በቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው - ቤተ ደጀኔ
ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ መስመሯን ሳትለቅ ቀጥ ብላ የመጣችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከውጭ ሆነው ተዋግተው ማሸነፍ ያቃታቸው መናፍቃን ያቋቋሙት ድርጅት ነው። እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ የተጀመረው፥ የዛሬ ፹፫ ዓመት፥ ከጣልያን ወረራ በፊት በ ፲፱፻፳፬ ዓ.ም. ነው። የመጀመሪያው ሰው አልፍሬድ ባክስተን የተባለ አሜሪካዊ ነው። ይህ ሰው በ ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ትምህርት ቤት ከፍቶ፥ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተመሳስለው በመግባት ከውስጥ የሚሸረሽሩ ሰዎችን እያሰለጠነ ያስመርቅ ነበር። የተመረቁትም ተበትነው እንዳይቀሩ "ሠራዊተ ክርስቶስ" የሚባል ማኅበር አቋቁሞላቸው ነበር። ይህ እንቅስቃሴ ለጊዜው በጣልያን ወረራ ምክንያት ቢቋረጥም፥ ከወረራው በኋላ ዴቪድ ስቶክስ የተባለው ሰው መጥቶ "ሠራዊተ ክርስቶስ" የተባለውን የተሀድሶ ማኅበር እንደገና አጠናክሮታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያንን ከውስጥ እየገዘገዟት ነው። ቤተክርስቲያን ግን አልጠፋችም። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን፡- "የገሃነም ደጆች (አጋንንት፣መናፍቃን) አይችሏትም፤"ብሏልና። ማቴ፡16 ቁ.18። ዛሬ በተለያየ ስም የሚጠሩ ዓላማቸው ግን አንድ የሆነ ብዙ የተሀድሶ ክፍልፋዮች አሉ። የገንዘብ ምንጫቸውም የፕሮቴስታንት ድርጅቶች ናቸው።
የተሀድሶ ዓላማ፤
ዋና ዓላማቸው የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች በተለያየ ዘዴ በማታለል ወይም በጥቅም በመደለል፥ ወይም በምንፍቅና ትምህርታቸው በማሳመን፥ በሂደት ቤተክርስቲያንን ወደ ፕሮቴስታንትነት መለወጥ ነው። ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችንን፡- "አርጅታለችና መታደስ አለባት፤"ይላሉ። ቤተክርስቲያን ግን የክርስቶስ አካል በመሆኗ አታረጅም። እምነቷም ሥርዓቷም የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመሆኑ ማርጀት ማፍጀት የለበትም። ቆላ፡፩፥፳፬፣ኤፌ፡፩፥፳፫፣1ኛ፡ቆሮ ፲፪፥፳፯፣ ሮሜ፡፲፪፥፭። ስለዚህ "ቤተክርስቲያንን ታረጃለች፤" ማለት ሕያው የሆነውን የክርስቶስን አካልና ሕያው ቃሉን ያረጃሉ የሚያ ሰኝ ክህደት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ፡- ፩ኛ/በቅዳሴ፡- የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትበት፥ በመዝሙርና በማኅሌትም እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሥፍራ (ሕንጻው)፤ ፪ኛ/የአንድ ክርስቲያን ሕይወት፤ ፫ኛ/የክርስቲያኖች አንድ ነት (ኅብረት) ቤተክርስቲያን ይባላሉ። ሦስቱንም ቤተክርስቲያን ያሰኛቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተው እምነትና ሥርዓት ነው። ስለዚህ እምነቱና ሥርዓቱ ከተለወጠ፥ እነርሱም ቤተክርስቲያን መባላቸው ይቀራል። ከዋናው ምንጭ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀዳውን የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት ይዘው እስካልተገኙ ድረስ፥ ስሙን ስለጠሩ ብቻም ክርስቲያኖች ናቸው ብለን አናምንባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ፡-የበግ ቆዳ የለበሱ (መጽሐፍ ቅዱስ የተሸከሙ) ተኩላዎች(ተጠራጣሪዎች)፣ ውሾች፣መናፍቃን፣ ወዘተ...