“ሥላሴ” የሚለው ቃል “ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስት ማለት ነው፡፡ ይህን ሦስትነት ለጌታ ስንቀጽለው “ልዩ የሆነ ሦስትነት” የሚለውን ፍቺ ያመላክታል፡፡
የእነርሱን /የቅድስት ሥላሴን/ ሦስትነት ልዩ የሚያደርገው በሦስትነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ሦስትነት ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት የሚሰጠው ትምህርተ ሃይማኖት “ምሥጢረ ሥላሴ” ይባላል፡፡ ይህ ትምህርት ምሥጢር መባሉ በዐይነ ሥጋ የማናየው፣ በዕደ ሥጋ የማንዳስሰው፣ በሥጋዊ ምርምር ፈጽሞ የማይደረስበት በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ምሥጢረ ሥላሴ የሰላም ወንጌልና የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ትምህርተ ሰላምነ ነአምን አበ ፈናዌ ወነአምን ወልደ ተፈናዌ ወነአምን መንፈሰ ቅዱስ ማኅየዌ አሐደ ህላዌ፤ በሰላማችን ትምህርት ላኪ አብን እናምናለን፤ ተላኪ ወልድንም እናምናለን፤ አዳኝ መንፈስ ቅዱስንም በአንድ ባሕርይ እናምናለን” እንዲል፡፡
ቅድስት ሥላሴ የእግዚአብሔር ልዩ መጠሪያው ነው፡፡ እግዚአብሔር ስንልም ስለ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መናገራችን ነው፡፡ ሊቁ “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” እንዲል፡፡ ቢሆንም ግን የእርሱን ነገር ልንመረምረው አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔር “ቅዱስ” ተብሎ በወንድ አንቀጽ፣ “ቅድስት” ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/ ተብሎ ሲጠራ እውነትም ከምርምር በላይ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሚመራመር አእምሮን ስለሰጠን በተወሰነ መልኩ “ቅዱስ እና ቅድስት”፣ “ልዩ ሦስትነት” የሚባልበትን ሃይማኖታዊ ምሥጢር በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
ቅዱስና ቅድስት መባል
ቅዱሳት መጻሕፍት ጾታ የሌላቸውን አካላት በወንድና በሴት አንቀጽ መጥራት ልማዳቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳን መላእክትን በወንድ አንቀጽ ሲጠራቸው “ወይሴብሕዎ ኩሎሙ መላእክቲሁ፤ መላእክቱ ሁሉ ያመሰግኑታል” ሲል በሴት አንቀጽ ሲጠራቸው ደግሞ “ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ሰማያት (መላእክት) የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” ይላል (መዝ. 148÷1-2)፡፡ ነፍስንም በወንድ አንቀጽ ሲጠራ “መንፈስ እምከመ ወጽአ ኢይገብእ፤ ነፍስ ከተለየ በኋላ አይመለስም” ሲል በሴት አንቀጽ ደግሞ “ትባርኮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች” ይላል /መዝ. 77÷39፣ መዝ. 102÷1/፡፡ እንዲሁም ፀሐይን በወንድ አንቀጽ ሲጠራ “ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢሁ፤ ፀሐይ መግቢያውን ዐወቀ” ሲል በሴት አንቀጽ ደግሞ ”ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ፤ እሳት ወደቀች ፀሐይን አላየኋትም” ይላል /መዝ. 103÷19፣ መዝ. 57÷8/፡፡ ስለዚህ ልማደ መጻሕፍት መሆኑን በዚህ ይረዷል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅድስና ሕይወት ለወንዱም ሆነ ለሴቷ የተሰጠ መሆኑን ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ የሚጠቀሰው የሰው ልጅ የእኩልነት ሚዛን ደግሞ “ቅድስና” ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ወንዶች እንዳሉ ሁሉ ቅዱሳት ሴቶች መኖራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ይልቁንም የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያምን ቅድስና ስናስብ እንዲያውም በወንድ ምን ቅድስና አለና! ያሰኛል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት /በቤተ ክርስቲያን/ ፍትሕ፣ ርትዕ እንጂ ዓመፅና አድልዎ የለም፡፡ “ዘአኮ ይዔምፅ እግዚአብሔር ከመ ይርሳዕ ምግባሪክሙ ወተፈቅሮተክሙ ዘአርአይክሙ በስሙ ወተልእክምዎሙ ለቅዱሳን ወትትለአኩሂ፤ እግዚአበሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትንም ሥራ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና፡፡ “እንዲል /ዕብ. 6÷10፡፡ እኛም ሃይማኖታችን የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የሰላምና