁ ቀርበናል እግዚአብሔር አምላክበማስተዋል ማንበቡን ያድለን አሜን በቀደሙት ጽሁፎቻችን እመቤታችን የውርስ ኃጥአት እንደማይመለከታት ከብዙ በጥቂቱ ለመመልከት ሞክረናል በዛሬው ጽሑፋችን ድንግልማርያም የውርስኃጢአት ይመለከታታል ማለት በመሰረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ላይ የሚያስነሳቸውን ተቃርኖዎች ለመመልከት እንሞክራለን ።
ከዚህ ቀደም ተከታታይ ባቀረብናቸው ጽሑፎች ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት እንደማይመለከታት ከብዙ በጥቂቱ ለማየት ሞክረናል ቀጣዩን ጽሑፋችንን ይዘንላችሁ ቀርበናል በአሰተውሎት ማንበቡን እግዚአብሔር ያድለንበክፍል አራት ጽሑፋችን«ወለደት ድንግል ዘፀንሰቶ እንዘ ኢተአምር ብእሴ በስጋ ዘፈጠሮ ለርእሱ ወወለደቶ ዘእንበለ ደነስ ወሕማም ወኢረሰስሐት በሐሪስ ሐፀነቶ ዘእንበለ ፃማ ወድካም ወአጥበቶ ዘእንበለ ድካም ወአልሐቀቶ በሕግ ዘሥጋ ዘእንበለ ትካዝ ።»
« ለተዋሕዶ የፈጠረውን ሥጋ ያለ ወንድ ዘር ያለ ኃጢአት ያለምጥ ወለደችው የአራስነት ግብርም አላገኛትም ያለድካም ያለመታከት አሳደገችው ያለድካም አጠባችው ለስጋ በሚገባ ሕግ ምን አበላው ምን አለብሰው ሳትል አሳደገችው» ሃይማኖተ አበው ዘአትናትዮስ ፳፰፡፲፱ትርጉም ማብራሪያውን በቀጣዩ ጽሁፋችን እንመለከታለን ብለን ነበር ያቆምነውሐዋርያዊው ቅዱስ አትናትዮስ ካስተማረው ትምህርት እመቤታችን የጥንተ አብሶ ፍዳ እንደማይመለከታት በሚገባ ማስተዋል ይቻላል ግልጽ ለማድረግም የሚከተሉትን ነጥቦች መመልከት ይቻላል፡፡
1.ያለ ኃጢአት ከሚለውቃልወላዲተ አምላክ ጌታን ምንም ምን ኃጢአት ሳያገኛት እንደወለደችው ያስረዳናል ፡፡
2.ያለምጥ የአራስነት ግብርም ሳያገኛት ከሚለው ደግሞ ሌሎች ሴቶች በጥንተ አብሶ ፍዳ ምክንያት በምጥ በአራስነት የሚወልዱ ሲሆን እረሷ ግን ከመርገመ ከእዳ ከበደል የተለየች በመሆኗ ምጥና አራስነት አልነበረባትምይህምከመላአኩየምስጋና ንግግር ተስማሚነትያለውነውቅዱስ ገብርኤልሲያበስራትከላይ ከተጠቀሱትየመርገምምልክቶችእመቤታችን የተለየች መሆኗን ሲያስረዳ«አንች ከሴቶት መካከል የተባረክሽ ነሽ » ሉቃ 1 ፡ 28 በማለት አመሰግኖአታል።ለመሆኑ እርሷ በሌሎች ሴቶች ያለ የመርገም ፍዳ ካለባት ከሌሎች ሴቶች መለየቷ ምን ላይ ሊሆን ነው ?ስለዚህ እመቤታችን የመርገም ፍዳ ይመለከታታል በሎ ማስተማር ፍጹም ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ የራቀ ትምህርት ነው ማለት ነው ። ውላዲተ አምላክ የጥንተ አብሶ ፍዳ እንደማይመለከታት ቅዱስ አትናትዮስ ብቻ ሳይሆን በርካታ ቅዱሳን አበውም መስከረዋል ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ድንግል ማርያም የጥንተ አብሶ ፍዳ እንደማይመለከታት ስያስረዳ እንዲህ በማለት በሚደንቅ ንግግር እንዲህ ይላል « ከመገባሪ ጠቢብ ሶበ ይረክብ ግብሮ ዘይትጌበር ይገብር እምኔሁ ንዋየ ሰናየ ከመዝ እግዚእነ ሶበ ረከበ ሥጋሃ ቅዱስ ለዛቲ ድንግል ወነፍሳ ቅድስት ፈጠረ ሎቱ መቅደስ ዘቦቱ ነፍስ » ሃይ አበ ዘአፈወርቅ 66 ፡14ትርጉም « ጥበበኛ ንጹህ አፈር ባገኘ ጊዜ ጥሩ እቃ እንደሚሰራበት ጌታችንም የድንግልን ንጹህ ሥጋዋን ንጹህ ነፍሷን ባገኘ ጊዜ ይዋሃደው ዘንድ ነፍስ ያለውን መቅደስ ሰውነቱን ፈጠረ » መቼም የቀናች የተረዳች ርትዕት የሆነች የተዋህዶ ምዕመን ሆኖ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን የማያውቅ አለ ማለት ይከብዳል ምንም በማያሻማና ግሩም በሆነ አገላለጽ ሊቁ እነዳስቀመጠልን አምላክ ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነው ምንም ምን እንከን ከሌለው ሰውነቷ ነው ሊቁ የእመቤታችንን ነፍስና ሰጋዋን በንጹሕ አፈር መስሎታል በዚህ አገላለጹ ከሰው ወገን ተመርጣ ለአምላክ እናትነት የበቃች መሆኗን አስረዳን ምክንያቱም የሰው ሁሉ ተፈጥሮው ከአፈር ነውና ። ወላዲተ አምላክ እንደሰው ሁሉ ተፈጥሮዋ ከአፈር ቢሆንም ቅሉ ሊቁ እንደተናገረው « ንጹሕ አፈር » የሚለው አገላለጽ በሰዎች ከደረሰ አዳማዊ መርገም የተለየች መሆኗን ያስረዳናል ቅዱስ ኤፍሬምም በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ዘር ያልተዘራባት እርሻ በማለት በንጹሕ እረሻ መስሎአታል ልበ አምላክ ዳዊትም « እንደ ዝናብ በንጹሕ እርሻ ላይ …….. ይወርዳል » መዝ 71 ፡6 በማለት ጌታን በዝናበ ሕይወት እመቤታችንን ደግሞ አረም ተዋስያን በሌሉት ንጹሕ መሬት መስሎ ትንቢት ተናግሮአል ይህም ምንም ተፈጥሮዋ ከሰው ወገን ብትሆንም የኃጢአት አረም ህዋስ ያልነካት ንጽህት ዘር መሆኗን ያስረዳናል ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በንጹሕ አፈር የመሰላት ። ሊቁ በመቀጠልም « ንጹሕ ስጋዋን ንጹሕ ነፍሷን ባገኘ ጊዜ » በማለት የወላዲተ አምላክ ነፍሷ ስጋዋ ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ ንጹሕ ቅዱስ መሆኑን ይመሰክራል ባገኘ ጊዜ አለ እንጂ ሊዋሐደው ሲል አነጻው አላለም ሰለዚህም እውነተኞች ቅዱሳን አበው በጥንቃቄ የመሰከሩትን የእመቤታችንን ንሕጽና ዛሬ ማንም ተነስቶ ሊያስተባብል አይችልም ተቀባይነትም አይኖረውም ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን « እኛ ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን » ገላ 1 ፡ 8 ባለው መሰረት ዛሬ ማንም ተነስቶ ሊሽረው ወይም ሊለውጠው አይችልም ቢሞክር እንኩአን የተለየ የተረገመ ነው ቅድስት ቤተክርስትያን የምትመራው ቀደምት ቅዱሳን ባስተማሩን እውነተኛ ትምህርት እንጂ አዲስ ዛሬ የሚፈጠር ምንም የለም ስለዚህ ከአንዳንድ የዘመናችን ሰዎች የተሳሳተ ትምህርት ብንሰማ እነሱ የተለዩ ይሆናሉ እንጂ የሰማይ መልአክ ነኝ የሚል ቢመጣ እንኳን የቤተክርስትያን አስተምሮ አይለወጥም፡፡
0 comments:
Post a Comment