ይላቸዋል። ማቴ፡፯፥፮ እና፲፭ ፣ የሐዋ፡፳፥፳፱፣ ገላ፡፭፥፳። እምነታቸው ጐደሎ ስለሆነም በመጨረሻው ቀን ዋጋ የላቸውም። ጌታችን በወንጌል፡-"በሰማያት ያለ ውን የአባቴን(የአብን) ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፡-ጌታ ሆይ፥ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ጌታ ሆይ፡-በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፡-ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፡-ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፤ (እፈርድባቸዋለሁ)፤" ብሏልና። ማቴ፡፯፥፳-፳፫። ለምሳሌ፡-አጋንንት ስሙን ይጠሩታል፥ ይለምኑታል፥ ያምናሉ፥ ይንቀጠቀጣሉ። በዚህ የተነሣ አማኞች ናቸው፥ ክርስቲያኖች ናቸው ማለት አይቻልም። ማቴ፡፰፥፳፰-፴፬፣ያዕ፡፪፥፲፱።
አካኼዳቸው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ለቤተክርስቲያን የተቆረቆሩ መስለው፡- ሥርዓቱን፣ወጉን፣ባህሉን ይቃወማሉ፤"ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ ቢለወጥ፥ቢሻሻል፥ቢቀር ምን አለበት?"ይላሉ። እንዲህ እያሉ ሁሉን ነገር ለነፍስ ሳይሆን ለሥጋ ፈቃድ እንዲመች ያደርጉ ታል። ለሥጋው ያደረ የሰው ልጅም ይከተላቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን፡-"ነገር ግን በመንፈስ ተመላለሱ፥የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፤" ይልባቸዋል። ገላ፡፭፥፲፮። አጥብቆ የሚከራከራቸውንም "ወግ አጥባቂ፥ፈሪሳዊ፣"እያሉ ይሰድቡታል። ስድብ ግን የሰይጣን እና የመልእክተኞቹ ነው። "ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፤.... እግዚአብሔርንም ለመሳደብ፥ ስሙንና ማደሪያውን (ያደረባትን እናቱን፣ያደረባቸውን ቅዱሳኑን)፥ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። " ይላል። ራዕ፡፲፫፥፭-፮። እኛ ከእግዚአብሔር የሆንን ግን የሚጠሉንን እንወዳለን፣ የሚረግሙንን እንመርቃላን፣ ለሚያሳድዱን እንጸልያለን። ማቴ፡፭፥፵፫። ምክንያቱም በስድቡም ሆነ በጥላቻው እንከብርበታለን እንጂ አንጐዳበትም። ማቴ፡፭፥፲፩።
ቅዱሳን አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተክርስቲያን ሥርዓት መጠበቅ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስረግም አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-"ወንድሞች ሆይ፡-በሁሉ ስለምታስቡልኝና አሳልፌ እንደሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናለሁ። ..... ወንድሞች ሆይ፡-ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና። .... በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን (በጽሑፍ) የተማራችሁትን ወግ ያዙ። " እያለ የሚመሰገኑትን አመስግኗል፥የሚመከሩትንም መክሯል። ፩ኛ ቆሮ፡፲፩፥፪፣፪ኛ፡ተሰ፡፪፥፲፫፣፪ኛ፡ ተሰ፡፫፥፮። ለምሳሌ፡-በጸሎት ጊዜ ሴቶች እንዲከናነቡ (እንዲሸፋፈኑ) ካስተማረ በኋላ፡-"ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። "ብሏል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፲፮። በመሆኑም ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያልነበረ አዲስ ልማድ ማምጣት አይገባም። ቤተክርስቲያን በዘመን ተፅዕኖ ስር ሳትወድቅ፥ በዘመን ሳትሸነፍ፥ዘመንን እያሸነፈች የምትኖር ናትና። ጠቢቡ ሰሎሞንም "አባቶችህ የሠሩትን የድንበር ምልክት (ሥርዓተ እምነት) አታጥፋ፤"ብሏል። ምሳ፡፳፪፥ ፳፰። አጥሩ ከፈረሰ፥ ቤቱም ይፈርሳልና፤የድንበር ምልክት ከጠፋ፥ ሀገርም ይጠፋልና፤ሥርዓተ ቤተክርስቲያንም ከጠፋ፥ ሃይማኖትም ይጠፋልና።