የአንድነት ሥርዓት እንጂ የሴቶች መጨቆኛ መሣሪያ አይደለም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ወገኖች ይህን የጠራ አስተምህሮዋን በእምነት መነፅር መረዳት አለባቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ “ቅዱስ” እና “ቅድስት” የመባሉን ነገር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በምሳሌዊ አገላለጽ “ኀበ ርኅራኄክሙ በዝኀ ወኀበ አልቦቱ መሥፈርት እለ ትሠመዩ በስመ ብእሲት ሥላሴ ዕደወ ምሕረት ግናይ ለክሙ፤ ቸርነታችሁ ከበዛና መሥፈሪያም ከሌለው ዘንድ “ቅድስት” ተብላችሁ በሴት ስም የምትጠሩ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ ለእናንተ መገዛት ይገባል” በማለት ምሥጢሩን እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ አስተምሯል፡፡
የሥላሴ በወንድና በሴት አንቀጽ መጠራት ምሳሌነት አለው ማለት ነው፡፡ ወንድ ኃያል ነውና ቢመታ ያደቅቃል፤ ቢወረውር ያርቃል፤ ቢያሥር ያጠብቃል፡፡ ሥላሴም ከቸርነታቸው በቀር ፍጥረቱን ሁሉ እናጥፋው ቢሉ ይቻላቸዋል፡፡ አንድም ወንድ ወጥቶ ወርዶ ነግዶ ሚስቱን ይመግባል፤ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡ ሥላሴም በፈጢር ወላድያነ ዓለም ናቸውና የፈጠሩትን ፍጥረት በዝናብ አብቅለው፣ በፀሐይ አብስለው ይመግቡታልና በወንድ አንቀጽ “ቅዱስ” ይባላሉ፡፡
“ቅድስት” ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ደግሞ ሴት /እናት/ በልጁዋ ወለደችው /አልወለደችው/ ተብላ እንደማትጠረጠረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም ፈጠሩት አልፈጠሩት ተብለው አይጠረጠሩም፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣ ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት /እናት/ ልጅዋ ቢታመምባት ወይም ቢሞትባት አትወድም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ እንኳ በዲያብሎስ እጅ ቢገዛባቸው አይወዱም፡፡ አንድም ሴት /እናት/ ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን ትመግባለች፤ ሥላሴም በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ ይመግባሉና በሴት አንቀጽ “ቅድስት ሥላሴ” እያልን እንጠራቸዋለን፡፡
2. ልዩ ሦስትነት
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ልዩ ሦስትነት የሚለው የምሥጢረ ሥላሴ ሃይማኖታዊ ትምህርት በቅድምና፣ በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በማሰገድ፣ በመመስገን፣ በክብር፣ በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት (ሥላሴ) የሚለውን ይገልጻል፡፡
2.1. በስም
የስም ሦስነታቸው አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው፡፡ ይኸንንም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል /ወልድ/ “እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው” ሲል አስተምሯል /ማቴ. 28÷19/ ታዲያ አብ በራሱ ስም አብ ቢባል እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ቢባል እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባልም፡፡ ስማቸው ፈጽሞ የማይፋለስ (የማይተባበር) ነውና፡፡
አንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ይህን ትምህርት በአግባቡ ካለመረዳታቸው የተነሣ “ኢየሱስ ብቻ /Only Jesus/” በማለት የአብንና የመንፈስ ቅዱስን ስም ለኢየሱስ (ለወልድ) ብቻ በመስጠት ስመ ተፋልሶ እያመጡ ኑፋቄን ይዘራሉ፡፡ እኛ ግን በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ስመ ተፋልሶ እንደሌለ እናምናለን፡፡ በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት ተሹሞ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ “አብሂ አብ ውእቱ ወኢኮነ ወልደ ወመንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ ወልድ ውእቱ ወኢኮነ አበ ወኢመንፈሰ ቅዱሰ፣ መንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ ወኢኮነ አበ ወኢወልደ፣ ኢይፈልስ ስመ አብ ለከዊነ ስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢይፈልስ ለከዊነ ስመ አብ ወወልድ፤ አብ አብ ነው ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ ወልድም ወልድ ነው አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ ወልድም አብንና መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ መንፈስ ቅዱስም አብንና ወልድን ለመሆን አይለወጥም” ሲል፣ ዮሐንስ ዘአንጾኪያም “አስማትሰ ኢየኀብሩ፤ ስሞች ግን አይተባበሩም” ብሏል/ ሃይ አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. 11 ገጽ. 18፣ ሃይ አበው ዘዮሐንስ/፡፡
ይህ የቅድስት ሥላሴ ስም እንደ ሰው ስም አካል ቀድሞት ኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ የሰው ስሙ አካሉ ቀድሞት ኋላ ይገኛል፡፡ ወንዱን በ40 ቀኑ “እገሌ” ሲሉት ሴቲቱን በ80 ቀኗ “እገሊት” ይሏታል፡፡ የተወለደ ዕለትም እናት አባቱ ዓለማዊ የመጠሪያ ስም ያወጡለታል፡፡ “ሰው” ሲባል ስሙ ከአካሉ አካሉ ከስሙ ሳይቀድም እንደተገኘ ሁሉ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው፣ አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡ (መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. 32/፡፡
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት “ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱ… ወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም ሳይሆን ባሕርዩ ነው … የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ ናቸው እንጂ” እንዲል /ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት 13-4-8/፡፡
2.2. በአካል
የቅድስት ሥላሴን የአካል ሦስትነት ስናይ ደግሞ አብ በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ወልድም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ይህን እውነት ሊቁ አቡሊደስ “ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ መለኮቶሙ፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣ በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” ብሏል /ሃይ አበው ዘአቡሊደስ ምዕ. 39-3/፡፡
ይህ አካላቸው ምሉዕ በኩለሄ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲሆን ዳር ድንበር፣ ወሰን የለውምና ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፣ ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይደረስበትም፡፡ ሁሉን ሥላሴ ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው የለምና፡፡ «ንሕነ ናገምሮ ለኩሉ ወአልቦ ዘያገምረነ አልቦ ወኢምንትኒ እምታሕቴነ እስመ ለኩሉ የዐውድ ዕበየ ኃይልነ አልብነ ውሳጤ ወአፍአ አልቦ ሰማይ ዘያገምረነ ወኢምድር ዘይጸውረነ፤ ሁሉን እኛ እንሸከመዋለን እንጂ እኛን የሚሸከመን የለም፤ ከእኛ በላይ ከእኛም በታች ቦታ የለም፣ ባሕርያችን ሁሉን ይወስናል እንጂ
የሚወስነው የለም» እንዲል /መጽ.ቀሌምንጦስ/፡፡
2.3. በግብር
በግብር ሦስትነታቸው ደግሞ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርጿልና፡፡ የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፤ ከአብ ሠርዷልና፡፡ “እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ”፣ “ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል” እንዲል /መዝ. 2÷7፣ ዮሐ. 3÷16/፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተረዳነው /ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደተማርነው) አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርጽም፡፡ ወልድ ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርጽም፤ አያሠርጽም፡፡ በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ተብለው ይጠራሉ፡፡