የሥርዓት መገኛ እግዚአብሔር ነው። ይኸውም ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በሠራው ሥርዓት ይታወቃል። በተለይ በአምሳሉ ለተፈጠረ ለሰው ልጅ የተሰጠውን የሃይማኖት ሥርዓት ስንመለከት በሰማይ ባለው የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ አምሳል የተሠራ ነው። "በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስ ሥሩልኝ፤"ያለ፥ ሥርዓቱንም ለሙሴ ያስተማረ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ፡፳፭፥፰። እግዚአብሔር የሰማዩን ቤተ መቅደስ ከፍቶ ሥርዓቱን ካስተማረው በኋላ "በእስራኤል ልጆች ፊት የዘለዓለም ሥርዓት ይሁን፤"ብሎታል። ዘጸ፡፳፯፥፳፩። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሠራው ሥርዓተ ሃይማኖት እጅግ ብዙ ነው። ለምሳሌ፡-የሰው ልጅ ደክሞ ከሚያገኘው አንድ አሥረኛውን(ዐሥራት) ለእግዚአብሔር እንዲሰጥ ያዘዘ እርሱ ራሱ ነው። ዘሌ፡፳፯፥ ፴፣ዘዳ፡፲፪፥፭፣ ዘዳ፡፲፬፥፳፪። በመሆኑም የታዘዘውን መፈጸም ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው።
ተሀድሶዎቹ፡-"ሥርዓት አያጸድቅም፤"እያሉ፥ሰውን ከሥርዓተ ሃይማኖት ይለዩታል። ይህም የሃይማኖትን አጥር ሥርዓቱን ካስፈረሱት በኋላ፥ በቀላሉ ከሃይማኖቱም ለመለየት እንዲመቻቸው ነው። እግዚአብሔር ግን፡-"ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን የምንመለሰው በምንድነው?ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም የሰረቅንህ በምንድን ነው? ብላችኋል። በዐሥራትና በበኵራት ነው። እናንተ፥ይህ ሕዝብ ሁሉ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉማን ናችሁ፤"እያለ ይገሥጻል። ሚል፡፪፥፯-፱። የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥርዓተ አምልኮ በሃይማኖት የሚመለክ አምላክ ሲሆን፥ በተዋህዶ ሰው በመሆኑ፥ለሰው ልጆች ሰጥቶት የነበረውን ሥርዓት መልሶ ሲፈጽም እናገኘዋለን። በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት ወስደውታል፤እርሱ ግን ያለጊዜው ደሙ እንዳይፈስ በተአምር ግዙር ሆኖ ተገኝቷል። ዘፍ፡፲፯፥፯-፲፬፣ሉቃ፡፪፥፳፩፤አርባ ቀን ሲሞላውም ወደ ቤተ መቅደስ ተወስዶ ሥርዓት ተፈጽ ሞለታል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አርባ ቀን መጠበቅ የማይገባት፥ልማደ አንስት የሌለባት ንጽሕተ ንጹሐን ብትሆንም ሥርዓቱን ጠብቃለች። ዘሌ፡፲፪፥፩፣ዘጸ፡፲፫፥፪፣ሉቃ፡፪፥፳፪-፳፬። ለበዓል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሄደው ሥር ዓቱን ጠብቆ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ነው። ሉቃ፡፪፥፵፩። ለእኛ ምሳሌ ለመሆን የጾመውም እንደ ሥርዓቱ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ነው። ማቴ፡፬፥፩። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ዘመን እነ ሙሴ፣እነ ኤልያስ የጾሙት አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ነው። ዘጸ፡፴፬፥፳፰፣፩ኛ፡ነገ፡፲፱፥፰። በትምህርቱም፡-"እኔ ሕግን እና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፥ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፤"ብሏል። ማቴ፡5 ቁ.17። ሥርዓተ ምጽዋትን፣ሥርዓተ ጸሎትን እና ሥርዓተ ጾምንም አስተምሯል። ማቴ፡፮፥፩-፳፩።
0 comments:
Post a Comment