የወልድ ከአብ መወለዱና የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጹ እንደምንድን ነው? ቢሉ ቃልና እስትንፋስ ልብ ሳይቀድማቸው አካላቸው ከልብ ሳይለይ ቃል እንደሚወለድና እስትንፋስ እንደሚወጣ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ቅድመ ዓለም አብ ሳይቀድማቸው እንበለ ተድኅሮ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ወልድ ከአብ ተወለደ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ፡፡ “ከመ ልደተ ቃል ወጸአተ እስትንፋስ እምልብ ከማሁ ልደቱ ለወልድ ወጸአቱ ለመንፈስ ቅዱስ እም አብ፤ ወልድ ከአብ የሚወለድበት ልደትና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚወጣበት አወጣጥ ከልብ እንደሚሆን እንደ ቃል መወለድና ከልብ እንደሚሆን እንደ እስትንፋስ አወጣጥ ነው” እንዲል /ርቱዐ ሃይማኖት/፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ድንቅ ምሥጢር አሁንም ቢሆን በዕፁብ ይወሰናል እንጂ በምርምር አይደረስበትም፡፡
ሆኖም ኦርቶዶክሳውያን አበው የመጽሐፍ ቅዱስን የቀና አስተምህሮ መሠረት በማድረግ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ እንደ ሠረጸ አስተምረዋል፡፡ ዳግመኛም በቁስጥንጥንያ በተካሔደው ዓለም አቀፍ ጉባኤም ላይ መቅዶንዮስን ተከራክረው የረቱ መቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፤ ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ ከአብ በሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ መንፈስ ቅዱስ እናምናለን” በማለት ከቅዱስ ወንጌል እውነታ በመነሣት ትክክለኛውን እምነት ገልጸዋል /ጸሎተ ሃይማኖት/፡፡
በአንጻሩ ግን ይህን ትምህርተ ሃይማኖት ወደ ኋላ በመተው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስ “ዘሠረጸ እም አብ ወወልድ፤ ከአብ ከወልድም የሠረጸ” የሚል ሥርዋጽ አስገብተዋል፡፡ ይህ የስሕተት አስተምህሮ በላቲን “ፊሊዮኬ (Filio tve)” ሲባል ትርጉሙ “እንዲሁም ከወልድ” ማለት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ኑፋቄ በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን መቼም ቢሆን ተቀባይነት የሌለው ትምህርት ሲሆን በላቲኖች ዘንድ ግን ተቀባይነትን ያገኘ አስተምህሮ ነበር፡፡
ለእነርሱ የስሕተት ትምህርት መሠረት የሆናቸው አውግስጢኖስ የተባለው ሰው (dusia is the Sours of trinity)፣ አብ ፍቅር ነውና ልጁን ወዳጅ ነው (The father is the one who loves or/over)፣ ወልድ ደግሞ በአብ ዘንድ ተወዳጅ ነው /The son is the one who is Loved or Beloved፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሁለቱ ፍቅር መካከል ያለ አያያዥ ነው /The Sprit is Love bond)” በማለት አስቀድሞ ያስተማረውን ችግር ያለበት ትምህርት በመቀበላቸውና መመሪያ በማድረጋቸው ሲሆን ይህን ተከትለው በ589 ዓ.ም በስፔን ቶሌዶ ካካሔዱት ጉባኤ ጀምሮ በ1014 ዓ.ም ተቀብለውት በቅዳሴያቸው አስገብተውታል፡፡ /The Doctrine of God P. 172/.
በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መረዳት ለማንም ቢሆን አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ ጥምቀት ተገልጧል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰላምታው ላይ “ለምህሮ ትሥልስት ሥላሴ በሌሊተ ጥምቀት ሐዲስ ዘአስተርአይክሙ በዮርዳኖስ በአምሳል ዘይሤለስ ግናይ ለክሙ፣ በዐዲሲቱ ጥምቀት ሌሊት ሦስትነታችሁን ለማስተማር በሦስት አካላት በዮርዳኖስ የተገለጣችሁ ሥላሴ መገዛት ለእናንተ ይገባል” እንዲል፡፡
እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ በርትዕት ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡ “ወአኮ ዘንብል አሐዱ ከመ አዳም ቀዳሜ ኩሉ ፍጥረት አላ ሠለስቱ እንዘ አሐዱ ህላዌ ናሁ ንሰምዖሙ ለአይሁድ እኩያን ወለእስማኤላውያን ጊጉያን እለ ይብሉ አሐዱ ገጽ እግዚአብሔር ወአሐዱ አካል በኢለብዎቶሙ ዕውራነ ልብ እሙንቱ፤ የሰው ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ እንደ አዳም አንድ ነው አንልም፤ ነገር ግን በባሕርይ አንድ ሲሆን በአካሉ ሦስት ነው እንላለን እንጂ፡፡ ክፉዎች አይሁድን በደለኞች እስማኤላውያንን እነሆ እናያቸዋለንና እግዚአብሔርን አንድ አካል አንድ ገጽ ሲሉ ባለማወቃቸው በልቡናቸው የታወሩ ናቸውና” በሚል ተግሣጽ አዘል ምክር ተችሮናልና /ቅ.ማርያም ቁ. 70/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
0 comments:
Post a Comment